በአማራና አናሳ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚፈጸም ተደጋጋሚ የዘር ማጥፋት ጥቃት በአስቸኳይ መቆም አለበት

zegochከሰሞኑ ለማመን የሚከብድ አረመኔያዊ  ወንጀሎች ተፈፅመዋል። የሞቱት ፣ የቆሰሉት ፣ የተዘረፉትና የተፈናቀሉት ትክክለኛ ቁጥር እየተጠናቀረ ነው ቢባልም  የዓለም አቀፍ ሚድያዎች የሞቱት ብቻ በትንሹ 40 አለያም እስከ 120 ይደርሳሉ ብለዋል፡፡  ይህ ጥፋት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። ላለፉት 30 ዓመታት ያህል በተሳሳተ አስተሳሰብ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አስተዳደር በአማራና አገው ማህበረሰብ ኢትዮጵያውያን ላይ የተቀረፀው ሕገ መንግስት ይዘት ያስከተለው የግዴታ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የዜግነት ጦስ ነው።  ዜግነት ተንቆ፣ ጎሰኝነት ተደንቆ፣ የአብሮነት ዕሴት ተደፍቆ፣ ሕዝባችን ተናንቆ እንዲተያይ፣ በግልፅና ስውር የገዥዎች ግፊት በብዙ የሀገራችን አካባቢዎች ሲደረስ የቆየ ውርጅብኝ ነው።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ከሌሎች ለየት የሚያደርገው ከአካባቢ ጎሳዎች ባለተወለዱ ነዋሪዎች ላይ የሚደረገው በደል ከሁሉም ክልሎች በባሰ ለብዙ ዓመታት የቀጠለ መሆኑ ነው።  በተለይ አጎራባች በሆኑት የክልሉ የአማርኛ ተናጋሪ ዜጎች ላይ ያተኮሩ ግድያዎች፣ ማሸማቀቅና ግፎች ሲካሄዱ ቆይተዋል። ከበታች የሚገኙት የቅርብ ዓመታት ዓለም አቀፍ ሚድያዎች በየጊዜው የዘገቡትን (ሊንኩን በመጫን) ይመልከቱ። የክልሉና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል ሌሎች ክልሎች የሚያቀርቧቸው መፍትሔዎች ቅንነት የጎደላቸው፣ መሠረታዊና  ተግባራዊ ያልነበሩ ነበሩ።

የወገኖችን ደህንነት መጠበቅ ዋነኛ ኅላፊነታቸው የሆኑት የፌደራል፤ የክልል፤ የዞንና የወረዳ አስተዳደሮች እንደዚሁም የመከላከያና የፓሊስ ሠራዊትና የህዝብ ደህንነት ተቋማት ለችግሩና ለእልቂቱ ቢያንስ ተከላካይ ከመሆን ይልቅ በአመዛኙ የጥቃቱ ተባባሪዎች እንደሆኑ ማስረጃዎች ያሳያሉ።  ከተጠቂዎች በኩል የመከላከልና የድጋፍ ጥሪዎች ለእነዚህ አካላት ሲቀርብ፤ አይመለከተንም፤ ከበላይ ትእዛዝ አልተሰጠንም፤ ካላችሁበት ለቃችሁ ውጡ ከማለት ሌላ የሥራ ግዴታቸውን ሲወጡ አልታዩም፡፡

በተለያዩ ጊዜና ቦታዎች እልቂቱና ጥፋቱ ከተፈጸመ በኋላም የክልሉና ከፍተኛ የመንግሥት ኅላፊዎች ተሰብስበው የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን አልፎ አልፎ ይቅርታ ከመጠየቅ ሌላ ለችግሮቹ ዘለቄታዊ መፍትሄ የሚሆን እርምጃ ሲወስዱ እስከአሁን አልታዩም፡፡ በዚህም ምክንያት የማፈናቀሉ፤ የግድያውና የዘር ማጥፋቱ ዘመቻ በስፋትና በጥልቀት እየተባባሰ መጥቷል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሽግግር መንግስት ምስረታ ሂደትን በተመለከተ የተዘጋጀ ሁለተኛ የምክክር ጉባኤ

