“  ከተሞች የአንድ ጎሣ መኖሪያ ይሁኑ ማለት ፣ፀሐይ በምእራብ እንድትወጣ ማሥገደድ ነው    …” መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

Addis Ababa  “  ከተሞች የአንድ ጎሣ መኖሪያ ይሁኑ ማለት ፣ፀሐይ በምእራብ እንድትወጣ ማሥገደድ ነው    …” መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ  “ብዙሃኑን በሃሳብ ማጥመድ የሚቻለው፣ሥለተወሳሰቡ፣ማህበራዊ፣ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ወዘተ።አንሥቶ
በማብራራት ንቃተ ህሊናቸውን ከፍ ለማድረግ በመሞከር ወይም ሚዛናዊነትን እና  ኃቅን የተመረኮዙ ትንታኔዎችን
በማቅረብ ሣይሆን፣ ወቅታዊ ፍላጎታቸው ላይ ተመሥርቶ ሥሜታቸውን በመኮርኮር  ነው።”
ሂትለር ሥለፕሮፖጋንዳ የተናገረው
ምንጭ፣አዶልፍ ሂትለር የተባለ መፅሐፍ
ተርጓሚ፣ተድላ ዓለማየሁ

ከገሃዱ ዓለም እውነት በማፈንገጥ፣በፊደራሊዝም ሰበብ፣ፍፁም ፊደራሊዝምን በሚቃረን አሥተሳሰብ ተዘፍቀው እና
በሌለ የቀለምና የዘር ልዩነት ጥቁር የሆነውን ህዝብ  እያወናበዱ ለማያባራ ግጭት የሚዳርጉ ግለሰቦች ከተሞቻችንን
ሠላም ማሣጣታቸው ይታወቃል።እነዚህ የራሳቸው ድብቅ አጀንዳ ያላቸው፣ይባሥ ብለው፣   ከተሞች የአንድ ኃይማኖትና
ቋንቋ ተናጋሪ  ብቻ ይሁኑ በማለት ፣ሀገርን በማያባራ ትርምሥ ና ሽብር ውሥጥ ለመክተት፣ በገሃዱ ዓለም የሚሰራ
የፊልም እሥክሪብት በመፃፍ ፣ የክፍለ ዘመኑን ታላቅ የእብዶች ሲኒማ  የኢትዮጵያን ምድር እንደእሥክሪን ተጠቅመው
በሰኔ ወር 2012 ዓ/ም     ለዓለም ህዝብ  ማሣየታቸውን አንዘነጋም።
ልንዘነጋው ፈፅሞ በማንችለው  በዚህ ሰቅጣጭ ና ዘግናኝ አእምሮ በጎደላቸው ሰዎች ተከታታይ በሆነ ሐሰተኛ
ፕሮፖጋንዳ ተቀነባብሮ በገሃዱ ዓለም፣ የተሠራ ፊልም ፣ የማይዘልቅ ሥልጣነ መንግሥትን ለማግኘት፣ ሆኖም
ለዘለቄታው ሀገርን በማያባራ ትርምሥ ውሥጥ ለመዝፈቅ፣በገንዘብ ሀገርን የሸጡ አያሌ የአእምሮ ችግር
ያለባቸው፣የሤጣን ምርኮኞች  ተሣትፈዋል። በዚህ አሣፋሪ ሤጣናዊ ጋሃዳዊ ፊልም፣ የቀን  ቅዠታቸውን ለማሳካት
በቀቢፀ ተሥፋ የተባባሩ ፖለቲከኞችም ጤነኞች አልነበሩም። ይህ እኩይ ወይም ሆረር ፊልም፣ በዘረፋ ለመክበር
ለሚፈልጉ መድረክ ከማመቻመች ፣ የንፁሐን ዜጎችን ህይወትና ንብረት በሚሠቀጥጥ ሁኔታ ከማጥፋት በዘለለ ቆመንለታል
እያሉ ለሚሸረድዱት ህዝብ ያመጣለት ትሩፋት የለም።
