ታከለ ኡማ ለምን አይታሰርም? ( ብሩክ አበጋዝ )

Takeleየአገራችን ሰወች የፖለቲካ እሳቤያችንና ሚዛናችን ከባለስልጣን ግለሰቦችና ብሄራቸው አልያም ቡድናቸው ማንነት ይልቅ በግለሰቦቹ አልያም ቡድኖቹ ድርጊትና ብቃት ላይ የተመሰረተ ቢሆን፣ ከዘውጌና ሃይማኖታዊ እሳቤ ይልቅ በፍትህና ርትዕ ላይ የቆመ የፖለቲካ ሥርዓት ቢኖረን ኖሮ ጠሚ ዓቢይ በአዲስ አበባ መሬት ዘረፋ ብቻ ከንቲባ ታከለን እና በተዋረድ እስከ ታች ድረስ ያለውን ብልሹ አመራር ሰብስበው ወደ ማረሚያ ቤት እንዲገቡ ቀጭን ትዕዛዝ በሰጡ ነበር።
ይሁንና ጠሚ ዓቢይ ታከለ ኡማንና ብልሹ ሰንሰለቱን ተጠያቂ በማድረግ ወደ ማረሚያ ይልካሉ ብየ አላስብም። ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉትን የኦዴፓ አመራሮች እነ ለማ መገርሳ፣ ሚልኬሳ ወዘተ ለምን ወደ ማረሚያ አላኳቸውም? ታከለም ለምን አይታረምም? መልሱ ብልጽግናም ሆነ ብልጽግናን የሚመራው መንግስት እንዲሁም ከፍትህ ይልቅ በብሄር ስሌት ፖለቲካን የሚያስበው ፖለቲከኛና በፖለቲከኛው የሚነዳው ዜጋ በአጠቃላይ መንግስታዊና ተቋማዊ መዋቅርና ሥርዓታችን ለእርምት እርምጃወችም ሆነ በእስር ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ ቀውሶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመቆጣጠር ዝግጁ አይደሉም።
እኔም በጠሚ ዓቢይ ቦታ ብሆን ላደርገው የምችለው ከዚህ የተለየ አይደለም። ከብሄር ማንነት ይልቅ አገራዊ መሻሻልንና ፍትህን የሚያስቀድም ዜጋ እና ተቋማት ስንፈጥር ይሄን ለማድረግ አይከብድም። በነገራችን ላይ ይኼ ሁሉ ያለፉት 27 ዓመታት የህወሓት አቀንጭራ ፖለቲካ ውጤት ነው። ዘውጌ ብሄረተኝነትን የምጸየፈው የአገራችን የተጠላለፉ ችግሮች ምንጭ እሱ ስለሆነ ነው፤ ታዲያ ችግሩን በፈጠረው እሳቤ ችግሩን እንፈታለን የሚሉ ትኩስ ብሄረተኞችን ሳይ “ችግሩን በፈጠረው አስተሳሰብ ላይ ቆመህ የችግሩን መፍትሄ አታገኝም” የሚለው የአልበርት ኢንስታይን ቃል ይታወሰኛል።
በነገራችን ላይ ከንቲባ ታከለ ኡማ በአንድ ወቅት “ከፈለግን ዓቢይን ቂጡን ገልበን እንገርፈዋለን” እስከ ማለትና በጠሚ ዓቢይ ላይም መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ እስከማሰብ የሚያስችል ኃይል፣ አቅምና ጉልበት እነደነበረው ለመገንዘብ አይከብድም። ራሱን ከጠሚ ዓቢይ ቀጥሎ አድራጊ ፈጣሪ 2ኛ የኢትዮጲያ ሰው አድርጎ የሚያይ ድፍረት የተሟላ ሰው ነው። ጠሚ ዓቢይ ተገዳዳሪወቻቸውን ተራ በተራ እየመገዙ በመሄድ ታኬንም ለጉልበቱ ምንጭ ከሆነው ቁልፍ የሥልጣን ቦታ አንስተውታል።
