በእስር ላይ የሚገኙት የህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች መግለጫ በድምፃችን ይሰማ ይፋ ሆነ

በእስር ከሚገኙ የህዝበ ሙስሊሙ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት የተሰጠ መግለጫ
ሰኞ ታህሳስ 14/2006

ኢትዮጵያ ከአንድ ሺህ አራት መቶ አመታት በፊት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ማህበረሰብ ካሰፈነው ፍትህ የላቀ ፍትህ ማስፈን ችላ ነበር። የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉስ በነቢዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) አንደበት ‹‹በሐበሻ አንድም ሰው የማይበደልበት ንጉስ አለ›› ተብሎለታል። እንዲህ አይነት ፍትህ በዚህ መልኩ ለማስፈን ምን ያህል ፍትሀዊ፣ እውነተኛ እና የሰለጠነ ማህበረሰብ መገንባት እንደሚጠይቅ ግልፅ ነው። በሀገራችን የነበረው ፍትህ በጊዜው ነፃነት እና ፍትህ ፍለጋ ይዋትቱ የነበሩትን ማስጠለል የቻለ እና ዘመናትን ተሻጋሪ ነበር። ግና የዛሬው አሳዛኝ እውነታ ‹‹ሰዎች ስለ ፍትህ ግንዛቤ ባልነበራቸው በዚያ ዘመን የፍትህ ጥግ የደረሰችው አገራችን ሰዎች ሁሉ ወደ ዲሞክራሲ እና ፍትህ ፊታቸውን ሲያዞሩ ለምን ጀርባዋን ሰጠች?›› ብለን እንድንጠይቅ አስገዳጅ ሆኗል።

ፍትህ ዘመን፣ ቦታና ሁኔታ የማይገድበው፣ በሃይማኖት፣ በሃገርና በብሔር ልዩነት የማይደረግበት፣ ሁሉም ለሁሉም እውን ሊያደርገው መጣር ያለበትና ሰው የመሆናችን ሚስጥር የሚፈታበት ጥልቅ እውነታ ነው። ግና ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ህጎች ፍትህን ቢደግፉትም ቅሉ በተጨባጩ ዓለም ግፍና በደል ተንሰራፍቶ ይገኛል። ቀደም ሲል አምባገነኖች በአደባባይ ይፈፅሙት የነበረውን ግፍ በዘመናችን ቅርፁን ቀይረው ፍትህ፣ ነፃነት እና እኩልነትን እየሰበኩ በተግባር ግን የህዝባቸውን ኑሮ የስቃይ ያደርጉታል።

መንግስት በሚዲያና በየስብሰባው ስለፍትህና ዴሞክራሲ በተደጋጋሚ ቢያነሳም መሬት ላይ ያለው ተጨበጭ ፍፁም ለማመን አዳጋች ነው፡፡ በማንኛውም ዘመን አምባገነኖች እንደሚያደርጉት ሁሉ ሰብዓዊነት የጐደለው ኢ-ፍትሃዊ ተግባር እየፈጸመ ሳለ ‹‹ህዝቡ ቦታ የሚሰጣቸው ሥነ-ምግባሮች፣ ህግጋትና መልካም እሴቶችን ለማስጠበቅ›› ሲባል የተሰራ እንደሆነ አድርጎ ለማቅረብ ይሞክራል። በመብት ትግላችን ሂደት ለሃይማኖታቸው ታማኝ በመሆን የፍትህና የነፃነት ጥያቄ ያነሱ ወገኖቻችን ሁሉ በመንግስት አካላት ስደት፣ እስራትና ሞት የደረሰባቸው ህብረተሰቡ የሚያከብራቸውን ስነ-ምግባሮች፣ እሴቶችና ህግጋት ሽፋን በማድረግ መሆኑ በእርግጥም ምጸት ነው።

