“ዳኛው ማነው?” መጽሐፍን አየሁት

በገ/ክርስቶስ ዓባይ
መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ/ም

ዳኛው ማነው?

ደራሲ ታደለች ኃ/ሚካኤል

አርታኢ ማንይንገረው ሸንቁጥ
አታሚ ኤክሊፕስ ማተሚያ ቤ/ት
የታተመበት ዓመት 2012 ዓ/ም

ይዘት የኢትዮጵያ አብዮት (የውርደትና የጸጸት) ታሪክ
ተደራሲ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ ደግሞ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ለፖለቲካ ፓርቲ ዓባላት

ነፃ አስተያየት በገ/ክርስቶስ ዓባይ

Birhane Meskel

በቅድሚያ እንዲህ ያለው እውነትኛ ታሪክ እንዲጻፍ በሰው አእምሮ ሊታሰብ በማይችለው፤ በእረቂቅ ጥበቡ ወ/ሮ ታደለች ኃ/ሚካኤልን በሕይወት በማቆየትና ልቡናቸውን በማነቃቃት አስጀምሮ ላስጨረሰ ለኢትዮጵያ አምላክ ለኃያሉ እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይድረሰው።

ይህ መጽሐፍ የተጻፈበት ዋናው ዓላማ ደራሲዋ እንኳ ሊረዱት በማይችሉት መለኮታዊ ጥበብ የተቀናበረና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትምህርት እንዲሆን ታስቦ የተሰናዳ ለመሆኑ በወቅቱ የነበርንና ለምስክርነት የታደልን  የዕድሜ ባለጸጋዎች የምናረጋግጠው ጉዳይ ነው።

በመሠረቱ የዚያ ትውልድ ወጣቶች የአገራችንን የቆየ ታሪክና ትውፊት፤ በጥልቀት መርምሮ ባለመረዳት፤ የውጭ ጸሐፍትና ፈላስፋዎች ያሳተሙትን መጻሕፍት ብቻ በማነብነብና የራስን ክብርና ዝና እንዲሁም የአባቶቻችንን ለሺ ዓመታት የቆየ ባህል በመናቅ፤ የተንሸዋረረ የባዕድ አስተሳሰብ አምላኪ ወይም ሰለባ መሆኑን ለመረዳት ‘ማነው ዳኛው?’ ከሚለው የወ/ሮ ታደለች ኃ/ለማርያም መጽሐፍ የበለጠ የመግለጽ ሃይል ያለው ሊኖር እንደማይችል በድፍረት መናገር ይቻላል።

በቅድሚያ ምንም እንኳ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት በእግዚአብሔር ኃይል እንደተጻፈ ሙሉ እምነት ቢኖረኝም ሁሉንም ነገር በሐቅ ላይ ተመሥርተው ለቀጣዩ የኢትዮጵያ ትውልድ መማሪያ ይሆን ዘንድ ጊዜ ወስደው ይህንን መጽሐፍ በማበርከታቸው እንደ አንድ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ፤ ደራሲዋን ማመስገን እፈልጋለሁ። በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱት ስመጥር ሰዎች እንደ እኔ አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ባለውለታዎች ሳይሆኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በከንቱ የጣሩ፤ በኋላም በተወሰነ መልኩ ተሳክቶላቸው አገራችንን አሁን ለደረሰችበት ውድቀትና ኪሣራ፤ ታሪክ ሲያስታውሰው የሚኖር ስህተት ፈጽመው እንዳለፉ ሊሠመርበት ይገባል።

እነዶ/ር ተስፋየ ደበሳይና ዶ/ር ታደሰ የተባሉት ሰዎች የካቶሊክ ሚሲዮን ተማሪዎች እንደነበሩ በመጽሐፉ ተተርኳል። አቶ ብርሃነ መስቀል ውቤ (ረዳ)ም ቢሆን፤ ኢትዮጵያን ሲያፈርሱ ከኖሩት ከዚያው የሰሜን ማኅበረሰብ ውስጥ የተገኙ በመሆኑ የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም የማይሻ ስለሆነ ለአገር ወይንም ለወገን ብሎ ያደረግው እንዳልሆነ መረዳት አይከብድም። የአያቱ የቀኛዝማች ረዳ፤ ገባሪ የነበረው ‘የአያ ሙሔ የኑሮ ሁኔታ አሳስቦት ወደ ትግል እንደገባ ነግሮኛል’ በማለት ደራሲዋ ወይም ባለቤቲቱ፤ ለሽፋን እንደተጠቀመበት እንኳ አሁንም የተረዱት እንዳልሆነ መገንዘብ አያዳግትም።

ይቅርታ ይደረግልኝና አንዳንድ የትግራይ ሰዎች ዘውዱ ከአፄ ዮሐንስ አራተኛ ወጥቶ ወደ ሸዋ መሄድ አልነበረበትም የሚል መሠረተ ቢስ ቁጭት አላቸው። ከዚህም የተነሣ ማዕከላዊውን መንግሥት በመክዳትና ለጠላት በባንዳነት በማደር ኢትዮጵያን ሲወጉ እንደነበር በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል።

እርግጥ ነው፤የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መሠረት አክሱም እንደነበር ቢታወቅም፤ የመጨረሻው ሰለሞናዊው ንጉሥ የነበረው አንበሳ ውድም በ950 ዓ/ም በአይሁድ እምነት ተከታይ በነበረችው ዮዲት ጉዲት አማካይነት ከሥልጣን ተወግዶ ወደ ደቡብ በመሸሽ አሁን መካነ ሰላም እየተባለ በሚጠራው የወሎ ግዛት ማለትም አማራ ሳይንት አካባቢ መሥፈሩና በቤት መንግሥት አካባቢ ብቻ ይነገር የነበረውን የአማርኛን ቋንቋ ማስፋፋቱ ይነገራል።

ከዚህ በኋላ በ12 ኛው ክፍለ ዘመን በይኩኖ አምላክ አማካይነት ለሦስት መቶ ዓመታት ገደማ ተቋርጦ የነበረው የሰሎሞናዊው ንጉሠ ነገሥት ሥርዓት እንደገና ቀጠሏል። ከዚያም በንጉሥ ኢዮአስ ዘመነ መንግሥት አሁንም የትግራይ ሰው በነበሩት በራስ ሥዑል ሚካኤል አማካይነት የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት እንዲጠፋ ሲደርግ አገሪቱ በተበታተነ መሳፍንት ስትተዳደር መቆየቷ ግልጽ ሲሆን፤ ይኽም ‘ዘመነ መሳፍንት’ በመባል ይታወቃል።

