“የሽግግር መንግሥት ይቋቋም” ከሚክያስ

Nobel ethiopian registrarየፓርቲ ድርጅቶችን ጠፍጥፎ በመስራት ረገድ እንደ ሕወሃት ያለ የጭቃ መሃንዲስ የለም። አማራውን ይወክላል የተባለው ኢህዲን ወይም ብአዴን ከመረሬ ጭቃ ነው የተሠራው። ኦሮሞውን ይወክላል የተባለው ኦሆዲድ ከቀይ አፈር ጭቃ ነው እነደ ቂጣ ተጠፍጥፎ የተጋገረው። የደቡቡ፣ የሶማሌው አጋር የተባሉት ሁሉ ካካባቢው ጭቃ ነው የተቦኩት። እነዚህ የጭቃ አጋሰሶች ከፊት ለፊት የሚታያቸውን መኖ እየተከተሉ ህወሃትን ለሰላሳ ዓመታት አገለገሉ። ሁሌ ጠፍጥፎ አደር መሆን የለምና፣ ሕወሃት ራሱ ጠፍጥፎ ከሰራው ማህል አንዱ የነቃው አደናግሮ ፈነገለው። “ጠፍጥፌ የሠራሁትማ ጠፍጥፎ አይሰራኝም” ሲል እልህ የተናነቀው ሕወሃት ወደ መቀሌ ፈርጥጦ በተራው ዋነኛ ተቃዋሚ ሆነ። አዲስ አበባን ፊንፊኔ እስከ ማለት የደረሰው ሕወሃት ራሱ ድሮ የሚፈጽማቸውን ሁሉ መቃወም የጀመረ ነፈዝ ሆኗል።

ዶክተር አብይ ኦህዲድን ለሁለተኛ ጊዜ ጠፍጥፈው ጠርበው ስሙን ኦዴፓ ብልጽግና አሉት። አዲሱ ኦዴፓ (ODP) ጠፍጣፊ ሆኖ ኢሕዴን-ብአዲንን እንደገና ጠፍጥፎ አዴፓ (ADP) ብልጽግና አለው። ኦህዴድ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ተጠፍጥፎ የተሠራው “አማራውን ወክያለሁ” እያለ የሚቃዠው የቀድሞው ኢሕዴን ሶስተኛ ጊዜው ነው ተጠፍጥፎ ሲሰራ። ኢሕዴን – አዴፓ ብልጽግና እስኪባል ድረስ ብዙ ጊዜ ተጠርቧል። “አማራው ጀግና ነው ጥፍጥፎች አይመሩትም” ያለው ጄኔራል በሴራ ከተወገደ በኋላ በታማኝናት የሚያገለግለው አዴፓ ዛሬ የኦዴፓ ካባ አልባሽ ሆኗል። ኦዴፓ ብልጽግና ባለጊዜና ተረኛ ሆነ።

ተረኛውን ባለጊዜውን ኦዴፓ (ODP) ብልጽግና ዶግ አመድ ለማድረግ የሚጥረው “ተጠፍጥፌማ አልሰራም” በሚለው አቋሙ የጸናው ሕወሃት ሌሎች የወንበር ሱሰኞችን እየገዛ በደሃው ሕዝብ ላይ በደሎችን እየፈጸመ ነው። የምስኪኑ አማራ ገበሬ ልጆች የሆኑ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎችን አሳፍኖ ከማስወሰድ አንስቶ በኦሮምያ ምድር የሚገኙ አማራና ኦርቶዶክስ ክርስትያኖች ለማውራት ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ በግፍ እስኪጨፈጨፉ ድረስ ሕወሃት ረዥም እጆች አሉት። ሕወሃት ግብረ አበሮቹን እያስተባበረ ኦዴፓ ብልጽግናን ፋታ አሳጥቶታል። “ሁለት ዝሆኖች ሲታገሉ” እንደሚባለው በሕወሃትና ብልጽግና መሃል ባለው የሥልጣን ትንቅንቅ መሃከል የተጎዳው አይዞህ ባይ፣ አዳማጭ፣ ተከላካይ የሌለው ሃገሬ ብሎ በየቦታው የሰፈረው አማራ ነው። እግዚአብሄር ግፉን በቃ እስኪል ድረስ አማራው እጆቹን ወደ ላይ ዘርግቷል።