ሙስሊሙ ህብረተሰብ ያነሳቸውና በወከላቸው ኮሚቴዎች አማካኝነት ለመንግስት ያቀረባቸው ጥያቄዎች ግልጽ፣ ቀላል፣ ሃይማኖታዊና ህገ-መንግስታዊ መብቶች መሆናቸውን መላው ኢትዮጵያዊና ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ያውቀዋል። መንግስት ግን ለሰው እምነት ከባለቤቱ በላይ ተቆርቋሪ፣ ለሃገር ደህንነትና ሰላም የሚያስብ ብቸኛ አካል እና ህገ-መንግስቱን አክባሪና አስከባሪ እንደሆነ በመደስኮር የመብት ጥያቄያችንን የሀሰት ቅርፅ ሊያስይዘው ሞክሯል። በመሰረቱ መንግስት ኃይልና ጉልበት ያለው አካል ሆኖ ሳለ በተቃራኒው ደግሞ ህዝብ ጉልበት ስለሌለው ሰላምንና ደህንነትን አጥብቆ የሚፈልገው ከመንግስት በላይ ህዝብ ነው። ህገ-መንግስት ደግሞ መንግስት ያለውን ኃይል በመጠቀም ህዝብ ላይ ግፍ እንዳይፈፅም የሚገድብ ህግ እንደመሆኑ በመንግስት እንጂ በህዝብ ሊጣስ አይችልም።

ከጅምሩ መንግስት የሙስሊሙ የመብት ጥያቄ ከጀርባው ምንም ሴራ እንደሌለው የሚያውቅ መሆኑን ብንረዳም በአባላቱም ሆነ በማህበረሰቡ ላይ ብዥታ እንዳይፈጥር ዓላማችንን እና ጥያቄዎቻችንን ለሁሉም ግልፅ አድርገናል። ይህም ሆኖ ግን በተለያዩ ብሄሮችና ሃይማኖቶች መካከል መከባበር እንዲኖር የማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት መንግስት ሙስሊሙን እርስ በእርስ፣ እንዲሁም ሙስሊሙን እና የሌላ ሀይማኖት ተከታዩን ህብረተሰብ ለግጭት የሚዳርጉ ተግባራትን ሲፈጽም ቆይቷል። አሁንም እያደረገ ይገኛል። ይህ አደገኛ አካሄድ ሊከሽፍ የቻለው በህዝባችን ብስለት እና ጨዋነት ብቻ ነው። ኩሩው የኢትዮጵያ ህዝብ ከህዝበ ሙስሊሙ የመብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የመረጠው በሳል አካሄድ ሊመሰገን የሚገባው ነበር። ይህ በሳል የህዝብ ምላሽ ሙስሊሙን እና ክርስቲያኑን ሊያጋጭ ይችል የነበረውን የመንግስት እንቅስቃሴ ቀልብሶ የህዝባችንን ጨዋነት፣ ተከባብሮ የመኖር ብቃት እና አስተዋይነት ዳግም ማሳየት ችሏል። ክስተቱም በታሪክ መዝገብ ውስጥ በወርቃማ ጽሁፍ የሚሰፍርበትና ለትውልድ የሚተረክበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።

በህዝበ ሙስሊሙ ላይ የፈጸማቸው በደሎች በህዝቡ ብስለት የከሸፉ ቢሆኑም ለህዝቡ ደንታ የሌለውና ስህተቱን አምኖ መቀበልን ውርደት አድርጐ የሚቆጥረው መንግስት ግን ህዝብ እየተቃወመው ህገወጥነቱን ቀጥሎበታል። በዚህም ምክንያት ‹‹መንግስት በሀይማኖታችን ጣልቃ አይግባብን! ያልመረጥናቸው ህገ-ወጥ የመጅሊስ አመራሮች ወርደው ፍትሀዊ ምርጫ ይካሄድ! የማናምንበት እምነት በግድ አይጫንብን!›› ብሎ የጠየቀውን ህዝብ ከነወኪሎቹ ለእስር፣ ለስደት፣ ለእንግልት እና ለሞት ዳርጓል።

የኢፌደሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 17 ንዑስ አንቀጽ 2 ‹‹ማንኛውም ሰው በህግ ከተደነገገው ስርዓት ውጪ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም›› ይላል። ነገር ግን ለፀጥታ ተግባር የተሰማሩት አካላት ህጉን በመጣስ ሰላማዊ ግለሰቦችን ሲይዙ የታጠቀ የጠላት ኃይል ላይ እንኳ ሊፈፀም የማይገባውን ግፍ፣ ድብደባ፣ ወከባ እና ስቃይ ይፈፅማሉ። ከፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ሳያገኙና ለባለቤቱ ሳይሰጡ ያስራሉ። ህግ ጥሰው ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት በኋላ የግለሰቦች ቤት ላይ ብርበራ ያካሂዳሉ። በብርበራው ወቅት በሚፈጥሩት ሁከት በቤተሰብ ላይ ከፍተኛ ስጋት እና ድንጋጤ ይፈጥራሉ። ይህ ሁሉ የሚካሄደው ህዝቡ በፍርሃት ከመብት ጥያቄው ወደ ኋላ እንዲል ቢሆንም ውክቢያውና እንግልቱ ግን የመብት ጥያቄው ይበልጥ እንዲፋፋም፣ ህዝቡ ፍርሃቱ ለቅቆት ለነፃነት የሚከፈል መስዋዕትነት ያለውን ልዩ ጣዕም እንዲያጣጥም እና ሙሉ መብቱን ወደ መጠየቅ እንዲሸጋገር ነው ያደረገው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዝምታ ወርቅ አይደለም - ከአባዊርቱ!

የህገ-መንግስቱ አንቀጽ 18 ንዑስ አንቀፅ 1 ‹‹ማንኛውም ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብርን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው›› ይላል። ህገ-መንግስቱ ይህን ቢልም ዜጐች መሆናችንን ጥርጣሬ ውስጥ በሚከት መልኩ ከያዙን በኋላ በማእከላዊ በክረምት ቀርቶ በበጋ እንኳን ቅዝቃዜው በማይቻለው ‹‹ሳይቤሪያ›› ተብሎ በሚጠራው ጨለማ ክፍል ለ3 ወራት አጉረውናል። መቋቋም የሚያዳግተውን የማሰቃያ ስልታቸውን በመጠቀም ያላሰብነውንና ያልሰራነውን ‹‹እመኑ! ተናገሩ! ፈርሙ!›› ብለው አስገድደውናል።

ለቀጠሮ ፍርድ ቤት ስንቀርብ የደረሰብንን ሰቃይ አሳይተን ቢያንስ ፍርድ ቤቱ ስቃዩን እንዲያስቆምልን ጠይቀን ነበር። ያገኘነው ውጤት ግን ወደ ማዕከላዊ ስንመለስ ከመርማሪዎቹ በቀልና ተጨማሪ ስቃይ ነበር። ፍርድ ቤቱ የደረሰብንን ስቃይና የተከሰስንበትን ጉዳይ አግባብ እንዳልሆነ አይቶ ዋስትና ሰጥቶን ሳለ ፖሊስ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ጥሶ ዋስትናውን በመከልከል ክስ መስርቶብናል። አሰቃዮቻችን ስለ ህገ-መንግስት እና መብት ስንናገር ‹‹ህገ-መንግስቱን ቀደህ ጣለው!›› እና ‹‹እኛ መሰዋዕትነት ከፍለን ነው እዚህ የመጣነው!›› ወ.ዘ.ተ በማለት ለህግም ሆነ ለሰው ክብር ደንታ እንደሌላቸው አሳይተውናል። ይህ ሁሉ መከራ በተቃራኒው ህገ-መንግስቱን ለማስከበር መታገል የሚያስፈልግበት ትክክለኛ ወቅት ላይ መሆናችን እንዲሰማን፣ እውነተኛ ፅናትና ወኔ እንዲኖረንም አድርጎናል።

በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ 5 ‹‹የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል የእምነት ቃል እንዲሰጡ፣ ወይም ማናቸውንም ማስረጃ እንዲያምኑ አይገደዱም። በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት የለውም›› የሚለውን ድንጋጌ መሠረት በማድረግ እዚያው ማዕከላዊ የምርመራ እስር ቤት እያለን የደረሰብንን ስቃይና እንግልት ገልፀን ክስ አቅርበን ነበር። በምርመራ ጣቢያው ቃላችንን የሰጠነውም ሆነ የፈረምነው ተገደን መሆኑን ገልፀን ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀናል። ሆኖም ግን ክሳችን ተዳፍኖ እና ተድበስብሶ እንዲቀር በመደረጉ በጊዜው ምላሽ ሳናገኝ ቀርተናል። ክስ ተመስርቶብን ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አቅርበን በኋላም በድጋሚ ጉዳዩን ያስረዳን ሲሆን አሁንም ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ሙሉ ለሙሉ የሚያደምጥበትንና ምላሽ የሚሰጥበትን ቀን እየተጠባበቅን እንገኛለን።

ከቤተሰብ፣ ከጠበቃና ከሀኪም ጋር እንዳንገናኝ አድርገው የፈፀሙብን የህግ-ጥሰት እና አስገድደው በማስፈረም እና ድምፅና ምስላችንን በመቅረፅ የፈፀሙብን በደል በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር 424 መሰረት እስከ አስር አመት የሚያስቀጣ ኢ-ሰብዓዊ ተግባር ነው። ነገር ግን የፖሊሱም፣ የዐቃቤ ህጉም፣ የፍርድ ቤቱም አለቃ በሆነውና የፍትህ ስርዓቱን ሰብስቦ በያዘው ገዚው ፓርቲ አምባገነንነት በተቃራኒው እኛ ተከሳሾች ሆነን ጉዳያችን ‹‹በፍርድ ቤት›› በመታየት ላይ ይገኛል።

በማዕከላዊ እስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ስነ-ልቦናዊ እና አካላዊ ስቃይ አድርሰውብናል። ከአስራ አራት ሰዓታት በላይ ያለ እረፍት ቀጥ ብለን እንድንቆም በማድረግ፣ ጀርባችን ሰንበር እስኪያወጣ እና እስኪገሸለጥ ራቁታችንን በሽቦ በመግረፍ፣ በሰንሰለት በማሰር እና ዓይናችንን በጨርቅ በመሸፈን የውስጥ እግራችን እስከሚላጥ ገልብጦ በመግረፍ፣ ቀንና ማታ አሰቃቂ በሆነ ምርመራ እና ድብደባ እንቅልፍ በመንሳት፣ ሃይማኖታችንንና ክብራችንን በመንካት፣ ፂማችንን በመንጨትና እንድንላጭ በማስገደድ፣ እንዲሁም ሰላት በመከልከል፣ ቤተሰብ፣ ጠበቃ፣ ሀኪምና የሃይማኖት አባት እንዳናገኝ በማድረግ፣ ከአቅም በላይ የሆነን ስፖርት በግድ በማሰራት፣ ብልት በመግረፍ፣ ‹‹ልጅህን እንገለዋለን! ሚስትህን አስረን በፊትህ ቶርች እናደርጋታለን! ብልትህ ላይ ሀይላንድ በማንጠልጠል መሀን እናደርግሃለን!›› ሲሉ በማስፈራራት ከፍተኛ የሆነ እንግልትና ስቃይ አድርሰውብናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዐብይ አሕመድ ወይስ ጭራቅ አሕመድ? - መስፍን አረጋ

