መንጋ ሆይ! እሽ ዓባይስ ያንተ ነው! ዘር ለማጣፋት የታረዱት ዜጎችስ የማን ናቸው?

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ዛሬም የዘር ጪፍጨፋ እየተካሄደ ባለበት ሰዓት ሰልፉ፣ ጩኸቱ፣ ድለቃውና ዘፈኑ “ዓባይ የኔ ነው” የሚል የሞኝ ዘፈን ነው፡፡

ኢትዮጵያዊ “ዓባይ የኔ ነው!” እያለ ነጋ ጠባ ሲወተውት “ከአንገቱ የተቸከለውን ጭንቅላቱን የእርሱ እንደሆነ” ያለመታከት ማስረዳቱ ነው፡፡ ዓባይ ከኢትዮጵያ ልብ እንደ ፍቅር መንጪቶ፣ ትከሻው እንደተቦጀረ ኮርማ እየተጎማለለ ተጉዞ፣ ገደል አፋፍ ሲደርስ እንደ ተሶረፈበት አንበሳ አግስቶ እሳት እየተፋ ሲነጉድ በዓይኗ በብረቷ እየታዬ “ዓባይ የኔ ነው!” እያሉ መደለቅ “እጄ የራሴ ነው!” እያሉ ለማስረዳት እንደ መዘባረቅ ነው፡፡

የዓባይ ጉዳይ የወንጀል መሻፋፈኛ ድሪቶ መሆን ተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ለገሰ ዜናዊ የፈጃቸውንና ያስፈጃቸውን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በቦንድና በግድብ ጎርፍ በማጠብ መንጋውን እንደ መስክ ከበት ነድቶት እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ሆዳም ዘፋኞችንም “ባህር አሻጋሪው ሙሴ”ን እንደዘፈኑለት ያሲያዙትን የማይለቀው ዩ ቱዩብ የሚመሰክር ነው፡፡

“ተመምሩ ደቀ መዝሙሩ” እንዲሉ የለገሰ ዜናዊ ትጉህ ተማሪም ዓባይን የዘር ፍጅት መሸፋፈኛ አድርጎ መንጋውን ድብዳብ እንደ ተሸከመ የጋማ ከብት ይነዳዋል፡፡ ሶስት ሚሊዮን ሕዝብ  እወክለዋለሁ ተሚለው ሕዝብ በወጡ ጪራቆች ሲፈናቀል ዓባይን ያነሳና ወንጀሉን ያጥበዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሚሰራውን የዘር ምህንድስና ለማረሳሳት የዓባይን ስብክት በፓስተር አንደበት ይሰብካል፡፡ የአማራን ልጆች ሲያስር ዓባይን ያነሳና የመንጋውን ልብ እንደ ላም ጡት ያልበዋል፡፡

የለገሰ ደቀመዝሙር የዩንቨርሲቲ ተማሪዎችን በጅቦች አስበልቶ ዜጎችን መጠበቅ አለመቻሉን ዓባይንና ኢትዮጵያን ያነሳና ያጥበዋል፡፡ ጣናን ተእንቦጭ መገላገል አለመፈለጉን የግድብ ዜና ያበዛና መንጋውን ያነሆልለዋል፡፡ በአካባቢ ፖሊስሶች፣ በከንቲባዎች፣ በቀበሌ ጪቃ ሹሞችና በጃዋር መንግስት ሰራዊት የዘርና የሃይማኖት ማጥፋት  ወንጀል ሲፈጠምም ዓባይን ያነሳና ተዓይኑ ጆሮውን የሚያምነውን ቀንድ የለሽ መንጋ አስረሽ ምቺው ያስደልቀዋል፡፡ መንጋው እንዳይደራጅና ራሱን እንዳይከላከል እያዘናጋ የዘር ፍጅቱን እንደ ተሸፈነ ቁስል ተቀን ወደ ቀን እየከፋ እንዲሄድ ያለባብሰዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ክህደትና ድጋፍ መንሳት- የፖለቲከኞች መሰሪ ስልት - ይገረም አለሙ

መንጋ ሆይ! እሺ ዓባይስ ያንተ ስለሆነ “ዓባይ የኔ ነው እያልክ ጩህ! በአካባቢ ፖሊሶችና ገዥዎች ተባባሪነት በየጊዜው በዘሩና በሃይማኖቱ ምክንያት የሚጨፈጨፍው ዜጋስ የማን ነው? ዓባይ የኔነው ብለህ በጮህበት ላንቃህ “የሃይማኖትና የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈጠሙት ለፍርድ ይቅረቡ!” ብለህ ለእግዚአብሔርም ሆነ ለዓለም ችሎት የምትጮኸው መቼ ነው? አገዛዙ የዘር ጪፍጨፋን ችላ በማለቱና ባላመስቆሙ ጉርንቦውን የምትይዘው መቼ ነው?

