ዓባይ ሆይ አደራ! – አገሬ አዲስ

nile

ነሓሴ 2 ቀን 2012 ዓም(08-08-2020)

ዓባይም ሞላልን፣ ያሰብነው ሆነልን!
ሲባል የነበረ በዘፈን ቀረርቶ፣
ምኞትና ሃሳብ በእውን ተተክቶ
ደሃ ሃብታም ሳይል ያለውን አዋጥቶ፣
ለማዬት በቅተናል ግድቡ ተሰርቶ።
ጨለማ አሶግዶ፣ድህነት አጥፍቶ፣
ብዙ የልማት ዘርፍ በሃገር ተስፋፍቶ፣
ተቋም ተዘርግቶ፣ፋብሪካ ተከፍቶ፣
ሠርቶ የመጠቀም ዕድል ተገኝቶ
የተራበው በልቶ የጠማው ጠጥቶ

በቂ ውሃ ቀርቦ በጉድጓድ በመስኖ፣
ጠፍና በረሃው የእርሻ ማሳ ሆኖ።
እርሃብ ቸነፈር ቀሪ ታሪክ ሆኖ

ጥቅም እንደሚሰጥ በስፋት ሲወራ፣
በግድቡ ውጤት ሲመካ ሲኮራ፣
በጉጉት ሲጠበቅ ብዙ ብዙ ሥራ፣
እንዳለፉት ሁሉ የውሸት ደመራ፣
አባይም በተራው ላም አለኝ በሰማይ እንዳይሆን አደራ!

በቅድሚያ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ለዚህ የህብረት ሥራ ውጤት  አበቃችሁ/አበቃን እላለሁ

ዓባይ የሚለውን ቃል ጠበቅ ስናደርገው ትልቅ የሚል ሲሆን፣ ላላ ካደረግነው ደግሞ ከሃዲ ፣ቃለአባይ፣ይሆናል።ለምን ቢባል  ለፈለቀበት አገርና ሕዝብ ያልጠቀመ፣በፈለቀበትና በሚፈስበት አገር ውስጥ ቀርቶ ጥቅም ያልሰጠ፣በቦታው ያልተገኘ፣መሬት ሰንጥቆ ሸለቆ ገብቶ የሚሸሽ ፣ለባዕዳን የሚጠቅም ፣ከሃዲ መሆኑን  ሊገለጽልን ይችላል።በዚህም ሆነ በዚያ ሲጠራ ኖሮ አሁን ላይ ጊዜ ስለፈቀደ ለሚመነጭበት አገር ሕዝብ ጥቅም እንዲውል ታስቦ መገደቡ ብዙዎች መሪዎችና ተራው ሕዝብ  ሲያልሙትና ሲመኙት የነበረ የጋራና ብሔራዊ ደስታ ነው።

በተለያዩ ዘመናት በሥልጣን ላይ የነበሩ መሪዎች የዓባይ ወንዝን በጥቅም ላይ ለማዋል ሲያስቡ ፣እንዲሁም ለአገራቸው ክብርና ልዑላዊነት መሣሪያና  ዋስትና አድርገው ሲጠቀሙበት እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል። ያ የመሪዎችና የሕዝቡም ህልምና ፍላጎት በዛሬው ትውልድ በተግባር በመገለጹ ለትውልዱ ኩራት ነው።ተፈጥሮ ያደለንን ሳንጠቀምበት ለብዙ ሽህ ዓመታት በከንቱ ሲፈስ የነበረው የዓባይ ወንዛችን  በሕዝቡ እርብርቦሽ ይኸው ዛሬ ለጥቅም እንዲውል ተገድቦ ለማዬት በቅተናል።

ይህ እርምጃ የመጀመሪያው እንጂ የመጨረሻው አይደለም፤ሊሆንም አይገባም።የመጨረሻ የሚሆነው የተነገረውና ሕዝቡም ተስፋ ካደረገው ጥቅም ላይ ሲውል ነው።ሕዝቡን ከድቅድቅ ጨለማና፣ለጤናና ለከባቢ ጉዳት ካስከተለው ከኩበትና ጭራሮ ማገዶ ሲገላግለው፣በመስኖ መስመር ዝግጅትና ሥራ ላይ አስተዋጽኦ አድርጎ ሕዝቡን ከርሃብና ድህነት ሊያወጣ በሚችልበት፣በአጠቃላይ ተጨባጭ በሆነ በሕዝቡ ኑሮ ደረጃ፣ የኤኮኖሚ እድገትና ለውጥ በሚያመጣው  ተግባር ላይ ሲውል  ነው።

