የወያኔ የኢትዮጵያ ክልሎች የድንበር ካርታ ለማያባራ ጦርነት ይዳርገናል! አዲስ አበባ እንደ ሻሸመኔ አትቃጠልም! ፀ/ት ፂዮን ዘማርያም

et6

ትግል ሲጀምሩ የእኔ ብጤ የደሃ ልጆች ነበሩ፣ በደርግ ቀይ ሽብር ዘመን በከተማ ውስጥ እንደ ከርከሮ ሲታደኑ አምልጠው በህይወት ለመቆየትና በልቶ ለማደር ጫካ ገቡ፣ ያኔ ባህር ማዶ መሰደድ አልተለመደም ነበር፡፡ በሻብያ፣ በወያኔ፣ በኦነግ ድርጅት ውስጥ ጠመንጃ አንግበው  ለአስራ ሰባት አመታት ታግለው ብዙ የደሃ ልጅና ወታደር ገድለው ስልጣን ያዙ፡፡   የህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድ  መሪዎች ለሃያ ዘጠኝ አመታት አገዛዛቸው፣ በግፍ ብዙ ሰዎች ገድለዋል አስረዋል፣ ገርፈዋል እጃቸው በደም የተጨማለቀ  ነው፡፡  ከእነዚህ ደሃ ገዳዬች በአማራ ህዝብ ላይ በዘርና በኃይማኖት ፍጅት (ጆኖሳይድ) በተደጋጋሚ ጊዜ  ፈፅመዋል፡፡ ብአዴን የራሱን ልጆች መብላት እንደጀመረ፣ እነ ሙሉዓለም አበበ፣  ዶክተር አንባቸው መኮንን፣ ምግባሩ ፣ እዘዘው፣ ብርጌደር ጀነራል አሳምነው ፅጌ፣  የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ሜጀር ጄኔራል ገዛዒ አበራ ጎዶቹን ገድሎ ኃውልት ያቆማል፡፡ የብአዴንን አመራር ያልተቀበሉ ደግሞ አዲስ ካቴናና እግረ ሙቅ ይገባላቸዋል፡፡ በብአዴን እስር ቤቶች ኢስብዓዊ ግርፋትና ስቃይ ብዙ ንፁሃን ዜጎች ቁም ስቅላቸውን አይተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የገዳዬች ፍብሪካ ኢሳያስ አፈወርቂ በአፋቤት በርሃ፣ መለሰ ዜናዊ በደደቢት በርሃ፣ ሌንጮ ለታ በወለጋ በርሃ ገዳዬች እንደ ጫጩት በኢንኩዩቤተር  አስፈለፈሉ፤ የሠለጠኑት ነፍሰ ገዳዬች፣ የቀኝ እጃቸው ቃታ መሳቢያ ጣታቸው የጎበጠ፣ ያለሙበት ዓይናቸው የተጠናገረ፣ አፍንጫቸው ባሩድ ያሸተተ ሱሰኞች፣ የእፅ ፋሪስ ሱሰኞች፣ የመጠጥ አንቡላ ልክፍተኞች፣ ሰው እንደ ዝንብ ገድለው መምጣታቸውን እረስተን ግድያ እንዲያስቆሙልን እንማፀናለን፡፡ በአጠቃላይ መሪዎቻችን ገዳዬቻችን መሆናቸውን እንረዳ፡፡ የብአዴን ገዳዬች የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት መሥርተው በደመነፍሳቸው  ሲገዙን ሃያ ዘጠኝ ዓመታት ተቆጠረ፡፡

 • ብአዴን የጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎና ሸዋን እወክላለሁ ቢልም የአማራ ክልል ካርታን ርስተ-ጉልት አሳልፎ ለትግራይ፣ ለኦሮሞና ቤኒሻንጉል አሳልፎ የሸጠ ምንደኛ ድርጅት ነው፡፡ የአማራ ክልልን ወሰንና ድንበር ያላስከበረ ተላላኪ ድርጅት ነው፡፡ ጨዋታው ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ፤ የጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎና ሸዋ የባንዳዎች ህብረት ፈርሶል፣ በባንዳዎች አንገዛም ትግላችን ጠንክሮ ይቀጥላል፡፡ ህወሓት/ ኢህአዴግና ኦዴፓ ብልፅግና የነቀዘ ስርዓት ተወግዶ አዲስ ሥርዓት ይገነባል፡፡
 • በአማራ ህዝብ ላይ ለደረሰ የዘርና ኃይማኖች ፍጅት (ጆኖሳይድ) ብአዴን/አዴፓ ተባባሪ በመሆን የአማራ ህዝብን አንገት ያስደፋ አሳፋሪና አጎብዳጅ የማፍያ ድርጅት ነው፡፡ የብሄረ-አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ባንዳ ድርጅት በአማራ ህዝብ ትግል በ2013 ዓ/ም በምርጫ ይወገዳል፡፡ የአማራ ህዝብ ድርጅቶች በጋራ አንድ በመሆን ብአዴን በማስወገድ ታሪክ የጣለባችሁን አደራ ተወጡ፡፡

