ግልጽ ደብዳቤ ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ – ተመስገን ተከተል    

abiyግራ የሚያጋቡ ጉዳዮች ይጥሩ

ከሰሞኑ በተፈጠረው የአሸባሪነት ተግባር ማለትም በድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያና ተያይዞ በተፈጠረው ግርግርና ሁከት እንዲሁም የንብረት ውድመትና የሰው ሕይወት መጥፋት ከፍተኛ የልብ ስብራትና ሀዘን እንደተሰማኝ መግለጽ እፈልጋለሁ። ድርጊቱም አሳፋሪና በሌሎች ዘንድ አንገት የሚያስደፋ ክፉ ተግባር ነው። ከዚህም የተነሳ አሁን የተጀመረው የህግ በላይነት የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሙሉ ተስፋ አለኝ።

የዚህ ደብዳቤ ዋና ዓላማ ከድምጻዊው ግዲያ ጋር የተያያዙ ነጥቦችን ለማተት ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በታችኛው አመራር ዕርከን አንዳንዴም በላኛው አመራር አካላት ደረጃ የሚታዩና ጥርስ ያገጠጡ እንዲሁም በየጊዜው የሚዘመርለት የመልካም አስተዳደር ችግሮች፥ የአሰራር ዝንፈቶች፥ የዘረኝነት አመለካከቶች፥ የጥፋት ተልዕኮዎችና ጣራ የረገጡ ማን አለብኝነቶች ምክንያታቸው ምን እንደሆነ በዚህ አጭር ደብዳቤ ለመጠየቅ ፈልግሁ።

ውድ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ዶ/ር አብይ አህመድ!

በኢትዮጵያ ውስጥ ሀብት ለመሰብሰብ የመንግስትና የፖለቲካ አመራር ሆኖ ማጭበርበርና መሞሰን አዋጭ የቢዚነስ ፕላን እንደነበርና እንደሆነም እርስዎም ያጣሉ ብዬ አላስብም። ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል፥ ሰብዓዊና በዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፥ እንደዜጋ በአገሩ ሠርቶና ነግዶ ማትረፍ፥ ተናግሮ መደመጥ፥ “ላም አለችኝ በሰማይ …” ሆኖ መቆየቱ ከእርስዎ የተሰወረ አይደለም። ሟቹ ጠቅላይ ሚ/ር አቶ መለስ ዜናዊ (ጊዜው 1987 ዓ.ም. አከባቢ ይመስለኛል) “ልማት ሁሉ ወደ ትግራይ የሆነው ለምንድን ነው?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “በጦርነት የተጎዳ አከባቢ ስለሆነ ይገባዋል፤እስካሁን ጦርነት እንጂ ልማት አላገኘም” (ቃል በቃል ባይሆንም) ብለው እንደነበር አስታውሳለሁ። በሕወሃት አገዛዝ ከጥቂቶች በስተቀር እንደ ኢትዮጵያዊነታችን ሁላችን ስለመጎዳታችን ከእኛው ሌላ ምስክር አያሻንም። ሁላችን የብሔር ብሔረሰብ ፍርጃ ደርሶብናል፥ በሃይማኖት ተበጣጥሰናል፥ ሀብታችንን ተቀምተናል፥ ከቤት ንብረታችን ተፈናቅለናል ወዘተ። ይህ ጉዳት በኦሮሞ ብሔረሰብ ላይ ብቻ የተከሰተ፥ ኦሮሞን ብቻ ያፈናቀለ፥ ኦሮሞን ብቻ የገደለ፥ ኦሮሞን ብቻ ያሰረ፥ ኦሮሞን ብቻ ያሳደደ አልነበረም።

