ጉዳዩ:  የሜ/ጄኔራል  ሃየሎም  አርአያ  አሟሟት እና  የአቶ  ሊላይ ”አዲስ መረጃ”

lilayበእርግጥ አቶ ሊላይ ሃይለማርያም  በፋና ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው ሰፊ ሽፋን ያገኘ ቃለ ምልልስ ማድረጋቸው ከወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት አንጻር መቀሌ በመሸጉት የትህነግ/ህወሃት አመራሮች መካከል  በአቦይ ስብሃት ነጋ፣በአቶ አባይ ጸሃዬ እና በአቶ ስዩም መስፍን ላይ ብቻ ማነጣጠራቸው እና ሊኖራቸው ከሚችለው ጥልቅ መረጃ አንጻር ፣ አቶ ጌታቸው አሰፋን እና ሌሎችን አለማንሳታቸው በተለይም ደግሞ የድርጅቱ ዋና ሞተር የሆኑትን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ትተው የ82 ዓመቱ ሽማግሌ አቦይ ስብሃት የሚመሩት ዳይናስቲ ናቸው ሲሉን ግራ አጋብተውናል።ኤርሚያስ ለገሰ ”የመለስ ትሩፋት” በሚለው መጽሃፉ የውስኪ ጠርሙስ ይዘው በየቢሮ የሚዞሩ መሆናቸውን የዘነጉት ይመስላል። ስለ ጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ ሲጠየቁ ይሄ ጂኒ ነው የሚሉ ሽማግሌ በጂኒ አብዮት ኢህአዴግን ለዚህ አላበቁትም። ቢያንስ አራዳው መለስ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚባል የት እንደተፈጠረ የማይታወቅ ማደናገርያ ሰርዓት አምጥተው ይሀው ዛሬ ድረስ እነ ደብረ ጽዮን መቀሌ መሽገው የማያቁትን ነጠላ ዜማ ይዘምራሉ።

አቶ ሊላይ ሃይለማርያም ከላይ የተቀመጡትን ጉዳዮች ከማብራራት ይልቅ ድርጅቱን ከሰላሳ ስድስት ዓመት በፊት ለቀው የወጡትን እና አሁንም ድረስ ከህወሃት በተጻራሪ ከለውጡ ጋር ያሉትን ዶክተር አረጋዊ በርሄ እና አቶ ግደይ ዘርዐጽዮን ላይ የሚያደርጉት ዘመቻም ዓላማው ግልጽ አይደለም።ከሁሉም የሚገርመው ደግሞ ጋዜጠኛ አበበ ገላውን ከፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ሞትጋር ማያያዛቸው ደግሞ ትዝብት ዉስጥ ጥሏቸዋል።ጊዜው የመለስ ሙት ዓመት በአድናቂዎቹ የሚዘከርበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አቤን መተንኮሳቸው የዛሬ 8 ዓመት እንደ መብረቅ ያቧረቀባቸውን ለመበቀል ያሰቡ ያስመስላል።በአራዳ ቋንቋ ሼም ነው ከማለት ውጭ ምን ይባላል። ለነገሩ አቤም የዋዛ አይደለም በፋና ቴሌቪዥን ሊጠዛጠዝ ቀጠሮ ይዟል።

ከፋና ቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ መካከል ቀልቤን የሳቡት Hilton Hotel ውስጥ ሰራሁት የሚሉት ስለላ፣የሜ/ጄኔራል ሃየሎም አርአያ እና የክንፈ ገብረመድህን ግድያዎች ናቸው።

