ለኢትዮጵያና ለመላው ኢትዮጵያዊያን ያለኝ የአዲስ ዓመት ምኞት – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

Happy New year

aklog birara1
አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ኢትዮጵያ ሃገራችን በታሪኳ ታላቅ የነበረች ወደፊትም ሁኔታዎች ከተመቻቹ የበለጸጉ ሃገሮች ከደረሱበት ደረጃ ለመድረስ በሁሉም ዘርፎች እምቅ የተፈጥሮ ኃብትና ታታሪ ሕዝብ ያላት አገር ናት። እመርታዊ ለውጥ የሚያስፈልገው የፖለቲካ ባህላችን፤ የአስተሳሰብ ሁለመናችንና ዘዴያዎቻችን ላይ ነው።

በግልጽ ላስቀምጠው፤ ከፍተኛው ተግዳሮቷ ወንድማማችነት፤ እህትማማችነት፤ አብሮና ተደጋግፎ፤ ተመካክሮ፤ ከመናገር በፊት ለማዳመጥ ትኩረት ሰጥቶ፤ አንዱ የሌላውን ገንቢና ብሩህ ሃሳብ ተቀብሎ፤ “ያንተ ችግር የኔም ነው” ብሎ ድህነትን፤ ኋላ ቀርነትን፤ የውጭ እርዳታ አምልኮን ለመቅረፍ ቆራጥነት ያለው ትውልድ አይታይም። እንዲያውም ለብዙ ሽህዎች ዓመታት የተዋለደውን፤ የተዛመደውን፤ የተሳሰረውን ሕዝብ በዘውግና በኃይማኖት እንዲለያይ ባደረገው፤ ሕዝቡ ተወያይቶና ተመካክሮ ባልወሰነው የቋንቋና የዘውግ ሕገ-መንግሥት እና አፓርታይድን በሚመስል የክልል አስተዳደር እርስ በርሱ እንዲጋጭ ተደርጓል።

የዚህ አሉታዊ ውጤት በግልጽና በተደጋጋሚ ታይቷል። ለብዙ ወራቶች ታዛቢዎች “ኢትዮጵያ ስንት መንግሥታት አሏት? ዘጠኝ አገሮች፤ ዘጠኝ መንግሥታት? ይህ ችግር በውይይት፤ በብሄራዊ መግባባት መፈታት አለበት” ሲሉ ቆይተዋል። በትግራይ ክልል የተካሄደው ሕገ ወጥ “ምርጫ” ተቀባይነት የለውም የሚለውን ተቀብየ፤ ይህ ብቻ በቂ አይመስለኝም እላለሁ። ምክንያቱም የነዋሪዎቹ ሰብአዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ተገፈዋል። ምርጫው ከወልቃይት-ጠገዴ-ጠለምት፤ ሰቲት-ሁመራ፤ ራያና አዜቦ የመሬት ነጠቃና “ታላቋን ትግራይ” ከመመስረት ጋር ግንኙነት እንዳለው አስቀድመው ያሳሰቡና ለነዋሪው ሕዝብ ድጋፍ እንዲሰጠው ምክር የለገሱ ግለሰቦችና ስብስቦች ነበሩ። ሰሚ ግን አላገኙም።

በምርጫ አሳቦም ሆነ በሌላ ዘዴ የሚካሄድ ህገ ወጥ ድርጊትና ውንብድና ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ያባብሳል። ማንም አሸናፊ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ አይታይም። ለኢትዮጵያና ለድሃው ሕዝብ የሚያስብ ግለሰብ ሆነ የፖለቲካ ድርጅት ካለፉት አርባ ዓመታት የእርስ በእርስ ግጭቶችና ውድመቶች ሊማር የሚችለው አስኳል ትምህርት ከብሄራዊ ውይይትና መግባባት ውጭ ሌላ አማራጭ አለመኖሩን ነው። በርሃብ አለንጋ የሚገረፈው ብዙ ሚሊየን ድሃ ሕዝብ ከድህነት አሮንቃ የሚያወጣውን አማራጭ እንጅ ኢትዮጵያንና መላውን ሕዝቧን የጦርነት አውድማ የሚያደርግ ኃይል አይደለም። ድህነት የዘውግና የኃይማኖት ድንበር የለውም።

