/

የዐማራው ሕዝብ እልቂት ኢትዮጵያን ያጠፋታል (አክሎግ ቢራራ (ዶር))

“ዐማራን እየገደሉ ኢትዮጵያን መግዛት የከሰረ ፖለቲካ ነው”
የጎንደር ሕዝብ በሰላማዊ ሰልፍ ያሰማው መፈክር
“በእኔ ዘመን አሳዳጅና ተሰዳጂ አይኖርም”
ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አሕመድ አሊ

Genocide 2

ክፍል አንድ

ከፍተኛ ትኩረት ከሰጠሁት ከሕዳሴ ግድብ ትንተናና ሙግት ወጣ ብየ ይህን ግምገማና ምክሮቸን ለማቅረብ ምን አስገደደኝ?

ሰሞኑን በመተከል አካባቢ፤ በቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ በዐማራውና በአገው ንጹህ ኢትዮጵያዊያን ላይ፤ ህጻናትን፤ ወጣት ሴቶችን፤ እናቶችንና ሽማግሌዎችን ሳይለይ የተካሄደው ዘውግ ተኮር እልቂት እጅግ አናዶኛል፤ አሳስቦኛል፤ አስቆጥቶኛል፤ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ያለኝን ጽኑ እምነት ተፈታትኖታል።

በእኔ ግምገማና እምነት ይህ እልቂት ሊወገድበት የሚያስችልበት እድል ነበር። ምክንያቱም፤ ማስፈራራቱ፤ ዛቻው፤ እንቅስቃሴው፤ አካባቢው የሽብርተኞች ምሽግ መሆኑ፤ በቀስትና በጦር በተደጋጋሚ የተደረገው የጭካኔ ግድያው፤ አፈናው ወዘተ ዛሬ የተጀመረ አይደለም። በሌላ አነጋገር፤ ብዙ ምልክቶች ነበሩ። ከዚህ አንጻር ስመለከተው፤ ለእኔ ጥያቄው ለምን ቸል ተባለ? የሚለው ነው።

የዚህ ትንተና መሰረት በዐማራው ሕዝብ ላይ በተከታታይ የተካሄደውና አሁንም ቀይ መስመር የሌለው አፈና፤ ብሄርና ኃይማኖት ተኮር ግድያ፤ መፈናቀል ወዘተ መንስኤውና መፍትሄው ምንድን ነው? የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ ለመመለስ መሞከር ብቻ በቂ አይደለም። ይህን ግምገማ ካደረግን በኋላ ማልቀሱ ብቻ በቂ አይደለም ብለን እልቂቱ እንዳይደገም እየተናበብንና እየተባበርን ወደ ተግባር የምናተኩርበት ጊዜ ነው።

ልዩ ልዩ አካላት ባወጧቸው መረጃዎች መሰረት ብቻ፤ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር፤ ከሰኔ 2012 ዓ.ም ወዲህ፤ በዐማራውና በሌሎች ኦሮሞና ክርስቲያን አይደሉም በሚል መስፈርት ብቻ በኦሮምያ አካባቢ ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ወገኖቻችን ተጨፍጭፈዋል። ሰማንያ በመት (80 percent) የሻሸመኔ ከተማ ወድማለች።

 

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይ እናቶችና አባቶች በለቅሶ ላይ እንዳሉ፤ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በመስከረም 2013 ዓ.ም. አብን በመሰጠው መረጃና ሌሎች ባስተጋቡት መሰረት፤ በቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ መተከል አካባቢ “160” የሚሆኑ ዐማራዎችና አገዎች ተጨፍጭፈዋል፤ ብዙዎች ወገኖቻችን ከቤትና ከንብረታቸው ተፈናቅለዋል። የክልሉ፤ የዐማራው ክልልና ልዩ ልዩ የፌደራሉ ባለሥልጣናት ወደ አካባቢው መሄዳቸው አግባብ አለው እያልኩ፤ ችግሩ እንዳይደገም ትኩረት እንዲሰጠው ጥሪየን ከአደራ ጋር አቀርባለሁ። ከሁሉም በላይ እልቂቱን ሊከላከል የሚችለው ነዋሪው ሕዝብ ስለሆነ አቅሙን ማጠናከር ወሳኝና አስቸኳይ መሆኑን አሰምርበታለሁ።