የዓባይ ግድብ ለሃገራችን የመጀመሪያውና የመጨረሻው አይደለም፣ከዚህ በፊት ቀድመው የተሠሩና  ወደፊትም ሊሠሩ የሚችሉ ግድቦች አሉ፤ ይኖራሉም።የዓባይን ግድብ ጎላ አድርጎ እንዲታይ ያደረገው ከሌሎቹ ግድቦቻችን  ትልቅና ሃይል  የማምረት አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ ነው።

አዎ ! ከአባይ በፊት በርከት ያሉ ግድቦች በተለያዩ ያገራችን ክፍሎች/ቦታዎች ተገንብተው ሃይል ለማመንጨት ችለዋል፤የሚያመነጩትም ሃይል ከሌሎቹ የአፍሪካ አገራት የበለጠ ነው።ስለሆነም አገራችን በሃይል ማመንጨቱ የመጀመሪያውን ቦታ ይዛለች።ግን የሚያሳዝነው ነገር ሕዝባችን ተጠቃሚ አለመሆኑና የጨለማ ኑሮ በመግፋት ከመጀመሪያው ቦታ ላይ መገኘቱ  በላይ ያሉትን የሃይል ማመንጫ ግድቦች እንኳን አለማወቁ ነው።እያለው የማያውቅና  ያጣ ሕዝብ!

ከብዙ ዘመናት ጀምሮ በተለይም አሁን ዓባይ አይገደብም ብላ ያዙኝ ልቀቁኝ የምትለው ግብጽ በሃይል ማመንጫ ረድፍ ከአፍሪካ አራተኛ ነች፤ሆኖም ግን ጠቅላላ ሕዝቧን ለ24 ሰዓት በመብራት ለማንበሽበሽ ችላለች። የዳቦ እጥረትም የለባትም፣ሕዝቡ በርሃብና በቸነፈር አልታወቀም።ያም አነሰኝ ብላ ነው በኢትዮጵያ ሕዝብ የጨለማ ኑሮ እየፈነደቀች  ዓባይ እንዳይገደብ  መሰሎቿን በማሰለፍ እንቅፋት ለመፍጠር ላይ እታች የምትለው።

የህዳሴ ግድቡን ሳይጨምር በዬቦታው ተተክለው የሚገኙት ግድቦች የሚያመነጩት የኤሌክትሪክ ሃይል ለአገር ውስጥና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ቢውሉ ኖሮ ሕዝባችን ከጨለማ ኑሮ ተላቆ የዕድገት ደረጃው ከፍ ባለ ነበር።ግን ለአገር ውስጥ ሳይሆን እንደሸቀጥ ለጎረቤት አገራት እዬተቸበቸበ  መሆኑ ማስረጃ የማያስፈልገው ሃቅ ነው። ስህተት ነው የሚባል ከሆነም የሚመነጨው ሃይል ዬት እንደገባና በምን  ጥቅም ላይ እንደዋለ መግለጽ ይገባል።የውጭ ንግድ አካል ከሆነም ለማንና የት እንዲሁም ስንት እንደተሸጠና የተገኘው ገንዘብ ከምን ላይ እንደዋለ የሚመለከተው አካል በተለይም የኤሌክትሪክና ሃይል መስሪያ ቤት የማብራራት ግዴታ አለበት።ይህም ሕዝብ ተስፋ የጣለበትን የህዳሴ ግድብ ለሕዝቡ የሚሰጠውን ጥቅም ሊያመላክት ይችላል።ይህ ካልሆነ ግን  የዓባይም ግድብ እንደተቀሩት ግድቦች ”ላም አለኝ በሰማይ” ሆኖ ይቀራል። ሕዝቡን የተስፋ እንጀራ ከመመገብ  ይልቅ ቀድሞ የተሰሩት ግድቦች ለምን ሕዝቡን ከጨለማ ኑሮ እንዳላወጡት  በማያምታታ ሁኔታ ለሕዝቡ መግለጽና ማስረዳት ተገቢ ነው።