ተረኝነት እንጂ ለውጥ በሌለበት ሁኔታ ቢዳክሩ ድካም ነው ትርፉ። “የሰበሩንን ሰበርናቸው” ከሚለው እስከ “ኦሮሞን እንገነባለን፣ ኢትዮጵያን እንደግፋለን” ድረስ የተረጨው ቅርሻት ሃገሪቱ አሁን ድረስ የቅርሻት መድሃኒት እንዳላገኘች ማሳያ ነው። በኦሮምያ ውስጥ ያለውን ሌብነትና ዘረፋ ማምከን ያልተቻለው ኦዴፓ ግድ ስለሌለው ነው። የኦሮምያ የስርቆት ባህል እንዲቀጥል የሚሹ ሁሉ -ጉዳይ አስፈጻሚ የሚባለው – ባለ ጉዳይንና የግብር ሰብሳቢዎችን፣ ባንኮችን፣ ማዘጋጃ ቤቶችን፣ ወዘተ፣ የሚያገናኘው የሙስና ድልድይ እንዲፈርስአይፈልጉም። ተገልጋዩ ቢንገላታ ኦዴፓ (ODP)ብልጽግና ምን ቸገረው? “ግብርህ ስምንተ መቶ ሺህ ብር ነው – አራት መቶ ብር ሺህ ብር ላስደርግልህና አንድ መቶ ሺህ ብር ስጠኝ” የሚሉት ሶስተኛ ወገን መዝባሪ አስመዝባሪ ፋይል አጋቾች፣ የዓመታት የሌብነት ልምድ ስላላቸው እነሱን አደብ ለማስገዛ ኦዴፓ (ODP) ብልጽግና ቁርጠኝነት የለውም። ኦዴፓ ብልጽግና በከንቱ ስብሰባ ስም የሚባክነውን አላስፈላጊ ወጪ እንኳን የማስቆም ኃይል የለውም። የየቢሮዎቹን መዛግብት አቀማመጥ ሳይቀር የሚያውቁት የኦሮምያ ምድር ቀማኞች ለሆድ አደሩ ባለሥልጣን “መቶኛ ድርሻውን” እያስታቀፉ ፍትህን ያስጨፈልቃሉ፣ ድህነትን ያስፋፋሉ፣ ሥራ አጥነትን ያበዛሉ። ኦዴፓ-ብልጽግና የራሱን አባላት ጠባይ ሳያርም እንደምን ለውጥ ማምጣት፣ ፍትህን ማስፈን፣ ደሃውን ቀና ማድረግ ይቻለዋል?

ንጹህና አገር ወዳድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጅግ ጥቂት ስለሆኑ ነው ይህ ሁሉ ምስቅልቅል። አብዛኛው የሚንሰፈሰፈው ለወንበሩ ነው። ወንበሩን የፈለገው ሃገሪቱን በሥርዓት ለማስተዳደር ሳይሆን ተረኛ ሆኖ ለመመዝበር ነው። ስርቆትና ምዝበራ ነውር መሆናቸውን የሚያስተምር አንድ ኃይል ያስፈልጋል። መስረቅ፣ ቅሚያና ሙስና የምጣኔ ኃብት ስልት ወይም ከድህነት አበሳ መገላገያ የሚመስላቸው ዘራፊዎች ካልተማሩ አልያም ካልተወግዱ በቀር ሙስና እንደ ጦር ትሾላለች። ብናስተውል ግን ሠርቆ የከበረ ሁሌም ደሃ ነው። በቅሚያ ወርቆች ያጌጠች ሴት አያምርባትም። የመስቀል በዓል እንዳይከበር ተከልክሎ ለእሬቻ ቢፈቀድ እግዚአብሄር ያያል። የኢትዮጵያን ባንዲራ አትያዙ ብሎ ለኦነግ ባንዲራ ቢፈቀድ የሚጎዳው ራሱ ፈቃጁ አካል ነው። ቀኑን ጠብቆ ሁሉም እንደ ጠዋት ጤዛ ይረግፋል። ማንም በራሱ የሚመካ ሁሉ ፍጻሜው ከእግዚአብሄር መጣላት እንዳይሆን ቢጠነቀቅ ይሻለዋል።

ዶክተር አብይ ኢትዮጵያን ከወደዱ – አሁንም አልመሸም ትልቅ ታሪክ ሊከውኑ ይችላሉ። ዶክተር አብይ ይመለከተኛል የሚሉትን የፖለቲካና ሕዝባዊ ድርጅቶች፣ ምሁራን፣ በሕዝብ የሚመረጡ የሃገር ሽማግሌዎችንና አባ ገዳዎችን፣ አዛውንቶችንና የኃይማኖት አባቶችን፣ ንቁ ወጣቶችንና ታዋቂ ግለሰቦችን፣ ለሕዝብ ሲሉ እየታገሉ ያሉ ሃቀኛ መምህራን ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ተዋንያን፣ ከያንያን፣ ወዘተ፣ አሰባስበው መፍትሄ ሲያፈላልጉ ትልቅ ሥራ ሠሩ ማለት ነው። ማንም ነገ ለይስሙላ በሚዘጋጀው ምርጫ ላይ አሸናፊ ቢሆንም ኢትዮጵያን ፋታ አግኝቶ ሊያስተዳድራት አይችልም።ዶክተር አብይ – “ይቀናቀኑኛል” የሚሏቸውን የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች አስረው አሸናፊ ቢሆኑ ሕዝብ ወዶ ፈቅዶ የሚገዛሎት ንጉሥ አያደርጎትም። ሃገሪቱ መፍትሄ የምታገኘው በሳልናማስተዋልን የለበሱ አዋቂ ሰዎች ተወያይተው፣ ተማምረው፣ ተማምነው ከራስ ወዳድነትና አድር ባይነት የጸዳ እውነተኛ የሽግግር መንግሥት ሲያቋቁሙ ነው። የሽግግር መንግሥቱ የሕዝባዊ መንግሥት መሠረትን ያነጥፋል። ኢትዮጵያ ከፍ አለች ማለት ይህን ጊዜ ነው።

ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች!

 

2 Comments

  1. Mikiyas Middle man! You do not have clear stand and no evidence for your article. Hasty generalization!

  2. ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ እንድትሻገር ራዕይ ያለው መሪ አልተገኘም።ሁሉም ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚለው አገሩን የሚወደውን ዜጋ እያማለለ እና እያደነዘዘ የነገድ የፖለቲካ ዓላማውን ለማሳካት በቅንጅት እየሠራ ነው።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.