ኢዜማ በአገራዊ ጉዳዮች ከየትኛውም ፓርቲ ጋር ለመስራት እንደሚፈልግ አስታወ

Azema አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአገራዊና የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋራ መስራት እንደሚፈልግ አስታወቀ፡፡ በአዲስ አበባ መሬት ወረራና በኮንዶሚኒየም ቤቶች አሰጣጥ ዙሪያ ያስጠናውን ጥናት በሚቀጥለው ሳምንት ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ገለጸ፡፡
ፓርቲው የአንድ አመት የሀገሪቱ የለውጥ ሂደትና ሊመሰረት ካስቀመጠው ግብ አንፃር የሄደበትን ርቀት ግምገማ የደረሰበትን ውጤት ጥናንት ለህዝብ ይፋ ባደረገበት ወቅት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ አንዷለም አራጌ እንደገለፁት፤ ፓርቲው ባደረገው ግምገማ በአገሪቱ እውነተኛ ዲሞክራሲ እውን እንዲሆንና እድገት መረጋገጥ እንዲቻል ከየትኛውም ፓርቲ ጋር በሚያግባቡ ጉዳዮች ዙሪያ መስራት እንደሚገባው ወስኗል።
ድርጅቱ ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉበትን ሁኔታ መገምገሙን አስታውሰው፣ ይሄንን መሰረት በማድረግ እንዴት እና በምን ሁኔታ በጋራ መስራት በሚቻልበት ዙሪያ የፓርቲው አመራሮችና አባላት ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል። በዋናነትም ከሁሉም ድርጅቶች ጋር በሀገር አንድነት፣ በዴሞክራሲ ተቋማት ግንባት እና በዜጎች በሰላም መኖር ላይ አብሮ መሥራት ይገባል የሚል መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
በተጨማሪም ኢዜማ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት ክፍት መሆኑን ግልጽ ማድረግ እንደሚገባ እና ተነሳሽነት ወስዶ ሊሠራበት እንደሚገባ ስምምነት መደረሱን አቶ አንዷለም ጠቁመው፤ ይህንንም ለማስፈጸም አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ መቋቋሙን አመልክተዋል።
የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በተደረገው ጥልቅ ግምገማ በፓርቲያችን ውስጥም ሆነ ፓርቲው ከሌሎች አካላት ጋር በሚኖረው መስተጋብር ሊነሱ የሚችሉ ግጭቶችን የመፍቻ መንገድ ምን ሊሆን እንደሚገባ ሰፊ ውይይት መደረጉን አመልክተዋል። በተለይም በፓርቲው ውስጥ የውይይት እና አብሮ የመሥራት ባህል ልምድ ሊዳብር እንደሚገባ መገለፁን ጠቁመዋል። በተጨማሪም ከሌሎች አካላት ጋር በሚኖር መስተጋብር ለሚፈጠሩ ግጭቶች የመፍትሄው መንገድ ውይይት እና በሕጋዊ መንገድ ብቻ ሊሆኑ እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።
እንደ አቶ የሽዋስ ማብራሪያ፤ በአጠቃላይ ፓርቲው ባደረገው የአንድ ዓመት ፍተሻ ያሉበትን ድክመቶች በመለየት እና ጠንካራ ጎኖቹን በማጎልበት፣ መርህ መሰረት አድርጎ ለሚደረገው ምርጫ በቂ ዝግጅት ለማድርግ ወስኗል። በሁሉም አደረጃጀቶች የፓርቲው እንቅስቃሴ በእውቀት ላይ ተመስርቶ የፖሊስ አማራጮችን በማቅረብ እና ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ መሥራት መሆን እንዳለበት በመረዳት ዜጎች በተለይ የኢዜማ አባላት በአካባቢያቸው ሠላም እና ደህንነት ከሁሉም አካላት ጋር ተባብረው ለመስራት ጥሪ አቅርቧል።
