ፕሮፌሰር መስፍንን ምን ነካቸው ? – አምባቸው ደጀኔ ( ከወልዲያ)

Mesfinዝም ብሎ መቀመጥም ላይቻል ነው፡፡ ዝምታህን የሚያደናቅፍና የሚያስጮህህ ጉዳይ በየቀኑ አታጣም፡፡ የ2013 መስከረምማ አለው ነገር፡፡ ከ2012ዓ.ም መስከረም ጀምሮ የጉድ መዓት እየተደራረበ መቆሚያ መቀመጫ አሳጥቶናል፡፡ ይህ አንድ መስከረም እስኪጠባ ስንትና ስንት ጉድ መስማት እንዳለብን አላውቅም፡፡ አንዱ ጉድ በአንዱ ላይ እየተነባበረ ይሄውና ጉደኛው የጎደሎው ዓመት የ2013 መስከረም ሊጠባ ሦስት ቀናት ብቻ ቀሩት፡፡ የጳጉሜ ቀናት ቁጥር ጎደሎ፣ በዚያ ላይ 13ኛ ወር ናት – ጎደሎ፤ የዓመቱም ሆነ የወርኃ ጳጉሜ ጎዶሎነት ደግሞ ከዚያው መከረኛ የዐውሬው ቁጥር ጋር የሚያያዝ መሆኑ ለቁጥር ሰንጣቂዎች የተመቻቸ ሆኗል፡፡ 13 እና 666 ቁጥሮች የዓለም ገዢ መለያ ናቸው፡፡ ኮሮናም ከነዚህ ቁጥሮች ጋር ግንኙነት እንዳለው አንብቤያለሁ፡፡

አንድ የሀገር ሀብትና ታላቅ ምሁር ቂጣ በቆረጠ መደዴ አንደበት መውቀስ ለአንዳንድ ወግ አጥባቂዎች የማይዋጥና የሚያዘለፍም መሆኑን አውቃለሁ፡፡ በተለይ በግለሰብ ማምለክ እንደባህል በሚቆጠርባት ሀገራችን አንድን ዕውቅ ሰው መንቀፍ ከማስተቸትም ባለፈ ያስቀስፋል፡፡ ይህ ካላስቀበረ የማይለቅ ጠባያችን ሰዎችን በዕብሪት እያነበረረና እያሳበጠ ተራራ በማሳከል የዞረ ድምር ውጤቱ እንጦርጦስ ሊከተን ሩብ ሐሙስ ያህል ቀርቶታል፡፡ “መሄዴ ነው ማጂ … አንተን ተማምኜ እንደናቴ ልጅ” ቀርቶ “ልሄድ ነው ሩዋንዳ፤ ልሄድ ነው ሦርያ፣ መሄዴ ነው የመን፣ መሄዴ ነው ኢራቅ፣ መሄዴ ነው ፊጂ እነሱን አምኜ እንደናቴ ልጅ…” የሚል የኦሮሙማ ዘፈን ማቀንቀን ከያዝን ድፍን ሁለት ዓመት ከአምስት ወርና ከስምንት ቀን ሆነን – “ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው” ይባላል (ፊጂ ለግጥም ማማር የገባች ናት – የነእስክንድር እስር ለጃዋር እስር መናጆ እንደሆነው – ውሸት ምን ያደርጋል)፡፡ ጎበዝ! ድፍን ወፈፌ ሀገር ምድሩን ሞልቶት ልንጨራረስ ነው፡፡ ተሰሚነት ያለው አስታራቂና ሃይ ባይ ትልቅ ሰውም ጠፋ፡፡ አንዳንዶች በጭንቀት ተውጠን “ሁሉም ሌባ ነው ሟደድ፤ ክርስቶስ ወርደህ አንድ ፍረድ” እያልን ነውል፡፡ በሰው ማምለክ አደጋ አለው፤ እንኳንስ ሰውና በመንፈሱ ዓለም ሊቀ ሣጥናኤል የእግዚአብሔርን ሥልጣን ተገዳድሮ በተነሳው