ዳኛውማ “ደርግ” ነው

መጽሐፍ አስተያየት፦ ነሲቡ ስብሐት ከሰሜን አሜሪካ ቨርጅኒያ (703)3004302 ([email protected])

ቀን፦ መስከረም 24 ቀን 2013 ዓ.ም. (September 04, 2020)

የመጽሐፉ ርዕስ ፡ “ዳኛው ማነው?” የብርሃነመስቀል እና የታደለች ህይወት በኢሕአፓ የትግል ታሪክ 2012 ዓ.ም. እና የብርሃነመስቀል የእሥር ቤት ቃል ምርመራ ሰኔ 1971 ዓ.ም.

Birhane Meskel

ደራሲ ፡ ታደለች ኃይለሚካኤል

ገጽ ብዛት 442

ታሪክ ያለው ይጻፍለታል፡፡ በኢትዮጵያ ህዝብ የትግል ታሪክ ኢሕአፓ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ስለ ኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ፣ ስለ 1966 የካቲት አብዮት፣ ስለ መሬት ለአራሹ፣ ዴሞክራሲያ መብት፣ የብሔር ጥያቄ፣ የሕዝብ መንግሥት ሲነሳ፣ ሲጻፍ፣ ሲነገር ኢሕአፓ ሁለት ነጥብ ነው፡፡ ኢሕአፓ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ጎኑ በተለያየ መልኩ ተጽፏል፣ ተነግሯል፡፡ ኢሕአፓ ሲባል ወጣቶች ውቅያኖሱ ናቸው፣ እናት አባቶች በልጆቻቸው ታሪክ ተቋድሰዋል፣ ታዳጊ ሕጻናት ወላፈኑ አግኝቷቸዋል፡፡ ስለ ኢሕአፓ ሲነገር ሀገር፣ ሕዝብ፣ ዓላማ፣ ጽናት፣ ትግል፣ ሥነጽሁፍ፣ ኪነት የመሳሰሉት ስለ ሚነገሩ ተወርቶ አያልቅም፡፡ አፈሳው፣ እሥሩ፣ ግርፊያው፣ ግድያው፣ ስደቱ፣ መቆዘሙ፣ ጀግንነቱ፣ መስዋዕትነቱ፣ ደፋርነት፣ አጅሃብ! እስኪያሰኝ ይደመጣል፣ ይነበባል፡፡ ፍርሃት፣ ቀላባጅ፣ አስመሳይ፣ ወሬኛ የራሳቸው ድርሻ ነበራቸው፡፡

ኢሕአፓ በኢትዮጵያ የትግል ታሪክ አምባገነንነትን የተፋለመ፣ ተፋልሞ የተደበደበ፣ ተደብድቦ የተሰናከለ፣ ተሰናክሎ ታሪክ የሠራ ቀዳማይ ፓርቲ ነው፡፡ የኢሕአፓ ታሪክ ለትግል መሠረት ነውና ሁሉም ያጠቅሰዋል፡፡ ስለ ኢሕአፓም ሆነ ስለ ያ ትውልድ ዘመን ጸሐፊዎች፣ ተራኪዎች፣ ቲያትር ሠሪዎች ሁሉም በትክክል ዘገቡ ወይስ አዛቡ ብሎ መቃኘት በተለይ የዘመኑ አባላት ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡ ዝም ከተባለ ቀጣይ ትውልድ የሚከራከርበት፣ የሚጠቅሰው ሞጋች ሀሳብ ያጣልና፡፡ የእኛ ሕይወት ዘላለማዊ እንዲሆን ከፈለግን ትውልድ ይመራመርበት፣ ኖ! ይህማ ልክ አይደለም ይልበት፣ ትምህርት ይቀስምበት ዘንድ አሻራችንን ታሪኩ ላይ ማዋል ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡

መንግሥቱ ኃ/ማርያም “ትንኝ ገድዬ አላውቅም” ሲል በመቶ ሺህ የሚቆጠረውን የትውልድ ፍጅት በሁለት መጽሐፍና በዘጋቢ ጸሐፊው አማካይነት ካደ፣ ፍቅረስላሴ ወግ ደረስ ሽምጥጥ አድርጎ በትውልዱ ተሳለቀ፣ ካደ፣ ፍስሀ ደስታ በይቅርታ ስም ትውልዱን አንቋሾ ካደ፣ ሌሎች ካዱ፣ ትረካቸው ለነፍሳቸው አደላ፡፡ መጽሐፈ ቀይ ሽብር ዘ መኢሶን ካደ፣ በምስክርና በሰነድ ወንጀለኝነታቸው የተረጋገጠባቸው እንደ ቀልቤሳ ነገዎ፣ ከፈለኝ ዓለሙ ዓይነቶች እንደካዱ ወደ እሥር ቤት ተወረወሩ፡፡ “የዘንድሮ ጅብ የሚያውቁት ሀገርም ሂዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ይላልና” የትላንት ወንጀላቸውን ደብቀው ዛሬ ስለ ዴሞክራሲ መብትና ስለ ሕዝብ ብሶት መድረኩን ያጣበቡ የዕድሜ ባለጸጋ ባለ ነጭ ጸጉሮችና ጸጉር አልባዎች ምን ያህል ልባቸው ለጭካኔ ቢደነድን ነው ጸጸትን የዘነጉት ያሰኛል፡፡

mengistu hailemariam

“ዳኛው ማነው?” መጽሐፍን ከሥነ ጽሁፍ አንጻር ለመገምገም ሙያውም ችሎታውም የለኝ፡፡ የታሪኩ መጠነኛ ተቋዳሽ ብሆንም ሁሉንም አውቃለሁ ብዬ አልንቦራጨቅም፡፡ ማንበብ፣ ማድመጥ ማወቅ ነውና ነበርን ከሚሉት ያላነሰ ታሪክን የሚዘግቡ፣ ለትውልድ የሚያስተላልፉ መኖራቸውን ያህል በመጠኑም ካገላበጥኳቸው፣ ዕድሜ የሰጠኝን ግንዛቤ በመጠቀም የዛሬዋ አምባሳደር፣ የትላንቷ ጓዲት ታደለች ኃይለሚካኤል መጽሐፍ ኢሕአፓን በሰፊው ስለሚነካ የተሰማኝን፣ የገባኝን፣ የኮረኮረኝን፣ ያስተከዘኝን፣ ያስቆጨኝን፣ ወይ ኢትዮጵያ! ወይ ሀገሬ! አይ ኢሕአፓ! እና ሌላም ያሰኘኝን ላስነብባችሁ ወደድሁ፤ ፈለግሁ፡፡

“ዳኛው ማነው?” በቅርብ ቀን በገበያ እንደሚውል ማስታወቂያ ስመለከት ከርዕሱ የመጽሐፉን መልዕክት ጠረጠርሁ፡፡ ያም ሆነ አንድ መጽሐፍ ሳይነበብ፣ የአንድ ሰው ቃለ መጠይቅ ሳይደመጥ ትችት አይሰጥምና በጉጉት የተጠባበኩት መጽሐፍ እጄ ገብቶ ወረድኩበት፡፡ መጽሐፉን ገና ሳላነበው አምባሳደር ታደለች በትግል ያገኙትን የወጣትነት ፍቅረኛቸውን፣ በውጭ ሀገር፣ በሀገር ቤት እና በእሥር ቤት ያወላለድ ታሪክ ያላቸውን የሦስት ልጆቻቸውን አባት ብርሃነመስቀል ረዳን በኢሕአፓ

በተሰጠው “የአንጃ መሪ” ተቀጽላ ሊከላከሉ እንደሚችሉ ገምቻለሁ፡፡ ግና በምን መልኩ? በአሳማኝ ነጥቦች በማስቀመጥ፣ ነገሮችን ግራ ቀኝ በመመልከት? ወይስ እንደ አንዳንድ ጸሐፊና ተናጋሪዎች በሆነው ባልሆነው ኢሕአፓን ጥላሸት በመቀባትና በማንቋሸሽ? በሌላ መልኩ ጥርጣሬም ቢኖራቸው የማያውቁት ላይ ድምዳሜ ከመስጠት ተቆጥበው የኢሕአፓውን መሥራች ብርሃነመስቀል ረዳ ባህሪ፣ ችሎታና፣ አስተሳሰብ አስታከው በተሸፋፈነና ግልጽ ባልሆነ መልኩ የተደረሰበት የአንጃ ፍረጃን የሚያውቁትን አስቀምጠው “አንባቢ ሆይ! እናንት ፍረዱኝ” በሚል በሩን ከፍተው ፤

“ከስህተታችን እንድንማር ለጊዜያችን ዳኝነት ለመስጠት ሁሉም በየራሱ ቡድንና ድርጅት የተከሰተውን ችግር ነቅሶ በማውጣት ችግሮቹን እንዳሉ መቀበል፡፡ ተነቅሰው የወጡትን ችግሮች ልዩነታቸውንና ተመሳሳይነታቸውን በመገንዘብ ብሔራዊ ተግባቦት ለመፍጠር መትጋት ያስፈልጋል፡፡” (ዳኛው ማነው? ገጽ 424)

በሚል ያቺ ለሞት የታጨች የያ ትውልድ ወጣት እንደስሟ ታድላ ዛሬ ላይ ሆና አንቱ ልበልና አስነብበውናል፡፡

የመጽሐፉን የመጀመሪያ ምዕራፍ 1 የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር አንብቤ ሦስት ገጽ እንደተጓዝሁ “ጥላሁን ግዛው የሞተ ጊዜ” በሚለው ርዕስ ሥር ያለውን የዓመተ ምህረት መዛባት ገና ከጅምሩ ሳይ፤ ስህተቱ ከእኔ አነባበብ ነው ብዬ መልሼ መላልሼ ባየው ያየሁት መዛባት ያው ነው፡፡ ማንበቤን አቋርጬ ዘጋሁትና ይህ እውነተኛ ታሪክ መጽሐፍ፣ ለአሁኑና ለነገው ትውልድ ተቀማጭ፣ በመረጃ ተደግፎ ተጽፎ ለነገ በመረጃነት የሚያገለግል ከና ከጅምሩ በዓመተ ምህረት ሲጣላ ገባ ሲባልማ መሣሪያ እንዳይማዘዝ ሰጋሁ፡፡ ከደራሲዋ በበለጠ በምስጋና የተወደሱት አንባቢያን ላይ አዘንሁ፡፡ 12 አንባቢያን 24 ዓይኖች እንዴት ዘለሉት አልኩ? አንብበዋል እንጂ አላስተዋሉም አልኩ፡፡

ወጣት ታደለች ህዳር 5 ቀን 1962 ዓ.ም. በ19 ዓመት የልደት ቀኗ ዕለት ወደ ስዊዘርላንድ ለትምህርት ተጓዘች (ገጽ 3) ከ3 ገጽ ጉዞ በኋላ ታህሳስ 19 ቀን 1962 ዓ.ም. ጥላሁን ግዛው የተገደለ ዕለት “እኔም ከጥቂት ጓደኞቼ ጋር እዚያው ታድሜያለሁ” ትለናለች፡፡ ስዊዘርላንድ በሄደች በወር ከ14 ቀን ማለት ነው፡፡ ጥላሁን ግዛው የአረፈበት ዕለትና ዓመተ ምህረት ትክክል በመሆኑ ለቀጣይ እትመት ወደ ስዊዘርላንድ የተጓዘችው ህዳር 5 ቀን 1963 ዓ.ም. በሚል ቢስተካከል ሳልጠቁም አላልፍም፡፡ ቀላል ሎጂክ??? በጥቅሉ መጽሐፋቸውን በቃላት ለቀማ እጅግ የተዋጣለት ሥራ ተሰርቷል፤ ቋንቋቸውና አጻጻፋቸውም ጭንቅላቴን ገና በገና “የአንጃ ሚስት” ብዬ በጥላቻ ሳይሆን፤ በምን መልኩ አቀረቡት? የሚለውንና ምን አገኝበታለሁ? በሚል ጉጉት ስለአነበብኩት ቋንቋቸውንና አገላለጻቸው ከዘመኑ ወጣቶች ቃላት ልዋስና ለእኔ ተመችቶኛል፡፡