ፓርቲው ከዚህ ቀደሙ አካሄዱ በተለየ መልኩ በፖለቲካ ርዕዮተ አለም ልዩነት ካላቸው ፓርቲዎች ጋር በሚያስማሙ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመወያየትና በጋራ መስራት እንደሚሻ ገልፀው፤ ለዚህም አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቁን አመልክተዋል።
በፓርቲው የሴቶች ጉዳይ ተጠሪና የብሔራዊ ኮሚቴ አባል በበኩላቸው ፓርቲው ኢትዮጵያ የሁሉንም መብት የሚያከብር እና ለሁሉም እኩል ዕድል የሚሰጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በጠንካራ መደላድል ላይ እንዲመሰረት ገንቢ አስተዋፅዖ ማድረግን ግንባር ቀደም ዓላማው አድርጎ መመስረቱንና ይህም እውን እንዲሆን ባለፈው አንድ አመት ከፍተኛ ርብርብ ማድረጉን አስታውቀዋል።
በድርጅቱ የአንድ ዓመት ጉዞ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው ሰፊ ውይይት እና ግምገማ ያደረገው ከሁለት አቅጣጫ በመጡ ግፊቶች መሆናቸውን አስታውሰው ፣የመጀመሪያው የፓርቲውን ስትራቴጂክ ግብ ለማሳካት እና ሀገሪቱ ያለችበት ውስብስብ ችግሮች ለመቅረፍ በአመራሩ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች አመርቂ መሆናቸውን ለማወቅ ያስችል ዘንድ እንደሆነ አብራርተዋል።
በተጨማሪም ለዚህ ሰፊ ግምገማ መነሻ ምክንያት የሆነው በተለያየ ጊዜ በፓርቲው ደጋፊዎች፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች፣ ምሁራን እና የፖለቲካ ተንተኞች እንዲሁም በተፎካካሪ ፓርቲዎች የተሰጡትን አስተያየቶች መነሻ በማድርግ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩልም የፓርቲው አመራሮች በቀጣዩ ምርጫ፥ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ባሉ ግጭቶችና በሌሎችም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ፓርቲው ለምን በይፋ አቋሙን እንደማይገልፅና ገዢው ፓርቲ እንደማይጠይቅ በጋዜጠኞች ተጠይዋል።
አቶ የሽዋስ ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ፤ ፓርቲው በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ማዘኑን በይፋ ከመግለፅ ባለፈ ቦታው ድረስ በመሄድ ጥናት ማካሄዱንና ለሚመለከተው የመንግስት አካል ጥቃቱ በአስቸኳይ እንዲቆም መጠየቁን ተናግረዋል።
በተደረገው ጥናትም ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ዳግም ለማቋቋም በመንግስት እየተደረገ ያለው ጥረት አመርቂ አለመሆኑን እንዲሁም በጥቃቱ የተፈናቀሉ ዜጎች ህይወት አሁንም ስጋት ላይ መሆኑን ማረጋገጡን ገልጸዋል ።
አቶ አንዷአለም በበኩላቸው፣ ፓርቲው ምርጫውን በሚመለከት መንግስት ያቀረበውን አመራጭ ቢቀበልም የምርጫ ዝግጅቶችና ውይይቶች ከወዲሁ ያለመጀመሩ የሚያሳስበው መሆኑን ተናግረዋል። በአዲስ አበባ መሬት ወረራና በኮንዶሚኒየም ቤቶች አሰጣጥ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በሚመለከትም ፓርቲው የህዝብን ጥቆማ መሰረት አድርጎ ጥናት ማጥናቱን፤ ለሚመለከተው አካልም ምላሽ እንዲሰጠው መጠየቁን ተናግረዋል።
ይሁንና እስካሁን ድረስ ፓርቲው ምላሽ ያልተሰጠው በመሆኑ በሚቀጥለው ሳምንት የደረሰበትን ሁኔታና ጥናቱን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 16/2012
ማህሌት አብዱል
ተጨማሪ ያንብቡ:  ኮለኔል ጎሹ ወልዴ (ወታደር፤ምሁር፤ዲፕሎማት)

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.