ይህንን የተበታተነ አስተዳደር እንደ ቀድሞው ወደ አንድ ማዕከላዊ መንግሥት ለማዋቀር ከፍተኛ ጥረትና ተጋድሎ ያደረጉት አፄ ቴዎድሮስ እንደሆኑ አይዘነጋም። አፄ ቴዎድሮስ ማዕከላዊ መንግሥት መመሥረት ብቻ ሳይሆን አገራቸውንም ለማዘመን ታላቅ ራዕይ የነበራቸውና  ከዘመኑ አስተሳሰብ ልቀው የተገኙ  ንጉሥም ነበሩ። በዚህ ወቅት የአውሮፓ ወራሪዎች በየጊዜው ሰላዮችን እያሰረጉ ያስገቡ ስለነበር፤ በተለይ 154 ሰላዮችን ልካ ከታገቱባት  ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር አለመግባባት በመፈጠሩ፤እርሳቸው በሾሟቸው ‘ካሣ ምርጫ’ በኋላ አፄ ዮሐንስ አራተኛ ከሀዲነት ፤ለእንግሊዙ ጀኔራል ሮበርት ናፒር በባንዳነት በማደር አፄ ቴዎድሮስን ለህልፈት እንዲዳረጉ ምክንያት መሆናቸው ግልጽ ነው።

ቀጥሎም ምንም እንኳ አፄ ዮሐንስ የልዑላዊያን ቤተሰብ መሆናቸው ማረጋገጫ ባይኖርም ከእንግሊዙ ጄኔራል በውለታ ያገኙትን የጦር መሣሪያ በመጠቀም የእህታቸው ባል የነበሩትን አማቻቸውን አፄ ተክለ ጊዮርጊስን ወግተው ከገደሉ በኋላ ዘውድ መጫናቸው በታሪክ ተመዝግቧል። አፄ ዮሐንስ መተማ ላይ ከደርቡሽ ጋር በነበረ ጦርነት መስዋዕት ሲሆኑ ዘውዱ በትክክለኛው ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት ሥር ማለትም የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ የልጅ ልጅ በሆኑት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሥር ወደቀች።

ከዚያም በኋላ አገራችን ኢትዮጵያ ከውጭ ጠላት የሚደርስባትን ትንኮሳ እየተጋፈጠች ያደረገችውን የዕድገት እንቅስቃሴ መረዳት አይከብድም። ይሁን እንጂ አንዳንድ የትግራይ ልሂቃን ይህንን በጥልቀት ሳይመረምሩ ዘውዱ የአፄ ዮሐንስ ልጅ ለነበሩት ለልዑል መንገሻ ዮሐንስ መሆን ሲገባው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እንደቀሟቸው አድርገው በመገመት የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግሥት ለማፍረስ ያልጠነሰሱት ሴራና ተንኮል የለም።

ወ/ሮ ታደለች ኃ/ሚካኤል ይህንን በውል ይረዱ አይረዱ ባይታወቅም፤ ስኳር እንደተቀባ የመድኃኒት እንክብል ምስጢሩን በጥልቀት ባልተረዳው የዩኒቨርስቲ ተማሪ መካከል “መሬት ላራሹ” የሚል መፈክር በማንገብና የእነ ማርክስ፤ኤንግልስ፤ሌኒንና ማኦ ፍልስፍናን እንደ አእምሮ መበረዣ በመጠቀም፤ ዓለም ሲደነቅባት የነበረችውን የአገራችንን ሰላም፤ አንድነትና ነፃነት ከማናጋት በላይ የኃያልነታችን መገለጫ የነበረው የዘውድ ሥርዓት እንዲፈርስ ምክንያት ሆነዋል።

አገራችን ኢትዮጵያ ከቀሪው የዓለም አገሮች የበለጠ እያዳበረች ያቆየችውን የማኅበራዊ ተቋማትን እሴት ለማፍረስ፤ በውጭ አገራት መሠሪ ሴራና በውስጥ ቅጥረኛ ባንዳዎች ያልተደረገ ጥረት የለም። ከእነዚህም አንዱ የብሔር ጭቆና የሚለው ነው። እስኪ ማን ይሙት የቱ ብሔር ነው ሌላውን ብሔር የጨቆነው? ለዚህ ትክክለኛና ተጨባጭ መልስ የሚሰጥ ፖለቲከኛ የለም። በእርግጥ ከአለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ወዲህ አይኑን አፍጥጦ ጥርሱን አግጦ፤ የወጣ ሁኔታ መከሰቱን አንክድም።

ይኸውም የትግራይ የበላይነት በግልጽ ሲንፀባረቅ ቆይቶ እንደነበር አሌ የማይባል ሐቅ ነው። ሕወሃት እንደ አሻንጉሊሊት ጠፍጥፎ የሠራቸውን የብሔር ድርጅቶቹን ለይስሙላ እያሳየ፤ የፖለቲካ፤የኢኮኖሚና የመከላከያውን ኃይል ጭምድዶ በመያዝ ለሃያ ሰባት ዓመታት ያህል የአገሪቱን አንጡራ ሀብት ከመበዝበዝ ባሻገር ከውጭ በብድር የተገኘውንና የአገሪቱ የወደፊት ትውልድ የሚጠየቅበትን ወደ 50 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ሳይቀር በመዝረፍ፤ በሥልጣን ላይ የነበሩ ወንበዴዎች ሁሉ ቱጃር ሆነውበታል፤ ትግራይንም ገምብተውበታል። እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ትግራይ መሠረተ ልማቷ የተሟላላት መሆኗ የአገሪቱ አንድ ችግር እንደተቃለለ አድርገን ልንወስደው እንችላለን። ነገር ግን ሌሎችን ክልሎች የተመለከትን እንደሆነ ከፍተኛ ግብር አግቢዎች ሆነው እያለ በቂ ትምህርት ቤት እንኳ ስለሌላቸው በጊዜያዊ ዳስ ተጠልለው እንዲማሩ ሆነዋል።

አገራችን የምትኮራባቸውንና ዓለም የሚቀናባቸውን በርካታ እሴቶቻችንን በማንቋሸሽና በማራከስ፤ እስከናካቴው ለማጥፋት ያልተደረገ ሙከራና ጥረት የለም። ሕዝብ በቋንቋና በሃይማኖት እንዲሁም በዘር ተከልሎ የጎሪጥ እየተያየ እንዳይጋባ፤ ቀየውን ለቆ እንዲሰደድ ሲደረግ ቆይቷል። የአብሮ አደጎች ማኅበር፤ ዕቁብና ዕድር ማኅበራዊ ትስሥርና መረዳዳትን  ስለሚያበለጽጉ እንደነዚህ ያሉ ማኅበራዊ ዋስትናዎችን ለማስቀረት ምስጢራዊ ፖሊሲ ተቀርጾ እንዲጠፉ ሲደረግ መቆየቱን የምንረሳው አይደለም።

