ኢትዮጵያዊነት ህብረብሄራዊ አሃዳዊነት ነው – አባዊርቱ ነኝ

ኢትዮጵያዊነት ህብረብሄራዊ አሃዳዊነት ነው
ተነሣ ተራመድ ለሀገር ብልፅግና!!!

እንዳሁን ዘመን የአፍላ ዘመኔን በቁጭት ያስታወሰኝ የለም።

ethiopian flag
የጠፋው
የተበላሸው
የተደበቀው
የዋለለው
የደከመው እየሞትንም ቢሆን ኢትዮጵያዊነት እያበበ ነው – ደስ ይበለን!
በአንፃሩ “የፖለቲካ እሥረኞቻችን ይፈቱልን” የምትሉ ወገኖች አስተውሉ። ወቅቱ ወንጀለኛን በፖለቲካ እስረኝነት ክራቫት የምናሳምርበት አይደለምና። ይብቃ በዚህ ትውልድ የፖለቲካ ደላላነት። ይቆጫችሁ የህዝባችን ድህነትና ኑሮ። የእንጦጦን ዳገት ይዛችሁ ወደ ሰላሌ መውጫ ኬላው ሳትደርሱ፣ ቁልቁል በጀርባቸው የቋጥኝ ያክል ክበደትን እንጨት ጭነው የሚወረወሩትን ወገኖች አስቡ። እስከመቼ?  ያንገበግባል። ትላንትና አንዲት ሴና  የተባለች “የዖሮሞ ውርስና ቅርስ ” ማህበር ሊቀመንበር በቪኦኤ ሰምቼ ህመሜን አብሶብኛል። የፓለቲካ እስረኞቻችን የምትላቸው የበቀለንና ጁዋርን አይነት በስመ ዖሮሞ በተግባር ቢላሽ የሆኑ የህውሀትን ጋሻጃግሬዎች መሆናቸው ነው። በሷ አተያይ እነዛ እንጨት ተሸካሚ የሸዋ ዖሮሞ አይነቶች የምትፋለምላቸው ዖሮሞዎች አይነቶች አይደሉም። ትውልድ ሞቶብናል የምለው ለዚህም ነው። ለዚች ልጃችን የዖሮሞ ጠላቶች ባለነፍጦች ብላም ያው አልሸሹም ዞር አሉ አይነት ገላልጣለች። ሀያ ምናምን አመታት አሜሪካ ለኖረ የዖሮሞ ሆነ የሌላው ኢትዮጵያዊ ወገን ዋና ጠላት መሆን የነበረበት ድንቁርና፣ ድህነት፣ ስደት፣ እርዛትና ሁዋላቀርነት መሆናቸውን በተረዳች ነበር – ብዙ ሥራ ይጠብቀናል ወገኖች።
እስቲ ይህን እንደ አባጨጓሬ የተጠየፉትን አሃዳዊነት እንመልከተው ወገኖች። በዛሬ ዘመን ማንም እንኳን ፊደል የቆጠረ ቀርቶ ሞባይል በየጎጆው ያስገባው ገበሬ እንደሚረዳው አሃዳዊነት ሲባል የጥንቱ የንጉሳዊ አስተዳደር እንዳልሆነ አይጠፋውም። ወይም በምንም ተአምር የአንድ ጎሣ የበላይነት እንደ ዘመነ ወያኔ ሊሆን አይችልም መቼስ። የዘመኑ ከንቱዎች አሃዳዊነትን እንደ  ጭራቅ ማስፈራርያ አድርገው  የሚጠቀሙበት የዘመነ ጃንሆይን ለመነካካት ስለሆነ ዝርዝር ይፈልጋል።