አቧራ ብዙ ጓደኞቹን ጉድ ሠርቷቸዋል፡፡ የኞቹ እነአቢይማ በዚህች ትንሽ ዕድሜና በዚህች ትንሽዬ አስተሳሰብ ምን አቅም አላቸው? በአንድ ጉባኤ ጭብጨባ ሰክረው የሚሠሩትን የሚያጡ ጉብሎች በአንዲት መስፈራርቾ ብቻ(ብላክሜይል) የዲያቢሎስ ባርያ ከመሆን አይመለሱም – ሀገራትን እያወደመ ያለው ዋና ምሥጢር እንግዲህ ትንሹ ኅሊና ቦታውን እየሳተ ለዓለም ሥልጣንና ዝና እንዲሁም አዱኛ የሚንበረከከው የዚህ ዓለም ባለሥልጣን ወሳኝ ወንበሮችን ስለሚይዝ ነው፡፡ አቢይ ኢትዮጵያን ማዳን ቢፈልግ እንኳ አይችልም – ነፍሱን ለዐወሬው አስረክቦ በሥጋው እንዲመቸው (ይህም መመቸት ተብሎ!) በደም ቀለም ተፈራርሟልና ይህ ልጅ ይህችን አገር ያሻግራታል ብለህ የምትጃጃል ሁላ ዕርምህን አውጣ፡፡ ለማንኛውም “ቁጭ ብለው የሰቀሉት ቆመው ማውረድ ያቅታል” እየተባለ የሚተረተው ልክ ነው፡፡ መንግሥቱን፣ መለስን፣ አቢይንና የጥንቱን ቀ.ኃ. ሥላሤን በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ አስገብቶ ማየት ነው፡፡ እነሱ ካሉ፣ አሉ ነው – ከተናገሩ ማለቴ ነው፡፡ ሁሉም ጠብ እርግፍ ይልላቸዋል፡፡ ሳያስነጥሳቸው መሀረብ የሚዘረጋው አሸርጋጅ ብዙ ነው፡፡ የሌለ ጉድፍ ለማንሳት ትከሻቸውን የሚጠራርገው እወደድ ባይ ቁጥር ሥፍር የለውም፡፡ ግደል ሲሉ ስንት እንጂ ለምን የሚል ሥልጡንና ሰብኣዊነት የሚሰማው ወታደር የነሱ ጠላት ስለሆነ ከአጠገባቸው ድርሽ አይልም፡፡ ባለሥልጣኖቻቸው ሁሉ በዐይን ጥቅሻ የሚታዘዙና በግልምጫ ብቻ መሬት ተሰንጥቃ ብትውጣቸው ደስ የሚላቸው ዞምቤዎች ናቸው – ልክ እንደደመቀ መኮንንና ሌሎች ብአዴናውያን የቤት ውስጥ ሥሪቶች፡፡ እነዚህ ኢዲያሚኖች ደግሞ የሰውን ልብ ስለሚያውቁ ያን ሰይጣናዊ ዕውቀታቸውን እስከጥግ ይጠቀሙበታል፡፡ በመጨረሻ ግን እነሱም ሀገርም እንጦርጦስ ይወርዳሉ፡፡ ታሪክ በግልጽ የሚመሰክረው ይህንን ሃቅ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ የአቢይ ደንገጡር የአማራው ክልል “መንግሥት” አቶ ሽመልስ አብዲሣን የዓመቱ ምርጥ ሰው ብሎ ሸልሞታል ሲባል ሰማሁ፡፡ ሌላው መስከረማዊ ጉድ! በሉ ሌላም ሌላም ጉድ እየጨማመራችሁ አስገልፍጡን፤ ሣቃችንንስ ጨርሰነዋል፡፡ በዚህ አሣፋሪ ተግባራቸው አብዲሣ ራሱ የክልሉን ባለሥልጣናት ሊከሳቸውና የሞራል ካሣ ሊጠይቃቸው ይገባል፡፡)

