የዐማራው ሕዝብ እልቂት ኢትዮጵያን ያጠፋታል – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

October 6, 2020
አክሎግ ቢራራ (ዶር)
Save Amhara

“ዐማራን እየገደሉ ኢትዮጵያን መግዛት የከሰረ ፖለቲካ ነው”
የጎንደር ሕዝብ በሰላማዊ ሰልፍ ያሰማው መፈክር
“በእኔ ዘመን አሳዳጅና ተሰዳጂ አይኖርም”

              /ሚንስትር ዶር ዐብይ አሕመድ አሊ

ክፍል ሁለት

በክፍል አንድ በዐማራው ሕዝብ ላይ በተከታታይ እልቂት፤ ጥፋትና ውድመት እንዲካሄድበት ትርክቱን በፕሮግራም ያዋቀረው ትህነግ/ህወሓት መሆኑና ይህንን የተሳሳተ ትርክት ስር እንዲሰድለት በታዛዢነት የፈጠሩት ትህነግና ኢህአፓ ናቸው። መጀመሪያ በዐማራው ስም የዘውግ መለያ እንዲኖረው ተደርጎ በታቀደ ስሌት፤ ራሱን የዐማራ ብሄራዊ ዴሞክራሳዊ እንቅስቃሴ (Amhara National Democratic Movement) ብሎ ጠራ፤ ኢህአዴግን ተቀላቀለ። ከዚያ በኋላ ደግሞ፤ ስሙን ቀይሮ፤ የዐማራ ዴሞክራሳዊ ፓርቲ (አዴፓ) ተባለ። ዛሬ የዐማራ ብልፅግና ፓርቲ ተብሎ ይጠራል።

ስም ቢቀያየር መሰረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ከሌለ የፖሊሲና መዋቅራዊ ለውጥ ስኬታማ ለማድረግ የማይቻል መሆኑን ከሌሎች አገሮችና ከኢትዮጵያ የቅርብ የፖለቲካ ታሪክ ልምዶች ለመማር ይቻላል።

ይህ መንደርደሪያ ወደ ዋናው የሁለተኛ ክፍል ትንተናየ ያመራኛል። አመጸኞች፤ የብሄር ጽንፈኞችና ጂሃዲስቶች በጋራ ሆነው በዐማራው ሕዝብ ላይ የሚፈጽሙት እልቂት በዐማራው ሕዝብ ላይ፤ በፅንሰ-ሃሳብና በፕሮግራም ደረጃ፤ ህወሓትና የፈጠረው የዐማራው ፖለቲካ ፓርቲ እየተናበቡና እየተመካከሩ የዐማራውን ሕዝብ በጂምላ “ትምክህተኛ፤ ነፍጠኛ፤ መጤ ወራሪ” ወዘተ የሚሉ ክሶችና ትርክቶችን ልክ እንደ ኮሮና ወረርሽኝ አገር አቀፍ በሆነ ደረጃ እንዲዛመቱ አደረጉ። በየትኛውም ክፍለ አገር ወይንም ክልል ዐማራው ኢላማ ሆነ፤ ተቆርቋሪ የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይኖረው ተደረገ።

ትርክት ተደጋግሞ ሲነገር እውነት ይመስላል፤ ተከታይ ይፈጥራል። ከተራ ትርክት ወደ ተቋሞች ይቀየራል። በኢትዮጵያ ሁኔታ ስከታተለው፤ በብሄር፤ ብሄረሰብና ሕዝቦች መብቶች፤ በማንነት፤ ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣን ምክንያቶችና ሰበቦች እየተደገፈ የተካሄደው ሁኔታ ከፍተኛና አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ለምሳሌ፤ ዛሬ በግልፅ የሚታየው የክልል የፖለቲካ ልሂቃን ኃይሎች በመሳሪያና በወታደር ኃይል የተደገፈው አቅምና ሥልጣን ከፌደራሉ መንግሥት ወታደራዊ ኃይሎች ጋር ተመጣጣኝ ወይንም የላቀ እየሆነ ሄዷል።

የአገር ውስጥ ጥናቶችና ታዛቢዎች እንደሚሉት ከሆነ “በልዩ ኃይሎች” የሚንቀሳቀሰው የወታደርና የመሳሪያ ኃይሎች አቅምና ብዛት እጅግ በጣም አሳሳቢ ከሆነ ደረጃ ላይ ደርሷል። ሶስቱ ክልሎች፤ የኦሮሞያ፤ በዝቅተኛ ሲታሰብ የሰለጠነውና የታጠቀው ልዩ ኃይል “ብዛት 400,000፤ የዐማራው 300,000፤ የትግራዩ ደግሞ የሚታወቀው ብቻ 250, 000 ነው” ተብሎ ይነገራል። በጠቅላላ እነዚህ ሶስት በብሄር የተዋቀሩ ክልሎች ልክ አገር እንደሆኑ በሚያመለክት ደረጃ፤ በጠቅላላው 950,000 የታጠቀ ወታደር አስልጥነው ተዘጋጅተዋል። ይህ የልዩ ኃይሎች ስልጠናና የባጀት ድጋፍ ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅም በላይ መሆኑ አያከራክርም። ከዚህ በላይ ግን አሳሳቢነቱ እንደሚከተለው ነው።

 • የተራውን ነዋሪ ሕዝብ ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ከሆነ የሚያስፈልገው ፖሊስ እንጅ ልዩ ኃይል አይደለም፤
 • ፖሊስም ቢሆን፤ ደህንነት ሲባል የመላውን ነዋሪ ደህንነት የመጠበቅ ልምዶችን ስኬታማ ማድረግ እንጅ፤ በኦሮምያና በቤኒሻንጉል እንደተፈጸሙት ወንጀሎች በዘውግና በኃይማኖት ለይቶ ጥቃት ሲካሄድ፤ ልክ እንደተባባሪ ቁሞ ማየት ፖሊሱና ልዩ ኃይሉ የችግሩ አካል መሆኑን የሚያሳይ ክስተት ሆኖ አገኘዋለሁ፤
 • ይህ በዘውግና በኃይማኖት እየለዩ ጭፍጨፋና የኃብት ውድመቶች ሲካሄዱ ቁሞ ማየት የሚነግረኝ የሕግ የበላይነት የለም የሚለውን አስጊና አገርን የሚያፈርስ ክስተት ነው።
 • በአስቸኳይ ካልተፈታ፤ ይህ የኃይል አሰላለፍ በአዲስ አበባ ለሚካሄደውም የመሬት ቅርሚት ግብአት ሊሆን ይችላል።

