የልደቱ እና የመስመር ዳኛው ‘ወንጀል’ * – አሁንገና አለማየሁ

Lidetuልጅ ሆነን የእግር ኳስ ቡድን ነበረን። ቡድናችን የአንድ ትልቅ ብዙ ቡድኖችን ያቀፈ የሰፈሮች እግርኳስ ሊግ አባል ነበረ። እጅግ በጣም ብዙ ጊዜ ዋንጫ በልተናል። በተከታታይ ዋንጫ የመብላታችን ሚስጥር እጅግ ጎበዝ በረኛ እና ኮከብ የተሰኙ አጥቂዎች ስለነበሩን ብቻ አልነበረም። እንደኔ ዓይነት ቀሺሞችም ነበሩበትና። ይልቁንም ደጋግመን የማሸነፋችን ዋናው ምስጢር እጅግ በጣም አስገራሚ፣ ብልጥና ብልህ አምበል ስለነበረን ነው። ይህ አምበላችን ጠቅላላውን ሊግ ያደራጀው እሱ ነው። ከሁሉም ቡድኖች ገንዘብ ተዋጥቶ ለማልያና ለዳኞች የሚከፈለውን ሁሉ የሚያስተዳድረው እሱ ነው። የወዳጅነትና የምር ግጥሚያዎች መርሐ ግብር የሚያወጣው፣ ሥልጠናም የሚመራው ይኸው አምበል ነው። የዋንጫው ግጥሚያ እኛ ሰፈር የሚደረግ ሲሆን ሌሎቹን ግጥሚያዎች ግን እየተዘዋወርን ነበር የምናደርገው። ይሄ ሁሉ ሲሆን እድሜያችን ገና ከአሥራ ሁለት ዓመት በታች ነበረ።

ታድያ ዳኛና መስመር ዳኛ የሚሆኑትን በእድሜ የሚበልጡንን ጎረምሶች ከተዋጣው ገንዘብ ከፍሎ የሚቀጥራቸው አምበላችን ስለሆነ የኛ ቲም ሲጫወት ብዙ ጥፋት እያደረግን እሱ ሲያፈጥባቸው በአድልዎ ለኛ ይፈርዱልናል። ካልፈረዱ የዳኝነት ፈቃዳቸው ጨዋታው ሳያልቅ የሚሰረዝ መሆኑን ስለሚያውቁ ማለት ነው። እኛ በኦፍሳይድ ያገባነውን ጎል ኦፍሳይድ ብለው ያሻሩ የተባረሩ የመስመር ዳኞች ነበሩ። በተለይ አንድ በሪጎሬ እንድንሸነፍ ያደረገን የመስመር ዳኛ አይረሳኝም። ብዙውን ጊዜ ግን በአምበላችን “ተሰጥኦ” ምክንያት ድል በድል ሆነን በደስታ እንኖር ነበር። ከእለታት አንድ ቀን ዓለም ተገለበጠችብን። ጎረቤታችን የነበሩት የዚህ አምበላችን ቤተሰቦች ከኪራይ ቤት ወጥተው ቤት ሠርተው ከመንገድ ማዶ እና የኛ ቁልፍ ተቀናቃኝ ቡድን እምብርት ከሆነችው ሠፈር ገቡ። እርሱንም ልጆቹ ተሻምተው ወሰዱትና የዚያ ሰፈር ኳስ ቡድን አምበል ሆነ። አሁን የአድልዎው ዋና ተጠቂ ኃይለኛ ተፎካካሪያቸው የነበረው የኛ የእግር ኳስ ቡድን ሆኖ አረፈው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “መጠየቅ ማንን ይጎዳል? ማስተዋልስ ማንን ያሳፍራል?”

ወደ ፖለቲካችን ስመለስ የአቶ ልደቱ ወንጀል እንደኛ ሰፈሩ የመስመር ዳኛ “ኦፍሳይድ!” ብሎ መጮኹ ነው። እርግጥ ገና ግጥሚያው ሳይደረግ ሽልማቱ ለኛ ቡድን ተዘጋጅቶ፣ እንደምናሸንፍ እርግጠኞች ሆነን፣ ወላጆቻችንን ሁሉ ጋብዘን፣ ሌላ ዙር መዋጮ ሰብስበን ድግስ ሁሉ ደግሰን ባለንበት የመስመር ዳኛው ከሜዳው ውጭ ያለውን ሁናቴ ሳያገናዝብ ኦፍሳይድ ብሎ ሕገወጧን የ90ኛ ደቂቃ ጎላችንን በመሰረዝ ጨዋታው በአቻ እንዲወጣ እና በሪጎሬ እንድንለያይ ማድረጉ “ወቅታዊ” አልነበረም ተብሏል። ወቅታዊ ሆነም አልሆነ የመስመር ዳኛው በትክክል ሙያዊ ግዴታውን ተወጥቷል። ለርሱ የተረፈው ግን በአምበላችን ‘አምባገነናዊ” ውሳኔ ከመስመር ዳኝነት ሥራው መባረር ነው ።  የአቶ ልደቱም እጣ ይህን ይመስላል።

ብልጽግና 90ኛው ደቂቃ ላይ ሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረችውን 5 ቁጥር “ላስተርጉም” ብሎ ያገባው የሥልጣን ማራዘም ጎል “ኦፍ ሳይድ” ነውና ጎሉ ተሰርዞ ጨዋታው በሪጎሬ ማለቅ አለበት ስላሉ ነው አቶ ልደቱ የዘብጥያ ፍዳ የሚከፍሉት፡፡ መሰለኝ።  በፍርድ ሂደት ስለሆኑ በመሰለኝ እንሰረው። መቼም አቶ ልደቱ በሁለት ሽጉጥ መፈንቅለ መንግሥት ሲሞክሩ ወይም የኦሮሞና የአማራ ቄሮ ለአመጽ ሲያደራጁ ለማሰብ የሚመች ታሪክ የላቸውምና ነው።

*ነገሩን በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት የቀረበ ንጽጽር ቢሆንም አባቶች “ምሳሌ ዘየሐጽጽ” በሚሉት ይያዝልኝ።

 

1 Comment

  1. ሕዝብ እንዲጫረስ ቅስቀሳ ሲያደርግ እንጂ አንድም ሰላም ሲሰብክ አላየሁም ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.