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፍልፈሉ! - በላይነህ አባተ

ፕሮፌሰር መስፍን “አዳነች – አስናቀች” በሚል ርዕስ አንድ አጭር ውዳሤ ማርያምን የሚያስንቅ ሙገሣ ለእመት አዳነች አቤቤ ሰሞኑን ደርሰውላታል፡፡ ይህን ውዳሤ ከንቱ ሳነብ ዐይኔን ተጠራጠርኩ፡፡ የጻፉትና የላኩት እርሳቸው መሆናቸውን ለማወቅ አንዳንድ ቦታ ደዋወልኩ፡፡ አጥጋቢ መልስ አላገኘሁም፡፡ ወደቤታቸው ሄጄም እውነቱን ለመረዳት ፈለግሁ – ያን ማድረጉ ግን ሞኝነት መሰለኝ፡፡

ብዙ ነገር ተጠራጠርኩ፡፡ “እሳቸው አይሆኑም” ብዬ ከራሴው ጋር ተከራከርኩ፡፡ “በርግጥ እርሳቸው ከሆኑ እስከዚህን ቀን ድረስ አላውቃቸውም ነበር ማለት ነው” አልኩ፡፡ ስማቸውን ተጠቅሞ የወይዘሮዋ ሎቢስት እንደጻፈውም ተጠራጠርኩ – አንዴውኑ ለመጠራጠር ፈጥሮኛልና፡፡ ግን ይህም ብዙም አላስኬደኝም – ብዙ ጠብቄ ማስተባበያ ቢጤ ከርሳቸው ወይም ከሌላ አካባቢ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ የጽሑፉ አቀራረብ የርሳቸውን ስለሚመስል ወደሳቸው አነጣጠርኩ፡፡ ቀጠልኩና አሟቸው ይሆናል አልኩ፡፡ በዚያም ብቻ አልቆምኩም፡፡ የታመመ ይተኛል እንጂ እንዲህ የተበለሻሸ ነገር አይጽፍምና ጃጅተው ቢሆንስ ወደሚለው አዘነበልኩ፡፡ እርጅና ከወጣትነት የባሰ አደገኛ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ፈጣሪ የሰውን ልጅ ከፈጠረ በኋላ በየዕድሜው ብዙ ጊዜ እየሠራ ይፈታታዋልና፣ እየፈታታም እንደገና ይገጣጥመዋልና ችግሩ ቁልጭ ብሎ ታየኝ፡፡ ሥራ ፈቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገንዘብ መድቦ በኑሮ ውጣ ውረድ የተጎሳቆለን ሰውነቷን እንደመጠገን በስተርጅና የዶክትሬት ዲግሪ የሰጣት ንጋቷ ከልካይ እንዴት ተጃጅላ እንደሞተች ስለሰማሁ ለመስፍኔም አዘንኩ – ጅማሬውን አሁን በደምብ እያየሁ ነዋ! በስተርጅና መቼም ገንዘብ ተከፍሏቸው እንደነ ነቢዩ ባዬ ለዚህች ሴት መስፍኔ ያሸረግዳሉ ብዬ ማመን ይከብደኛል ብቻ ሣይሆን ማሰቡ ራሱ ኃጢኣት ይሆንብኛል፡፡ በርግጠኝነት ሊሆን የሚችለው በእርጅና (ሴኒሊቲ) ምክንያት ከሚከሰት አሉታዊ ተፅዕኖ የተነሣ ነው፡፡ እንጂ አቤቤ – ማናት – አዳነች የመስፍኔን ትችት ብታመልጥ ቢያንስ የዝምታቸውን እርዚቅ ተጠቃሚ መሆን ነበረባት፡፡ ዝምታን አልፈው ከመሬት ተነስተው እንዲህ ቡራኬያቸውን ከሰጧት ግን በሌላ ማስጠርጠሩ አይቀርም፡፡ የማይታወቅ ሌላ! ነገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየተወሳሰቡ ፍች-አልባ ዕንቆቅልሽ መሆናቸውን ቀጥለዋል፡፡

“ደኅና ሰው ሲበላሽ ቅራሪ የለውም” ከሚለው ይልቅ “ካረጁ አይበጁ” የሚለው ፕሮፌስርን ይበልጥ እንደሚገልጥልኝ አመንኩ፡፡ ለራሴም አዘንኩ፡፡ ወጣት መሣይ ሽማግሌ (ወመሸ) እንደመሆኔ ወደርሳቸው ዕድሜ ስጠጋ እንደሳቸው እንዳልሆን ከአሁኑ በጣም ፈራሁ፡፡

እነዚህ አቢይና ታከለ፣ ነቢዩና መሰሎቹ የሚባሉ ወጣቶች ዘልለው ያልጠገቡና ብዙ ነገር የሚያምራቸው – የሚያምራቸውንም ሁሉ ለማግኘት የማይፈነቅሉት ድንጋይና የማይቀነጥሱት ቅጠል የሌላቸው ውሪዎች ናቸው፡፡ የገንዘብ፣ የሥልጣንና የወሲብ ፍቅር ናላቸውን የሚያዞረው የኦሾ ቲዮሪ ሰለባዎች በመሆናቸው ለሥጋዊ ጥቅም ሲሉ ዓለምን ከነሀብት ንብረቷ በሃራጅ ሊሸጡ ይችላሉ፡፡ ፈጣሪ እንዳማረ እንደማይገድል ባምንም የሀገር ዋልታና ማገር የምንላቸው ፕሮፌስር መስፍን ግን ይህን ያህል ወርደው የፍትህን ዐይን በዘረኝነት ወስፌ ስትደነቁል የነበረችን አሁንም ያን ኃላፊነት ይበልጥ እንድትወጣ ባልጠፋ ሰው፣ ባልጠፋ ኦሮሞ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከአራቴ በላይ ከአንዱ ሥልጣን ወደሌላው እንደፌንጣ የምትዘልን ሴት እንዲህ ቅድስተ ቅዱሣን ማድረግ የጤና አይመስለኝም፡፡ ፕሮፌሰር ዘመድ ወዳጅ ካላቸው አሁኑኑ ወደሚቀርባቸው የአእምሮ ህክምና ማዕከል ይወሰዱና ከዚህም በከፋ መሳቂያና መሳለቂያ ሳይሆኑ ምናልባትም ለአቢይ ታቦት ይቀረጽለት ሳይሉ ይታከሙ፡፡ አንድ እንጂ ሁለትና ሦስት መስፍኖችን በአንድ ሰውነት ውስጥ ማግኘት አይገባንም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የመጨረሻው ኑዛዜ - በልጅግ ዓሊ