የማንነት ጥያቄ ወደ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ጥቅም ሲቀየር ሊያስከትል የሚችለውን ጭካኔና አገርን የማፍረስ ሁኔታ፤ በተለየ ደረጃ በዩጎስላቭያ አይተናል። ይህች የፈደራል ስርዓት የነበራት አገር ከመፈራረሷ በፊት ተመሳሳይ ሁኔታዎች ይታዩ ነበር። ሰርብያኖች፤ ክሮዓቶች፤ የክርስትናና የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ወዘተ ተለያይተው የሚገዳደሉበት፤ ቀስ በቀስ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ የገቡበት ዘመን ያችን የፌደራል ስርዓት የነበራትን ጠንካራና ዘመናዊ አገር አፈራረሳት። የፌደራል ስርዓት ትርጉሙ እየተለጠጠና ፈር እየለቀቀ፤ ልዩነቱ ሲሰፋና ማእከላዊው መንግሥት ከሚቆጣጠረው አቅሙ በላይ ሲደርስ መፈራረስ ያለው እድል ከፍተኛ ይሆናል።

በተመሳሳይ፤ አፍጋኒስታንም ሲካሄድ የቆየው ግጭት ልዩ ኃይሎች (regional and tribal militias and warlords) እየጠነከሩ ሄደው ሁሉም አለቃ ነኝ የሚልበት ሁኔታ ሲፈጠር መአከላዊው መንግሥት የውጭ እርዳታም ቢኖረው አቅሙ እየደከመ መሄዱን የሚያሳይ ክስተት ነው። ይህን ክስተት አሜሪካኖችም ሊፈቱት አልቻሉም።

የኢትዮጵያን የዘውግ ልሂቃንና ምሁራን የፈጠሩትን ሁኔታ በሚመለከት ጥያቄዎችን ላቅርብ። በሶስቱ ክልሎች ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱት ልዩ ኃይሎችና የሚደግፏቸው የዘውግ አለቃዎች (War lords of each Kilil) የተዘጋጁት ምን ለማድረግ ነው? ማንን ለመዋጋት ነው? የክልላቸውን ሰላምና እርጋታ ለመጠበቅ መሆኑ አከራካሪ ነው። ኢትዮጵያን እንደ ሃገር ለመቀጠል ቆራጥነት ካለ እትዮጵያ ወደ አላስፈላጊ የእርስ በእርስ እልቂትና ጦርነት ከመሸጋገሯ በፊት እነዚህ የክልል ልዩ ኃይሎች መፍረስ አለባቸው። እነዚህ ግዙፍ ኃይሎች እስከ ትጥቃቸው ወደ ፌደራል ፖሊስና ወደ ፌደራል መከላከያ ተቋማት መሰራጨት አለባቸው። ሲሰራጩ ደግሞ የሚመደቡት በየክልላቸው ሊሆን አይችልም። በችሎታቸውና በብቃታቸው እየተገመገሙና ልዩ ልዩ ስልጠና እየተሰጣቸው ወደ ሕብረብሄራዊ ተቋማት መመደብ አለባቸው።

ስለዚህ፤ የልዩ ልዩ ኃይሎች አባላት ምን ይሁኑ? የሚለው ሊፈታ ይችላል። ህይወትና ቤተሰብ አላቸው የሚለው ጥያቄ አግባብ አለውና ሊታሰብበት ይገባል ማለቴ ነው። ላጠናክረው የምፈልገው የፖሊ ለውጥ፤ ፈቃደኛና ችሎታ ያላቸውን በፌደራል ፖሊሱና በብሄራዊው መከላከያ እንዲሰማሩ ማድረግ ሃላፊነት የሚያሳይ አማራጭ ነው።

በተጨማሪ፤ እያንዳንዱ ክልል በቂና ጥራት ያለው የፖሲስ አገልጎት የሚሰጥ አካል ስለሚያስፈልገው፤ ፍላጎትና ብቃት ያላቸውን ግለሰቦች ለይቶ፤ ሁሉንም የክልሉ ነዋሪዎች እንዲያገለግሉ አቅማቸውን በማጠናከር፤ ስለ ሰላም፤ ስለ አብሮ መኖር ጠቃሚነት፤ ስለ ኃብት እንክብካቤ፤ ስለ ጸረ-ወንበዴነትና ሽብርተኛነት፤ ስለ የህግ የበላይነት ትርጉም፤ ሰለ ዘመንዊ የፖሊሲ ሚና ወዘተ ሥልጠና ተሰጧቸው  ዘመናዊነትንና ፍትሃዊነትን የሚያንጸባርቅ የፖሊስ ስራ እንዲሰሩ ለማድረግ ይቻላል። ልክ በአሜሪካ እንደሚታየው፤ ጥቁሩን ከነጩ እየለዩ መደብደብ፤ መግደልና ማዋረድ ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያዊያንን እንደ ዜጋ፤ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር የሚያኮራ የፖሊስ፤ የፍርድና ሌላ አገልግሎት ስኬታማ ቢሆን ኢትዮጵያ እንደ ተምሳሌት የምትጠቀስበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም።

