የጎንደር ሕብረት ሕወሓት በምርጫ ስም በወልቃይት እና ራያ ሕዝብ ላይ ዘምቷል ሲል መግላጫ አወጣ ሙሉውን ያንብቡት

Gonder hibretነሐሴ 28 2012 (9/4/2020)

ህወሓት፣ በምርጫ ስም በወልቃይትና በራያ ሕዝብ ላይ ዘምቷል

ደጋግመን እንደገለጽነው፣ በረጅሙ ታሪካችን ውስጥ ሆኖ የማያውቀው የቋንቋና ብሔር ተኮር መካለል ህወሓት ካመጣብን ወዲህ በሕዝቦች መካከል መቃቃር መገፋፋት፣ ስደት እልቂት መፈናቀል የታሪካችን አንድ ገጽ ሆኗል። ወያኔ ታላቋ ትግራይን ለመፍጠር ባለው ቅዠት የወልቃይትን፣ ጠገዴን ጠለምትንና ራያን በጦርነት በመዋጥ ወደ ትግራይ ከጠቀለለ ቆይቷል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦች በግዴታ ትግራይነትን አንቀበልም በማለታቸው በጅምላ ተፈጅተዋል፤ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ተሰደዋል። ታስረው በመሰቃየት ላይ የሚገኙትን የትግራይ እስር ቤቶች ይቁጠሩት። ምን ይህል ስቃይ እየተቀበሉ እንደሆን አንዳንድ ከእስር ያመለጡ የሚናገሩትን የሰማ ሁሉ ያውቀዋል። በመሬቱ ላይ የሚገኙት በአማርኛ እንዳይናገሩ ተከልክለዋል። ወደ አማራ አካባቢ እንዳይንቀሳቀሱ ታግደዋል። አያት፣ ቅድመ አያቶቻቸው በኖሩበትና ተወልድው ባደጉበት አንገታቸውን ደፍተው እንዲኖሩ ተገደዋል። ትግሬነታችሁን ካልታቀበላችሁ ውጡ እየተባሉ ነው።

ጠባቡና እብሪተኛው ህወሓት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ከተጣላ ሁለት ዓመታት አልፈውታል። ዛሬ ብቸኛው አፈንጋጭ ወያኔ ሲያሰኘው ኑልኝ ልግጠማችሁ ብሎ ይፎክራል። ሌላ ጊዜ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ልትወረር ነው! ከእኔ ጋር ከተሰለፍክ ብቻ ነው መዳን የምትችለው እያለ የፍራቻ ቅዠት ይቃዣል። በሙስና የተዘፈዘፉና በጸረ ኢትዮጵያነታቸው የታወቁ የህወሓት አመራሮች መቀሌ ላይ ከትመው የትግራይን ሕዝብ በማስፈራራትና በውሸት ፕሮፖጋንዳ ምሽግ ለማድረግ እየጣሩ ነው። እራሳቸው በዋነኛነት ከፈጠሩት የፌዴረሽኑ ምክር ቤት አሰራር፣ ህግ፣ ስርአት እና አካሄድ ካፈነገጡ ቆይተዋል። ለቅዳሜ ነሐሴ 30 2012 የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ጉዳይ የህወሓት አመራሮች አጀንዳ አለመላኩ ጦርነት እንዳወጀ ይቆጠራል በማለት አንገኝም ብለዋል። አጀንዳ አለመላክ ጦርነት ሲያስነሳ ይህ በዓለም ታሪክ የመጀመሪያው ሊሆን ይሆን?!

