ኢትዮጵያ ነፍሰ ገዳዮች እንጂ ንጹሕ ፖለቲከኞች የላትም

Oromo 2 ኢትዮጵያ ነፍሰ ገዳዮች እንጂ ንጹሕ ፖለቲከኞች የላትምበገ/ክርስቶስ ዓባይ
ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ/ም

በውጭ ዓለም ያሉ ፖለቲከኞች ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ማለትም ከ17-18 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ስብሰባዎች እየተገኙ፤ ጥያቄ በመጠየቅ፤ በምርጫ ጊዜም የተለያዩ በራሪ ወረቀቶችና የቅስቀሳ ጽሑፎችን ለብዙኃኑ ሕዝብ በማደል ድርጅታቸውን እያስተዋወቁ ይሳተፋሉ። ከዚያም በየጊዜው በሚያደርጉት እንቅስቃሴና ከሕዝብ ጋር ያላቸው ግንኙነት እየጎላ ስለሚሔድ፤ በዕድሜያቸውም ሆነ በአእምሮአቸው እየተቡ ስለሚመጡ ቀስ በቀስ ከተራ ዓባልነት ወደ ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ይደርሳሉ። በመቀጠልም ያከናወኑትን የሥራ ውጤትና ከሕዝብ ጋር ያላቸውን ተሰሚነትና ክብር ከግምት ውስጥ በማስገባት ፓርቲያቸውን ወክለው ለወረዳ፤ለአውራጃ፤ ለክልል ወይም ለፌድራል ምርጫ እንዲወዳደሩ ይታጫሉ። እንዲህ ያሉ ፖለቲከኞች ዕድሜ ልካቸውን ያደጉበት ስለሆነ በተግባርም ሆነ በቲዮሪ ጥልቅ የሆነ ዕውቀትና ግንዛቤ ይዘው ያድጋሉ።

ከላይ እንደተጠቆመው ከ17-18 ዓመት ዕድሜ ጀምረው በፖለቲካ ዓባልነት ተሳታፊ ሆኑ ማለት እንግዲህ የ11ኛ ወይም የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች እያሉ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። ከዚህም የተነሳ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ወይንም ወደ ዩኒቨርስቲ ሲገቡ፤ እንደ ዝንባሌያቸው በፖለቲካል ሣይንስ፤ በኢኮኖሚክስ፤ በሕግ፤ በሕዝብ አስተዳደር፤ ወይንም ደግሞ በፋይናንስ መስክ በመማር ችሎታቸውን በየጊዜው ያዳብራሉ።

እንዲህ ያሉት ሰዎች የፖለቲካውን ሁኔታ ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉበት ስለሆነ ዓላማቸው፤ ለሕዝባቸው ፍትሐዊ አስተዳደርና ለአገር ዕድገት የሚጠቅም አግልግሎት ለማበርከት ብቁ ሆነው ለመገኘት በርትተው ይሠራሉ። የላቀና የመጠቀ ዕውቀት ከልምድ ጋር ሲያካብቱ የቆዩ በመሆኑም በራሥ መተማመን ያላቸው ናቸው።

ቀዳሚ ዓላማቸው፤ የመረጣቸውን ሕዝብ በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ስለሆነ ለሙስናና ለግል ጥቅም የቆሙ አይደሉም። እንደዚህ ያሉ የፖለቲካ ሰዎች በሠፊው ሕዝብ ታዋቂና ዝና ያላቸው በመሆኑ ራሳቸውን ከፖለቲካ ሲያገሉ እንኳ፤ ሳይውሉ ሳያድሩ ወዲያውኑ ያገኙት ከነበረው ደመወዝ ሦስት እጥፍ እየተከፈላቸው በግል ኩባንያዎች ሊቀጠሩ ይችላሉ።