እስካሁን የሚታየው ሁኔታ ግን ባጠቃላይ ከሩቅ ሆኖ ለሚመለከተው ታዛቢ ወንበዴዎች፤ አመጸኞችና ጽንፈኞች እንዳሸን የፈሉባት ኢትዮጵያ ልዩ ኃይሎች ሁኔታውን አባብሰውታል ለማለት የሚያስችሉ ብዙ መረጃዎችና ታዛቢዎች አሉ።

ዐመጸኞች፤ ጽንፈኞች፤ ጅሃዲስቶች:- የዘውግና ኃይማኖት ተኮር ጭፍጨዎች ጥልቀት/ስፋት  

ያመጸኞች አለቃው (The demagogue) ጃዋር ሞሃመድ በነፍጠኛውና በትምክህተኛው ዐማራ ላይ የሃሰት ወሬ ሲያሰራጭ “አንተ ሰው አቁም፤ ይህ ፕሮፓጋንዳ እልቂት ያመጣል፤ የዐማራው ሕዝብ በኦሮምያ የመኖር መብት አለው” ብሎ ደፍሮ የተናገረ ባለሥልጣን አለመኖሩ እኔን እጅግ አስደንግጦኛል፤ አሳስቦኛል፤ አስግቶኞል። ኢትዮጵያ ወደ የት እየሄደች ነው? ወደሚል ጥያቄ ወስዶኛል። “ተፎካካሪ ፓርቲዎች” በዚህ ጉዳይ ላይ ለምን የማያሻማ አቋም አልወሰዱም? ማንን ፈርተው ነው? የሚሉ ጥያቄዎችንም እንዳነሳ አስገድዶኛል።

ጃዋር ሞሃመድ በነፍጠኛውና በትምክህተኛው የዐማራ ሕዝብ ላይ የእልቂት ጥሪ ሲያደርግና ተከታዮቹን ሲቀስቅስ፤ ይህን ትርክት ከየት ቀሰመው የሚለውን ትኩረት እንድትሰጡት አሳስባለሁ። ድንገተኛና ከሰማይ የወረደ ጥሪ አይደለም። ታሪክ አለው።

በህሊናችሁ እንድትስሉት የምፈልገው የሚዘገንን ሃቅ አለ። ይኼውም፤ የዓለም ትሥስር በጠነከረበት በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን (in a globalized world of the 21st century) ምን አይነት ህሊና ቢስ ነው? ንጽሁን የሰው ፍጥረት እንደ በግ በገጀራ ወይንም በሌላ መሳሪያ አንገቱን/አንገቷን የሚያርደው? እንደምታስታውሱት በሊቢያና በሶርያ አይሲስ የምእራባዊያንን እና የሌሎቹን ንጽሃን አንገት ቆርጧል!!! አገሮችን አውድሟል።

በኦሮምያና በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ የዐማራውን፤ የአገውን አና የሌላውን “ንጹህ ኦሮሞ” ወይንም የክልሉ ነዋሪ አይደለህም/አይደለሽም በሚል መስፈርት ብቻ ለይቶ ጭፍጨፋ ተካሂዷል፤ አንገታቸው እንደ እንስሳ ተቆርጧል። ተምረናል የሚሉ ግለሰቦች ሲሳተፉበት ደግሞ ሁኔታውን ያባብሰዋል። የሚዘገንን ያደርገዋል። ይህ ጭካኔ የሚካሄደው ታስቦበት እንጅ በድንገት አይደለም።

ጃዋርና ደጋፊዎቹ ከላይ የጠቀስኩትን ትርክት እንዲሰርጽ አድርገው በኦሮምያ የሚኖረውን የዐማራ ሕዝብ አስጠንቅቀው ነበር። “ዐማራ እንደ ጨፈረ አይቀርም…ዋጋ ይከፍላል (They will pay a price) ፤ ዐማራው ያለው አማራጭ እኛ እንደምንፈልገው መገዛት ወይንም ለቆ መውጣት” ነው። ይህ ዛቻ ያስታወሰኝ በግራኝ ሞሃመድ ወረራና ይህን ወረራ እንደ ክፍተት ተጠቅመው ኦሮሞዎች ኢትዮጵያን እየወረሩ አካባቢውን ሁሉ እያጸዱ፤ እምቢ ያለውን እየጨፈጨፉ፤ እሽ ያለውን የራሱን ማንነት እንዲለውጥ አያደረጉ ከ 28 ያላነሱ ነዋሪ ዘውጎችን (Indiginous peoples) እንዲጠፉ ያደረጉበትን ዘመን ነው።

ጃዋር፤ በአገር ውስጥና ውጭ የሚገኙ የብሄር ጽንፈኞችና አመጸኞች (A gang of terrorists) በኦሮሞ ሕዝብ ስም በዐማራውና በሌሎች የዘውግና የክርስትና ኃይማኖት አባላት ላይ ይቅርታ የማይደረግለት ወንጀል ፈጽመዋል። እንደ ሻሸመኔ ባሉ የህበረ ብሄር ከተሞችና ሌሎች አካባቢዎች በብዙ ቢሊየን ብር የሚገመት ኃብት አውድመዋል። እንደ ሃገር ሲታይም በኢትዮጵያ ላይ ወንጀል ፈጽመዋል።

የእኔ ጥያቄ ግን፤ ጃዋርና ግብረ አበሮቹ አርቲስት ሃጫሎ ሁንዴሳን አስበውና አቅደው “ከመግደላቸው” በፊት ሁኔታዎችን  ለማመቻቸትና የእርስ በእርስ እልቂት እንዲካሄድ በሜድያ ሲያሰራጩት የነበረው የእልቂት ትርክትና የዝግጅት ቅስቀሳ ለምን ትኩረት አልተሰጠውም? ለምሳሌ፤ ሌላውን ሁሉ እንርሳው ብንልም እንኳ፤ “ይህን መንግሥት ከፈለግን ልናወርደው እንችላለን” ብሎ እንደ ፎከረ ትዝ ይለኛል።  “ይህን መንግሥት” ሲል የማንን መንግሥት ማለቱ ነበር? የዐማራው ሕዝብ የፖለቲካ የበላይነት ይዟል እንዳይባል፤ አንድም የበላይነት መረጃ የለም። ቁም ነገሩ፤ ጅብ ከጮኽ እንዲሉ ሁኔታው ሊወገድ የሚችልበት እድል ነበር።

