መንግሥት የውጭ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ኩባንያዎች እንዳይገቡ ወሰነ!

117003647 619705011927076 202118003994250419 n መንግሥት የውጭ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ኩባንያዎች እንዳይገቡ ወሰነ!
በመካሄድ ላይ ባለው የቴሌኮም ዘርፍ የለውጥ ትግበራ፣ የውጭ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ኩባንያዎች እንዳይገቡ መንግሥት እንደወሰነ ታወቀ፡፡የቴሌኮም ዘርፍን ገበያ በመክፈት የውጭ ኩባንያዎች እንዲገቡ ለመፍቀድ መንግሥት በዝግጅት ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡የቴሌኮም ዘርፍ የለውጥ ትግበራ ሁለት ክፍሎች አሉት።የመጀመርያው በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመራው ለ126 ዓመታት በብቸኝነት የቴሌኮም አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው በአፍሪካ አንጋፋው ኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያ፣ 40 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ለውጭ ኩባንያ ለመሸጥ የሚደረገው ጥረት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ሁለት ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው፣ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት የሚያስችላቸውን ፈቃድ ለመስጠት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡የለውጥ ትግበራው ቀልባቸውን ከሳበው የውጭ ኩባንያዎች መካከል፣ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ገንብተው የሚያከራዩ ኩባንያዎች ይገኙበታል፡፡እንደ ሞባይል ምሰሶዎች ያሉ መሠረት ልማቶች የሚያከራዩ ኩባንያዎች ኃላፊዎች ወደ አዲስ አበባ ሲመላለሱ ከርመዋል፡፡

ጉዳዩ ባለፉት ዓመታት በቢሊዮን ዶላሮች ወጪ በማውጣት የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች በመላ አገሪቱ ሲዘረጋ የቆየውን ኢትዮ ቴሌኮምን አስቆጥቷል፡፡‹በቂ መሠረተ ልማት ገንብተናል፣ ለሚገቡት ኩባንያዎች አከራይተን ከፍተኛ ገቢ ማስገባት እንችላለን› ያሉት የኢትዮ ቴሌኮም ማኔጅመንት አባላት ያቀረቡትን አቤቱታ መንግሥት ተቀብሎ፣ የውጭ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ኩባንያዎች ላለማስገባት እንደወሰነ ታውቋል፡፡

የ2012 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ የውጭ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ኩባንያዎች እንዳይገቡ እንደተወሰነ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የውጭ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ኩባንያዎች እንዳይገቡ መንግሥት ወስኗል፣ አይገቡም፡፡ የሚገቡት ኦፕሬተሮች ወይ ከእኛ ይከራያሉ ወይም የራሳቸውን ይገነባሉ፤›› ያሉት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ኩባንያዎቹ የኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ምሰሶዎችንና የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮችን መከራየት እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በሊበራላይዜሽን ሒደቱ ላይ ያሉትን ሥጋቶችና ቅሬታዎች በጽሑፍ ለኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን አስገብቶ፣ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሆነ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ባለሥልጣኑ የኢትዮ ቴሌኮምን ህልውና የሚጎዳ አካሄድ ይከተላል ብለን አናምንም፡፡ ነገር ግን ከስምምነት ላይ ያልደረስንባቸው ቀሪ ጉዳዮች አሉ፤›› ብለዋል፡፡በተያያዘ ዜና የኢትዮ ቴሌኮም የንብረት ትመና ሥራ በማከናወን ላይ የሚገኘው ኬፒኤምጂ (KPMG) የተሰኘው ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት፣ ሥራውን በማጠናቀቅ ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡ የንብረት ትመና ሥራውን አጠናቆ ሁለት ዙር ሪፖርት ለኢትዮ ቴሌኮም ማኔጅመንት እንዳቀረበ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ተናግረዋል፡፡በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ አሠራር ሥርዓት ሪፖርት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ኢዜአ

1 Comment

  1. በጣም ጥሩ ውሳኔ ነው እህቴ በርቺ። አየር መንገድና ኢትዮቴሌኮምን የመሰሉ የብዙ አመታት ክህሎትና፣ ልምድ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ማንነት ፣ያዳበሩና፣ከሁሉም በላይ ትርፋማ የሆኑ ወይንም ለመሆን የተሻለ potential ያላቸው፣የመንግስት ድርጅቶችን መሽጥ ፣ ለእኔ ፣ ከታላቅ ይቅርታ ጋር፣በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ፣ሀገር እንደመሸጥ የሚቆጠር ምህረት የማያስጥ የክህደት ተግባር ነው። በዚህ ረገድ የሌሎች liberalize ያደረጉ የአፍሪካ ሀገሮች ልምድ የሚያሳየው መልካም ዜና አይደለም፣ እስቲ አቶ ክቡር ገና በተደጋጋሚ የሚያስማውን አቤቱታ ስሙት፣ እግዚአብሔር ይባርከውና። በተቃራኒው ያሉ አሻሻጭ አማካሪዎችን እባካችሁ አትስሙ። እነርሱ አሻሽጠው ወደሚሄዱበት ይሄዱና ስለውድቀታችን ደግሞ ፅፈው እንደገና ይበላሉ፣ in modern buisness parlance ‘ ቢዝነስ ‘ ይስራሉ። ወደቅን አልወደቅን ፣ከሰርን፣ አልከሰርን፣ እነርሱ፣ጉዳያቸው አይደለም፣ They won’t hesitate from making money even out of our failers as they are driven by the neo-liberal killer inistinct! ብራቮ ቴሌ በርቱ ። ኢትዮጵያዊት ማለት እንዲህ ነው። እውነት፣እውቀት፣ድፍረት፣ in equal measure!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.