ብዙ ጊዜ ትንተናዎችን ሳቀርብ ችግሩ ምን እንደሆነ ካሳየሁ በኋላ መፍትሄዎቹን አቀርባለሁ። ይህን ዘገባ ግን በመፍትሄ እጀምራለሁ።

የዐማራው ሕዝብ ታላቅ፤ ራሱን አክብሮ ሌላውን የሚያከብር፤ ከሌሎቹ የዘውግ አባላት ጋር ተጋብቶና ተዛምዶ የሚኖር፤ በታሪኩ የሚኮራ፤ ለሃገሩ ለኢትዮጵያ ነጻነት ከወገኖቹ ጋር ሆኖ ከፍተኛ መስዋእት የከፈለ፤ በጨዋነቱ የዓለም ሕዝብ ያደነቀው፤ አገር ወዳድና ታታሪ ሕዝብ ነው። እኔ የዐማራውን ሕዝብ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዌነት መለያዎቻችንና እሴቶቻችን ለይቸ ለማየት አልችልም።

እኔ እስከማውቀው ድረስ፤ የዐማራው ሕዝብ በመላው ኢትዮጵያ በኢትዮጵያዊነት የዜግነት እሴቱና መብቱ ተማምኖ፤ እየታገለና ከሌላው ወንድምና እህቱ ጋር ተጋብቶ፤ ተዋልዶ፤ ተዛምዶ፤ ተፋቅሮና ተቻችሎ

የሚኖር ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ ነው። በመሆኑንም፤ ህወሓት/ኢህአዴግ የብሄርና የቋንቋን ልዩነቶች ትርክትና ሌሎች የጥቁር የአፍሪካ መንግሥታትና ሕዝቦች ንቀውት የተውትን በዘውግና በቋንቋ መለያዎች የተዋቀረውን ሕገ መንግሥትና መለያችን የሆነውን የክልል አስተዳደር መዋቅር ተቋም ከማድረጉ በፊት የዐማራው ሕዝብ፤ በተለይ ምሁሩና ልሂቃኑ በዐማራነት ተደራጅተው አያውቁም።

ዛሬ በዓለም ደረጃ እንደ ዐማራው በብዛት የተማረ፤ የሚሰበሰብ፤ የሚነጋገር፤ ለሃገሩና ለኢትዮጵያና ለመላው ኢትዮጵያዊ የሚቆረቆር፤ ድርጅቶ መስርቶ ድርጅት የሚያፈርስ ወዘተ የሚኖር ያለ አይመስለኝም። ግን፤ የሚታይ ከፍተኛ ክፍተት አለ። ይኼውም፤ በዓላማ አንድነት ላይ የጋራ ግንዛቤ አላየሁም።

ሁለተኛውና አደገኛው ክፍተት የዐማራው ምሁር፤ ልሂቃና ድርጅቶች ለመሰብሰብ፤ የገንዘብና የእውቀት ተሰጧቸውን (Financial and knowledge/expertise) ፈሰስ ቢያደርጉም፤ ይህ እምቅ አቅም ወደ ተግባር አልተቀየረም፤ መቀየር አለበት። ወሳኙ ክፍተት ለመተግበር አለመቻል መሆኑን አሳስባለሁ።

የዐማራው ሕዝብ እምቅ አቅም ለዚህ ሕዝብ ህልውና ብቻ ሳይሆን፤ አደጋ ላንዣበባት ውድ አገራችንም ቀጣይነት ወሳኝ ሆኖ አገኘዋለሁ።

አንዳንድ ግለሰቦች በሶሻል ሜድያ ለዐማራው ህዝብ ካልሆነች “ኢትዮጵያ በጭንቅላቷ ትደፋ” የሚሉ አሉ። ይህ የተሳሳተና አደገኛ ብሂል ነው። የጃዋር ደጋፊዎች “Down Down Ethiopia” ሲሉ፤ እኔ እንደገባኝ ከሆነ “ኦሮምያ” የምትባል አማራጭ አገር እንመስርት ማለታቸው ነው። በኢትዮጵያ መቃብር ላይ ማለት ነው።