በፖለቲካ ብስለትና ፍላጎት እምብዛም የሆነችው ታደለች በስዊዘርላንድ ህይወቷ የኢሕአፓውን መሥራች ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይን፣ አክሊሉ ህሩይ በአጋጣሚ በሀገር ልጅነት ተዋውቃ እንዴት ወደ ፖለቲካው ልትሳብ እንደቻለች ሂደቱን ስትተርከው የነተስፋዬን ትዕግስት፣ የአክሊሉን ብልጠት አስታኮ ምን ያህል ሴቶችን በትግሉ ለማሳተፍ የነበራቸውን ጥረት ያሳያል፡፡ እውነትም ተሳክቶላቸዋል፡፡ ኢሕአፓ ሴቶችን ከቤት እመቤትነት ወደ ትግል እመቤትነት ያወጣ ጠንካራ ፓርቲ ነበርና፡፡ “ተዋት! በርግጠኝነት አንድ ቀን ትመጣለች” (ገጽ 21) ይል የነበረው ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ “የማትመጪው ፈርተሽ ነው አይደል?” (ገጽ 17) በሚል በሞራሏ የሚጫወተው አክሊሉ ህሩይ በውይይት መድረካቸው “ፍቅር እስከ መቃብር”ን በማቅረብ አስጀምሮ ወደ ተማሪዎቹ ስብሰባ እየተጎተተች፣ እየተሳበች ሳታስበው ጥልቅ እንዳለች ስታስቀምጠው በወቅቱ የነበሩ ሴቶች ኢሕአፓውያን እንዴት ድርጅቱን እንደተቀላቀሉ መለስ ብለው የ46 ዓመት ካሴት ወደ ኋላ እንዲያጠነጥኑ ታደርጋለች፡፡ ለአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የበቁትና የውጭ ዕድል አግኝተው በትምህርት መስክ ያሉት በኢሕአፓም ሆነ በመኢሶን በኩል የተሰለፉት ወጣት ሴቶች በወቅቱ በኑሮ ደረጃም ሻል ያሉ ነበሩ፡፡

ታደለች በውጭ ትምህርቷ ተከራይታ የምትኖርበትን ቤት ተስፋዬ ደበሳይ ለአንድ ቀን እንድትፈቅድለት በጠየቃት መሠረት ታዋቂው ብርሃነመስቀል በእንግድነት መጥቶ ከወጣት ታደለች ለመተዋወቅና የትዳር ጓደኛ የመሆንን ሂደት በጥሩ መልኩ ገልጻዋለች፡፡

በነሐሴ ወር 1961 ዓ.ም. ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር የአውሮፕላን ጠለፋ ላይ ተሰማርቶ ወደ አልጀሪያ ካቀናው ቡድን ውስጥ ብርሃነመስቀል ረዳ ከዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ጋር ለመገናኘት ወደ ሲዊዘርላንድ በመጣ ወቅት የጋራ ውይይታቸው በታደለች የትምህርት መኖሪያ ቤት ተካሂዷል፡፡ ሁለቱ ዝነኛ ታጋዮች በያዙት የሀገር፣ የህዝብ፣ የድርጅት፣ ሌላም ሌላ ጉዳይ ውይይት ሁኔታ ታደለች በዚህ መልኩ ትገልጸዋለች

“. . . እኔ አዘገጃጅቼ እስክጨርስ ምንም አላቆሙም፤ በለሆሳስ አፍ ለአፍ ገጥመው ያወራሉ፡፡ አንደኛው ሲያቆም ሌላኛው ይቀጥላል፡፡ . . .” (ገጽ 39) “. . . እቤት ደርሼ ቁልፉን ስከፍት እንደዚያው ጥያቸው እንደሄድኩት ወሬያቸውን ጠምደዋል፡፡ ምግቡን በልተው አላነሱትም፡፡ ወይኑንም ጥቂት ቀምሰውታል እንጂ አልጠጡትም፡፡”

በሚል ለታላቅ የሀገርና የህዝብ ገድል ረዥሙን ጉዞ እንዴት እንደሚጀምሩት? ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚነጋገሩት ሁለቱ አንጋፋ የኢሕአፓ ምሰሶዎች አፍ ለአፍ የገጠሙት ማሳረጊያቸው ሆድና ጀርባ ሲሆን ያማል፤ ያቆስላል፡፡ ለሰው ልጅ ዛሬ በፍቅር፣ በእምነት፣ በጽናት የተሳሰርንበት ዓላማ ነገ በአንዲት ጠብታ ሤራ እሳትና ጭድ ሊኮን እንደሚችል ይመጣብናል፡፡ ሰዎች ያመኑት ሰዋቸው ሳያቁት ነገ እሚሰምጥ ገደል ላይ (Sinkhole) አቁሟቸው ውስጡ ሲስቅ ይታያችኋል፡፡ “ሰውን ውደደው እንጂ አትመነው” ቢያቃጭልባችሁም እንዴት ተደርጎ በኢሕአፓ ያለ እምነት? ያስብላችኋል፡፡ ሌላም ሌላ፡፡

ሰው የፈለገ ቢሆን ፍቅርን ይወዳል፤ የተቃራኒ ጾታ ፍቅር ደግሞ እጅጉን ይወደዳል፡፡ ከምስኪኑ ድሀ እስከ ባለጸጋው፣ ከመሃይሙ እስከ ምሁሩ ብቻ የሰው ዘር በሙሉ የተቃራኒ ጾታ ፍላጎት ገደብ የለውም፡፡ ከዚህ አኳያ በትግል ለትግል ከተሰለፉ ሴቶች መጽሐፉ ውስጥ በሰፊው ከተወሱት ፍቅርተ ገ/ማርያም፣ አበበች በቀለ፣ አዳነች ፍስሃዬ ጀምሮ ማርታ መብራቱ ፣ መዝገብነሽ አባዩ፣ ገነት ግርማ፣ ሰላማዊት ዳዊት መሰል ከፍተኛ የኢሕአፓ መሥራች ሴቶች በአብዛኞቹ የአመራር አካሉ ፍቅረኛ ወይም ባለቤቶች መሆናቸው ትግልና ፍቅር መጣመዳቸውን ያሳየናል፡፡

የዛሬዋ አምባሳደር ታደለች መጽሐፍን ካነበብሁ በኋላ በቀጥታ ጉዞ ወደ ብርሃነመስቀል አደረግሁ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ሁለት ጊዜ አንብቤውና ትዝብት ወርሼ፣ ሀዘኔን ቋጥሬ “ያ ትውልድ” ድረ ገጽ ላይ “ምን ብለው ነበር?” (http://yatewlid.com/images/PDF/MinBlewNeber/Berhanemeskel.pdf ) በሚል ዐምድ ሥር ወደ ተቀመጠው 96 ገጽ የብርሃነመስቀል ቃል ምርመራ ሠነድን “ዳኛው ማነው” ከሚለው መጽሐፍ ጋር እያዛመድሁ፣ እያገናዘብሁ ማንበብ ጀመርሁ፡፡ ጸሐፊዋ ይህንን ሰነድ አንድ ጊዜ (ገጽ 271) ብቻ ቢጠቅሱትም መጽሐፋቸውና የብርሃነመስቀል የምርመራ ሠነድ አንድ ናቸው፡፡ በመሆኑም መጽሐፉን ከመገምገም ጋር እራሱ የተናገረውን፣ የሰጠውን ቃል ይበልጥ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ከላይ እንደገለጽኩት አምባሳደር ውድ ባለቤታቸውን፣ የሦስት ልጆቻቸውን አባት እንዴት ብለው ተሳስቷል ይላሉ? እንዴት ብለው ደርግ ፋሽስት ነው ይላሉ? ብዬ በኢሕአፓ ያለችኝን አንድ ጠብታ ውሎና ዕድሜ ከሰጠኝ ግንዛቤ በመነሳት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ልጽፍ ፈለግሁ፡፡

“ዳኛው ማነው?” የሚለውንም ሆነ ስለሌሎች መጽሀፍት ስለእያንዳንዱ የራስ ግምጋሜ መስጠት ቢቻልም እኔ ያተኮርኩት በብርሃነመስቀል እና የአንጃ ጉዳይ ጋር የተነሱት ነጥቦች ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ መጽሐፉን አንብቦና አጣጥፎ መጽሐፍ መደርደሪያው ላይ በማስፈር መቋጨቱ በተለይ በኢሕአፓ ጉዳይ በተደጋጋሚ በመጽሐፍም ሆነ በቃለ ምልልስ የሚደናገረው የአሁኑ ትውልድም ሆነ መጪው ትውልድ ይህ ተጽፏል ብሎ ይወያይበት፣ ይከራከርበት ዘንድ ያለኝን ነጥብ ማካፈሉ ከዝምታ ይሻላል ብዬ ወርውሬአለሁ፡፡

ኢሕአፓ ፕሮግራሙን ለሕዝብ አሰራጭቶ እራሱን ይፋ በአደረገበት ነሐሴ 26 ቀን 1967 ዓ.ም. የደርግ አገዛዝ ዓመት ሊሞላው ከሁለት ሳምንት ያነሰ ቀናት ነበር የሚቀረው፡፡ በቀጣይ ዓመት 1968 ማለት ኢሕአፓ ሙሉ በሙሉ የጀመረውን መዋቅሩን በማጠናከርና በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ ይዟቸው የተነሳውን ወቅታዊ መፈክሮች ማታገያ አደረጋቸው:: ደርግ በ1967 የካቲት 25 ቀን የመሬት አዋጅን ቢያውጅም የሚያካሂደው አመቃና አፈና ጎልቶ መውጣቱ የኢሕአፓ ማታገያ መፈክሮች የኃይል ሚዘኑ ወደ ህዝብ እንዲያጋድል ሆኗል፡፡ “የዴሞክራሲ መብት ያለገደብ” መፈክር ተቀባይነት ማግኘት ከደርግ ይልቅ ኢሕአፓ ተደመጠ፣ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት አሁንኑ” መፈክር ደርግ ወደ ጦር ሠፈሩ ይመለስ ዘንድ በወጣቱና በህዝቡ ዘንድ እምቢታን አስከተለ፣ “የብሄር ብሄረሰቦች መብት እስከመገንጠል” ኢሕአፓ ቢቀበልም ቅስቀሳውና ትግሉ የመደብ ትግል ላይ ማተኮሩ በብሔር የተደራጁ ኃይሎችን ተደማጭነት አሳጣ፡፡ ይህ የአንድ ዓመት በተለይ የ1968 ዓ.ም. እንቅስቃሴ ኢሕአፓን እንደስሙ ሕዝባዊ አድርጎታል፡፡ የሕዝብን ስሜት ይዞ ስለተነሳ ተደማጭነት፣ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ከዚህ ሂደት በኋላ ኢሕአፓ የወጣቱ፣ የሴቶች እህቶቻችን፣ የላብ አደሩ፣ የአርሶ አደሩ፣ የጭቁን ወታደሩ፣ የመምህራን፣ የተማሪዎች፣ የሠራተኛው፣ የእናቶች፣ የአባቶች በጥቅሉ የሕዝብ ሆኗል፡፡ ይህ ነበር የዚያ ጊዜ ዘር ቆጠራው፡፡ ክርስቲያኑን ከሙስሊሙ ለአንድ ዓላማ ያስተቃቀፈ ፓርቲ፡፡ በመዋቅርና በማደራጀት ደረጃ ኢሕአፓ ካስመዘገበው ከፍተኛ ድል በኋላ ኢሕአፓ የብርሃነመስቀል፣ ኢሕአፓ የጌታቸው ማሩ በሌላ በኩል ኢሕአፓ እንደ መጽሐፉ አባባል “የክሊኩ”

(የዶክተር ተስፋዬ ደበሳይ፣ የዘርዑ ክሸንና የክፍሉ ታደሰ) ሳይሆን የሀገርና የሕዝብ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት እና ሌሎች መሥራች አመራር አካላት ድርጅቱን በጋራ መሥርተው ሕዝባዊ እንዳሉት በአጭር ጊዜ ሲሳካላቸው ከዚያ በኋላ ንብረትነቱ የህዝብ ነው፡፡ በተለያየ ጊዜ በውስጣቸው ሊከሰት በሚችል አለመግባባት በርካታ አባላቱና ደጋፊዎቻቸው የጥቃቱ ሰለባ ሊሆኑ ባልተገባ ነበር፡፡ እዚህ ላይ ነው የብርሃነመስቀል ስህተት፡፡

