ኢትዮጵያ የብር ኖቶችን ቀየረች (የአገር ጉዳይ ያስጨንቃል፤ ያስጠብባል!) – በገ/ክርስቶስ ዓባይ

በገ/ክርስቶስ ዓባይ
መስከረም 10 ቀን 2013 ዓ/ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እጅግ በጣም ዘግይቷል ካልተባለ በስተቀር የብር ኖቶቹን መቀየሩ ተገቢ እርምጃ መሆኑን ሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የሚስማማበት ጉዳይ ነው። ነገር ግን የብር ኖት ሲቀየር እስከሚረጋጋ ድረስ በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ አገር የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የሚያስከትለው ጫና እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከዚህም ባለፈ አሜሬካንን በመወከል ዓለምን እንደፈለጋቸው የሚዘውሩት ታላላቆቹ የገንዘብ ተቋማት ማለትም የዓለም ባንክ (World Bank) እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF, International Monetary Fund) አጋጣሚውን በመጠቀም የገንዘብ ምንዛሬውን አሳንሶ ለመተመን እና በዚሁ ሰበብ የአገሪቱን ሀብት ለመበዝበዝ የራሳቸውን የስሌት መጠን ማስቀመጣቸው አይቀርም። በዚህ ወቅት አዲሱ የብር ኖት በገበያ ላይ ውሎ በሕዝብ ተቀባይነት እስከሚያገኝ ድረስ ‘ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል’ እንዲሉ፤ በመንግሥት ከፍተኛ ቁጥጥር ካልተደረገ አስመጭ ነጋዴዎችም ከፍተኛ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ የዋጋ ጭማሪ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም።

119508362 1758311590986848 1446637338946732611 oመንግሥት ከእነዚህ ሁለቱ ተቋማት ጋር ያደረገውን ድርድር እና የተስማሙበትን አጠቃላይ መረጃ ለሕዝብ በይፋ ማሳወቅ ይኖርበታል። በተለይ የዓለምን ኢኮኖሚ እንደ ወርቅ፤ በየጊዜው እየተቆጣጠረ ያለው የነዳጅ ዋጋ ላይ ለውጥ እንዳይታይ መንግሥት ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይጠበቅበታል። በነዳጅ ዋጋ ላይ የአንድ ሳንቲም እንኳ ለውጥ ከታየ በአጠቃላይ የንግዱ እንቅስቃሴ ላይ የዋጋ ማዋዠቅን ስለሚያስከትል የአንድ ዕቃ ዋጋ ቀደም ሲል ከነበረው ዋጋ አንዴ ከፍ ካለ በኋላ መልሶ ለማውረድ እንዲህ በቀላሉ የታሰብ አይሆንም።

እንዲህ ያለው ለውጥ በተለይ በመካከለኛ ገቢ በሚተዳደረው የመንግሥት ሠራተኛ ላይ የሚያስከትለው የኑሮ ጫና ከባድ እንደሚሆን ይገመታል። የወር ደመወዝተኞች ገቢ የተወሰነ ስለሆነ ቀድሞ ይገዙበት ከነበረው ዋጋ በላይ ተጨማሪ ገንዘብ የሚጠይቃቸው ከሆነ ከፍተኛ የሆነ ምሬት ውስጥ ይገባሉ። በሥራ ገበታቸውም ላይ ደስተኛ በመሆን ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም። በተለይ ደግሞ በሕዝብ አገልግሎት ዘርፍ ላይ የተሠማሩ ከሆነ ባለጉዳዩን ማጉላላትና ሌላም ነገር መፈለግ ይጀምራሉ። እንዲህ ያለው አካሄድ ቢሮክራሲውን ተብትቦ ስለሚይዘው የአገርን ዕድገት ወደኋላ ይጎትታል። የችግሩንም ሁኔታ ለመቅረፍና የዋጋ ግሽበቱን ለማስተካከል መንግስት ጣልቃ በመግባት ለሠራተኛው የደመወዝ ማስተካከያ አደርጋለሁ ቢል፤ በቀላሉ ሊወጣው ከማይችለው የችግር አዙሪት ውስጥ ገብቶ መውጫ መንገድ እስከሚያመቻች ድረስ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው ጫና ቀላል አይሆንም።

በተጨማሪም ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለው የንግድ ልውውጥ፤ በነበረበት ካልቀጠለ የአገሪቱ ሀብት በሕገወጥ መንገድ ሊወጣና መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ጥቅም ሊያጣ ይችላል። ከአሁን ቀደም ሌሎች ተጨማሪ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው፤ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ የተከሰተውና ወገኖቻችንን የፈጀው አስከፊው ጦርነት የተቀሰቀሰው ኢትዮጵያ የብር ኖቶቿን ከቀየረች በኋላ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው።