በችሎታ እርከን በየጊዜው እያደጉ ለከፍተኛ ደረጃ ከበቁት ውስጥ ተጠቃሽ የሚሆኑት የወቅቱ የቻይና መሪ ሺ ዢንፒንግ ናቸው። የሺ ዢንፒንግ አባት የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ዓባልና ከፍተኛ ባለሥልጣንም ነበሩ፤ ነገር ግን በቻይና የባህል አብዮት ጊዜ በፓርቲው ውስጥ በነበረ ሽኩቻ ከኃላፊነት ተወግደዋል። ሺ ዢንፒንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ያገኙ ሲሆን የፖለቲካ ተሳትፎአቸውን ለማሳደግ ሲሉ ደግሞ ሕግ አጥንተው የዶክትሬት ዲግሪ አላቸው።

ከዚህ የምንረዳው ፖለቲከኛ ሁልጊዜ ተማሪ መሆኑን ነው። ሺ ዢንፒንግ በመጀመሪያ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ዓባል ለመሆን ማመልከቻ አስገቡ። ይሁን እንጂ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ጥያቄያቸውን ውድቅ አደረገባቸው። እርሳቸው ግን ከሚኖሩበት አካባቢ ጀምረው ያላቸውን ጊዜና ችሎታ በሕዝብ አገልግሎት ማዋላቸውን ቀጠሉ። ከትንሽ ጊዜ በኋላ እንደገና አመለከቱ፤ የኮሙኒስት ፓርቲውም ጥያቄያቸውን አልተቀበለውም። በዚህ ሁኔታ ለበርካታ ጊዜ ያህል ሳይሰለቹ የዓባልነት መጠየቂያ ፎርም እየሞሉ ቢልኩም ተቀባይነት ሳያገኙ ቀርተዋል።

እርሳቸው ግን ለሕዝብ የሚሰጡትን አገልግሎት በከፍተኛ ደረጃ አሳደጉ። ቀስ በቀስም በሚያደርጉት ድንቅ አስተዋጽዖና ተሳትፎ በአካባቢያቸው ሕዝብ ዘንድ የበለጠ እየታወቁና ዝናቸውም እየጎላ መጣ። ቀጥሎም ቀስ በቀስ የእርሳቸው ስም በሠፊው ሕዝብ ዘንድ በበጎ መወሳት ጀመረ። በዚህ ወቅት ያቀረቡት የፓርቲ ዓባልነት ማመልከቻ ፎርም ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀባይነት አገኘ። ከዚያም ሺ ዢንፒንግ ከቀበሌ ወደ ወረዳ ከዚያም ወደ አውራጃ ቀጥሎም ለክልል በመጨረሻም ለርዕሰ ብሔርነት የአመራር ደረጃ ለመድረስ በቅተዋል። እንዲህ ያለው አሠራር በችሎታ ብቃት ማደግ ሜሪቶክራሲ (Meritocracy) በመባል ይታወቃል። ሺ ዢንፒንግ የርዕሰ ብሔርነትን ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ እንኳ፤ በተለይ አገራቸው ቻይና ከኃያሏ አሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት በጥበብ እየመሩ በመሆኑና፤ ከአፍሪካ ጋር የተጀመረውን ወዳጅነት ላቅ ወደ አለ ደረጃ ከማድረሳቸውም በላይ ብራዚል፤ሩሲያ፤ ሕንድ፤ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ በዓባልነት የታቀፉበትን (BRICS) የተባለውን የገንዘብ ተቋም በግንባር ቀደም አስተባባሪነት ለማቋቋም በቅተዋል።

ሺ ዢንፒንግ እየሠሩት ካለው ውጤታማ ተግባራቸው የተነሳ፤ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ለሚቀጥሉት 16 ዓመታት ማለትም እስከ 1936 ዓ/ም ድረስ የመሪነቱን ሥልጣን ይዘው እንዲቆዩ አጽድቆላቸዋል።