ምክንያታዊና በስምምነት የተላለፈውን ምርጫ ከፌደራል መንግሥቱ ውጭ፣ ነጻነትን ከማወጅ ባልተናነሰ እርምጃ በክልሌ ምርጫ አካሂዳለሁ ብሎ የተነሳው ህወሓት ወታደራዊ ሰልፍ ማሳየት እንኳ ሳይቀር ሲደነፋ መክረሙ የሚታወቅ ነው። የፕሮፖጋንዳ ድንፋታው አቋርጦ አያውቅም። በዚህ ድንፋታ ሰለባ የሆኑት አናምናችሁም የሚሏቸው የወልቃይት፣ የጠገዴ የጠለምትና የራያ ነዋሪዎች ተቀዳሚ ናቸው። በገዛ ቀያቸው በአያት ቅድመ አያት እርስታቸው ላይ የሚኖሩ እንደገና ለግድያ፣ ለእስራትና ለስደት እየተዳረጉ ነው። በትውልድም ሆነ አብረው ያልኖሩት የህወሓት ሹሞች መቀመጫ መቆምያ ነስተዋቸዋል። የህወሓትን ምርጫ የሚቃወሙት የእነዚህ አካባቢ ነዋሪዎች ባላቸው ጠንካራ የሆነ ኢትዮጵያዊነት ምክንያት እራሳቸውን ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጥለው አያዩም። በወያኔ አመራሮች እየተገፋ ያለውን የፖለቲካ መስመር ይቃወማሉ። በምርጫውም ለመካፈል ፍላጎት የላቸውም።

የወልቃይት፣ ጠገዴ ጠለምትና የራይ ነዋሪዎች ህወሓት የሚያክሂደውን የምርጫ ሂደት በመቃወማቸው
1/ የልዩ ሓይልና ሚሊሺያ አባሎችን ወደማያውቁት የትግራይ አካባቢ ማዛወር፣
2/ የምርጫ ካርድ ያላወጡትን $500 ብር ቅጣት እና ስድስት ወር እስራት እንዲፈረድባቸው ማድረግ።
3/ ሸቀጣ ሸቀጦችን፣ እንደ ስኳር እንዳይገዙ መከልከል።
4/ ተሰሚነት ያላቸውን በትግራይ ቴሌቪሽን ቀርበው ድጋፍ እንዲሰጡ ማስገደድ።
5/ በተቃዋሚነት ወደፊት ድምጻቸውን ሊያሰሙ ይችላሉ የተባሉትን እንዲታሰሩ ማድረግ።
6/ ጥቂት የማይባሉ ተፈናቅለው ክልሉን ለቅው እንዲወጡ ማስገደድ። በተጨማሪ በተለመደው የወያኔ አፋኞች ታፍነው ተወስደው ይሆናል የሚባሉም የት እንደ ደረሱ ያልታወቁ ግለሰቦችም አሉ። ስለሆነም

1) ለዚህ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ሕዝብ የፌደራል መንግሥቱ ሊደርስለት ይገባል። መንግሥት በአስቸኳይ አካባቢውን ተቆጣጥሮ ህዝቡን ከደረሰበት ሰቆቃ እንዲታደግ እንጠይቃለን። ወረራን፣ ግፍን፣ ቅሚያንና ሰቆቃን ባጠቃላይ ኢሰባዊ ድርጊትን አውግዘን ለፍትህ ካልቆምን የግፍ ድርጊት የይቀጥል ፍቃድ መስጠት ይሆናልና ህወሃትን ማስቆም አለብን።
2) ወያኔ በእብሪት የሑመራ፣ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ እና ጠለምት ተከዜ ምላሽ ተሻግሮ ግዛቶቻችንን በማናለብኝነት ሲሰፍር ይህን ለመቀልበስ የጎንደር ሕዝብ መራር ትግል ሲያደርግ ኖሯል። የወያኔ አምባገነን አገዛዝ ተንኬታኩቶ መቀሌ እንዲመሽግ ለማድረግም ግንባር ቀደም ድርሻ አለው። ስለሆነም ሕዝባችን የታገለበት ተከዜ ምላሽ ወሰኖቻችን ወደ ህጋዊ እና ታሪካዊ ይዞታቸው እንዲመለሱ አጥብቀን እንጠይቃለን። የትም ይሁን የትም በጉልበት፣ በፍጅትና በማፈናቀል የተወሰዱ ቦታዎች ሁሉ ወደ ታሪካዊ ግዛታችው መመለስ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው። ህወሓት ከእኩይ ተግባሩ ጋር መውደቅ አለበት።

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር።
የጎንደር ሕብረት

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.