ኦነግ ሰላማዊ ትግልን ብቸኛ አማራጨ አድርጌያለሁ አለ

olf
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሰላማዊ ትግልን ብቸኛ አማራጩ አድርጎ እንደሚቀጥል ገለጸ፡፡
የድርጅቱ ሊቀ-መንበር የነበሩትን የአቶ ዳውድ ኢብሣ ከስራ መታገድ እና በቀጣይ ሰላማዊ ትግል መምረጡን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በመግለጫው የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን ለ21 ዓመታት በሊቀ-መንበርነት የመሩትን አቶ ዳውድ ኢብሣ ከስራ ማገዱን አስታውቋል፡፡
በአቶ ዳውድ የስልጣን ዘመን ድርጅቱ ሶስት ጊዜ የመከፋፈል አደጋ እንደደረሰበትና በተያዘለት ጊዜ ጉባኤ ሲያደርግ እንዳልነበር በድርጅቱ አመራሮች ተገልጿል።
የድርጅቱ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ እንዳሉት “ኦነግ ሰላማዊ ትግልን መርጦ አገር ቤት ከገባ በኋላም አንዳንድ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ጫካ ካለውና የትጥቅ ትግል ከመረጠው አካል ጋር ሲሰሩ ነበር፤ የአመጽ ጥሪም ሲያስተላልፉ ቆይተዋል”።
አቶ ዳውድ በድርጅቱ ህገ-ደንብ መሰረት ከተቋቋመው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጋር የመስራት ፍላጎት የላቸውም ያሉት ቃል አቀባዩ “የፓርቲውን ንብረት በህገ-ወጥ መንገድ ለራሳቸው ሲሰበስቡ ነበር” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
“ድርጅቱ በአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት የሚመራና በግለሰቦች ፍላጎት የሚነዳ አይደለም” ብለዋል።
“አቶ ዳውድ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ጠቅላላ ጉባኤው እስኪሰበሰብ ታህሳስ 2013 ድረስ ከድርጅቱ ሊቀ-መንበርነት ታግደዋል” ነው ያሉት አቶ ቶሌራ።
በምትካቸው ምክትል ሊቀ-መንበሩ አቶ አራርሶ ቢቂላ ድርጅቱን እንደሚመሩ ተገልጿል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አገር ቤት ሲገባ በገባው ቃል መሰረት ሰላማዊ ትግልን ብቸኛ አማራጩ አድርጎ ይቀጥላል ብለዋል።
ድርጅቱ ውስጥ ሆነው ሰላማዊና የትጥቅ ትግልን አማራጭ የሚያደርጉ አካላትን የማጥራት ስራ እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡
የድርጅቱ ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ አራርሶ ቢቂላ “ኦነግ በአንድ ግለሰብ የተመሰረተ ባለመሆኑ በአንድ ግለሰብ ሊፈርስ አይችልም” ብለዋል፡፡
“በተለያዩ አገራት በመሆን ድርጅቱን እና አገሪቱን ለማተራመስ የምትሰሩ አካላት ከድርጊታችሁ ተቆጠቡ”ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ለበርካታ ዓመታት ተቀማጭነቱን በውጭ አገራት አድርጎ የቆየው ኦነግ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ከሁለት ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ይታወቃል።
ኢፕድ

71 አ

ስተያየቶች

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.