ስለሆነም ኦሮሞ ብቻ ለብቻው እንደተጎዳ የሚወራውና የሚነገረው ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። ኢትዮጵያ በኦሮሞ ብሔረሰብ ብቻ አልተገነባችም፥ በኦሮሞ ብቻ አልለማችም፥ ኢትዮጵያ የሁሉም ብሔረሰቦች ተዋጽኦ ውጤት ነች እንጂ። የለውጡ ሀይል ኦሮሞ፥ የሞተው ኦሮሞ፥ ታሪክ የሠራው ኦሮሞ በሚል ትርክት ቅድሚያ ለኦሮሞ ብሔረሰብና ለኦሮሞ ወጣቶች ተብሎ በየመድረኩ የሚነገረውና የሚሰበከው ወደ ባለተረኛነት እንዳይሆን ፍርሃት አድሮብኛል። ለለውጡ የኦሮሞ ቄሮ፥ የአማራው ፋኖ፥ የጉራጌው ዘርማ፥ የሲዳማው ኤጄቶ፥ የአዲስ አበባ ወጣት፥ (ስም አልወጣለትም)፥ የጎፋው ጎዝዳ፤ የጋሞው ናቶ፥ የወላይታው __ (ስሙ ጠፍቶብኝ ነው) በጋራ ከደም እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ከፍሏል። የአዲስ አበባ ወጣት ከየቤቱ እየተጎተተ ደብዛው ጠፍቷል፤ የአዲስ አበባ ነዋሪ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል። በደርግ ዘመን የነበረው መፈክር “ኢትዮጵያ ትቅደም” ነበር አሁን በብልጽግና ዘመን “ኦሮሞ ይቅደም” እየተባለ መሆኑ አሳዝኖኝና አስገርሞኝ የሆዴን ብሶት መግለጽ ወደድኩኝ።

በህወሃትና ግብረ አበሮቹ ከተዘረፈው መሬት ይልቅ በብልጽግና ፓርቲ የታቀፉና የለውጥ አርበኛ የተባሉ ነገር ግን በውስጣቸው ኦነጋውያን፥ በምግባራቸው ህወሃታውያን፥ በመድረክና በከንፈራቸው ብልጽግናውያን፥ ላያቸው ብልጽግና ውስጣቸው ግን ህወሃትና ኦነግ የሆኑ ድብቅ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚጥሩ ሹማምትና የሰፈር ደላሎች (እዚህ ጋር ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ብሔረሰቦች ያጠቃልላል) የዘረፉት መሬት ይበልጣል። ኡባስ ብሎ “አሁን ተራው የእኛ (የኦሮሞ) ነው” የሚሉ የኦሮሞ ሹመኞች በወረዳና በክፍለ ከተማ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት የተሰገሰጉና በተጭበረበረ ሰነድና  ከላይ እስከታች በጥቅም ተሳስረው የዘረፉትን መሬት የከተማ አስተዳደሩ ያልሰማ ያላየ ስለመሰለኝ ትንሽ ማስታወሻ ብጤ ለመስጠት ፈለግኩኝ። “የአርሶ አደር ልጅ” በሚል ሽፋን ደላሎች ከተለያዩ የአሮሚያ አከባቢዎች የኦሮሞ ተወላጆችን ወደ አዲስ አበባ እያመጡ “ይህ መሬት የአባቴ፥ የአያቴ ነበር፥ ነው” እንዲሉ በማድረግ  የሚፈጽሙትን የመሬትና የኮንዶምኒየም ቤት ወረራና ቅሚያ የከተማ አስተዳደሩ ያላወቀ ያልተረዳ ከሆነ ሹክ ለማለት ወደድኩኝ። በህወሃት ወይም በዘመነ ኢህአደግ ወደ መሬት ባንክ የገባና ካሳ የተክፈለበት መሬት ተብሎ የነበረው አሁን ምክንያቱ ባልታወቅ መንገድ በቡድን ተደራጅተው የሚዘርፉትን መሬት የከተማ አስተዳደሩ ያልደረሰና የተሰወረ ከሆነ ቁጥጥር እንዲያደርግ ሀሳብ ለመሰንዘር አሰብኩኝ። ትናንት ከዩኒቨርሲቲ ምረቃ በኋላ የመንግስት ሥራ ፍለጋ ስንከራተት የነበረ አንድ ወጣት በተቀጠረ በስድስት ወሩ ከሠላሳና አርባ ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት የሰበሰበው የሻኪሶን ወይም የቤንሻንጉልን ወርቅ ነግዶ ሳይሆን መሬት ቸብችቦ ነውና ስብዕናቸውን የጣሉን ሕሊና የጎደላቸውን የለውጥ ሳይሆን የነውጥ ሐዋሪያትን የማጣራትና አደብ የማስገዛት ሥራ መሥራት የሚቻል ከሆነ ብዬ ማስታወሻ ማስያዝ ፈለግኩኝ። የአዲስ አበባ ህዝብ ትዝብት፥ ዝምታ፥ ቻይነት፥ ትዕግስትና አቃፊነት እንደ ሞኝነት ወይም እንደ አላዋቂነት ተቆጥሮ ከሆነ ህዝብ አይሞኝም፥ ህዝብ አይሳሳትም፥ ህዝብ አይታለልምና የከተማ አስተዳደሩ አላየሁም አልሰማሁም እንዳይል ወሬ ማቃበል ተገቢ መስሎ ታየኝ።