ወደ እኛዋ አገር ኢትዮጵያ ስንመለስ ግን ሁኔታው ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኖ እናገኘዋለን። አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችም ሆኑ ዓባላት፤ አንድም በሀብታቸው፤ ወይንም ደግሞ በምላሳቸው ፖለቲከኛ መስለው መታየት እንጂ በተጨባጭ የሠሩት ሥራና ለሕዝብ ያበረከቱት በጎ ተግባር ፈጽሞ ይህን ያህል የጎላ አይደለም። ምናልባት ጥቂቶቹ ራሳቸውን በቲዮሪ ለማሳደግ   ዩኒቨርስቲ ገብቶ በመማር ብቻ ሳይሆን፤ የተለያዩ መጻሕፍትን በማንበብ የግል ጥረት አድርገው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አብዛኛዎቹ በራስ መተማመን የሌላቸውና፤ ፖለቲከኛነታቸውን የሥራ ፈጠራ አድርገው የወሰዱ ናቸው። ከዚህም የተነሳ በሕዝብ ላይ ችግር ሲከሰትና ጉዳት ሲደርስ እንኳ ጠንከር ያለ አቋም ወስደው፤ ከሕዝብ ጎን መቆማቸውን እና መቆርቆራቸውን የሚገልጽ መግለጫ የሚያወጡት እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።

እንዲህ ያሉት ሰዎች አድርባይ (Opportunists) እንጂ ፖለቲከኛ ተብለው ሊጠሩ አይችሉም። እንደዚህ ያሉት ተልካሻ ሰዎች ደግሞ የሐሳብ ድሆች ስለሆኑ አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ሽንጣቸውን ገትረው በተቃዋሚነት በመቆምና የሌላውን ፓርቲ ዕቅድና ፕሮግራም በማጥላላት ላይ ተጠምደው ነው። የፓርቲ መሪዎች ሁልጊዜ ተማሪዎች መሆናቸውን በመዘንጋት ‘ለሕዝቡ የማውቀው እኔ ብቻ ነኝ’ በማለት ራሳቸውን ይኮፍሳሉ። ሕዝቡን በማወያየትና ፍላጎታቸውን ለመረዳት ጥረት አያደርጉም። ይህም ታላቁ የድክመታቸው ምልክት ነው።

ከሥራቸው በየደረጃው ያሉትን ካድሬዎቻቸውን በየጊዜው የማሠልጠንና ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ዕቅድም የላቸውም። ምክንያቱም ካድሬው እየተማረና እያወቀ ሲሔድ፤ የፓርቲውን የወደፊት ፕሮግራም የመመርመርና የመጠየቅ፤ እንዲሁም የመተቸትና ከመሪው የተሻለ አመለካከት ይዞ የመቅረብ ባህርይ ሊያስከትል ስለሚችል እንዲህ ያለው አካሄድ፤ መሪዎቹን የሚገዳደር ስለሚሆን አይፈልጉትም። ስለሆነም የበላይነቱን የተቆጣጠሩት መሪዎቹ እንደ መሆናቸው መጠን የሚፈልጉት፤ የበታቾቹ ካድሬዎች የሚሰጣቸውን መመሪያ ብቻ እየተቀበሉ የሚተገብሩ፤ በአጭሩ ‘ተናጋሪ በቀቀኖች’ እንዲሆኑላቸው ብቻ ነው።

በዚህም ምክንያት ከፍ ያለ ቁመናና አንደበተ ርቱዕ የሆነ፤ ወይም መሪዎቹን በምክንያት የሚሞግት ሐሳብ ይዞ የሚንቀሳቀስ ደፋር የበታች ዓባል ከፓርቲው ውስጥ በአጋጣሚ ቢከሰት፤ የሆነ ዘዴ ተፈልጎ ከዓባልነት እንዲገለል፤ ወይንም ደግሞ እስከነአካቴው በምስጢር ሕይወቱን በማጥፋት ማስወገድ ይሆናል። እንዲህ ያለው ደካማ አካሄድ አገርን መጥቀም ሳይሆን፤ አገርን መጉዳት እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል።