የኦሮሞው፤ የትግራዩ፤ የዐማራውና ሌላው ሰፊ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ አገር የለውም። ብሄራዊ መግባባት፤ እርቅና ሰላም ወሳኝ መሆናቸውን አሰምርበታለሁ። የፖለቲካ ሥልጣን፤ መንግሥት፤ ሕገ መንግሥት፤ የአስተዳደር መዋቅርና ሌላው ሊለወጥ ይችላል። ምንም መተኪያ የሌላት ግን ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያን ከአደጋ፤ ማለትም፤ ከመፈራረስ መታደግ የእያንዳንዳችን ግዴታ ሆኗል።

ስለዚህ፤ ዐማራውም ሆነ ኦሮሞው፤ ትግራዩም ሆነ ሶማሌው፤ አፋሩም ሆነ ወላይታው ወዘተ ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ አገር የለውም የሚለውን ወሳኝ መርህ እንድትቀበሉትና እንድትመሩበት አደራ እላለሁ።

በዐማራው ሕዝብ ላይ በተከታታይ የተካሄደውን አፍራሽና ለጥቃት ያጋለጠ ትርክት መስበር አለብን። ይህን በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ታላቅ ሕዝብ “ነፍጠኛ፤ ትምክኽተኛ፤ ወራሪና” ሌላ የግድፈት መለያዎች እየሰጡ ኢላማ ሆኖ በተከታታይ እንዲጨፈጨፍ፤ ከቤትና ከንብረቱ እንዲወገድ፤ እንዲዋረድ፤ እንዲፈናቀል፤ እንዲሰደድ ወዘተ ያደረጉት ኃይሎች የሚሰሩትን ተንኮል ያውቁታል። በእነሱ አጀንዳ ላይ አልጀምርም። በእነሱ አጀንዳ አልበከልም፤ አልዳኝም።

በዐማራው ሕዝብ ላይ በተከታታይ ከፍተኛ ዘውግና ኃይማኖት ተኮር እልቂቶችና ፍልሰቶች ተካሂደዋል። ስርዓቱ እስካልተቀየረ ድረስ እልቂቱና ፍልሰቱ ይቆማል የሚል እምነት የለኝም። ይህ አደገኛ ሁኔታ ካልተቀየረ ግን ስጋቱ ለኢትዮጵያና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚሆን አሳስባለሁ። ብልህነትና አርቆ አስተዋይነት የሚያስፈልገው የአደጋው መጠን ለኢትዮጵያ ህልውናም አስጊ ሆኖ ስለማየው ጭምር ነው። ከዓላማ አንድነትና ከተግባር ወሳኝነት ላይ ትኩረት ካደረግን ስኬታማ ለመሆን ያለን እድል ሰፊ ነው። የምንሻማው ከጊዜ ጋር ሆኗል። ጦርነቱ ከሃሳብ ጋር ነው።

የዓላማ አንድነትና ተግባር ስል፤ ድርጅት፤ ዐመራር፤ መረጃ መለዋወጥ፤ በየፈርጁ የተራውን ሕዝብ አቅም፤ በተለይ የዐማራውን ማጠናከርና ያልተቆጠበ ድጋፍ መለገስ ወሳኝ መሆናቸውን ለመጠቆም ነው።

በዚህ አጋጣሚ አንድ የተሳሳተ ብሂል ስላለ የራሴን ግምገማ ግልጽ ላድርግ። የዐማራው ሕዝብ መሪና ተቆርቋሪ የለውም የሚለውንም ብሂል አልቀበልም። መሪዎች ጠንካራና ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉት ስንከባከባቸው ነው። በማንኛውም ዓለም ለመምራት፤ የሚያዳምጥና የሚመራ ሕዝብ ያስፈልጋል። ሁሉም መሪ ከሆነ ማን ይመራል? ሁሉም መሪ፤ ሁሉም አዋቂ ሊሆን አይችልም።

እኛ፤ ተከታዮቻቸው ለመሪዎች ራሳችን የዘውግ ስብስቦችና ልሂቃን “ኢትዮጵያዊያን” በማለት ፋንታ በዘውግ ለያይተው “ዐማራ ነህ/ንሽ ብለው፤ ኦሮሞ ነህ/ነሽ፤ ትግሬ ነህ/ነሽ ወዘተ ከከፋፈሉን በኋላ ማዘዝን እንጅ መታዘዝን ወይንም መመራትን አሻፈረኝ አልቀብልም ማለታችን ለዐማራው እልቂትና ብሎም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት እሴቶች መዳከም ግብዓት ሆኗል።