ብርሃነመስቀል እንደሚለው እና ባለቤቱ ታደለች እንዳስነበበችን “በክሊኩ” አንጃ ተብሎ ተፈረጀ፣ ከፖሊት ቢሮ አባልነቱ ተነሳ፣ ከፓርቲው ተገለለ፣ በቀጣይነት ሊገደል ተፈለገ፣ ሸሸ፡፡ ጥሩ፤ ለምን ግን “በክሊኩ” እልህ የኢሕአፓ ልጆች እንዲጠቁ፣ ምንም ሳናውቅ እየታገልን ያለነው በመቶ ሺዎች እሚቆጠሩ ቤተሰቦች ላይ ፈረደ? እውን ትልቅ ሀገራዊ አጀንዳ ይዞ ያን ያህል ለትግሉና ለኢሕአፓ ትልቅ ስም የያዘ ብርሃነመስቀል መርሃቤቴ ገብቶ ከተራ ሽፍታ መንግሥቴ ደፋር ጋር ሲደራደር አያሳፍርም? ብርሃነመስቀል “በክሊኩ” ንዴት የተነሳ ከሚያውቃቸው ተባባሪዎቹ ጋር (በመጽሐፉ እንደተነገረው ከእርማት ንቅናቄው ጋር) በመሆን የኢሕአፓ ድርጊት እንዳይሳካ ማሰናከልና ምስጢር አሳልፎ መስጠት ማንን እንደጎዳ ሲታሰብ አያሳዝንምን? እውን ብርሃነመስቀል አላአግባብም ሆነ በአግባብ አንጃ ተብሎ እንደ ጌታቸው ማሩ በእጃቸው ላይ ስላልወደቀ ሁኔታዎች እንዳበቁለት ተገንዝቦ ከሀገር ለመውጣት ሙከራ ቢያደርግ በተገባ ነበር፡፡ በደርግ ከተያዘም በኋላ ሕይወቱን ለማዳን ሲል ለታሪክ ጥሎ ያለፈውን የምርመራ ቃል ከሚሰጥ በቆራጥ ዓላማው ተተልትሎ ቢሞት ስሙ እጅግ በተለወጠ፡፡ በዓይኑ ያየውን የሸሸበትን መርሃቤቴ ነዋሪ እህልና ጎጆ የሚያቃጥል፣ የሚያወድም ደርግ እንዴት እኔን ይምረኛል ብሎ ተስፋ አደረገ? እውን ከደርግ ጋር ተቀላቅሎ ገራፊና ገዳይ ካድሬ ከመሆን ሌላ ምን ያተርፍ ነበር? በየከፍተኛው፣ በየክፍለ ሀገሩ እየከዱ ለደርግ እጃቸውን የሰጡ አንዳንድ የኢሕአፓን ልጆች ለጥፋት በነጻ እርምጃ ከመሳተፍ ጀምሮ፣ እራሳቸውን ቀይረው ያሉ ኢሕአፓዎችን ከየተደበቁበት በማስያዝ፣ በመግረፍ፣ በማስገደል ድርጊታቸው ነው የሚታወቁት፡፡ በፖለቲካው እረገድ ትልቁን ተንኮልና ሤራ ያሰለጠኑትን መኢሶኖች የበላ መንግሥቱ፣ ከጎኑ የነበሩትን ኪሮስ ዓለማየሁን፣ ሻለቃ ሲሳይ ሀብቴን፣ ብ/ጄነራል ጌታቸው ናደውን፣ ብ/ጄ አማን አንዶምን፣ ጄ/ ተፈሪ በንቲን፣ ኮ/ሌ አጥናፉ አባተንና በርካታ የደርግ አባላትን መግደሉን በተግባር ያየ የኢሕአፓው መሥራች ብርሃነመስቀል እውን ከፋሽስት መንግሥቱ ኃ/ማርያም ጋር “ጓድ” ሊባባል ሲያስብ እንኳን ያኔ ዛሬ ያማል፡፡

የችግሩ መነሻ

ብርሃነመስቀል ከፖሊት ቢሮው ለመውጣት ዋናው ምክንያት የሆነው ፓርቲው ከመታወጁ ነሐሴ26 ቀን 1967 ዓ.ም. በፊት በተደረገው ክስ/ውንጀላ እንደሆነ በሰጠው የምርመራ ቃል ገጽ 7 እንዲህ ይላል

. . . የስብሰባው ዋና ተግባር ለመለስተኛ ጉባኤው መዘጋጀት ሲሆን ሌላው ሰፊ ጊዜ የፈጀው ውይይት ከታጠቀው ቡድን ጠፍተው ስለወጡት 7 ሰዎች ነበር፡፡ በዚህም ውይይት ዋናው ዓላማው ሰዎቹ የጠፉት በፖለቲካ መስመር ልዩነት ሳይሆን በኔ አስተዳደር ብልሹነት መሆኑን ለማሳመን ነበር። . . .” ስርዝ የተጨመረበት። በማስከተል

“ . . . ስህተቴን በመጠቆም ፈንታ እኔ ባልተገኘሁባቸው ስብሰባዎች ስለእኔ ሥራ ብዙ ክሶች ይቀርቡ ስለነበር. . . ከጉባኤው በፊት እውነተኛ ጓዳዊ መንፈስ እንዲሰፍን ሂስና ግለ ሂስ ይደረግ ብል አጣዳፊ ተግባሮች አሉና ከጉባኤው በኋላ ሂስና ግለ ሂስ እናካሂዳለን ተብሎ ነገሩ በዚህ ተደፋፈነ። . . .”

የብርሃነመስቀል መነሻ ልዩነት ከታጠቀው ቡድን ጥለው የወጡት 7 ሰዎች ምክንያት መሆኑን እራሱ ይመሰክራል፡፡ ወደ አሲምባ የገባው የመጀመሪያው የኢሕአሠ ቡድን ኤርትራ በረሃ እያለ የካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም. ከታወጀው የመሬት ለአራሹ አዋጅ በኋላ እዚህ ምን እናደርጋለን? የምንታገልለት ጥያቄ ተመልሷል ዓይነት ጥያቄዎች በቡድኑ ውስጥ ሲነሱ በአግባቡ እንዳልተስተናገዱ ተዘግቧል፡፡ በኤርትራ ቆይታቸው ብርሃነመስቀል ቡድኑን ትቶ ወደ አውሮፓ መጓዝና በሌላም በኩል ከሻቢያ ጋር በምን ጉዳይ ተስማምቶ ወደ አሲምባ ሊገቡ እንደተፈቀደላቸው ለሚነሱ ጥያቄዎችና ለተነሱ ቅሬታዎች አግባብ መልስ አለመሰጠቱ በአንድ ምሽት ወደ ግማሽ የሚሆኑት ለደርግ እጃቸውን ለመስጠት መሠወር የብርሃነመስቀልን የአመራር ብቃት ጥያቄ ውስጥ እንዳስገባውና ከሌሎች የፓርቲው አመራር አካላቱ ጋር የቅሬታና የልዩነት አዝማሚያ መነሻ ነው ቢባል ያስኬዳል፡፡ ከዚህ ሂደት በኋላ ብርሃነመስቀል ከነሐሴ ወር 1967 ዓ.ም. ቀደም ሲል በተካሄደው የኢሕአፓ እወጃ ኮንፈረንስ ላይ ይሳተፍ እንጂ የጸሐፊነቱን ቦታ ሁሉ ክብር ሳይሰጠው ጉባኤውን ሊከፍት አለመቻሉ የሚያሳድርበትን የሞራል ድቀት መረዳት አያዳግትም፡፡ ይህንንም ሲገልጽው

“ . . . መለስተኛ ጉባኤ ሲካሄድ ለሚቀርቡት ሪፖርቶች ስንነጋገር በየትኛውም ሌላ ማርክሲስት ሌኒንስት ፓርቲ ትራዲሽን የሌለ ፕሮሲጀር አቀረቡ፡፡ ይኸውም በሕጋዊ መንገድ ከኃላፊነቱ ያልተነሳ ዋና ጸሐፊ እያለ ሌላ ተራ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ጉባኤውን እንዲከፍት የሚል ነበር፣ በኔ በኩል ያኔ በእኔ ላይ ፐርሰናል ቅሬታ ስላላቸው እንጂ ከማዕከላዊ ኮሚቴ በስተጀርባ የተቋቋመው ክሊክ በመመስረቻ ጉባኤ የተመረጡትን የፓርቲው መሪዎች ዘዴኛና ድብቅ በሆነ መንገድ ለማውረድ ማቀዳቸውን አልገመትኩም ነበር፡፡ . . .” እያለ የሚነበበው የብርሃነመስቀል የቃል ምርመራ ገጽ 12 መጨረሻና ገጽ 13 መጀመሪያ እንዲህ ይለናል

“ . . . ከዚህ በኋላ ማዕከላዊ ኮሚቴው አዲስ ፖሊት ቢሮ ይምረጥ ተባለና ቀደም ብሎ ይተበተብ የነበረው በመመሥረቻው ጉባኤ ላይ የተመረጡትን መሪዎች የመለወጥ ሴራ ይፋ ወጥቶ ህጋዊ መልክ ያዘ፡፡ በዚሁ ምርጫ መሠረት የሚከተሉት ሰዎች ለፖሊት ቢሮ አባልነት ተመረጡ፡፡ 1ኛ ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ 2ኛ ክፍሉ ታደሰ /የኢሠማው/ 3ኛ ዘሩ ኪሸን 4ኛ ጌታቸው ማሩ 5ኛ አበራ ዋቅጅራ ነበሩ፡፡ . . .” በማለት ከገለጸ በኋላ አበራ ዋቅጅራ በተደረገው ምርጫ ባለመደሰቱ በህመም ምክንያት እኔ እንድተካው ቢጠይቅም በፖሊት ቢሮው መግባት እንደሌለበትና ገና ኢሕአፓ ሳይታወጅ የነበረውን ልዩነት እንዲህ ያስቀምጠዋል።

“. . . በእኔ በኩል ከተቀሩት አራት ሰዎች ጋር የፖለቲካ አስተሳሰብና የርዕዮተዓለም ልዩነት /በተለይም በኮሚንስት ፓርቲ ስነምግባር ረገድ/ ስለአለኝ የፖሊት ቢሮ ሥራ በየጊዜው በሚነሳ ክርክርና ጭቅጭቅ እንዳይደናቀፍ መግባት የለብኝም፣ . . .” ሥርዝ የተጨመረበት፡፡

ይህ የብርሃነመስቀል ቃል ምርመራ የሚነግረን ብርሃነመስቀል ከአመራሩ አካል ወሳኝ ሰዎች ጋር ቅራኔ/አለመግባባት የገባው ከነሐሴ 26 ቀን 1967 ዓ.ም. በፊት መሆኑን ነው፡፡ ይህ አለመግባባትም ከላይ በስርዝ እንደተቀመጠው የፖለቲካ ልዩነት ነበር ይለናል፡፡ በመሆኑም ብርሃነመስቀል በ1968 ዓ.ም. የኢሕአፓ ጣፋጭ የትግል ዓመት በምን ሁኔታ አሳለፈ? የሚለው ለቀጣይ አለመግባባቶች መሠረት ነበሩ ቢባል ያስኬዳል፡፡ የደርግ የግንባር ጥሪ የመጣው ከ7 ወር በኋላ ሚያዝያ 12 ቀን 1968 ዓ.ም. ሲሆን፣ የመንግሥቱ ኃ/ማርያም ግድያ ጉዳይ በዓመቱ መስከረም 13 ቀን 1969 ዓ.ም. ሲሆን በዚህ እረገድ ብርሃነመስቀል ካስመዘገበው ልዩነት በፊት ጉዞው ሁሉ የተነጠለ እንደነበር ያመላክታል፡፡

ብርሃነመስቀል ለ7ቱ ከኢሕአሠ ለከዱት አባላት ተጠያቂ አድርጎ ጉዳዩን እጅግ ሞራል በሚነካ መንገድ ከማክረር ለምን በሂስና ግለሂስ መፍታት አልተቻለም? የብርሃነመስቀል ኢሕአፓን በመመሥረት አኳያ ያስመዘገበው ጥረት ቀላል አይደለምና ለድርጅቱ አንድነት ሲባል እልህ ከመጋባት በምክርና በግሳጼ ቢታለፍ ምናለበት? የሚሉ ምኞቶች ይመጣሉ፡፡ እዚህ ጅምር ንትርክ ላይ ነው በአጠቃላይ የአመራሩ ድክመት፡፡ ከዚህ ሂደት በኋላ ብርሃነመስቀል የሚናገረውም የማይጥማቸው፣ ተደማጭነቱም እየቀነሰ መምጣቱ ሰብአዊ ባህሪውን እየተፈታተነ ቢመጣ ሊደንቀን አይገባም፡፡

 

ማታገያ መፈክሮች

ብርሃነመስቀል ስለ መስከረም 1968 ዓ.ም. ስለተጠራው የሠራተኛው የሥራ ማቆም አድማ፣ ስለ ሚጠየቁት ጥያቄዎች፣ ደርግ መስከረም 1968 ዓ.ም. ስለ አወጀው “አስቸኳይ ጊዜ አዋጅና” አስከትሎም በተለይ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች ላይ ስለአደረገው እሥርና ፍጅት የሰጠው ቃል (ገጽ 15 እና 16 ዝርዝሩን ተመልከቱ) በእውነቱ አምኖበት ነው ወይስ ሰው ነውና ደርግ ይምረኛል በሚል ተስፋ እራሱን ለማዳን? ያሰኛል፡፡

የቀረቡት የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት እና የዴሞክራሲያ መብት መፈክሮች በደርግ ተሳኩ አልተሳኩ ማታገያነታቸውን እንዴት ሊቀበላቸው አልቻለም፡፡ እንደውም ኢሕአፓን ከህዝብ ያስተቃቀፉት እነኚህ ሁለት መሠረታዊ መፈክሮች ናቸው፡፡ እንኳን ያኔ ዛሬም ምላሽ ያላገኙ አታጋይነታቸው ህያው ነው፡፡

“. . . እኔ እንኳንስ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት እስኪቋቋም የሥራ ማቆም አድማውን ቀጥሉ ልንል የሠራተኛው ማህበራት መሪዎች ዴሞክራሲያ መብቶች ካልታወጁ የሥራ ማቆም አድማ እናደርጋለን ማለታቸው ስህተት ነው የሚል ነበር። . . .”