እንግዲህ የኢዜማ ጥናታዊ የዘረፋ ማጋለጫ ሰነድ በጠሚ ዓቢይ መደርደሪያ ላይ ይቀመጥና ከንቲባ ታኬን የሚያስበረግግ፣ አድርግ የተባለውን እንዲያደርግ ማስፈራሪያ አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ ክስ የሚመሰረትበት ዶሴ ይሆናል ማለት ነው። እንግዲህ ታኬ የጠሚ ዓቢይን ፊት በማየት ሲስቁ መሳቅ፣ ሲያዝኑ ማዘን እንዲሁም አድርግ የተባለውን ማድረግ እንጂ ዝንፍ ማለት የለም። ዝንፍ ካለማ ዶሴው ከመደርደሪያው ይነሳለታል። በአንድ በኩል የኢዜማ ጥናት ለጠሚ ዓቢይ ጉልበት የሚያስገኝላቸው ሲሆን በሌላ በኩል ፓርቲያቸው ብልጽግና ከአዲስአበባ ሕዝብ ልብ ውስጥ ተፍቆ እንዲወጣ የሚያደርግ ነው።
እዚህ ላይ መናገር የምፈልገው ልክ እንደ ታከለ ኡማ መሬት የወረረና ያስወረረው ሰውዬ አማራ ወይም ትግሬ ቢሆን ኖሮ የአማራና የትግራይ ብሄረተኞች ዘረፋውን ወይም ወረራውን ከመሸፋፈን በላይ፣ የእነሱን ሰው ከማድነቅና ንጹህና ታታሪ ሰው ነው ከማለት ወደ ኋላ አይሉም። ዘውጌ ብሄረተኝነት ለዘውጌው ቁንጮወች እንጂ አንድም ቀን ለዘውጋቸው የታችኛው ሰወች ጠቅመው አያውቁም ሊጠቅሙም አይችሉም። ታከለ ኡማ ሱልልታም ሆነ አዲስ አበባ ከንቲባ ሆኖ ያስወረረው መሬትና ዘረፋው ባሌ ጊኒር አልያም ወለጋ ሻሙቡ ለሚኖር ገበሬ አንዳችም ትርፍ የለውም።
ፖለቲካችን ከዘውጌያዊ እሳቤ እስኪወጣ እንዘጭ እምቦጩ ይቀጥላል። ኢትዮጵያን የምትወዱና የአገራችሁ እጣ ፈንታ የሚያሳስባችሁ ሁሉ የምላችሁ ነገር ቢኖር የችግሮች ምንጭ የሆነው ህወሓትና አጋሩ ኦነግ ጥርሳቸውን በነቀሉበት የዘውጌ ብሄረተኝነት ፖለቲካ ውጤት እናመጣለን ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ ዛሬውኑ መንቃት እንዳለባችሁ ነው። ህወሓትና ኦነግን በሜዳቸው በዘውጌ ብሄረተኝነት እንገጥማለን ማለት ቂልነት ነው፤ ምናልባት አገር ታፈርሱ ይሆናል።
የ27 ዓመት የህወሓት ስልታዊና መዋቅራዊ አገር የማፍረስ ፖለቲካ በሴራ፣ በተንኮል እንዱሁም በብልጠት ቀስ በቀስ የተከናወነ ነው። ለዚህ መፍትሄው ደግሞ በህወሓት የዘውጌ ፖለቲካ እሳቤ ተቸንክሮ ያለውን ዜጋ ወደ ትክክለኛ መስመር የምትመልሰው አገርን የማዳን የፖለቲካ ሴራና አሻጥር በመጫወት፣ ጉልበት በመሰብሰብ፣ የችግሩን ግንድ ተራ በተራ በመመገዝ እንጂ በግልጽነት፣ በሀቀኝነት እንዲሁም በመርህ አይደለም።
118729510 3328073387248080 66225779867560593 n
ግንባር ቀደሙ ግብረ አበር አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚና አስተባባሪ ኮሚቴወች በመሬት ወረራና በሌሎች ኢፍትሃዊነት አሰራሮች ዙሪያ ምክክርና ግምገማ ሲቀመጥ በስብሰባወቹ ሁሉ የፌስቡኩን ዘውዳለም ገጸ ባህሪ የሚተውኑ የታኬ ሽፋን ሰጭ ናቸው።
ታኬን የሚገመግሙትን ሁሉ መረጃ የላችሁም፣ ጭፍን ጥላቻ ነው ወዘተ በማለት የእነ ዘውዳለምን የፌስቡክ ወሬ በስብሰባው ለማሸማቀቂያ በመጠቀም እውነት ይዘው የሚሞገቱትን የአርሶ አደር ልጆች የሚያሰበረግጉ ናቸው። እንኳን አስበርግገዋቸው እንዲያውም የበረገጉ ናቸው!!