ከጽንፈኞች፤ ከአመጸኞች፤ ከወንበዴዎች፤ ከጠባብ ብሄርተኞችና ከውጭ ደጋፊዎቻቸው፤ በተለይ ኢትዮጵያን ለማፈራረሰ ቀን ከሌት ከምትሰራው፤ የውክልናንና የሳይበር ጦርነትን ከምታካሂደው ከግብፅ የማያቆም ጫና የቅርብ ታሪክ ለመማር የምችለው አንድ መሰረታዊ ክስተት አለ። ይኸውም የተባበረችና የተከበረች ኢትዮጵያን ለማቆየት ከተፈለገ፤ በህብረት እና በመናበብ ከመስራት ውጭ አማራጭ የለንም የሚለውን ነው።  “ተባበሩ፤ አለያ ተሰባበሩ” የሚለውን የብልሆች ምክር ማስተጋባት ወሳኝ ሆኗል። ኢትዮጵያ ብትፈራርስ ማንኛውም ዘውግ ወይንም ኃይማኖት በሰላም፤ በነጻነትና በክብር የሚኖርበት ሁኔታ አይታየኝም።

በሌባኖን፤ በየመን፤ በተለይ በሳውዲ አረብያ በግፍ የሚሰቃዩት፤ በቅርቡ በሳውዲ አረብያ የተገደሉት ኢትዮጵያዊያን በዘውግ ወይንም በኃይማኖት ተለይተው አይደለም፤ በኢትዮጵያዊነታቸው፤ በድህነትና በስራ እድል ያለመኖር ቀውስ ባመጣቸው ምክንያቶች ነው። በማንነት ላይ ከማተኮር ይልቅ፤ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ብናስወግድ ኖሮ እንደ ሌሎች የበለጸጉ አገሮች በራሳችን አገር ተከብረንና ተፋቅረን ለመኖር እንችል ነበር። ማሌዢያ ልዩ ልዩ ኃይማኖቶችና እምነቶች አሏት፤ ችግሮቿን ፈትታ በመበልጸግ ላይ ትገኛለች።

ድህነትንና ኋላ ቀርነትን በዐማራው ሕዝብ ላይ መጫን ራሱ የኋላ ቀርነት አስተሳሰብን የሚያንጸባርቅ አመለካከት ነው። በተመሳሳይ፤ የዐማራ አክቲቪስቶች፤ ልሂቃንና ምሁራን መጠንቀቅ ያለባቸው ክስተት አለ። ይኼውም፤ ለዐማራው ሕዝብ ሆነ ለኢትዮጵያ ሁሉንም “ጠላት ነው” በሚል መፈክር ትግላችን ካስተጋባን ውጤታችን ያማረ አይሆንም። ለዐማራውና ለኢትዮጵያ ጠላት አናብዛባቸው የሚል ምክር አቀራባለሁ። በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ፤ የዐማራው ሕዝብና ኢትዮጵያ ብዙ ወዳጆች ስላሏቸው ትኩረታችን ከእነሱ ላይ እንዲሆን እመክራለሁ።

በቅርቡ የባልደራስ የውጭ ጉዳይ አካል አንድ ተስፋና አቅጣጫ የሚሰጥ መግለጫ አውጥቶ አነበብኩ። ስለ ህብረትና ስለ አንድነት ከጻፉ ምሁራን መካከል አንዱ እኔ ስለሆንኩ መግለጫው ሳበኝ። ህብረት ወሳኝ መሆኑን ካስተዋሉት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ባልደራስና መኢአድ ተመካክረው አንድ “ቅንጅትን” የሚመስል ክስተት ያስታወሰኝ  “ቅንጅትንም” ባይሆን ጥምረትን የሚመስል ፓርቲ መመስረታቸውን በአድናቆት ሰምቻለሁ። ባልተለመደ ደረጃ በእስር ቤት የሚሰቃየውን እስክንድር ነጋን ሊቀ መንበር፤ ማሙሸት አማረን ምክትል ሊቀ መንበር አድርገው ሰይመዋል። ይህ እመርታዊ የፖለቲካ አደረጃጀት ለውጥ ነው። በመግለጫው ላይ እንዳስታወቁት ተመሳሳይ ራእይና ዓላማ ያላቸው “ሌሎች ፓርቲዎች እንዲቀላቀሏቸው” ጥሪ ማድረጋቸው አግባብ አለው።

ሌላ ተስፋ የሚሰጥና አቅጣጫ የሚቀይስ ክስተት ስለሰማሁ ልጥቀሰው። በትህነግ/ህወሓት የተቀነባበረ፤ ተከታታይ ትውልድ የማይረሳው በዐማራው ሕዝብ ላይ የተካሄደው ግፍ፤ በደል፤ ጭካኔና ለም መሬቶችን እየነጠቁ የነዋሪዎቹን የሕዝብ ስርጭት ስር ነቀል በሆነ ደረጃ መቀየር (Systematic uprooting and change in the demographic composition of the indigenous population) የተካሄደው በወልቃይት፤ በጠገዴ፤ በጠለምትና በሰቲት ሁመራ ነው። ይህ ከመሬት ነጠቃ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ኢ-ሰብአዊና ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት አሁንም ይካሄዳል። እየነጣጠሉ ማጥቃት የተለመደ ዘዴ ስለሆነ፤ ለብዙ ዓመታት ይህን ግፍና በደል ለመቋቋም የሚቻለው ለአንድ ዓላማ በጋራ መታገል ብቻ ነው የሚለውን ድምጽ የሚያሰሙ ተቆርቋሪዎች ነበሩ፤ አሁንም አሉ።

ለአንድ ዓላማ መቆምና መንደርተኛነት አብረው አይሄዱም።

በቅርቡ ይህን ምክር ያጤኑትና ወደ ተግባር ለመለወጥ ቃል ኪዳን የገቡት የወልቃይት ጠገዴ የዐማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴና ልሣነ ግፏዓን በአንድነት ለመስራትና የነዋሪውን ሕዝብ ሰብአዊ መብት ለማስከበር የወሰዱት እርምጃ መደገፍ አለበት። ይህ ኩሩ፤ ቆራጥ፤ ጀግና፤ አገር ወዳድና በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን የዐማራ ሕዝብ ከትህነግ/ህወሓት መንጋጋ መጥቆ እንዲወጣ ማድረግ የተቀደሰ እርምጃ ነው።

በአንዲት አገር ዘጠና ዘጠኝ ፓርቲዎች እንዴት ይደጋገፋሉ?