እነኚህን አታጋይ መፈክሮች ለሕዝብና ለሠራተኛው ማስተዋወቂያ አንዱ የሰላማዊ ትግል ዘዴ የሥራ ማቆም አድማ መሆኑን መቃኘት የሚከብድ አይደለም፡፡ ደርግ ጥያቄውን ይመልሳል ብሎ ተስፋ ለማድረግ ሳይሆን፤ ትግሉ እንዲጎመራ ዘልቆ ህብረተሰቡ ዘንድ እንዲሰርጽ ሰላማዊ የማታገያ ዘዴ በመጠቀም ተግባራዊ ሲደረግ ባህሪው ነውና ደርግ ያሥራል፣ ይደበድባል፣ ይገድላል፡፡ ታጋይ እስርና ሞት ከፈራ ትግል መጀመርም የለበትም፡፡ እሥርና ግድያ ተፈርቶ ሠላማዊ ሰልፍ ካልተደረገ፣ የሥራ ማቆም አድማ ካልተጠራ፣ መፈክሮችና በራሪዎች በየግድግዳው ካልተለጠፉ፣ በሕዝባዊ መድረኮች ላይ ቅስቀሳ ካልተደረገ ትግል ምኑን ትግል ሆነ!

በኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም. እጁን በደም ያጨማለቀው ደርግ ሙሉውን ዓመት “በፍየል ወጠጤ” ሲያስካካ መክረሙ በቀጣይ ዓመትም 1968 ዓ.ም. ገና በመጀመሪያው ወር በአየር መንገድ ሠራተኞችና በሠራተኛው ማህበራት ላይ ያደረገው እሥርና ግድያ እየቀጠለ ሙሉው 1968 ዓ.ም. ኢሕአፓ አንድም መሳሪያ ሳያነሳ አልነበረምን ልጆቹንና አባላቱን ሲገብር የኖረው?

ብርሃነመስቀል ቀጠል አድርጎ ስለ ደርግ ተራማጅነት እንዲህ ሲል ቃሉን ይሰጣል (ገጽ 16)

“. . . በዚሁ ወቅት በአየር መንገድ ሠራተኞች ላይ በጸጥታ ኃይሎች የተከፈተው ተኩስና ከዚያም ተከታትሎ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንግሥት በልዩ ልዩ ምክንያት በተለይም በተጋነነ መረጃ ተሣሥቶ ያወጣው ቢመስለኝም ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ፀረ ዲሞክራሲያዊ እንዳውም ፋሽስታዊ ዝንባሌ ባላቸው ኃይሎች ተፅዕኖ ስር የወደቀ መስሎኝ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ እኔም እንደተቀሩት የፓርቲ መሪዎችና የፓርቲ አባላት በመንግስቱ ተራማጅነት ተስፋ ማጣት አድሮብኝ እንደነበር ልሸሽግ አልችልም፡፡ ስለሆነም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በነበረበት ወቅት ይታየኝ የነበረው ዋናው አብዮታዊ የትግል ዘዴ የትጥቅ ትግል ነበር፡፡ ደግነቱ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት በኋላ የወሰደው ተራማጅ ርምጃ ይህ ስሜት ተጨባጭ የፖሊሲ ርምጃዎችን ከማቅረቤ በፊት ሊያስለውጡኝ ችሏል፡፡ . . .” ይለናል የኢሕአፓው መስራች ብርሃነመስቀል ረዳ፡፡

ይህንን ቃል ብርሃነመስቀል የሰጠው በሰኔ ወር 1971 ዓ.ም. ሲሆን እሱ በሸሸበት መርሀቤተ ጨምሮ በመላው ሀገሪቷ ደርግ ያደረሰውን እልቂትና ሰቆቃ ሰምቷል፣ ተመልክቷል፡፡ በዚህ ወቅት ደርግ ኢሕአፓን ብቻ ሳይሆን አጠገቡ የከበቡትንም መኢሶን፣ ወዝ ሊግ፣ ኢጭአት ሳይቀሩ የበላና አንድ አምባገነን ፈላጭ ቆራጭ ፋሽስታዊ አገዛዝ ይበልጥ የተንሰራፋበት ወቅት መሆኑን እያወቀ ምን ያህል ነፍሱን ለማዳን ደርግን መሸንገሉ እጅጉን አሳዛኝ ነበር፡፡ ክብርና ስሙን እንደያዘ ቢሰዋ ምናለ ያሰኛል፡፡

እውን የደርግ ተራማጅነት እና አብዮት ደርግ ከህግ በላይ ገዝፎ በአንድ ምሽት ህዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም. 54 የቀድሞ የዓጼ ኃ/ሥላሴን ባለሥልጣናት፣ ከደርጉ ሊቀመንበር ጄነራል አማን አንዶምና ሌሎች አምስት ተራማጅ ወገኖች ጋር ደባልቆ የረሸነ ዕለት ይበልጥ አክትሞለታል፡፡ ደርግ ማንነቱን ያሳየበት ዕለት ነበር፡፡ መንግሥቱ ኃ/ማርያም በዋዜማው የሰጠው የጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅት ምን ያህል በደርጉ ውስጥ ወሳኝ ምዕራፍን በበላይነት እንደያዘ አመላካች ነበር፡፡ “ . . . እነዚህ እርምጃዎች ከዚያ በፊት ያልነበረኝን ያህል በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ተራማጅነት ከፍተኛ ተስፋ አደረብኝ፡፡ . . .” (ገጽ 17) የሚለን ብርሃነ የእስረኞች መፈታትን እነደ አብነት ከሚጠቅሳቸው ውስጥ ናቸው፡፡ ደርግ ገና ከሥልጣን ጅምሩ ማሠር፣ መፍታት ዋናው ተግባሩ ነው፤ የቀረው ቢኖር “የእሥርና ግድያ ሚንስትር” አለማቋቋሙ ብቻ ነው፡፡ እድሜ ለመኢሶን ባንዳ ምሁሮች ደርግ የኢሕአፓን ሕዝባዊ ቅላጼ በግልባጩ በመለፈፍ ለፕሮፓጋንዳ የሚጠቀም ብሄረተኛ አይደለምን? ስለ ባንዲራና ሀገር እየለፈፈ አይደል እንዴ ትውልድ የቀበረው? እርጉዝ አስገድሎ ንጹሀን ሠራተኞችን በአደባባይ አስረሽኖ የሕዝብ ቁጣ ሲያይልና ለአጎት ልጁ ሲል ግርማ ከበደን ቢረሽን “ደርግ ተራማጅ ሆነ” ልንል አግባብነት አለውን? ይህ ነው እንግዲህ አምባሳደር ታደለች መመልከት የሚገባቸው፡፡ በወጣትነት እድሜያቸው በአፍላ ትግሉ ወቅት ሲዊዘርላንድ ከዚያም መርሀቤተ ቢሆኑም የሀገራችን እልቂትና የደርግ ፍጅት በንጹሀን አርሶ አደሮች ላይ ሳይቀር ክምር እህልና ቤታቸውን ማጋየት እንደነበር በገጽ 330 ሲገልጹት እንዲህ ብለውናል

“እጅግ አሳዛኝ የነበረው ጉዳይ በጎተራ የተሞላ እህል፤ ሲያሻቸው በእሳት አለዚያም ቁልቁል በገደሉ በማፍሰስ፣ ከብቶችን በማረድና በመግደል ካልሆነም በመንዳት፣ ህዝቡ እንዲማረር መደረጉ ነው፡፡

“ከአንድ ከባድ አሰሳ በኋላ ደህና የተደራጀ የገበሬ ቤት እየመረጡ ገብተው ያለውን በማደፋፋት ጎጆዎችን ያቃጥላሉ፡፡ የዚህ የጭካኔ ዓላማ “ገበሬው በንብረቱና በጎታው ከመጡበት የተሸሸጉትን አማፂዎች አሳልፎ ይሰጣል” በሚል ሥሌት እንደሆነ ይታሰባል፡፡ ይህን ተግባር የሚፈጽሙት ግለሰቦች ግን ከዚያም ያለፈ አረመኔያዊ ባህርያቸውን፣ የሰውን ስቃይ በማየት የመርካት ጥማቸውን የሚወጡ ለመሆናቸው በአይኔ ያየሁት ድርጊት ምስክር ነው፡፡”

በሚል የትላንቷ ወጣት ታደለች ስታስነብበን ደርግ ሰጥ ለጥ አድርጎ ለመግዛት ፍጅት ዋናው መመሪያው እንደነበር ያሳየናል::

የግንባር ጥሪ

ሚያዝያ 12 ቀን 1968 ዓ.ም. በደርግ ስለታወጀው የብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራምና በመንግሥቱ ኃ/ማርያም የተደረገው የግንባር ማቋቃም ጥሪ ግንባሩ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ በኢሕአፓ በኩል እንዲሟሉ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ብርሀሃመስቀል ሲወነጅል

“ . . . ክሊኩ ስምምነት ላይ የተደረሰበትን ውሳኔ ትርጉም ለማሳሳት ሥራዬ ብሎ መንግሥት ሊቀበላቸው የማይችላቸው ጥያቄዎችን መደርደር ጀመረ፡፡ . . .” ይለናል፡፡

መቼም ኢሕአፓ በወቅቱ በእያንዳንዱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ ጨምሮ በተከሰቱ ሁኔታዎች በዴሞክራሲያ ዕትሙ ያልዳሰሰው ጉዳይ አልነበረም፡፡ እነኚህ የዴሞክራሲያ ዕትሞች “የክሊኩ” ናቸው ካልተባሉ በቀር ዛሬም አሉ፡፡ “የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ በሕብረት ግንባር ላይ ያለው አቋም” ዴሞክራሲያ ልዩ ዕትም ቁጥር 3

ግንቦት ወር 1968 ዓ.ም. (ሙሉውን ለማንበብ http://yatewlid.com/images/PDF/Democracia/Demo_01/Demo_Vol_1_LeyuEtim_No_03_Hibret.pdf) ይጠቁሙ፡፡ ባወጣው ዕትሙ

“. . . ወታደራዊው መንግሥት ሚያዝያ 12 ቀን 1968 ለአብዮታዊ ግንባር መቋቋም ያቀረበውን ጥሪ በመሠረተ ሀሳቡ የምንቀበለው ለዚህ ነው፡፡ . . .” በሚል አቋሙን በመግለጽ ካስቀመጠ በኋላ ስለ ግንባሩ ከመንግሥት ጋር ውይይት ለመጀመር በቅድሚያ በግዴታ መሟላት አለባቸው በሚል የተዘረዘሩት ነጥቦች እንደሚከተለው አስቀምጧል፦

ሀ. ዴሞክራሲያዊ መብቶች የጸረ ፊውዳል፣ የጸረ ኢምፔሪያሊስት፣ የጸረ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊስት አብዮት ደጋፊ ለሆኑት መደቦች /ላብ አደር፣ አርሶ አደር፣ ንዑስ ከበርቴ/ እነዚህን ለሚወክሉ ቡድኖችና እንቅስቃሴዎች ሁሉ ያለገደብ እንዲታወጅ:: አብሮም ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለመገደብ ተብለው የወጡት ግፈኛ ደንቦች ሕጎችና አዋጆች ሁሉ እንዲሻሩ፡፡

ለ. በኤርትራ ላይ የሚካሄደው ማናቸውም የክተት ዝግጅት በፍጥነት እንዲቆምና እንዲሻር፣ ቤሌሎች ጭቁን ብሔሮች ላይ የሚደረገው ዘመቻ እንዲቆም፡፡

ሐ. የወታደራዊው መንግሥት በሰፊው ሕዝብ ላይ የሚያካሂዳቸው ጭፍጨፋዎች ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመሩና ይፋነታቸው እየተባባሰ እንደሄደ ሰሞኑን በኪነት ሠራተኞችና በሜይ ዴይ ተሠላፊዎች የተወሰዱት የግፍ እርምጃዎች እንኳን በቂ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ በአዋሽ ሸለቆ የእርሻ ሠራተኞች መሪዎች ላይ አስበ ተፈሪ ውስጥ የተደረገው ፍጅት ሳይበቃ አሁንም አርሶ አደሮችና ላብ አደሮች በየቦታው ይረሸናሉ፡፡ ያለፍርድ የሚገደሉት እስረኞች በተለይም ኤርትራውያን ቁጥር እጅግ ትልቅ ነው፡፡ እነዚህና እነዚህን መሰል በሠፊው ሕዝብ ላይ የሚካሄዱ የጭፍጨፋ ርምጃዎች ያለአንዳች መወላወል ባስቸኳይ እንዲቆሙ፡፡

መ. የታሠሩ አብዮታውያንና ዲሞክራሲያውያን በሙሉ በነፃ እንዲለቀቁ መንግስቱ በተራማጆች ላይ የሚያደርገው ማሳደድና መከታተል በፍጥነት እንዲቆም፣ ይህም ከላብ አደሮች ከመምህራን ከተማሪዎች ከዘማቾች ሌላ የገበሬ ማህበራት መሪዎችና አባላትን በየትኛውም የብሔር እንቅስቃሴ የታሠሩ ታጋዮችንና በታጋይነታቸው ምክንያት የታሠሩ ወታደሮችንና ፖሊሶችን የግዴታ ማጠቃለል ይኖርበታል፡፡