የህዳሴ ግድብ ሳይጨመርበት የቀድሞ ግድቦች የሚያመነጩት የሃይል ምርት በተለይም የኤሌክትሪክ መብራት አቅርቦት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከበቂ በላይ እንደሆነ የሌሎቹን አገሮች ማዬትና ማወዳደር ሊያረጋግጥልን ይችላል።ቁም ነገሩ ብዙ ምርት ማምረቱ ሳይሆን ምርቱ ለሕዝቡ እንዲዳረስ ማድረጉ ላይ ነው።ለሕዝብ ደንታ የሌለው የወንበዴና ዘራፊ ቡድን የሚመራው አገር ሕዝብ ለመከራ የተጋለጠ መሆኑን ከራሳችን ማዬቱ በቂ ማስረጃ  ነው።ይህ  የዘራፊዎችና የሌቦች ስርዓት  ካልተወገደ በግድብ ላይ ግድብ ቢሰራ ከጨለማ ኑሮ ፈቀቅ እንላለን፣ከድህነት እንወጣለን ማለት ዘበት ነው።

በአገራችን ውስጥ ያሉትን የሃይል ማመንጫ ግድቦችና የሃይል ምርት መጠናቸውን ከዚህ በታች ለማቅረብ እወዳለሁ።ዝርዝሩ የሌሎቹንም የአፍሪካ አገሮች የግድብ ሥራዎችና የሚያመነጩትን የኤሌክትሪክ ሃይል ብዛት የሚያሳይ ነው።ይህንን  ያገኘሁት ከዓለም አቀፍ የውሃና የግድብ ሥራዎች ተቋም በፖስተር መልክ አዘጋጅቶ ባቀረበው የ2019 ዓመት ሪፖርት ላይ ነው።ትክክል ለመሆኑም በሌላ በኩል በጎግልና በመሳሰሉት የመረጃ ምንጮች ለማረጋገጥ ችያለሁ።ያም ሆነ ይህ ሌሎችም ኢትዮጵያዊ  ባለሙያዎች ክትትል ሊያደርጉና  ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል። የዓለም አቀፉ ተቋም በአፍሪካ  የየአገራቱን የኤሌክትሪክ ሃይል ምርት በሰንጠረዥ ካቀረበው ሰነድ  በፊት ከላይ በጠቀስኳቸው ምንጮችና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና መብራት ሃይል ባለሥልጣን በኩል ያገኘሁትን መረጃ ለማቅረብ እወዳለሁ።

በዓለም አቀፉ ሰነድ መሰረት አገራችን ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች ሁሉ በአንደኛ ደረጃ የተቀመጠች ሲሆን የምትከተለው ደቡብ አፍሪካ ናት። በሶስተኛነት አንጎላ ፣በአራተኛነት ደግሞ ለኢትዮጵያ እራስ ምታት ሆና የኖረችውና አሁንም በአባይ ግድብ ላይ ያዙኝ ልቀቁኝ የምትለው አገር ግብጽ ነች።ይህችው ጉደኛ አገር ናት  ከኢትዮጵያ ያነሰ ሃይል አመንጭታ ሕዝቧን ለሃያአራት ሰዓት የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ አድርጋ በኢትዮጵያ ሕዝብ  ላይ የጨለማ ኑሮ እንዲኖር የምትፈርደው።የግብጽ ሌላው ፍላጎቷ ኢትዮጵያ የአክራሪ እስላም ሃገር ሆና ማዬት ወይም  ፈራርሳ  ሰርጎ በመግባት በመዳፏ ውስጥ በማሳደር አባይን ከምንጩ መቆጣጠር ነው።ያንን  የዘመናት ምኞቷን  አሁን አገራችን በጎሰኞች ስርዓት በምትታመስበት ወቅት በቅጥረኛ  ባንዳዎች በኩል አሳካለሁ በማለት ጥረት በማድረግ ላይ ብትሆንም  ግን አይሳካላትም።የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ሁሌውም በመጣችበት መንገድ አሳፍሮ ይመልሳታል የሚል እምነት አለኝ። ለዚያ ዋስትናው በቅርብ እርቀት ላይ ያሉትን አገር በቀል ተላላኪዎች፣ባንዳዎችና ጆሮ ጠቢዎቿ ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ነው።በአገራችን የተለምዶ አባባል

ጠላትማ ምንጊዜም ጠላት ነው፣

አስቀድሞ መምታት በቅርቡ ያለውን፣

ባንዳ፣ ተላላኪ፣ ጆሮ ጠቢውን ነው። ይባል የለ!