መሪና ትእዛዝ አልቀበልም ባይነት ራስን ከአደጋ ከመከላከልና ከዲሞክራሲ ጋር አብረው አይሄዱም። ይህንን ሆነ ተብሎ የተጫነብንን የእሚቢተኛነት ሽክም እንደማንም ብለን ለማስወገድ እንሞክር። ልጆቻችንን ሥርዓት እንዲያከብሩ እናስተምር። ማንኛውም ሕዝብ የድርጅትና የመንግሥት መሪ ያስፈልገዋል። ማንኛውም ሕዝብ የዘውግንና የኃይማኖትን አጥሮችንና ግንቦችን ለማፍረስ ካልቻለ ሰላም፤ እርጋታ፤ ልማት የሚኖርበት ሁኔታ አይታየኝም።

የዐማራው ሕዝብ ብልህና አርቆ አስተዋይ መሪዎች ነበሩት፤ አሁንም አሉት። ብዙ ምሳሌዎችን ለመጥቀስ እችላለሁ። ከታላላቅ የዐማራ መሪዎች መካከል ዓለም ያደነቃቸው፤ ከልጅነቴ ጀምሬ የታወቁትንና ሲጠቀሱ የሰማኋቸውን መሪዎች ስም ላቅርብ። ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የታገሉትና ለፈረንጅ እጀን አልሰጥም ብለው ራሳቸውን መስዋእት ያደረጉት ታላቁ መሪ አጼ ቴዎድሮስ ከፍተኛ ቦታ የያዙ የጎንደር ዐማራ ናቸው። ገና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስማር በነበረበት ጊዜ ስለኒህ አባትና መስራች መሪ ቲያትር እንሰራ ነበር።

መላው የዓለም ሕዝብ፤ በተለይ የጥቁሩ ሕዝብ የሚያደንቃቸውና ቅኝ ገዢዎች ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ እንዲያከብሩና እንዲፈሩት ያደረጉት መሪያችን ታላቁ የዐማራ ሕዝብ በረከት፤ አጼ ምኒልክ (እምየ ምኒልክ) ናቸው። አጼ ምኒልክል የአመራር ጥበብ ያላቸውና ሁሉንም የኢትዮጵያ ዘውግና ኃይማኖት አባላት የሚያፈቅሩ፤ የመላውን ኢትዮጵያዊያን ፍቅርና አድናቆት ያገኙ መሪ ናቸው። በሁሉም የልማት ዘርፎች ዘመናዊ የኢኮኖሚ መሰረት የጣሉና ተቋማትን የመሰረቱ፤ ከልዩ ልዩ የውጭ መንግሥታት ጋር ግንኙነቶችን የፈጠሩ ናቸው። እኒህን ለነጻነት፤ ለብሄራዊ አንድነት፤ ለክብር፤ ለዘመናዊነት የታገሉና ዓለም ያደነቃቸውን መሪ፤ ዐማራ ስለሆኑ ብቻ “ነፍጠኛ፤ ትምክህተኛ፤ ጨቋኝ፤ ወራሪ” እና ሌላ የሚዘግንን ስም ሰጥቶ ማዋረድ ራስን ማዋረድ ነው። ከነጻነትና ከኋላ ቀርነት ይልቅ “ፈረንጆች ቢገዙኝ ይሻለኝ ነበር” ከማለት ለይቸ አላየውም።

ሩሲያኖች ታላቁን ፔጥሮስን፤ ጀርመኖች ቢስማርክን፤ ቱርኮች ከማል አታተርክን፤ ፈረንሳዮች ናፖሊዮንን ወዘተ እንደ ታላቅ መሪዎቻቸው ይጠቅሳሉ። እኛም ከላይ የጠቅስኳቸውን መሪዎች በሚያኮራ ደረጃ እናስታውሳቸዋለን። መብታችን ነው፤ ግዴታችን ነው። ዐማራዎች ብቻ መሆናቸው አይደለም። በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነታቸው ኮርተውና ተከብረው እኛንም ስላስከበሩን ነው። በተመሳሳይ፤ የሚያኮሩ የኦሮሞ፤ የትግሬ፤ የሶማሌ፤ የወላይታ፤ የአፋርና ሌሎች መሪዎች አሉን።

ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ሥልጣን ይዞ የዐማራው ሕዝብ በዱር በገደሉ ሲጨፈጨፍ መኢአድን የመሰረቱት ዶር አስራት ወልደየስ የተከበሩ ዐማራና በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነታቸው ኮርተውና ተመስግነው ያለፉ መሪያችን ናቸው። በኢህአዴግ ስርዓት ውስጥ ያደጉና ለሥልጣን የበቁ ናቸው የሚለው እንዳለ ሆኖ፤ የዐማራው ክልል ፕሬዝደንት የነበሩት፤ ያለ ጊዚያቸው የተቀጩት ወጣቱና አስተዋዩ መሪ ዶር አምባቸው መኮነንም፤ ለዐማራው ሕዝብ ተቆርቋሪ እንደነበሩ በአካል ነግረውናል፤ ነግረውኛል።

በዓለም ደረጃ እውቅና ያገኘው፤ ትሁቱና መንፈሳዊው፤ በህወሓት አስከፊ አገዛዝ በእስር ቤት ተሰቃይቶ ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አሕመድ አሊ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ተለቆ፤ ለመላው የአዲስ አበባ ሕዝብ መብት በመቆም ባልደራስን የመሰረተውና እንደገና በዐብይ መንግሥት “በአመጸኛነት” ወንጀል ተከሶ በእስር ቤት የሚሰቃየው እስክንድር ነጋ ለዐማራ ቁሜያለሁ ብሎ በግልፅ ባይናገርም፤ እሴቱና አመለካከቱ ከላይ ከጠቅስኳቸው የዐማራ መሪዎች ጋር ተመሳሳይነት አለው። ልክ እንደ እኔ፤ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ የማያወላውል አቋም አለው። ሌሎችንም ለመጥቀስ ይቻላል። ዋናው ትኩረቴ የዐማራው ሕዝብ መሪዎች ያሉት መሆኑን ለማሳየት ብቻ ነው።

ለዐማራው ሕዝብ በመቆም፤ በመሟገትና ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት በመቆምና በመሟገት መካከል ልዩነት አለ የሚለውን የተሳሳተ ብሂል አልቀበልም። የዐማራው ሕዝብ በመላው ኢትዮጵያ የሚኖረው በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነቱ ተማምኖ ነው። የሕዝብ የድምፅ ዘገባ (Public Poll) አይካሄድም እንጅ፤ ቢካሄድ ኖሮ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድብልቅ መሆኑ ይታመናል። መምህር ታየ ቦጋለ በአንድ ስብሰባ ላይ የተናገረው ትዝ ይለኛል። በመልክ ዘገባ “እኔን ከእናንተ እንዴት ልትለዩኝ ትችላላችሁ” የሚል መንፈስ የያዘ መልእክት ነው ያቀረበው። እሱንና እኔን የሚለየን ቋንቋ ብቻ ሊሆን ይችላል። ቋንቋ ደግሞ መገናኛ እንጅ መለያያ አይደለም። ቋንቋ መለያያ የተደረገባት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አትቀርም።

የዐማራውን ሕዝብ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነቱ ለይቸ የማላይ መሆኔን ግልጽ ለማድረግ እፈልጋለሁ።

ትኩረት ልሰጠው የምፈልገው ሃሳብ፤ በህወሓት የተመሰረተውና እነ በረከት ሰምዖን ልክ የህወሓት አጃቢ አድርገው ይመሩት የነበረው ብአዴን አመራሩንና አባላቱን ሲቀይር እንደ ቆየ ተመልካቾች ይናገራሉ። ጥርጣሬ መሆሩን እያስተናገድኩ፤ የዛሬው የዐማራ ብልፅግና ፓርቲ የህወሓት “አጎብዳጅ ወይንም አሽክከር” ነው የሚለውን ግን ሙሉ በሙሉ አልቀበልም። በዚህ ድርጅት ውስጥ የዐማራውን ሕዝብ ሰቆቃ የሚቃወሙ፤ ለኢትዮጵያ ክብር፤ ብሄራዊ አንድነት፤ ነጻነትና ሉዐላዊነት፤ ለኢትዮጵያዊነት የዜግነት መለያችን የሚታገሉ ግለሰቦችና መሪዎች እንዳሉ ይታመናል። በዐማራውና በኦሮሞው ወንድማማች ሕዝብ መቀራረብና አንድነት ላይ ውይይትና መተማመን እንዲደረግ የሚሞክሩት ወገኖቻችን ሊመሰገኑ እንጅ ሊተቹ ማድረግ አግባብ የለውም።