መንጋ ሆይ! ነገም ከማታጣው ዓባይ ይልቅ ተመልሶ የማይመጣውን ክቡር የሰው ህይወት የምታስቀድመው መቼ ነው?

መንጋ ሆይ! እሽ ዓባይስ ያንተ ነው! ዘራቸውን ለማጥፋት በመደዳ የታረዱት አማራዎች፣ ጉራጌዎችና ጋሞዎችስ የማን ናቸው? “ነፍጠኛ ውጣ!” እየተባሉ በገጀራ የታረዱት አማራዎች የማን ናቸው? “ኦርቶዶክስ ውጣ!” እየተባሉ በሰይፍ የተቀሉት ክርስትያኖች የማን ናቸው? “አማራ ውጣ!” እየተባሉ በስለት የተዘለዘሉት እርጉዞችና አዛውንት የማን ናቸው?

A piece of evidence about the current genocide while the herds are dancing “Abay is mine”: https://www.youtube.com/watch?v=kgZLz1XsudU

 

ሐምሌ ሁለት አስራ ሁለት ..

 

 

8 Comments

  1. ሀሳብህን እደግፈዋለሁ ነገር ግን የተዋጣለት አላማ ሌላ ነው አላማውን አያስትም ወይ?

  2. እሺ የዘር ጭፍጨፋ አለ ነገር ግን ጭፍጨፋው አማራና ኦርቶዳክስን ኢላማ ያደረገ ብቻ ነው ማለት ይሄም መርዘኛና ጠርዘኛ አስተሳሰብ ነው!!!