እኛ ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይ ፊደል የቆጠርነው፤ ድርጅቶች መፈብረክ እንወዳለን፤ መስርተን ማፍረስ ልምዳችን ሆኗል። ተቻችለን መስራት ግን አልቻልንበትም። የፓርቲ ፋይዳ ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ አልተመለሰም።

በእኔ እምነት፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለመታደግ ከተፈለገ፤ በዘውግና በኃይማኖት የተመሰረቱ ፓርቲዎችን ህገ ወጥ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪ፤ ኢትዮጵያ ዘጠና ዘጠኝ ፓርቲዎች አያስፈልጓትም። የተበታተኑ ፓርቲዎች አቅም አይኖራቸውም፤ ለመላው ሕዝብ የሚጠቅሙ አማራጮችን ለማቅረብ አይችሉም። ብዛት ጥራትን አያሳይም። በዜግነት ላይ የተመሰረተ፤ በሃሳብ ልዩነት፤ ከብሄራዊ ራእይ፤ ተልእኮና ፕሮግራም ላይ በብልሃት የተዋቀረ ፓርቲ ለዲሞክራሲ ግንባታ ወሳኝ ነው። እውነተኛ የፖለቲካ ውድድር እንዲካሄድ ከተፈለገ ከአምስት የማይበዙ ተፎካካሪ ሊሆኑ የሚችሉ ሕብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች እንዲስፋፉና የሕዝብ ድጋፍ እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል።

በተጨማሪ፤ ፓርቲዎች ብቻቸውን ዲሞክራሳዊ ስርዓትን ለመመስረትና ለመደገፍ አይችሉም። ለሕዝብ አገልጋይና ደጋፊ፤ ባንዳንድ ሁኔታዎች ላይ ጠበቃ የሚሆኑ ልዩ ልዩ የሞያ፤ የወጣቶች፤ የሴቶች፤ የጥናትና የምርምር ወዘተ የመንግሥትና የፓርቲ ያልሆኑ ድርጅቶች በብዛት ያስፈልጋሉ።

ይህን ተከትሎ የምመክረው፤ እንደ አብን ያሉ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት፤ በዜግነት መብት፤ በፍትህ፤ በዲሞክራሲ ወዘተ ላይ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች ሁሉ እየተመካከሩ አዲሱን የባልደራስ-መኢአድ ፓርቲ ቢቀላቀሉ ድርጅታዊ አቅማቸውን ሊያጠናክሩ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንዲሉ፤ ዐማራውንና ሌላውን ወገኑን ከእልቂት ለማዳን፤ ኢትዮጵያን እንደ ሶርያ በእልቂትና በውደመት እንዳትበከል ለማድረግ፤ የባሰውን ልክ እንደ ዩጎስልቭያ እንዳትበታተን ለመከላከል ከተፈለገ ከህብረት ውጭ አማራጭ የለንም።

ይህን ካደረግን ኢትዮጵያን ከፍ እናረጋታለን። የኢትዮጵያ ጠላቶች ያከብሯታል፤ ሰርገው የሚገቡበትን በር ለመዝጋት እድል ይኖረናል።

በተጨማሪ፤ ለዐማራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፤ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት የቆሙ ኃይሎች በጋራና በመናበብ ጥሪ እንዲያደርጉ የምመኘው የሕገ መንግሥቱንና የክልሉን አስተዳደር መዋቅር ለውጥ አስፈላጊነት ትኩረት እንዲሰጡት ነው። ይህ ሕገ መንግሥት እና የክልል አስተዳደር እስካልተቀየሩ ድረስ ሰላምና እርጋታ፤ የሕግ የበላይነት፤ ፍትሃዊና ዘላቂነት ያለው ልማት አይቻልም።

እነዚህን አማራጮች ካቀረብኩ በኋላ ቀደም ሲል ወዳቀረብኩት የዐማራውን ሕዝብ “ትምክህተኛና ነፍጠኛ” ብሎ በመወንጀልት የእልቂት ኢላማ ማን አደረገው? ወደሚለው ትንተናየ ልሂድ።

መልሱን አግባብ ባለው መልኩ ለመረዳት ግን መጀመሪያ የዐማራው ሕዝብ መለያዎች ምንድን ናቸው? በሚለው ጥያቄ ላይ የእኔን ግንዛቤ ላቅርብ፤

 1. ቅድመ አያቶቻቸው ለብሄራዊ ነጻነቷና አንድነቷ ለብዙ ሽህዎች ዓመታት ታግለው ከሌሎች የዘውግና ኃይማኖት አባላት ጋር ተዋልደውና ተዛምደው በመሰረቷት በመላው ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቴ ተከብሮ የመኖር መብቴ መከበር አለበት የሚል የኢትዮጵያዊነት መለያ ያለው ሕዝብ መሆኑ፤

 

 1. በአብዛኛው፤ የዐማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ፤ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስትያን እምነት ተከታይ መሆኑ፤ የራሱን እምነት ተቀብሎ ግን የሌላውንም ወገኖቹን አክባሪና አስተናጋጅ መሆኑ፤

 