በመሠረቱ እኔም መስፍንም አንድ ነን፡፡ ሰው ነን፡፡ እንደሰው ተወልደናል፤ አድገናል፤ በተወሰነልን ጊዜም እንሞታለን፡፡ ሁለታችንም ለዚህች ምድር ኢምንት ነን – ከጉንዳን እኩል፡፡ የሚለየን ከመቃብር በላይ ትተነው የምንሄደው ታሪክ ነው፡፡ ታሪካችንን ደግሞ እኛው ነን የምንሠራው፡፡ ስንፈልግ እናጣምመዋለን፡፡ ስንፈልግ እናቃናዋለን፡፡ ስናጣምም ሆነ ስናቃና ግን በምክንያትና በአሳማኝ አመክንዮ መሆን አለበት፡፡ በአንድ ነገር ውስጥ ሁለት ተቃራኒ ነገሮች ሊኖሩ አይችሉም፡፡ ብርሃንና ጨለማ ኅብረት የላቸውም – ተጠፋፊ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ አነጋገር ትናንት አንድ መቶ ሰው የመገበ ሩህሩህ ሰው፣ ዛሬ አንድ መቶ ሰው በጭካኔ ቢገድል “አይ፣ ያ ሩህሩህ ሰው አንዳች ነገር ሽው ቢለው ነውና ይህን መጥፎ ድርጊት የፈጸመው በትዝብት ብቻ እንለፈው” እንደማይባል ሁሉ መልካም ስምና ዝና ያለውና የመጨረሻው የትምህርት እርከን ላይ የደረሰ ሰው እንደፈለገው ይጻፍ ይናገር ከተባለ የፈጣሪም፣ የኅሊናም፣ የምድርም … ህግጋት ተሰባበሩ ማለት ነው፡፡ እንደዚያ መሆን ደግሞ ፍልስፍናውን በመስበርና በመሰባበር ላይ የመሠረተውን ኦነግ/ኦህዲድን መሆን ነው … “ነፍጠኛ ጨብሲቴ…” ምናምን ሲሉ ስለሰማሁ ነው፡፡

በጣም የሚገርመው ግን ሀገራችን እንዲህ በግልጽ እያየናት እየመከነችና እያረጠች መሄዷ ነው፡፡ የምንሰማው ሁሉ አስደንጋጭ ነው፡፡ ሀገራችን ሰው የላትም፡፡ ትልቁ ዳቦ እንዲህ ሊጥ እየሆነ ካየን ዛሬ ከዩቲዩብ እንደሰማሁት እነሰርጸ ስብሃት፣ ነቢዩ ባዬና ያሬድ ሹመቴ ታከለ ኡማ ሥር ተነጥፈው ለአንዲት እንጀራ፣ ለአንዲት ጭብጥ ምሥር ብለው እንደኤሣው ብኩርናቸውን በመሸጥ ኢትዮጵያን ከነሕዝቧ ባወጡ ቢቸበችቡ ማን ይፈረድባቸዋል? ለዚያውስ ፈራጅ ሲኖር አይደል! እግዚአብሔር ፊቱን ያዞረብን እኮ ከምድር እንስሳት በስተቀር እንደፈጠረው ያገኘ መልካም ሰው በማጣቱ ነው፡፡  የጠፋ ትውልድ ሀገርን ከሞትም ሆነ ከውድቀት ሊያነሳ አይችልም፤ ከሆዱ ባለፈ ማሰብ ይሳነዋልና፡፡ አዳሜ ሱፉን ገጭ አድርጎ “ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ” ሲል እውነት የሚመስለን ተላሎች ብዙ ነን፡፡ ይህ ቀን ሲያልፍ (የሚደርሱ ሰዎች) ኢትዮጵያ ስንት እውነተኛ ልጆች እንዳሏት የሚያዩት ይሆናል – በርግጠኝነት ግን መቶ እንደማይሞሉ መገመት አይብድም፡፡