ጎሣ ፣ቋንቋን እና ኃይማኖታቸውን መሣሪያ በማድረግ፣”በላም አለኝ በሰማይ …  “ቅሥቀሳቸው፣በከሰቱት
ሁከት ፣ሰው የሆነው፣ የዓለም ህዝብ አውግዟቸዋል። ዘር ና ኃይማኖትን መሠረት አድርገው ሰውን የሚያህል ክቡር
ፍጡር አጥፍተዋልና በዘር ማጥፋት ወንጀል ይከሰሱ አሰኛቸው እንጂ ፣እኩይ ድርጊታቸው  “ሰውን የሚያፈቅሩ፣ለሰው
ያላቸው መውደድ የሚያሥቀና እና ከፍቅራቸው ጥልቀት የተነሳ፣ሰው ለሆነው ወገናቸው ህይወት ቀጣይነት ሲሉ፣
መሥዋትን የከፈሉ “ሰማዕትት” ተብለው አልተመሠገኑም።
በኦሮሚያ ክልል እንዲፈፀም ያቀነባበሩት ሴራ እና የጭካኔ ተግባር” የሂትለር ደቀመዝሙር የኢንተር ሃምዌ
ወንድም ። የለየላቸው እብዶች!…” አሠኛቸው እንጂ ፣ቆመንለታል ባሉት ህዝብ እንኳን ተቀባይነት
አላሥገኘላቸውም።
ድርጊታቸው ተጀምሮ እሥኪጨረሥ የእብድ ሰው ተግባር ነበር ።ሲጀመር ፣በከተማ የሚኖር ሰው ከአንድ ፋብሪካ
እንደወጣ እቃ ተመሣሣይ አይደለም።በከተማ የሚኖር ዜጋ ከአራቱም ማዕዘን የመጣ ድብልቅ ህዝብ ነው።
ድብልቁን የከተማ ነዋሪ በኃይማኖቱ ፣በቋንቋው እና በጎሣው መከፋፈል አይቻልም።ይህ  ፈፅሞ በከተማ
ሊተገበር  የማይችል የእብድ ሃሳብ ነበር። ሰዎቹ ዓላማቸውን ፣በኃይል ና በነውረኛ ተግባር በሴራ ለማሳካት
መጣጣራቸው እብደታቸውን አጉልቶ የሚያሳይ ነው።
በኦሮምያ በተወሰኑ ከተሞች የተፈፀመው ነውረኛ ድርጊት በነዚህ ፣ፀሐይ በምእራብ እንድትወጣ እና በምሥራቅ
እንድትጠልቅ  ተሰብስበው በወሰኑ  ህልመኞች ፣ የእብደት ውሳኔ የተፈፀመ ነው።  ማሰብ የተሳናቸው የጥቂት “ሙቅ
አኛኪ ” እብዶች ውሳኔ ያሥከተለውን ውድመትና ዘግናኝ ጥፋት ኢትዮጵያ ለዘላለም አትረሳውም።
ኢትዮጵያ፣ይህንን እኩይ ድርጊት አትረሳውም።ታሪክም “በተቃወሰ አእምሮ ተነሳስቶ፣ አንድን ከተማ የአንድ
ኃይማኖት ና ጎሣ  ተናጋሪ መኖሪያ ከተማ ለማድረግ ማቀድ በራሱ፣በከተማው አንገት ላይ ሸምቀቆ አሥገብቶ ከተማውን
እንደማናቅ ይቆጠራል።”በማለት የድርጊቱን አውዳሚነት በጥቁር ቀለም ይመዘግበዋል።
ከላይ ለተጠቀሰው፣ በጥቁር ቀለም ለሚመዘገበው ታሪክ ጥቂት ማብራርያ ያሥፈልጋል።
ለምሳሌ  ጎሳ ና  ነገድን እንዲሁም ኃይማኖትን  ተገን በማድረግ  የእኔ ጎሣ  ና ኃይማኖት ተከታይ ብቻ
እዚህ ከተማ መኖር አለበት የሚሉ አሥቀድመው መሞታቸውን ያወጁ እና  በዘረኝነት እናሳድገዋለን ያሉትን ህዝብም
በቁም የቀበሩት እንደሆነ የተረዱት አይመሥለኝም።ከህዝቡ ጋር በዘላቂነት የሚኖሩትን ማለቴ እንደሆነ ይሰመርበት።