ሠ. መንግሥቱ በነዚህ ነጥቦች ላይ መስማማቱና በሥራም ላይ ማዋሉ በሬድዮ በጋዜጦችና በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች በይፋ እንዲገለጽ፡፡

ከመንግሥቱ ጋር ለውይይቱ ከመቅረባችን በፊት እነዚህ አምስት ነጥቦች አንዳቸውም ሳይጓደሉና ሳይጣመሙ በሙሉ ግዴታ መሟላት ይኖርባቸዋል፡፡ . . .” በማለት ነበር ዴሞክራሲያ የፓርቲውን ግልጽ አቋም ያስነበበችው፡፡

እውን ይህን “የክሊኩ” አቋም ብሎ መፈረጅ አባላቱንም ሆነ የሕዝቡን ትግል አለማገናዘብ ነው፡፡ እንደ መኢሶን ምንም ጥያቄ ሳናቀርብ ከደርግ እንተቃቀፍ ካልተባለ በቀር ይህ የወቅቱ የኢሕአፓ አቋም ልዩነት ፈጣሪ ይሆናልን? እውን ብርሃነመስቀል በዚህ የእሥር ቤት ቃለ ምርመራ እንደምንም የሚለውን ብሎ ሕይወቱን ሊያተርፍ ፈልጓል ወይም እጅጉን ፖለቲካው ተምታቶበታል ያሰኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ትንታኔ መስጠት ቢቻልም አንባብያን ለግንዛቤ የብርሃነመስቀልን ቃለ ምርመራና ከላይ የጠቀስኩትን የዴሞክራሲያ ዕትም ማንበቡ እንደሚረዳ በመጠቆም ወደ ሌላው ጉዳይ ልገስግሥ፡፡

ኢሕአፓ በዚህ የግንባር ጥሪ ዕትሙ የተቃወመውንና የማይቀበለውንም በግልጽ አስቀምጦታል፤ እንዲህ ይነበባል

“ይህን ጥሪ በመሠረተ ሀሳቡ ብንቀበለውም የወጣውን ፕሮግራም እንደ ሕብረት ግንባር ፕሮግራም አድርገን አንቀበለውም:: ከፕሮግራሙ ጋር አብሮ የወጣውን የአደራጅ ጽ/ቤት ልንቀበል አንችልም፡፡ ጽ/ቤቱ በመንግሥት ቀጥተኛ ቁጥጥር ሥር የሚገኝ ከመሆኑም ሌላ በአመራረጡ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ፣ ስለዚህም አሰራሩ አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ እቅድ የማይኖረው ይዘቱም የተለያዩትን ተራማጅ ክፍሎች በውከላ መልክ ያልያዘና ግፋ ቢል የአንድ ጠባብ ቡድንን ድምጽና ጥቅም ብቻ የሚያስተጋባ በመሆኑ መቋቋሙን አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ . . .” በሚል በሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤት አማካይነት በወቅቱ 900 ብር የወር ደሞዝ የሚያስከፍለውን (የመኢሶኑ አቶ አንዳርጋቸው አሰግድ በነገራችን ላይ ከደረጀ ኃይሌ ጋር ያደረጉት ውይይት) የመኢሶንን ዕቅድና አካሄድ አጋልጧል፡፡

 

የመንግሥቱ ኃ/ማርያም መወገድና የኢሕአፓ የመከላከል እርምጃ

“ዳኛው ማነው” ስለ ከተማው እራስን የመከላከል ሂደት እና ስለ መኢሶን እየተደጋገመ ኢሕአፓ የሚወነጀልበትን በገጽ 254 እና 255 የተዘረዘረው የብርሃነመስቀልን የቃል ምርመራ በማጠናከር ነው፡፡

ብርሃነመስቀል ስለ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ግድያ ተቃውሞውን ያሰማበትን እዚህ አልዘረዝረውም በምርመራ ቃል ዘገባው ገጽ 21 እስከ 23 ያለውን አንብቡ፡፡ ብርሃነመስቀል በዚህ ዘገባ ስለ መንግሥቱ ኃ/ማርያም አለመገደል አጥብቆ ይከራከራል፡፡ በእውነት በዚያ ዘመን የደረሰባቸውን እጅግ ዘግናኝ ግርፊያና ትልተላ ተቋቁመው እንኳን መዘላበድ አይደለም የሚያውቁትን ምስጢር እንደያዙ የተሰዉ ወጣት ወንድምና እህቶቻችን ለኢሕአፓና ለሀገር ብለው ነው፡፡ ያውም በሕይወት ኖሮ የቀይ ሽብርን ፍጅት የተመለከተ፣ ደርግና ፋሽስቱ መንግሥቱ ኃ/ማርያም እንዴት እያደረገ ተቃዋሚ ኃይሎችን ብቻ ሳይሆን ጎኑ ያሉትንም እንደረሸነ የሚያውቀው ብርሀነመስቀል እንደ ፍቅሬ ዘርጋው “በኢሕአፓ ውስጥ ልዩነት ቢኖርም ከእኔ ግን ምንም አታገኙም” ብሎ ተተልትሎ እንደተሰዋው ቆራጥነቱን ቢያሳይ እውን ዛሬ ሌላ በተጻፈ፡፡ ግና ስለ ብርሃነመስቀል ባለቤቱ ወ/ሮ ታደለች ሊመሰክሩ ከሚችሉት በላይ እራሱ ተናግሯልና ለዚህ ነው “ዳኛው ማነው?” መጽሐፍና የብርሃነመስቀል የምርመራ ቃል ዘገባ ግንኙነትና ተዛማጅነት ያላቸው የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች በመሆናቸው ትኩረት የሰጠሁት፡፡

መንግሥቱ ኃ/ማርያም ደርግ አስተባብሪ ኮሚቴ ብሎ እራሱን ማሰባሰብ ከጀመረበት ዘመን ጀምሮ ፈርጥጦ ከሄደበት እስከ ግንቦት 1983 ዓ.ም. በሀገራችንና ሕዝባችን ላይ የሠራውንና የፈጸመውን ግፍ ለመዘርዘር አንድ መጽሐፍ አይበቃውም፡፡ በትንሹ መንግሥቱ ላይ ኢሕአፓ የመግደል ሙከራ ማካሄዱ ልክ ነበር ወይስ አይደለም የሚለውን እይታዬን ብቻ አቀርባለሁ፡፡

ከየካቲቱ 1966 ዓ.ም. የአብዮት ፍንዳታ በኋላ በተሰባሰበው የወታደሩ ክፍል ውስጥ የመንግስቱ ኃ/ማርያም ስም ገኖ የወጣው ያለምክንያት አይደለም፡፡ በማንኛውም አንድ እንቅስቃሴ ውስጥ ሁልጊዜም ቁንጮ ሆነው ስማቸው የሚጠራ ግለሰቦች አሉ፡፡ በተማሪው ንቅናቄ እነ ጥላሁን ግዛው፣ ዋለልኝ መኮንን፣ በኢሕአፓ እነ ተስፋዬ ደበሳይ፣ ብርሃነመስቀል፣ በመኢሶን ኃይሌ ፊዳ የመሳሰሉት የሚጠቀሱት ከእንቅስቃሴው ጎላ ብለው ስለወጡ መሪነቱን ስለወሰዱም ጭምር ነው፡፡ እነኚህን የመሰሉ ግለሰቦችና መሪዎች ታዲያ ሁሉም አንድ ናቸው፣ ሁሉም በበጎ ጎን ብቻ ይነሳሉ ሳይሆን በጥፋታቸውም ጎልተው ይነሳሉ፡፡ የጀርመኑ አዶልፍ ሂትለር በጨካኛነቱ ክብረ ወሰን በመስበሩ እስከዛሬ ይተረክለታል፡፡ የእኛም መንግሥቱ ኃ/ማርያም በጎልማሳ እድሜው ስሙ ብቅ ብቅ ማለት ጀምሮ ይበልጥ ኃ/ሥላሴን በማውረድ ሂደቱ ላይ እዮ በልዩ ቤተ መንግሥት በመገኘት ቀጥተኛ ተሳታፊ ከመሆን ጀምሮ በተለይ በኅዳር ወር 1967 ዓ.ም. የ60ዎቹ ጅምላ ፍጅት እጅጉን ስሙ ጎላ፡፡ በላቸው ነበር የተባለለት፡፡ ከዚያ ወቅት ጀምሮ በደርጉ ውስጥ የሚካሄደውን ሂደት ኢሕአፓ እንደ ፓርቲነቱ ይከታተላል፡፡ ከደርጉ ውስጥ ደጋፊ ብቻ ሳይሆን ንቁ ተሳትፎ ያላቸው አባላት እንዳሉት ይታወቃል፡፡ የደርግ ስብስብ ውስጥ ቀና ሀሳቢዎችና የመጡበትን ተልዕኮ አጠናቀው ወደ መንግሥትነት ከመቀየር ይልቅ ወደ ጦር ሠፈራቸው መመለስ እንደሚገባቸው የሚጥሩ፣ የሚመክሩ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሂደት በአንድ ስብስብ ውስጥ ወደ አምባገነንነት የሚያመራ አንድ ግለሰብ ብቅ ሲል ተስተውሏል፡፡ በስተመጨረሻም የመጣው ሁሉንም ተራማጅ ኃይሎች ደምስሦና ረሽኖ “ከአንድ ፈላጭ ቆራጭ አመራር ጋር ወደፊት!” ያሰኘ አምባገነን ብቻ ሳይሆን ፋሽስት መሪ ነበር ሀገሪቱ የገጠማት፡፡ ይህ እንዳይመጣ ነበር አርቆ አሳቢው ኢሕአፓ አስቀድሞ ያስገነዘበው፡፡

ይህ ሳይገጥም በፊት ሂደቱን ለመግታትና ሌሎቹ የደርግ አባላት የኃይል ሚዛን እያዩ ወደ ነፈሰበት የሚያዘነብሉ ምን እንደሚሠሩ እንኳን የማያውቁ፣ ግልጽ አቋም እንዳልነበራቸው ይታወቃል፡፡ ቢሆንም በወቅቱ የመንግሥቱ ኃ/ማርያም ተከታዮችም አልነበሩም ማለት አይደለም፡፡ ኢሕአፓም በ1967 ዓ.ም. እና በተለይ ደግሞ በ1968 ዓ.ም. የትግል ጉዞው በአደረገው ሙሉ ሰላማዊ ትግል እጅጉን የሠመረለትና የተዋጣለት ነበር፡፡ ኢሕአፓን ከፍ ካደረጉት ዋና ጉዳዮች አንዱ እራሱን ለሕዝብ ይፋ ከማውጣቱ በፊት የተዘጋጀበት፣ የተገነባበት የትግል መሠረቱ ነው፡፡ ዝም ብሎ ዘሎና ተሰብስቦ ፓርቲ ነኝ ያለ ድርጅት አይደለም፡፡ ይህ ጠንካራ መሠረቱ ነው እራሱን ይፋ ባወጣ በአንድ ዓመት ውስጥ በመላ ሀገሪቷ መዋቅሩን አስፋፍቶ፣ ትግሉን በበላይነት የመራው፡፡ በዚህ ሂደት ገና ከጅምሩ “ለደርግ ሂሳዊ ድጋፍ” ያለው መኢሶን በድርጊቱ እንኳንስ ከወጣቱ፣ በፖለቲካው ጥልቅ ዕውቀት ባይኖራቸውም እንኳ በእናት አባቶች የተጠላው፡፡ መኢሶን በአጭር ጊዜ በአጣው ሕዝባዊ ድጋፍ (Mass Base) ምክንያት “ለደርግ ሂሳዊ ድጋፍ” የሚለውን “ትንታኔውን” ደርግን ተገን በማድረግ ኢሕአፓን ማዳከም፣ ማጥቃት እየለወጠው መጣ፡፡ ለዚህ ሂደቱም ዋና መሣሪያ ሆኖ ያገኘው መንግሥቱ ኃ/ማርያምን ነበርና የጥፋት እርሾውን ጠነሰሰ፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ ደርግ ሥልጣኑን ከያዘበት 1967 ዓ.ም. ጀምሮ የነበረውን የገዳይነት ስሜት ይበልጥ በመረዳት በመኢሶን ገፋፊነት በ1968 ዓ.ም. ይበልጥ የሚያደርጋቸው እሥር፣ ማሰቃየት፣ ግድያ ከሕዝቡ የዕለት ተዕለት ህይወት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነበር፡፡ ተያዙ፣ ተደመሰሱ፣ ይወድማሉ፣ እርምጃ ተወሰደባቸው በእነዚህ ዓመታት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የየዕለት ዕትም ላይ ያልወጣበት ወቅት አልነበረም፡፡ የዚህ የደርግ ወደ ጨካኝነት አካሄድ እና የመኢሶን ደባ ለኢሕአፓ አመራር የቅርብ እውቅናና ክትትል የነበረው ለመሆኑ የወቅቱን ዴሞክራሲያ ዕትሞች ማንበብ በቂ ነው፡፡