አዲስ አበባ እንደ ሻሸመኔ አትቃጠልም! በሻሸመኔ የዘርና የኃይማኖት ፍጅት (ጆኖሳይድጀ) በአጋንቱን ቄሮ  አንድ መቶ ሰማንያ ሰባት ሰዎች ሲገደሉ፣ ከተማዋ ስትነድ የደረሰ አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ ሠራዊት እጁን አጣጥፎ ይመለከት ነበር፣ ከኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ ቢጠብቁም ትዕዛዝ የሰጠ አልነበረም፡፡  የብአዴን ተመስገን ጥሩነህ ድጋፉን ሽመልስ አብዲሳን ካባ በማልበስ ገልፆል፡፡  ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም  በአባይ ሚዲያ እንግዳችን ፕሮግራም “የአዲስ አበባ ወጣት ሲነሳ የሻሸመኔው ቀልድ ይሆናል” በማለት የአዲስ አበባ ወጣት ከተማዋን እንደሚያቃጥላት በስህተት ተንብየዋል፡፡ ሆኖም የአዲስ አበባ ወጣት በ1966ዓ/ም አብዬት ሲፈነዳ በጨዋነት በትግሉ ተሳተፈ እንጂ ጥፋት አልፈፀመም፡፡ በግንቦት 20 ቀን 1983 ህወሓት/ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ በፊት ጀምሮ ከተማዋን ሲጠብቅ ነበር እንጂ ከተማዋን አላወደመም፡፡  ከተማ በማቃጠል ወጣቶች የሚያገኙት ጥቅም ስለሌለ ወጣቱ ለአዲስ አበባ ከተማ ዘብ ይቆማል እንጂ በአዱ ገነት ላይ እጁን አያነሣም፡፡ በ2012ዓ/ም  በሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተጠንስሶ የነበረውን እልቂትና ውድመት የአዲስ አበባ ወጣቶች በባዶ እጃቸው የአጋንቱን ቄሮ ገጀራና ሜንጫ በመማረክ በትሬንታ ተጭኖ የገባውን መንጋ አስተምሮ በመልቀቅ ባይመክት ኖሮ ቄሮ አዲስ አበባን እንደ ሻሸመኔ ዶጋ አመድ ለማድረግ ነበር ፍላጎቱ፡፡ ‹‹ምኒሊክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፣ ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ግዜ ሀበሻ›› ተዘፍኖለታል፡፡ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ባለጸጋ ኢንቨስተሮች ለአዲስ አበባ ወጣቶች ሥራ በመፍጠር  መተዳደሪያ ገቢ እንዲያገኙ በማድረግና በጥበቃ ሥራ በማሳተፍ ለሥራ አጦች ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያምና ጋዜጠኛ መዓዛ መሃመድ ያላወቁት ነገር በሻሸመኔ ቄሮ በግፍ ሰዎች ያረዱ፣ ከተማዋን ያቃጠሉ፣ ከሌላ አካባቢ በትሬንታ ኮትሮ ተጭነው የመጡ ወጣቶች ናቸው፡፡ በሻሸመኔ በብዙ ቢሊዮን ብር የሚቆጠር ንብረት ወደመ፣ ህዝብ መተዳደሪያ ስራውን አጣ፣ በከተማዋ ሊሰሩ ያሰቡ ኢንቨስተሮች ሸሹ፣ በከተማዋ ይስተናገድ የነበረ መንገደኛ ተገታ፣ ድህነት ሰፈነ፣ ለስንቱ ይተርፉ የነበሩ ባለጸጎች ተመፅዋች ሆኑ፡፡ የቄሮ ፅንፈኞች ድንቁርና ፋብሪካ በማቃጠል ወጣቶችን ስራ ፈት ማድረግ ነው፣ ትምህርት ቤት፣ ክሊኒክ ፣ሆቴል በማቃጠል ድንቁርና በሽታን ከማስፋፋት በቀር ምን አገኙ፡፡ የኦህዴድ/ ኦዴፓ ብልፅግና ፓርቲ የኦሮሞ ፅንፈኛ የቄሮ ወጣቶችን አዕምሮ በማነፅ፣ የሃይማኖት አባቶች ፈሪሃ እግዚአብሄር ትምህርት ቢያስተምሮቸው፣ አባ ገዳዎችና ሽማግሌዎች ልጆቻቸው ሠርተው እንጂ ዘርፈው የመብላት የወሮበላ ቅጥረኛ ነፍሰገዳይ ስራ እንዳይሰሩ ቢመክሮቸው የተሸለ ቀን ይመጣል እንላለን፡፡ በአፋጣኝ ይህ እርምጃ ካልተወሰደ የኦሮሚያ ክልል ህዝብ ለባሰ ድህነትና ድንቁርና ተጋልጦ የክልሎች ጭራ ይሆናል፡፡