ቋሚ መኖሪያቸውን እነዛ ከተሞች ላይ አድርገው ሲያበቁ ፅንፈኛ(አክራሪ)ኃይማኖተኛ  ወይም ሌላ ኃይማኖት ጠል
በመሆን፣ የተሰጣቸውን የከተማውን ህዝብ  ፀጥታና ሠላም የመጠበቅ ኃላፊነት ከመጤፍ ባለመቁጠር ፣ሰው በኃይማኖቱ
እየተለየ ንብረቱ ሲቃጠል ና ሲወድም ፣እንደ ፊልም ቆመው በማየታቸው በቁማቸው መሞታቸውን አሥመሥክረዋል። ይህ
ነው እንግዲህ የራሥን ከተማ ማነቅ ።ያልኩት።
ትላንት በሻሸመኔ ፣በዴራ፣ በአርሲ ፣በአጋርፋ፣በአርሲ ሮቤ፣ በጅማ ከተማ ወዘተ። በተፈጠረው አሣፋሪ ድርጊት
ከሁሉ በላይ ማፈርና መፀፀት ያለባቸው የከተማዎቹን ኗሪዎች ሠላምና ፀጥታ ለማሥከበር ተገቢውን ሥልጠና ወሥደው
ቃለ መሐላ ፈፅመው የፀጥታ ማሥከበር ሥራ ላይ የተሠማሩት የፀጥታ ኃይሎች ናቸው።እናም በዚህ ድርጊታቸው
የራሳቸውን ከተማ ለመግደል ሸምቆውን በአንገቷ ማሥገባታቸውን ይመኑ።…
በዚህ አጋጣሚ የህዝብን ፀጥታና ሠላም ለማሥጠበቅ ሲሉ ከአበዱ ፅፈኛ ና ሽብርተኛ ኃይሎች ጋር ሲፋለሙ
የወደቁ ፖሊሦችና ሚሊሻዎች ክብር ይገባቸዋል። ቤተሰቦቻቸውም ከመንግሥትና ከህዝቡ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል።
እነዚህ ሰማእታት ከተማው የእነሱም ከተማ መሆኗን ተገንዝበው፣ከተማዋ ሥትወድም ከማየት ሞትን ሳይፈሩ
ፊትለፊት ከፅፈኞቹ ጋር መፋለማቸው  ጀግና እና ታላቅ ሰው ያሰኛቸዋል።
ከተሞች በተፈጥሯቸው ሁሉንም ኃይማኖት፣ቋንቋ፣ባህል ፣ወዘተ።የሚያሥተናግዱ እና አዋህደው የሚያኖሩ
በመሆናቸው እነዚህ ፖሊሶች መሥዕዋት የሆኑት በከተማው ውሥጥ ለሚኖሩት ድብልቅ ለሆኑት ህዝቦች እንጂ፣ለአንድ
ቋንቋ ተናጋሪ ና ለአንድ ኃይማኖት ብቻ አይደለም።እነዚህ መሥዋት የሆኑ ፖሊሶችና በህይወት ያሉ መሠሎቻቸው፣
የፀጥታ የሠላም አለኝታዎች፣ በአንድ ከተማ ውሥጥ ከጎዳና ተዳዳሪ እሥከ ከተማው ከንቲባ ድረሥ እንደሚኖር
የሚያውቁ እና ለእነዚህ ሁሉ ዜጎች ዘብ መቆም እንዳለባቸው የተገነዘቡ ና ህግን ለማሥከበር የቆሙ፣ የዜጎች ሁሉ
መመኪያ ናቸው።
እነዚህ ዘላለማዊ ክብር የሚገባቸው ፖሊሶች ጥቂት በመሆናቸው፣ በዚህ በቴክኖሎጂ ዓለም ተራቃ ፣እንደወንዝ
የሚፈሰውን ትውልድ  በየፈርጁ፣ለሥልጣኔዋ ቀጣይነት የበኩልን አሻር እንዲጥል ፣ዓለማቀፋዊ ትበበርን በምትሻበት
ዘመነኛ ወቅት፣ በእኛ ሀገር ውሥጥ በአንዳንድ ከተሞች ከእንሥሣ እንኳ የማይጠበቅ ዘግናኝ ድርጊት መፈፀሙ በእጅጉ