ከዚህ በላይ ምን ልትጽፍ ፈለግህ አትበሉኝና ከላይ እጅግ በአጭሩ ያስቀመጥኩላችሁን ትንታኔ ከደርጉ ውስጥ አደገኛ አካሄድን እየገፋፋና እየመራ የተጓዘው መንግሥቱ ኃ/ማርያም ነበር፡፡ በሠላማዊ መንገድ የፖለቲካ የበላይነቱን እየተቆጣጠረ የገሰገሠው ኢሕአፓ ላይ ደርግ ኅሙስ መስከረም 6 ቀን 1969 ዓ.ም. “ፀረ ሕዝብ ሁሉ በጭቁኑ ጫማ ሥር እንደድመት ያለቅሳል” በሚል በሠጠው መግለጫ ኢሕአፓን በጠላትነት በመፈረጅ የማጥፋት ጦርነት አወጀበት፡፡ ኢሕአፓም ለዚህ የማጥቃት እወጃ ለመከላከል ተዘጋጀ፡፡ በመሆኑም በደርግ ውስጥ ብቅ እያለ የመጣው የመንግሥቱ ኃ/ማርያም አምባገነናዊ ሂደት በአጭር መቀጨት እንዳለበት በፓርቲው ሲወስን የመንግሥቱ ኃ/ማርያም መወገድ ያለ ጥርጥር የወቅቱን የፖለቲካ አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ ይቀይረው ነበር፡፡ በወቅቱ በመዋለል ላይ ያሉት የደርግ አባላት በአብዛኛው ወደ ቀና አስተሳሰብና ዴሞክራሲያዊ ጎዳና መሳብ አስቸጋሪ አልነበሩም፡፡ የመኢሶንና ወዝ ሊግ መሪዎች በማግሥቱ ሻንጣቸውን ሸክፈው ከሀገር ይወጡ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ ሊቀየር ይችል ነበር፡፡ ሆኖም ግን አልተሳካም፣ አልሆነም፡፡ ከዚህ በኋላ ነው የኢሕአፓ ስህተት ሊጠቆም የሚችለው፡፡ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ከአደጋው ስለተረፈ “ብለን ነበር” ማለት የፖለቲካ ትርፍ/የበላይነት አያስገኝም፡፡ ኢሕአፓ ሲጀመር ይህንን እርምጃ ሲወሰድ ሁልጊዜ ሊገጥሙ የሚችሉ ጉዳዮች አሉና በቂ ዝግጅት ተደርጎበታል ወይ? ባይሳካስ ቀጣይ ፕላን ምንድነው? የሚለውን ማየት ተስኖት ነበር፡፡

ከመስከረም 13ቱ የመንግሥቱ ኃ/ማርያም ግድያ ሙክራ መክሸፍ በኋላ ኢሕአፓ ለሌላ እርምጃ ከመጓዙ በፊት የዚህ እርምጃ መክሸፍ በራሱ የሚያመጣውንና በመንግሥት በኩል ሊወሰድ የሚችለውን እርምጃ የትግል ሥራውን እየሠራ መከታተል ነበረበት፡፡ በወቅቱ መስከረም 21 ቀን 1969 ዓ.ም. የተደረገው የመኢሶን አመራር አባል ፍቅሬ መርድ ግድያ ለምን አስፈለገ? የሚለው ዛሬም ያቃጭልብኛል፡፡ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ላይ የተሞከረው ግድያ ሳቢያ የደርግና የግል እርምጃቸው ምን ሊሆን እየተገመተ ወዲያውኑ ከመኢሶን አመራር መግደል የመንግሥቱ ኃ/ማርያምንና የመኢሶንን ግንኙነት እጅጉን ከማጠናከሩም በላይ መኢሶን ኢሕአፓ ላይ ይበልጥ በትሩን ለማሳረፍ አጋዥ ኃይል ያገኝ ዘንድ አመቻችቶለታል፡፡

በእኔ አመለካከት ዛሬ ኢሕአፓ ለድል ስላልበቃና ስለተመታ የምቃወመው ሳይሆን ኢሕአፓ ከትግል ጉዞው አንጻር በመርህ ደረጃ የተጀመረው የከተማው እራስን ከጥቃት መከላከል እርምጃ አግባብ ነበር እላለሁ፡፡ ስህተቱ ፓርቲው ለዚህ ሲዘጋጅና ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት መመለስ የነበረባቸው ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ እነኚህን ጥያቄዎች ዛሬ ላይ ሆኜ ሳያቸው የከተማው ፓርቲውን የመከላከል ሂደት በቂ ዝግጅት ሳይደረግበት መጀመሩ አግባብ እንዳልነበር መናገር ይቻላል፡፡ ለምሳሌ፦ በቂ የመሣሪያ፣ የትጥቅ አቅርቦት ነበር ወይ? መጠነኛም ቢሆን በወታደራዊ መስክ የሠለጠኑና ልምምድ ያደረጉ እስኳዶች ነበሩ ወይ? በ1967 እና 1968 የትግል ወቅት በተለያየ አጋጣሚ ለመንግሥት የተጋለጡ አባላቱን ወደ ገጠር የማሸሽ ዕቅድ ነበር ወይ? በከተማው እጅግ ባስቸገሩ ግለሰቦች ላይ በሚወሰደው እርምጃ መንግሥት ለሚወስደው አጸፋ የሚጋለጡና አካባቢ መልቀቅ ላለባቸው አባላቱ አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ግብረኃይል ነበር ወይ? እርምጃ የሚወሰድባቸው በሚገባ ጥናት ተደርጎ በኮሚቴና በሚመለከተው አካል የሚወሰን ነበር ወይ? እና መሰል ጥያቄዎችን ስንቃኝ ያለምንም ምስክር ደካማ ጎኖቹ ያመዝናሉ፡፡ ለዚህ ነው እየከፋ ለመጣው የደርግ አጸፋዊ ምላሽ መሸሽ እንኳ ሳይቻል እምሽክ ያልነው፡፡ ስህተቱ በየከተማው እራስን ከጥቃት መከላከል መጀመሩ ሳይሆን ለመጀመር የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው ነበር ወይ? የሚለው ነው ሊታይና ሊተችበት የሚገባው ባይ ነኝ፡፡

ብርሃነመስቀል መረዳት የነበረበት በኢሕአፓ የታቀፉ አባላት፣ ደጋፊዎች በጥቅሉ ፀረ-ደርግ ትግሉ የጥቂት አመራሮች ወይም እሱ እንደሚለው “የክሊኩ” አልነበረም፡፡ በዚህ የግል ዝና እጦት ወይም ብርሃነ እንኳ እራሱ ትክክል መሆኑን ቢገምትም ከኢሕአፓ የሚያገኘውን መረጃ ለማክሸፍና ተግባራዊ እንዳይሆን በሚያደርገው ሂደት እየጎዳና አሳልፎ እየሰጠ የነበረው በዚያ ጊዜ በአሥራዎቹና በ20ዎቹ ውስጥ ያለነውን በርካታ ወጣቶችን እንኳ አላሰበንም፡፡ በብርሃነመስቀል የተሰባሰበው ቡድን ለደርግ የኢሕአፓን መዋቅርና ምስጢር አሳልፎ በመስጠት ምን ያህል የሕዝብ ልጆችና ድርጅቱንም እንደጎዱ መሠመር ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም ድርጊቱ ኢሕአፓን በማዳከሙ የሱም አሻራ ቀላል እንዳልነበር ከምርመራ ቃሉ ገጽ

 • ላስነብባችሁ

“ . . . ጥር 17 ቀን 1969 ከፓርቲው ኮሚቴዎች ከተገለልን በኋላ/በማዕከላዊ ኮሚቴው ውሳኔ መሠረት/ በእኔ በኩል ክሊኩ ከአስቀመጠኝ ቦታ ማለትም ከሰባ ደረጃ አካባቢ በመሰወር ግንኙነት አቋረጥሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ዋናው ተግባሬ የእርማት ንቅናቄውን ማስፋፋት ሲሆን ከጥር 18 ቀን 1969 ዓ/ም ጀምሮ ክሊኩ ሊወስዳቸው ያቀዳቸውን ፋሽስታዊ የግድያና የኃይል እርምጃዎች መቃወምና በተግባርም ማክሸፍ ነበር፡፡ . . .” (ሥርዝ የተጨመረበት) እያለን የድርጅቱን ምስጢርና ሥራዎችም የሚያገኘውን ሲገልጽ

“. . . መመሪያውም የደረሰኝ ከእርማት ንቅናቄው መስራቾች አንዱ ከነበረው በክሪ የአ/አበባ ዞን 1 /መርካቶ አካባቢ/ ፀሐፊ ስለነበር በእሱ አማካኝነት ነበር፡፡ . . .” ይህ አሳዛኝ መረጃ ብርሃነመስቀል በእልህ ስንቱን አባላት እንደጎዳና ድርጅቱን በተቻለው አቅም ለደርግ አሳልፎ እንደሰጠ ጠቋሚ አይሆንምን?

እዚህ ላይ ነው ብርሃነመስቀልና ጌታቸው ማሩ ቅድሚያ ተግባራቸው ፓርቲውን በሚያውቁት የመዋቅር ሰንሰለት እየበጠሱ፣ የሚተላለፉ መረጃዎችን እያፈኑ፣ ከመዋቅር ውጭ የሚያውቋቸውን እየተገናኙ የሚችሉትን ያህል ማዳከሙን እንደገፉበት ኢሕአፓም ያውቀዋል የቃል ምርመራውም ይነግረናል፡፡ ታዲያ ይህ የአንጃነት ተግባር አይደለምን?

 

ስለ እርማት ንቅናቄው

አምባሳደር ስለ እርማት ንቅናቄው በሰፊው ዘግበዋል፡፡ ይህንን ክፍል ብርሃነመስቀል በቃል ምርመራው ላይ በደንብ አልዘረዘረውም ምናልባት እንደገና ኢሕአፓን ልታደራጅ ነው በሚል ክሱ እንዳይጠነክርበት ወይም ከስም ያልዘለለ እንቅስቃሴ በመሆኑ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ክፍል ሳነበው እራሴን 1969 አጋማሽ ነፃ እርምጃ፣ ከዚያም 1970 ዓ.ም. ቀይ ሽብር ቀጥሎም ከሞት የተረፉት የእሥር ቤት ኑሮ የተፈታነው ደግሞ ሕይወት እንደገና የቁም እሥር ስቃይ ላይ እራሴን አስቀምጬ ነው፡፡

ስለ ቀይ ሽብር አምባሳደርም ሆኑ ሌሎች አንባቢያን እጅግ በርካታ የተጻፉ እውነተኛ መጽሐፍትን ማንበቡ በመጠኑም ቢሆን ግንዛቤ እንደሚሰጥ እየጠቆምሁ በካዛንችስ አካባቢ የነበረውን የቀይ ሽብር ሁኔታ የራሴን እውነተኛ ታሪክ መጽሐፍ “ፍጹም ነው እምነቴ የከፍተኛ 15 ቀይ ሽብር እውነተኛ ታሪክ” መስከረም 2007 ዓ.ም. ትመለከቱት ዘንድ እጠቁማለሁ፡፡ ቃላት ካልተገኘለት የደርግ አስከፊ ግርፍና ግድያ የተነሳ መላ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያስደነገጠና እግዚዮ ያሰኘ ዘመን ነበር፡፡ ሁሉም ወጣት ራሱን የሚያድንበት መንገድ ፈላጊ ሲሆን፤ ወላጆች የተሰቃዩበት፣ ሕጻናት የፈዘዙበት፣ ቤተሰብ በጥቅሉ የሀዘን ማቅ የለበሰበት ዘመን ነበር፡፡ ይህ ወቅት ኢሕአፓ፣ አንጃ እየተነጠለ ሳይሆን ወጣቶች በጅምላ እየታደኑ የሚገደሉበት፣ የሚሰቃዩበት ዘመን ነበር፡፡ ከደርግ እሥር ለጊዜው አምልጠው ወደ ዘመዱና ወደ ክፍለ ሀገር የሄዱት እንኳን በሄዱበት ሁሉ ተመሳሳይ ሂደት በመኖሩ ተመልሰው እየመጡ “ለሞት” እጃቸውን የሰጡበት ወቅት ነበር፤ እንኳን ሌላ ሊታሰብ፡፡ በዚህ አስከፊ ሁኔታ የኢሕአፓ መዋቅር እየተበጣጠሰ ድርጅታዊ መረጃ በጠፋበትና መተማመን በተሸረሸረበት ወቅት “እርማት ንቅናቄ” ብሎ ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ እንደነበር ለማመን ያዳግተኛል፡፡ ከአዲስ አበባ መውጣት መግባትም ሆነ በየትኛውም ክፍለ ሀገር መዘዋወር እጅጉን አዳጋች ነበር፡፡ በጸጉረ-ልውጥነታቸው ብቻ እየተጠረጠሩ የተያዙ የተገደሉ ቀላል አልነበሩም:: ሽሽቱና ከሀገር መውጣቱ ተሳክቶላቸው የነበሩ ዕድለኞች ናቸው ከማለት ሌላ የሚኖር አይመስለኝም፡፡

