ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ – ከአቶ አባተ ካሣ

abateከአቶ አባተ ካሣ፧ የፋይዳ ትንታኔ መጽሐፍ ደራሲ  08/20/2020

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በጎሣ ፖለቲካና በዜጋ ፖለቲካ ማህል ተከፍላ ትገኛለች። በእኔ እይታ የዜጋው ፖለቲካ አቋም እነደሚከተሉት ናቸው።

፩ኛ. የጎሣ/የዘውጌ ፖለቲካ የሚያስበው ለራሱ ጎሣ ብቻ የሆነ ከፋፋይ፣ አግላይና የጥላቻ ፖለቲካ ስለሆነ ለአገር-ወዳድ ዜጎች አይመቸንም።ኢትዮጵያዊነት ልዩ-ልዩ አሸብራቂ ልማዶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና እምነቶች ያሏቸው ማኅበረሰቦች ውህደት የፈጠረው የወል ማንነት መገለጫ የሆነ እኛነት ነው። ከአንድ ትውልድ ለዘለቀ ጊዜ እነኝህ ስብጥራዊ ማንነቶችን መሠረት ያደረጉ ልዩነቶች ሥር እንዲሰዱ ያደረገ አደገኛ ፖለቲካ በአገራችን ላይ ያስከተለውን መዘዝ በሃዘኔታ እያየን ነው። ኢትዮጵያችን የጋራ አሸብራቂ እሴቶቻችንን በየፈርጁ እያበለጸገች ዜጎቿ በእኩልነት የሚኖሩባትና የጋራ ተጠቃሚ የሚሆኑባት፣ ሁሉም በኩራት የእኔ የሚሏት ጠንካራ የጋራ አገር እንድትሆን ይህንን ሕዝብ ከፋፋይ መርዘኛ የጎሣ ፖለቲካ ማስወገድ ያስፈልጋል። የአገራዊ አንድነት ስሜት ዳግም እንዲያንሰራራ፣ ሕዝብ የተረጋጋ ሕይወት እንዲኖረውና ኢትዮጵያ ጠንካራ መሠረት እንዲኖራት በደንብ የታሰበበትና የመጠቀ ስትራተጂ ያስፈልጋታል። የጎሣ ፖለቲካ እንደ ዩጎዝላቪያ ሊበታትነን ስለሚችል እሱ ትምሕርት ይሁነን። ኢትዮጵያዊነት የዜግነት ማንነታችን ነው። ብዙ ሆነን አንድ የሚያደርገን ኢትዮጵያዊነታችን ነው። ለኢትዮጵያውያን የተለያዩ ማንነቶቻችን የጋራ ጌጣችን እና የፈጠራ ምንጫችን ሲሆኑ አንድነታችን ደግሞ ኃይላችን ነው።

፪ኛ. አሁን ያለውን ፌደሬሽን ያቋቋመ ሕገ-መንግሥት ጎሣነትን፣ቋንቋን፣ ልዩ ልዩ ባህሎቻችንን፣ እሴቶቻችንን በእኩልነት እንዲታዩና በአብሮነትና በኢትዮጵያዊነት እንድንኖር ከማበረታታት ይልቅ በሕዝባችን ማህል ‘የእርስ-በርስ ግጭቶችን’ የሚያቀጣጥል፣ መለያየትን እያስፋፋ ያለና ለዜጎች እውነተኛ እኩልነት፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ ለጋራ ብልጽግና እና ለአገራዊ አንድነት ጠንቅ በመሆኑ፣ የበለጠ አደጋ ከማስከተሉ በፊት በፍጥነት ሊሻሻል ወይም በሌላ ሊተካ ይገባል። ስለሆነም ከፈረሱ በፊት ጋሪው እንዳይሆን ከምርጫ በፊት አዲስ የኢትዮጵያ ርዕሰ-ሕግ ያስፈልገናል። አዲስ አበባም የማንኛውም የተናጠል ማኅበረሰብ የግል ይዞታ ሳትሆን የኢትዮጵያ ማለትም የ86 ስብጥር ማንነቶች ያሏቸው ማኅበረሰቦች እና የኗሪዎቿ ሁሉ ዋና ከተማ መሆኗ ሊታወቅ ይገባል፤ መሆንም አለባት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወያኔ: የነፃው ፕሬስ ፀር!

፫ኛ. የዜጋ ፖለቲካ ደጋፊዎች ሰንደቅ-ዓላማችን ምንም ዓይነት እዝልና ተደራቢ የሌለበት ንጹሁ ‘አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ነው።

፬ኛ. ኢትዮጵያዊ መሆንና የአንድ ጎሣ አባል መሆን የሚደጋገፉና አብረው የሚሄዱ መሆናቸው መታወቅ አለበት። ሆኖም ግን አገርን በጎሣ ማንነት መለያየት ለውጭ ጠላት መሣሪያ መሆን ነው። ኢትዮጵያ የዜጎች እኩልነት የተረጋገጠባት፣ ጠንካራና የበለጸገች አገር እንድትሆን ከማኅበራዊ አደረጃጀት ውጭ በማንነት ላይ የተመሠረቱ የፖለቲካ ድርጅቶች የማፊያ መንግሥት ከነበረው ከሕወሓት ጀምሮ በሕግ ሊፈርሱና ወደፊትም ያ ዓይነት ፖለቲካዊ አደረጃጀት እንዳይፈቀድ ማድረግ ያስፈልጋል።