በውጭ አገር ያለውን የፖለቲካ ልምድ ያየን እንደሆነ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ከላይ እንደተጠቀሰው ስለፖለቲካ በቂ ዕውቀት፤ ችሎታና ልምድ ያላቸው ናቸው። ስለሆነም የሐሳብ ልዩነታቸውን በስብሰባ አዳራሽ፤የምክር ቤት ዓባላትም ከሆኑ በምክር ቤቱ ውስጥ፤ ዱላ ቀረሽ ክርክር ያደርጋሉ። ከአዳራሹ ሲወጡ ግን ልክ እንደ ቅርብ ጓደኛ ሆነው ይወያያሉ። ምክንያቱም የሐሳብ ልዩነታቸው፤ አገርን ለማሳደግና ሕዝብ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ፤እንዲሁም ለቀጣዩ ትውልድ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሚሻለው ‘የእኔ ሐሳብ ነው’ በሚለው ላይ ተመሥርተው ስለሚከራከሩ እንጂ እንደጠላት በመተያየት አይደለም።

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችን ታሪክ ስናይ ግን ከኢሕአፓ፤ መኢሶንና የደርግን አመሠራረት ጀምረን ስንመለከተው የአንድ አገር ልጆች ለአንድ አገር ዕድገትና ብልጽግና መቆማቸውን በመርሳት እርስ በእርሳቸው እንደጠላት በመተያየት፤ አንዱ ሌላውን በማደን ያለ ርህራሄ በጥይት ተገዳደሉ። በዚያን የሥልጣን ሽኩቻ ወቅት፤ አገራችን የነበሯት ጥቂት የተማሩ ብርቅዬ ልጆቿ እየተፈለጉ አረመኔያዊ በሆነ መንገድ ተረሸኑ። ኢትዮጵያ የአንድ ትውልድ ዕድገቷ ወደ ኋላ ተመለሰ።

በቀጣይም ሕወሃት ወያኔ በኢትዮጵያ ጠላቶች እየተረዳ መንበረ መንግሥቱን ሲቆጣጠር፤ ያደረገው የተለየ አልነበረም። ምሁራንን እያሳደደ ከሥራ ማሰናበት፤ ለአገር ሉዓላዊነት ሲጋደሉ ዕድሜያቸውን ያሳለፉ፤ በዕውቀትም በልምድም የተካበተ የሙያ ባለቤት የሆኑ የጦር መኮንኖችን ‘የደርግ ወታደር’ የሚል ስም በመስጠትና በማዋረድ፤ ከፍተኛ በደል ሲፈጽም ቆይቷል። ከስድሳ በላይ የሚሆኑ የዩኒቨርስቲ ምሁራንን፤ መርጠው ባልተወለዱበት ማንነታቸው እየተፈረጁ ከሥራ ሲታገዱም እንደነበር የሚዘነጋ አይሆንም።

አሁንም የተያዘው ተመሳሳይ አካሄድ ነው። ዘርን መሠረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ የ17ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ ተሸካሚዎች፤ ‘ተረኞች እኛ ነን’ በማለት በፖለቲካ ፓርቲ ሽፋን፤ የፖለቲካ ሀሁ የማያውቁ ሠርቶ አደር ዜጎችን፤ ከእንስሳ ባህርይ ባልተላቀቁና በደመ ነፍስ የሚመሩ መንጋዎችን በማሠማራት የነፍስ ግድያ፤ የንብረት ዘረፋና፤ የኢዱስትሪ ውድመት ማድረሳቸው በስፋት ተዘግቧል።

ይሁን እንጂ በሥልጣን ላይ የሚገኘው የገዥው ፓርቲ ተወካዮችም፤ ከላይ ከተጠቀሱት ሴረኞች እኩል፤ ለፍትሕ፤ ለዲሞክራሲና እንዲሁም ለሰብአዊ መብት መከበር፤ የነጠረ አቋም ይዘው የሚንቀሳቀሱትን እነ እስክንድር ነጋንም ከወንጀለኞች ጋር አዳብለው ማሠራቸው ከነፍሰ ገዳይነት ተለይቶ የሚታይ አይደለም።