እነሱን አቅፎ ሰላም ና ያገር ህልውና ሊከበር አይችልም፤ቢከበርም ብዙ መስዋእት ያስከፍላል። ያለውን ሥርዓት መለኮታዊ አድርጎ ማዬቱም አንዱ ድክመት ነው።በውጭ ሃይሎች/መንግሥታት ተደግፎና ሰልጥኖ የመጣ፣ለነሱም ጥቅም የሚቆም መሆኑን ማወቅና ማጋለጥ ተገቢ ነው።

በአገራችን ያሉት የሃይል ማመንጫ ግድቦች ዝርዝር የሚከተለው ነው።

የግድቡ ስም                              የሚያመነጨው ሃይል        የተገነባበት ዓመት እአአ

አባ ሳሙኤል                                    6,6 ሜጋዋት                   1932

ቆቃ/አዋሽ 1                                    43 ሜጋዋት                     1960/1966

አዋሽ 2+3                                      64 ሜጋዋት                     1971

ፊንጫ                                          134ሜጋዋት                     1973

ፊንጫ አመርቲንሽ                              95 ሜጋዋት                    2011

ግልገል ጊቤ 1                                   184 ሜጋዋት                   2004

ግልገል ጊቤ 2                                  420 ሜጋዋት                   2010

ግልገል ጊቤ 3                                 1870 ሜጋዋት                   2016

መልካ ዋኬና                                    153 ሜጋዋት                   1989

ጣና በለስ                                       460 ሜጋዋት                  2010

ተከዜ                                            300 ሜጋዋት                  2010

ጢስ አባይ                                        84,4 ሜጋዋት               1953/2001

ገናሌ ዳዋ                                        254 ሜጋዋት                   2017

በጠቅላላው                                    4068 ሜጋዋት የመነጨ ሲሆን

ስራቸው ያልተጠናቀቁት ግድቦች

ኮይሻ                                             2160 ሜጋዋት

ገናሌ ዳዋ                                          257 ሜጋዋት

ትልቁ የህዳሴ ግድብ                             6450 ሜጋዋት

ድምር                                             8867 ሜጋዋት

የተጠናቀቁትና በግንባታ ላይ ያሉት ግድቦች  ሲጠናቀቁ  12,935 ሜጋዋት ይሆናል።ይህ የሃይል ክምችት ከዚህ በታች በተዘረዘሩት መስኮች የተገኘውን የሃይል መጠን አይጨምርም።

ከእንፋሎት ወይም ከፍል ውሃ/Geothermics/ የሚገኙት የኤሌክትሪክ ሃይል መጠኖች የሚከተሉት ናቸው

አሉቶ 1                 ላንጋኖ                    7,3 ሜጋዋት              1998 እአአ

አሉቶ 2                                          75   ሜጋዋት

በግንባታ ላይ ያሉና ገና ጥቅም ያልሰጡ

ተንዳሆ                   ዱብቲ                 10 ሜጋዋት

ኮርቤቲ 1                 ሻሼመኒ                10 ሜጋዋት

ኮርቤቲ 2                ሻሼመኒ                50 ሜጋዋት

ቱሉሞዬ 1                አርሲ                  50 ሜጋዋት

በዚህ ዘርፍ እስከ 2027  እአአ ድረስ 1020 ሜጋዋት ለማመንጨት ከባለሃብቶች ጋር ስምምነትና እቅድ አለ።

ሌላው ደግሞ ከጸሃይ ጨረር/Solar park/ የሚገኝ የኤሌክትሪክ ሃይል ነው።በዚህ በኩል ብዙም የሚያመረቃ  ውጤት ባይኖርም በንድፍና ዕቅድ  ደረጃ መያዙ ታውቋል።ከእቅዶቹም ውስጥ

መተሃራ ውስጥ በ2019 እንደሚያልቅና 100 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ የተጠበቀውና ተግባር ላይ ያልዋለው ይገኝበታል።

