/

ወያኔና አማርኛ – ዶር. ኀይሌ ላሬቦ

haile larebo
ዶር. ኀይሌ ላሬቦ

በቅርቡ የቀድሞው የመረጃ [ኢንፎርመሺን] መረብ ደኅንነት ወኪል (ኢንሳ) ዋና ሥራአኪያጅ የነበረው ደጃዝማች [ሜጀር ጀኔራል] ተክለብርሃን ወልደአረጋይ ለአንድ ሬድዮ ጣቢያ በሰጠው ቃለምልልስ [ለመስማት ከፈለጉ በዚህ ድረገጽ አድራሻ https://www.facebook.com/seid.yimer.9210/videos/2657909104444913/ ይመልከቱ።] የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ [ሕወሓት] በመባል የሚታወቀው የፖለቲካ ግንባር ኅቡዕ ዓላማ ምን እንደነበር፣ ለምንስ ወደበረሃ እንደገባ ግልጥ ከማድረግ ባሻገር፣ ስለአማርኛም ቋንቋ ያለውን ጥልቅ ጥላቻውን አካፍሎልናል። የሕወሓት ኅቡዕ ዓላማ ነበር በመባል የተነገረልን ኢትዮጵያን አፍርሶ ትግራይን የመገንባት ጉዳይ ሲሆን፣ ይኸም ባንዳንድ ጐራ እንደድብቅ ሁኖ ይታሰብ እንጂ የግንባሩን ጥንተመነሻ ለሚያውቅ ሁሉ ግልጥ እንጂ ሥውር አልነበረም። የዛሬው ጽሑፌ የሚያተኩረው በግንባሩ ዓላማ ላይ ሳይሆን፣ ደጃዝማቹ ከቀባጠራቸው የተለያዩ የፍሬከርሥኪ ንግግሮች በልጅነቴ “አማርኛ በመማሬ ያጠፋሁት ጊዜ ይቈጨኛል” በሚለው ላይ ነው። ደጃዝማቹ ይኸንን ሊናገር የበቃው፣ አሁን ብዙዎች ኢትዮጵያ በወያኔ ቅኝ ግዛት ሥር ነበረች ብለው በሚያምኑበት ወቅት፣ የድርጅቱ አባላት በፈጸምነው ዘረፋና ዐመፅ እንጠየቅ ይሆናል ብለው ሠግተው ከአዲስ አበባ ሸሽተው እየተንፈላሰሱም እየተርበደበዱም ከሚኖሩባት ቀሳ ቢጤ ከገቡበት ከመቀሌ ምሽግ ውስጥ ሁኖ ይመስለኛል።

ወያኔዎች በአማራና በአማርኛ ላይ ያላቸው ጥላቻ ሥርየሰደደ እንደሆነ የአደባባይ ምሥጢር መሆኑ አይካድም።ደጃዝማች ተክለብርሃን የመረጃ ተቋም ሥራአስኪያጅ በነበረበት ወቅት፣ በሙስና ከተዘፈቁ ዋኖቹ የወያኔ ባለሥልጣናት አንዱ እንደነበረ በየቦታው ይወራል። ይሁንና ለዚህ አገርዐቀፍ ሹመት ካበቁትም መስፈርቶች፣ ዋናውም ባይሆን አንዱ፣ የገዛ መንደሩን ቋንቋ [ከዚህ በኋላ “ዘይቤ” እለዋለሁ] ማለትም “ትግርኛ”፣ ወይንም በወያኔ ዘመን “የሥልጣኔ” አመልካች እንደሆኑ በሚቈጠሩት ባንዱ በምዕራባውያን ቋንቋዎች፣ በተለይም በ“እንግሊዝኛ” መናገር በመቻሉ ሳይሆን፣ “መማሬ ይቈጨኛል” በሚለው አገርበቀል በሆነው ብሔራዊ ቋንቋ ማለትም በ“አማርኛ”ችን አሳቡን ጥርት አድርጎ ለጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመግለጥ በመብቃቱ እንደሆነ አይጠረጠርም። አለበለዚያ፣ በትንሽቷ ትግራይ ውስጥ እንደዛሬው ተወሽቦ ከመቅረት ውጭ ወዴትም አይደርስም ነበር ብል የተሳሳትሁ አይመስለኝም። ይኸ ብቻ አይደለም። በትግራይ ተወስኖ ቢቀር ደግሞ እምብዛም ጥቅማጥቅም ባላገኘ። ይኸም ማለት፣ ከትውልድ ዳራውም ሆነ ከትምህርት ዕውቀቱና ደረጃው አኳያ ሲታይ አሁን ለደረሰበት ክብርና ማዕርግ የመድረስ ዕድሉ የመነመነ ነበር ብቻ ሳይሆን፣ ብዙዎቻችንም ቃለምልልሱን ለመስማት ምናልባት ፍላጎትም ዝንባሌም፣ ችሎታም ባልኖረን። ስለዚህ በኔ አስተያየት፣ ይኸንን ሁሉ ጥቅም ካገኘ ግለሰብ፣ አማርኛን “መማሬ ያኰራኛል” ከማለት ይልቅ “ይቈጨኛል” የሚለው ንግግር የሥነልቦናና የማንነት ቀውስ ከሚያጠቃው እንጂ፣ በሱ ደረጃ ካለ ሹም ከቶውኑ መሰማት የሚገባ አልነበረም።