እንግዲህ እኒህን ነጥቦች ለመንደርደሪያ ካየን በኋላ ወደ ተደረገው የብር ኖት ለውጥ የተሰማኝን ሐሳብ ልግለጽ።

በመጀመሪያ ደረጃ የ200 መቶ ብር ኖት አስፈላጊነቱ ይህን ያህል የጎላ አይመስለኝም። ምናልባት የቁጥሩን ብዛት በማሳነስ የኅትመቱን ዋጋ ለመቀነስ ሲባል የተወሰደ እርምጃ እንደሚሆን መገመት አይከብድም። ይሁን እንጂ አንደሚታው ግን የገንዘቡ የመግዛት አቅም እንደቀነሰ የሚገልጽ መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን ከመጠቆም አይዘልም። በእርግጥ የገንዘቡ የመግዛት አቅም በቀነሰ ቁጥር አንድ ሰው ቀደም ሲል በቦርሳው ሊይዘው የሚችለው አንድ ሺህ ብር ቢሆን እና ተመሳሳይ ዕቃ ለመግዛት ከዚያ በላይ የሚጠይቀው ከሆነ ቦርሳው እስኪወጠር ድረስ ተጨማሪ ግንዘብ መያዝ ይገባዋል ማለት ነው። ነገር ግን ቦርሳው የሚይዘው አንድ ሺህ ብር ብቻ ቢሆን አሁን የ200 መቶ ብር ኖት በመታተሙ በቀደመው የቦርሳው የመያዝ አቅም ሁለት ሺህ ብር መያዝ ይችላል ማለት ነው። በአጭሩ ብዙ ወረቀቶች ከመያዝ ጥቅል ኖቶቹን መያዝ ይቀላልና። ዞሮ ዞሮ ግን የዋጋ ግሽበትን ከማመላከት በስተቀር የሚፈይደው ስለሌለ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል የሚል እይታ አለኝ።

ነገር ግን ዋናው ኮር የሆነው የአንድ መቶ ብር እንዳለ ሆኖ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የገበያ ለውጥ እንደሌለና በነበረው ላይ ብቻ የማቃለያ እርምጃ እንደተወሰደ ብቻ ማሳየት ይቻል ነበር።

ይኸውም፤ ባለ 20 ብር ኖትን መጨመር ይቻል ነበር። ከአሁን ቀደምም በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የ20 ብር ኖት ነበር። አሁንም ሌላ ተጨማሪ ስሕተት ለመሥራት በዕቅድ እንደተያዘ ጠቅላይ ሚንስትሩ የጠቆሙት ጉዳይ አለ። ይኸውም የባለ5 ብር ኖት በሳንቲም ሊተካ መሆኑን መናገራቸው ነው። እንዲህ ከሆነ መንግሥትም ይሁን በአጠቃልይ አገሪቱ ልትወጣው ከማትችለው የኢኮኖሚ አዘቅት ውስጥ መውደቋ አይቀሬ ነው። ይልቁንም የ5 ብር ኖት እንደሌሎቹ ታትሞ እንዳለ እንዲቀጥል ሆኖ፤ ባለ2 ብር ሳንቲም ቢጨመር ግን የብርን የመግዛት አቅም በአለበት ሁኔታ እንዲቀጥል በማድረግ ገበያውን ማረጋጋት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ።

አሁንም ቢሆን ቀደም ሲል የተሠራውን ስሕተት ማረም ባይቻልም ተጨማሪ ስሕተት እንዳይደገም መጠንቀቁ የተሻለ ይመስለኛል። ነገር ግን የ5 ብሩ ኖት በሳንቲም የሚተካ ከሆነ የአንድ ብር ዋጋ የቀድሞውን የ10 ሳንቲም ቦታ ሲይዝ አምስት ብር ደግሞ ልክ እንደ አንድ ብር ይቆጠራል ማለት ነው። ይህም ለገበያ ግሽበትና የመግዛት አቅም የመቀነስ ምልክት ዓይነተኛ ጠቋሚ መሆኑን ይገልጻል።