፭ኛ. በአንድ አገር የሚኖሩ ዜጎች እርስ-በርሳቸው መግባባት የማይችሉ ከሆነ አብሮ ለማደግ ይቸገራሉ፣ ልዩነትም እየሰፋ ይሔዳል። ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ካለው ወገናቸው ጋር የሚግባቡበት የጋራ ቋንቋ ሊኖራቸው ይገባል። የአማርኛ ቋንቋ ከ600 ዓመት በላይ ዕድሜው ያደገው ከልዩ ልዩ ቋንቋዎች ቃላትን ወስዶ እንደሆነ እንገንዘብ። ስለሆነም፣ ለረጅም ዘመናት በይፋ አገራዊ የሥራ ቋንቋ ሆኖ ያገለገለውና የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ መግባቢያ የሆነው አማርኛ በዚህ በሽግግር ወቅት 110 ሚሊዮን ሕዝቧ በዚህ የጋራ እሴት ተጠቃሚ እንዲሆኑና በጽሑፍ ደረጃም ሁሉም ቋንቋዎቻችን በአፍሪቃ ብቸኛ በሆነው የጋራ ጥሪታችን በግዕዝ ፊደል እንዲሆኑ ማድረግ ሁላችንንም በአንዲት አገር ዜግነታችን ይበልጥ ስለሚያስተሳስረን ለጋራ እድገታችንና ብልጽግናችን አስፈላጊ ይሆናል።

፮ኛ. ከፋሽስታዊ አምባገነን (የጣሊያኑ)፣ ንጕሣዊ አምባገነን፣ ወታደራዊ አምባገነን፣ የሠርቶ-አደር አምባገነን፣ እንዲሁም ከዛሬው የአንድ አውራ-ፓርቲ አምባገነን ሥርዓት ካመጣብን ድህነትና ስቃይ ትምሕርት ቀስመን ወደ ዲሞክራሲያዊው መድበለ-ፓርቲ ስርዓት መሸጋገሪያ ወቅቱ አሁን መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል።የአንድ ብቸኛ ፓርቲ አገር አምባገነን እንጅ ዲሞክራሲ አትሆንም።

፯ኛ. ብዙ የተማረው ኢትዮጵያዊ የሚገኘውና የሚኖረው በውጭ አገር ስለሆነ፣ ለሁለቱም ለሀገርና ከአገር ውጭ ለሚኖረው ኢትዮጵያዊ (ለዲያስፖራ) የጋራ ጥቅም ሲባል እንደሌሎች ተራማጅ አገሮች ኢትዮጵያም በውጭ አገር ለሚገኙ ዜጎቿ የጥምር ዜግነት (dual citizenship) ሕግ የማውጣት ሥራ ትኩረት ልትሰጥ ይገባል። አገራችን በሁሉም ረገድ እንድትሻሻልና በቴክኖሎጂ እንድታድግ የሰው ካፒታልን ፋይዳ ሊጨምር የሚችልና እሱንም ማዕከል ያደረገ እውቀት-መር የሆነ የአቅም ግንባታ መርኅ ቢኖር ጠቀሜታው ከፍተኛ ስለሆነ፣ በውጭ ለሚገኙ (ለዲያስፖራ) ኢትዮጵያዊያን ትክክለኛውን ዓይነት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ አስፈላጊ ይሆናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሀሳብን አወላግዶ ትርጉም መስጠት ከሀሳብ ነጻነት ሊመደብ አይገባም (ሰመረ አለሙ)

፰ኛ. የአሳብ ልዕልና ለአገር ኢኮኖሚ ግንባታ የተሻለው አማራጭ ስለሆነ ለሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች እኩልነትን የሚሰጥ ዜጋ-ተኮር ሥርዓትን ማወጅ፣ በአሳብ ልዕልና ብቻ መወዳደር እንጅ በጐሣ ማንነት እና በሐይማኖት ላይ ተመርኩዞ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማቋቋም በሕግ መከልከል ይኖርበታል።ለዚህ መድኃኒቱ ሕገ-መንግሥቱን በመሻሻል የጎሣን ፖለቲካ በሕግ ማስወገድ ነው።

፱ኛ. ኢትዮጵያ የሚገባትን ያህል አላደገችም። ምክንያቱም አርቆ አስተዋይነት፣ ብልህነት፣ ቆራጥነት እና ሆደ-ሰፊነትን የተላበሰ አመራር ስለሌላት ነው። ይህም ድህነትን ከአመራር ግድፈት የመነጨ ችግር ያደርገዋል፣ ምክንያቱም የአመራር ብቃት ዋጋ አለውና። ኢትዮጵያ አሁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿ እየተራቡ የሚገኙባት የኢኮኖሚ ስንኩል አገር የሆነችው በሕዝቧ ድክመት ሳይሆን በመሪዎቿ ውድቀት ነው። በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው የሁላችንም ችግር ከሆነው ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መታደግን ነው።

፲ኛ. ኢትዮጵያን ከውስጥ እና ከውጭ ጠላቶቿ ለመታደግ የመተባበሪያው ጊዜ አሁን ነው። ስለሆነም፣ ለቀጣዩ ነፃ እና ፍትኀዊ ምርጫ በሚደረገው ዝግጅት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያንን የተንዛዛ ቁጥራቸውን አንዳስፈላጊነቱ በመቀነስ አሸናፊ በሚሆኑበት ተባብሮ በመሥራት አማራጭን ለዜጎች የሚያቀርብ የፓርቲ መርኃ-ግብር ወይም ማኒፌስቶ በማዘጋጀት በትክክለኛው የታሪክ መስመር ላይ እንዲቆሙና ለውጥ እንዲያመጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

“ሁሉም ለአንድ ኢትዮጵያ፣ አንድ ኢትዮጵያ ለሁሉም”

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.