የትግራይ እናቶች ካለፈው ታሪክ ሊማሩ ይገባል፣ እነዚህ ሰዎች የራሳቸውን ልጆች በውጪ እያኖሩ የደሃውን ልጅ ለጦርነት መቀስቀስ ተገቢ አይደለም

TPLFስልሳ ሺህ ልጆቿን የገበረች የትግራይ እናት ድጋሜ ሌላ ስልሳ ሺህ ልጆቿን እንድትገብር የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ ይገኛል፡፡ ገዳይና አስገዳይ አሁንም አሉ የሚሞተው የደሃው ልጅ ነው። ይህ ሊወገዝ ይገባል።
• የትግራይ ህዝብ ለህወሓት ተገዢ ሆኖ እንዲኖር ለማድረግ ሲባል አሁንም በድህነት እንዲማቅቅ፤ ከሶስት ሚሊዬን ህዝብ በላይ በሴፍቲኔት እርዳታ እንዲኖር ተገድዷል፡፡ ይህ የሆነውም አንድ ጥያቄ ወይም አመጽ የሚያነሳ ቢኖር በሴፍቲኔት ድጋፏ እንዲቀጣ ለማድረግ ነው፡፡
• አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ላለ ችግር ሁሉ መንስኤው ያኔ በ1997 እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የጠነሰሱት ሴራ ነው፡፡ ምክንያቱም ህወሓት የሴራ ድርጅት ነው፤ የተንኮል ድርጅት ነው፤
• አሁን ላይ ሆኜ ሳየው በጠቃላይ የተካሄዱት ሁሉም ጦርነቶች ስህተት ናቸው፡፡ በተለይ ከኢዲዩ ጋር ያደረግነው ጦርነት ምንም ምክንያት አልነበረውም፡፡ ዋናው ትልቁ ችግርም የድርጅቱ (ህወሓት) አፈጣጠር ነው፡፡
• በኢትዮጵያ ቀይ ሽብር በተፋፋመበት ወቅት በ1970 እና 71 ብዛት ያላቸው የትግራይ ልጆች ከአራቱም ማዕዘን ወደ በረሃ ፈሰሱ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 90 ከመቶው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ፣ ወይም የሃይስኩል ተማሪ፣ በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ትልልቅ ቦታ ላይ የሚሰሩ ነበሩ፡፡
• ወደ በረሃ ከወጡ ወጣቶች መካከል ባለ ምጡቅ አእምሮ የነበራቸው የአድዋ ልጆችም ነበሩበት፡፡ ሆኖም የህወሓት ቡድን በተለይ የስብሃት ኔትዎርክ ጽዳት በሚል ያንን በረሃ የመጣውን ምሑር ሁሉ የተለየ ሃሳብ አለው በሚል እስር ቤት አስገብቶ አንድም የወጣ ሰው የለም በሙሉ ጨረሳቸው፡፡ እንደወጡ ቀሩ፡፡
• ህወሓት ስልሳ ሺህ ታጋዮች ተሰውተዋል ይላል፡፡ ከዛ በላይ ግን ራሳቸው ገድለዋቸዋል፡፡ በጦርነት ላይ ከሞተው በላይ በህወሓት አመራሮች የተገደሉት ይበልጣሉ፡፡ ከደርግ፣ ከኢህአፓ፣ ከአዲዩን ጨምሮ በአምስቱ ግንባር ተዋግተን ከተሰዋብን ታጋይ በላይ፤ በህወሓት አመራሮች በተለይም በስብሃት ኔትዎርክ የተገደለው ታጋይ ይበልጣል፡፡
• ለኢትዮጵያ ህዝቦች መብቶች መከበር ዋጋ የከፈሉ፤ ለህወሓትም ለዚህ መብቃት አካላቸውን የገበሩ ስልሳ ሽህ ታጋዮች ዛሬ በየቦታው ተበትነው ቀርተዋል፡፡ በአዲስ አበባና በየአካባቢው የተበተኑ 40ሺ ታጋዮች ይገኛሉ፡፡ አስር ለማኞች ብታገኝ አምስቱ ወይ ስድስቱ የህወሓት ታጋይ ነበሩ ናቸው፡፡ በርካታ ታጋይ እህቶቻችን ደግሞ ስጋቸውን እየሸጡ ለመኖር ተገድደዋል፡፡
• በትግራይ ውስጥም ከ20 ሺህ በላይ ታጋዮች ተበትነውና በየጎዳናው ወድቀው ይገኛሉ፡፡ ከ100 ሺ በላይ እናቶች ፍጹም ድህነት ውስጥ ይገኛሉ፤ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አካል ጉዳተኞች ህክምና እንኳን አያገኙም፡፡ በክልሉ መኖር ያቃታቸው የሰማዕታት ልጆችም አገር ጥለው እየተሰደዱ በየመን፣ በሊቢያና በሌሎች አካባቢዎች በየባህሩ እየሰጠሙ ቀርተዋል፡፡
• የትግራይ ህዝብ የታገለው ለነጻነትና እኩልነት ቢሆንም፤ ታግሎ ያመጣው ግን ጭቆናና ባርነትን ነው፡፡ በትግራይ ህዝብ ላይ እየተሰራ ያለው ድራማም ቀላል አይደለም፡፡
• በኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት የፌዴራል ስርዓት አልነበራትም፡፡ በአንድ ቤተሰብ የዘር ሃረግ የሚመራ የአሃዳዊ ስርዓት ነበር የሰፈነባት፡፡ አሁን እየተሰራ ያለው ፌዴራሊዝምን ለማፍረስ ነው እየተባለ ያለውን በተመለከተም፤ መሆንም ያለበት የነበረውን የይስሙላ ፌዴራሊዝም አፍርሶ ትክክለኛ ፌዴራሊዝም መገንባት ነውና መፍረሱ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡
• የትግራይ ህዝብም ሆነ ወጣት እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝቦችና ወጣቶች፣ ጽንፈኞችና አክራሪዎች ዳር ይዘው በተነሱ ቁጥር አብሮ ከመነሳት ይልቅ የተሻለ አገር የሚፈጥሩበትን፤ የጠንካራ የኢኮኖሚ ባለቤት የሚሆኑበትን አቅጣጫ በጋራ መክረው በጋራ ሊሰሩ ይገባል የሚል መልዕክት አለኝ፡፡
* ከቀድሞው የህወሓት ነባር ታጋይ አቶ ሊላይ ኃይለማርያም ጋር አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ያደረገውን ቃለ ምልልስ ከሰሞኑ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል
በወንድወሰን ሽመልስ
ፎቶ ጸሃይ ንጉሴ

1 Comment

  1. አመድ መስለዋል ጨው ነዝቶባቸዋል መጠጡ ነው? የሰሩት ክፉ ተግባር እያቃጃቸው ነው? ገንዘቡን ያስቀመጡበት ክዷቸው ነው? ቋሚ ከዚህ ተማር።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.