በእርግጥ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ በግምገማ አናት አናቱን ተብሎ ተኮርኩሞ በdemotion ከአዲስ አበባ ብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊነት ወደ ዋናው ብልጽግና ጽ/ቤት ተዛውረዋል። የፌድራል አቃቤ ህግ በመሬት ወረራው ዙሪያ መረጃው እንዳለው ለማወቅ ችለናል፤ ታዲያ ታኬ ላይ ምርመራም ሆነ ክስ የሚቀርብ ከሆነ በ2ኛ ደረጃ ስማቸው የሚጠቀሰው አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ መሆናቸው አይቀርም።

2 Comments

  1. መንግሥት ሲኖር እኮ ነው ህግ የሚጥሱትን እንድ ኡማ ያለውን ደንቆሮ አዛባ ፍርድ ፊት የሚቀርበው፡፡ያንን ጫታም ጀዋርን የስንት ንጹሃን ደም እጁ እያለ ፕ/ሚሩ እሹሩሩ እያለው ነው፡፡ በጣም ያሳዝናል ከወያኔ ዘረኝነት ወደ ኦሮሞ ዘረኝነት አስተዳደር መሸጋገራችን! ወያኔ እንኳን አገሬ ኢትዮጵያ እያለ እያቀነቀን ነበር የግፍ ሥልጣን ላይ የቆዩት፡፡
    አብይና ቢጢዎቹ ደግሞ ኢትዮጵያን ሊያጠፉ፣ ታሪክን፣ ቋንቋን፣ ባህልን ሊያጠፉ ተግተው የሚሰሩ የእንሰሳ ስብስብ የአገር ፣ የታሪክ ከሃዲዎች ናቸው፡፡ ይሂ ሁሉ ግድያና ሰቆቃ፣ አገር ማጥፋት ድግሞ የሚፈጸመው ባለፉት 3 ዓመት ውስጥ በዚሁ ፕ/ሚር በአንድ እጁ ችግኝ እየተከለ በሊላው እጁ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ሳይሆን የኦሮሞ ክልልን አጀንዳ ነው የሚሰራው፡፡ ፕሊስ ህዝብ በቢላ ሲታረድ ብቅ አይልም ኢዜማ ስብሰባ አድረገ ብሎ ግን ሰላማዊ ስብሰባ ሊበትን ይመጣል፡፡ ይሄ ሁሉ የአስተዳደሩ ድክመትና ቅድሚያ የሚስጡት አዲስ አበባችንን ለመሸጥ የኦሮሞ ሰፈራ ነው የያዘው፡፡ እግዚአብሔር ስራቸውን ይፋረዳቸው!!ጀዋርን እሹሩሩ
    እንደኔ ክሆነ ክዚህ የባሰ ሰው አዘቅዝቆ የሚያሰቅል መንግስት ስለማይመጣ ህዝቡ ያሻውን መርጦ ቢለይለት ይሻላል እንጂ ከዚህ ካልበሰለ መሪ አገር ይገኛል ብሎ ማሰብ ትንሽ ያስቸግራል፡፡ አገር በቢላ እየታረደ በቢጤውቹ እሱ ችግኝ ተክላ ነው ዋናው አጀንዳው፡፡ This P/m guy must to go! he’s a bad karama.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.