ከታከለ ኡማ የሚበልጥ ሀብትና ገንዘብ አለኝ የሚል ካለ ይወራረደኝ፡፡ ከነቢዩ ባዬ የበለጠ ገንዘብ አለኝ የሚል የዩኒቨርስቲ መምህር ወይም መካከለኛ ሀብታም ካለ ይውጣና ይንገረን፤ ስንትና ስንት የሀገር አለኝታ ምሁራንና ዐዋቂዎች የምንላቸው ዜጎች ሁሉ በገንዘብ ፍቅር ነፍዘው ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በፍቅረ ንዋይ ለውጠዋል፡፡ እነእንቶኔ አርቱን ወደወሲባዊ ሸቀጥነት ለውጠው ድራሹን አጥፍተውታል፤ እነአቡነ እንቶኔና እነዘማሪ ወሰባኪ እንቶኔ ሃይማኖቱን ወደ ሸቀጥ ለውጠው ምዕመናንን በተኩላና ቀበሮ አስፈጅተውታል፤ እነፓስተር እንቶኔ ክርስቶስን እንደቅርብ ጓደኛ “በስልክ ሳይቀር እያነጋገሩ” ልዩ ድራማ በመሥራት የዋሃንን ማፍዘዣና መበዝበዣ አድርገውታል፤ እነእንቶኔ ፖለቲካውን ወደዘር ሐረግ ለውጠው ሀገራችንን ወደ ጦር ዐውድማነት ለውጠዋታል፤ እነእንቶኔ ገበያውን እንደመንኮራኩር ሽቅብ እየተኮሱ የኑሮ ውድነቱን ከጥቂት ሙሰኞችና ሲራራ ነጋዴዎች በስተቀር ማንም እንዳይደርስበት አርቀው ሰቅለውታል (የስሙኒ ቲማቲም 50 ብር ሲገባ፣ የ30 ብር ጤፍ 5000 ብር ሲገባ … አንድም ሃይ ባይ የለም፤ መንግሥት አልባነት ከዚህ በላይ አለ ታዲያ? በኪነ ጥበቡ ይመሻል፤ ይነጋልም፡፡) እነእንቶኔ ሌት ከቀን በየመሸታ ቤቱና በየራቁት ዳንስ ቤቱ እየተበሻቀጡ ሞራላችንንና ወግ ልማዳችንን በዜሮ አባዝተው ልቅ ማኅበረሰብ በመፍጠራቸው ፈጣሪንም ተፈጥሮንም አስኮርፈዋል፣ ምን ደኅና ነገር አለ? ምንም፡፡ ዙሪያው ገደል፤ ሙላው ጨለማ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የዘር ማጥፋት ወንጀል /Crime of Genocide/ ምን ማለት ነዉ? ሊወሰዱ የሚገባቸዉ ቅድመ ጥንቃቄዎችስ ምንድን ናቸዉ? ሸንቁጥ አየለ

ላጠቃል፡፡ አዳች አቤቤ አሥር ሚሊዮን ብር ብትከፍል ማንም እንደፕሮፌሰር ያለ መልክዓ-አዳነች ሊጽፍ አይችልም፡፡ አዳነች ወንበሯ ላይ ገና ተስተካክላ አልተቀመጠችም፤ ቢሮዋ በቅጡ ጸድቶ በክብር አልተሰየመችም፡፡ ተረካክባ የጨረሰች እንኳን አይመስለኝም፡፡ በዚያ ላይ የዚህች ሴት ግለ-ታሪክ (ትራክ ሪከርድ) በቁም ጠፍተው በቁም እያጠፉን ከሚገኙት ከነአቢይ ታከለ የኦህዲድ ኩታራዎች የማትለይ የኦሮሙማ ዛር አዶከብሬ የሚያስጨፍራት ዘረኛ ናት፡፡ ፕሮፌሰሩ ምን ዐይተው ነው ታዲያ ውዳሤ-አዳነች ደርሰው በዐይኔ ላይ ሂጂ ያሏት? ምን አጣደፋቸው? ትንሽ ቢቆዩ ለምሥጋናውም ለወቀሳውም ያደርሳቸው አልነበረም? ወ/ሮ አዳነች በእርሳቸው ዐይን ላይ ለመሄድ ፈቃደኛ ከሆኑ መብታቸው ነው፤ ለኔ ዓይነቱ ግን ሚጥሚጣና በርበሬ ስለሆነች ትቅርብን፡፡… ከፍ ሲል የጠቆምትን ልድገመው – ዘመድ ካላቸው ቶሎ ውደ ሀኪም ቤት!

እግዚአብሔር ሆይ! እንደሥራችን ሣይሆን እንደቸርነትህ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ነገ ዛሬ ሳትል አሁኑኑ ጎብኝ! ያዞርክብንን ፊትህን መልስልን! ከኛ አንዳች መልካም ነገር እስክታገኝ ከጠበቅህ ምሕረትህን መቼም ቢሆን አናገኝምና እባክህን እንዲሁ ዝም ብለህ ማረን፡፡ አሜን፡፡….

ጽሑፋቸው ከዚህች አንቀጽ ሥር ከዘሃበሻ ድረገፅ ተጠልፎ እንዳለ ቀርቧል፡፡ ተዝናኑበት፡፡ ፕሮፌሰሩ አዳነችን ልክ እንደቢጤዎቿ እንደነአቢይና ሽመልስ “ኢትዮጵያን ተምቦራጨቂባት” እያሏት ይመስላል፡፡ ልክ ነው፤ ቀን ይነሳል፤ ቀን ይሰጣል፡፡ ለሁሉም ቀን አለውና ይምቦራጨቁባት፡፡ ለአፈርም ጊዜ አለው፤ ለቅጠልም ጊዜ አለው፤ ለነሐሥም ጊዜ አለው፤ ለወርቅ ወይም ለዕንቁም ጊዜ አለው፡፡ እውነቱ ያ ስለሆነ እንጂ እነዚህ ዕብድ ልጆች ለኢትዮጵያ የሚገቡ ሆነው እንዳልሆነ እንኳንስ እግዚኣብሔር የሥምሪት ዘርፍ ኃላፊያቸው ሊቀ ሣጥናኤልም አሳምሮ ያውቃል፡፡