ይህን ችግር ከብሄራዊ ክብር አንጻር ላቅርበው። በ2020 በብዙ ሚሊየን የሚገመት ድሃ ሕዝብ አሁንም የሚኖረው በውጭ ለጋሶች ድጎማና ድጋፍ ነው። ድህነትና ብሄራዊ ክብር አብረው አይሄዱም። ለመከበር ከፈለግን ድህነትን መቅረፍ አለብን። ለማስታወስ፤ ኢትዮጵያ የውጭ ድጎማና እርዳታ ማግኘት የጀመረችው በ1952 ነው። ያን ጊዜ፤ ብዙ የምስራቅ ኤዢያ አገሮች በቅኝ ገዢዎች ይገዙ ነበር። ዛሬ የለሙ አገሮች አባላት ናቸው።

የውጭ እርዳታ እመርታዊ ለውጥ አላስገኘም።

የውጭ እርዳታን ሚናን ስመራመር፤ አሜሪካኖች ለኢትዮጵያ ድጋፍ መስጠት የጀመሩት አጼ ኃይለ ሥላሴና የአሜሪካው ፕሬዝደንት ሮዝቤልት በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረገውን ስምምነት በ 1952 ከተፈራረሙበት ጊዜ ጀምሮ ነው። ዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ድጎማና ብድር መለገስ የጀመረው ተቋሙ ከተመሰረተበት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት መጨረሻ ከ 1944 ጀምሮ ነው።

ኢትዮጵያ በውጭ አገሮችና ተቋማት ድጎማና ብድር ልትለማ ብትችል ኖሮ እስካሁን ያገኘችው ግዙፍ ድጎማና ድጋፍ መሰረታዊ፤ መዋቅራዊና ተቋማዊ ለውጦች እናይ ነበር። የውጭ ድጎማና ብድር ተጠቃሚዎች የፖለቲካ ልሂቃን፤ አለቃዎች፤ ስብስቦች፤ ቤተሰቦች፤ ወዳጆች፤ የፖለቲካ ነጋዴዎችና ተመሳሳይ ክፍሎች ናቸው። አርባ ቢሊየን ዶላር ድጎማ ተሰጥቶት አርባ ቢሊየኑን የውጭ ምንዛሬ በሙሉ የተዘርፈበት አገር ማነው? ብለን ብንጠይቅ ኢትዮጵያ ብቻ ናት።

አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚኖርበትን ሁኔታ ሳስበው ይዘገንነኛል። ክጭቃና ከሳር በተሰራ ቤት የሚኖረው ገበሬ፤ እንኳን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሊያገኝ ቀርቶ ቤተሰቡም፤ ከብቱም፤ ፍየሉም፤ በጉም፤ ዶሮውም ባንድ መኖሪያ ቤት የሚኖሩባት አገር ናት። በዚህ ሁኔታ የሚኖር ህዝብ ጤናማ ሊሆን አይችልም። ዛሬ አንድ አዲሱን በዓል ለማክበር የሚፈልግ ቤተሰብ አንድ በግ ለመግዛት እስከ 6.000 (ስድስት ሽህ) ብር ፈሰስ ማድረግ አለበት። የቤት ኪራይ ንሯል። መሬት ጠቧል። የስራ እድል የሌለው ወጣት በብዙ ሚሊየን ይገመታል። ኢትዮጵያ በያመቱ ቢያንስ ሁለት ሚሊየን የስራ እድል መፍጠር አለባት። የዓለም ሁኔታ እየተለወጠ ስለሄደ ይህ ወጣት ትውልድ ተሰዶ ስራ ለማግኘት ያለው እድል ጠቧል፤ ወደፊትም እየጠበበ ይሄዳል።

ይህ ሁኔታ የሚያስተምረን ብዙ ነገሮች አሉ። ከእነዚህ መካከል የሰራነውን ማውደም፤ ኢ-ሰብአዊ፤ ኢ-ፍትሃዊ፤ ጸረ-ህዝብና ጸረ-አብሮነት መሆን አንዱ ገጽታ ነው። ሻሸመኔና ዝዋይ የተካሄደው እልቂትና ውድመት ዋናና በምንም መደገም የሌለበት ምሳሌ ነው። በወልቃይት-ጠገዴ-ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ፤ ራያና አዜቦ የሚካሄደው ጭካኔ የተሞላበት የመሬት ነጠቃና ቅርሚት ባስቸኳይ ካልቆመ ተመሳሳይ እልቂትና ውድመት እንደሚከተል ማሰብ ያስፈልጋል።