  3. የመንጋ እይታ የራስን አስተሳሰብ ይነጥቃል። ያው ስልጠና ላይ እንዳለ ወታደር ወደ ቀኝ ሲሉት መዞርና ባለህበት ሂድ ሲባል እዚያው መርገጥ አይነት ነው። በዚህ አስተሳሰብ ላይ የዘርና የቋንቋን ብሎም የሃይማኖትን እይታ ሲታከልበት ጭራሹን ብርሃን አልባ አድርጎ በጠራራ ጸሃይ ደንበር ገተር ያስኛል። የሃበሻው ፓለቲካ እንዲህ ነው። ግድቡን በተመለከተ አያሌ ቀሪ ነገሮች አሉ። መዝፈንና መጨፈሩ መብራት አመንጭቶ ቤታችን ሲደርስ ቢሆን እሰየው በሆነ። አሁን የሚደነፉብን እልፍ ጠላቶች አሉብን። በዚህም ላይ የአሜሪካው መሪ ሃሳብ ሲጨመርበት ክራራይሶ ያሰኛል። መሪው ዛሬ ያሉትን ነገ የሚያፈርሱ፤ ሁልጊዜ በአለም አንደኛ ነን እያሉ የሚፎክሩ፤ ውሳኔያቸው ስሜታዊና ቅጽበታዊ መሆኑ የሃገራቸውን የወታደር ሃይል ሳይቀር ግራ አጋብቶታል። እናም በአባይ ዙሪያ የሆነውና የሚደረገውን የሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጭ ያሉ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ድጋፍና ፍልሚይ በጽሞና አይቸዋለሁ። ግብጽ ያው እንደተለመደው ተጨፈኑና ላሞኛችሁ ነው ስራዋ። እንግሊዞች ለራሳቸው የጥጥ ማሳ ፍጆታ በተመኑት የውሃ ፍጆታ ዛሬም እንዲያው ልቀጥል ማለቷ የአለምን የፓለቲካ አሰላለፍና እምርታ አለመረዳት ነው። ግብጽ ለኢትዮጵያ ተኝታ አታውቅም። ዛሬም አትተኛም። አሁን ጦርነት አንፈልግም ያለው አልሲሲ በሊቢያ ከቱርክ ጋ ከተላተመና የሳይናይ በረሃ ከበረቱበት ዲሞክራቲክ በሆነ መንገድ የተመረጠውን አፈር መልሶ አሁን እኔ ነኝ የግብጽ መሪ ያለው አል ሲሲ ከሃበሻ ጋር መላተሙን አልወደደውም። የሱዳን/የደቡብ ሱዳን/የኤርትራን/ የሱማሊያን ወዘተ እርድኝ ጠይቆ ለጊዜው ተነፍጓል። አሁን የቀረው ወያኔን መጠቀምና ከሶማሊያ የተገነጠለችውን ሶማሊያ የጦር ሰፈሩ በማድረግ ሃገርን ማሸበር ነው። ለዚህም ሥራው የኦሮሞን ህዝብ ነጻ እናወጣለን የሚሉ ሙታኖች በወለጋ ወገናቸውን እየገደሉ ነው። እንዲህ ነው እንግዲህ ጉዳዪ!
    ያበዱ ኦሮሞዎች መንገድ ዝጉ፤ እንጀራ አትብሉ፤ ነፍጠኛን አስወጡ ( ነፍጠኛ ማለት ኦሮሞ ያልሆነ ኦሮምኛ የማይናገሩ ሁሉ ማለት ነው) ለዚህም ነው የታታሪዎች የጉራጌ ወገኖቻችን ቤትና ንበረት በቆንጨራ አንጋች ኦሮሞዎች የጋየው። የኦሮሞ ሴራና ጥላቻ ስር የሰደደ ነው። አባገዳዎች ሳይቀሩ የተሰለፉበት ሴራ ነው። አቶ ለማ መገርሳ ያን ያህል ኩንታል ያክል ስለ ኢትዮጵያ ህዝብና አንድነት ተናግሮ በሚኒሶታ ተመላልሶ በተሰበከለት የጥላቻ ፓለቲካ ነው ለአሜሪካ ድምጽ የኦሮምኛ ክፍል ዝግጅት ክፍል ” እኔ ይህ መደመር የሚባል ነገር አይገባኝ” በማለት ግራና ቀኝ ተናገሮ ከጽንፈኞች ጎን መቆሙን ግልጽ ያረገው። ባይደመር እማ የወያኔን ስልጣን ንክችም ባላረገ ነበር። ግን ያለፈ ነገር ይረሳል አይደል? አሁን የሰው ሃብትና ንብረት እየዘረፉ፤ አንገት እየቆረጡ፤ ቤት እያቃጠሉ፤ በመጠለያ ያሉ (ምስራቅ ሃረርጌና ሌሎች) መጣንባችሁ እያሉ የሚያስጨንቁ የሙታን ስብስቦች ከክልል፤ ከከተማው ባለስልጣኖች ሁሉ ድጋፍ አላቸው። ማን ማን እንደሆኑ የስም ዝርዝር ስጡን መረጃ አቀብሉን ብሎ የተቀበለው ፓሊስ ለተጠቆመው ሰው ሂዶ ወይ ያን ሰው አጥፋ ወይ አንተ ጥፋ ብሎ የሚወሸክት ሙያ የለሽ የዘር ተሰላፊ ፓሊስ ነው። ነገሩ ግራ ያጋባል። የሞተበት ሲያለቅስ ከሚስቅ የሰው እንስሶች ጋር አብሮ መኖር እንዴት ይቻላል?