 1. በታሪኩ ከኤርትራ ጀምሮ እስከ ሃረርጌ፤ ከጎንደር እስከ ባሌ፤ ከወሎ እስከ ጋምቤላ ወዘተ ለብዙ ሽህ ዓመታት በተደረጉት የሕዝብ እንቅስቃሴዎች ዘውግና እምነት ሳይለይ፤ ከሌሎቹ በኢትዮጵያ ከሚኖሩ ወገኖቹ ጋር ትሥስር የፈጠረ፤ ከሁሉም በላይ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር መሆኑን የተቀበለ መሆኑ፤

 

 1. የሚፈልገውና የሚመኘው ሰብእነቱ ታውቆ፤ የግለሰብ መብቱ በሕግና በተቋማት ያለምንም ገደብና አድልዎ ተከብሮ፤ ጥሮ፤ ግሮ ራሱን፤ ቤተሰቡንና አገሩን ከድህነት አሮንቃ አውጥቶ መኖርን ብቻ መሆኑ፤

 

 1. “እኔ የኢትዮጵያዊነት መለያየ፤ የሰብአዊ እና የዜግነት መብቴ ተከቦሮ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልፍ በሰላምና በክብር ልኑር፤ ሌላው የዓለም ሕዝብ ከደረሰበት ደረጃ ልድረስ” እያለ ድምጹን የሚያሰማ ሕዝብ መሆኑ፤

 

 1. ፊደል፤ የቀን መቁጠሪያና ሌሎች የዓለም ሕዝብ ያደነቃቸውን መለያዎችን ፈጥሮና ለመላው የጥቁር ሕዝብ ሥልጣኔ አስተዋጾ ያደረገ ሕዝብ መሆኑ ይገኙበታል።

በእነዚህ የዓለም ሕዝብ፤ በተለይ የጥቁር ሕዝብ ባደነቃቸው እሴቶች ምክንያት የዐማራው ሕዝብ መወገዙ፤ መጨፍጨፉ፤ “አገር አልባ” እንዲሆን በተከታታይ መገደዱ ለራሱ ህልውና ብቻ ሳይሆን፤ ለኢትዮጵያም ቀጣይነት አስጊ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። የማስታውሰው የጣሊያን ፋሺስቶች ኢትዮጵያን እንዲወሯት ያመቻቹት ምሁራን “የዐማራውን ሕዝብ” በተለየ ደረጃ እንዲፈራና እንዲወገዝ ኮንነውት ነበር። ትህነግ/ህወሓት እና ኦነግ ሽኔ፤ ጃዋር ሞሃመድ፤ የዘውግ ጽንፈኞችና ጅሃዲስቶች የተከተሉት መርህ ተመሳሳይ ነው።

ህወሓት መሸገ እንጅ አልተለወጠም

ወደ መቀሌ ሂዶ የመሸገው ህወሓት በወልቃይት ጠገዴ፤ በጠለምት፤ በሰቲት ሁመራ፤ በዋልድባ ገዳም አካባቢ በሚኖሩ የዐማራ ሕዝብ አባላት ላይ ትልቅ ወንጀሎችን ሰርቷል። የዚህ ወንጀለኛና “የቀን ጅቦች” ቡድን በእልቂትና በመሬት ነጠቃ ብቻ መገምገም በቂ አይደለም። የመሰረታቸው ተቋማትም መፈተሽ አለባቸው። ከተከላቸው ጠንቆች መካከል የፖለቲካ ድርጅቶች ክፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፤ አሁንም ይጫወታሉ። ለምሳሌ ትህነግ/ ህወሓት የራሱን ዘውጋዊ ጥቅም በአስተማማኝነት በውክልና እንዲሰራለት ከፈለፈላቸው ድርጅቶች መካከል በዐማራው ስም ኢህአፓና ትህነግ በጋራ ተመካክረው ያቋቋሙት “የዐማራ ብሄራዊ ዴሞክራሳዊ ንቅናቄ ( Amhara National Democratic Movement) ይገኝበታል። ይህ በዐማራው ስም የተመሰረተ የፖለቲካ ድርጅት በቅርብ ቢገመገም ዋናው ስራው በረከት ሰምዖንና ታማኝ የሆኑ ዐማራዎች ለህወሓት እንዲያገለግል ታዛዥ አድርገው የተጠቀሙት ድርጅት ነበር።

ይህ ድርጅት ስሙን ቀይሮ የዐማራ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (አዴፓ) እንደተባለ አውቃለሁ። ራሱንም ለመለወጥ እንደሞከረም ይነገራል።  ዛሬ የሚጠራበት ስም የዐማራ ብልጽግና ፓርቲ ተብሎ ነው። ፓርቲዎች ስማቸውን መቀየራቸው የተለመደ ነው። ስም ሲቀየር ግን መሰረታዊ የሆኑ የፖሲሲና ፕሮግራም፤ የአመራርና የአባላት አመራረጥና ስርጭትም አብረው የሚካሄዱበት ሁኔታ አመላካች ምልክቶች ይኖራሉ። ይህ እንዳለ ሆኖ፤ እኔ የምከራከረው ዛሬ “ራሱን በቀየረው ፓርቲ” ላይ ያለውን ሁኔታ በሚመመለከት አይደለም። ከምስረታው ትኩረትና በዐማራው ሕዝብ ላይ ከተከሰቱት ስህተቶችና ጥፋቶች ላይ ነው። ጥፋቶች ከተሰሩ ይህን አምኖ የዐማራውን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ አግባብ አለው።

ታላቁን፤ ጀግናውን፤ ጨዋውን፤ እንግዳ አስተናጋጁን፤ መንፈሳዊውን ወዘተ የዐማራውን ሕዝብ ባልፈጸመው ወንጀል አግባብ የሌለው በደል መሆኑን የኤርትራው ፕሬዘደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ፤ የሶማሌው ክልል ፕሬዝደንት ወጣቱና በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምነው ሙስታፋ ኦመር አሳስበዋል። መሪ ማለት ስህተትን ማመን ጭምር ነው።