ይህም አልበቃ ብሏቸው በሃገሪቱ የቅጣት ጣሪያ የመጨረሻ የሆነውን የወንጀል አንቀፅ ጠቅሰው ከሰሱን። ‹‹ህገ-መንግስት ይከበር!›› ብለን በጠየቅን ህገ-መንግስትን ለመናድ በመንቀሳቀስ ወነጀሉን። ተቃውሟችን ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ ሳለ ‹‹ከእኛ ውጪ ያሉ እምነቶች ከሃገሪቱ መጥፋት አለባቸው ብለዋል›› ሲሉ ከሰሱን። ሃይማኖታዊ የመብት ጥያቄያችንን ‹‹ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ነው›› በሚል ሊያጠለሹ ሞከሩ። ‹‹ህዝብ ያልመረጣቸው የመጅሊስ አመራሮች በህገ-ወጥ መንገድ መጥተው አይመሩንም! ፍትሀዊ ምርጫ ይካሄድ!›› ባልናቸው ‹‹መንግስት ይውረድ! መንግስት አያስተዳድረንም! ብለዋል›› በሚል ወነጀሉን።

ያዘጋጁት ክስ የህግ ባለሙያ ቀርቶ ማንም የህግ ግንዛቤ የሌለው ሰው በሚረዳው ደረጃ በህግ ስህተቶችና አመክኖአዊነት በጐደላቸው ሃሳቦች የተሞላ፣ በህግ ወንጀል ያልሆኑ አረፍተ ነገሮች እና ቃላት ወንጀል ተደርገው የተጠቀሱበት ፍፁም ተራ እና የሃገሪቷን የፍትህ ሁኔታ የሚያስገምት ክስ ነው። ምንም እንኳን ‹‹ክሱን ዳኞች ስርዓት ሊያስይዙት ይገባል›› በሚል የፀረ-ሽብር አዋጁን በመቃወም እና ክሱ ላይ ያሉ ስህተቶችን ሁሉ ነቅሰን በማውጣት የክስ መቃወሚያ ያቀረብን ቢሆንም የዳኞች ብይን ክሱን ይበልጥ የማይገባና ውስብስብ አደርጎታል።

ከታሰርን ጀምሮ የደረሱብን የህግ ጥሰቶች እና የፍትህ እጦቱ ከፍርድ ቤት ሂደት ራሳችንን ሙሉ ለሙሉ እንድናገል የሚገፉ ነበሩ። ሆኖም ግን የተወነጀልንበት ክስ ምን ያህል ከእውነት የራቀ፣ ጥያቄያችን ሃይማኖታዊ እና ህገ መንግስታዊ መሆኑን እና እንቅስቃሴያችንም ፍፁም ሰላማዊ እንደነበር ለህዝባችን በፍትህ አደባባይም ጭምር ለማሳየት ስንል የፍርድ ሂደቱ ውስጥ መግባቱ የተሻለ መሆኑን በማሰብ ሃሳባችንን ቀይረናል።

መንግስት በአግባቡ ሊተውነው ያልቻለውን አሳፋሪ የፍርድ ቤት ድራማውን ህዝብ እንዳያይበት ለመሸሸግ በመገደዱ ‹‹የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በኋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለህዝብ ግልፅ በሆነ ችሎት የመስማት መብት አላቸው›› የሚለውን ህገ-መንግስታዊ መብት በመጣስ ችሎቱ ዝግ እንዲሆን ተደርጎ ቆይቷል። በዝግ ችሎቱ የምስክር መስሚያ ጊዜ ብዙ አስገራሚ ድራማዎችን አይተናል። ዓቃቤ ህጎች ዳኞች የሚሰጡትን ብይን እንደማይቀበሉ እስከመግለጽ የደረሱበትን እና ምስክሮችን ማለት ያለባቸውን አሰልጥነዋቸው እንደሚያመጡ አምልጧቸው የተናገሩበትን አጋጣሚ ታዝበናል። በወቅቱ ‹‹ጋዜጠኞች፤ ዲፕሎማቶች እና ህዝባችን ምነው ይህንን አይተው በነበር?›› ብለን ከመመኘት ውጭ ምርጫ አልነበረንም።