Thermal/ ICSTermal plant ይህ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚመነጨው ከእርሻ ምርት ገለባና አረም፣ከቅጠላቅጠል፣አታክልትና ፍራፍሮ ትርፍራፊ፣ከቁሻሻ ቃጠሎ የሚገኝ ሲሆን በዚህ ግዙፍ አምራችና ተጠቃሚ የሆኑት የትልልቅ እርሻ በተለይም የሸንኮራ አገዳ /ስኳር አምራች በሆኑት ፋብሪካዎች ናቸው።ፋብሪካዎቹ የሚያገኙትን ሃይል መልሰው ለፋብሪካው ማንቀሳቀሻና ለመብራት አገልግሎት ሲጠቀሙበት የተረፋቸውን ለሌላ ተጠቃሚ በመሸጥ ገንዘብ ያገኙበታል።መንግሥትና አንዳንድ ተቋማት የአምራቾቹ ደንበኞች ናቸው።የመብራት ሃይል መስሪያ ቤትም አንዱ ሸማች ነው።

ጎን ለጎንም በአዲስ አበባ ከከተማው  ኑዋሪ ቤት የሚሰበሰበው ቁሻሻ ተሰብስቦ ለተመሳሳይ ተግባር ይውላል።በተለምዶ ቁሼ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ የተገነባው የቁሻሻ ማቃጠያ የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨቱ ተግባር ላይ ተሰማርቱዋል። ይህ የሃይል ማመንጫ 110 ሜጋዋት ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን አሁን ያለው አቅሙ ግፋ ቢል 50 ሜጋዋት ነው።ከዚያ ውስጥ አሁን የሚያመርተው ከ25 ሜጋዋት አይበልጥም።የዚህ ድርጅት  ባለቤቱ ግን ማን እንደሆነ አይታወቅም።ከዬቤቱ ተሰብስቦ በሚቃጠለው ቁሻሻ በሚገኘው የኤሌክትሪክ ሃይል የከተማው ሕዝብ ቀርቶ በቁሼ አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ ተጠቃሚ መሆኑ ያጠራጥራል።በገዛ ዳቦዬ ልብልቡን አጣሁት እንዲሉ! ምናልባት የከተማው አስተዳደርና ግለሰቦች የገነቡት ሊሆን ይችላል።ቅድሚያም ለትልልቅ ሆቴሎችና የመዝናኛ ቦታዎች ስለሚሆን የሕዝቡ እጣ ፋንታ እንደተለመደው ያው በገሌ ነው።ትላልቅ ሆቴሎችና የንግድ ተቋማት ከመብራት እጦት የተነሳ  የራሳቸው ኤሌክትሪክ ማመንጫ ጀኔሬተር መኖሩ ግድ ሆኖባቸዋል።በሳምንት ውስጥ ቢያንስ ለሶስት ቀናት መብራት በማይገኝበት ከተማ ሌላ አማራጭ እንዲኖር ማድረጉ ግዴታ ነው።

የቁሻሻው መሰብሰብ የሚሰጠው ጥቅም ቢኖር ለከባቢው ጽዳትና፣ከቁሻሻ ጋር ተያይዞ ለሚመጣው በሽታ ሙሉ ለሙሉም ባይሆን በከፊል ለመቀነስ ያስችላል፤በስፋት መለመድ ያለበት እንቅስቃሴ ነው። በጽዳት ጥበቃው ዙሪያ ለተሰማሩት ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩ ሌላው ተጨማሪ ጥቅም  ነው።

በዚህ የቃጠሎ የሃይል ማመንጫ ተግባር ውስጥ የተሳተፉትና  የሚያመርቱት የኤሌክትሪክ ሃይል መጠን እንደሚከተለው ነው።

ወንጂ ሸዋ ሱካር ፋብሪካ         አዳማ             30 ሜጋዋት

መተሃራ  ስኳር ፋብሪካ           መተሃራ            9 ሜጋዋት

ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ              ፊንጫ             30 ሜጋዋት

ከሰም ስኳር ፋብሪካ               አሚባራ           26 ሜጋዋት

ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ             አሳይታ            60 ሜጋዋት

