ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ የምታመጥቀው ሳተላይት በዓይነቱ የተለየ መሆኑ ተገለጸ

118346444 1734733333344674 4453605473738503391 nአዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው፤ በሚሸፍነው ቦታ፤ በተልዕኮውና በእድገት ዑደት ለየት የሚያደርጋትን ‹‹ ET SMART RSS ›› የተሰኘች ሳተላይት በ2013 ዓ.ም በመጀመሪያ አራት ወራት ውስጥ ልታመጥቅ መሆኑን የኢትዮጵያ እስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ሳተላይቷን ለማምጠቅ የሚያስችለው የግንባታ ሥራ መጠናቀቁን ገለጸ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ኢንስቲትዩቱ በ2013 ዓ.ም ከታኅሣሥ ወር በፊት ሁለተኛዋን በዓይነቷ የተለየች ሳተላይት ለማምጠቅ የግንባታ ሥራውን አጠናቋል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገራት ብዙ የኢኮኖሚና የልማት ችግራቸውን ለመፍታት ብዙ ሳተላይቶችን ማምጠቅ ይጠበቅባቸዋል። በዚህም መነሻነት ኢንስቲትዩቱ እየሰራ ይገኛል።
ሳተላይትን ማምጠቅ ሀብት ማከማቸት እንደሆነ የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በየጊዜው ሳተላይቶቹን የማሻሻል ተግባር ስለሚከናወን የሚገኘው መረጃም የጠራና ሰፊ ይሆናል። በዚህም መሠረት በቅርብ ወራት ውስጥ ለማምጠቅ ዝግጅት እየተደረገ ያለው ሳተላይት ከመጀመሪያዋ ሳተላይት ብዙ ለየት የሚያደርጓት ነገሮችን አካታለች። በዋናነትም በቴክኖሎጂው፤ በሚሸፍነው ቦታ፤ በተልዕኮውና በእድገት ዑደቷ የተለየች መሆኗን ጠቅሰዋል።
ሳተላይቷ ከመጀመሪያዋ ሳተላይት ሥራ በተጨማሪ በስፋት ከድርቅ ጋር ተያይዞ ትኩረት አድርጋ እንድትሰራ የታሰበ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከቀደመው ሳተላይት የተወሰዱ ልምዶችንም መተግበሪያ ትሆናለች ብለዋል።
ET SMART RSS የተሰኘችው ሳተላይት የክብደት መጠኗ አነስተኛ በመሆኑ ‹‹ናኖ›› በመባል በሳተላይት የክብደት መጠሪያ የምትገለጽ መሆኗን ጠቅሰው ክብደቷ ቀንሶ፣ የቴክኖሎጂን ጥራት በማምጣት የተሰራች መሆኗን ተናግረዋል። ክብደቷ 12 ኪሎግራም እንዲመዝን ሆኖ መሰራቷ ደግሞ ህዋ ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳያጋጥማትና የተሻለ መረጃ በመላክ አገርን የመጥቀም ዕድል እንዳላት ገልጸው፤ በተጨማሪም ETRSS-1 ሳተላይትን በመጠቀም ማግኘት የማይቻሉ መረጃዎችን ለማግኘት የምታስችል መሆኗን አብራርተዋል።
የቴክኖሎጂ ሥራ የብዙ አካላትን ወዳጅነትና በጋራ መስራትን የሚጠይቅ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ስለሆነም ከቻይና ጋር በወዳጅነት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል። ፕሮጀክቱ በኮሮና ምክንያት ትንሽ እንደዘገየ ተናግረው ሆኖም ግን የጋራ የምርምር ሥራ ከአጋር አካላቱ ጋር ብዙ ተለፍቶ ከግብ እንዲደርስ እየሰሩ ይገኛሉ። አሁንም የግንባታ ሥራው የተጠናቀቀው በዚሁ ርብርብ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ጊዜያት በተላከችው ሳተላይት ተቋማት ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ መረጃዎች በማግኘታቸው አገር ተጠቃሚ እየሆነች ነው ያሉት ዶክተር ሰለሞን፤ አሁንም በርከት ያሉና ጠንካራ መረጃዎች መሰብሰብ ተችሏል። ስለዚህም በቅርቡ መረጃዎቹን በመስጠት የተሻለ ሥራ የሚሰራ ይሆናል። አሁን በምትላከውም ሳተላይት የተሻለ መረጃ እንደሚገኝ ይታመናል።
በቀጣይ 15 ዓመታት አሥር ሳተላይቶች ለማምጠቅ እቅድ በመያዙ የመረጃ እጥረት ተፈቶ የአገርን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚቻል ተናግረዋል። ኢንስቲትዩቱም የሕዋ ሳይንስ ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ የጥናት እና ምርምር እንዲሁም ወደ ተግባር የሚቀየሩ ሥራዎችን ለመሥራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል።
ባለፈው ታኅሣሥ ወር ላይ የመጠቀችው ETRSS-1 ክብደቷ 72 ኪሎግራም ሲሆን፤ በቻይና ስድስት ሚሊዮን ዶላርና በኢትዮጵያ ሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ የተገነባች መሆኑ ይታወሳል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17/2012

1 Comment

  1. Ethiopia pays china to launch the space craft. Ethiopia doesn’t have the infrastructure and technology to launch rocket to the space.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.