ለመግቢያ ያቀርብኩት እንዳለ ሆኖ፤ ያለፈውን ዓመት ሸኝተን ወደ አዲሱ ዓመት ስንሸጋገር እኔ ለኢትዮጵያና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የምመኛቸው የሚከተሉትን ነው።

 1. የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ማህበረሰባዊ ተቋማት በጋራ ሆነው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለድርድር አይቀርቡም፤ ይህ ሂደት አይታሰብም የሚል አቋም መውሰድና ይህን ብሄርዊና አገራዊ አቋም ለመላው የኢትዮጵያ፤ የአፍሪካና የዓለም ሕዝብ ይፋ ማድረግ አለባቸው።

 

 1. በእኔ እምነት ዜግነቴ አማራ፤ ኦሮሞ፤ ትግሬ፤ ሶማሌ፤ ወላይታ፤ ጉራጌ፤ አኟክ ወዘተ ነው የሚለው ትርክት አገራችን እያፈራረሳት ነው። ሌሎች የጥቁር አፍሪካ አገሮች ንቀውት ያለፉትን የዘውግ መለያ ሂደት እኛ እንዴት ለመቀበል ተገደድን፤ ማን አስገደደን? የሚለው ጥያቄ የሚመለስበት ወቅት አሁን እንጅ ኢትዮጵያ እንደ ዩጎስላቭያ ከተበታተነች በኋላ ሊሆን አይችልም። ይህን የእሴት አመለካከት ለወጣቱ የምንሳተምርበት ወቅት ቢዘገይም ከአሁን በኋላ ለነገ ሊባል አይችልም።

 

 1. ሕገ መንግሥቱና የክልሉ አስተዳደር ስርዓት በተደጋጋሚ ለተነሱት ግጭቶች፤ እልቂቶች፤ ውድመቶች፤ ውንብድናዎች፤ ዘረፋዎች፤ የሕግ ጥሰቶች፤ መፈናቀሎች፤ ያለ መረጋጋት ሁኔታዎች ወዘተ መንስኤ መሆናቸው በግልጽ ስለሚታይ፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂነት፤ ሉዐላዊነትና ለመላው ሕዝቧ እውነተኛ ፍትህ፤ ልማት፤ ነጻነትና ዲሞክራሳዊ መብት የሚያገለግል፤ ችሎታ ባላቸው ሞያተኞች የተጠናና ሕዝብ ድምጽ የሚሰጥበት አማራጭ እንዲቀርብ ኮሚሽን መመስረትና ሕዝብ እንዲያውቀውና እዲወስንበት ያስፈልጋል።

 

 1. የኢትዮጵያ መሰረታዊ የውስጥ ችግሮችና ተግዳሮቶች ተራው ሕዝብ አይደለም። ሕዝቡ እጅግ በጣም ጨዋና አስተዋይ ነው። በተደጋጋሚና በመሬት ላይ የሚታየው ተግዳሮት መነሻዎች የፖለቲካ ሽሚያ፤ ዘረኛነትና ተረኛነት፤ ጠባብ ብሄርተኝነት፤ ጽንፈኛነት፤ መንደርተኛነት፤ አክራሪነት፤ ጂሃዲስትነት፤ በነጻነት ስም የሚካሄድ ውንብድነት፤ የፖለቲካ ቁማርተኛነት፤ የጥቅም ነጋዴነት፤ ግፋ-በለውነት፤ ሃሰት ተናጋሪነት፤ ሌብነትና ሙሰኛነት፤ የአመራርና የአስተዳደር ስንኩልነት የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህ ባህሪዎች አገራችንን በዓለም ደረጃ ስመለከተው ዝቅ አድርገዋታል። ቀረብ ብሎ ሲገመገሙ፤ አብዛኛው ሕዝብ በየትኛውም “ክልል” ና በፌደራል ደረጃ፤ በመሪዎች፤ በባለሥልጣናትና በሃላፊዎች ላይ ያለው እምነት ቢያሚያስፈራ ደረጃ ወርዷል፤ “በተፎካካሪ ፓርቲዎች” ላይም እምነትና ተስፋ አይታይም። ሜድያው ሁኔታውን አባብሶታል። “መንግሥት የለም” የሚለው ክፍል ተዛምቷል።