 • ‹‹ወጣሁልህ ወጣሁልህ፣ዝንጀሮ ጎረቤት ከሆነህ!››ሽመልስ አብዲሣ

‹‹ከአራጂ የቄሮ ጎረቤት፣የዝንጀሮ ጎረቤት ይሻላል›› ያሸመኔ ህዝብ

 • ‹‹ኦሮሞ ለመናገር በሚከብድ ደረጃ ችግር ውስጥ እንዲገባ በቅኝ ገዥው ሥርዓት ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል ጉዳት ደርሶበታል፡፡›› ዶክተር አብይ አህመድ

የኦዴፓ ብልፅግና ሽሮ ፈሰስ ፓርቲ መሪ ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ሥርዓት እንደነበርና የኦነግ ኦሮሞ ህዝብም እንደ ሻብያ ኤርትራ፣ ህወሓት ትግራይ፣ ሲአን ሲዳማ ህዝብ ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል እንደተገዛ ዓይነት አድርጎ ተናግሮል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ  ቅኝ ገዥ አገራቶች ‹‹በበርሊን የአፍሪካ ቅርምት›› ከ1884 አስከ 1960እኤአ ተብለው በዘመኑ የሚታወቁት ልዕለ ኃያል አገራት  እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ ጣሊያን ፖርቱጋል፣ ስፔን የነበሩ ሲሆን ኢትዮጵያም ነበረች ማለት ድንቁርና ሲሆን ከአንዳችም መፅሃፍትና ጎግል ድረገፆች የማይገኝ ፌክ ኒውስ (የውሸት ወሬ) ነው፡፡ ጣልያን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ወረራ ያካሄደችውና ኢትዮጵያዊያንም ለነጻነታቸው ተጋድለው በድል አድራጊነት ነፃ የወጡት ታሪክ ምስክር ነው፡፡ የዲጂታል ቴክኖሎጅ ዘመን ወጣቶች በቅፅበት ከእጅ መዳፋቸው ላይ በምትገኝ ሞባይል ጠቅላዩን ፉርሽ ስለሚያደርጎቸው ሌላ ውሽት ፍጠሩ እንላለን፡፡  ዶክተር አብይ ስለ ቅኝ ግዛት ዘመን (Colonialism) በዓለም አቀፍ ደረጃ የካፒታሊስት ሥርዓት የደረሱ አገራት ጥሬ እቃ ለማግኘት የቅኝ ግዛት ሥርዓት በመንደፍ አንድን አገር ህዝብና ግዛት በፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳይ በጦር ኃይል በመውረርና በቁጥጥር ስር በማድረግ የሃገሪቱን የመዕድን ኃብት ነዳጅ፣ ወርቅና አልማዝ፣በመበዝበዝና መሬቱን ለጥጥ እርሻ በመጠቀም ለልብስ ፋብሪካ ጥሬ እቃ ግብዓት በመጠቀም መመዝበር ላይ ያተኮረ እንዲሁም በባህላዊ የባዕድ ወረራ የሃገሬውን ባህል በማጥፋት የበታችነት ስሜት ውስጥ በመዝፈቅ፣ ቅኝ ገዥዎቹ ያልሰለጠነ ህዝብን ለማዘመን እንደመጡ በመስበክ የሚገዙበት ሥርዓት ነበር፡፡ ‹‹ Colonialism is the policy of a country seeking to extend or retain its authority over other people or territories, generally with the aim of economic dominance. In the process of colonisation, colonisers may impose their religion, economics, and other cultural practices on indigenous peoples. Wikipedia››

