እኛም ባላደራዎች ነን!! – ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ

Global እኛም ባላደራዎች ነን!!   ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ

መስከረም 1 ቀን 2013 ዓም  (11-09-2020)

ትውልድ ሄዶ ትውልድ ሲተካ እዬተቀባበለ  የሚያኖረው ትልቁ  አደራና ቅርስ ቢኖር የአገርን አንድነትና ልዑላዊነት ማስከበር ነው።ስለሆነም የአሁኑ የእኛም ትውልድ ከአያት ቅድመአያቶቹ የተረከባትን አገር፣ኢትዮጵያን አስከብሮ ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ ግዴታና አደራ አለበት፣አለብን።ስለሆነም  እኛም ባላደራዎች ነን።

ይህንን የትውልድ ግዴታና ተልእኮ በግንባር ቀደምትነት ለመወጣት በባላደራ ስም ተደራጅቶ የሚንቀሳቀሰው ድርጅት በአዲስ አበባ ከተማ ና በኑዋሪው እጣፈንታ ላይ ያንዣበበውን አደጋ ለመመከት የሚያደርገውን ታሪካዊ ትግል የብዙ ፖለቲካና የሲቪክ ማህበራት የትብብርር መድረክ የሆነው ድርጅታችን  ከልብ የሚደግፈውና የሚቆምለት ዓላማ መሆኑን ሊያረጋግጥ ይወዳል።ይህን ብሔራዊና  የማንነት ጥያቄ አንግበው የሚታገሉትን የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ንቅናቄ አባላት ትግላችሁ ትግላችን ነው ለማለት እንወዳለን፤ብሎም የሚደርስባቸውንና በመድረስም ላይ ያለውን መንግሥታዊ ጥቃት እናወግዛለን።

የኢትዮጵያን አንድነት ከፈተና ውስጥ የከተተው የጎሰኞች ቡድን  ስምና መልኩን እዬቀያዬረ በሥልጣን ኮርቻ ላይ መቀመጡን ተከትሎ በሚያደርሰው ጉዳት የአገራችን ህልውና ብቻ ሳይሆን የያንዳንዱ ዜጋ የመኖር መብትና ዋስትናው በጥያቄ ውስጥ ከገባ ውሎ አድሯል።ከስጋትም ባለፈ ብዙ ጥቃቶች ተፈጽመውበታል።በሚዘገንን ሁኔታ፣እንኳንስ ሰላማው  የሰው ልጅ፣ህጻን ወጣት፣ ሽማግሌ፣አሮጊት ቀርቶ  ሊያጠቃ የመጣ አውሬ በማይገደልበት መልኩ ተገሏል፣ተጨፍጭፏል፣ተፈናቀሏል፣ንብረቱ ወድሟል።ይህንን  ጥቃትና አደጋ የመከላከል ግዴታ የሁሉም ነው፤ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ ሳይሆን ሰው መሆን ይበቃል።አገርና ሕዝብ ሳይኖር ሰላምና እድገት አይታሰብም።

በአገራችንና በሕዝቡ ላይ ላለፉት ብዙ ዓመታት በተለይም ላለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ጎሳን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋና በደል እንደተፈጸመ ማንም አይክደውም።ያንንም ጭፍጨፋና በደል የመሩና ያስተባበሩ  ወንጀለኞች መኖራቸው፣ከነሱም መካከል ጥቂቶቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል። ይህ በተቀናጀና መንግሥታዊና የመንግሥት ባለስልጣናት ተሳትፎም ባለበት መልኩ የተፈጸመ ትልቅ የጭፍጨፋ ወንጀል  በዓለም አቀፍ ደረጃ  በፍርድ ቤት የሚያስጠይቅ ጉዳይ ነው።ድርጅታችንም ለሚመለከተው የዓለም ወንጀል ፍርድ ቤት የአቤቱታ ደብዳቤውን ማቅረቡንና ለትኩረትም በቅደም ተከተል ተራ ውስጥ እንደገባ  ለመግለጽ እንወዳለን።

በስልጣን ላይ ያለው አካል ወንጀለኞችን በመያዝ ሂደቱ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ የመምታቱን ስልት እንደተጠቀመበት ለማዬት ችለናል።