ባለንበት ዘመን ለኔ እንደሚገባኝና ብዙው ወገን ይገባዋል ብዬም ተስፋ እንደማደርገው የብሄራትን አሃዳዊነትን ነው አሃዳዊ ሲባል። ኢትዮጵያ በብዙ ንኡሳን ብሄራት ማጠራቀሚያ ገንዳነት የምትመሰል ይመስለኛል። በቁጥር በንፅፅር የበዙት ዖሮሞና አማራ እንኳ የብዙሀንነትን ማእረግ ለየግላቸው ማግኘትን አይችሉትም። በነፍስወከፍ ንኡሳን ናቸው። ብዙሀን ያስመሰላቸው ከነ ጋሞና ወላይታ ስለሚስተያዩ ነው። ይህ እንዲህ ከሆነ ኢትዮጵያ የየብሄራት melting pot መሆኗን ነው። እንደ ኢትዮጵያ ሀገረመንግስት ለመዝለቅና እስካሁንም በህይወት ለመቆየት የብሄራት አሃዳዊነት የግድ ነው። ይህ የብሄራት አሃዳዊነት በተለይም በውጭ ጠላቶች ጥቃት ወቅት እየገነነና እየበረታ ወደላይ ሲወጣ አገር ሰላምና ስትረጋጋ  ደግሞ በውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ አገሪቱ በመታመስ አሃዳዊነቱ የላላ ይመስላል። አክራሪዎቹና ፅልመቶቹ ሊሸውዱን ካልዳዱ በቀር አይን ያወጣውስ አሃዳዊነት በታሪካችን የነበረው በንጉሱ ወይም ደርግ ዘመን ሳይሆን በዘመነ ህወሃት ነው። እንዴት? የይስሙላ ተለጣፊ ፌዴራሌ ፈልፍሎ ከበላይ ከብሄርም አልፎ የአንድ ቤተሰብ አስተዳድር ስር ነበረች ኢትዮጵያ በረጅም ታሪኩዋ። ከዚህ በላይ አሃዳዊነት የትም አገር አልሰማሁም። የአቦይ ስብሀትና ተቀፅላዎቹ የ ሀያሰባት አመታት አሃዳዊ አስተዳደር። ይህን አሃዳዊነት ነው እነ በቀለ ገርባና ህዝቅኤል ገቢሣ ጎናቸው ሸጉጠው እየተፎጋገሩ ስለ አቢይ አህመድ የአሃዳዊነት አዝማምያ አፍ አለኝ ብለው የሚያወሩት። እኔን የሚያቃጥለኝ እንደብዙሀንነታችን የሰው ዝምታና እንዲህ በአደባባይ ዖሮሞ ልክ ውክልና የሰጣቸው ይመስል በነዚህ ደነዞች የተነሳ ሲሰደብ ሳይ ነው። ዝም ብላችሁ የምትሰሙና የምታነቡ ከልብ አዝንላችሁዋለሁ።
ውድ ወገኖች!
በፈረንጆቹ በዚህ አመት ኢትዮጵያ ከሺህ አመታት ፍዳ ጭንቅላቷን ቀና ያደረገችበት ስለመሆኑ ከግርጌ አሳያለሁና ተከታተሉኝማ። የሰሞኑ እልቂት ይሁን የባለፉት ሁለት አመታት የሆኑት ለምክንያት ነው። ይህንን  ሙስሊምና መላው ክርስትያን ወገኖቻችን  የዋቃፌታ አማኞችም ልብ ሳትሉ የቀራችሁ አይመስለኝም።
፩) የኮሮና ወደ አገራችን ብቅ ማለትና የምርጫው መራዘም – በበኩሌ ይህን ምርጫ ከጅምሩም ፈጥኖብኝ ስለነበረም ይተላለፍ እያልኩ ስማለድ ነበር። ባልጠበኩት መንገድ ኮሮናው መጣና ለመተላለፉ በቂ ምክንያት ሆነ። እስቲ አስቡት ይህ ባይሆን ኖሮና ባይተላለፍ ኖሮ፣ ሀ) ጁዋር እንዲህ እንዳነጠነጠ ወደ ምርጫው ገብተን ቢሆን ኖሮ፣ ለ) ህውሀት ከላይ ያዙኝ ልቀቁኝ እያለች ካዝናዋን እየደባበሰች ውስጥ ለውስጥ እንደምስጥ እየሰረሰረችን ለምርጫው በቅተን ቢሆን፣ ሐ)  ጭምብል ፌዴራሌዎች ከህውሀት