ኦሞ ኩራዝ 1 ስኳር ፋብሪካ       ኩራዝ              45 ሜጋዋት

ኦሞ ኩራዝ 2 ስኳር ፋብሪካ       ኩራዝ             60   ሜጋዋት

ኦሞ ኩራዝ 3 ስኳር ፋብሪካ       ኩራዝ             60 ሜጋዋት

ኦሞ ኩራዝ 4 ስኳር ፋብሪካ       ኩራዝ            120  ሜጋዋት

ጠቅላላ                                                440  ሜጋዋት ሲሆን ከዚህ ውስጥ በጥቅም ላይ የዋለው  167 ሜጋዋት ብቻ ነው።ሌላው ዬት ገባ?በተጨማሪም ግንባታው ተጀምሮ ያልተጠናቀቀው

በጋዝ የሚንቀሳቀሰው የአዲ ጉደን  ፕሮጀክት  500 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ሃይል እንደሚያቀርብ የሚጠበቅ ሲሆን ግንባታው ባለፈው ዓመት በማርች ወር 2019 እንደተጀመረ መረጃው ያሳያል።

በዚህም በዚያም ሆኖ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረተው የኤሌክትሪክ ሃይል ጠቅላላ ድምር

ከግድቦች                                                    4068  ሜጋዋት

ከእንፋሎት/ፍል ውሃ                                        82,3 ሜጋዋት

ከጽሃይ ጨረር                                               0000

ቅጠላቅጠል፣ገለባና ከቁሻሻ ቃጠሎ (ባዮተርማል)            167    ሜጋዋት

በጠቅላላው                                                4317,3  ሜጋዋት

ይህ ከዚህ በላይ የቀረበው ዝርዝር ከኢትዮጵያ መብራትና ሃይል ባለሥልጣን  (EELPA/Ethiopian Electric Light and Power Authority) ከጎግልና ከሌሎቹ መረጃ ምንጮች ያገኘሁት ሲሆን በዓለም አቀፉ የውሃ ግድብ ሥራና የሃይል ማመንጫ ምዝገባ ቢሮ በኩል ያገኘሁት ዝርዝር መረጃ ደግሞ የሚከተለውን ይመስላል።

ዝርዝሩን ያገኘሁት አሁን በቅርቡ ነው።እስካገኘው ድረስ  አገራችን እንደዚህ ያለ የኤሌክትሪክ ሃይል አመንጭና ባለቤት መሆኑዋን አላውቅም ነበር።ሕዝቡም ቢሆን አለማወቁን ከገለጽኩላቸው ጥቂት ሰዎች ለመረዳት ችያለሁ።

ምንም እንኳን ለኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ መሰራት እንዳለበት ባምንም፤ለሕዝቡ ጥቅም ካልዋለ ከንቱ ነው እላለሁ።ጎን ለጎንም እስከ አሁን ድረስ በአገር ውስጥ ጥቅም ሳይሰጡ በከንቱ  የሚፈሱ ወንዞችና ጅረቶች ለመስኖ ሥራ ቢውሉ ለእህል እርዳታ የምንዘረጋው የልመና እጅ ይታጠፍ ነበር፣ከሚያሳፍርም ተደጋጋሚ ድርቅ፣እረሃብና ድህነት ለመዳን ይቻል ነበር እላለሁ።ቅድሚያና ትኩረትም  በዚሁ መስክ ቢሰጠው የተሻለ ነው የሚል እምነት አለኝ።

ኢትዮጵያውያንም እውነት ላገራችን እድገትና ለሕዝቡ ኑሮ መሻሻል የምናስብ ከሆነ፣ነዋሪውና መስራቹ ሕዝብ የከተማ ባለቤትነቱ በተካደበት፣የመኖር ዋስትና ባጣበት ሁኔታ  በከተማ የድንጋይ ቤት ሰርቶ በማከራዬት ገንዘብ የመሰብሰቡን ውድድርና ሩጫ ትተን ወይም ቀነስ አድርገን ገንዘባችንን በሌሎች ልማታዊ እንቅስቃሴዎች በተለይም በእርሻው ዘርፍ ላይ ብናውለውና አገራችን ከምግብ ልመና ብትወጣ   የበለጠ ደስታ ባለቤቶች እንሆናለን እላለሁ።ያንን ሊያስተካክል የሚችለው ኢትዮጵያዊ የሆነ መንግሥትና ተቋም ሲመሰረት ነው። ብዙሃኑን ጥርጣሬና ስጋት ውስጥ የከተተው፣ለተደጋጋሚ አደጋም ያጋለጠው ይኸው የጎሰኞች ስርዓት መኖሩ ነው።