ማንኛውም ታራሚም ሆነ ተጠርጣሪ በማረሚያ ቤት ሊያገኛቸው የሚገቡ በህግ የተደነገጉ መብቶች አሉ። መብቶች ግን እንደተለመደው ከወረቀት ዘለው መሬት ጠብ ማለት አልቻሉም። የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ላይ ሲሆን ደግሞ መብቶች በቅጣት ይተካሉ። ካለው የጋራ ችግር በተጨማሪ በእኛ ላይ በተለየ መልኩ በጥላቻ እና በበቀል ስሜት የደረሰብን እንግልት ህሊና ያለውን ሁሉ የሚጎዳ ነው። ከቤተሰቦቻችን መካከል ከጥቂቶች ጋር በስተቀር እንዳንገናኝ ተደርጓል። የምንጠየቅበትንም ሰዓት ከእስረኞች ሁሉ በመለየት በቀን ለሃያ ደቂቃ ብቻ እንዲሆን በማድረግ አድሎ እና መገለል ተፈፅሞብናል። በመካከላችን ልጆቹና ቤተሰቦቹ እንዳይጠይቁት የተደረገም አለ። ከሁሉም በላይ ከባድ ህመም ያለባቸው፤ ሆስፒታል ሄደው እንዲታከሙ የታዘዘላቸው፤ ቀዶ ጥገና እንዲደረግላቸው የተመራላቸው እና በማእከላዊ የደረሰባቸውን ድብደባ ለመታከም የጠየቁ ለዓመት ከአራት ወር በላይ መፍትሄ ሳያገኙ ስቃዩን ይዘው ‹‹የፍትህ ያለህ!›› እያሉ ይገኛሉ። ማረሚያ ቤት የደረሱብን እና እየደረሱብን ያሉ አድሎዎችንና እንግልቶችን ሁሉ ዘርዝረን ጉዳያችንን ለሚመለከተው ፍርድ ቤት ብናቀርብም የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ፍርድ ቤት እንኳ ለመቅረብ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ሶስት ጊዜ ቀጠሮ አሳልፈዋል።

ሙስሊሙ ማህበረሰብ የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴውን ከጀመረ በኋላ መንግስት በነጋዴውና በተማሪው፣ በመንግስት መዋቅር ውሰጥ በሚሰሩ አካላት፣ በሃይማኖት አባቶች እና በአስተማሪዎች፣ እንዲሁም በኢስላማዊ ተቋማት ላይ ሰብዓዊነት የጎደለው እና ህገ-መንግስቱን የሚጻረር የመብት ጥሰት መፈጸሙን ቀጥሎበታል። በበርካታ የክልል ከተሞችና ሙስሊሙ ደስታውን በሚገልጽበት የዒድ ዕለት በአዲስ አበባ ፈጽሞ ልንረሳው የማንችለውና ጭካኔ የተሞላበት ግፍ ፈጽሞብናል። የምንሳሳላቸው እና የምንወዳቸው ወገኖቻችንን እና ቤተሰቦቻችንን ለእስር፣ ለሞትና ለአካል ጉዳተኝነት ዳርጎብናል። ይህ ሁሉ ስቃይ እና መከራ በአንድ በኩል የመንግስትን ግፍ እና ለህግ ተገዢ አለመሆን ሲያጋልጥ በሌላ በኩል የህዝባችንን ፅናት እና ቁርጠኝነት አሳይቶናል። በየትኛውም ሃይማኖት፣ ባህል እና ልማድ ግፍ የተጠላ ሲሆን ለመብት ሲሉ መሰዋት ደግሞ ክብር ነው። ስለዚህ ለሃይማኖታችሁ፣ ለክብራችሁ እና ለደህንነታችሁ ለተሰደዳችሁ፣ ለታሰራችሁ፣ ለተደበደባችሁ እና ቤተሰቦቻችሁን ላጣችሁ ሁሉ ያለንን ክብር እንገልጻለን፤ በሀገራችን ለሚሰፍነው የሃይማኖቶች ነፃነት እና እኩልነት የመሰረት ድንጋይ የሚሆነው ዛሬ እናንተ የከፈላችሁት መስዋእትነት ነውና!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካው ጨዋታ ተጨማሪ 3 ነጥብ አይቀነስባትም ሲሉ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ተናገሩ