 

 1. እነዚህ የፖለቲካ ባህልና የሥልጣን ሽሚያ፤ በተለይ የሞራል ውድመት፤ የኃላፊነትና የግልጽነት ክፍተቶችና  ተግዳሮቶች ዋናውን ብሄራዊ/አገራዊና ህዝባዊ ተግዳሮት ወደ ጎነ ትተውታል። ይኼውም የኢትዮጵያና የ 115 ሚሊየን ሕዝቧ መሰረታዊና ዋና ችግር ድህነትና ኋላ ቀርነት መሆኑን ነው። የተራበ ወጣት ሕዝብ እርስ በርሱ ይናከሳል፤ ስርዓት አልባ ይሆናል።

 

 1. የበለጸገ ሕዝብ ህግን ያከብራል። የዚህ ችግር መፍትሄ ደግሞ ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ያለው ልማትን ማካሄድ ብቻ ነው። ከሁሉም በላይ በራስ መተማመን ሊፈጥር የሚችለው አማራጭ ብሄራዊ/አገራዊና መዋቅራዊ ለውጥ የሚያመጣ ልማት ሲኖር ነው። በኔ ጥናትና ምርምር እትዮጵያ በአስር ዓመታት ውስጥ መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገሮች ክበብ፤ ማለትም በዓመት የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ከ $1,026-$12,475 ሲሸጋገር ነው። የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ ገቢ በአሁኑ ወቅት በዓመት $790 ነው።

 

 1. ዓለም ባንክ የሚሰሩ ታዛቢዎችን የሚያነጋግር ሰው ሊገነዘብ የሚችለውን ባጭሩ ላቅርበው። “Political disruption, the need for accountability and transparency” የሚሉ መሰረታዊ ችግሮች ይነገራሉ። የፖለቲካው አለመረጋጋት፤ ሃላፊነትና ግልጽነት አለመኖራቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። እነዚህን ለልማት ወሳኝ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች ማስተካከል ያለበት መንግሥት ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ልክ እንደ ሌላው ሁኔታ ቆራጥነት ወሳኝ ነው። የሕግ የበላይነት ቆራጥነትን ይጠይቃል። ባጀት፤ የውጭ ድጎማና ብድር እንዳይባክን ለማድረግ ቆራጥነት ያስፈልጋል። ኃብትና ንብረት እንዳይባክን ከተፈለገ ያባከኑ ወንበዴዎችን ወይንም ወንጀለኞችን መቅጣት ያስፈልጋል፤ የተዘረፈውን ኃብት ማስመለስ ያስፈልጋል ወዘተ።

 

 1. መልካም አገዛዝ ወይንም አስተዳደር (Good and strong governance) የደፋርና የቆራጥ ባለሥልጣናንት ሚናንና ሃላፊነትን ይመለክታል። አንዱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የምመኘው ቆራጥ፤ ደፋር፤ አገር ወዳድና በፍትህ የሚያምን አመራር እንዲኖረው ያስፈልጋል የሚለውን ነው።

 