“ታጥቆ አደራጅና አንቂ ቡድን (ታአአቡ)” እራሱ ስሙን ሳየው መኢሶን ነው ትዝ ያለኝ፡፡ “ለነቃ፣ ለተደራጀና ለታጠቀ የሕዝብ ትግል” በሚል ገና ከጅምሩ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ታጥቆ መታገል ሲገባው በረሃና ውጣ ውረዱ፣ አቀበትና ቁልቁለት እንዴት ይደፈራልና በሂሳዊ ድጋፍ ቤተመንግሥት ተቀምጦ በሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ስም ሲፒኤ የማያውቀው የመንግሥት በጀት ተመድቦለት በዚያ ጊዜ በትንሹ በወር 900 ብር ደሞዝ እየተከፈላቸው ትግል ካሉት መዶለትን መረጡ፡፡

እናም ታአአቡ በአጭር ጊዜ የተደራጀውን፣ የታጠቀውን ኢሕአፓ እና በእሱም ሥር የተሰባሰቡትን ንቁ አባላቱንና ሕዝባዊ ድጋፉን አራግፎ እንደገና ለነቃ፣ ለተደራጀ፣ ለታጠቀ የእርምት ንቅናቄ ሲባል እውን አዋቂነት ነው ወይስ የመረበሽና የንዴት ውጤት? ያሰኛል፡፡

ታጋይ ታደለች በዚህ ጉዳይ የሰጡን ትንታኔ ብርሃነመስቀል በወቅቱ የእርማት ንቅናቄ በሚል በድርጅት ላይ ድርጅት ምሥረታ እንደተያያዘ ነው፡፡ እዚህ ላይ ነው አንጃ የሚያሰኘው፤ ከባዱም ጥፋት፡፡ የእርማት ንቅናቄውን ለማጠናከር እነ ብርሃነመስቀል ከፓርቲው ሰው ለማሰባሰብ ውስጥ ውስጡን ቅስቀሳ ሲያካሂዱ፣ ዕቅድ ሲያወጡ፣ ፓርቲውን ሲሸረሽሩ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህንን ነበር ኢሕአፓም በወቅቱ ለአባላቱ ያሳወቀው፡፡ ለዚህም መጽሐፉ በገጽ 302 ይህንን መረጃ ያስነብበናል፡፡

“ . . . የእርማት ንቅናቄው ቅድሚያ ዝግጅት በማድረግ፣ ከከተማም ሰዎች በማሰባሰብና መሣሪያም በማምጣት አንድ ድርጅታዊ መዋቅር መስርቶ ሰዎችንም ማወያየት ተጀመረ፡፡” ሥርዝ የተጨመረበት፡፡ ገጽ 302

“ . . . የእርማት ንቅናቄውን ለመመሥረት የሥራ ክፍፍል በማድረግ ለመንቀሳቀስ የተሰየሙት ብርሃነመስቀል፣ ጌታቸው ማሩ፣ አብዩ ኤርሳሞና በክሪ ነበሩ፡፡” 299

“ . . . የእርማት ንቅናቄው ጥያቄ ሌላ ሳይሆን ፓርቲው የሚያካሂደውን ህገ ወጥ የተሳሳተ የትግል መስመር በመያዝ ጠቅላላ ጉባኤ የሚጠራበትን ለማመቻቸት ነበር፡፡ . . .” ገጽ 298

“የእርማት ንቅናቄው ቁጥራቸው 20 የሚደርሱ አባሎችን (በተለያየ ጊዜ የተቀላቀሉ) ይዞ፣ ሰፊ ውይይት በማድረግ ከአላማው ጋር የሚሄድ፣ ታጥቆ አንቂና አደራጅ ቡድን (ታአአቡ) እንዲቋቋም ተደረገ፡፡” ገጽ 303

ብርሃነመስቀል በሰኔ 1967 ዓ.ም. ከኢሕአፓ ፖሊት ቢሮ ዝቅ በማለቱና በማዕከላዊ ኮሚቴ መካተቱ የበላይነቴን ተነጠቅሁ የሚል ስሜት ቢያድርበት አይፈረድም፡፡ ግና ደርግ ተራማጅ ነው፣ ደርግ ፋሺስት አይደለም፣ ከደርግ ጋር ያለ ቅድመ ሁኔታ ግንባር መፍጠር አለብን፣ በከተማው የተጀመረው እራስን የመከላከል እርምጃ መቆም አለበት የሚሉ አመለካከቶች፣ የመስመር ልዩነቶች ከኢሕአፓ እየነጠለውና ጥያቄ ውስጥ እየከተተው መምጣቱን በራሱ የምርመራ ቃል የተቀመጠ ነው፡፡ ኢሕአፓ እሱ በሚፈልገው መንገድ እንዲሄድ ስላልቻለ በእርማት ንቅናቄ ስም ሌላ ድርጅት ለማዋቀር በሚያደርገው ሂደት ፓርቲውን ለማፈራረስና ለማዳከም ድርጅታዊ ምስጢር ወጥቷል፣ ተሰጥቷል፣ አባላት እንዲጋለጡ ተደርጓል፣ መሳሪያና ገንዘብ ተወስዷል ሌላም ሌላ፡፡ ይህ ነው አሳዛኙና ዋናው መሠረታዊ ስህተት፡፡ ኢሕአፓ በ1968 ዓ.ም. ለገነባው ሕዝባዊነት እንኳንስ ወዳጅ ጠላት የመሰከረው እና ግራ የገባው ወቅት ነበር፡፡ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አባላቱም ድርጅቱ ፍጹም አይደለምና ከመለስተኛ ድክመቶቹ ጋር ቅድሚያ ጉዟቸው፣ ትግላቸው፣ ጥንካሬያቸው ደርግን ከሕዝብ ጫንቃ ላይ ማውረድ ነበር፡፡ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ወይም “ባልበላም ጭሬ አፈሰዋለሁ” አባባል እና አካሄድ ሀገር ልታገኛቸው የማትችል ብርቅዬዎችን አሳጣ፣ ኢሕአፓንም አስመታ፡፡ እውን ከኢሕአፓ ደርግ ይመረጥ ነበርን? እውን ከኢሕአፓ መኢሶን ተወዶ ነበርን? ዛሬ ላይ ሆነን እንኳ “ምነው እነኛ ኢሕአፓዎች በተንቀሳቀሱ” የሚባልበት ምክንያት ሁሉም ጥንካሬውንና ለሀገርና ለሕዝብ ያለውን ቁርጠኛነት ስለሚረዳው ነው፡፡ ይህንን ጠንካራ ኃይል ውስጥ ሆኖ ዕቅድ በመንደፍ ሌላ መዋቅር

ለመዘርጋት መነሳሳት “ዳኛው ማነው” በሠፊው የገለጸልን ምስክርነት ፓርቲው የሚለንን ይበልጥ በማጠናከሩ በኢሕኢፓ ውስጥ ስለተፈጠረው አንጃ አካሄድ ግልጽ የሆነ መልስ አግኝቼበታለሁ፡፡

መኢሶን የቀይ ሽብርን ዕቅድ አውጥቶና ጠንስሦ ካበቃ በኋላ ከደሙ ንጹህ ነኝ ለማለት “በሁለት በኩል ተጠቃን” ይለናል፡፡ “ዳኛው ማነው” መጽሐፍም በድርጅት ላይ ድርጅት ሊመሠርት የተነሳውን የእርማት ንቅናቄ ቡድን “. . . በሁለት ኃይሎች መካከል ኢላማ ተደርገዋል፡፡ . . .” ገጽ 299 ይለናል፡፡ እንግዲህ ደርግ ፋሽስት አይደለም፣ ደርግ ገዳይ አይደለም የተባለለት አቋም ለምንሳ ከኢሕአፓ የተገነጠለውን ለማሳደድ ፈለገ?

እዚህ ላይ ግልጽ ለማድረግ እንደውም ኢሕአፓ ነው ከውስጥ በነብርሃነመስቀል፣ ከፊት ለፊት በደርግና ከባቢዎቹ በተለይ መኢሶንና ወዝ ሊግ፣ ከጀርባ በህወሓት/ወያኔ፣ በመሰሪ ሤራ በሻቢያና በባዕዳን ኃይላት ተከቦ ኢትዮጵያን የት ሊያደርስ የሚችል ትውልድ እምሽክ የተደረገው፡፡ በዐድዋ እና ማይጨው ወረራ ያላገኟትን ኢትዮጵያ በተቀነባበረ ታላቁ ሤራ ትውልዷን ቀብረው፣ አንድነቷን ሸርሽረው ዛሬ ኢትዮጵያ ትኑር አትኑር እልውናዋ አጠያያቂ እሆነበት ደረጃ ትገኝ ዘንድ ጠላቶቿ ለጊዜውም ቢሆን ተሳክቶላቸዋል፡፡

በጥቅሉ “የብርሃነመስቀል እና የታደለች ህይወት በኢሕአፓ የትግል ታሪክ” የሚያወሳው “ዳኛው ማነው” የሚለው መጽሐፍ የኢሕአፓን አንድ የታሪክ ገጽታ ስለሚዳስስ በርካታ ጉዳዮች ሊጻፉበት ይችላል፡፡ ስለ ኤርትራ ጉዳይ፣ ብርሃነመስቀል የመጀመሪያው የኢሕአሠ አስኳል በኤርትራ በረሃ በታገተበት ወቅት ወደ አውሮፓ ጉዞና በቀጣይነትም ከሻቢያ ጋር በምን ጉዳይ ቢስማሙ ነው ወደ አሲምባ ሊገቡ የቻሉት? በሌላ በኩል በመጽሐፉ ገጽ 170 እንደተቀመጠው

”ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይና ዘርዑ ክሸንን ኤርትራ ሜዳ ሄደው ፣ ከፓርቲው ፕሮግራም ውጪ ገና አቋም አልወሰድንም በሚል በፓርቲው ስም ያንን አወዛጋቢ ኮሚኔክ ፈርመዋል፡፡ ጉዳዩን ለምን እንዳደረጉ ግን በዚያን ወቅት በውል ማወቅ አልተቻለም፡፡” እንደቀልድ የሚታለፍ አባባል አይደለም፡፡ እንደ መጽሐፉ አባባል እውን ዘርዑ የተስፋዬን ደካማ ጎን ተገን አድርጎ ተጠቅሞበታል? አባባሎች ጠንከር ያለ ውይይት ቀስቃሾች፣ ብዕርና ወረቀት ፈላጊዎች ናቸው፡፡

 

አንዳንድ ነጥቦች

 • ከገጽ 246 እስከ 249 የተዘገበው የፍቅርተ ገ/ማርያም፣ አበበች በቀለና አዳነች ፍስሃዬ ከፓርቲው መዋቅር ውጭ ስለፓርቲው ጉዳይ ታደለችን ሊያናግሯት መምጣታቸውንና የተፈጠረውን ትርዕይት ሁሉም የተጠቀሱት ሴቶች በሕይወት አሉና የራሳቸውንና የሚያቁትን ቢያስነብቡን መልካም ነው እላለሁ፡፡
 • ዳኛው ማነው መጽሐፍ እውነተኛ ታሪክ እንደመሆኑና በአጠቃላይ ትረካው ስም እየተጠቀሰ ሲሆን በገጽ 242

“የሴቶች እንቅስቃሴ” በሚለው ምዕራፍ 14 “የህቡዕ እንቅስቃሴና ንትርክ” ከገጽ 242 ላይ የተካተተው ፍሬ ሀሳብ ላይ ለምን ስም መጥቀሱ እንደተዘነጋ ግልጽ አይደለም፡፡

 • ገጽ 271 ፍቅሬ መርዕድ መስከረም 16/1969 እንደተገደለ የተዘገብው መስከረም 21 ቀን 1969 ዓ.ም. መሆኑን መስከረም 23 ቀን 1969 ዓ.ም. የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዘግቦታልና ይስተካከል
 • ገጽ 243 በቢቢሲ ዜና፣ በአውሮፓ የኢሕአፓ ተወካይ በሚል የተዘገበው ስሙ ቢጠቀስ መልካም ነበር

 

መደምደሚያ

አምባሳደር ታደለች ከስዊዘርላንድ-አዲስ አበባ-መርሀቤቴ-ከርቸሌ የሕይወት ጉዞና ውጣ ውረድ ለታዋቂው ባለቤታቸው ብርሃነመስቀል ረዳ ያላቸውን ፍቅርና ስሜት አስነብበውናል፡፡ ሁላችንም ስህተትን መቀበል የከበደን ዘመን ላይ ብንሆንም እሳቸውም በብርሃነመስቀል በኩል የተሠሩ ስህተቶች እንዳሉ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ በጥቅሉ ደግሞ ኢሕአፓ ከጠንካራ ጎኖቹ አኳያ ከድክመትም እንዳልጸዳ መቀበል ይኖርብናል፡፡ በተለይ በአመራር በኩል፡፡ ኢሕአፓ ታጋይ እንጂ አመራር የለውም፡፡ ይህ ችግር ለውድቀቱ የራሱ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ ሁላችንም ፍጹም ልክ ነን ካልን ታዲያ የተሳሳተው ማነው?

