የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያምን ነፍስ በአፀደ ገነት ያኑርልን ሞትን ከስሻለሁ (ዘ-ጌርሣም)

Mesfin Woldemariamማንስ ሊያደንቀው ነው
ደግ አደረክ ሊለው
አፈሩ እንድሆነ አያመሰግነው
ሞትን ከስሻለሁ

ገና በለጋነት በወጣትነቱ
በተቀበረበት የህፃን ዕትብቱ
ሩጦ ሳይቀድም
ገና በልቶ ሳይጠግብ
ታግሎ ሳያሸንፍ
ልዩ ልብ ተሰጥቶት የምትንሰፈሰፍ
ከወዲሁ ገብቶት
ግዴታና መብት
የፍትህ ምንነት
የሕዝብን መጨቆን
ረሃብ ጥማቱን
ቀድሞ ስለገባው
መፍትሄው አንድ ነው
አማራጭ የሌለው
በማለት ቆረጠ
ልቡን አሳመጠ
መታገል መረጠ
ቃሉን ለቃል ምሎ
ገባበት በይፋ
ሊደክም ሊለፋ

ማንስ ሊያደንቀው ነው
ደግ አደረክ ሊለው
አፈሩ እንድሆነ አያመሰግነው
ሞትን ከስሻለሁ

ተሟግቶ ሳይረታ ጭራሽ ላይመለስ
በማይሆን ሽንገላ ያለመለሳለስ
ቀጠለች ህይወቱ መረጠች እንግልት
የከፋ ቢመጣም እጅን ላለመስጠት
በገባው ቃልኪዳን ራሱን ተማምኖ
ጽናቱን አሳይቶ ሕዝብን አሳምኖ
ሲታገል ሲያታግል በእንግልት ኖረና
ይኸው ዛሬ አለፈ ኖረ ተባለና
ሞት የሚባል ዕዳ
የማይቀረው ፍዳ
አመስጋኝ የሌለው
ሁሉም የሚጠላው
ምን ያደርግለታል
ምንስ ጎሎበታል
ሞልቶት ተትረፍርፎት
የኖረውን ትቶ ያልኖረ እሚጎትት

ማንስ ሊያደንቀው ነው
ደግ አደረክ ሊለው
አፈሩ እንድሆነ አያመሰግነው
ሞትን ከስሻለሁ

እንዴት በባዶ ቤት ተከፍቶ በኖረው
ማንም በሌለበት አንድ ቢኖር በላው
ሞትን ከስሻለሁ
ጠበቃ ገዝቸ እሟገተዋለሁ
ምስክር አልሻም እኔው እበቃለሁ
ያልተጋፋውን ሰው ሲበላ እይቻለሁ
ትልቁ ችግሬ ዳኛ ማግኘቱ ነው
ሞትን ሙት በማለት የሚፈርድልኝ ሰው

ማንስ ሊያደንቀው ነው
ደግ አደረክ ሊለው
አፈሩ እንድሆነ አያመሰግነው
ሞትን ከስሻለሁ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.