  1. የስለላ ስራ በ HILTON ADDIS ABABA

በ1970ዎቹ  በአቶ ማሞ ውድነህ ተተርጉመው ከቀረቡት የስለላ መጽሃፎች መካከል “የካይሮ ጆሮ ጠቢ”  ውስጥ  የዎልፍጋንግ  ሎትዝን  እና “የኛ ሰው በደማስቆ”  በሚለው ደግሞ የኢላይ ኮህንን  የስለላ ብቃት አንብበን ላደግን የስለላ ስራ እንዲህ በአጋጣሚ የተሞላ የድርሰት ስራ ሊሆን እንደማይችል ጠንቅቀን እንረዳለን። እንዲህ አይነት ትላልቅ ሆቴሎች በአስተናጋጁ አገር ሰላዮች የ24 ሰዓት ክትትል የሚደረግባቸው በመሆኑ ይህን ስራ ለመስራት በህዝብ ደህንነት ሚኒስቴር ውስጥ በከፍተኛ ሃላፊነት ላይ ያለ ሰው ትብብር ማግኘት ግድ ይላቸዋል። በHILTON HOTEL MANAGEMENT  ውስጥ ተባባሪ የሆነ የውጭ መንግስት ሰላይ ይኖራል የሚል ግምት አለኝ።እሳቸው እንደሚሉት በ HILTON ADDIS HOTEL የህወሃት ሰላይ ሆነው ሲሰሩ ስለ ራሳቸው ያልገለጹልን ብዙ ጉዳዮችን ማብራራት ይጠበቅባቸዋል።

ከአዲስ  አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ Washington, DC 2009 G.C የተላከው  ኬብል   WikiLeaks  ተጠልፎ  እንደተነበበው፣በወቅቱ የደህንነት ሃላፊ የነበረው አቶ ጌታቸው አሰፋ ብዙዉን ጊዜ የማይታይ(elusive)፣ያልተለመደና እንግዳ ባህርይ ያለው (eccentric)፣ከስራ  ባልደረቦቹ ጋር የማይወያይ እና ብቸኛ (reclusive) ፣ቶሎ የሚቆጣ(hot tempered)  በመሆኑ የስራ ባልደረቦቹ ባህሪውን ለማወቅ እንደሚቸገሩ በዚህም ምክንያት ትርጉም  የማይሰጡ  ውሳኔዎችን  የሚወስን  ግለሰብ  መሆኑን  አምባሳደር  ዶናልድ ያማቶቶ  ለበርካታ  የአሜሪካ  የደህንነት መስርያ ቤቶች  አሳውቀዋል። ጠ/ሚኒስትር መለስም  ይህን  ባህሪይ  እንዳረጋገጡላቸው  እና  ግን  ደግሞ  የፓርቲው ታማኝ  መሆኑን  ገልጸውላቸዋል። እንዲህ  አይነት ሰዎች በፓርቲ  ታማኝነት በሚሾሙበት ሃገር ከአቶ ሊላይ የተለየ የደህንነት ሙያዊ ብቃት አልጠብቅም።

 

አቶ ዳዊት እንዲህ ዓይነት ስለላ በመንግስት ሆቴል ሊሰራ አይችልም የሚል መከራከሪያ አቅርበሃል። Hilton Addis Ababa ባለቤትነቱ 80% የኢትዮጵያ መንግስት ቢሆንም የ MANAGEMENT ስራው ግን በስምምነታቸው መሰረት በ Hilton International ደንብ በመሆኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ተጽእኖ ነጻ ነው። እንዲህ አይነት ስለላ አይደለም በሆቴል ውስጥ በቤተመንግስት ውስጥ ይካሄድ እንደነበር በማስረጃ ላቀርብልህ እወዳለሁ።

አሜሪካ ሆኖ በ1981 ዓ.ም ኢትዮጵያ ውስጥ የከሸፈውን ኩዴታ በበላይነት ያስተባበረው የነጻ ኢትዮጵያ ወታደሮች እንቅስቃሴ አባል የነበሩት ሻለቃ ጌታቸው የሮም እውነተኛ ታሪካዊ ሰነድን መሰረት አድርገው በጻፉት“ፍረጅ ኢትዮጵያ ”  በሚለው መጽሃፋቸው ገጽ 61 ላይ የዚሁ ድርጅት አባል የነበሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ  ኩዴታውን በአንድ በኩል ከሻዕቢያ እና ከነ ሜ/ጄኔራል መርዕድ ንጉሴ እና ሜ/ጄኔራል ፋንታ በላይ ጋር በሌላ በኩል ደግሞ ከኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ስላሴ ከደርጉ የደህንነት ሚኒስትር  እና ከፕሬዝዳንት መንግስቱ  ሃ/ማርያም ልዩ ረዳት ከነበሩት ከመንግስቱ ገመቹ ጋር እንዳስተባበሩት ተዘግቧል።