ለሁለት ዓመታት ያለ ምንም መሰላቸት እንግልቱ፣ ማስፈራሪያው፣ እስሩ፣ ድበደባው እና ግድያው ሳይበግራቸው እና ሰላማዊውን የተቃውሞ መስመር ሳይለቁ ለሃይማኖታቸው ያላቸውን ፍቅር ላሳዩ፣ እንዲሁም ይህን ድንቅ ታሪክ ለሰሩ አባቶች፣ የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች /በተለይ ደግሞ ወጣቶች እና ሴቶች/ ያለንን ከፍ ያለ ክብር እና ምስጋና ልናቀርብ እንወዳለን። በሰራችሁት ሁሉ ተደስተናል፤ ኮርተንባችኋልም!

መንግስት የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር ያደረገውን ሙከራ ንቆ በመተውና ጉዳዩን በብስለትና በሰከነ መንፈስ በማየት፣ እንዲሁም እውነታውን ለመረዳት ጥረት በማድረግ ረገድ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን፣ በተለይም ህዝበ ክርስትያኑ ላደረጋችሁት ትብብር ሳናመሰግን አናልፍም። በእውነቱ የሃይማኖት ልዩነት ሳያግደን በህዝብ ደረጃ ተከባብረን ስለመኖራችን ከተነሱ ምሳሌዎች ሁሉ በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ያሳየነው መከባበር እና አንድነት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። ይህ ብሄራዊ አንድነት የበለጠ ተጠናክሮ በጋራ ለምንገነባት ሃገራችን ታላቅ ብርታት እንደሚሆን ጠንካራ እምነት አለን።

በተጨማሪም የፕሬስ ነፃነት በተነፈገበት ተጨባጭ የመብት ጥያቄያችንን እውነታ ለመገንዘብ ማስፈራሪያዎችን እና ዛቻዎችን አልፋችሁ፣ የመንግስትን የተሳሳተ እና ኢ-ህገመንግስታዊ አካሄድ ለይታችሁ ሂደታችን ላይ አዎንታዊ አስተያየቶች እና ገንቢ ትችቶችን ለሰጣችሁ ጋዜጠኞችና በሚዲያው ዘርፍ ለተሰማራችሁ ባለሙያዎች ሁሉ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን።

ወገኖቻችሁ ያጡትን ፍትህ እና ነጻነት በሃገራችሁ ለማየት በመጓጓት የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ለማበርከት የምትጣጣሩ በስደት የምትገኙ ሙስሊሞችና የሌሎች ሀይማኖቶች ተከታይ ወገኖቻችን በሙሉ ላደረጋችሁት ሁሉ ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው። በሀገር ውስጥ ለተጠናከረው የአጋርነት ስሜት የእናንተ አስተዋጽኦ የመጀመሪያውን ድርሻ ይይዛል።

በአጠቃላይ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ነጋዴው፣ አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩ፣ ተማሪው፣ ሴቱ፣ ወንዱ፣ ወጣቱ፣ አዛውንቱና ሌላውም፣ እንዲሁም በመንግስት መዋቅር ስር ሆናችሁ የመንግስትን የተሳሳተ አካሄድ ስትቃወሙ የነበራችሁ ዳኞች፣ ዓቃቤ ህጎች፣ አባቶች፣ ፖሊሶች፣ የጦር ሰራዊትና የፓርላማ አባላት በሙሉ ከፍ ያለ ምስጋናችንን እናቀርብላችኋለን። የጥረታችሁን ፍሬ በቅርቡ ያሳያችሁ ዘንድም አላህን እንለምናለን!