ደራሲዋ፤ ጠላት ከመቶ ዓመት በላይ ኢትዮጵያን ለማሳነስ ብሎም እንደ ዩጎዝላቪያ ከዓለም ካርታ እንድትደመሰስ ሲመኘው የነበረውን ዕቅድ፤ ለሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ እንቆቅልሽ ሆኖ የቆየውን ፈር ቀዳጅ አገር የማፍረስ ሁኔታ የፈጸሙት ዘርዑ ክሕሽን እና ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ መሆናቸውን በገጽ 169 ላይ ይፋ አውጥተዋል። ለዚህም መረጃ እንደ አንድ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ታላቅ ምስጋና ይገባቸዋል እላለሁ።

ዘርዑ ክሕሽን እና ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ የኤርትራ ጉዳይ ‘የቅኝ ግዛት ጥያቄ’ መሆኑን በማመን እስከ መገንጠል በሚል የያዙትን የፖለቲካ ትግል ዕውቅና የሰጡ መሆናቸውን ደራሲ ታደለች ኃ/ሚካኤል አረጋግጠዋል። ምንም እንኳ በፓርቲው (ኢሕአፓ) የበላይ ሥራ አመራርም ሆነ በበታች ዓባላት ተቃውሞ ቢገጥመውም ሁለቱ ግለሰቦች በፈጠሩት ስሕተት ‘ኢሕአፓ’ በሕዝብ ዘንድ የነበረው ከፍተኛ ተቀባይነት ድንገት እንደሟሸሸና በተቃራኒ ለቆሙት ለመኢሶን እና ለወታደራዊው ደርግ፤ ኢሕአፓን ከሕዝብ ልብ ለማውጣት ከፍተኛ የሆነ የፕሮፓጋንዳ ግብአት ተፈጥሮላቸዋል። ይሁን እንጂ አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ለወደቀችበት ውስብስብ የፖለቲካ ኪሣራ እነዚህ ሰዎች ያደረጉት አስተዋጽዖ ምንጊዜም በታሪክ ሲነሳ ይኖራል።

በእርግጥ ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ለ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት ያደረገው አስተዋጽዖና መስዋዕትነት በቀላሉ የሚታይ ባይሆንም በስተመጨረሻ ግን በውዴታም ይሁን በግዴታ እንዲህ ያለ ከባድ ስሕተት ፈጽሞ ማለፉ በጣም ያሳዝናል።

ደራሲዋ በማስቀጠልም ባለቤታቸው አቶ ብርሃነ መስቀል ረዳ ስለ ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አስቀምጠውታል። “ተስፋዬ ለትግሉ ከፍተኛ ከበሬታና ዕውቀት ቢኖረውም፤በነበረው የትግል ልምድ ማነስ፤ በተለይም በተማሪው እንቅስቃሴ ያልነበረና ዘግይቶ የመጣ በመሆኑ ምክንያት፤ ዘርዑ የተስፋዬን ደካማ ጎን ተገን አድርጎ ተጠቅሞበታል” በማለት ይገልጹ እንደነበር ጠቁመው፤ በተጨማሪም “ዶ/ር ተስፋዬ ትሁትና የከተማ ጮሌነት የማይነካካው ሲሆን፤ በተቃራኒው ዘርዑ ምንም የሚገድበው አለመሆኑ፤ በንባብ የተደገፈ ዕውቀትን ለማዳበር ስንፍናም የተጫነው፤ መርህ የማይከተል ቅጽበታዊ ድል የሚያስፈነጥዘው ወይ በአጭር ድል የሚረካ ነበር። ያችን ድል ለማግኘት ያልሆነውን ቢሆን፤ ምን ይሉኛል የሚል ስሜት አልፈጠረበትም” በማለት አጫውቶኛል ሲሉ አብራርተዋል።

በገጽ 204 በአራተኛው አንቀጽ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያውቀው የሚገባ አንድ ዓቢይ ጉዳይ አንስተዋል። ነገር ግን በሚገባ ሳያብራሩ አልፈውታል። ጽሑፉ እንዲህ ይነበባል፡

“ወቅቱ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት የተላቀቁበት ነበር። በተለይም ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡት አገሮች የተማሩ ዜጎች ቁጥር አናሳ መሆንና በአንዳንዶቹ ጨርሶም ያልነበረ በመሆኑም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለነፃነታቸው ያደረገውን ድጋፍ በሰው ኃይል ልማትም ለማገዝ ወሰነ። ነፃ ከወጡት የተለያዩ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት አገሮች ከጋና፤ናይጀሪያ፤ከኬንያ ከታንዛንያና ከሌሎችም፤ የነፃ ትምህርት ዕድል የተሰጣቸው በዩኒቨርስቲ ኮሌጆቹ መማር ጀምረው ነበር” ብለዋል።

ይህን አባባል እንደ ‘ፍትሕን ፍለጋ’ በተባሉት መጽሐፍት በዝርዝር ተወስቷል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን አርቆ አስተዋይነትና ታላቅነት የሚያጎላ ስለሆነ የእርሳቸው ተቃራኒ በሆኑ ሥልጣን ፈላጊዎችና አገር አፍራሾች እንዲወሳ አይፈቀድም። ጥሬ ሐቁ ግን እንደሚከተለው ነው።

ታላቁ ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በቅድሚያ ለዓለም የቅኝ ግዛት አገሮች ነፃ መውጣት ያደረጉት አስተዋጽዖ ጉልሁን ድርሻ የሚይዝ መሆኑ በዓለም የነፃነት ታሪክ ተመራማሪዎች የተመዘገበና በአርያነት የሚጠቀስ መሆኑን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊኮራበት የሚገባው ተግባር መሆኑን መጠቆም አስፈላጊ ይሆናል። በመሠረቱ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች አህጉሪቱን ከመቀራመታቸው በፊት መላዋ አፍሪካ ‘ኢትዮጵያ’ እንደነበረች ማወቁ ተገቢ ነው።