ከሽመልስ አብዲሣና ቄሮ ጎረቤትነት የዝንጀሮ ጎረቤትነት የተሸለ ነው ቢያንስ አያርዱህም፡፡ ሽመልስ ይሄን አረመኔ ፅንፈኛ የቄሮ ባህል መቶ ሰማንያ ሰባት ሰዎች  ማረድና ሴት መድፈር፣ ንብረት ማቃጠል ሆቴል ማጋየት፣ ትምህርት ቤት ማንደድ፣ ፋብሪካ ማቃጠል፣ መንግሥታዊ ተቆማትን ማውደም አልቻለም፡፡ ሽመልስ ለማስቆም እውቀትም ችሎታም የሌለው ፖለቲከኛ ነው፡፡ ኢንቨስተሮች ከኦሮሚያ ክልል ወጥተዋል፤ ወደፊትም ኢንቨስት ለማድረግ አያስቡም  የኦሮሞን ህዝብ ደሃ እንዲሆን አደረጋችሁት፡፡ በዚህ የተረገመ ስራው የአማራ ክልል ክልላዊ መግሥት ምስለኔው ሹመኛ ፕሬዜዳንት ተመስገን ጥሩነህ ካባ አለበሱት ህዝቡም፣ ‹‹አህያ ለአህያ ቢራገጥ ›› ብሎ ተረተባችሁ፡ ብአዴን/ ኦዴፓ ከሥልጣን መንበሩ እስካልተወገደ ድረስ የአማራ ህዝብ ነፃ አይወጣም፡፡ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥትን ለማሽመድመድ  የጎንደር፣ የወሎና ሸዋ ህዝብ ራሱን አደራጅቶ የእራሱ አስተዳደር በመመሥረት ከተመስገን ጥሩነህ አገዛዝ መላቀቅ አለበት፡፡

ኦነግ/ኦህዴድ/ ኦዴፓ አዲስ አበባ ከተማ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ነው ሲሉ አንድም የእነሱ የሆነ አሻራ የጠፋ ኪነ-ህንፃ፣ ብርቅና ድንቅ ቅርሳ ቅርሶች፣ መንግሥታዊ ተቆማት የተገነባ ህንፃዎች፣ ወዘተ ለላንቲካ ያህል በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ማሳየት በተቻላቸው ነበር፡፡ በ1889 እኤአ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና መዲና ሆና በዳግማዊ ምኒሊክ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያና ግርማዊት ንግሥተ ነገሥታት እቴጌ ጣይቱ ቡጡል ተቆረቆረች፡፡ ከዛ በፊት ያለውን የአዲስ አበባ ታሪክ በበረራ መጽሃፍ ያንብቡ፡፡ በዛ ዘመን ታላቁ የዳግማዊ ምኒልክ ቤተ-መንግሥት፣ ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት፣ እቴጌ ጣይቱ ሆቴል፣ የምድር ባቡር ጣቢያና የባቡር አገልግሎት፣ ዳግማዊ ሚኒልክ ሆስፒታል፣ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ ወዘተ ሁሉ ሥልጣኔ በእሳቸው ዘመን የገባ ነበር፡፡ ታላቁ የዳግማዊ ሚኒልክ ቤተ-መንግሥት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ አንጡራ ኃብትና ቅርሳችን በመሆኑ ኢትዮጵያዊ መሪዎች ዘር ማንዘር ሳትመርጥ፣ ከቀ.ኃ.ሥ፣ ኮነሬል መንግሥቱ ኃለማርያም፣ መለስ ዜናዊን፣ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ዶክተር አብይ አህመድን  በመሪነት አስተናግዳለች፡፡ አዲስአበባ የዛሬ 131አመታት በፊት በኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና ተቆረቆረች፡፡ የሸዋ ክፍለሃገር ዋና መዲና ተባለች፣ በሸዋ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ ትግሬ፣ ሱማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ወዘተ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መዲና ናት፡፡ ‹‹ኦሮሞ ለመናገር በሚከብድ ደረጃ ችግር ውስጥ እንዲገባ በቅኝ ገዥው ሥርዓት ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል ጉዳት ደርሶበታል፡፡›› ዶክተር አብይ አህመድ እያለ በኦሮሙኛ ቌንቌ ለኦሮሞ ተናጋሪዎች ያወራል፡፡እንዲህ ዓይነት አስተምሮት ከአንድ መሪ የማይጠበቅ እንደዛ ለመደረጉ ማስረጃና መረጃ የሌለው ተራ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡

አዲስ አበባ እንደ ሻሸመኔ አትቃጠልም!!! የአዲስ አበባ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ጋርድ ሁሉም ህዝብ ከቀበሌው፣ ወረዳው፣ ክፍለ ከተማው ጀምሮ በሰላማዊ መንገድ ህብረተሰቡንና ንብረቶቹን መጠበቅ ሓላፊነትና ግዴታ አለበት፡፡  ዶክተር አብይ አህመድ ‹‹ሪፓብሊካን ጋርድ›› ገንብቶ የእራሱን ፀጥታና ደህንነት ቤተመንግስቱንና መናፈሻዎቹን ማስጠበቅ ችሎል፡፡ ሰማንያ ሰባት ሰዎች ሲታረዱ ዝምታ፣ መቶ ሰማንያ ሰባት ሰዎች ሲታረዱ ዝምታ ብሎም አጣጥሎ ምንም እንዳልሆነ ነካክቶ ማለፍ የሞራል ውድቀትና የህሊና ልሽቀት፤ የግብርገብነት ደዌ ነው እንላለን፡፡   አረመኔዎቹ ፅንፈኛ ቄሮዎች ሰው ሲያርዱ፣ ሴቶች ሲደፍሩ፣ ንብረት ሲያወድሙ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ ኃይል ሊታደገው አልቻለም፡፡ ደሞዝ የሚቆርጥለትና ቀለብ የሚሠፍርለት ደሃው ህዝብ ሲታረድና ንብረቱ ዶጋ አመድ ሲሆን ይመለከቱ ነበር፡፡  ከእንግዲህ ለአዲስ አበባ ሁሉም ዘብ ይቆማል!!!…..  ‹‹ ዘጠኝ ሞት መጣ ቢለው አንዱን ግባ አለው!!! ›› የአዲስ አበባ ልጆች፡፡