 1. ኢትዮጵያ ሃገራችን የመንፈሳዊ፤ የስነ ምግባርና የግብረ-ገብነት ውድመት (Catastrophic degeneration of ethics and morality) ከሚታይባቸው የተወሰኑ አገሮች ማከከል ከፍተኛ ደረጃ የሚታይባት አገር ናት። ሃሰት መናገር፤ ማጭበርበር፤ ሌብነት፤ ሙሰኛነት፤ ጭካኔ፤ ሰውን፤ ዘውግን፤ ኃይማኖትን ማዋረድ፤ “እኔ ብቻ አውቃለሁ” ባይነት፤ አዳምጦ ከሌላው ለመማር አለመፈለግ፤ ለሌላው ሰው አለማሰብና አለመቆርቆር ( Lack of empathy) እነዚህ ሁሉ በድምራቸው ያስከተሉትና የሚያስከትሉት አሉታዊ ውጤት ክፍተኛ ዋጋ እያስከፈለን ነው። በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከምመኛቸው መካከል አንዱ፤ የግብረ ገብ ትምህርት ለወጣቱ ትውልድ እንዲሰጥ ነው። ለምን ዓላማ? ተብየ ብጠየቅ፤ ሰላምን፤ ፍቅርን፤ መግባባትን፤ አብሮነትን፤ ፍትህን፤ ዲሞክራሳዊ ባህልን ለማጠናከር የሚል መልስ እሰጣለሁ።

 

 1. ኢትዮጵያ አገራችን በዓለም የታወቀ ታሪክ፤ የራሷ ፊደልና የቀን መቁጠሪያ፤ አስደናቂ ባህል ያላት፤ በፍጥነት ለመልማት የምትችል አገር ናት። ግን፤ የራሷ ዲፕሎማቶች ይህችን አገር ለዓለም አላስተዋወቋትም። ትዝ የሚለኝ፤ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የትም ቦታ ስሄድ የነበራት ዝና በአርባ ዓመታት፤ በተለይህ ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ የውሃ ሽታ መሆኑ ነው። አንዱ የምመኘው ተስፋ ይህን መልሶ የማደስ ታሪክ በዓለም ዙሪያ እንዲካሄድ ነው። ይህን የተቀደሰ ስራ መንግሥት ብቻውን ሊሰራው አይችልም። እያንዳንዳችን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነን ልንሰራው እንችላለን የሚል እምነት አለኝ።

 

 1. እነዚህን መሰረታዊ ምኞቶቸን፤ ተስፋዎቸንና አቅጣጫዎች ማን ስኬታማ ያደርጋቸዋል? የሚል ጥያቄ እንደሚመጣ አስባለሁ። እኔ በማያሻማ ደረጃ የማምነው በቆራጡና በትእግስተኛው በኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። አደራ የምለውም ሕዝቡ ለራሱ መብት፤ ለጥቅሙ፤ ለፍትህ፤ ለእውነተኛ እኩልነት፤ ለብሄራዊ ክብርና ለኢትዮጵያ ሉዐላዊነት በአንድነት እየተፈላለገና እየተናበበ ድምጹን እንዲያሰማ ያለኝን ምኞት እገልጻለሁ። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እንቁና ክብር ናቸው። እንከባከባቸው!!

 

 1. በዚህ አጋጣሚ፤ በተከታታይ ካየሗቸው የኢትዮጵያ መንግሥታት መካከል፤ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አድናቆትና ክብር ማን አበርክቷል? ተብየ ብጠየቅ የምጠቅሰው የአፄ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት ነው እላለሁ። ያኔ፤ ራሴን ከፍ አድርጌና ኮርቸ “እኔ ከኢትዮጵያ ነኝ፤ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ” እል ነበር። የኢህአዴግ መንግሥትና መስራቾቹ ይኼን ክብሬን ነጥቀውኛልና መልሱልኝ እላለሁ።

 

 1. አምላካችን፤ ፈጣሪያችን ኢትዮጵያንና መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ። ይህችን የተባረከች አገር አናዋርዳት፤ አንከፋፍላት፤ ተባብረን እናልማት። የህዳሴን ግድብ ስኬታማ አድርገን በጨለማ ዓለም የሚኖሩትን ወገኖቻችን የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት እንዲያገኙ ድርሻችንን እንወጣ!!

September 9, 2020

 

 

 

2 Comments

 1. ይህችን የተባረከች አገር አናዋርዳት፤ አንከፋፍላት፤ ተባብረን እናልማት።

 2. Good job, Aklog. Some people don’t even know what they are doing and send new year congratulations and wishes to the nation as if they are heads of state. You are one of them, Aklog. Don’t try to elevate yourself by acting as if you are the president of Ethiopia. We have one, President Sahle Work, and we don’t need your pretentious message. You should be ashamed of yourself. Thanks to TPLF’s democracy that allowed people like you to shamelessly act as head of state.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.