በ 1982 ዓ.ም ምጽዋ ላይ ቆስሎ በሻዕቢያ ተማርኮ የነበረውና ከሳህል በረሃ ወታደራዊ ምስጢር ይዞ ያመለጠው ሃምሳ አለቃ ታደሰ ቴሌሳልቫኖ ፕሬዝዳንት መንግስቱን ባነጋገረበት ወቅት ያቀረበላቸው የሻዕቢያ መረጃ እሳቸው እዛው ቤተ መንግስት ውስጥ የተናገሩት መሆኑን መረዳታቸው ምን ያህል ጠላት ጓዳቸውን እንደሚከታተል ማሳያ መሆኑን “አይ ምጽዋ ” በሚለው መጽሃፍ አስነብቦናል።

  1. የሜ/ጄኔራል ሃየሎም አርአያ ግድያ

በሀገር መከላክያ ሚኒስቴር የዘመቻ ዋና መምሪያ አዛዥ የነበሩት ሜ/ጄኔራል ሃየሎም አርአያ ረቡዕ የካቲት 6 1988 ዓ. አዲስ አበባ ከተማ ኦሎምፕያ አካባቢ“ ቦለሎች “  በሚባል ባህላዊ ምግብ ቤት ውስጥ ከሰዓት በኋላ ከአቶ ጀሚል ያሲን በተተኮሰ ጥይት መገደላቸውን የሰማሁት አምባሳደር ቲያትር ፊት ለፊት በሚገኘው የመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መስርያ ቤት በስራ ላይ እያለሁ ነው።እኔ የምሰራበት የመገናኛ መምሪያ ደግሞ በሳቸው ዕዝ ስር በመሆኑ የአለቃችንን አሟሟት እና ገዳይ ለማወቅ ሁላችንም በየአቅጣጫው መረጃ ማሳደድን ተያያዝነው።በዚህም መሰረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ገዳዩ ኤርትራዊ እንደሆነ እና ከኤርትራ መንግስት ጋር አቀናብሮት ሊሆን እንደሚችል፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር የነበረው የአራንሺ አበልጅ እና የቅርብ ጓደኛ እንደሆነ ፣ ጀሚል ያሲን ጄኔራል ሃየሎምን ተተናኩሶት ወደ ደጅ ሲወጣ ሃየሎም ሲከተለው   ምግብ ቤቱ በር ላይ ተኩሶ መግደሉን አረጋገጥን።

በወቅቱ የምግብ ቤቱ የጋራ ባለቤት የነበረችው ድምጻዊት የዝና ነጋሽ በ Oct 20, 2019 YouTube  በተለቀቀው የሰይፉ በEBS ፕሮግራም ላይ ስለዚሁ ጉዳይ ተጠይቃ “ያ ነገር “ እያለች በስሙ ለመጥራት እንደምትፈራ ይታይባት ነበር። በወቅቱ ይደርስባት ከነበረ ጫና ለማምለጥ በሚመስል መልኩ ለአንድ ዓመት ኪራይ ከፍለው ብዙ ብር ለጥገና ያወጡበትን ቤት አንድ ወር ከአስር ቀን ብቻ ተጠቅመውበት ለቀው ወጡ። በአጭር ጊዜም ውስጥ አብራት ትሰራ ከነበረች ሌላ ዘማሪት ጋር ወደ እንግሊዝ  አቅንተው ኑሯቸውን እዛው መሰረቱ።በግድያው ጊዜ ከሃየሎም ጋር አብሮ የነበረው ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዉሎ እንደ ተጠርጣሪ ሆኖ አልተጠየቀም።በዚህ ጉዳይ ላይ መግለጫም ሰጥቶ አያውቅም።ይህም የጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጓደኛ ስለነበር ነው።