የ2013 ዓ/ም የፖለቲካ ግርዶሽ በኢትዮጵያ

 • የታላቁ ህዳሴ ግድብ ወኃ ሙሌት በዶክተር አብይ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መንግሥቶች የታየ የፖለቲካ ክርዶሽ
 • መለስ ዜናዊ ኤርትራን ለሻብያው መሪ ኢሳያስ አፈርቂ ሸጦ ከመረብ መልስ ኢትዮጵያን ገዛ፡፡
 • ዶክተር አብይ አህመድ ለሕወሓት /ኢህአዴግ ለዶክተር ደብረፂዮን ሰጥቶ ከተከዜ መልስ ኢትዮጵያን ገዛ፡
 • የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥትነት የማንነት ጥያቄ ስም አፈራርሶ ለሲዳማ ክልላዊ መንግስት ሰጠ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ፣ ሃዲያ፣ ጋሞ፣ ጌዲኦ፣ ከፋ፣ ከንባታ፣ ኩሎ፣ ጎፋ፣ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የማንነት ጥያቄ ትግል ይቀጥላል፣ የወያኔ ህገ-መንግሥት ወይ ይፀድቃል ወይ ይደርቃል፡፡
 • ዶክተር አብይ አህመድ የወደፊት እቅድ የኦሮሚያን ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ከኢትዮጵያ የሚችለውን ያህል እንደ ወያኔ ዘርፎ ለመገንጠል ማመቻቸት ይሆናል፡፡ የአብይን መንግሥት ለመጣል ከተንቀሳቀስክ ኦሮሚያ ትገነጠላለች አብራም  አዲስ አበባ ይዛ ወደ ሰማይ ታርጋለች በሚል የፖለቲካ ግርዶሽ የህዝቡን ዓይን በመጋረድ አስተዳደራቸው ይቀጥላል፡፡ አዲስ አበባን ከተማ በኦሮሚያ ስነ-ህዝብ ፕወዛ አጠንክሮ በመቀጠል አንባገነናዊ አገዛዙ ዓይን ያወጣ ይሆናል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አንድ ሜትር ካሬ ቦታ ሦስት መቶ ሽህ ብር እያወጣ መሬት በመሸጥ ከወርቅና ዘይት መዕድን የበለጠ መዛቅ መቻሉን ከህወሓት/ ኢህአዴግ የተማረው ኦዴፓ ብልፅግና በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ድርድር የለውም፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ካርታ አዲስ አበባን ጠቅልሎ እንዲቀጥል ለማድረግ ህገመንግሥቱን እነ ዶክተር አብይ አህመድ መቀየር አይሹም፡፡ ለማና የአብይ ቲም  በኢትዮጵያ ስም በመማልና በመገዘት ኦሮሚያን መገንጠል ድብቅ አጀንዳ እንዳላቸው ለመረዳት የፖለቲካ ብፁሃን አይጠበቅባቸውም፡፡  የአብይ መንግሥት ከቲም ለማ፣ ከጁሃር መሃመድ በአጠቃላይ ከኦነግ፣ ኦነግ ሸኜ፣ ኦፌኮ፣ ወዘተ ጋር የዓላማና እቅድ ልዩነት የላቸውም በብዙ ነገር አቆማቸው አንድ ነው፡፡ በአባ ገዳዎች አብይና ጁሃር ይታረቃሉ ፡፡
 • በ2013ዓ/ም የብልፅግና ፓርቲ የኢትዮጵያዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳይጠናከሩ ማድረጉ ይቀጥላል፡፡ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ መሪ እስክንድር ነጋና ጎዶቹን  በፀረ ሽብርተኛነት ክስ በመመስረት ህዝብ እንዳያውቅ ተድበስብሶ አልፎል፡፡ በተመሳሳይ ብልጽግና ፓርቲ የአማራ ድርጅቶች በተለይም አብን፣ መአድ፣ ወዘተ  የ2013ዓ/ም የጥቃት ኢላማቸው መሆናቸው ጠንቆይ መቀለብ አያሻም፡፡
 • ግንቦት ሰባት ኢዜማ የፖለቲካ ጨዋታው ምጣዱን የማሰስ ያህል ነው ከሚጋገረው እንጀራው ድርሻ የለውም፡፡ ግንቦት ሰባት ኢዜማ ከኤርትራ በርሃ ሳለ ከተለያዩ የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባሮችና ከኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጭ ግንባር ጋር ተፈራርሞ የመጣበትን ድብቅ የፖለቲካ ስምምነት ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ብልፅግና ፓርቲ ጋር ሆነው ለመቶ አመት ለመግዛት አቅዶል፡፡ ወያኔ መቶ አመት ብሎ ሃያ ሰባት አመት ባጭር ተቀጨ፣ ብልፅግና መቶ ብሎ አምስት አመት ከገዛ ባጭር ይቀጫል፡፡ ኢዜማ በ2013 ዓ/ም ለሁለት ይከፈላል የአብይ ሥርዓት ደጋፊዎችና ነቃፊዎች ጎራ ይፈረጃሉ፡፡ የኢዜማ ነቃፊዎች ከኮንዶሚኒየም ፖለቲካ ተሸግረው ወጥተው በሃገሪቱ የዘርና የኃይማኖት ፍጅት (ጆኖሳይድ) መፈፀሙን በአቆም መግለጫቸው ሲገልፁ፣ በህገ-መንግስቱ ጉዳይ ላይ ያላቸው አቆም፣ በአዲስ አበባ ጉዳይና በነጁሃር መሃመድ  የኦነግ ፖለቲካ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር አንድ መሆን ሲገለፅላቸው ይፋታሉ፡፡
 • የኢዜማ ፕሮፊሰር ብርሃኑ ነጋ በሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተነሳ የተፈጸመ የዘርና ኃይማኖት ፍጅት (ጆኖሳይድ) ያለመቀበል ክህደትና ተራ ግጭት አድርጎ ማለፍ የኦዴፓ ብልፅግና ፓርቲ ከመደገፍ የመነጨ  አድርባይነት ካልሆነ በስተቀር ኢዜማ እራሳቸው ሄደው  (ጆኖሳይድ) መሆንና አለመሆኑን በማጣራት አቆም እስካልወሰዱ ድረስ በኢትዮጵያ ህዝብ ተቀባይነት አይኖራቸውም፡፡ በተመሳሳይ በህገመንግስት ጥያቄ፣ በአዲስ አበባ ጥያቄ፣  በዘር ፌዴራሊዝም ጥያቄ ወዘተ ያላቸውን የፖለቲካ አቆም ለህዝብ ግልፅ ማድረግ ይጠየቅባቸዋል እንላለን፡፡

 

የህግ ሉዓላዊነት በኢትዮጵያ ይከበር!!!

ባልደራስ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች የህሊና እስረኞች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም፣ እንዲሁም ልደቱ አያሌው፣ ይፈቱ!!!

አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ክልላዊ መንግሥትነት ይገባቸዋል!!!

መልካም አዲስ አመት ይሁንልን!!!

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.