ስለዚህ ‘ሳይደርቅ በእርጥቡ ሳይርቅ በቅርቡ’ እንዲሉ መንግሥትም ሆነ ብሔራዊ ባንክ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ጠለቅ ያለ ጥናትና ውይይት አድርገውበት ቢያርሙት ጠቃሚ እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይሆንም። መቼም የገንዘብን ምንዛሬ መዋዠቅ ለመቆጣጠር ቀላል እንዳልሆነ በሙያው ላይ የበሰለ ግንዛቤ ያላቸው ምሁራን የሚያውቁት ጉዳይ ነው። መንግሥት የውጭን ምንዛሬም ለመተመን ቢሞክር የበለጠ ለችግር እንደሚጋለጥ ግልጽ ነው። ነገር ግን ለስለስ ያለ አቋም በመያዝ በገበያ ምሪት በመመርኮዝ መጠነኛ የአገልግሎት ዋጋ ብቻ የሚጠይቅ ከሆነ የጥቁር ገበያውን መቆጣጠር ይችላል። ነገር ግን ኃይልን ከመጠቀም ይልቅ በሕዝቡ ዘንድ ያለውን አመኔታ ማሳደግ የበለጠ ጠቃሚ ይሆናል። ሕዝቡ ያለውን ሀብትና ገንዘብ ያለምንም ማዕቀብ እንደፈለገ በነፃነት በፈለገው ጊዜ ከባንክ የሚያወጣና የሚያስገባ ከሆነ ማንም ገንዘቡን በእጁ ይዞ እየተሳቀቀ መኖርን አይፈልግም። ፍጹም አስተማማኝ በሆነው በበንክ ውስጥ እንዲቀመጥለት ይመርጣል።

ቀደም ሲል ወደ ሃያ የሚደርሱ ባንኮች መዘረፋቸውን ምክንያት በማድረግና፡ ከፊታችን ያለው አወዛጋቢ የምርጫ ጉዳይ ዋና የመወያያ ርዕስ በሆነበት በተለይ በአሁኑ ወቅት፤ በመንግሥት ላይ ያላቸው እምነት አስፈሪ በመሆኑ በርካታ ባለሀብቶች ገንዘባቸውን በጆንያ አጭቀው በየቤታቸው እንደያዙ ይገመታል።

አገር እንመሥርታለን በማለት የሕልም ፈረስ እየጋለቡ የሚገኙትም የሕወሃት ዓባለትና ደጋፊዎቻቸው ከዚሁ የተለዩ አይደሉም። የነበራቸውን የማይንቀሳቀስ ንብረት እየሸጡ ገንዘባቸውን ባንክ ከማስገባት ይልቅ በጆንያ ጠቅጥቀው ወደ መቀሌ መኮብለላቸውም ይታወቃል። ታዲያ አገራችን እንዲህ ባለው የተዘበራረቀ ሁኔታ ውስጥ ባለችበት ወቅት የ200 ብር ኖት ማሳተሙ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ለምን ቢባል በርካታ ገንዘብ በቀላሉ ለማሸሽ ወይም ለመሰወርም አመቺ ይሆናል። ከዚህ በላይ ግን የገንዘቡ የመግዛት አቅም እያሽቆለቆለ መሆኑንም ያመላክታልና ከመቸኮል ረጋ ብሎ ማሰቡ አይከፋም። አሁንም መንግሥት ከአሁን ቀደም እንዳደረገው ሁሉ የባለ 20 እና ባለ 5 ብር ኖቶችን ቢያሳትም እና የባለ 2 ብር ሳንቲምም እንዲጨመር ቢያደርግ የተሻለ መሆኑን እንደ አንድ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የተሰማኝን ለመጠቆም እወዳለሁ።

-//-

ስለጽሑ ያላችሁን አስተያየት በ [email protected] ኢሜል ብታደርጉ በክብሮት የምቀበል መሆኑን እገልጻለሁ። ሁሉም ለአገሩና ለወገኑ የሚበጀውን መመኘት ብቻ ሳይሆን፤ የሚችለውን ሁሉ ያድርግ!

1 Comment

  1. Many merchants buy cattles by traveling in the middle of nowhere bringing cattles to town market selling them for profit.

    Many merchants by traveling in the middle of nowhere buy crops from farmers to bring the crops to town markets selling them for profit.

    Now due to this bank note changing rule the traveling merchants have to convert the birr notes they have on hand by depositing the cash into bank accounts , meaning their cash on hand will be tied up in the bank for quiet sometime until this merchants feel safe enough to withdraw the cash. Of course for safety reasons traveling merchants will deposit their cash in the banks and refrain from taking the money out all at once right away because in a country where more than 30 banks got robbed the bank customers will not feel safe going in with the old cash notes and come out with the brand new cash loads . This inturn might bring disruption in agricultural product availability at local markets creating soaring prices in food items and add millions of people to the already 15 million Ethiopian people who need emergency urgent food assistance in Ethiopia.

    Local police is given permission to take above a certain amount cash money they find to curb cash hoarding . The cash the police finds being hoarded the police are given license to keep it for themselves meaning many traveling merchants are currently afraid they will be robbed of their cash by the dirty police officers who might rob two hundred thousand birrs from ten separate traveling merchantseach then the police can simply claim they found two million on hand of just one merchants, since the limit to have on hand is $1.5 million birrs now and if police finds more cash than $1.5 birrs on hand the police is given permission to confiscate and keep the money according to the new rule.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.