መልእክታችን

1/ በሙስሊሞች መካከል እና በሙስሊሙና በክርስትያኑ መካከል የታየውን አንድነትና መከባበር ሁላችንም በጋራ እንድንጠብቀው፣ እንዲሁም መሰረቱ የፀና ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ እንድንጥር አደራ እንላለን። ሀገራችን ከእርስ በእርስ ሽኩቻዎች ወጥታ የእድገትና ብልጽግና ጉዞ እንድትጀምር ከተፈለገ ትክክለኛ የሃይማኖት ነፃነት፣ እኩልነት እና መከባበር በቅድሚያ እውን መሆኑ አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው። የሃገራችንን እድገት የጋራ አላማ አድርገን፣ የጋራ ተጠቃሚ ሆነን መኖር የምንችለው ስጋትና ጥርጣሬውን በፍቅርና መተማመን ስንተካው ነው።

2/ በፅናት ሰላማዊ የመብት ትግሉን የምንቀጥል መሆኑንና የሚያስከፍለንን መስዋዕእትነት ሁሉ ለመክፈልም ዝግጁ መሆናችንን ለህዝባችንም ሆነ ለመንግስት መልእክት ለማስተላለፍ እንወዳለን። ለቀጣዩ ሰላማዊ የመብት ትግል እርከንም እኛም ህዝባችንም በሙሉ ዝግጅት ላይ መሆናችንንና ለመብታችን ተግተን ሰርተን መስዋዕት ከመሆን ወደኋላ የማንል መሆኑን ስንገልጽ በከፍተኛ ወኔ ተሞልተን ነው!

3/ መንግስት እየፈጸማቸው ያላቸውን ኢ-ህገ መንግስታዊ ተግባራት፣ በህዝበ ሙስሊሙ ላይ እየፈጸመ ያለውን እስራት፣ ግፍ፣ መስጂድ ነጠቃ፣ የሀሰት ውንጀላና የሃይማኖት ሰዎችን፣ ጋዜጠኞችንና የመብት ጠያቂዎችን በሽብርተኝነት መፈረጅና መሰል ህገ መንግስታዊ የመብት ጥሰቶችን በአስቸኳይ እንዲያቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን። በማእከላዊና በተለያዩ እስር ቤቶች የሚፈጸሙት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እንዲቆሙና የህሊና እስረኞችም መለቀቅ እንደሚገባቸው ለመግለጽ እንወዳለን። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእውነተኛ ሰላም፣ ፍትህ፣ ዴሞክራሲ እና ልማት ባለቤት ሆኖ ማየት የዘወትር ህልማችን መሆኑንም ሳንገልጽ አናልፍም፡፡

በመጨረሻም በቃል ኪዳናችን ጸንተንና መነሻው ላይ ከነበረው በተሻለ ሁኔታ ተንቀሳቅሰን ፍጹም በሰለጠነና በተጠና መልኩ የተሟላ ፍትህ እና ነፃነት ለማግኘት በጽናት እና በቆራጥነት ሁሉም ባለድርሻ አካል እንቅስቃሴውን ከዳር እንዲያደርስ አደራ ለማለት እንወዳለን። የእንቅስቃሴው ማብቂያ ድልና ስኬት እንደሚሆን አንጠራጠርም!

አላሁ አክበር!

ግልባጭ፡- እዚሁ አገር ውስጥ እና በውጭ አገራት ለሚገኙ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች

2 Comments

  1. I have prepared myself for fighting injustice in my beloved country and the world at large. I am always standing by my people side and ready to pay ultimate price for democracy and the rule of law. It is inevitable that People’s power win at last.

  2. ፍትህ ትቆያለች እንጂ አትጠፋም። ጨቋኞችም አንድ ቀን የእጃቸውን ያገኛሉ።

Comments are closed.

Share