በሁለትኛ ደረጃ እኒሁ ታላቅ ንጉሥ ከነፃነት በኋላ የኅብረትን ጥቅም በመረዳት፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመሥረት አንድ ታላቅ ፕሮጀክት ነደፉ። ይህንን የተረዱት እንግሊዞች ሊሳካ እንደማይችል በመገመት እያሾፉ ሳቁባቸው፤ ተሳለቁባቸው። ንጉሡ ግን በመጀመሪያ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅትን አቋቋሙ። ከዚያም በቅኝ ግዛት የዘረኝነት ፖሊሲ ከፍተኛ ትምህርት እንዳይማሩ የተከለከሉትን ተማሪዎች በማወዳደር የነፃ ትምህርት ዕድል እንዲያገኙ እስኮላርሽፕ መስጠት ጀመሩ። እነዚህ በመላው አፍሪካ የሚገኙ ተማሪዎች ዕድሉን ለማግኘት እያመለክቱ ከተወዳደሩ በኋላ ብቃት ያላቸውና መመዘኛውን (ታሪክ ወይም ፖለቲካል ሳይንስ የመማር ዝንባሌ ያላቸው) የሚያሟሉ ሆነው የተገኙ ሁሉ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እየገቡ የነፃ ትምህርት ዕድሉን በማግኘት ተመርቀዋል። ይህ ብቻም ሳይሆን ከተመረቁም በኋላ በየአገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ውስጥ እንዲመደቡ የዲፕሎማሲ ድጋፍ ሲደረግላቸው ቆይቷል።

እነዚሁ ተማሪዎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቆዩባቸው ዓመታት የአማርኛን ቋንቋም ተምረው ማንበብና መጻፍ ይችሉ እንደነበር ሲታወቅ፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ቻርተር ያረቀቁት እኒሁ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተማሩት እንደነበሩ ግልጽ ነው። ታዲያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቆይታቸው አብዛኛዎቹ ይተዋወቁ ስለነበር የአፄው ዕቅድና ፍላጎት ተግባራዊ ሆኖ በእነርሱ መነሻነት የተዘጋጀው ቻርተር የአፍሪካ መሪዎች ተሰብስበው ተወያይተው ከአጸደቁት በኋላ ‘የአፍሪካ አንድነት ድርጅት’ ተመሠረተ። እንግሊዞችም አይሆንም ብለው የገመቱት ተግባራዊ በመሆኑ ዓይናቸው ደም ለበሰ።

ሂደቱ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት ከቡር አቶ ከተማ ይፍሩ እልህ አስጨራሽ የሆነ የዲፕሎማሲ በረራዎችን ማድረግ ነበረባቸው። ሚንስትሩ የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን መልዕክት ይዘው ጧት ወደ ውጭ አገር ሄደው ማታ ይገቡ የነበረ ሲሆን፤ ማታ ገብተው ከሆነም፤ የንጉሡን መልዕክት ይዘው ጧት ደግሞ ተመልሰው ወደ ሌላ አገር ይጓዙ እንደነበር በወቅቱ የነበርን ሰዎች የምናስታውሰው ነው። ታዲያ እንዲህ ያለውን የንጉሡን (ታላቅ ውጤት) ክሬዲት በሕዝብ እንዳይታወቅ የተደረገበት ምክንያት ሆን ተብሎ ይሁን ወይንም ካለማወቅ፤ ይህንን የሚያውቁት ደራሲዋ ናቸው። በነገራችን ላይ ንጉሡ አገራቸውን ለማሳዳግ ከነበራቸው ታላቅ ራዕይ የተነሳ የአባታቸው የራስ መኰንን እርስት የነበረውን ግቢ በመስጠት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዲቋቋም ማድረጋቸውን ስንት ኢትዮያውያን እናውቅ ይሆን?

አገራችን እንዳታድግ ዙሪያውን በጠላት ተከባ እያለ፤ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ፤ እጅግ በረቀቀ ዘዴ ከትቢያ አንስተው ባስተማሯቸው፤ የበሉበትን ወጭት ሰባሪዎች፤ ለክብራቸው እንኳ የሚመጥን የቀብር ሥርዓት አልተፈቀደላቸውም። በተለይ ሟቹ መለስ ዜናዊ የአፄው ሃውልት ከነከዋሚ ንክሩማ ጎን እንዳይቆም  ማድረጉን በትዝብት የምናስታውሰው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

በገጽ 224. “በውጭ ወራሪ ኃይሎች ላይ የተደረጉት አንጸባራቂ ድሎች፤ ስለምን በአገር ውስጥ የተንሠራፋውን ጭቆናና አሰቃቂ ድኅነት በማስወገድ አልተደገመም?

እንዴት በወኔና በቁጭት የአገሩን ሉዓላዊነት ለማስከበር ሃሞቱ የቆረጠ ሕዝብ፤ ስለአስከፊ ኑሮውና ድኅነቱ ሊያስብ አልቻለም? እንዴት የገዥዎቹን ቅጥ ያጣ ይሉኝታ ቢስነትና ብዝበዛ እምቢኝ አሻፈረኝ ማለት አቃተው? የፖለቲካ መንኮራኩሩን የያዙት ንጉሠ ነገሥቱም ሆነ የሥርዓቱ ተጠቃሚዎችስ እንዴት ዓነስተኛ ጥገናዊ ለውጥ እንኳን ሳይሞክሩ ቀሩ?”  በማለት ደራሲዋ የተለያዩ ጥያቄዎችን ከአዥጎደጎዱ በኋላ ይህንን አስከፊ ሁኔታ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በመረዳታቸው ለተጨቆነው ሕዝብ የሥርዓት ለውጥ ለማምጣትና የሕዝቡን ብሶት ለባለሥልጣኑ ለማሰማት በጽሑፍ፤በግጥም፤በቅኔ፤በጩኸት፤ በሰልፍ ተቃውሟቸውን በተማሪ ድርጅት አማካይነት አስተላለፉ” ሲሉ የተማሪውን ትግልና ሕዝባዊነት ለማጉላት ሞክረዋል።

ከዚህ የምንረዳው አንድ ሐቅ አለ። ይህም በወቅቱ በነበሩ የውጭ መጽሐፍትን አንብበናል በሚሉ አነብናቢዎች ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ያላገናዘቡና የውጭን አስተሳሰብ በአገር ውስጥ ለመጫን የሚራወጡ (critical thinkers) ያልሆኑና እራሳቸውን እንደሊቅ የሚቆጥሩ ጉረኞች፤አገራችንን እንደ እነርሱ በዓለማዊ ጥበብ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ጥበብ ጭምር፤ አገራቸውን ሲሰነዝርባት ከነበረ የተለያዩ የጠላት ወረራዎችን በጀግንነት ተቋቁመው ማቆየታቸውን በመዘንጋት፤ በዚያም በዚህም ያለውን ሥርዓት በማጥላላት በአቋራጭ ሥልጣን ላይ ቁብ ለማለት እንደነበር ለመረዳት አይቸግርም። በአጠቃላይ ሲሠሩ የቆዩት ሁሉ የጠላትን አጀንዳ ለማስፈጸም ካልሆነ በስተቀር ለአገር የሠሩት ግን ከጥፋት በስተቀር አንዳችም ጥቅም አላስገኘም።

