ለውጡ አብዮት ሳይሆን ሪፎርም ነው – አቶ ፍቃዱ ተሰማ፣የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ

Fekadu“በሰለጠነ አገር ሆነው ያልሰለጠነ መልዕክትና ፀያፍ ነገሮችን ከማስተላለፍ ይልቅ ወደ ህሊናቸው ተመልሰው ሁኔታዎችን ዳግም ማየት አለባቸው” – አቶ ፍቃዱ ተሰማ፣የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤
• ለውጡ አብዮት ሳይሆን ሪፎርም ነው። ሪፎርሙ ውስጥ ደግሞ የተለያዩ አካላት አሉ። ሪፎርሙን ወደፊት ይዘው መሄድ የሚፈልጉ አሉ፤ ሪፎርሙን ወደኋላ የሚመልሱ አሉ። እነዚህ ወደኋላ መመለስ የሚፈልጉ አካላት የራሳቸውን የቡድን ፍላጎትና የግለሰብ ፍላጎት ማዕከል አድርገው ነው።
• ለውጡን ሊቀለብሱና ወደኋላ ሊመልሱ ከሚፈልጉት ውስጥ አንዱ እንደ ህወሓት አይነቱ በሴራ ፖለቲካ አካሄድ ስልጣን ላይ የነበረና ያንን ስልጣን ያጣ ነው።ከተቻለ ወደስልጣን ለመመለስ፣ ካልተቻለ ደግሞ ሀገር ለመበተን የሚደረግ ሩጫ ነው።
• ሌላው ደግሞ ከውጪ የመጣውና ለውጡን እኔ ነኝ ያመጣሁት ብሎ የሚያስበውና አክቲቪዝም በዓለም ላይ ጫፍ የረገጠበትን አጋጣሚ ተጠቅሞ በዚህ መስመር የመጣ አዲስ ተስፈኛ አካል የተፈጠረበትና ነው።
• ይህ ደግሞ ቀደም ሲል የዴሞክራሲ ምህዳር ችግር ስለነበረ በውጪ የነበሩት ለውጡን ተከትሎ በተፈጠረው ምህዳር ወደ አገር ውስጥ የገቡ፤ የሪፎርሙ ውጤት ተደርገው የሚታሰቡ ናቸው።
• ለውጡ በአብዮት መጥቶ ቢሆን ግን ሁሉንም ጠራርጎ ነው መልክ የሚያሲዘው እንጂ ይሄን አይነት እድል አይሰጥም ነበር። ሪፎርም ግን በዚህ ሁሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ በብልሃትና በትዕግስት መስዋዕትነትም ጭምር እየከፈልክ የምትሄደው ስለሆነ፤ ያ ትዕግስትና የተከፈተው የዴሞክራሲ በር ነገሮች የመሰሉትን እንዲመስሉ አድርጓል።
• ሁሉም ወደ አገር በሚገባበት ጊዜ በሰላም እታገላለሁ ብሎ ነው የገባው። ከገባ በኋላ ግን ሁለት ቦታ የመቆም ሁኔታ ነው የታየው። በተለይ ኦነግ ሸኔ በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ በህቡዕ የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ነበረ።
• የተከፈተው የዴሞክራሲ በር ሰዎች እንደልባቸው እንዲፈነጩ፤ ግለሰቦች መንግስት መስለው እንዲታዩ ያደረገበት ሁኔታ ነበር፤ ይህም በየደረጃው ያለው አመራር አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል።
• የህግ የበላይነቱን ሙሉ በሙሉ ለማስከበር የሚደረገው ጥረት በራሱ የዴሞክራሲ ምህዳሩ እንዳይጠብ የሚል ስጋት ነበር።
• የዴሞክራሲ ምህዳሩ ጠቦ ያለፉ ነገሮች ተመልሰው ዴሞክራሲው አጣብቂኝ ውስጥ እንዳይገባ በሚደረገው ጥረት ሰፊ ክፍተቶች ተፈጥረዋል። በዚህ መሀል የችግሩ ሰለባ የሆኑ ሰዎች የሉም ማለት አይቻልም። ነገር ግን በአብዛኛው አመራሩን ይገልጻል ማለት ግን አይደለም።
• በተለያየ ጊዜ የሚደረጉ የሁከትና ጥፋት ጥሪዎች የሚከሽፉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ህብረተሰቡ ጥሪያቸውን አልሰማም ያለበት ዋናው ምክንያትም ህብረተሰቡ ውስጥ ያለው የጠነከረ አንድነት ነው፤
• የትኛውም አይነት ጽንፈኝነት በህዝብ ደረጃ ተቀባይነት የለውም። ሙስሊሙ ክርስቲያን ላይ ተነስ፤ ክርስቲያኑ ሙስሊሙ ላይ ተነስ፤ አንዱ ብሄር ሌላው ብሄር ላይ ተነስ በሚል የሚገለጽ በህብረተሰቡ ውስጥ የለም።
• ከወጣቶቹ ጋር ሰፋ ያሉ ውይይቶችን አድርገናል። ውጪ ተቀምጠው ወደዚህ የሚያስተላልፉት መልዕክት አይጠቅመንም የሚል ድምዳሜ ላይ እየደረሰ ነው።
• በየጊዜው የሚተላለፉ መልዕክቶች የሚከሽፉበት ዋናው ምክንያትም ይሄ በመሆኑ ነው። ይሄንን አጠናክሮ በመቀጠል ከውጪ የሚያዝ አካል ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሚያጣበት ሁኔታን ለመፍጠር እየተሰራ ነው።
• ህብረተሰቡ በተደራጀ አግባብ በየአካባቢው ለሰላሙ መረጋገጥ የጸጥታ ስራውን ሆነ የልማት ስራውንም እንዲሰራ፤ በዚህም የልማቱም የሰላሙም ባለቤት እንዲሆን ማስቻል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።