እጅግ በጣም የሚዘገንነው ደግሞ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን በምሥጢራዊ ሤራ በማስገደል፤ የሌላ ማኅበረ ሰብ ዓባላት ወንጀሉን እንደ ፈጸሙት በማስመሰል በዘር ተለይተው ጥቃት ለደረሰባቸው ሰለባዎች ተመጣጣኝ ካሣ ሳይሰጥ፤ የነፍሰ ገዳዮቹ መሪ የሆኑት አቶ ሺመልስ አብዲሳ፤ ‘ለደረሰው ጥፋት ይቅርታ እንጠይቃለን፤ ኢንቨስተሮች ለልማት ወደ በኦሮሚያ ብትመጡ አስፈላጊውን ድጋፍ የምናደርግ መሆኑን እናሳውቃለን’ በማለት ያስተላለፉት ተማጽኖ ስላቅ ከመሆን በስተቀር፤ ከልብ ተቀባይነት ሊኖረው ይችላልን?

‘ጓደኛህን በምን ቀበርከው? በሻሽ፤ የኋለኛው እንዳይሸሽ’ እንዲሉ በምን ዋስትና ነው አንድ ኢንቨስተር ችግር ሞልቶ በሚፈስበት፤ ሕግ በማይከበርበት፤ ሥርዓት አልበኝነት በነገሠበት፤ ክልል ገንዘቡን የሚበትን? ‘ሰዶ ማሳደድ ከፈለግህ ዶሮህን በቆቅ ለውጥ!’ እንዲል የአገራችን ሰው። አቶ ሺመልስ አብዲሳ ዓይናቸውን በጥሬ ጨው አጥበው ይህንን በድፍረት ለመናገር ያበቃቸው በውስጣቸው ‘ኅሊና’ የሚባል ነገር ስሌላቸው እንደሆነ አረጋግጠዋል። ‘ዓይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ’ ዓይነት አነጋገር የኢትዮጵያን ሕዝብ ምን ያህል እንደሚንቁ  ዋና ማሳያ ነው። እንዲህ ያለው የፖለቲካ ሹመት ውጤቱ አገር የሚገነባ ሳይሆን፤ ኅሊናን የሚፈትን አገር የሚያፈርስ እርምጃ መሆኑን ነው።

‘ከአንጀት ከአለቀሱ ዕንባ አይገድም’ እንዲሉ፤በእርግጥ አቶ ሺመልስ አብዲሳ በሁኔታው ተጸጽተው ከሆነ በቅድሚያ በኦሮሚያ ክልል ጉዳት ለደረሰባቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተመጣጣኝ ካሣ ለመክፈል ቁርጠኛ የውሳኔ አቋም መያዛቸውን ማሳወቅ ይኖርባቸዋል።

የውጭ ጠላቶቿ የሚሸርቡት ሴራ ሳያንስ፤ እስከ አሁንም ድረስ የኢትዮጵያን ዕድገት እግር ከወርች ቀፍድዶ አላላውስ ያላት የፖለቲካ ሹመኛ ነው። የፖለቲካ ሹመኛ ደግሞ በላቡና በችሎታው ሳይሆን፤ አድር ባይ፤ ሆድ አደር፤ ሰምቶ አደር፤ከርስ አደር ስለሆነ፤ ፍትሕና ርትዕ የሚባሉ ነገሮችን ከቁብ አይቆጥራቸውም። አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለመሆኑ ኅሊና የሚባል ነገር በጭንቅላታቸው ውስጥ አለን?