ከአርባ ስድስት ዓመት በፊት በ1966 ዓም እኔና ለውጥ ፈላጊ ጉዋደኞቼ የወታደሩን ክፍል በመንግሥት ላይ አስነሳችሁ ተብለን በታሰርንበት ጊዜ  በእስር ቤት  ባወጣነው “ተነሳ ተራመድ” በሚለው  መዝሙርም ላይ

ወንዞች ይገደቡ ይዋሉ ለልማት፣

በከንቱ ፈሰዋል ለብዙ ሽ ዓመታት።

የሚል የጥሪና ማሳሰቢያ መልእክት ተላልፎ ነበር።

 

ይህንን ጽሁፍ  ካዘጋጀሁት ወራቶች ቢያልፉም በህዳሴ ግድብ እርብርቦሽ ላይ ጥቁር ነጥብ እንዳይጥል፣ ብሎም ግብጽ ለከፈተችው ዘመቻ መጠቀሚያ እንዳይሆን በማሰብ ቢያንስ የውሃ ሙሌቱ ተጀምሮ  መቆም የማይቻልበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ጠብቄ  ለሕዝቡ ለማቅረብ በወሰንኩት መሰረት ይኸው አሁን ለሕዝቡ አቅርቤዋለሁ። ሕዝቡ የአባይን ግድብ ሂደት እለት በእለት እንዲከታተልና ተጠናቆ ሥራው ሲጀምር ቃል የተገባለት እውን እንዲሆንና የሌሎቹንም ግድቦች  የሃይል ምርት እንዲያውቅ፣ ባለቤትነቱን እንዲያረጋግጥና የት ገባ ብሎ እንዲጠይቅ ጊዜው አሁን ነው እላለሁ።ገና ብዙ ግድቦች መሠራት አለባቸው የሚል እምነትና አቋም አለኝ።

ሌላው መነሳት ያለበት ጥያቄ እቅዱ ሲወጣ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ለግድቡ ሥራ ከ80 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር(5-6 ቢሊዮን ዶላር) በላይ እንደሚያስፈልግ  የተገለጸ ቢሆንም ሥራው አሁን ከደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ እንደወጣ የሚመለከተው ክፍል ገልጿል።ከዚያ ውስጥ 13 ቢሊዮን ብር  ከሕዝብ የተሰበሰበ  እንደሆነ  በቅርቡ መግለጫ ሰጥቷል።ታዲያ ይህ ከሆነ ቀሪውከ 100 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነው ከየት መጣ?መልስ ይፈልጋል።የአገር ውስጥ  ወይም የውጭ አገር  ተቋማትና ባለሃብቶች በሽርክና ገብተውበትም ከሆነ ለሕዝቡ ቢገለጽ መልካም ይሆናል።

