በድንበር በኩል ሊገባ የሚችልን ህገ ወጥ ገንዘብ የመቆጣጠርና የማምከን ስራ ይከናወናል … የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

119476322 2747109385531523 5805834621345604745 n
የኢትዮጵያን የብር ኖት ለውጥ ተከትሎ ከአጎራባች አገራት ሊገባ የሚችልን ህገ ወጥ ገንዘብ የመቆጣጠርና የማምከን ስራ የሚከናወን መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ነባሮቹን የ10፣ የ50 እና የ100 ብር ኖቶችን ጨምሮ የ200 ብር አዲስ የብር ኖት ይፋ ተደርጓል።
የ5 ብር ገንዘብ ባለበት ቀጥሎ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ሣንቲም እንደሚቀየርም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ የብር ለውጡን ተከትሎ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር ዝግጅት ተደርጓል።
በተለያዩ ጎረቤት አገራት የኢትዮጵያ የብር ኖቶች ክምችት መኖሩን የጠቀሱት ዶክተር ይናገር፤ ለብር ለውጡ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።
ለዚህም ከጸጥታና የደህንነት አካላት ጋር በመነጋገር የመቆጣጠርና የማምከን ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።
በተለይ በድንበር አካባቢ የሚገኙ ባንኮችም በብር ለውጡ ለህገ ወጥ ድርጊቶች እንዳይጋለጡ ጥብቅ ክትትል ይደረጋል ነው ያሉት።
የብር ቅያሬውን ለማከናወን ማንኛውም ግለሰብ የብር ኖቶቹን ራሱ በባንክ መቀየር ሲገባው በሌላ ግለሰብ በውክልና መቀየር የማይችል መሆኑንም ተናግረዋል።
በ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን የብር ኖት መታተሙንና የመጠባበቂያ ክምችት እንዲኖር ተጨማሪ የብር ኖቶች እየታተሙ መሆኑን አመልክተዋል።
ባለፉት ጥቂት ወራት አዳዲሶቹን የብር ኖቶች ወደ ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የማጓጓዝ ስራ መሰራቱንና አሮጌውን ገንዘብ መቀየር የሚያስችል በቂ ክምችት እንዳለ ገልጸዋል።
አዳዲሶቹ የብር ኖቶች እንዳይበላሹ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባና ይሄም ኢትዮጵያ የተበላሸ ገንዘብ ለመተካት የምታወጣውን ብዙ ወጪ ያስቀራል ብለዋል።
ህገ ወጥ ተግባራት የሚፈጽሙ ባንኮች እንደ ጥፋታቸው መጠን ቅጣት እንደሚጣልባቸውም ገልጸዋል።
ኢፕድ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.