ግልጽ ደብዳቤ …ለክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ – ከኢትዮጵያውያን ማህበር በአውሮፓ

EU ethiopian ass.ቀን: 03.09.2020 (እንደ አውሮፓ አቆጣጠር )

ከኢትዮጵያውያን ማህበር በአውሮፓ
ፍራንክፉርት ጀርመን

ለክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፣

በ 13 አውሮፓ ሀገሮች የምንኖር ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያውያን ማህበርን በአውሮፖ ስንመሰረት እና የቃል ኪዳን ሰነድ ስናፀድቅ በኢትዮጵያ ሉአላዊነት፣ በሕዝቦቿ ደህንነት እና በህግ የበላይነት አበክረን እንደምንሰራ ቃል በመግባት ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እርስዎ የሚመሩት መንግስት ለመጣው ለውጥ የሀገር አንድነትን አላማው እና ግቡ አድርጎ እንደሚሰራ ገና ከጅምሩ ሲያውጅ እኛም በመላው አለም የምንኖረው ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከጎንዎ በመሰለፍ ዳር ቆሞ ተመልካች ሳይሆን እየጋመ በመጣው ለውጥ በቀጥታ ተሳታፊ በመሆን ወገናዊ ድርሻችንን እይተወጣን እንገኛለን።

ይህንን ደብዳቤ በማህበራችን ስም ለመጻፍ ያነሳሳን በኢትዮጵያ ህዝብ እና በውጭ ሀገር በምንኖር ኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰብን የስነ ልቦና መረበሽ በመግለፅ በሀገራችን እና በህዝቡ ላይ እየደረሰ እና ለወደፊትም ሊደርስ የሚችለውን አደጋ በመገመት ነው። ለዝህ ደግሞ መነሻ ምክንያታችን በቅርቡ በማሀበራዊ ገጾች እና በተለያዩ የብዙሀን ማሰራጫ የተዝገበውን የወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት የአቶ ሽመልስ አብዲሳ ንግግር ነው።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በግምት ከስምንት ወር በፊት በሪፖርት መልክ ያሰሙት ንግግር በተባበሩት መንግስታት ኮንቬንሽን አንቀፅ 20 ቁጥር 1 እና 2 ላይ የስብአዊ መብትን የሚጥስ እና በሀገራችን የመጣውን ለውጥ እና ቆመንለታል የተባለውን አጀንዳ በፍጹም በሚባል ደረጃ የሚጻረር ብቻ ሳይሆን ሀገርን የሚያፈረስ ፣ ህዝቦችን እርስ በእርስ የሚያጋጭ እና በለውጡ የመተማመን መንፈስን በመሸርሽር በሀገራችን ውስጥ ጥርጣሬ እንዲነግስ ማድርጉን ለእርሶዎ ለመግለጽ አንደፍርም። ምክንያቱም እያበጠ የመጣው እና በተወሰኑ ማህበረሰብ መሀካከል በማንነታቸው እና በእምነታቸው ብቻ ኢላማ ሆነው ለጥቃት ሲጋለጡ: የመጠላላት መንፈሱ ወደማያባራ እልቂት በማስገባት ቁጥሩ እጅግ ብዙ የሆነ የቤተሰብ አባል ለመግለጽ በሚዘገንን ደረጃ በማንነቱ ብቻ ደም አንጥረው አጥንት ቆጥረው ለሞት ፣ እንግልት እና በገዛ ሀገሩ ከእርስቱ እና ጉልቱ በማፈናቀል በነዋሪው ላይ ሊጠገን በሚያስቸግር ደረጃ ለስነልቦና ድቀት ተዳርጓል።

የሀገራችን የፖለቲካ ፣ የማህበራዊ እና ፍትሀዊነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ከገባ ውሎ ማደሩን ስናስተውል እንደ ዜጋ በዝምታ የማንመለከተው ብቻ ሳይሆን በጽኑ የምንታገለው አቋማችን መሆኑን አበክረን ልንገልጽ እንገደዳለን።

በየወቅቱ ለመሰማት እና ለማየት የሚዘገንን ክስተት ማስተናገድ እንደ ሀገር መቀጠል የማንችልበት አቅም ላይ መድረሳችንን ስንረዳ ከገፈት ቀማሹ ህዝብ በመቀጠል እኛንም ሆነ ቤተሰቦቻችንን ይረብሸናል። ይህ በእንዲህ እያለ ከላይ ልንጠቅስ በሞከርነው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት አፍራሸ እና የጥላቻ ንግግር ማንንም ተጠያቂ አለማድረግዎ የሚመሩትን መንግስት በጥርጣሬ እንድናየው ተገደናል።

የአቶ ሽመልስ አብዲሳ በሪፖርት መልክ ያቀረቡትን ንግግር ከብዙ በጥቂቱ ስንጠቅስ:

የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደ ቁማር ጨዋታ መሆኑን፣ የቻሉትን አሳምነው ያልቻሉትን አደናብረው ቁማሩን እሳቸው እና ፖርቲያቸው እንደበሉ፣ የሀገሪቷ የስራ ቋንቋ የሆነውን እና ኪነጥበብ፣ድራማ፣ ግጥም፣ ቅኔ፣ዜማ እና ሽለላ በአጠቃላይ ደስታችን እና ሀዘናችንን ሁሉ ከዳር እስከዳር በሚባል መልኩ በአማርኛ ቋንቋ የምንገልፅበትን የጋራ ሀብታችንን ከተቻለ ለማጥፋት ካልቻለ በማዳከም የኦሮምኛ ቋንቋን በመተካት ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት፣-የአዲስ አበባን ከተማን አላስፈላጊ የማድረግ ወዘተ…

ጥንት አባቶቻችን በባዶ እግራቸው በዱር በገደል፣ ሌሊት በቁር ቀን በሀሩር ዘምተው ያቆዩልን ሀገር የዘመኑ የፖለቲካ ወጠጤዎች በጫማ መጥተው በውድ መኪና እየተጓዙ እና በተንፈላሰሰ ቪላ እየኖሩ ኢትዮጵያን ሲያፈርሷት ቆመን የማናይ መሆናችንን ስንገልፅ የመረረ አቋማችን እንደሆነ በማሳወቅ የኢትዮጵያዊያን ማህበር በአውሮፓ አባላት ባሳለፍነው ውሳኔ መሰረት፤

1.የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር እንደገና እንዲፈተሽ እና ወንጀለኞች ስራቸውን ለቀው ለፍርድ እንዲቀርቡ።

2.አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባደረጉት አፍራሽ ንግግር በፍጥነት ከሀላፊነታቸው ተነስተው በህግ እንዲጠየቁ ስንል እናሳስባለን።

እኛም ለኢትዮጵያ እንሁን: ኢትዮጵያም ለእኛ ትሁን ! ሁላችንም ሰላም እንሁን!

የኢትዮጵያ ማህበር በአውሮፓ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

EU ethiopian

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.