መቀሌ ላይ ቡናና ውስኪ እየተቃመሱ ስለፌክ ፌዴራሊዝም እየዘፈኑብን እንዳለ ቢሆን ኖሮ፣ መ) የነ አክራሪ ሀይላት መቀሌ እየተመላለሱ ደጅ እየጠኑና በተዘዋዋሪም የቀድሞ ገዳዮቻችንን በተዘዋዋሪም ቢሆን ደጅ ሊያስጠኑን የነበረበት አጋጣሚ ውስጥ ምርጫው ተካሂዶ ቢሆን ኖሮ አገራችን እውን የትላንት በስቲያውን አንድነት ፓርክ ምረቃ እንዲህ ተረጋግተን ይተገበር ነበር?? ፈጣሪ ኢትዮጵያን አብዝቶ ይወዳታል የሚባለውም ለዚህ ይመስለኛል።
፪) የብሄራት አሃዳዊነትን ፍራቻ ዝምታን ወልዷል ባይ ነኝ
ከትላንት በስትያ ባወጣሁት መጣጥፍ ዝምታ ወርቅ አለመሆኑን በምክንያት አውስቼ ነበር። የዝምታው ዋናው መንስኤ የዚህ የብሄራት አሃዳዊነት ፍራቻ ሳይሆን አይቀርም ብዬ አስባለሁ። አንዳንዶች ኢትዮጵያ የምትባለው ስም እንደሚያማቸው እሙን ነው። ቁጥራቸው እጅግ አናሳ በመሆኑ ቦታ ሰጥተናቸው ለውይይትም ማቅረቡ ተገቢ አይመስለኝም እንጅ። ሆኖም የብሄራት አሃዳዊነትን እንደ አንድ ደሃ የአፍሪካ ሀገር መኖርን መቼስ  ያምኑበታል ለብቻው አሃዳዊነትን ይዘው ማስፈራርያ ያደርጉታል እንጅ ። ካሁን በሁዋላ እነዚህ የፖለቲካ ዋልጌዎች ስለአሃዳዊነት ሲቀባጥሩ ዲፌንሲፍ ከመሆን ስለ ብሄራት አሃዳዊነት ጥቅምና አብሮነት በዝርዝር መግለፅና አፍ ማስያዝ ይጠበቅብናል። ዬትኛው የአፍሪካ ይሁን ኤዥያ፣ ይሁን ላቲኑ ነው የብሄራት አሃዳዊነትን ያላስተናገደና እንደ ሀገር በእግሩ ያልቆመ? ለምንድነው በኢትዮጵያ ሲሆን ከቀልቡ የተጣላ ነፈዝ ምሁር ተብዬ ቃር ቃር የሚለውና የሀገረ መንግስት መገለጫ የሆነውን የብሄራት አሃዳዊነትን የምንሸሸው? ከ 66ቱ አብዮት በሁዋላ ማለት ከዘውድ አስተዳደር መገርሰስ በሁዋላ አሃዳዊነትን ልክ እንደ ዙፋን እምባ ጠባቂነት ስለሚታይ እየተሸሸ በዝምታ ወገን ተሸብቦ አገራችን ጫፍ ደረሰችብን።ዛሬን እንጋፈጠውና ዝምታችንን እንስበረው። ኢትዮጵያ የንኡሳን ብሄራት ጥርቅም እስከ ሆነች ድረስ የሰማንያ ምናምኑን ብሄራት ሁሉ አሃዳዊነት እንፈልጋለን። የነዚህ ብሄራት አሃዳዊነት ዋንኛው መሣርያ ደግሞ በሪጅናል ኦቶኖሚ ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም ነው።
፫) የብሄራት አሃዳዊነት  (Federation of nationalities) መተግበርያው ሪጅናል ዖቶኖሚ ነው።