“መሬት ላራሹ!” የሚለው መፈክር እራሱ የባላበትን ሥርዓት በማፍረስ ለአገር ሉዓላዊነትና ለሕዝብ ደኅንነት የታገሉትን የአርበኞች ልጆች፤ የነበራቸውን መተዳደሪያ ባልተጠና መንገድ በመውረስ፤ በአንድ ሌሊት የሚበሉት የሚቀምሱት አሳጥተው፤ ያጣ የነጣ ደሀ ማድረግ እንደ ታላቅ ስኬት ሊቆጠር የሚችል አይመስለኝም። ይልቁንም ጠላትን የተዋጉ የአርበኞች ልጆችን እንደመበቀል የሚቆጠር የጠላት አጀንዳ መሆኑን አልተረዱም፤ ለመረዳትም ፈቃደኞች አልነበሩም። በተጨማሪም፤ የሶቪዬት ኅብረትን፤ የኲባን፤ የላኦስ፤ የካምቦዲያና፤ የቬትናምን….ወዘተ. ጉዳይ ከኢትዮጵያ ነባራዊና ታሪካዊ ሁኔታ ጋር ሳያገናዝቡ፤ በአምልኰ እግዚአብሔር የምታምነውንና በቅኝ ግዛት ያልተገዛችውን፤ የንጉሠ ነገሥት መንግሥት ጥንታዊ አገር የሆነችውን ኢትዮጵያ እምነት አልባ የኰሚኒስት አገር ለማድረግ፤ የሄዱበት እርቀት ምን ያህል ጭፍንና በጀብድ የተሞላ እንደነበር በግልጽ መረዳት ይቻላል።

ይህ ብቻም አይደል ሥልጣን ናፋቂዎች እነክፍሉ ታደሰ፤ ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ጸጉሩ እሣት የታጠቀውን የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደርን የ(ደርግ)ን መንግሥት በግብታዊነት በመተንኮስ፤ የዕንቁራሪትና የአንበሳ በሚመስል ግብግብ የወሰዱት እርምጃ፤የድሀን ልጅ ከማስፈጀት በአለፈ የአንድን ትውልድ በማጥፋት ከፍተኛ ወንጀል ፈጽመዋል። አሁንም ቢሆን እንደዚህ ያሉ ነፍሰ ገዳዮች ሕግ ፊት ቀርበው ለሠሩት ወንጀል ተመጣጣን የሆነ ፍርዳቸውን ማግነት ይገባቸዋል። የእነርሱን የሥልጣን ጥማት ለማርካት ሲባል በእነርሱ ምክንያት የብዙ ንጹሐን ወገኖቻችን ሕይወት በመቅጠፍ የዕልፍ አዕላፍ ቤተሰቦችን የወላድ መካን ያደረገ መሆኑን በቁጭት የማናስታውሰው ነው። የእነዚህ ንጹሐን ዜጎች ደማቸው አሁንም በእግዚአብሔር ፊት ይጮሃልና!

በሴቶች አደረጃጀት ላይ በውጭ የነበሩት የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር የያዙትን ማንኛውም ዓባል በድርጅት ዓባልነቱ ብቻ የመምረጥና የመመረጥ መብት ፍትሐዊነት ትክክለኛ አቋም በሚቃረን መልኩ በአመራር ላይ የሚቀመጡት የማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለምን የተቀበለ መሆን አለበት የሚለው አቋም የተቀነቀነው በእነዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይና በእነአቶ ክፍሉ ታደሰ አማካይነት መሆኑንና ለሕዝብ ልዕልና ሳይሆን ሥልጣንን በቋራጭ ለመውሰድ የተቀየሰ ዘዴ እንደነበር ደራሲዋ ማጋለጣቸው፤ አስተዋይ ካለ ለቀጣዩ ትውልድ ከፍተኛ ትምህርት ይሰጣል የሚል እምነት አለ። የሚገርመው ደግሞ የፓርቲ የበላይ አካላት የሆኑት ባለሥልጣናት በሙስና የተዘፈቁና ሁሉም ከሴት ጋር የሚርመጠመጡ የሥነ ልቦና ደሀዎች የነበሩ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። ለምሳሌም ወ/ሮ አዳነች ፍሥሐዬ የአቶ ክፍሉ ታደሰ ባለቤት መሆናቸውን እንደማሳያ ብንወስድ ሌሎችም ከዚሁ የተለየ አቋም እንዳልነበራቸው ተጠቁሟል።

የደራሲዋ ባለቤት አቶ ብርሃነ መስቀል ረዳ (ውቤ)ም ልቤን ነክቶኛል ለሚሉት የእነ አያ ሙሔን መሰል ገበሬዎች ኑሮ ለማሻሻል በቅንነት አስበው ከሆነ ማድረግ የነበረባቸው ልክ ለብሔራዊ አገልግሎት አሶሳ ሄደው በነበረበት ወቅት ያዩትን የመጻሕፍት ዕጥረት ለመቅረፍና ለማሻሻል የወሰዱትን እርምጃና ያደረጉትን ጥረት የሚመስል ተከታታይ አገር አቀፍ መነሳሳት በተቋም መልክ እንዲቀጥል ማድረግ በተገባቸው ነበር። ነገር ግን አገራችን ኢትዮጵያ ያለባትን የተቀነባበረ የጠላት ሴራ ተቋቁማ እያደረገች የነበረችውን እንቅስቃሴ በመረዳት አጋዥ መሆን ሲገባ፤ ግልብ አስተሳሰብና አንድ አቅጣጫ ብቻ በመያዝ፤ የአገሪቱን ባለውለታዎች እንደ አድኃሪ አድርገው መፈረጃቸው የነበራቸው አስተሳሰብ የበሰለ ሳይሆን እጅግ በጣም ጨቅላ እንደነበር ለመገመት አይቸግርም።

ምክንያቱም ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት “በግዛታችን ፀሐይ አትጠልቅም” (The Sun will never set down in the British Empire) በማለት እንግሊዞች ሲኩራሩ በነበሩበት ወቅት በግዞት የነበሩትን 154 የእንግሊዝ ዜጎች አስመልክቶ፤ በቀጣይም በአድዋ ጦርነት ጊዜ ጥቁር ሕዝብ የነጭን ወራሪ ኃይል ድባቅ የመቱ ኢትዮጵያውያን በመሆናቸው፤ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ፤ አሁንም በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ አማካይነት የዓለም ቅኝ ተገዥ አገሮች ነፃ እንዲወጡ ከፍተኛውን ድርሻ የተወጡ በመሆኑ፤ በአራተኛ ደረጃም የቀድሞዋን ኢትዮጵያ የአሁኗን አፍሪካ ወደ አንድ ለማምጣት ከፍተኛና እልህ አስጨራሽ ተግባር ፈጽመው “የአፍሪካ አንድነት ድርጅት”ን ያቋቋሙት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በመሆናቸው፤ ምክንያት ቀጣዩ የኢትዮጵያ ትውልድ በጠላት የተወሰነብንን የበቀል ዕዳ የምንከፍልበት የረቀቀ ሴራ መኖሩን አለመገንዘብ ነው።

ከዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ (land locked) እንድትሆን ከማድረግም ባሻገር ደም አፋሳሽ የሆነ ካርታ ዙሪያዋን በመንደፍ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ የተጠመደብን መሆኑን አለመረዳት ነው። ይህ ብቻም አይደለም ማንኛውም የመሠረት ልማት ቁሳቁስና ማሽነሪ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ከፍተኛ የሆነ ዓለም አቀፍ የስለላ ማዕቀብ የሚደረግባት አገር መሆኗን አለመመርመር ነው። ታዲያ የዚያ ትውልድ የግልብ ዕውቀት ተመጻዳቂዎች ‘አልተማሩም’ ብለው የሚኰንኗቸው አርቆ አስተዋይ አባቶች፤ በሰላም ያቆዩአትን አገራችንን ኢትዮጵያን በደም አበላ ሲያጥቧት እንደነበር በትዝብት የምናስታውሰው ነው። በመሆኑም ለሕዝቡ ዕድገት ሊያመጡ ቀርቶ ከነበረችበት ደረጃ አውርደው፤ የሀገሮች ሁሉ ጭራ እንድትሆን አድርገዋታል። ይህ እጅግ በጣም አሳፋሪ የሆነው ትውልድ በቀደደው የተሳሳተ መስመር አገሪቱ ተዘፍቃ፤ ወደ ብረት ዘመን (Iron age) የኋሊዮሽ እየተጎተተች ከገባችበት የዘር አረንቋ ለመውጣት ባለመቻሏ፤ የዘመኑ ትውልድ በደረሰበት የማንነት ጥያቄ  (Identity Crisis) ውስጥ ተዘፍቆ የሚያወጣው ፍለጋ እየባዘነ ይገኛል። ይህም ሂደት በአህጉራችን በዘግናኝነቱ የሚታወሰውና እኤአ በ1991 ዓ/ም በሯንዳ የተፈፀመው  የእርስ በእርስ ዕልቂት ወደ እኛም አገር እየተንደረደረ ለመሆኑ ሰፊ ምልክቶች መኖራቸውን ከሞኞች በስተቀር ብልሆች ግን በፍርሃትና ጭንቀት የሚከታተሉት ጉዳይ ነው።

ደራሲ ወ/ሮ ታደለች ኃይለ ሚካኤል በብዙ መልኩ ስህተት እንደሠሩ የሚመስል ጸጸት ቢያሳዩም የባለቤታቸውን የብርሃነ መስቀል ረዳን ታላቅ ድክመት ግን በመሸፈን ግሩም ድንቅ እንደሠራ አድርገው ለማሳየት ሞክረዋል። የብርሃነ መስቀል አንባቢነትም ሆነ አርቆ አስተዋይነት የሚለካው አውሮፕላን በመጥለፍ ጀብድ በመሥራት ወይንም የአገሩን ታሪክ ሳይመረምር የውጭ አገራትን ጽሑፍ ብቻ በማነብነብ ከእነዚያ ታሪክና ባህል ከሌላቸው አገሮች ጋር ለማነፃጸር መሞከሩን እንደ ልዩ ተዓምር አድርገው ለማሳየት ሞክረዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ እንዲህ ያለው አገላለጸ እንኳን ለኢትዮጵያውያን ቀርቶ ከአብራኩ ለተፈጠሩት ልጆቹም ቢሆን የሚያኮራ እንዳልሆነ መታወቅ አለበት።

ምናልባት አቶ ብርሀነ መስቀል ረዳ ሥልጣን ፈላጊ ላይሆኑ ይችላል። ነገር ግን በእሳቸው የአስተሳሰብ ጉድለት ምክንያት በተወሰደው እርምጃ አገራችንን እስከአሁን ድረስ ለዘለቀና ወደፊትም በቀላሉ መቋጫ ለማይገኝለት ውስብስብ የመሬት ስሪት ዳርጎናል። በአሁኑ ወቅት የመሬት ባለቤት የሆነው በሥልጣን ላይ የሚገኘው የፖለቲከኛ ድርጅትና ካድሪዎቹ ሲሆኑ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን በጢሰኝነት እየማቀቀ ይገኛል። ይህንን እንደ ታላ1ቅ ጀብድ ቆጥረው አሁንም “መሬት ላራሹ” የሚለውን ቃል የቀመረው ብርሃነ ምስቀል ረዳ ነው በማለት ዝናቸውን ለማጉላት የሄዱበት ርቀት የሚያስተዛዝብ ከመሆን በላይ ‘ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ’ የሚለውን የአበው ፈሊጣዊ አነጋገር እንድናስታውስ ያደርገናል።

የዚያ ዘመን ትውልድ ኪሣራ ተዘርዝሮ አያልቅም፤ የራሱን ባህል በማንቋሸሽ የባዕድን ጋጠወጥ የሆነ ልማድ ተሸካሚ ነበር የሆነው። ወንዱ ቤል ቦተም ሡሪ፤ ባለተረከዛማ ጫማ መልበስና ፒፓ ማጨስ፤ ሴቷም ስፒል ጫማ መጫማትና ሚኒ እስክርት በመልበስና ጭኗን ማሳየት፤ እንደ  ሥልጣኔ አድርገው የወሰዱበት እጅግ አሳፋሪ ወቅት ነበር። እንዲህ ያለው የባህልና የሥነ አእምሮ ወረራ የተከሰተው ርካሽ መጻሕፍትን በማንበብና ወደ አገራችን ሆነ ተብሎ የሚገቡ የስኒማ ፊልሞችን በማየት እንደዚያ ለመሆን እየተኮረጀ ስለነበር ነው። ቀደም ሲል የነበሩት ተማሪዎችም ሆኑ ባለሥልጣናት የቤተ ክርስቲያን ወይንም የመስጊድ ትምህርታቸውን በወጉ ያጠኑ ስለነበር ፈሪሃ እግዚአብሔር ነበራቸው። የዚያ ዘመን ትውልድ ግን ክርስቲያኑ ቤተ ክርስቲያን የማያውቅ እስላሙም መስጊድ ሄዶ የማያውቅ በመሆኑ እንኳን ሕዝብን እግዜአብሔርንም የማይፈራ ሆነ።