ወድ የለውጥ ሐዋሪያ የኢፌዲሪ ጠ/ሚኒስትር

ህወሃት የኢትዮጵያን ታሪክ አውድሞ የራሱን ታሪክ ለመሥራት ታሪካዊ ቤቶችን ሲያቃጥል፥ ሐውልቶችን ሲያፈርስ፥ ቅርሶችን ሲያውድም፥ መንገዶችንና ጎዳናዎችን የኢትዮጵያነት ስሜት እንዳይኖራቸው አድርጎ በአፍርካ አገራት ስሞች ሰይሞ አዲስ አበባን ታሪክ አልባ አድርጓታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየመንደሩ፥ በየታክሲው፥ በየመንገድ ጠርዙ፥ በየጎረበቱ “የጊዜ ጉዳይ እንጂ እያንዳንዳችሁን እንለቅማለን፥ የሠራችሁትና የገነባችሁት ቤትም ሆነ ህንጻ የእኛ (የኦሮሞ) መሆኑ አይቀርም” የሚል ወሬ ሲሰማ ይህ ነገር እውነት ነው ብዬ ልጠይቅህ ወደድኩኝ። ይህ ብቻ አይደለም ከድምጻዊ ሀጫሉ ሞት በኋላ ወንዝ ዳሪቻዎች፥ ክፍት መሬቶች፥ ለግብርና የተሰጡ ጊዜያዊ ቦታዎችና በሀይል የታጠሩና የተዘረፉ መሬቶች ሳይቀሩ በሀጫሉ ፎቶ የተጥለቀለቀበት ምክንያት ስላልገባኝ መልስ ፈለግሁ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በአዲስ አበባ በሀጫሉ ስም ትምህርት ቤቶችን፥ መንገዶችን፥ አደባባዮችን፥ ፓርኮችን ሰይመናል እንዲሁም ሐውልትም በስሙ እንደሚቆምለት ነግሮን ነበር። ታዲያ በየክፍለ ከተማውና በየወረዳው ለመሬት ቅሚያና ዝርፊያ የሀጫሉ ፎቶና ፖስተር እንዴት መሸፈኛ ሆነ? ይህም ሳያንስ አንዳንድ ግለሰቦች በተለይም ኦሮሞ ተወላጆች (ኦነግ ይሁኑ፥ የጃዋር ተከታይ ወይም ሸኔ አልታወቀም እንጂ) ሕገወጥ መሳሪያ ታጥቀው ህዝብን ማስፈራራትና ዛቻ መጀመራቸው መንግስት በስውር ፈቃድ ሰጥቷቸው ሳለ እኔ አላወቅሁም ይሆናል ብዬ ማብራሪያ ቢጤ እንድሰጠኝ ፈለግሁ። አሁን ባለው ሁኔታ የመሳሪያ አያያዙ ሲታይ ህገ ወጥነት ሳይሆን እኔ አቅም አንሶኝ አልገዛሁም ይሆናል እንጂ ለሁላችንም ሳይፈቀድ እንዳልቀረ ልቤ ጠርጥሯልና ካልሆነ እታረማለሁ መላሽ ፈልጋለሁ።