ያሳዝናል።በአንክሮ ሥናጤነው እኮ አሁን ዓለም ከምትገኝበት ሥልጣኔ አንፃር በሀገራችን የተፈፀመው ኃይማኖት እና
ቋንቋን መሠረት ያደረገ የጥፋት ተግባር ሀገራችንን ያሳፈረ ነው።እንኳን በአንድ ከተማ የሚኖሩ
የተዛመዱ፣የተዋለዱ፣እና ሀብትና ንብረት ያፈራ ሰዎች ይቅርና ዛሬ ሀገራት በኢኮኖሚ፣በፖለቲካና በማህበራዊ ጉዳይ
ካልተሳሰሩ ህልውናቸው አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ያውቃሉ።
በነገራችን ላይ እንኳን የእኛ ከተሞች ይቅርና በምንኖርበት ዓለም የሚኖሩ መንግሥታት ሁሉ፣ከዓለም ኃያላን
ጋራ ተባብረው የመኖር ግዴታ አለባቸው።”ለምን?” ቢሉ ፣  “የዛሬው ዓለም አኗኗር እንደ ሸማኔ ድር
የተሳሰረ፣እንደ ሸረሪት ድር የተቆላለፈ በመሆኑ ነው።” በመተሳሰብ መኖርን የሚመርጡት።ያልበለፀጉት ሀገራት
ለመበልፀግ  የበለፀጉትን ሀገራት ድጋፍና ትብብርን ይሻሉ።
ዓለም ዛሬ በኢኮኖሚ ፣በማህበራዊ ና በፖለታካዊ ጉዳዮች ተቆላልፋለች።ያለበለፀጉት ሀገራት የህዝባቸውን
ማህበራዊ አኗኗር ከፍ የሚያደርጉትም ሆነ ወደአዘቅት የሚከቱት ከሌሎች የበለፀጉ ሀገራት ጋር ባላቸው የኢኮኖሚ ና
የፖለቲካ ትብብር ከፍታ እና ዝቅታ አንፃር እንደሆነ ይታወቃል።…
የአንድ ያልበለፀገ ሀገር መንግሥት  ከበለፀጉት ሀገራት ጋር “ከፍተኛ ትብበር  አለው።” ማለት ፣ቤታቸውን
ቤቱ  አድርጎታል ማለት ነው።የእነሱ ቢሊየነሮች በሀገሩ ላይ እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው መሥራት ከቻሉ እና
ሀበታቸውን የበለጠ ማሳደግ ከቻሉ፣በተወሰነ ደረጃ ሀገሩን ለማልማት እገዛ አደረጉ ማለት ነው።በተቃራኒው በጥቂቱም
ቢሆን ለብዝበዛቸው እንቅፋት የሚሆን መንግሥት ከሆነ ወደእንጦረጦሱ ወይም  ወደአዘቅቱ እንዲወድቅ ቀን ከሌት…
ያሴሩበታል።
በአፍሪካ ዛሬ የበለፀጉት ሀገራት እየተገበሩት ያለው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጫዎታ ይኸው ነው።
ይህንን ፖለቲካዊ ጫዎታ ሰጥቶ መቀበል ይሉታል። በዛሬው የዓለም ፖለቲካ ጫዎታ ውሥጥ፣ ካልሰጠህ ማንም የራሱን
በነፃ አይሰጥህም።   የዓለም ባንክ እና ኢንተርናሽናል ሞኒተሪ ፈንድ” ግንባር ፈጥረው ለማደግ የሚፈልጉትን
ሀገራት በሚፈልጉት አቅጣጫ እንዲጎዙ የሚያደርጓቸው ፣”በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው።”ትንሽ ይሰጡሃል በብዙ ወለድ
ይከብሩብሃል።ወዳጄ ነፃ ሥጦታ ብሎ ነገር የለም።የረጅም ጊዜ ብድር እና የእፎይታ ጊዜ እንጂ።እናም እፍኝ ቆሎ
