የቁጠባ ቤቶቹ ጉዳይ – አበበ ገላው

Abebe 1የጸረ ሙስና ኮሚሽን በህግ አግባብ ተቋቁሞ በጀት ከማባከን ውጪ እዚህ ግባ የሚባል ስራ ሰርቶ አያውቅም። በዘመነ ህወሃት እነ ኤፈርት፣ አዜብ መስፍን፣ አባዬ ጸሃዬ፣ ስብሃት ነጋና ቤተሰቡ፣ ብርሃነ ገብረክርስቶስ፣ እነ ስዩም መስፍን፣ ክንፈ ዳኘው…ባጠቃላይ ህወሃትና አጋሮቹ ህዝብና አገርን በጠራራ ጸሃይ ሲዘርፉ አላየሁም አልሰማሁም ብሎ ጋቢውን ተከናንቦ ተኝቶ ነበር።

በእርግጥ አልፎ አልፎ ከእንቅልፍ እየባነነ ኮሚሽኑ አሳነባሪዎቹን ትቶ ትናንሾቹን አሳዎች ማለተም የበታች ሹማምንቶችና ደላሎችን ያሳስር ነበር። ይሄው አይጦቹን አባሮ የደለቡ የሙስና ሸለመጥማጦችን የመተው አባዜ አሁንም የለቀቀው አይመስልም።

ህዝብ ተዘርፍኩ፣ ተበደልኩ እያለ ሲያነባ የእንባ ጠባቂ ኮሚሽኑም ቢሆን የማንንም እንባ አብሶ አያውቅም። መቼም ወያኔ ወገኛ ነበረች። ህዝብን እየዘረፈች የሙስና ኮሚሽን፣ ህዝብን ደም እያስነባች የእንባ ጠባቂ ኮሚሽን፣ ሰብአዊ መብት እየጣሰችና እየጠቀጠቀች ሰብአዊ መብት ተከበረ እያለ ቱባ ቱባ መግለጫ የሚያውጣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ማቋቋሟ ግን በከንቱ አልነበረም። በተቋማት ግንባታ ስም ፈረንጅ እያጃጃሉ ዶላር በጆንያ ወደ ግል ካዝናቸውና ኪሳቸው ያሸጋግሩ ነበር።

አሁን አንኳ ቢሰማን ለሙስና ኮሚሽኑ ስራ እንጠቁመው። በመዲናችን በበርካታ ሺዎች የሚቆየሩ የቁጠባ ቤቶች በህገወጥ መንገድ ቤሳ ቤስቲ ላላዋጡ፣ በህጋዊ መንገድ ላልተመዘገቡ፣ የረጅም አመታት ወረፋ ላልጠበቁ፣ ተቸግረው ላልቆጠቡ ግለሰቦች በህገ ወጥ መንገድ መተላለፉ ተሰምቷል። ከዚህ በስተጀርባ የቢሊዮን ብሮች ሙስና መኖሩን በቀላሉ መገመት አያዳግትም።

እንደምንሰማው ከሆነ ብዙዎቹ ቤቶቹን በነጻ የተረከቡት የሲኖ ትራክ ባለቤቶች፣ የናጠጡ ነጋዴዎች፣ የፓርቲ አባላት፣ ዘመድ ያላቸው ተማሪዎች፣ ከሌሎች ከተሞች ባስቸኳይ ድረሱ እየተባሉ በዘመድ አዝማድ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ተደረጉ እንጂ እንደ ተባለው ገበሬዎች ቤቶቹን ተረክበው ሞፈራቸውን ግድግዳ ላይ አልሰቀሉም። እንደውም ብዙዎቹ ቤቶች በውድ ዋጋ በፍጥነት በጥቁር ገበያ አየር ባየር እየተቸበቸቡ መሆኑ እየተሰማ ነው።

በርግጥ የምንሰማው ሁሉ በቂ አይደለም። መመርመርና መፈተሽ ይገባዋል። ጸረ ሙስና ካስፈለገም ከእንባ ጠባቂው ጋር በመተባበር ትኩረት ሰጥቶ የዚህን አይን ያወጠ የህዝብና የአገርን ሃብት ዝርፊያ ጉዳይ መመርመርና ውጤቱን ለህዝብ ይፋ ማድረግ የገባዋል። እንደለመደው ካልሆነለት ሌላ ነጻና ገለልተኛ ኮሚሽን ይቋቋም። ይሄ ጉዳይ ልክ እንደትናንቱ በቸልታ ከታለፈ ነገ አየር ባየር ምን ሊሸጥ እንደሚችል መገመት ይቻላል።

የኮንዶሚንየሞቹ ጉዳይ መመርመር ብቻ ሳይሆን በምርመራው ውጤት መሰረት ቤቶቹ ለህጋዊ ባለቤቶቻቸው እንዲመለሱ ሊደርግ ይገባል። እስከዛው ድረስ ቤቶቹ እንደ ወንጀል ኤግዚቢት (exhibit) ተይዘው አንዳይለወጡና እንዳይሸጡ፣ በህገ ወጥ መንገድ ለሌላ ተላልፈው እንዳይሰጡና እንዳይከራዩ ማድረግ ተገቢ ነው። ቤቶቹን አየር ባየር ቸብችበው የናጠጡ የአዲስ አበባ አስተዳደር ባለስልጣናትም ቢሆን ከህግ ተጠያቂነት ማምለጥ የለባቸውም።

የትናንቶቹ የህወቶች የሙስና አጋሮች ወደ ዋና ተዋንያን ከፍ ማለታቸው ግልጽ ነው። ባለፉት ሁለት አመታት ቀላል የማይባል ለውጥ መምጣቱ የማይካድ ሃቅ ቢሆንም ብዙ ያልጠሩ ነገሮችም አሉ። ገዢው ፓርቲም ህዝባዊ አመኔታን ሙሉ በሙሉ ከማጣቱ በፊት በራሱ አነሳሽነት ሙሰኞችና በስልጣን ብልግና ህዝብን የደም እንባ የሚያስለቅሱን መመንጠር ይገባዋል።

ለውጥ መምጣቱን ሁላችንም እሰየው ብለን እልል ብለን ተቀብለነዋል። የእልልታ ጊዜ ግን አልፎ ሁሉም ለውጡ መሬት ላይ ወርዶ በየደረጃው በተግባር ሲተረጎም ማየት ይፈልጋል። ህወሃቶች የሰሩትን ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ኦህዴድና ብአዴን እየተፈራረቁ በተለመደውና ህዝብን ባስመረረ አሻጥር ሲደግሙ ማየት ማንም አይመኝም። የፍትህና የእኩልነት ጥማት በእኩዮች ሲመክን ለማየት የቋመጠ አለ ብሎ ማመን ይከብዳል። ካለም ያው ህዝብ መዝረፍና ማስለቀስ የለመደ ብቻ ነው።

እነ ሰናይት ዳምጤስ በአንድ ሳምንት ውስጥ ማመልከቻ እንዲያስገቡ ለተደረጉ በሺዎች ለሚቆጠሩ ግለሰቦች ቤት የሰጡበት አሰራርስ በየትኛው ህግ መሰረት ነው? የታከለ ኡማና የሌሎች ሹማምንቶች ሚናስ ምንድን ነው? ከዚህ ህገወጥ ንግድ ማን ምን አተረፈ? እንዚህና ሌሎች ተዛማጅ ጥያቄዎች ጥልቅ ምርመራ የሚፈልጉ ጉዳዮች ናቸው። አላየንም አልሰማንም ብሎ በጠራራ ጸሃይ ጋቢ ተከናንቦ መተኛት ለማንም አይጠቅም።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.