ለዚህ መገለጫው እንኳን የሚያውቀውን አብሮ አደግ ጓደኛውን ይቅርና በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረውን ሌላውን የማይታወቅ ሰው እንኳ ለመግደል አይጨክንም ነበር። ነገር ግን ምንም እንኳ አቶ ብርሃነ መስቀል ረዳ በሐሳብ ፍትጊያ እንጂ በመገዳደል የማያምኑ ቢሆንምና ነፍስ ባያጠፋም ሕይወታቸውን ግን ከአረመኔዎች ሊታደጓት እንዳልቻሉ ተረድተናል።

የደራሲዋ የተመሰቃቀለ ሕይወትና የቤተስቦቻቸውን ሥቃይ ምን ይመስል እንደነበረ ቁልጭ አድርገው አስቀምጠዋል። ወ/ሮ ታደለች ኃይለ ሚካኤል ምናልባት አንድም የልብ ቅንነት ስላላቸው ወይንም ደግሞ እግዚአብሔር ያዩትን እና የተረዱትን እንዲጽፉ፤ ከአንድ ምንቸት የተቀቀለ ጥሬ ውስጥ ሳይበስል እንደሚወጣ ቅርጣን ለምስክርነት እንዳተረፋቸው የሚያውቀው የእማማ ብርአልጋ አምበሬ፡(ልጃቸው ከእስር ቤት እንድትፈታ ከአስር ዓመታት በላይ ሲጸልዩ የነበሩ የወ/ሮ ታደለች ኃ/ሚካኤል እናት ናቸው) አምላክ ብቻ ነው። የዚያን ዘመን ወላጆች ያለፉበትን ሥቃይ ለመግለጽ ከሚችሉ ጥቂት መጻሕፍት ‘ዳኛው ማነው?’ አንዱ እንደሆነ የሚያጠራጥር አይደለም።

ደራሲዋ ስለመሬት ጉዳይ በስተመጨረሻ ሲያብራሩ “መሬት በመንግሥት መያዙ (nationalize) ይኸው እስከ ዛሬ እራስ ምታት ከመሆን አልፎ እንደ ቀድሞው ከመንግሥት ጋር የተቆራኙ ፖለቲከኞች የሚያዙበት ሆነ። ቆይቶም በኢሕአዴግ ብሔር ተኮር የሆነው የፖለቲካ ሥርዓት የብሔሮች ልሂቃን፤ መሬት በመሸጥና በመለወጥ ዋነኛው የሀብት ማፍሪያ ዘዴ ሆነ። በመሆኑም የማምረቻ መሣሪያነቱ ቀርቶ በማገለባበጥ በሚሊዮኖች የሚሸጥና የሚለወጥ የፖለቲከኞችና እነርሱን የተጠጉ የሚበለጽጉበት መሣሪያ ሆነ” በማለት ገልጸውታል።

ከዚህ የምንረዳው የዚያ ትውልድ አቀንቃኞች የአገራቸውን የመሬት ሥሪት ታሪክ፤ የኢኮኖሚ፤ማኅበራዊና የዓለም አቀፉን የፖለቲካ ሁኔታ በደንብ ባለማጤንና ባለመረዳት የውጭ ደራሲያን የጻፉትን በማንበብና የቅኝተገዥዎችን የነፃነት የትግል ታሪክ በቀጥታ ወደ እኛው አገር በማምጣት የጫኑት መሆኑን በቀጥታም ባይሆን አጋድመው የያዙት አቋም ትክክል እንዳልነበር መጸጸታቸውን ያመለክታል።

በተጨማሪም ታዲያ ለምን ነበር ኢሕአፓ ግቡን ሊመታ ያልቻለው? በማለት ይጠይቁና “ ከየትኞችም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሻለና በቁጥርም የበዛ ቆራጥ ዓባሎችን፤ምሁራንን፤ ገበሬዎችን፤ሠራተኝችን፤ወጣቶችንና ሴቶችን ይዞ፤ የት ይደርሳል የተባለ ድርጅት፤ እንዴት በአጭር ዕድሜው ተቀጨ? ብለን ስንጠይቅ፤ ውጫዊ ከሆነው ፍጹም ጨካኝና ፍርደ ገምድል የወታደራዊው መንግሥት ዳኝነት ባሻገር፤ በዋናነት የራሱ ውስጣዊ ችግሮች ለውድቀት እንዳበቁት እንገነዘባለን” ሲሉ አክለዋል።

ቀጥለውም “ለቀረጸው ፕሮግራም ተዓማኒነቱን በመርሳት፤ ከገጥር ወደ ከተማ የሚለውን የትግል ስልቱን በመለወጥ፤ በአጭር መንገድ በከተማ አመጽ (armed insurrection) ለሥልጣን እበቃለሁ ብሎ ማሰቡ፤ የኢሕአፓ አመራር (ክሊኩ) የአመለካከት ችግር ዋነኛው መገለጫ ነው። ይህንንም ውሳኔውን ከራሱ አባሎች በመሰወር፤ የማዕከላዊ ኮሚቴውንም ሥልጣን በመርገጥ፤ በጥቂት የአመራሩ አካል ነበር የወሰነው።……. በአጠቃላይ ይኸው ጥቂት ቡድን የሚከተሉትን ዋነኛ ስህተቶች ፈጽሟል።

 • ዓባላት የተስማሙበትን የትግል ስልት መቀየር
 • ልዩነቶችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ልዩነቱን ማግዘፍ
 • የዓባላትን ስሜት አለማዳመጥና ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን መንፈግ
 • በአንድ ጎን የደርግን ኢዲሞክራሲያዊነት እየተቃወመ፤ እራሱም ይቃወሙኛል የሚላቸውን የሌላ ፓርቲ ዓባላትንና በመጨረሻም ያለፍርድ ወደ እርስ በእርስ ግድያ ላይ መሠማራቱ ነው” በማለት የተሰማቸውን ገልጸዋል።