አዳነች አስናቀች! “በከፈትሽው መንገድ ምሪበት!!! ተባረኪ‼ – መስፍን ወልደ ማርያም

by ዘ-ሐበሻ

ጳጉሜን 2012
===============
አዲስዋ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች የእውነትን በር ከፈተች! ቃል በተግባር ከተደገፈ ወይዘሮ አዳነች ጠቅላይ ሚኒስትሩንም፣ አገሪቱንም፣ ብልጽግናንም አድናለች፤ አዳነች ለወላጆቿ ምስጋና ይድረሳቸውና! ይህ እውነት ሆኖ ከያዘ ስም ወደተግባር ይመራል የሚባለውም እውነት ይሆናል፤ በከፈትሽው መንገድ ምሪበት! ተባረኪ!

የሚመርር ቢሆንም እውነትን መቀበልና ስሕተትንም ሆነ ጥፋትን ከመሸፋፈንና ከማድበስበስ ይልቅ ፊት-ለፊት መጋፈጡ ወንድነት ነው፤ ለወይዘሮ አዳነች ስል ወንድነት ማለቱን በመሻር ሴትነት እለዋለሁ! ይህ የመጀመሪያው እርምጃ ሲሆን የተደረገውን ጥፋት የማረሙ ሁኔታ እንዲሁ በይፋ እንድናውቀወ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ፤ ይህ ጥፋት ማዘጋጃ ቤቱን ሳያበላሽ፣ ብልጽግናን ሳያበላሽ፣ አገሩን ሳያበላሽ፣ አገሩ በብልሽት ሳይፈርስ ወይዘሮ አዳነች ቁልቁለት የጀመረውን የኢትዮጵያ ፖሊቲካ ወደዳገት እንደምታወጣው እንጠባበቃለን፡፡

በዚህ ሁሉ ውስጥ ኢዜማ እንደፖሊቲካ ቡድንም ሆነ እንደየነቃ ዜጋ ያቀረበው ጥናትና ያጋለጠው ጥፋት በአሉባልታ ብቻ የሚንጫጩትን የፖሊቲካ የሚያስተምር በመሆኑ የሚያስመሰግነው ይሆናል፡፡
ለወይዘሮ አዳነች ከመጽሐፈ ምሳሌ በአሥራ አንድና በአሥራ ሁለት ምዕራፎች ላይ የሚገኙ አንቀጾችን ልጥቀስላት፡–

አባይ ሚዛን በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው
መልካም መክር ከሌለ ዘንድ ሕዝብ ይወድቃል፤ በመካሮች ብዛት ግን ደኅንነት ይሆናል፤ ተግሣጽን የሚወድድ እውቀትን ይወድዳል፤ ዘለፋን የሚጠላ ግን ደንቆሮ ነው፤ ሥልጣን ላይ ያሉ ሁሉ በሰሎሞን ምክር ቢመሩ ጠቃሚዎች ይሆናሉ፤ አደራ ከመብላት ይድናሉ፡፡

ወይዘሮ አዳነችን ይበልጥ የማመሰግናት የከንቲባነቱን ወንበር ስትለቅ ሳትማስን የቀረች እንደሆነ ነው፤ እግዚአብሔር ይጠብቃት!

 

9 Comments

 1. Oh ! How powerful, realistic, clear and straightforward !!! I truly agree and appreciate !
  Yes, it is time to call a spade a spade regardless of one’s age or academic status or any other consideration if we desperately need to do something good for our country and of corse for ourselves as good citizens .

  Great comment sir !

 2. so what? the prof maybe trying to encourage her to do a good work….or givin her the benefit of the ddoubt….what I do not understand is ur garbage and you are on hell of an angry shit…careful of ur blood pressure…none sense

 3. I wonder how an Ethiopia could bear childern whose color and behavior is diametrically different as we can prove it from the comments of T. Goshu and Mr Anonymouse, I mean Anonymous, here above. Look how they are so different; of course, difference is natural and expected. But if the difference occurs on how to differentiate the darkness from light, and if people call the obvious darkness (as) light or vice-versa, then it is not a difference; it is rather an ignorance which could be intrinsic or on purpose….
  Dear Mr Anonymous, try to be sensible citizen. Be a member of this IT age. Don’t relive the time of the past wherein the stain (dirt) of “የኔታዎች” was considered as a blessing.
  Moreover, don’t waste your precious time by insulting the innocent. By doing so, you are dirtying your karma while you could clean it before it is too late.
  Though truth might be relative, I wrote the truth in my piece. And I know I am not perfect but am ready to learn if there are decent teachers unlike you. You should simply oppose my ideas point by point without resorting to ዘለፋና ሥድብ። These things (ዘለፋና ሥድብ)are the pillars pf empty minds. … I understand that I am talking with the wind but it doesn’t matter, for there are many who can take a lesson from you and me. God bless you deer bro, oops! … sometimes my English is stupid, dear bro. …hahaha just Kidding …