ከላይ እንደገለፅኩት ኢትዮጵያ የብዙ ብሄራት አሃዳዊነት መገለጫ ከሆነች በውስጧ ያሉትን ብሄራት ወደ በጠቅላይ ግዛቶች ወይም ክፍለሀገሮች ከፍ ማድረግ። ልክ በንጉሱ ጊዜ እንደነበረው። መቼስ ከንጉሱ መውረድ በሁዋላ አዲስ የፈለቁ ብሄራት የሉብንምና ጥንትም የነበሩ ከሆነ አስተዳደሩን በሪጅናል ኦቶኖሚ (ጥንት ጠቅላይ የነበሩትን) መለየት። እነ ወልቃይትንና ራያን ለባለቤቶቹ መመለስ ግድ ነው። አለበለዚያ የሰው ቤት ዘርፎ (ያውም በአስገዳጅነት) ሰላም አይኖርም። የጥንት አባቶች ታሪክን የሚያውቁ ሳያሸልቡ ይህን ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ ወደፊት የሚያቃውሰንን በወያኔ ህልፈት ላይ መቋጨት ግድ ይሆናል። እውነት ብትመርም እውነት ናትና።  እናም ወደሪጅናል ኦቶኖሚው ስንመለስ፣
የዖሮምያ ኦቶኖመስ ሪጅን – አምቦ ዋናው ከተማ
የአማራው ኦቶኖመስ ሪጅን – ባህርዳር
የደቡብ ሪጅን (ከሲዳማ እስከ ሁሉም)
የምስራቅ ሪጅን (ሶማሌና አፋርና ሃራርጌ)
የሸገር ዲስትሪክት (ሸገርና አካባቢው ሰበታ፣ ሱሉልታ፣ እያለ) District of Sheger
የድሬዳዋና ሃረር ዲስትሪክት
የሰሜንና ምስራቅ ሸዋ ዲስትሪክት (ተጠሪነቱ ለ አማራው ኦቶኖመስ ሪጅን)
የደቡብና ምእራብ ሸዋ ዲስትሪክት (ተጠሪነቱ ለ ዖሮምያው ኦቶኖመስ ሪጅን)
እነዚህን ለማዋቀር ብዙ ድካም የማይፈልግ ነው። ያሉትን ለይቶ ማጠናከር ብቻ ይሆናል። አማርኛና አፋን ዖሮሞን የፌዴራል ልሣን ካደረግንና ቁቤን በረጅም ጊዜ እቅድ አጥፍተን በግእዝ ፊደላት ብንተካ አደለም ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን ብቻ ሳይሆን አህጉራዊ ብቃታችንን ማስመስከርያ ይሆናል። አንዳንድ ደካሞች የግእዝን ፊደል ዖሮሞ ሆኖ መጠቀምን ልክ እንደ ወንጀል ወይም የስልጣኔ ጉድለትን ያዩታል፣ ወይም ” የጠላት” ቋንቋ ያደርጉታል። የላቲኑን ፊደል “ቁቤ” በመሰኘት ልክ ኣብሮን እንደተፈጠረ ዖሮሞ ወገን በመቁጠር ዘመድ ያደርጉትና ቁቤውን እንደራሳቸው ፊደል በመቁጠር ይኩራሩበታል። መቼስ አንድ ትውልድ በቁቤ ተወልዶ በቁቤ ስለጎለመሰ በህውሀት መቃብር ላይ የኢትዮጵኛ ፊደላችንን ለአፋን ዖሮሞ መገለጫ ይዋል ይደር እንጅ ማድረጋችን አይቀርም። አማርኛና  አፋን ዖሮሞም የአፍሪካ አህጉራዊ ሌላው ቢቀር የክብር ቋንቋ ይሆናሉ ወደፊት  እንግሊዘኛና ፈረንሣይኛን መገልገያ አድርገው። ይህ ይሆናል ወገኖች ከጣርንበት እንደ ህዝብ – ቢያንስ ካልተገዳደልንበት። የአንዲት ናይጂርያዊ አክትረስ የቅርብ ጥረትን ልብ ይሏል በዚህ ጉዳይ።
፬) ተነሣ ተራመድ፣ ለሀገር ብልፅግና!