ከሁሉም በላይ ይሉናል ወ/ሮ ታደለች “ከሁሉም በላይ ፓርቲው ቢሳሳት፣ እነ ተስፋዬ ሊያርሙት ምንም አይቸግራቸውም ብዬ ነው የማስበው፡፡ እነ ብርሃነ ችግሩን አይተው “ስህተት እየተፈጸመ ነው” ሲሉ፣ እነተስፋዬ በተቃራኒው ይቆማሉ የሚል እምነት አልነበረኝም፡፡ በተለይ ተስፋዬ ለብርሃነ የነበረው መልካም አስተሳሰብ እና ብርሃነ ለተስፋዬ የነበረውን አክብሮት ሳስበው፣ በምን ምክንያት ስለጉዳዩና ስለችግሮቹ መነጋገርና መፍትሄ መሻት እንዳቃታቸው ግራ ይሆንብኛል፡፡ ለምን እያልኩም አዘውትሬ ጠይቄዋለሁ፡፡” (ገጽ 269፣ 270) አባባል ሳነበው ዛሬ ላይ ሆነን ይህ ቢሆን ኑሮ የምንል በርካቶች ልንሆን እንደምችል ገመትሁ፡፡

የሆነው ሆኗል ቀላል ያልተባለ ትውልድ ኢትዮጵያችን አጥታለች፡፡ የዚያ ዘመን ውጤት ዛሬም ያስከተለው መዘዝ ቀላል አይደለም፡፡ ሁላችንም ከስህተት እራሳችንን አጽድተን ወደፊት ለመጓዝ አልቻልንም፡፡ የተሠሩ ስህተቶችን በታሪክነታቸው ተቀብለን ለሀገር ለህዝብ ሲባል በተለይ ደግሞ ለአሁኑና ለተተኪ ትውልድ ስንል መግባባትንና ብሔራዊ ዕርቅን ተግባራዊ አድርገን ብናሸልብ ይመረጣል፡፡ እንደተባላ ጀምሮ እንደተባላ ያለፈ ትውልድ አይሁን ታሪካችን፡፡ የያ ትውልድ አካላት ስለ ሀገር፣ ስለ ህዝብ ያለን አመለካከታችን፣ አካሄዳችን ተለያይቶ ለውድቀት አበቃን እንጂ ሁላችንም ኢትዮጵያችንና ሕዝባችንን እንወዳለንና ትውልድ ዕርቅን፣ ይቅር መባባልን ይቀጥልበት ዘንድ አርኣያ እንሁን፡፡

የሸንበለል፣ ውበት (ማሚኩ) እና ሐቂ እናት፣ የስድስት ታዳጊዎች አያት፣ የኢሕአፓው መሥራች ብርሃነመስቀል ረዳ ባለቤት የትላንቷ ጓዲት የዛሬዋ አምባሳደር ታደለች ኃይለሚካኤል ፦ ይህን መጽሐፍ በማስነበብዎ እንኳን ደስ አሎት፡፡ ይህ አስተያየቴ ፖለቲከኛ ስለሆኑ እንደ ኢሕአፓ ትውልድ ታሪክ ተከላካይነት እንደሚመለከቱት ተስፋ ባደርግም ለልጆችዎ ግና ይከብዳል፡፡ የእርሶ ልጆች አባታቸውን አያውቁም፣ የተስፋዬ ደበሳይ ልጅ ሐምራዊት አባቷን አታውቅም፡፡ ለአንድ ዓላማ ተነስተው ታሪካቸው የተለያየው ወንድማማቾች ለልጆቻቸው አባት ናቸውና እኩል ስሜታቸው ይጎዳል፡፡ ይህ ሆኗል ከዚህ ታሪካችን ትውልድ ይማርበት ዘንድ “በእኛ ይብቃ” ብለን ዳግም እንዳይደገም ጥሩውም ደካማውም ጎን አስተማሪነቱን እንቀበለው፡፡ “ዳኛው ማነው?” ብለው እርዕስ ለሰጡት መጽሐፍዎ ለ17 ዓመታት በሀገራችን ኢትዮጵያ እራሱ አሳሪ፣ እራሱ ከሳሽ፣ እራሱ ሕግ አውጪ፣ እራሱ ፈራጅ፣ እራሱ ገዳይ፣ እራሱ ቀባሪ ሆኖ ሀገሪቱን ያመሰቃቀለው ፋሽስትና አምባገነን መሪ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ይመራ የነበረው የደርግ ስብስብ ነበርና “ዳኛውማ ደርግ ነው” ብያለሁ፡፡

በአለኝ ግንዛቤ የተሰማኝን ከራሴ አመለካከት አንጻር ሀሳቤን ስሠነዝር ከመጽሐፎ ያገኘኋቸው ቁምነገሮችና አሁንም በጥያቄ ያሉ ያልተመለሱ ምስጢሮች ውስጤ ተመላልሰዋል፡፡ እንደቆጨኝ ይዤ ያለሁት በጥቅሉ “ያ ትውልድ” ላይ የተጠነሰሰው ቀደምት ሤራ ኢትዮጵያ ዛሬ ላለችበት አስከፊ አደጋ የራሱ አስተዋጽዖ እንዳለው ይሰማኛል፡፡ ኢሕአፓን አምነው፣ ዓላማው ዓላማቸው ሆኖ በንጹህ ፍቅርና እምነት ለምስኪኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመሬት ለአራሹ መፈክር ጀምሮ ለድሀ መማር፣ ነጻ የህክምና አገልግሎት ማግኘት፣ ለዴሞክራሲያዊ መብት እና ለሕዝብ መንግሥት ምስረታ ሕይወታቸውን የሰጡ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች ሁሌም ልናከብራቸው፣ ልናስባቸው ይገባል እላለው፡፡ ተምሮ ሥራ መያዝን አጥተውት ሳይሆን ቅድሚያ ሀገራችን፣ ሕዝባችን ብለው ነውና ድፍት ያሉት፤ አጥንታቸው ሊወጋን ይገባል፡፡ በተጨማሪ በኢሕአፓ አመራር እርከን ላይ የነበሩ አባላትና የሴቶች እህቶቻችን የነበሩበት የኑሮ ሁኔታ ሳስበው በአብዛኛው ለእራሳቸው ከበቂ በላይ የተመቻቸላቸው ነበሩ፡፡ ማንነታቸውን ለሀገርና ሕዝብ ሰጥተው እግራቸውን ለጠጠርና እሾህ፣ እምቡጥ ገላቸውን ለሀሩር ፀሐይና ለነጎድጓዳማ ዝናብ አሳልፈው ጨቋኝና በዝባዥ ሥርዓትን፣ አምባገነን አገዛዝን የተጋፈጡ እንስቶች እጅጉን ሊከበሩ ይገባል::

 

ይብቃኝ! ስለ ኢሕአፓ ሲወራ ያመኛል፣ ይነዝረኛል፣ በሚሰማኝ ኩራት ላይ ቁጭት ይወረኛል፡፡

አስከፋውም አስደሰትኩም የምለውን ብያለሁ፡፡

ቸር ይግጠመን፡፡

ነሲቡ ስብሐት ከሴሜን አሜሪካ ቨርጂንያ (703) 300 4302

[email protected]

መስከረም 24 ቀን 2013 ዓ.ም. (September 04, 2020)

መጽሐፍ አስተያየት፤ ነሲቡ ስብሐት …………………………………………ዳኛውማ “ደርግ” ነው………………….መስከረም 24 ቀን 2013 ዓ.ም.          13

4 Comments

 1. ውድ አቶ ነሲቡ
  ስላም እና ጤናዎን ተመኘሁ፡፡ በመዝጊያው ላይ ስላሰፈርዋት ትንሽ ልበል፡
  “ይብቃኝ! ስለ ኢሕአፓ ሲወራ ያመኛል፣ ይነዝረኛል፣ በሚሰማኝ ኩራት ላይ ቁጭት ይወረኛል፡፡ አስከፋውም አስደሰትኩም የምለውን ብያለሁ፡፡”
  ስሜትዎ ግልጽ ነው፡ አይፈረድብዎትም። ግን እስከመቼ? ክዚህ በኋላ ድንጋይ መወራወሩስ ምን ይጥቅማል? በጥቅሉ ክታሪክ ሽሚያ እና ከሂሳብ ማወራረድ ቢወጣ ጥሩ አይመስሎትመ? ሁሉም የሚያውቀውን ይጻፍ፡፡ ታሪክ ጸሐፊዎች ደግሞ “እውነቱ” የቱ ጋ ነው ብለው ይጨነቁበት፡፡ እርስዎም በዚህ state-of-mind መቀጠል አይደለም መቆየትዎ በራሱ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም፡፡
  በግሌ (in hindsight) ያ ዘመን ወጣቱን ክፉኛ ከበደለው ተጸዕኖ ውስጥ መሰረታዊ የሆነው “መንፈሳዊ” ህይወቱን እንዲያቋርጥ ማድረጉ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የሞራል ብቃት ብቻውን (ያለ መንፈሳዊ አስተሳሰብ) ከጥፋት እንደማያድን የገባኝ ከእትዮጵያ አብዮት ነው፡፡ ኮሚንስቶች ለምን “እግዚአብሄር የለም” እንደሚሉም የገባኝ ቆይቼ ነው፡፡ አለዚያማ ኮሚንስቶችስ በሞራል ብቃት ይታማሉ እንዴ? ስለዚህ አሁንም መፍትሄው ያለው እዛው ወደ ተቋረጠው መንፈሳዊ ህይወት መመለስ ይመስለኛል፡፡ በተለይ በዚህ እድሜ፡፡ የየትኛውም ሃይማኖት መሆን ይችላል፡፡
  ሌላው ማንኛውም ስው ቢያነበው ጥሩ ነው የምለው መጸሐፍ አለ፡፤ “Battlefield of the Mind”, by Joyce Meyer ። እርስዎ ያነበቡት አልመሰለኝም፡፡ ምከንያቱም እሱን መጸሐፍ ካነበቡ (ማለትም ካነበቡ!) በዚህ state-of-mind ሊቆዩ አይችሉም፡፡ ከተሳሳትኩ ይቅርታ፤ ታርሜአለሁ! ግን እንደገና ያንብቡት!
  በተፈፈ ቸሩ መድሃኔአለም ከቂም እና እልህ ያውጣዎት፤ መረጋጋቱንም ያብዛልዎ፡፡
  ህይወት ያለይቅርታና ንስሃ ወደ ፊት መጓዝ ያስቸግራታል፡ ለይቅርታ አና ለንስሃ ደግሞ ጊዘው አጭር ነው!! ያስቡበት
  መልካሙን ተመኘሁ፡፡

 2. “የዓመተ ምህረት መዛባት ገና ከጅምሩ ሳይ፤ ስህተቱ ከእኔ አነባበብ ነው ብዬ መልሼ መላልሼ ባየው ያየሁት መዛባት ያው ነው፡፡ = መስከረም 24 ቀን 2013 ዓ.ም. (September 04, 2020)”
  እዚህ ላይስ እንዴት ነው፣ ለማስታወስ ያህል ብቻ September’ን በ’October የመለወጥ አስፈላጊነቱስ?

 3. Communism Dergs dictatorship style leadership is very much alive and well in many Ethiopians families. Almost all children’s in their families or in schools in Ethiopia got no democracy , got no freedom and children got no chance to voice their concerns or got no freedom whether at school. Which leads to the young rebeling acting up the first chance they get by doing opposite to the way the society raised them . They create unexpected groups contrary to their upbringings. Querro was not expected to act the way it is acting but it is because it lived without freedom for long not even within their homes got no freedom , so when they reach certain age we see what happened.
  -It should be outlawed for parents to beat up their children in Ethiopia.
  -It should be outlawed for children to.perform forced labor.
  -It should be outlawed for children to be treated as less human beings than their elders.
  To reach national reconciliation this issues should be brought I to.tge agenda
  I don’t see no benefit in beating up children , making children do forced labor while the youth unemployment rate is the highest .

 4. Communism Dergs dictatorship style leadership is very much alive and well in many Ethiopians families. Almost all children’s in their families or in schools in Ethiopia got no democracy , got no freedom and children got no chance to voice their concerns or got no freedom whether at school or elsewhere. Which leads to the young rebeling acting up the first chance they get by doing opposite to the way the society raised them . They create unexpected groups contrary to their upbringings. Querro was not expected to act the way it is acting but it is because it lived without freedom for long not even within their homes got no freedom , so when they reach certain age we see what happened.
  -It should be outlawed for parents to beat up their children in Ethiopia.
  -It should be outlawed for children to.perform forced labor.
  -It should be outlawed for children to be treated as less human beings than their elders.
  To reach national reconciliation this issues should be brought I to.tge agenda
  I don’t see no benefit in beating up children , making children do forced labor while the youth unemployment rate is the highest or treating children as pets. When they grow up they take revenges by joining groups who slaughter human beings because they were so controlled while they were raised they think to insure their freedom they act out.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.