የትግራይ ድንበር ተከዜ ነው

የዐማራውን ሕዝብ “ትምክህተኛና ነፍጠኛ” ያሉ የብአዴን መስራቾች፤ መሪዎችና አባላት ከላይ ከጠቅስኳቸው ሊማሩ ይገባል። በተጨማሪ፤ ዛሬ የዐማራውን ክልል የሚመራው የዐማራ ብልጽግና ፓርቲ በወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ፤ ራያና አዘቦ ላይ የሚከተለው ፖሊሲ ቆራጥና የማያሻማ መሆን አለበት። ምክንያቱም፤ የእነዚህ ለም መሬቶችና የነዋሪዎቹ ዐማራዎች የወደፊት እድል ከዐማራው ህልውና ጋር የተያያዘ ነው።

በሶሻል ሜድያና በሌላ እንደሚነገረው ሁሉ፤ የጎንደር ዐማራን ሕዝብ ከሚያስጨንቀውና ከሚያስቆጣው መሰረታዊ ችግሮች መካከል ህወሓት/ትህነግ የጎንደርን መሬት ለመንጠቅ በቀየሰው የመስፋፋት ዘዴ ድንበሩን ከተከዜ ለማሻገር ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጉ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ መስዋእት ተከፍሏል፤ አሁንም እየተከፈለ ነው። ጥናቶችና ምርምሮች በማያሻማ ደረጃ የሚያሳዩት የትግራይ ወሰን ተከዜ መሆኑን ነው።

ስለዚህ፤ የዐማራው የብልጽግና ፓርቲ አቋም በማያሻማ ደረጃ ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ፤ ራያና አዜቦ የዐማራ ክልል አካል መሆናቸውን ይፋ የማድረግ ውሳኔ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው። ትግራይ ነገ ጥዋት የመገንጠል አዋጅ ቢያውጅ እነዚህ መሬቶች የታላቋ ትግራይ ናቸው ማለቱ የማይቀር ነው።

በእኔ እምነትና ጥናት፤ ጠቅለል አድርጌ ስለመለከተው፤ በአገር ቤትም ሆነ ውጭ የምንኖር ዐማራነታችንና ኢትዮጵያዊነታችንን አጣምረን የምንቀበል ሁሉ መረባረብ ያለብን የዐማራው ሕዝብ ጠላቶች በሚወረውሩልን አጀንዳ በማስተናገድ አይደለም። የእንሱ አጀንዳ ዐማራውን ጎድቶታል። እንደ ዐማራው ምሁር፤ ባለሞያና ሌላ የሚሰበሰብ፤ አንዱን ድርጅት አፍርሶ ሌላ የሚፈበርክ፤ ሌላውን ወንድም እህቱን በጥራጣሬ የሚገመግም፤ የሚተች፤ በየኪሱ የራሱን ዘውድ ይዞ ለጋራ ዓላማ በቆራጥነት በመታገል ፋንታ የሚሰራውን ወገኑን የሚያማ፤ የራስክን መሪዎች ተንከባከብ ሲባል “እሱ ማነውና” ብሎ ለሌው የማያጎበድድ፤ በተለይ በውጭ ከምንኖረው መካከል ፈልጌ አላገኘሁም። መንደርተኛነት፤ ጎጠኛነት፤ ቂም በቀልነት የዐማራውንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ይጎዳል። በሌላ በኩል፤ ብቅንነት መተቸትና ገንቢ አማራጮችን ማቅረብ ጨዋነት ነው። በጭፍንና በጅምላ ሁሉን ነገር መቃወም ደግሞ የሚረዳው ዐማራውንና ኢትያኦጵያን አይደለም፤ ጠላቶቻችን ነው። ግብፅን፤ ህወሓትን፤ ኦነግ ሸኔንና ጀሃዲስቶችን ጨምሮ።

የዐማራውን ተቆርቋሪ ህወሓትና ኦነግ ሽኔ የሚበልጡት ለዚህ ነው። ቢያንስ ቢያንስ እነዚህ ድርጅቶችና መሪዎቻቸው ለአላማቸው ስኬት በአንድ ላይ ይሰራሉ፤ ስህተታቸውን ይሸፋፍናሉ። ሰርቀውም፤ ገድለውም ሽፋን ያገኛሉ። ለምሳሌ፤ ወዳጀ፤ ፕሮፌሰር መራራ ወደ አሜሪካ ሲመላለስ “ስንቅ” ስጡኝ፤ እኔ ለፍትህ እታገላለሁ” ይለን ነበር፤ እኛም የተቻለንን እናደርግ ነበር። ፕሮፌሰር መራራ ሽንጡን ገትሮ ሕግ የጣሱትን፤ አመፀኞችን፤ ጽንፈኞችን፤ ጠባብ ብሄርተኞች ይፈቱ ብሎ ሲከራከር ስሰማ ለሱ አፈርኩለት። ይህ እንዳለ ሆኖ አሁንም ቢሆን፤ እኔ ፕሮፌሰር መራራን የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን ጠላት ነው አልልም። ራሱ በስህተቱ ይጨነቅበት እንጅ እሱን ወደ መተቸቱ አልገባም። ምክንያቱም ለኢትዮጵያና ለዐማራው ሕዝብ ጠላት ለማብዛት አልፈልግም።

የዐማራው ሕዝብ በመላው ኢትዮጵያ የሚኖር፤ ከሌላው ጋር የተጋባ፤ የተዛመደ፤ አገር ወዳድና ቆራጥ ሕዝብ ነው። ተጋልጦ የሚጠቃው በመላው ኢትዮጵያ ስለሚኖር፤ ስለሚሰራና በተለይ አገር ወዳድ በመሆኑ ነው። ይህ ሁኔታ ብዙ ጠላቶችን ፈጥሮለታል። ሁኔታውን ካወቅን መፍትሄውንም አብረን መፈለግ አለብን፤ ለምሳሌ ወዳጅ እየፈለግን ወዳጁን እናስፋፋለት።