አቶ ጀሚል ያሲን መኪና ውስጥ ከፖሊስ  ኮሚሽነሩ አራንሺ ጋር በቀጥታ የሚገናኝበት ሬድዮ ነበረው። በየትኛውም የዓለም ክፍል ውስጥ ስውር ፖሊስ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ዜጋ እንዲይዝ አይፈቀድለትም።ይሀው ግለሰብ በአንድ አጋጣሚ በሽርክነት አብሮት ከሚሰራ ግለሰብ ጋር በገንዘብ በተጣላበት ጊዜ ሊረዱት በአራንሺ ከተላኩት ፖሊሶች መካከል ከግልፍተኘቱ የተነሳ አንድ ፖሊስ ላይ ተኩሶ ጉዳት አድርሶ ምንም አልሆነም።ጀሚል ያሲን እዩኝ እዩኝ ማለት የሚወድ፣ሌሊቱን ሙሉ ከየምሽት ክለቡ የማይጠፋ እና ችኩል ሰው ነበር።

የጄኔራል ሃየሎም ግድያ ከቤተመንግስት በመጣ መመሪያ መሰረት ታሪኩ ተቀይሮ የሟቹን ስብዕና በማይመጥን መንገድ፣ እዛ ቦታ መገኘት እንዳልነበረበት እና የእሱ ግዴለሽነት ለሞቱ ምክንያት እንደሆነ መነገር ተጀመረ። ሌላው በጣም የሚገርመው ሃየሎም ከሰዓት በኋላ በግምት ከ8 እስከ 12 ሰዓት አካባቢ ምግብ ቤቱ በር ላይ ተገድሎ እያለ ማታ ተብሎ መቀየሩ ከመጠጥ ጋር በተፈጠረ አምባጓሮ ጠብ እንደተነሳ ለማስመሰል ነው።ከመከላከያም  ኮማንዶዎች ምሽት ላይ ተልከው ገዳዩን ሲፈልጉ የኦሎምፕያን  አካባቢው ቀውጢ አደረጉት።እንደዚህ ዓይነት ትላልቅ ጉዳይ ሲያጋጥም የፌዴራል ፖሊስ፣የብሄራዊ ደህንነት እና የመከላከያ ሚኒስቴር አብረው መስራት የተለመደና አሁንም የሚተገበር ነው። የአዲስ አበባ ፖሊስ ክሱን ወደ ፍርድ ቤት ከመውሰድ ባሻገር የጎላ ሚና እንደሌለው መረዳት ችያለሁ።ዉሎ ሲያድር ደግሞ ጄኔራሉ በኤርትራ ጉዳይ ከነመለስ የተለየ አቋም ስለነበራቸው ከደቡብ ዕዝ አዛዥነት አንስተው መከላከያ ያመጧቸው ሆን ብለው ነው የሚል ቲዎሪ ውስጥ ውስጡን ይወራ ነበር። እኔም ይህን ሃሳብ እጋራለሁ። በተለይም ገዳዩ ጀሚል ያሲን የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሲጀመር መገደሉ ደግሞ የበለጠ አጠራጣሪ አደረገው።አቶ ሊላይ ጄኔራል ሃየሎም በሴራ ተገደለ የሚሉትን አስተሳሰብ በርካቶች የሚጋሩት ጉዳይ ነው።

