አባ ሻውል* በሸገር (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

`አባ ሻውል አሥመራ ውስጥ ያለ ጌቶ ነው። ቃሉና ተግባሩ በአውሮፓ አይሁዳውያን ይታጎሩባቸው ከነበሩ ተልካሻ ሰፈሮች የመነጨ ቢሆንም ቃሉም ተግባሩም የብዙ የምእራብ ከተሞች ገጽታ ሆኗል። ጌቶ ማለት ብዙ ሰው እንደሚያውቀው አንድ ከተማ ውስጥ እጅግ የተጨናነቀ እና በጣም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች የሚኖሩበት የእውነተኛ ጭቆና መገለጫ፣ ደሃ ደሃን ወልዶ ከድህነቱ ሳይወጣ የበለጠ እየደኸየ እንዲኖር ተለይቶ እንዲቀመጥበት የተከለለ የከተማ ክፍል ነው። አስፈላጊ የመሠረተ ልማት የሚጎድለው ነው። አብዛኛው የኤርትራ ሰው ግንባታ፣ የጸዳና የተብለጨለጨ ነገር በጣም ይወዳል። ታድያ ጣልያን ኤርትራን በቅኝ ግዛት ረግጦ ሲገዛ የዘላለሜ ብሎ ያሰባትን የራስ አሉላን ከተማ አሥመራን አብረቅርቆና አሳምሮ ሲገነባት ብዙ ኤርትራውያን ለአምልኮ በሚጠጋ ማንቆለጳጰስ ተጠምደው ነበር። በዚያው ልክ በነጻነት ራሳችን የሠራናት እድሞ (ሀድሞ = በኤርትራና በትግራይ የተለመደ የድንጋይ ካብ፣ ወይም የእንጨት ጎጆ/ ወይም ፎቅ ቤት) ትሻለናለች የሚሉ ነበሩ። እነዚህ ነጻነት ወዳዶች በየገበያው እየተሰቀሉ ለጣልያን ሥልጣኔ ምስክር ተደርገዋል። የሟቾቹ ተቃውሞ አሥመራ ለምን አማረባት ብለው ሳይሆን ይቺን የሚያሳምራትን ሃገር እኛ በባርነት ብቻ እንድንኖርባት ነው እያዘጋጃት ያለችው እና በገዛ ሀገራችን ባሪያ ከምንሆን የፈለገው ይቅር ብለው ነበር። የሆነ ሆኖ ያሉትም አልቀረም አሥመራ ተገንብታ ሳታልቅ አዋጆች ወጡና አንድ ኤርትራዊ በዋና ጎዳናዎቿ ላይ ትውር እንዳይል ተደረገ። በመኖሪያ ሠፈርነትም ለኤርትራውያን የአባሻውል ጌቶ ብቻ ነበር በአሥመራ የተፈቀደላቸው። በዘመኑ በሐማሴን አባ ሻውል የሚሉ ዘፈኖች የበዙትም በሐዘን በደስታ የኖሩባትን ይቺን ሰፈር በማስታወስ የተቀነቀኑ ዜማዎች ስለነበሩ ነው።

Aba Shawel Asmera Eriteria
አባ ሻውል*

ያዲሳባን ደሃ ከመሃል እያወጡ ወደ ዳር መግፋት በመለስ ዜናዊ የተጀመረ ሥራ ነው። ይህ እነመለስ ከከተማው እምብርት ያባረሩት ደሃ ደግሞ ባዲስ አበባ ዳርቻዎች እንዳቅሙ ጎጆ ቀልሶ ሲቀመጥ እነ ታከለ በካልቾ ይጠልዙታል። ሀገሬ ነው ብሎ ተሻግሮ ኦሮሚያ ውስጥ ቤት ሠርቶ ሲኖር ደግሞ የሲዖሉ ብርጌድ ጠይባ ሃሰንን እና ኩባንያዋን ጣለበት። በነገራችን ላይ ይህ ተፈናቃይ አማራ ነው ክርስትያን ነው ምንምን የሚባለው ፉገራ ነው። እስላምና ክርስትያን ያሉበት በዘውግ እና ብሔርም የተደባለቀ ነው። እነ ጠይባ “አማራ” ብለው ከጣፎ ያፈናቀሏቸው ብዙ ሙስሊሞች ኦነግ ሰሜን ኦሮሚያ እያለ ከሚያላግጥባት ከወሎ የመጡ ናቸው። መሄጃ ከማጣታቸው የተነሳ እነዚህ ሙስሊሞች በፖሊስ እስኪባረሩ ድረስ በቤተክርስትያን ተጠልለው ነበር። ለነዚህ ቤተሰቦች እርዳታ የሰጡ የጣፎ አካባቢ ኦሮሞ ቤተሰቦች ዱላና ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል። አሳዛኝና አስቂኝ ምጸት።