የኦሮሚያ ፖሊሶች፥ የወረዳና የክፍለ ከተማ አመራር አካላት በሌሎች ብሔረሰቦች ላይ የሚያደርሱት ግፍ፥ የሚፈጥሩት ጫና፥ የሚፈጽሙት አድልዎ፥ የሚያሳዩት ማንአለብኝነት ሀይ ባይ አጥቷልና ምናልባት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልሰሙም ከሆነ ትንሽ ወሬ ሹክ ልበል ብዬ ነው። ወንጀል የፈጸመ አንድ ኦሮሞና አንድ ንጹህ የሆነ ሌላ ብሔረሰብ ፖሊስ ጣቢያ ብደርሱ ያለ ጥያቄ የሚደበደበውና የሚታሰረው፥ ያለጥፋቱ የሚወንጀለው ሌላ ብሔር የሆነው ግለሰብ ነው። እባክዎትን የዚህ ምስጢር አልገባ ብሎኛልና መልስ እሻለሁ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌላው ግራ የገባኝ “ለውጥና ነውጥ” ለይተው የማያውቁ ሹማምት በየክፍለ ከተማውና በየወረዳው መሾማቸውና መከማቸታቸው ነው። ላለፉት ሁለት ዓመታት ለውጡ ወደ ታችኛው እርከን አልወረደም ብለን የምንጮኸው አልተሰማም። ይህ ብቻ አይደለም ሌላው ቀርቶ በሚኒስትር ማዕረግ የተሾሙም ቢሆኑ ለውጡ አልገባቸውም። የህወሃት አመራር ተመልሶ ይመጣል ብለው የሚጠብቁ ብዙ እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች የታዘብኩት ብዙ ነው። በተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እስከአሁን ለውጥ ያልመጣውና “ከእጅ አይሻል ዶማ” የሆነውም ለዚህ ነው። ሙስናና ብልሹ አሰራር ጫፍ የረገጠውና አቤት ሲባል ፊቱን የሚያዞርና መብቱን በገንዘብ የሚገዛ ዜጋ የበዛው ለዚህ ነው። ሌላው ይቅርና ውሃን የመሰለ ነገር ለህብረተሰቡ ለማቅረብ የአዲስ አበባ ከተማ ዉሃና ፈሳሽ አገልግሎት ባለስልጣን ያልቻለው ለዚህ ነው። በሳምንት ወይም በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ውሃ ለህብረተሰቡ በፈረቃ ይለቀቃል። በየመንደሩ የተደረደረውን ቢጫ ጀርካንና ውሃ የሚጠብቀውን ሰው ብዛት ማየት ለችግሩ በቂ ማሳያና ማስረጃ ነው። አንድ ግለሰብ ውሃ ለማስገባት ብፈልግ ከ30 እስከ 40 ሺ ብር (እንደ አከባቢው ሁኔታ የሚጠየቀው ብር ይለያያል) መጠየቅ የተለመደ ተግባር ሆኗል። በየሰፈሩ ያለው የደላላ ብዛት ከተማዋን መንግስት አልባ አስመስሏታል፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ያለደላላ የወረዳም ሆነ የክፍለ ከተማ አመራር አካላት ምንም መሥራት የማይችሉበት ደረጃ ደርሷልና እባክዎትን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይጠየቅልን።  በለውጥ ሰበብ ነውጥ የሚያስነሱ፥ ክፍት ቦታዎችን የሚያሳጥሩ፥ መሬት የሚሸነሽኑ፥ በሀሰት ሰነድ ካርታ የሚያወጡ፥ ማፊያዎችን የሚያደራጁ፥ ሰዎችን እያስፈራሩ ጉቦ የሚቀበሉ፥ የቢሮ ሥራ ትተው በየመንደሩ እየዞሩ ገንዘብ የሚሰበስቡና ከደንብ አስከባሪዎች ጋር በመመሳጠር ሕገወጥ ግንባታ የሚያስፋፉ፥ ለህገወጦች ከለላ የሚሰጡና ህዝብን የሚያሸብሩ አመራር አካላት መብዛት ከሁለት ዓመታት በፊት ለ27 ዓመታት በፍርሻና በማፈናቀል የታወቀውን የህወሃትን አሰራርና የግብረ አበሮቹን ምግባር አስታወሰኝና አሁን ያለነው በለውጥ ሂደት ውስጥ ነን ወይስ በነውጥ?

በእውነቱ ሪፎርም አለ ወይ? ሪፎርም በወሬ ይመጣል ወይ? አሁን እየተሠራ ያለውና በዓይናችን የሚናየው የስም ለውጥ መኖሩንና የቀድሞው ስም አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሪፎርም መቀየሩ እንጂ።

በሌላ ደብዳቤ እስክምንገናኝ ደህና ሰንብቱልኝ

ተመስገን ተከተል

 

2 Comments

  1. የተከበሩ፣ጠቅለይ፣ምንስትር፣አብይ፣አህመድ፣ሰለም፣ለርሶና፣ለኢትዬጲያ፣ህዝብ፣በሙሉ፣አቀርባለሁ፣ኢኔ፣የአድስ፣እበበ፣ነወር፣ስሆን፣እርሶ፣የመረጡት፣የአድስ፣አበበ፣ከንትባ፣በደንብ፣የምየውቁት፣አልመሰለኚም፣ይህ፣ከንትባ፣በአሥሩም፣ክፍለ፣ከተማ፣የሥቀመጠቸውና፣እስከታች፣መወቅር፣ድረስ፣የእድስ፣አበበ፣ነወር፣እየስለቀሱት፣እስከመቼ፣ነው፣ዝምብለው፣የምየዩት።የዝህን፣መልስ፣ከጋኛሁኝ፣በደሉን፣ዝርዝር፣አቀርባለሁ፣አድነቅዋት፣ነኝ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.