በተጨማሪ መዘንጋት የሌለበት  ነገር የህዳሴ ግድቡ ያለበት ቦታ  አመራረጥ ብዙ ጥርጣሬዎችን ሊጭር እንደሚችል ከግምት ውስጥ ማስገባቱ ነው። በአገራችን የሰፈነው የጎሳ ማንነት ስርዓት ያዋቀረው የክልል “መንግሥት” ካልተወገደ  በግድቡ ባለቤትነት  ላይ ችግር ሊከሰት እንደሚችል ነው።እንደሚታወቀው ስርዓቱ በክልሎች ቅምር የተሰናዳ ነው።ሕገመንግሥት ተብዬውም የተገንጣዮች ሰነድ ክልሎች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን እስከ መገንጠል ድረስ ያላቸውን መብት ያውቃል።ግድቡ ደግሞ ቤኒሻንጉል በሚባል ከጎጃም ክፍለሃገር፣ከመተክል አውራጃ ተቦጭቆ ህወሃት/ኢሕአዴግ በፈጠረውና በቅርበት ሊቆጣጠረው በሚችለው ክልል ውስጥ የሚገኝ ነው።አሁን ሁሉም ክልል እንኳንስ በውስጡ ያለውን ቀርቶ በአጎራባች ክልል ውስጥ ያለውን መሬትና የተፈጥሮ ሃብት እዬነጠቀ  ለወደፊቱ እመሰርተዋለሁ  ለሚለው አገር እራሱን በማጠናከር፣ ሃብት በመሰብሰብ ላይ መጠመዱ የሚካድ አይደለም። ታዲያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር የኔ ብሎ የተሳተፈበት የህዳሴ ግድብ ህልውና ማረጋገጫው ምንድን ነው? የህወሃት ስትራቴጅም ከግድቡ ምስረታ ጋር ይህንኑ የተከተለ እቅድ እንዳለው ፍንጮች ይጠቁማሉ።ቤኒሻንጉል ብሎ ክልል ሲመሰርት ለኑዋሪው አስቦ እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። ቀደም ሲል ኤርትራን አስገንጥሎ ኢትዮጵያን የወደብ በሮቹን በማሳጣት ትግራይ ትግርኛ የሚል አገር እመሠርታለሁ ብሎ እቅድ እንዳወጣው ሁሉ ይህንንም ቤኒሻንጉልን አስገንጥሎ በፌዴሬሽን ስም ክልሉን በመዳፉ ውስጥ አስገብቶ የለም መሬትና የህዳሴው ግድብ ባለቤት የመሆኑ ፍላጎት እንዳለው መዘንጋት አይገባም፤ በተጨማሪም የአባይን ወንዝና ግድቡን ከውጭ አገር በተለይም ከአረቦችና ከሌሎቹ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ጋር የመደራደሪያ መሣሪያ ሊያደርገው ይችላል።ያንን ተረድቶ እንዳይሳካ ማድረግ ተገቢ ነው።ለዚያ መፍትሔና ዋስትናው በኢትዮጵያ የሰፈነውን የጎሳ ስርዓትና የሱ አካል የሆኑትን ሕገመንግሥት መቀየርና  ክልል የተባለ የልዩነት ግምብ ማፍረስ ነው።ሕዝብ በጎሳ ማንነቱ ሳይሆን በኢትዮጵያዊ ዜግነቱ እንዲያምን ማድረግ ነው።አሁን የሚታዬው የእርስ በርስ እልቂት፣ሰላም ማጣትና ተስፋ መቁረጥ የዚሁ የጎሰኞች ስርዓት ውጤት ነው።አገር ከዚህ በተለዬ መልክ ከተዋቀረ አፈናቃይና ተፈናቃይ፣አሸባሪና ተሸባሪ አይኖርም።በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ተባብሮ በመሥራት ያድጋል፣ይጠቀማል ኑሮው ይሻሻላል።ያ ካልሆነ ግን እርስ በርሱ እዬተላለቀ ከድህነት ሳይወጣ ለውጭ አገር ወራሪ የተመቼ ሆኖ ይቀራል። እንኳንስ ሰው ሰራሽ መብራት ቀርቶ የተፈጥሮ ጸሃይ ብርሃን በነጻነትና በሰላም ለመጠቀም አይችልም።ከዛም በላይ አገረቢስ ይሆናል።

በዓለም አቀፉ ድርጅት የቀረበው  ስዕላዊና አሃዛዊ ዝርዝር ከዚህ በታች ያለውን ይመስላል።

ዝርዝሩ የደበዘዘና ቦታ ላለመውሰድ የተጠጋጋና ያሳነስኩት  በመሆኑ አጉልቶ ለማዬት በሚያስችላችሁ ዘዴ እንድትጠቀሙ ከወዲሁ ላሳስብ እወዳለሁ።

ኢትዮጵያ በነጻነትና በአንድነት ለዘላለም ትኑር!

ያወቁትን ማሳወቅ የደፋሮችና የሃቀኞች ግዴታ ነው!!ዝምታ የፈሪዎችና የሬሳ፣ መናገር የህያው ድርሻ  ነው።

1 Comment

  1. It is good to express what we feel about any desirable things we may see happening ! It is from this perspective that the above piece is appreciable ! But, we at the same time need not to victims of highly emotional and unrealistic way of thinking as we have a very, very and very long and challenging way to go . So, slow down and think critically !

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.