ይህ መዝሙር ከ 45 አመታት በፊት የያኔውን ወጣት አይምሮ ኮርኩሮ የገባና ወጣቱን ለእናት ሀገሩ ዘብ ያስቆመበት ነበር። የዛሬው የአቢይ እድሜ ያኔ የአዝማችነት ካልሆነ የያኔው ወጣት እጅግ በእድሜም ወጣት ነበር። ሆኖም የያኔው ወጣት አሃዝ የዛሬውን በኮሮና ብቻ ቤት ዩዋለውን ሀያ ስድስት ሚሊዮን ሲሶም አያክልም ነበር። እንደውም የኢትዮጵያው ጠቅላላው ህዝብ ቁጥር ዛሬ ቤት ከዋለው ወጣት ብዙም አይበልጥም ነበር የያኔው ። አስቡት ወገኖች። ይህን ትኩስ ሀይል በብቃት ሀርቨስት የሚያደርግ ብርቅዬ መሪ እኮ ነው ፈጣሪ የሰጠን። ከትህትናው እስከ ትውፊቱ፣ ከውጥኑ እስከ ጉልበቱ። የናንተን ባላውቅም ከዚህ የአንድነት ዘጋቢ ፊልም በሁዋላ ዶር አቢይ በእሣት የተፈተነ ድንቅ መሪ ነው። በበኩሌ እስትንፋስ ውስጤ እስካለ በቅንነት ሌላው ቢቀር በበጎነት አገሬን ለማገልገል ቃል እገባለሁ። ሲያጠፋና ሲያበላሽ እየመከርነውና አብረን በመስራት ብንተባበረው እቅዱ ሁሉ ከአገር ፍቅር ይመስላል ። ለምሳሌ  የቤተመንግስቱ ሲገርመኝ የወንጪውና ጎርጎራውን ፕላን ስሰማ ደግሞ በደስታ ተስፋ ያሰንቃል። እድል ሆኖ በዚህ አለም ላይ ብዙ ቦታ አይቻለሁ። ከደሴቶች እስከ ጭው ያለ በረሀ ያሉባቸውን፣ ከሜትሮፖሊስ እስከ ትናንሽ የአለም ከተሞች። ሁሌም እንደማንኛውም ለአገሩ ቅን እንደሚያስብ ዜጋ ” ወይኔ ይህ ላንጋኖ ላይ፣ ያ ወንጪ ላይ፣ ሆኖ ቢሆን” ብዬ እንዳልተመኘሁ በህይወት እያለሁ ይህ ድንቅ ሰውዬ ቤተመንግስቱን በወራት ቀይሮ በአይኔ  አሳየኝ። ያውም አገሪቱ በአራቱ ማእዘን በመከራ ማእበል ተወጣጥራ፣ የቅርብ ወንድም ያህል የሆነ የትግል ጓድ የጎሪጥ እያየ ወይም እያደባ።  እንግዲህ  የወደፊቱ በአንፃራዊ ሰላም ውስጥ የሚተገበረው ወንጪና ጎርጎራ ከቤተመንግስቱ በላይ ደምቀው በጉጉትና ተስፋ ከመጠበቅ የበለጠ ምንስ አዱኛ አለ?
ማጠቃለያ!