ይሠጡህና ቁና ሙሉ ያልተቆላ ገብሥ ይወሥዱብሃል። ይህንን ብዝበዛ ነው እነሱ ሰጥቶ መቀበል የሚሉን።ግን ምን
አማራጭ አለን? የእነሱ ብዝበዛ ከመንግሥትም ሆነ ከግለሰብ የሪል እሥቴት ከባንክ ከተቋራኘው የረዢም ዓመት
(የሃያና የሠላሳ ዓመት) የሥንጥቅ ወለድ ክፍያ ብዝበዛ በምንሥ ተለይቶ ነው፣እነሱን ብቻ በዝባዥ የምንላቸው።
በአጠቃላይ ህጋዊ ቢሆኑም ባንኮች ሲባሉ በሰው ገንዘብ ቁማር የሚጫወቱ ሥንጥቅ የሚያተርፉ ነጋዴዎች  አይደሉም
ወይ???እና ለምን የብሔር ሥም ይሰጣቸዋል?ለዛ ጎሳ በነፃ የሚሰጡት ብር አለ እንዴ? (ባንኮች ገንዘብህን እንጂ
ቋንቋህን አይቆጣጠሩም
የዓለም የአኗኗር እውነት ይኽ ከሆነ፣ጥቂት እብዶች ጎሣ፣ ቋንቋና ኃይማኖትን የሙጥኝ ብለው ለምን አጭርና ጣፋጭ
ህይወታችንን መራራና በሥቃይ የተሞላ ብቻ ለማድረግ ለምን ይጥራሉ?ለምን አሥተዳደራዊ ሥያሜን እንደ ቋንቋና ጎሣ
የበላይነት ይቆጥራሉ?ለምንሥ በክልል ሳቢያ እያንዳንዱ ከተማ፣ የእያንዳንዱ ቋንቋ እና ኃይማኖት መኖሪያ ብቻ
ይሁን እያሉ የእብድ ቅሥቀሳ ያደርጋሉ?
ከተሞች የአንድ ኃይማኖትና ቋንቋ ተናጋሪ  ብቻ ይሁኑ ብሎ አመፅን  ለማሥነሳት መቀሥቀሥ በራሱ እብደት ነው።
ፈፅሞ ሊሆን የማይችልን የእብድ ሰውን ዓላማ ለማሳካት አጉልና አውዳሚ ጥረትም እንደማድረግ ይቆጠራል።
ከተማ ፣የማህበራዊ ትሥሥር  የንግድ እንቅሥቃሴዎች መድረክ ነው። በከተማ ውሥጥ ተዋንያኑ በልዩ ልዩ የኑሮ ሁኔታ
የተሠማራው ከተሜው ብቻ አይደለም። ገጠሩም የከተማ ቱሩፋት ተቋዳሽ ነው። ያመረተውን ሸጦ፣ ከከተሜው
የሚያሥፈልገውን ይሸምታልና! በሚያውቀው ቋንቋ ተነጋግሮ ነው፣ሰጥቶ የሚቀበለው።
የራሴ የሚለው ቋንቋ ቢኖረውም፣የእርሱን ቋንቋ ከማያውቀው ጋር በጋራ መግባቢያው በአማርኛ ቋንቋ ይጠቀማል።
እሥካግባባው እና የሚፈልገውን እሥካሥገኘለት  ድረሥ በቋንቋው መናገሩ ክፋት የለውም።   ቋንቋ እንደፈረሥ
ነው።ያደርሥሃል እንጂ አይዋጋም። እናም ጠብህ ከሰውየው ነው ከፈረሱ??(ከሰውየው ጋር ፀብ ካለህ በጠረጴዛ ዙሪያ
ፍታ እንጂ በቋንቋ አትነግድ)ቋንቋ ተካፍለን እንድንበላ የሚያደርገን መግባብያ ነው።የምንረዳዳበት እንጂ
የምንተራረድበት አይደለም።ኃይማኖትም በፈጣሪ አምነን ከሞት በኋላ የምንኖርበትን ዘላለማዊ ህይወት የምናመቻችበት
እንጂ፣እንደ ሴጣን ሰው የምናርድበት አይደለም። (የምንከተለው ሴጣኒዝም -የሴጣን ኃይማኖት – ካልሆነ
በሥተቀር!)