  • ሺመልስ አብዲሳ የኦሮሞ ክልል ፈላጭ ቆራጭ በኦሮሚኛ ሲናገር ለሰሚዎቹ ጠባብ፣ኢትዮጵያ ጠል ሆኖ ይቀርባል።በአማሪኛ ሲናገር ደግሞ ወኦሮሚኛ የተናገረው የተሰማበት አይመስለውም።ይህን አስተያየት ሰጪን፣ አንብቡት ፕሮፌሰር መስፍንን ቅራሪ፣ ካረጁ አይበጁ፣እብድ ባለበት አማሪኛ፣ ዘለፋና ሥድብን በእንግሊዘኛው ልሳኑ ሲያወግዝ ታነባላችሁ።በዛ አያበቃም የየኔታዎች ቁሻሻ፣ እድፍ፣መጨቅየት በኢትዮጵያ የሚመሰገን የሚመረቅ የሚወደስ ነው በማለት በጅምላ ግምት ሌላ ስድብ ሌላ ዘለፋ ይቀጥላል።

   ሃሳቡን የተቃወመውን ደግሞ ሥልጡን ዜጋ አይደለህም እንዴ?የ ኢንፎርሜሺን ቴክኖሎጅ ዘመን ሰው ሁን እንጂ ይለዋል። ዘመናዊነት ምንድነው?ሥልጡን ዜጋስ መስፍን ወልደ ማሪያምን፣ በድንቁርናው ሕክምና መርምሮ ወደ እብዶች ሆስፒታል የላካቸው ኩታራ ነው?? እንቧቸው ስሙን ተሳሳትኩ እንቧ!!! አሰኝቼ ከብት አደረኩት፣ ሊረዳው የሚገባ የዘመናዊነት እንዱ መገለጫ የሐሳብ ብዝሃነት ሲሆን፣የፕሪፌሰሩ የሃሳብ ነጻነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣በጨዋነት አሳባቸውን መቃወሙ ደግሞ የእንተ መብት ነው።ያንን አትችለውም።ዳቆኑ ቅዳሴው ቢልቅበት ቀረርቶ ሞላበት ሆነና ፣በእንቧቸው በተሰናከለ እድገትህ፣ በለብ ለብ ትምህርትህ ድንቁርናህ፣ እንፍረድና አንተን ነፃ እናውጣህ። ወግ አጥባቂዎች፣ በግለሰብ የሚያመልኩ፣ትንሽ ሕሊና የምትላቸው አንጃ ግራጃዎች ሰፋ ያለ መጣጣፍ የሚያስፈልገው ቢሆንም፣ካንተ ጋር መሟገቱ በራሱ ውድቀት ነው።

   ሌላ የሚገርመው በራስ መተማመን ማጣትህ ነው።በአማሪኛ ለጻፍከው መጣጣፍ በእንግሊዘኛ ሞጋችህን መልስ የሰጠኸው በእንግሊዘኛ ነው።በቋንቋህ ኩራት፣በማንነትህ መመካት የለህም ማለት ነው።በእንግሊዘኛ የሞገተህ አማሪኛህን አንብቦ ተርድቶ ነው።የእንግሊዘኛውን ሙግት የጻፈው ምናልባት ባዕድ አገር ተወልዶ አማሪኛውን ማንበብ የሚችል ፣መጻፉ የማይሆንለት ወይም በሌላ ምክንያት ሊሆን ይችላል።አንት ግን በባዕድ ቋንቋ መመለስህ የበታችነት ስሜትህን (sometimes my English is stupid)፣ወደ አንዳች ከፍታ ለማውጣት ካልሆነ በስተቀር፣አንተ የምታውቀው ጎዶሎ ምክንያት ሊኖርህ ይችላል። በሌላ ዓይነት ዘለፋ፣በሌላ ዓይነት ሰው ማዋረድ፣በሌላ ዓይነት ጥራዝ ነጠቅነት እስክንገናኝ ደህና ሰንብት።

   • ኢትዮጵያ 114 ሚሊየን ሕዝብ ያላት አንተም ተቆጥረህ ከሆነ ይገርመኛል። ቆጣሪውንም እንሥሳን እንደሰው በመቁጠር ወንጀል ዘሄግ ላይ እገትረዋለሁ። እንደሰው የተቆጠረውን ሰው መሣይ ዐውሬም ወደሚቀርበኝ የእንሥሳት መኖሪያ (zoo) እንዲገባ እጠይቃለሁ። …
    ሃሃሃ… ‘ነፃ አስተያየትህን’ እንዳነበብኩልህ ለመጠቆም እንጂ አይዞህ ቃሌን ባለማክበር የእንሥሳነት ባሕርይህን አላስነካብህም – ራሥህ ተጠይፈህ ካልተውከው በቀር። ደግሞስ አንተ ባትኖር እንዲህ ማን ያዝናናኝ ነበር? መጃጃል እኮ መብት ነው።