እና “አባ ሻውል”ም ከተዉልህ እድለኛ ነህ። ያዲስ አበባ ደሃ ሆይ። በነገራችን ላይ ደሃ ሲባል ድሮ በምታስቡት ደረጃ አይደለም ድህነት ወይም ሃብታምነት። ከባንክ ያለ ማስያዣ መቶ ሚሊዮኖች ተበደሩ የሚባሉት ሰዎች፣ መሬት በሄክታር ወስደው ሸጡ የሚባሉት ሰዎች ባሉበት በደርግ ዘመን የምናውቀው አዲስ አበቤ ሁሉም፣ አዎ ሁሉም መናጢ ደሃ ነው ማለት ነው። ቤትም ያለው፣ መኪናም ያለው፣ ሥራም ያለው፣ ሱቅም ያለው ሳይቀር። ነገ ከአረቡ እና ከፈረንጁ ሌላ እጅግ ውድ የሆነውን ኑሮ ተቋቁመው በአዲስ አበባ መኖር የሚችሉት የፊተኞቹ ብቻ ናቸው።  ሌላው ሁሉ የነገዋ አዲስ አበባ ውስጥ ለመኖር ፈጽሞ የማይችል፣ ያለውን ጥሪት ሸጦ ለውጦ ለመውጣት የሚገደድ ነው። የት ይሄዳል ነው ጥያቄው።

አዲስ አበቤ አባ ሻውል ትኖረዋለች ወይ

መኖር አለባት፤ ምክንያቱም የትኛውም ከተማ የሠራተኞች ሠፈር ያስፈልገዋልና። የአዲስ አበባ እየጠበበች መሄድን ከግምት ካስገባነው ደግሞ አባ ሻውል ካላትም ኦሮሚያ ውስጥ ነው የሚሆነው ማለት ነው። በዚች በኦሮሚያ ውስጥ አሁን ያለው አዝማሚያ ከቀጠለ ነገ ኦሮሞ አይደለህም የተባለ ሰው “መኖር” ይችል ይሆን? ስለዚህ አባ ሻውል ካለችም በዘር የጸዳች በአዲስ አበባ ዳርቻ የምትገኝ የኦሮሞ ድሆች ከተማ ነው የምትሆነው።  ሌላው ሕዝብስ? ሌላውስ ያዲስ አበባ ደሃ? ደሃ ማለት መንገድ ላይ የሚለምን ብቻ አለመሆኑን ቅድም ከተጠቀሰው እያስታወሰን።

ሙሴያችን

ጽላት ካለህ አምጣ አለዚያ አትገግም
የወርቅ ጥጃ ተስፋን ይቅር አንፈልግም
ጽላት ካለህ አምጣ ዝለቅና ሲና
አንድ ሁለት ሦስት ብለን በሰላም ጎዳና
ከሰውም ካምላክም ተጉዘን በጤና
የምንደርስበት ካሰብናት መዲና።
በቀር
ለግዑዙ ጣዖት ላመለክነው አምና
ለግብጹ ባርነት ምልክት ነውና
ጥጃ አትስራልን በወርቅ ብልጽግና።

2012 ዓ.ም,

 