ወገኖች እጅ ለእጅ መያያዣው ወቅት አሁን ነው። እናንት የወያኔ አገልጋዮች በተለይም በሰሜን አሜሪካ ያላችሁ የአሉላ ሰለሞን ቢጤ ግብዞች! ገንዘቡም ያልቃል፣ ወዳጆቻችሁም በፈጣሪ ፍቃድ ዳግም ላይነሱ ማሸለባቸው አይቀርም ። ኢትዮጵያውያን አለም እንደተዘባበተብን አንቀራትም። አንገታችንን በፈጣሪና በዚህ ቅን አቢይና አጋር የስራ ባልደረቦቹ  ብሎም በሁሉም አገር ወዳዶች አንድነትና ትጋት ከፍ ማድረጋችን አይቀርም ።  ያኔ ለቫኬሺን ይሁን ለመከሸን ትግራይ ይሁን ማንኛውንም የኢትዮጵያ አፈር መርገጡ ሊቸግር ይችላል ህሊናው ካለ። አሉላ ሆንክ ብርሃን መስቀል እድሜአችሁ ገና ነው። ስለምን ህዝቡን ደም ታቃባላችሁ?  ድንገት የተረፈች ህሊና ካለች ብዬ እንጅ ነፍሰገዳይና አስገዳይ ውስጥ ይህ እንኳ አይታሰብም ።
በመጨረሻም ለጁዋርና ደጋፊዎቹ መልእክት አለኝ። ይህ የፓለቲሻናችን ይፈታ ዶርሢሣችሁን በጉያችሁ ያዙት። ምን ብትፈርጡና ብትጮሁ ጁዋር ፍርዱን ሳያገኝ ከዛች ቤት የሚያወጣው ምድራዊ የሽምግልና  ሀይል አይኖርም ። እስካሁንም የልኩን አለማግኘቱ ይቆጫል። ይልቅ እዚያው እንደተሞላቀቀ የሚያቅበጠብጠው የሰው ደም ይሁን የጫት አራራ ምናልባት የጫቱን እሳቤ ይደረግለት ዘንድ መጠየቁ አይከፋም። በተረፈ በፈለገ መስፈርት በቁጥርም ይሁን ጥራት የጁዋርን ትክክለኛ ፍርድ የሚሹ ዬትየለሌ ስለሆኑ የመንግስትን ልክ ባትሞክሩት ይሻላል። ይልቅ በሱ ምክንያት በፈሰሰው ደም ይሁን በጠፋው ንብረት ተመጣጣኝ ቅጣቱን ይቀበል ዘንድ ፍርዱ በአስቸኳይ ይበየንለት። ይህ “የናቴ መቀነት አሰናከለኝ” አይነት የፈጠራም ይሁን የምር የወህኒ ቤት ህመም አላማረኝም። ሀኪም አያለሁ ብሎ ከዚህ ቀደም በስውር የተማማሉበትን ኮድ መቀባበያ ስልት እንዳትሆን ብዬ እሰጋለሁ። አለም ያወቀለትን ጁዋርን አልን እንጅ ለኦቦ ለማም መልእክት አለኝ። ግድየለህም፣ የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳንስ አንተን ባለውለታውን ቀርቶ በቁም የቀበሩትን ህውሀቶችንም ይቅር ብሏልና ወደ አይምሮህ ተመልሰህ በጀመርከውና ባስለመድከን ሱስ ቀጥልበት እባክህ ። ያንተው የእናት መርዶን ያህል ነው ብዙዎቻችንን ያመመን። ስላንተ ቆፍጣናነት ምንስ ያላልነው ነበር ኦቦ ለሚቶ። ለሁሉም ሰላም ለአገራችንና ህዝባችን ይሁንልን ። አሜን!!
አባዊርቱ ነኝ

1 Comment

  1. You started out good but messed it up àt the end. Its not Abiy’s job to beautify it should be left to others like city hall. His job is to keep peace in the country, stop excution by his own tribe, ensure safety of people and their wealth, make sure there is harmony, make sure individual rights are respected, and the list goes on. Unfortunately your Abiy fails in all these areas of governace. He does not know what leadership is and keeps lying and denying what his eyes see. That is not a sign of a good leader and no Ethiopia does not have a leader period end of story. And yes he is much inferior to Atse Haileselassie like you said. You need to begin to look at him as a leader not a lover.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.