ስለዚህ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ካልተደረገበት በዓለማችን እንዳየነውና እንደሰማነው በሩዋንዳና በጀርመን የሆነው ዓይነት የከፋ እልቂትና የዘር ማጥፋቱ ዘመቻ አሁንም በሀገራችን ሊፈጸም እንደሚችል ለአንዳፍታ እንኳን አንጠራጠርም፡

ይህንንም የምንለው በጆሯችን ከሰማነውና ባይናችን ካየነው በመነሳት ነው። ማለትም እኤአ በጃንዋሪ 2019 ዓም 8 አባላትን ያካተተ የኢትዮጵያዊነት ቡድን ሀገር ለመጎብኘት ባህር ዳር ከተማ በተገኘበት ወቅት ከመተከል ዞን የተፈናቀሉ ብዛታቸው ከ300 ያላነሱ አባወራዎች፤ ሴቶችና ህጻናት ከከተማው ወጣ ባለ መጋዘን ውስጥ ተጠልለው ያየናቸው አስረግጠው የገለጹልን የተፈናቀሉት ህብረተሰባቸው የሞትና የድብደባ ጥቃት በአካባቢው ነዋሪዎች ስለተፈጸመባቸው እንደሆነ ነበር። ይኸንን በተመለከተ ከኣማራ ክልል አስተዳደር ጋር ባደረግነው ውይይት ተፈናቃዮቹ ወደ መጡበት ከመመለስ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ነግረውን ነበረ፡፡ ተፈናቃዮቹ ግን ደጋግመው ያሳውቁን ቢመለሱም ያለምንም ዋስትናና መከላከያ ሞትና ስቃይ እንደሚጠብቃቸው ነበረ፡፡  በኋላም እንዳጣረነው በወቅቱ በመተከልም ሆነ በአማራ ክልል መሪዎች በኩል አጥፊዎቹን  በህግ የመቅጣትም ሆነ ወንጀሉን የመከላከል ተግባር ፈጽሞ አልተፈጸመም። እንዳውም የመተከል አስተዳደሩ የጥፋቱ ተባባሪ እንደሆነ በሰፊው ይነገራል፤ ተፈናቃዮቹ እንዳሉትም እነሆ እስካሁን ድረስ ለተከታታይ ጥቃትና እልቂት ተጋልጠው ይገኛሉ፡፡

ክልሉ ሕዳሴ  ግድብ የሚገኝበት በመሆኑ ኢትዮጵያን ለማዳከም የቅርብና የሩቅ ባዕዳን የጂኦፖለቲካ  ኃይሎች በስውር የሚራኮቱበት  ተጋላጭ ቦታ መሆኑን እንረዳለን። ይሁንና ከልብ ከታሰበ የአካባቢውን ፀጥታ ለመጠበቅም ሆነ ከውጭ የሚሸረቡትን ሴራዎች ለመቆጣጠር መንግሥት ለችግሮቹ የሚመጥን ዕቅድና የመዋቅር ለውጥ ለማድረግ አቅም ያንሰዋል ብለን አንገምትም።