    በትግራይ ወታደር አሰልፎ መሳሪያ አስታጥቆ ወዮ እያለ ለምን ይህ ሆነ ተብሎ ሲጠየቅ ጮሌዋ የወያኔ ቃለ አቀባይ ውሸት ነው ምንም እንዲህ የሆነ ነገር የለም። ይህ የባንዳዎች ወሬ ነው በማለት አይናቸውን በጨው ታጥበው እዪኝ ስሙኝ ሲሉ ወቸው ጉድ ይህች ሃገር መቼ ነው እውነት የሚናገር ሰው የሚኖርባት ያስብላል። ለመኖር መግደል፤ ማሰር፤ መዋሸት፤ መዝረፈ ሙሉ ሙያ የሆነው በሃበሻው ምድር ብቻ ነው። የትግራይ ልጆች ሁሉ ወደ ትግራይ ኑ እያለ የሚጣራው ወያኔ ለመገንጠል ፈልጎ ለመሆኑ ማሳያዎች አሉ። አዎን ግብጽ የመጀመሪያዋ ሃገር ትሆናለች የትግራይን መገንጠል ለመቀበል። ግን በትግራይ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ከአሁኑ መገመት ይቻላል። ምርጫ አረጋለሁ ብሎ ሃተፍ ተፍ የሚለው ወያኔ ምርጫው እንደ ሻቢያው የመገንጠል ምርጫ (ባርነት ወይስ ነጻነት) ብቻ ነው ምርጫው። አሁን ማን ይሙት ሰው ፈታ ብሎ በራሱ አስቦና ገምቶ በትግራይ ውስጥ መምረጥ ይችላል? ጭራሽ! የትግራይ ህዝብ ነጻ ምርጫ ተሰቶት አያውቅም። እኛ እናውቅልሃለን በሚሉ የመንደር ልጆች መሪነት ፍዳ ሲቆጥር እልፍ ዘመን ሆነ። ግራ ያጋባል? የነጻነት መመዘኛው ምንድን ነው።
    ጠ/ሚር አብይ በትግራይ ሁኔታ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሊሰጡ ይገባል። የእርሳቸው መንግስትን አቋምና የወያኔን ሴራ ቁልጭ አርገው ለትግራይ ህዝብ ማስታወቅ አለባቸው። አሁን በወለጋና በአዲስ አበባ ከግብጽ ስልጠና ወስደው፤ ወይም ወያኔ አስልጥኖ የላካቸውን ይዘናል እየተባለ ይወራል። ከሆነ እውነትነት ባለው መልኩ የትግራይ ህዝብ የወያኔን የሃገር ማፍረስ ዘመቻ ሊነገረው ይገባል። የጠ/ሚሩ መንግስት ዝምታ ወያኔ ለሚያደርገው የጦርነት ፕሮፓጋንዳ ይጠቅመዋል። ጠ/ሚሩ በማያሻማ ሁኔታ ያለውን ለኢትዪጵያ ህዝብ በተለይም ለትግራይ ህዝብ ማሳውቅ ግዴታቸው ነው። ወያኔ በሃውዜን እንዳስጨረሳቸው ንጽሃን ዜጎች አሁን በዚህና በዚያ ቦንብ እያፈነዳ፤ ሰው እየገደለ ሻቢያ ነው፤ አማራ ነው፤ ተከበሃል፤ ተነስ ማለቱ አይቀሬ ነው። ለወያኔ ሞት የኮረሪማ ንግድ ነው። እነርሱን አይነካምና! የትግራይ እናቶች ባለፈው ጉዳታቸው አልቅሰው አልጨረሱም። ዛሬ የጦርነት አዋጅ ማወጅ የወያኔን እብደት ያሳያል። እናስተውል። ትንሽ እሳት ሃገር ያቃጥላል። እብደታችን ይቁም። ትግራይም ሆነ ሌላው የሃገሪቱ ክፍል እፎይ ይበል። እናንተ ቄሮዎች እንጀራ እንዳትበሉ የተባላችሁም ብሉ። እዚህ እነርሱ ሃበርገራቸውን እየገመጡ ነው የድሃ ልጆችን የሚያገዳድሉት። ለኦሮሞ ህዝብ መብትና ነጻነት የሚታገል ኦሮሞን አይገድልም። የጎረቤቱን ቤትና ንብረት አይዘርፍም። የጃዋርና የበቀለ ገርባ ፓለቲካ በህዝቅየል ገቢሳ የጫት የሂሳብ ስሌት የተቀመረ ነው። ሁሉን የሚያደነዝዝ። እንደዛ ስለሆነ ነው ዶ/ር መራራ ሳይቀሩ ከሙታን ጽዋ ጨላጭ ያረጋቸው። አይጣል። ስንቶችን የበላ ፓለቲካ ዛሬም ሌሎችን እንዲበሉ ከሩቅ መንገድ ያዘጋጃል። አበስ ገበርኩ። እንዲህም ብሎ የነጻነት ታጋይ የለም። እንጀራ እንዳትበሉ የሚሉ ገጀራ አንጋቾች! በቃኝ!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.