• ብልጽግና የክልላችንን ህዝብ ጥያቄ ለመመለስ የመጣ ፓርቲ ነው ብዬ ነው የማየው። በስፋቱ ልክ መወከል አለብኝ የሚል ጥያቄ ነበር። ይሄ የፍትሃዊነት ጥያቄ ነው።
• የህግ የበላይነትን ከማስከበር አኳያ አጠቃላይ ህብረተሰቡን አሳትፈን ችግሩን ለዘለቄታው የመፍታት ስራ ተሰርቷል። አሁን በጥባጩ አካል የሚቆጣጠረው ዞንና ወረዳ ቀርቶ የሚቆጣጠረው ቀበሌ የለም።
• ብልጽግና አንድ ነው። በክልሎች ደረጃ ጽህፈት ቤት ነው ያለው። በአገር አቀፍ ደረጃ ዋናው ጽህፈት ቤት ነው ያለው። አንድ ወጥ ስራ አስፈጻሚ እና አንድ ወጥ ማዕከላዊ ኮሚቴም ምክር ቤትም ነው ያለው።
• እዚህ ደግሞ በክልሉ ሁለት ነገሮችን አስታርቆ ነው ብልጽግና የሚሰራው። የመጀመሪያው አገራዊ አንድነትን ፣ ሁለተኛ ደግሞ የብሄር ማንነትን ማዕከል አድርጎ ፌዴራሊዝምን ማስቀጠል ነው። ስለሆነም በጋራ ነው ተልዕኮ የምንወስደው፤ በጋራም ነው የምንፈጽመው።
• ባለፈው በክልላችን ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ ችግሩን ከመከላከል አኳያ ከአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጋር አብረን ስንሰራ ነበር።
• ጽንፈኛው ሃይል አጠቃላይ ኦሮሞ በአማራ ላይ እንደተዘመተ ተደርጎ ስለተቀሰቀሰ፤ በዛ በኩልም ይሄን ነገር ተረድቶ ይሄ ነገር እንዳልሆነና ጽንፈኛ ሃይል የቀሰቀሰው እንደሆነ፤ እና ኦሮሞ አማራ ላይ ሊነሳ እንደማይችል የማስገንዘቢያ ስራዎች ባይሰሩ እና በተቀሰቀሰው ልክ ግጭት ቢፈጠር ኖሮ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ትልቅ ነበር የሚሆነው።
• በተመሳሳይ ከሶማሌ ብልጽግና ፓርቲ ጋር፣ ከአፋር ብልጽግና ፓርቲ ጋር፣ ባጠቃላይ ከሁሉም ክልሎች ብልጽግና ፓርቲ ጋር በየጊዜው እየተገናኘን እንገመግማለን፤ የተሞክሮ ልውውጥም እናደርጋለን። ስለዚህ አንድ ላይ ነው የምንሰራው ማለት ይቻላል።
• በአንድ ግምገማና በአንድ ኮንፍረንስ ሁሉም ችግሮች በአንድ ጊዜ ጠርተው ይጠፋሉ ማለት አይቻለም። ነገር ግን በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ከአሁን በኋላ ፈተናዎች እየቀነሱ ይሄዳሉ፤
• ህብረተሰቡ የሰላሙም የልማቱም ባለቤት እንዲሆን ካደረግነው በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ችግሮችን ማቃለል ይቻላል፤ ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳን መቋቋም ይቻላል።
• ከቀበሌና ወረዳ ጀምሮ በትልልቅ ከተሞች ላይ ነው ማጥራት ያደረግነው። እንደገናም ወደ 11 የሚሆኑ ዞኖች ላይ የማጥራትና መልሶ የማደራጀት ስራ ሰርተናል።
• ሰፋ ያለ ቁጥር ያለው አመራር ከታች እስከላይ የማጥራትና የማስተካከል ስራ ነው የተሰራው። ይህ ደግሞ አገር መቀጠል አለበት፤ ህዝብ መቀጠል አለበት፤ ፓርቲ መቀጠል አለበት በሚል የተከናወነ ነው።
• ብልጽግና ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች በእኩልነት የሚሳተፉበት፤ በፍትሃዊነት የሚወከሉበትም ፓርቲ ነው። እንደገናም በአገራችን ፈተና እየገጠመው ዴሞክራሲ እንዲያብብ ለማድረግ ነው።
• ሀሳብ አለኝ የሚል አካል እዚህ መጥቶ ሀሳቡን ይዞ ሰላማዊ ትግል ማግረግ ይችላል ከዚህ ውጪ ከኦሮሞ ባህል፣ እሴትና ተፈጥሮ ውጪ ኦሮሞን መሳል የሚፈልጉ የኦሮሞ ጽንፈኞችን ህዝቡ በቃችሁ ሊላቸው ይገባል።
• ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ብሄር ብሄረሰቦችም ጋር አንድ ሆኖ ዋጋ የከፈለበትን ለውጥና በለውጡ የጀመረውን ጉዞ ማስቀጠል፤ አካባቢውንም ሰላም ማድረግ አለበት፤ የሚል መልዕክት አለኝ።
ምንጭ አዲስ ዘመን ነሐሴ 25/2012

1 Comment

  1. You are running the same system except changes of minsters
    the same ideolgy , belife , constitution , the same party …
    it is not reform either !!!
    your still in trouble to define what is the change about
    confused !!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.