በወንጀሉ የሚጠረጠሩትን ጥቂት  ግለሰቦች ከማሰሩ ጋር ተያይዞ የመንግሥትን ተግባር የሚነቅፉትን፣ አማራጭ የፖለቲካ መፍትሔ የሚያቀርቡትን፣በሃሳብ ልዩነት የሚሞግቱትንና መንግሥትና የመንግሥት አካላት የፈጸሙትን ወንጀል በማጋለጥ ፍትህ የጠየቁትን  ግለሰቦችና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፣ደጋፊዎችን ጭምር በተፈጸመው ዘግናኝ የሕዝብ ጭፍጨፋ ወንጀል ሽፋን ማሰሩ ግን ትክክልና አግባብ ያለው ነው ተብሎ አይታመንም።ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ የሚለውን ምሳሌ መተግበር ይሆናል። ከሁሉም መስፈርት የወረደና የሥልጣን ተግደርዳሪ ይሆናል ከሚል ስጋትና ፍርሃት  የመነጨ እኩይ እርምጃ እንደሆነ ድርጅታችን ያምናል።ለዚያም ነው በገሃድ የሚታይ  የቃል፣የምስልና የተግባር ማስረጃ ካለባቸው ወንጀለኞች ጋር ንጹሃንን ቀላቅሎ ማሰርና ለከፍተኛ ቅጣት የሚያበቃ ክስ መመስረት ዱባና ቅል ሆኖብናል።በተቃዋሚነት ቢመሳሰሉም፣ሁለቱም በሥልጣን ላይ ያለውን አካል ቢቃወሙም በተቃውሞ ይዘትና በፖለቲካ አስተሳሰባቸውና መስመራቸው  የተለያዩ መሆናቸውን ማንም አይክደውም።ያላቸው ልዩነት ኢትዮጵያን በማጥፋትና ኢትዮጵያን በማዳን መካከል  ያለ ልዩነት ነው።

በዚህ ዓይን ባወጣ መንግሥታዊ ሸፍጥና ሴራ ለጥቃት የተዳረጉት ሃቀኛ አገር ወዳድ ዜጎች ብዙ ቢሆኑም ከነሱ መካከል ሕዝቡ የሚያውቃቸውና የሚያምናቸው ብሎም መንግሥት ባቀረበባቸው የክስ መንጀል ላይ የሚሳተፉ ሳይሆኑ ወንጀሉን የሚቃወሙ ሰዎችን ከባላደራ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ   አቶ እስክንድር ነጋን፣አቶ  ስንታዬሁ ቸኮልን፣ወ/ሮ አስቴር ስዩምን፣አቶ  ሄኖክ አክሊሉን፣ እንዲሁም በእነሱ የክስ መዝገብ ውስጥ የተካተቱትን ሁሉ፣በተጨማሪም በሌላ የክስ መዝገብ የተጠቀሱት  አቶ ልደቱ አያሌውን  በነጻ እንዲለቅ ድርጅታችን ይጠይቃል።

የባላደራዎች ወንጀል ሆኖ የተቆጠረባቸው በዃላ ቀሩ  በገዳ ህሳቤ አዲስ አበባንን ነዋሪውን ሕዝብ “ሞጋሳ” የማድረጉን ሂደት በመቃወማቸው ሲሆን የአቶ ልደቱ አያሌው ደግሞ ብዙሃኑ የሚጠይቀውን የሽግግር መንግሥት ጥያቄ በማንሳታቸው ነው።

እነዚህን ሃቀኛ የሕዝብ ልጆች  በአገር አሸባሪነት፣በአመጽ ቀስቃሽነትና ፍጅት አዘጋጅነት መወንጀል የሚያሳፍር ከመሆኑም በላይ  አህያውን ፈርቶ ዳውላውን እንደሚሉት ይሆናል።ስለሆነም መንግሥት በጎሰኝነት ስነልቦና  ለሚቀርባቸው ወንጀለኞች ሂሳብ ማወራረጃ አድርጎም ለመጠቀም  የወሰደው እርምጃ  ከሆነም በጥፋት ላይ ጥፋት እዬከመረ መውደቂያውን  ከሚያፋጥን ይልቅ ጥፋቱን አምኖና አርሞ  ንጹሃኑን እንዲፈታና በሃሰት ላቀረበባቸው ውንጀላም ይቅርታም መጠዬቅ አለበት እንላለን።

አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ እንደሚባለው መንግሥት የተስፋ ዳቦ እያጎረሰ፣ በብልጭልጭ ትእይንትና ፕሮፓጋንዳ የሕዝቡን ትኩረት በመለወጥ በሃቀኛ ለውጥና አገራዊ አንድነት አስከባሪዎች ላይ የከፈተውን ዘመቻ በአስቼኳይ እንዲያቆም እንጠይቃለን።መንግሥት  በባላደራዎች  ላይ ዘመቻ ለማካሄድ ያቀደው ” የግልጽ ጦርነት” አዋጅ  ወንጀሉ ተፈጸመ  ከተባለበት ጊዜ በፊት መሆኑን ለማስታወስ እንወዳለን።

ፍትህ ለእውነተኛ አገር ወዳዶች!

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ
International Ethiopian Solidarity Forum
E mail  inter.ethiopiansolidarityforum1@gmail.com

1 Comment

  1. This is the way we need to talk to those horribly hypocritical , conspiratorial , extremely dishonest ethnocentric ruling elites who continued playing the very bloody political game they played for a quarter of a century . Yes, they must be told that there will not be any innocent Ethiopian who will keep neither silent nor inaction whenever the very essence of his or her tolerance for the sake of saving the country is badly compromised ! Yes, they must be told that they need to behave and act with a certain degree of human common sense and help the situation they terribly spoilt get better !’
    The powerful words of enough is enough ! desperately need to be armed with the movement of action , not business as usual !’n

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.