እና አባ ሻውልን እያሰቡ የጣልያን ብልጭልጭ ግንባታ ከሥልጣኔ ይልቅ የባርነታቸው ካስማ መሆኑ የሐማሴንን አርበኞች ቢያስተክዛቸው፣ ዛሬም የሸገር ሸሞንሟኔ ፕሮጄክቶች የት ነው መውደቂያዬ? ነገ ልጆቼ ይኖሩብሽ ይሆን? በሚል ሰቀቀን የታጀቡ ናቸውና ሁሉን አዲስ አበቤ አይደልሉም። ኤርትራ ውስጥ ከድንጋይ ካብ ይልቅ የተገነባው የፍትሕ ሥርዓት ቢሆን ኖሮ እውነተኛ ሥልጣኔን ፈጥሮ ዛሬ ጦሱ ትውልዶችን ተሻግሮ ልጆቿ ጥይት በጀርባቸው እየተተኮሰ ካገራቸው እየተሰደዱ ላረብ ቢላዋና ለቀይ ባሕር አሳ መጫወቻ ባልሆኑ ነበር። አሁንም በሀገራችን ፍትሕ ካልቀደመ፣ እርቅ ካልወረደ፣ የጥላቻ ስብከት ካልታረመ፣ ፊንፊኔ ላይ የጉለሌ ልጅ ባእድ የባሌ ልጅ ቤተኛ (ለምሳሌ ነው) የሚደረግበትን ሥርዓት በመዘርጋት የታጀቡ ብልጭልጭ ነገሮች እድሜም ይሁን ትርጉም አይኖራቸውም። ሻሸመኔን ያየህ ተቀጣ ነው።

 

*አባ ሻውል የትግራይ የጦር መኮንን የነበሩና በመጀመሪያ በስማቸው በተጠቀሰው የአሥመራ ክፍል የሰፈሩ ናቸው። አባ ሻውል የፈረስ ስማቸው ሳይሆን አይቀርም። የፈረስ ስማቸው ደግሞ በሸዋ የተለመደው ሺህ አውል ወይም ሻውል መሆኑ አባ ከሚለው የኦሮምኛ  ባላቤትነትን የሚያሳይ ጠቃሽ ጋር ተደምሮ የኢትዮጵያን ውሕድና ሕብረ ብሄራዊ ማንነት የሚያዘክር ሆኖ እናገኘዋለን። በአንድ ሰው የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የትግሬ ትውፊት የተገለጸበት ይመስላልና።

 
ድንጋይ
በድንጋይ ላይ ድንጋይ ድንጋይ መወርወሩ
ለሰላም ለፍትሕ መች ይሆናል በሩ?
ልብን ከአለትነት ከዚያ ከጠጣሩ
ወደ ሩህሩህ ሥጋ አካል መቀየሩ
ያ ነው ቁም ነገሩ::
2000 ዓ. ም.

 

1 Comment

  1. ዋናዉ ነገር ኤርትራዉያን ታሪካቸዉን በደምብ የሚዘግቡ ናቸዉ። ስለ አባሻዉል ጌቶነት የጻፉት ያለ አይመስለኝም። ጣልያን የአስመራ ነዋሪ ሊያሰፍራቸዉ አስቦ የነበረዉ ቦታ አክርያ ይባላል። በዛ ቦታ እስካሁን የአስካሪ መኖርያ ቅሪቶችም አሉ።
    የፈጠራ ታሪክ አይጠቅምም።
    አዲስ አበባ ኢንተርናሺናል ከተማ ናት። ባይሆን ጨምሮ ባትሰፋ፡ ነገር ግን ንጽህናና ዘመናዊነት ያስፈልጋታል። እነ ኒውዮርክም ስላም የነበሩ አከባቢዎችን አፍርሰዉ ነዉ እንዲህ የሆኑት።
    ከክፍለገር መጥተህ አዲስ አበባ በምታየዉ ምስቅልቅል ያለ ነገር መሰቃየት ያለ ነዉ። አዲስ አበባ ካለ ህዝብ ብዛትና መጨናነቅ ምን የሚታይ ጥሩ ነገር አላት? ከዉጭ የሚመጣ የኛን መጥፎ ገጽታ ገና ለገና ከአዲስ አበባ ያገኘዋል።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.