ስለዚህ አቶ ዳዊት ከበደ አንተ እንደ አንድ ጋዜጠኛ ፖሊስ ባቀረበው ማስረጃ፣አቃቤ ህግ በመሰረትው ክስ እና ክቡር ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን አመዛዝኖ በሰጠው ውሳኔ መሰረት የዘገብከው ዘገባ በነበረህ መረጃ መሰረት ትክክል ነህ።ነገር ግን የተድበሰበሰ ጉዳይ ሲኖር እውነቱን ለማውጣት በሚደረግ ጥረት ውስጥ እንዲህ አይነት ሀሳቦች ይመጣሉ። በእንግሊዘኛ እንዲህ አይነቱ መረጃ Conspiracy Theory ይባላል። በአማርኛ ሴራ የሚለዉ ቃል አንድን አካል ለመጉዳት የሚል እሳቤ ስላለው አልተጠቀምኩትም። ለምሳሌ በአሜሪካ ኮንግረስ የኬኔዲን ግድያ እንዲመረምር የተቋቋመው Warren Commission “ የፕሬዝዳንት ኬኔዲን ገዳይ Lee Oswald Harvey  ነው ብሎ ፋይሉን ዘግቶ እያለ ዛሬም ድረስ ከ 50 ዓመታት በኋላ  Conspiracy Theory አራማጆች የተለያየ መላ ምት ይወረውራሉ።ከዚ መሃል የኬኔዲን ሚስት ያገባው ግሪካዊ ነጋዴ ኦናሰስ፣የቴክሳስ የነዳጅ ሃብታሞች፣የጣልያን ማፍያ እና ሌሎችም።ለዚህም ምክንያት ሲያቀርቡ ሚስተር ሃርቪ በዳላስ ፖሊስ ጥበቃ ስር እያለ በጃክ ሩቢ መገደሉ የመረጃውን ዱካ ለማጥፋት ነው ይላሉ።እዚህ አሜሪካ ውስጥ የተለመደ አባባል አለ እሱም “Where there is a smoke, there is a fire”.

  1. የክንፈ ገብረመድህን ግድያ

የክንፈን ግድያ ማንሳት የፈለኩበት ድርጊቱ የተፈጸመው በጦር ሃይሎች መኮንኖች ክበብ ውስጥ በመሆኑና በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝን እይታ ለማካፈል ነው። አቶ ክንፈ የህወሃት ማከላዊ ኮሚቴ አባል ስለ ነበር እና ከመቀሌው መከፋፈል በኋላ ከደህንነት ስራ ይልቅ እንደ ካድሬ ስብሰባ ሲመራ ነበር። ለሞቱ ምክንያት የሆነው የመጨረሻው ስብሰባ የተካሄደው ከመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች(ከሻለቃ በላይ) ጋር ነበር። እኛም በኋላ ተወያይተን  እንደተረዳነው የዉይይቱ አጀንዳ “ኢትዮጵያ ውስጥ የትግራይ ገዢ መደብ ፈጥረናል”  የሚል ነበር።ይህ አባባል እኛ ነጻ አውጪ ነን እያለ ሲዘምር ለነበረ የህወሃት ታጋይ ዱብዳ ነበር። ብዙዎች ተከዳን በሚል እልህ ውስጥ ገብተው ነበር። ጓደኞቼ እንደነገሩኝ ታይቶ እና ተሰምቶ በማይታወቅ መንገድ ትግሬዎች ሁሉን መስርያ ቤት ተቆጣጥራችሁታል እያለ እንዲሽማቀቁ ሲደረግ የኦሮሞ፣ የአማራ እንዲሁም የደቡብ ተወላጆች ትግሬዎች ላይ ያላቸዉን ቅሬታ እና ጥላቻ እንዲያነጉዱ ይደረግ ነበር። በኔ ግምት እንደዚህ የተደረገው ሌሎች ብሄሮች ወደነ መለስ ድጋፍ እንዲሰጡ እና ለውጥ ይደረጋል የሚባል የውሸት ተስፋ መመገብ ነበር።

በእንዲህ ዓይነት የስብሰባ ወቅት ገዳዩ ሻለቃ ጸሃዬ ወልደስላሴ የመናገር እድል ሲጠይቅ አይፈቅድልኝም በማለት እና የድሮ ቂምም ስለነበር እሁድ ግንቦት 5 1993.  በሽጉጥ ተኩሶ አቶ ክንፈ ገብረመድህንን ጦር ሃይሎች መኮንኖች ግቢ ውስጥ ገደለው።

