የአማራ ክልል መንግስት እንቅስቃሴዎችን አስቸጋሪ እንዲሆኑ አድርጓል – ጌታቸው ረዳ

የአማራ እና ትግራይ ክልሎችን የሚያገናኙ መንገዶች “ዝግ ናቸው፣ ዝግ አይደሉም” የሚሉ መከራከሪያዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት ተደጋግመው ይነሳሉ።
ታዋቂ ፖለቲከኞች እና አክቲቪስቶች በሚሰጧቸው ቃለ-ምልልሶች የፌደራል መንግስት መንገዶችን በማስከፈት ረገድ አሳየ ያሉትን ቸልተኝነት ሲወቅሱም ይደመጣል።
ጉዳዩን በተመለከተ ኢትዮጵያ ቼክ ያነጋገራቸው የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ሁለቱን ክልሎች የሚያገናኙ መንገዶች እንዲሁም ክልሉን አቋርጠው ወደ ትግራይ ክልል የሚያመሩ የፌደራል መንገዶች ክፍት መሆናቸውን ተናግረዋል።
መንገዶች ከሁለት ዓመታት በላይ ተዘግተዋል ተብሎ የሚወራው ወሬ ሀሰተኛ መሁኑን የገለጹት አቶ ግዛቸው የአማራ ክልላዊ መንግስት “መንገዶችን አልዘጋም፣ የመዝጋት ፍላጎትም የለውም፣ ለመዝጋት ከሚፈልጉ አካላት ጋርም አይተባበርም” በማለት ጨምረው ገልጸዋል።
በ2008 ዓ.ም መጀመሪያ በክልሉ ከነበሩ ግጭቶች ጋር በተያያዘ ለጥቂት ቀናት መንገዶችን የመዝጋት እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ያስታወሱት ሃላፊው፣ ይህም በሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች ከተስተዋሉ መንገድ የመዝጋት ድርጊቶች የተለየ አልነበረም ብለዋል።
Getachew
የህወሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የድርጅቱ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቻው ሁለቱን ክልሎች በሚያገኙ መንገዶች መካከል “የበርሊን ግንብ አልተገነባም፣ ነገር ግን የአማራ ክልል መንግስት እንቅስቃሴዎችን አስቸጋሪ እንዲሆኑ አድርጓል” ብለው ለኢትዮጵያ ቼክ ተናግረዋል። አቶ ጌታቸው ስለ መንገዶቹ ሁኔታ ቁርጥ ያለ ምላሽ ባይሰጡም፣ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መኖሩን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ ቼክ ያነጋገራቸው የዘመን 1ኛ ደረጃ ሀገር አቋራጭ አውቶብስ ባለንብረቶች ማህበር የስምሪት ክፍል ሰራተኛ አቶ በቀለ ተካ መንገዶቹ ክፍት መሆናቸውን አረጋግጠዋል። አቶ በቀለ ማህበራቸው በየቀኑ ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች አውቶብሶችን እንደሚያሰማራ ገልጸው፣ በተጠናቀቀው 2012 ዓ.ም የተዘጋ መንገድ እንዳላጋጠማቸው ተናግረዋል። ማህበራቸው የአዲስ አበባ — ደሴ — አላማጣ — መቀለ መስመርን እንደሚጠቀምም ጨምረው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ቼክ በመንገዶቹ አዘውትረው የሚመላለሱ ሁለት አሽከርካሪዎችን ያነጋገረ ሲሆን፣ መንገዶቹ ክፍት ስለመሆናቸው ምስክርነታቸውን ሰጠዋል።
በተመሳሳይ በሪፖርተር ጋዜጣ ከፍተኛ ሪፖርተር የሆነው ጋዜጠኛ ሳሙዔል ጌታቸው በትናንትናው ዕለት ከመቀለ ወደ ወልድያ መጓዙንና መንገዱ ክፍት መሆኑን ለኢትዮዽያ ቼክ ተናግሯል።
የአዲስ አበባ —ወልዲያ—መቀለ፤ የጎንደር—ሊማሊሞ—ሽረ እንደስላሴ፤ የላሊበላ—ሰቆጣ—ተንቤን መንገዶች የአማራ እና የትግራይ ክልልሎችን ድንበር የሚያቋርጡ ዋና ዋና መንገዶች ሲሆን ሌሎች ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው መንገዶችም ሁለቱን ክልሎች ያገናኛሉ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.