 4. በመጀመሪያ ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ትክክል ቢሆንም ፣የምንሰጠው አስተያየት በሃሳብ ላይ ቢያተኩር ሁላችንም ተጠቃሚዎች እንሆናለን ።ትችቱ ግን ፀሐፊው ላይ ሲሆን ማንም ተጠቃሚ እንደማይሆን ግልፅ ሊሆን ይገባል።ከዚህ አስተሳሰብ ወጥቶ ማንም ሰው መፃፍ ስለቻለ ብቻ ሰውን በፆታ/በዕድሜ/በአካል ጉዳተኝነት/ወዘተ ዝቅ ለማድረግ መሞከር ይበልጥ የተቺውን አቅም ነው የሚያጋልጠውና ብንጠነቀቅ ፣የሃሳብ መንሸራሸርን በህብረተሰቡ ውስጥ በዘለቄታው እንዳይዳብር ምክንያት ልንሆን አይገባም እላለሁ።ከዚህ በተጨማሪ እኔ ከቆምኩበት ቦታ ካላያችሁ ብሎ ወይንም የኔ እውነት ነው ትክክል ነው ብሎ እንዲህ አራምባና ቆቦ እየረገጡ ሃሳብ ተቀባይነት ያገኛል ብሎ ማሰብ እራስን ማስገመት ብቻ ነው ትርፉ።ፕሮፌሰሩ ያሉት ጅምሩ ጥሩ ነው ፣የተሰራውን ጥፋት ማመን መልካም ጅምር ነው ብሎ ማወደስ ምኑ ላይ ነው ክፋቱ?ደግሞስ እሳቸው ምስጋናም ሆነ መወድስ ለመስጠት እኛን ማስፈቀድ ነበረባቸው እንዴ?ይሄ አካሄዳችን የትም አያደርሰንምና ስንችል አስተማሪ አስተያየት ካልቻልን ደግሞ እርስዎ እንዳሉት ዝም ብሎ መቀመጥ ሳይሻል አይቀርም እላለሁ።

 5. ፕ/ር መስፍን ደርግን በ ኢትዮጵያ ህዝብ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደረጉ ሰው ናቸው። ንጉሡን በሆነ ባልሆነው በመቃወም ይታወቁ ነበርና። 60 ዎቹን ታላላቅ ሰዎች እና ሚኒስትሮች በ መርማሪ ኰሚሽን ሊቀመንበርነት በ ደርግ ተሹመው ያስገደሉ ናቸው። አዳነች አቤቤ ተቀባይነት እንድታገኝ ተመልምለው ይሆናል እንጂ እስከዛሬ አቋሟን ሳያውቁ ቀርተው አይመስለኝም።
  ሸፍጠኝነታቸውና የማመዛዘን ችሎታቸውም ያጠያይቃል። ምንም በማያሳምን ምክንያት አማራ የሚባል ዘር የለም ያሉ ሸፍጠኛ ሰው ናቸው። ኦሮሞ ወይም ትግሬ የሚባል ጎሳ የለም ሊሉ ግን አልፈለጉም። እነሱ እንዲደራጁ አማራ ግን እንዳይደራጅ ስለተፈለገ ይሆናል።

 6. Most men agree Adanech got one quality better than her predecessor , an attractive figure , nothing else. Same as most women are fond of Takele’s outfits.

 7. አቶ አምባቸው እንዲያው አንዳንዴ ዝም ብንል ምናለበት፡፡ አልፎ አልፎ ጣል የሚያደርጓቸው መጣጥፎች ግርም ይሉኛል፡፡ አሁን እስኪ ባማን ሞት ይህ ቋቋቲያም አንድ እግሩ ጉድጓድ ውስጥ የገባ ሸማግሌ በምን ሂሳብ ነው የሃገር ሃብት የሚሆነው፡፡ መርገምት እንጂ፡፡ እናዛን 60 አዛዎንቶች በደርግ አስረሸን፡፡ ያም አልበቃ ብሎት በወያኔ ህገ መንግስትና አዋጂ በተገኘበት ዘሩ እንዲጠፋ የተፈረደበትን መከረኛ የአማራ ህዝብ የለም በባማለት ለጨፍጫፊዎቹ አለኝታነቱን አረጋግጧል፡፡ ስለዚህ ምን የሚያስደንቅ ነግር ኑሮ ነው አሁን አዳነችን አስናቅች አለ ተብሎ እንደ ውሻ የሚያስጮህ፡፡ ለማንኛውም እግዚአብሄር ደግ ነው ሰውዪው ሞቱን እንኳ ቢለምን በምድር ስቃዩን እያየ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ቅጣት የለም፡፡

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.