ከግድያው በኋላ የውይይቱ አጀንዳ ተቀይሮ ማእከላዊ ኮሚቴው በጋራ ሳይወያይ  በተናጠል የተወሰደ አቋም ነው እንጂ የትግራይ ገዢ መደብ የለም በማለት መለስ ጥሩ አሳቢ እና ክንፈ ደግሞ መጥፎ ሃሳብ አራማጅ ተደርጎ ተደመደመ። አጋጣሚውን አገኘን ብለው የለፈለፉ በርካቶች እስር ቤት ገቡ።

በደርግ እና በኢህአዴግ መካከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት እዚህ ላይ ነው።ደርግ ሊገልህ ከፈለገ ወይ በሬድዮ እና ቴሌቪዥን የፍየል ወጠጤ እያቅራራ ይገልሃል። ወታደራዊ መሪም ከሆነ በጦሩ ፊት ይረሸናል።በተረፈ በፍርድ ሂደት ውስጥ ገብቶ ድራማ አይሰራም።

በኢህአዴግ ዘመን ግን ፍርድ ቤትን ጨምሮ በየቦታው ያሉ ሃላፊዎች የፓርቲ አባል እንዲሆኑ ይደረጋል። በቂ የትምህርት ማስረጃ ሳይኖር በዓመት 2 እና 3 ክፍል እንዲያልፉ ተደርጎ በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ እንዲማሩ እየተደረገ ዲግሪ ይቀበላሉ።ክዚህ በተጨማሪ ደግሞ የግዢ ዲግሪም ይታደላሉ። የስራ ግብረገብነት(ethics) ባለመኖሩ የፍርድ ቤት ውሳኔ በሚፈለገው መንገድ ማስወሰን ይቻላል። ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እያለ ሁሉንም በላይነት ይቆጣጣረው ነበር።ከሱ መሞት በኋላ ግን እንደ ሶማልያ የጦር አበጋዞች በዙና የግለሰብ እስር ቤቶች እንዳሉ ሰማን።ምንም እንኳን ባለፉት ሁለት ዓመታት የለውጥ ጎዳና ላይ ቢኮንም የተዘረጋውን ስርዓት ለመቀየር ጊዜ ይፈልጋል።

በዚህ ነባራዊ ሁኔታ ላይ እያለን 5 ዓመታት በጉባ በረሃ በአባይ ግድብ ግንባታ ሌት ከቀን ሲባዝን የነበረው ኢንጅነር ስመኝ በቀለ መሃል አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ላይ ሃምሌ 19 2010.  ተገድሎ በቀኝ እጁ ራሱን ተኩሶ ገደለ ተባልን፣ ግልጽ ባልሆነ መንገድ በብ/ጀኔራል አሳምነው ጽጌ አስተባባሪነት በተደረገ ኩዴታ የኢፌዲሪ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ስዓረ መኮንን በገዛ ቤታቸው በጡረታ ከወጡት ሜ/ጄኔራል ገዛኢ አበራ ጋር በአጃቢያቸው ሰኔ 16 2011.  ተገደሉ።ከዚሁ ጋር ተያይዞ  የአማራ ክልል ረዕሰ መስተዳድር እና እዘዝ ዋሴ በተመሳሳይ ቀን ሲገደሉ አቶ ምግባሩ ከቆሰሉ በኋላ በሰኔ 18 2011 .  መሞታቸው ተነግሮን ቤተሰቦቻቸው እስከአሁን ፍትህ አላገኝንም እያሉ አቤቱታቸውን በየማህበራዊ ሚድያ እያሰሙ ነው። ጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድም በበኩላቸው እኔው አስፈትቼው ብ/ጄኔራል አሳምነውን ገደልክ ብለው ይጠረጥሩኛል ብለው ሲናገሩ ተስምቷል።