አቶ ታከለ ኡማስ ቢሆን? አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በደረሰበት አረመኔያዊ አገዳደል ያለላዛነና ያልተቆጨ ኢትዮጵያዊ የለም፤ ነገር ግን ለመታሰቢያ ተብሎ የተሰወሰነውን ስናይ ደግሞ፤ የአቶ ታከለ ኡማን ችሎታ የሚገምትና፤ ለተቀመጡበት ቦታ ይመጥናሉ ወይ? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ እንገደዳለን።

ለመሆኑ ሟቹ ምን ስለሆነ ነው ይህን ያህል የተጋነነ፤ የመንገድ፤ የፓርክ፤የት/ቤት ፤የድልድይ እና ወዘተ….. ማስታወሻ ይደረግለታል የተባለው? እጅግ በጣም አሳፋሪና አስተዛዛቢ ተግባር ነው። ይህም በራሱ ከነፍሰ ገዳይነት በምን ይለያል?

ለነገሩ በፈጠራ ትርክት አኖሌን የመሰለ የጥላቻ ሐውልት አርሲ ላይ አቁሞ፤ ጀግኖችና ጥበበኞች አያት ቅድመ አያቶቻችን በነፃነት የአቆዩልንን አገር ለማፍረስ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይመክርበትና ሳይስማማበት በሴረኞች የተረቀቀውን ሕገ መንግሥት ሙጥኝ ብሎ፤ ኦሮሚያ የምትባል አገር እንገነጥላለን በሚል፤ የሕልም ካርታ አምቦ ላይ  አስቀምጦ፤ ኢትዮጵያን በሰላም አስተዳድራለሁ ብሎ ማሰብ ራሥን ከማታለል በስተቀር የሚገኝ ፋይዳ የለም።

የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ በጥልቀት ስንመረምር ፖለቲከኞች የራሳቸውን ጥቅምና ሥልጣን ያስቀድማሉ እንጂ ለሀገር ዕድገትና ለወገን ክብር የሚበጅ፤ ከእነርሱ የተሻለ ሐሳብ እና ዕቅድ ይዘው የተገኙትን ሌሎች ግለሰቦችና ቡድኖች፤ እንደ ጠላትና ደመኛ አድርጎ በመፈረጅ በቅድሚያ የስም ማጥፋት ዘመቻ ይካሄድባቸዋል። በቀጣይም ስብእናቸውን የሚያዋርድ ተግባር እንደፈጸሙ ተደርጎ ይወነጀሉና በተቀነባበረ ሁኔታ የሐሰት ምስክር ሁሉ ተዘጋጅቶ ወደ ወኅኒ እንዲወርዱ ሲደረግ ቆይቷል። እንዲህ ያለው አሠራር በወያኔ ሕወሃት ዘመን ጎልቶ ይታይ የነበረ ቢሆንም ዛሬም እየተካሄደ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት በድጋሜ እንዳይፈጸም መታረም ሲገባው፤አሁንም እየተሠራበት ስናይ ስንደግፈው የቆየነው ለውጥ፤ እንዲህ መሆኑን ስንረዳ ደግሞ እጅግ በጣም ኅሊናን ያደማል።