በተጨማሪ፤ አብን የተባለው የወጣት ዐማራዎች እንቅስቃሴ ቆራጠነት የሚያሳይና ተስፋ የሚሰጥ ወጣት መሪዎችን ያፈራና የሚያፈራ ድርጅት መሆኑ ይታመናል።

ለእነዚህ ሁለት “በዐማራው” ሕዝብ ስም ለሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች አመራሮች የምሰጠው ምክር ተደጋጋፊ እንዲሆኑ፤ እየተናበቡ እንዲሰሩ፤ ልዩነቶቻቸውን በውስጥ ውይይቶችና በታወቁ ሽማግሌዎች፤ አባቶች፤ እናቶችና ምሁራን አማካይነት እንዲፈቱ ነው። በተለይ፤ ዛሬ በሃገራችን ላይ ባንዣበበው፤ ህወሓትና ኦነግ “አገር ልትፈርስ ትችላለች” እያሉ በሚሳለቁባት ኢትዮጵያ የዐማራውን ሕዝብ የሚወክሉ ኃይሎች በሙሉ አንድነታቸውን የማጠናከር ግዴታ አለባቸው።

የዐማራው ሕዝብ ራሱን የሚለየው ክሁሉም በላይ በመላው ኢትዮጵያ፤ በኢትዮጵያዊነቱ ተማምኖ የሚኖር መሆኑ ነው። በትክክል ባይታወቅም እንኳን፤ በኦሮምያ፤ በሶማሌ፤ በደቡብ፤ በጋምቤላ፤ በአፋር፤ በቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ ወዘተ የሚኖረው የዐማራ ሕዝብ በብዙ ሚሊየን እንደሚሆን ይታመናል። በተጨማሪ፤ የዐማራው ህዝብ ከሌሎቹ ወገኖቹ ጋር ተጋብቶ፤ ተዋልዶ፤ ተዛምዶ በያካባቢው ቋንቋውን፤ ባህሉን፤ ታሪኩን፤ ልምዱን ወዘተ ተቀብሎ ይኖራል። ይህ ስብጥርነት ትልቅ ኃብትና ጸጋ ነው። በምንም ሁኔታ የማይለያይ ሕዝብ መኖሩን የመቀበል ግዴታ አለብን።

ልድገመውና ላስምርበት። ዐማራው በመላው ኢትዮጵያ የሚኖር ሕዝብ ነው። ተጋብቷል፤ ተዛምዷል የሚለውን መርህ ከተቀበልን፤ ወዳጁን ማስፋት ግዴታችን ነው። አፋሩም፤ ትግሬውም፤ ሶማሌውም፤ አኗኩም፤ ወላይታውም፤ ጉራጌውም ኦሮሞውም ወዘተ ወዘተ ወዳጁ ነው።

ትኩረት መስጠት አግባብ ያለው መሆኑ አንዳለ ሆኖ፤ ለዐማራው ደህንነትና ህልውና መታገል ያለበት ዐማራው ብቻ አይደለም። ሁሉም ወገኖቹ ጭምር ናቸው። ልክ ጎንደሬው አንድ ሰሞን “የኦሮሞ ደም ደማችን ነው” ያለውን መፈክር ማስተጋባት ለሁሉም ይበጃል።

ይህን ስል ግን፤ ራስን መከላከል የሚጀምረው ከቤት መሆኑን አሳስባለሁ።

ክፍል ሁለት የአመጸኞችን ትርክት፤ በዐማራው ላይ የሚፈጸሙትን እልቂቶችና መንስኤዎቻቸውን ይገመግማል። መፍትሄዎችን ይጠቁማል።

September 24, 2020

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.