“ብናምንበትም፤ ባናምንበትም ሕገመንግሥቱን ያወጣው ህወሓት ነው አሁን ግን መልሶ የወለደውን ልጅ ራሱ እየገደለ ነው” አቶ አንዷለም አራጌ የኢዜማ ምክትል መሪ

119023400 1751725158312158 5564687758887267681 o 747x1024 ብናምንበትም፤ ባናምንበትም ሕገመንግሥቱን ያወጣው ህወሓት ነው አሁን ግን መልሶ የወለደውን ልጅ ራሱ እየገደለ ነው   አቶ አንዷለም አራጌ የኢዜማ ምክትል መሪ«ብናምንበትም፤ ባናምንበትም ሕገመንግሥቱን ያወጣው ህወሓት ነው፤ ሲመራበት ነበር፤ እሱን አላከበራችሁም እየተባልን ብዙ በደል ደርሶብናል፤ አሁን ግን መልሶ የወለደውን ልጅ ራሱ እየገደለ ነው» አቶ አንዷለም አራጌ የኢዜማ ምክትል መሪ
• ሕወሓት ዕድሉ በነበረው ጊዜ ዴሞክራሲ በአገሪቱ ማስፈን ሳይችል አሁን ላይ ለዚያውም ሕገመንግሥት ጥሶ በሚያካሂደው ምርጫ ዴሞክራሲ ለማስፈን ነው ቢል ተቀባይነት አይኖረውም።
• የሚያሳዝነው ነገር ጦርነት ቢቀሰቀስ አንዱም የህወሓት ባለሥልጣን ሄዶ አለመሞቱ ነው። በተመሳሳይ የብልፅግና አመራር ሄዶ አይሞትም።
• የሚሞተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። የሚጋደሉት የኢትዮጵያ የደሃ ልጆች ናቸው። ይህንን ግፊት እያደረገ ያለው ደግሞ በዋናነት ህወሓት ነው።
• ሕወሓት እንደሌሎቻችን ታግሶ መጠበቅ ሲኖርበት በተለየ መንገድ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ለመምሰል ሲባል ሕዝብን ለማጫረስ ጥረት እያደረገ ነው።
• ሕወሓት ከብልፅግና ሰዎች ጋር በተጋባው እልህ ምክንያት እንዲህ ዓይነት የተዛባ ነገር መስራት ትክክል አይደለም።
• የትግራይ ሕዝብም እንደሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጦርነት ጠግቧል፤ ችግር ጠግቧል፤ መከራ አይቷል፤ ብዙ ልጆችን ቀብሯል። አሁን ደግሞ እንደገና ሌላ ዓይነት ደም መቃባት ውስጥ መግባት የለበትም።
• በፌዴራል መንግሥት በኩል ወደ ጦርነት አለመገባቱን በጣም ነው የምደግፈው። በእኛ አጉል ፉክክር ልጆቻችን መሞት የለባቸው።
• ይህን ጉዳይ መዝጋት የሚቻለው በሰላም መንገድ ነው። እርግጥ የሰላም መንገድ ብዙ ጊዜ ከባድ ነው። ግን ውጤቱ ደግሞ በጣም ጣፋጭ ነው።
• ችግሮች እንዳይፈቱ የማያደርገው የገዢዎችና ተወያዮች የአስተሳሰብ ችግር ካንሰር ሆኖ ሲቆይ ነው። ይህ ዓይነቱ ካንሰር ያለባቸው ሰዎች የሞት ሽረት ካልሆነ ብለው አሻፈረኝ ይላሉ።
• እንዲህ ዓይነቱን ሰዎች ወደጎን ማድረግና ቀናነት ያላቸው ሰዎች ወደመድረኩ የሚመጡ ከሆነ ችግሩ አይፈታም ብዬ አላስብም።
• የትግራይ ክልል ምርጫ ማካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ለጊዜው ብዙ ችግር ላይኖር ይችላል። ግን ደግሞ አገር አቀፉ ምርጫ ሲካሄድ ትግራይም ውስጥ መካሄድ አለበት።
• አሁን ላይ በትግራይ ለዓመታት ተቃዋሚ ሆኖ የቆየው አረናን ጨምሮ ሌሎችም አይሳተፉም። ምንአልባት ህወሓት አንድ ሁለት ፓርቲዎችን ይዞ ብቻውን ሊወዳደር ይችላል። በእርግጠኝነት ደግሞ በከፍተኛ ልዩነት አሸነፍኩኝ ሊል ይችላል።
• ከዚያ በኋላ አገር አቀፉ ምርጫ ትግራይ ላይ ሲካሄድ ምንድን ነው የሚሆነው? በእኔ እምነት ያን ጊዜ ትልቅ ፍጭት ይፈጠራል። ምክንያቱም አንዴ ተመርጬያለሁ መንግሥት ነኝ ማለቱ አይቀሬ በመሆኑ ነው።
• ስለዚህ የሚቆይ ግን የሚጠብቀን ሌላ ችግር እንዳለብን ነው የማስበው። መዘዙ ሰንሰለት ሆኖ ከሚመጣ ግን አንዱ ለሌላው የወንድ በር ሰጥቶ በመግባባት ችግሩን ማስቆም ይገባል።
• መንግሥት ከህወሓት ጋር ጦርነት እንዲገጥም አንፈልግም። ምክንያቱም የህወሓት ሰዎች ስላልሆነ የሚዋጉት ሕዝብ ከወንድሙ ጋር እንዲጋደል አንፈልግም።
• ለዴሞክራሲ መሠረቱ የሕግ የበላይነት ነው። የሕግ የበላይነት ደግሞ በአንድ ምሽት የሚረጋገጥ አይደለም።
• መንግሥት ምርጫውን ማራዘሙ የሚወቀስበት ነገር ነው ብለን አንወስድም።በዓለምአቀፍ ደረጃ በኮሮና ምክንያት በርካታ ምርጫዎች ተራዝመዋል።
• በፍርድቤት የተዘያዙ ጉዳዮች ላይ ብዙ መናገር አልፈልግም። ነገር ግን ፍርድ ቤት የፍትህ ቤተመቅደስ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ።
• እኛ በታሰርንበት ጊዜ ፍርድ ቤት የፍትህ የምትሰቀልበት አደባባይ ሆና ነበር የቆየችው። በውሸት እየተመሰከረብን ዳኞች ከቤተመንግሥት በቀጥታ ትዕዛዝ እየተቀበሉ የሚፈርዱበት ሁኔታ ነበር የነበረው። ያ እንዲለወጥ እንፈልጋለን።
• በግሌ የሚያጓጓኝ ምክር ቤት መግባት ሳይሆን ትክክለኛ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ነው። እኔ እዛ የሚከፈለኝ ደመወዝ ሌላ ቦታ ተቀጥሬ ላገኘው እችላለሁ። እሱ አይደለም ግባችን ። እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንሰራበት ዘመን ነው የምንመኘው።
ምንጭ አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.