ለመሆኑ አገራችን ኢትዮጵያ ከነፍሰ ገዳይነት ነፃ የሆኑና በራሳቸው የሚተማመኑ እውነተኛ ፖለቲከኞችን የምታገኘው መቼ ይሆን? ከዚህ የምንገነዘበው ጠ/ሚንስትራችን ከመሪነት መንበር ላይ ተቀመጡ እንጂ በትረ ሥልጣኑን ገና አለመጨበጣቸውን ነው። በትረ ሥልጣኑን ቢጨብጡ ኖሮ የተንሸዋረሩ የሕገ መንግሥት አንቀጾችን ይሠርዛሉ፤ ለሕዝብ አንድነትና ለአገር ሉዓላዊነት ጠንቅ የሆኑ ምልክቶችን ይነቅላሉ እንዲሁም በወጣቱ ትውልድ ላይ ሲዘሩ የቆዩ ልብ የሚያሻክሩ፤ የፈጠራ ትርክት መርዞችን ይሽራሉ፤ ሆነ ብለው ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨትና መንግሥታቸውን ለማፍረስ የሚራወጡትን ደግሞ ለፍርድ በማቅረብ ፍትሕን ያሰፍኑ ነበር። ነገር ግን ‘የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም’ እንዲሉ፤እንኳን ለሚያስተዳድሩት ሕዝብ ደኅንነት፤ አንድነትና ሰላም ሊደርሱ ይቅርና የራሳቸውንም ኅልውና ለማስጠበቅ የሚያስችል የሕግ የበላይነትን ማስከበር አልቻሉም። ምክንያቱም ‘ኢትዮጵያ ነፍሰ ገዳዮች እንጂ ንጹሕ ፖለቲከኛ የላትም።’

-//-

 

4 Comments

 1. ውድ አቶ ገብረ ክርስቶስ አባይ ባቀረብከው ትንተና ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ። በደንብ እንዳተትከው የኛ አገር ፖለቲከኞች ከታች ወደ ላይ እየተኮተኮቱ የሚያድጉ ሳይሆኑ ከላይ የሚቀመጡ ናቸው። ጭንቅላታቸው በፍልስፍና፣ በቲዎሪና በተፈጥሮሳይንስ ያልተገነባና፣ እንዲሁም ደግሞ በክርክርና በውይይት ያልተፈተነ ስለሆነ አገርን ወይም አንድን አካባቢ ለመገንባት የሚያስችል የተወሳሰበ ሃሳብ መንደፍ አይችሉም። በደንብ እንዳስቀመጥከው አንድ ፖለቲከኛ ከፍተኛ ቦታ ከመያዙ ወይም ጠቅላይ ሚኒስተር ከመሆኑ በፊት በመንደር ወይም በወረዳ ደረጃ መፈተንና ልምድ ማካበት አለበት። በአንድ መንደር ውስጥ ከተማውን በስርዓት የሚገነባ ከሆነ፣ ለህዝብ ግልጋሎት የሚሰጡ በቂና አስፈላጊ ተቋማት የሚገነባ ከሆነ፣ ለወጣቱ የሙያ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የሚገነባ ከሆነ፣ ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስቱሪዎች እንዲተተከሉ ዕቅድ የሚያወጣ ከሆነ… ወዘተ. ባጭሩ በዚያ አካባቢ ለሚኖረው ህዝብ የስራ መስክና የባህል ማዕከሎችና መዝናኛ ቦታዎች የሚገነባና ህዝባዊ ሀብትም የሚፈጥር ከሆነ ለሚቀጥለው ከፍተኛ ቦታ ሊታጭ ይችላል። የኛ አገር ፖለቲከኞች ይህንን ዐይነቱን ደረጃ ሳያልፉና ሳይፈተኑ ጠቅላይ ሚኒስተር ይሆናሉ። እንደነዚህ ዐይነት መሪዎች ደግሞ በውስጣቸው ምንም ዐይነት እሴት ያላዳበሩ ስለሆኑ ከውጭ የሚመጣን ትዕዛዝ ተግባራዊ በማድረግ አገር ያፈርራሳሉ። ባህልን ያወድማሉ። አገርንም የጦርነት አውድማ ያደርጋሉ። ሰሞኑን ሁላችንም እንደተከታተልነው የዛሬው ፖለቲከኞቻችን ፖለቲካ የሚባለውን ሳይንሳዊ ጽንሰ ሃሳብ የተረዱት ተንኮል መጠንሰሻና አንዱን ጎሳ በሌላኛው ላይ እንዲነሳ ማድረጊያ አድርገው ነው። የአቶ ሺመልስ አብዲሳን ንግግርና ስራውን ተመልከት። ትልቅ ክልል ይዞ አካባቢውን ከማልማትና በህዝቡ ዘንድ መተማመንና መፈቃቀር እንዲኖር ከማድረግ ይልቅ ህዝብን ያስጨርሳል። በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ሚሊሺያኖች በማሰልጠን ህዝብን ያስፈራራል። መንፈሱ የተረበሽና ለጦርነትም የተዘጋጀ ሰው ነው የሚመስለው። ለማንኛውም ላቀረብከው ግሩም ትምህርታዊ ሀተታ በጣም አመሰግንሃለሁ። ፍላጎት ካለህ ድረ-ገጼን ገብተህ ተመልከት።