ለወደፊቱ በአማራውና በአነስተኛ የህብርተስቡ ክፍሎች ላይ በማንነታቸው ላይ የሚፈጸም ከፍተኛ ጥቃትና  እልቂት ከመድረሱ በፊት፤

 1. የፌደራሉ መንግሥት በሀላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙት የአማራና መተከል አመራሮች፣ በተደጋጋሚ ለሰው ህይወት መጥፋትም ሆነ ለንብረት መውደም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተጠያቂዎች መሆናቸውን ተቀብሎ ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፤
 2. መንግሥት የጥፋቱ ተሳታፊዎችን አሳዶና ተከታትሎ በመያዝ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እንዲያደርግ፤
 3.   መንግሥት ለወደፊቱም እንዲህ ዓይነቱ የዘር ማጥፋቱ ተግባር እንዳይፈጸም የሚያግድ የህግና የድርጅታዊ  ዝግጅት እንዲዲያደርግ፤
 4. መንግሥት ለተጎዱት ወገኖች አስፈላጊውን ካሳ እንዲከፈሉ እንዲያደርግ
 5. በተደጋጋሚ የጥፋቱ ስለባ የሆኑት የህብረተሰቡ ከፍሎች ለወደፊቱ ከተመሳሳይ ጥቃት እራሳቸውን የሚክላከሉበት ዘዴ እንዲያመቻቹና ለዚሁም የፌደራሉና የመተከል አስተዳደር ሁኔታዎችን እንዲፈቅዱና እንዲያመቻቹላቸው እናሳስባለን፡፡
ተጨማሪ ያንብቡ:  ብሔራዊ ጭቆና የትግላችን መዘዉር ሆኖ ይቀጥላል! | የሳዲቅ አህመድ የቪዲዮ ዘገባ

በተጨማሪም፣ ሀገራችን በተደጋጋሚ ማንነት ላይ ያተኮረ መረን የለሽ ዘመቻ በየአካባቢው እየተከሰተ ለመሆኑ ዛሬ በየሜዲያ አውታሮች እየተመለከትን ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት በአመዛኙ የችልተኝነት፣ አይቶ እንዳላየ፣ አንዳንዴም የተባባሪነት ባህርይ እያሳየ ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች መጥቀስ ይቻላል ፡፡ በዚህ አኳያ የፌደራሉ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ስጥቶት አስቸኳይ ሥር ነቀል ሕጋዊና ዘለቄታዊ እርምጃ እንዲወስድ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

በዚህ አጋጣሚ የጥፋቱ ስለባ ለሆኑት ወገኖቻችን በሙሉ ነፍስ ይማር እያልን ለተረፉትም መጽናናቱን እንዲሰጥልን እንመኛለን፡፡

ኢትዮጵያዊነት፤ የዜጎች መብት ማስከበሪያ ጉባኤ 

 

(1) Bloomberg reported on Sept 17, 2020: At Least 140 Killed in Ethiopian Ethnic Clashes This Month;

https://www.bloomberg.com/news/articles/2020-09-17/at-least-120-killed-in-ethiopian-ethnic-clashes-this-month

 1. Reuters Reported on June 26, 2020: More than 50 killed in attacks in western Ethiopia: regional official

https://www.reuters.com/article/us-ethiopia-security-violence/more-than-50-killed-in-attacks-in-western-ethiopia-regional-official-idUSKCN1TR2FI

3.    Ethiopia Observer wrote on July 29, 2020: 14 killed in attacks targeting Amharas

https://www.ethiopiaobserver.com/2020/07/29/14-killed-in-attacks-targeting-amharas/

 1. TRT World reported on 3 May, 2019: dozens killed in ethnic clashes in Ethiopia: https://www.trtworld.com/africa/dozens-killed-in-ethnic-clashes-in-ethiopia-26359
 2. Xinhua News Agency reported on April 29, 2019: 17 PEOPLE KILLED IN CLASHES IN BENISHANGUL GUMUZ REGIONAL STATE

http://www.xinhuanet.com/english/2019-04/29/c_138022548.htm

 1. Reuters reported on June 21, 2018: Driven away by conflict, thousands of Ethiopians stranded without a home

https://www.reuters.com/article/us-ethiopia-landrights-displacement-idUSKBN1JH0ZA

 

2 Comments

 1. We Ethiopians got an expired pride. The honor of being an Ethiopian does not exist anymore. Ethiopians live in the past giving blind eye to our current reality. Human rights are not respected in Ethiopia . We Ethiopians are treated as animals or as pets by our own government .

 2. በመተከል ዞን ጦጣና ዝንጀሮ እየተባሉ በአንድ ጊዜ ብቻ የተጨፈጨፍይትን ከ500 የሚበልጡትን የጉሙዝ ወገኖቻችንንም እናስታዉሳቸዉ አደራ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.