በማጨረሻም ምን እናድርግ? በሚል ይጠይቁና ያሳለፍነውን የሕይወት ውጣ ውረድ በትክክል ተገንዝበን ጠንካራውን ከደካማው ለይተን በማበጠር በድፍረትና በንጹሕ ኅሊና መወያየትና ልንማርበት ይገባናል፤ ካሉ በኋላ ‘ይህንን ለማድረግ በሰከነ መንፈስ ምን ተደረገ? ምን ላይ ስህተት አደረጉ? ዛሬ ላይ ያን ያደረጉትን ስህተት የምንላቸውን በማወቅ ነቅሰን በማውጣት ላለመድገምና ትምህርት በመውሰድ ታሪክን ወደፊት ማስቀጠል ይገባል። የአንድን ግለሰብ የአሳብ ልዕልና አለመቀበል ቢያንስ ለማስተናገድ አለመሞከር፤ ከስህተቶችም በላይ ነው። ከአሉ በኋላ ‘ስህተትን አግዝፎ በአስተሳሰብ ላይ የነበረውን ልዩነት ወደ ስብዕና በማውረድ በማንነት፤በብሔር፤በጎሳና በሃይማኖት በማተኮር ከስህተትም በላይ ስህተት በመፈጸም ምንም ትምህርትም ሆነ ዳኝነት ሊገኝ ወደማይቻልበት የቁልቁለት ጉዞ እየሄድን ነው” በማለት ጸጸታቸውንና ተሞክሯቸውን አጋርተዋል።

ይህም አሁን የአለንበትን ዘመን ማለትም ፍትህ በተከለከሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ስዎችን (እስክንድር ነጋን እና አቶ ልደቱ አያሌውን ) ሁኔታ እንድናስታውስ ይጠቁመናል።

በአጠቃላይ ደራሲ ወ/ሮ ታደለች ኃ/ሚካኤል ጊዜ ወስደው የዚያን ትውልድ እንቅስቃሴና ምንም እንኳ የተሳሳት መስመር ቢይዝም የነበረውን የአገርና የወገን ፍቅር ቁልጭ አድርገው በማሳየት ቀጣዩ ትውልድ ከተመሳሳይ ስህተት እንዲታቀብ የሚያስተምር መጽሐፍ በማበርከታቸው የተሰማኝን አድናቆት መግለጽ እወዳለሁ።

ይህ መጽሐፍ ከ11ኛ ክፍል በላይ እስከ ዩኒቨርስቲ ባሉት የትምህርት ተቋማት እንደ ፍቅር እስከመቃብር ሁሉ ተማሪዎች አንብበው እንዲገመግሙና እንዲማሩበት ቢደረግ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ መሆኑን ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ለከፍተኛ ተምህርት ተቋም ባለሥልጣናትም ማስታወስ እፈልጋለሁ። የዚያን ትውልድ ታሪክ በወፍ በረር ካልሆነ በስተቀር በቂ ዕውቀት ለሌላቸውና በተለይ ለፖለቲካ ፓርቲ ዓባላትና ዕድሜያቸው ከሃምሳ ዓመት በታች ለሆኑ ሌሎችም ዜጎች ቢያነቡት ጥሩ ግንዛቤና ትምህርት ሊቀስሙበት እንደሚችሉ አስተያየቴን ለመግለጽ እወዳለሁ።

-//-

ስለዚህ ጽሑፍ ያላችሁን አስተያየት በ gkabbay@gmail.com መላክ የምትችሉ መሆኑን በትህትና እንገልጻለን።

2 Comments

 1. በውነቱ ምን ይባላል ስለ ጸሀፊዋ ምስጋና ሲያዥጎደግዱ ሳይመቸኝ የመጀመሪያውን ፓራግራፍ እየከበደኝ አነበብኩት በሁዋላ የነገሩን ጭብጥ አገኘሁት ስለዚህ ወንጀለኛ ድርጅት ብዙ ነገር የሚያውቁ ሳይሆኑ አይቀሩም ሰው ቋሚ ባለስስነው ስስስስመሆኑ ጊዜ ወስደው የነ ክፍሉ ታደሰን ማፍረሻ ቢጽፉልን መልካም ነው።
  በተረፈ በማህደር ውስጥ የሚገባ ትልቅ ስራ እርሶም አበርክተዋል እናመሰግናለን እንደ ወንጀለኛ መቅጫ ክፉ ነገር በኢትዮጵያ ጠላቶች የሚመዘዘው ከነዚህ ስዎችና ዋለልኝ ከሚባል ግለሰብ ነው ምንም እንኳን እሱ ተላላኪ ቢሆንም። ከዚህ በላይ መሄድ ግሩም የሆነ ጽሁፎን ማደብዘዝ ስለሚሆንብኝ እዚህ ላይ አበቃሁ።አመሰግናለሁ

 2. አስተያየት ስጪው የፀሐፊዋን መልክት ሳይሆን የተቹት የራሳቸውን የተዘበራረቀ አመለካከት ከወዲያያወዲህ በማሞታታት እንድንቀበል ነው የጣሩት:: ያን ትውልድ ባጠቃላይ መዉቀስና መወንጀል የጠባብነትና የትምክህተኝነት ባህርይ ነዉ:: እርስዎም ውስጡን በሚገባ የማያውቁትን ድርጅት እባላት (ያ ትውልድ ተብሎ በጅምላ የሚጠራውን) ጅሮ ጠገብ በሆነ እውቀትዎ ማንቋሸሽ እና ከንቱ ማድረግ የሞራልም ሆነ የህሊና ብቃት የለዎትም ያ ትውልድ በድፍረት ከደርግ ጋር ስፋለም እርስዎ ምን ሲሰሩ እንደነብር እራስዎን ሊጠይቁ ይገባል እንደ እርስዎ ያሉ አድርባዮች ጅምላ ፍጅት አግባብ አለመሆኑን መናገር በማይደፍሩብት ወቅት ስርዓቱን ግብ ግብ የገጠመን ጀግና ትውልድ ሲይንቋሽሹት እና ሲያናንቁት መስማት ያማል
  እርስዎ የሚናፍቁት የዘውድ ስርዓት ከሰራው መልካም ሥራ ባልተናነሰ ስልጣኑን የሙጥኝ ብሎ በመያዙ አሁን ወደ ወረድንበት አዘቅት የግፋን መሆኑን ማስተባበልና ችግሩን ወደ ያ ትውልድ መግፋትን መርጠዋል ያትውልድ የታገለለትን መሬት ላራሹ በማንቋሸሽ እርስዎ”የአርበኛ ልጆች ” መሬት መነጠቅና ድህነት ሲቆጩ የሰፊው ጭሰኛ እና ገባር ህይወት ምን ያህል ስቃይ እንደነበር አላሳሰበዎትም::
  በአጠቃላይ ግልብ በሆነ እውቀት ተነስተው ከመዘባረቅና በግፍ የፈሰሰ ወጣት ደም ቋሚ ቤተሰቦች ሞራል ላይ ተጨማሪ ሀዘን ጉዳት ማድረስ አግባብ ስለአይደለ ትችት ከማቅረብዎ በፊት ደጋግመው ያስቡ
  ስላም እና ፍቅር ለሁላችን!!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.