ከአፍ እሥከአፍንጫችን ብቻ በማሰብ ለምን ቋንቋ አምላኪ ለምን እንሆናለን ? ከፈጣሪ የበለጠ ፈጣሪ ልሁን
ባይነተሥ ሴጣንነት አይደለም እንዴ!?
የቱንም ያህል አክራሪ፣ የቱንም ያህል ጎሠኛ፣ ብትሆን እንኳን ፣   ሳተወድ በግድ የምትፈልገውን ለመግዛት
ወይም ለህክምና አገልግሎት የምትጠላው ቋንቋ ተናጋሪ ዘንድ ልትሄድ እና በምትጠላው ቋንቋ እንድትናገር እና
የህክምና  አገልግሎት እንድታገኝ የከተማ አፈጣጠር እና የኑሮ መሥተጋብር ያሥገድድሃል። (በሁሉም ከተማ  ታክሲው
፣ወፍጮ ቤቱ፣ዳቦ ቤቱ፣ቡቲክ ቤቱ፣ምግብ ቤቱ፣ወዘተ። የአንድ ጎሣና ኃይማኖት ተናጋሪ ሰው ብቻ  አይደለም።)
ከተማ በባህሪው በሰጥቶ መቀበል ላይ የተገነባ ነው። በንግድ እና በፋብሪካ እንቅሥቃሴ የተሞላ ነው።እናም
ሀብትና እውቀትን ይፈልጋል። ያንን ተፈላጊ ሀብትና እውቀት አንዱ ቋንቋ ተናጋሪ ሌላው ጋር ይዞ ይሄዳል።
በሀብቱና በእውቀቱ ንብረት ያፈራል።ከዛ አካባቢ ተወላጅ ጋር በጋብቻ ይዛመዳል።ልጅ የወልዳል። ለልጁ ሀብቱን
አውርሶ ይሞታል።በዚህ ምሳሌ ከአራቱም ማዕዘን የመጣ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ በአሰላ፣ በበቆጂ፣ በአጋርፋ፣
በዲክሲስ ፣በሻሸመኔ፣በመቀሌ፣በሽሬ፣በአድዋ፣በመተከል፣በመቱ፣በበደሌ፣በጅማ፣በነቀምቴ፣በአንቦ፣በሆለታ፣በአዳማ፣በሐረር
፣በድሬ፣በጅግጅጋ፣በቀብሪደሃር ፣በጋቤላ ፣በቤንሻንጉል  ፣በአሣይታ፣በቦንጋ፣በአርባ ምንጭ፣ በአዋሳ፣ በጎንደር፣
በባህር ዳር፣በደሴ፣በመተማ ወዘተ። ይነሥም ይብዛ ንግድን ና ሥራን ብቻ መሠረት አድርጎ የመጣ፣ ሲጀመር የዛ
አካባቢ ያልሆነ ሰው አለ።
ይህንን ሰው አንዳንዶች መጤ ቢሉትም ፣ በበኩሌ ሁሉም ሰው መጤ ነው ባይ ነኝ። በአጭሩ እኛ ወደእዚች ምድር
ለአጭር ጊዜ ለመኖር የመጣን መጤዎች  ነን ። እናም ለዚች ምድር ሁላችንም መጤዎች እንጂ ከምድሪቱ የበቀልን
የተፈጥሮ እፅዋቶች አይደለንም። ከዛሬ ሦሥት ሺ ዘመን  በፊት ይቅርና ከአምሥት መቶ አመት በፊት  የእኛ ወላጆች
የት እንደሚኖሩ አናውቅም።እናም “ይሄ የእኔ መሬት ነው።” ብለን በሙሉ አፋችን ለመናገር አንችልም።እንዲህም ሥል
በምንኖርበት ሀገር የመንግሥት ሥርዓት መሠረት ግብር የምንከፍልበት ለጊዜው የእኔ የምንለው መሬት የለንም ማለቴ
አይደለም። …ዓለም በዝንጋታ ገመድ እየጎተተች ወደመቃብር እሥክትወሥደን ድረሥ  የእኔ የምንለው ቁሥ እና
ጥሪት እንዳለን ግን ይታወቃል።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.