ግብጾች በተለየ ደረጃ ለዐማራው ሕዝብ ፍቅር አያሳዩም። ብዙ ምክንያቶች ለመደርደር እችላለሁ። ከሁሉም በላይ ግን ሰብሳቢው ምክንያት የዐባይ ወንዝ ነው። የሕዳሴ ግድብ ውዝግብ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ከፈርዖኖች ዘመን የጀመረ ታሪክ አለው።

ህወሓት ዐማራውን በጠላትነት በይኖታል። መሬቱን ይፈልገዋል። ሕዝቡን ይጠላዋል። ኦነግ ሽኔና ጅሃዲስቶች፤ ግብጽን ተገንና ደጋፊ አድርገው በተመሳሳይ ደረጃ ዐማራውንና የዐማራውን ተቋማት ፈጽሞ ከምድር ለማጥፋት ከወሰኑ ቆይቷል። በተለይ፤ ጅሃዲስቶች ዐማራውን እንደ ዘውግ፤ ኃይማኖቱንና ሌሎቹን መለያዎቹን በመጨፍጨፍና በማውደም ላይ ናቸው። ባጭሩ ይህ ሕዝብ መፈናፈኛ እንዳይኖረው የተቀነባበረ ሴራ እየተካሄደበት ነው።

የዐማራውን ሕዝብ ለመታደግ እውቀት፤ ድርጅት፤ መረጃ፤ ህብረት ወሳኝ ነው። ብአዴን ሲመሰረት የነበረውን ሁኔታ ተመራምሬ በአጭሩም ቢሆን ለማሳየት እንደሞከርኩት፤ እውቀትና ለሌላው ማጎብደድ ወይንም አድርባይነት አብረው አይሄዱም።

የዐማራው ሕዝብ መሰረታዊ ችግር ምንድን ነው? በሚለው ጥያቄ ላይ የጋራ ግንዛቤ ቢኖረን ቢያንስ ቢያንስ ይህ ታላቅና አገር ወዳድ ሕዝብ ህልውናው እንዲቀጥል የምንችልበት ሁኔታ አለ። ይህን በክፍል ሶስት አቀርበዋለሁ።

 

October 6, 2020

4 Comments

 1. Amaras way of thinking is the past. For Ethiopia to move into the future there needs to be less Amara way of thinking and more of civilised modern way of thinking. If we stick to the Amaras way of life then we might as well forget the growth and transformation plan. Amaras need to open up their minds.

 2. There is no genocide and Crimes Against Humanities in Kenya . Comparing the situation in Ethiopia as if it is similar to the situation in Kenya as some try to do is very dangerous because comparing the situations I’d n Kenya and Ethiopia is similar to comparing an atomic bomb to a hand grenade. Both nuclear bomb and a hand grenade are bombs but the severity of the damages they cause are not comparable . Only foolish individuals or those who perpetrated and keep benefiting from the ongoing Crimes Against Humanities diminish the situation in Ethiopia as just another ethnic violence.

  Patience is running out for the victims who suffered for way too long. That is why we all need to come to the solution by first and foremost admiting there is an ongoing genocide and ethnic cleansing in Ethiopia. Diminishing the danger in Ethiopia by claiming it is just another ethnic violence similar to some African countries such as Kenya went through is similar to seeking medication of an airborne allergy while the patient is on the verge of death sick from CoronaVirus.

 3. አማራ ለ ጥቃት የተጋለጠው እራሱን ሲከላከል የ ሰው ሕይወት በ እጁ እንዲያልፍ ስለማይፈልግ ነው። የዚህም ምንጩ ኦርቶዶቅስ ሃይማኖታችን ነው። ሰው ከ ገደልክ ጽድቅ አትገባም እያሉ ሲያስተምሩን ኖረዋልና። የ ሃይማኖት አባቶቻችን መስዋዕት ሁን እንጂ እራስህን ተከላከል ብለው ስለማያስተምሩ ለ አደጋ እንድንጋለጥ ሆነናል። ከዚያም በተጨማሪ አማራ በጣም ሰብአዊ ስለሆነ ነፍስ ማጥፋትን እጅግ ይጸየፋል። ችግራችን አስተሳሰባችን ነው። ሌሎችም የሚጫወቱብን ይህን አስተሳሰባችንን ስለሚያውቁ ነው። ከ ዕልቂት ለመዳን የ ሃይማኖት አባቶችን አስተምህሮ ችላ ብሎ ተባብሮ በ መቆም ህልውናን ለ ማረጋገጥ መዋደቅ ነው።

 4. “የአማራውን ህዝብ ለመታደግ ፣ እውቀት ፣ድርጅት ፣ መረጃ ፣ህብረት ወሳኝ ናቸው።”ትክክል ዶር አክሎግ ።
  በአሁኑ ሰዓት የአማራውን ህዝብ ለመታደግ ሕብረት ለመፍጠር ትልቆቹ እንቅፋቶች ሶስት ናቸው ። ብአዴን ፣ ኢዜማአና በድርጅቶቹ ያሉ የህወሓትአና የኦነግ ሠርጎ ገቦች ናቸው ።ኢዜማ እንደ ብአዴን “አማራውን ለማጥፋት ከተዘጋጁት ኃይሎች ጋር (ኦነግ ፣ኦፒዲ)ተባብሮ ይሠራል ።ከብአዴን ጋርም እንደዚሁ ። የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዞ ኢትዮጵያን ለሚያደርሱት ድርጅቶች ጋር በጥብቅ ተባብሮ እየሰራ ነው።
  ኢትዮጵያን ለማትረፍ የአማራውን ሕልውና ለመታደግ ሕብረቱ መቋቋሙ አይቀሬ ነው።ግን እነዚህን የግብፅን ቅጥረኞች ለማሸነፍ “እውቀት ፣ድርጅት መረጃ ያስከፍልጋል።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.