  ፈቃዱ በቀለ

 2. ውድ አቶ ገብረ ክርስቶስ ዓባይ !

  ሀተታህ ሙሉ በሙሉ ዕውነትን ያዘለ ነው። በደንብ እንዳተትከው የአገር አስተዳዳሪዎች የሚሆኑት በመጀመሪያ ደረጃ በመንደርና በወረዳ ደረጃ ልምድ ያላካብቱና በተግባርም ስራቸውን ሳያሳዩ ጠቅላይ ሚኒስተርና የኢኮኖሚ ሚኒስተር የሚሆኑ ናቸው። ስልጣን ላይም ከወጡ በኋላ ዕውቀታቸውን ለማሻሻል መጽሀፍ አያነቡም፣ ወይም ተጨማሪ ትምህርት አይወስዱም። የአገራችንን የኢኮኖሚ ዕቅድ የሚያወጡ ፈረንጆች ናቸው። በማንኛውም ረገድ የገዢው መደብ በፈረንጆች ነው የሚተማመነው። በዚህ መልክ አገርን አስተዳድራለሁ የሚለው የገዢ መደብ በመሰረቱ የውጭ ኃይሎች ተላላኪ ነው። እራሱን እያደለበ አገሪቱን ወደ ጦር አውድማነት የሚለውጥ ነው። ሀብትን የሚያዘርፍና የብልግና ኢንዱስትሪ የሚያስፋፋ ነው። ከፎቶው ላይ እንደሚታየው ሁሉም አገርን የመምራትና የመገንባት ብቃት የላቸውም። መንፈሳቸው የጦርነት ስለሆነ ካለምንም ርህራሄ ንጹሁን ዜጋ ይገድላሉ። በሌላ ወገን ደግሞ እንደነዚህ ዐይነት ገዳዮች አቶ እየተባሉ ይወደሳሉ። ትግል አድርገናል በሚሉበት ዘመን አንድም መጽሀፍም ሆነ ሌላ አገርን ለመገንባት የሚያስችል ጽሁፍ ጽፈው አያውቁም። በግብዝነት ብቻ ስልጣን ለመውጣት ይታገላሉ። ስልጣንንም ከጨበጡ በኋላ እንደምናየው ተራ ገዳይ ይሆናሉ፤ ወይም በቁጥጥራቸው ስር ባሉት ፖሊሶች ያስገድላሉ። በእኛ አገር ፖለትከኛ ማለት ገዳይና ተንኮለኛ ነው። ሳይንስንና ጥበብን ያልተካነ፣ ተልዕኮው ስልጣኔ ሳይሆን ጥፋት ነው። ፈቃደኛ ከሆንክ የሚከተለውን ድረ-ገጽ ጎብኝለኝ።

  ለግሩም ጽሁፍህ ከልብ አመሰግንሃለሁ!

  ፈቃዱ በቀለ

 3. ሃሳብ፥ ሃሳብ፥ ሃሳብ፥ ሃሳብ
  ችግር መፍቻ፥ ጥበባ ጥበብ
  የወተት ስልባቦት ሳይሆን ኣልባብ
  የዴሞክራሲ እምብርት፥የግብረገብ
  የፍጥረታት ማንነት፥ የዕኩልነት ድባብ
  መች፥ መች የጨረባ ተስካር ግሳንግስ፥ስብስብ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.