ለማጠቃለል ያህል ከላይ በዝርዝር እንደተገለጸው በተፈጠረው ምግባረ ብልሹነት እና ሙስና ሹመኞች ስራቸውን በአግባብ መስራት አልቻሉም። ስለዚህ ፈጣንና ፍትሃዊ ብይን ለመስጠት መንግስት ወይ በቂ አቅም የለውም አለበለዚያ በሁለት ቢላዋ የሚሰሩ ሹመኞች ለፖለቲካዊ ፍጆታ ፍትህ እያዛቡ ነው።

ሰለሞን ታደሰ (ሻምበል)

Boston, Massachusetts

 

1 Comment

  1. የአቶ ሊላይ ቃለ መጠየቅ እውነትን ያዘለ እንጂ ከሚያልፍ ወንዝ የተቀዳ አለመሆኑን የሚያመላክቱ ተጨማሪ ሌሎች መረጃዎች አሉ። በመሰረቱ በድርጅት ምስጢር ጠባቂነት ትብታብ እውነቱን ህዝብ እንዳያውቅ ታፍነውና ወደው ዝም ብለው አፈር ከለበሱ ይልቅ የሚያውቁትን ነገር በሚስጢርም ሆነ በግልጽ እንደ አቶ ሊላይ መናገሩ ለትውልድ ጠቃሚ ይመስለኛል። አቶ ሊላይ ወያኔ ልታስገድለው ስትል አምልጦ ለደርግ እጅን ከሰጠ በህዋላ በሂልተን ሆቴል የወያኔ የመረጃ መረብ ሰላይ እንደነበር መናገሩ የሚያጠራጥር አይደለም። ደም አፍሳሹ ስብሃት ነጋ እኮ በአንድ ትልቅ ባለስልጣን ቤት ዘበኛና አትክልተኛ ሆኖ ይሰራ ነበር። ሻቢያና ወያኔ እስከ መንግስቱ ቢሮ ድረስ የስለላ ሰዎች እንደነበሯቸው ግልጽ ነው። ወያኔ ገድሎ ገዳዪን መግደልም ከበረሃ ጀምሮ የተካነበት ስልቱ ነው። የጄ/ል ሃይሎም፤ የስለላ መረብ ሰራተኛው አቶ ክንፈ ከአሜሪካ በአስቸኳይ ተጠርቶ መገደል፤ የእውቁ ከያኔ ኢያሱ በርሄና ሌሎች በአዲስ አበባ በትግራይ በጎንደር በሌሎችም የሃገሪቱ ክፍል የተረሸኑ እልፍ ናቸው። ደርግ በትግራይ ህዝብ ላይ ግፍ ሰርቶ ገለ መሌ የሚሉት እነዚህ ሃይሎች ደርግ ከገደለው ይልቅ ራሳቸው የገደሉት የትግራይ ተወላጅ ቁጥር ይበዛል። ደርግ ገዳይ እንደነበር ማንም ያውቃል። ግን ለሚያመልከው ባህር ተሻግሮ የመጣ ርእዪተ ዓለም አሜን ብሎ ሰው እካደረ ድረስ ደርግ ዘርና ቋንቋው ግድ አይሰጠውም ነበር። በብሄር የተቃመሰቱ ሻቢያና ወያኔ ዛሬ ሃገሪቱን ሁሉ በዚሁ የወረርሽኝ በሽታ አስለክፈው አሁንም በእርጅና ዘመናቸው ክፋትን እንደጋቱና እንዳስጋቱ ይኖራሉ።
    አቶ ሊላይ የወያኔ ጥይት ሳይበላቸው የሚያውቁትን ሁሉ በማሰባሰብና ካለፉ ጓዶቻቸው ጋር በመነጋገር ከትግል እስከ አሁን ያለውን በመጽሃፍ መልክ ቢያቀርቡልን መልካም ይመስለኛል። የአቶ ሊላይን ሃሳብ የማይጋራ ማንም ቢሆን መብቱ ነው። እኔ ግን የሚያውቁትን ሳይደብቁ ቢነግሩን መጪው ትውልድ ከተሰራውና እየተሰራ ካለው ስህተት ይማራል የሚል እምነት አለኝ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.