ያም ሁኖ፣ በፊት እንደገለጥሁት፣ “አማርኛ”ን መጥላት ለወያኔ አዲስ ነገር አይደለም። ምንም ዐይነት ኅቡዕነትም አለው ማለት አይቻልም። የአማርኛንም ጥላቻ በግልጽ በማስተጋባት ደጃዝማቹ ከወያኔ አባላት መካከል የመጀመርያው አይደለም። ቋንቋውን በጥራት በማወቃቸው እንደደጃዝማቹ ለወግና ለማዕርግ ከበቁት፣ ሁኖም ግን እንደሱ ጥላቻቸውንና ንቀታቸውን እየነዙ ከሚሄዱት መካከል በርካታዎችን መጥራት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል፣ የአዲስ አበባ ዩኒቬርሲቲ የፍካሬመለኮት የዲፕሎማ ምሩቅ እንደሆነ የሚነገርለት መምህር ገብረኪዳን ደስታ ከነዚህ አንዱ ነው። መምህር ገብረኪዳን የተደላደለ ኑሮ ለመኖር የበቃው በጐንደርና በአክሱም የአማርኛ መምህር በመሆን ነው። በአክሱም በሚያስተምርበት ወቅት ወደበረሃ ሄዶ ወያኔን ተደባለቀ። ግን ኑሮውን ስላልቻለ፣ ዓመት እንኳን ሳይሞላው ወደደርግ መንግሥት ኮብልሎ በመግባት “ሕወሓቶች ዋጋ የላቸውም አትከታተሏቸው” እያለ ስብከቱን አሰራጨ። ይኸንንም ዐይነት ከፍተኛ ቅስቀሳ ሲያካሄድ ብዙ እንዳስገደለና እጁን ደም በደም እንዳጨማለቀ በሰፊው ይወራበታል። ኋላም የቀዬው ልጆች ማለትም የዱሮ የበረሃው ጓዶች በትረመንግሥት ሲጨብጡ፣ እሱም ተመልሶ ለወያኔ ዐደረ። የተካነው በፖለቲካ ወረት እንደመሆኑ፣ ጥንት በካዳቸው ጌቶች ዘንድ ግርማና ሞገስ ለማግኘት ሲል ያልፈነቀለው ድንጋይ፣ ያላስተናገደው ውሸት አልነበረም ሲባል ይወራል። አለሙያው ገብቶ የታሪክ ዐዋቂ በመምሰል፣ በአህያ ቢጭኑት እንኳን የሚከብድ እምቢታ አንፃር ወረርቲ፤ ታሪክ ሃፀይ ዮሐንስ 4ይ ንጉሠነገሥቲ ዘኢትዮጵያ የተባለ ባለሰፋፊ ገጾች መጽሐፍ በትግርኛ ጻፈ። በደራሲው አንደበት እንግለጠው ከተባለ፣ መጽሐፉ የተጻፈበት ዋናው ምክንያት “እውነታውን ፍርጥ አድርጎ በመናገር የተጣመመውን የኢትዮጵያን ታሪክ ለማቃናት፣ የተዛባውን ለማስተካከል” ነበር። ይሁንና ይኸንን ከፍተኛ ግብ ለመምታት ከፍተኛ ሥልጠናና ዝግጅት የሚፈለግ ሲሆን፣ ከመምህር ገብረኪዳን ይኸንን መጠበቅ ራስን አላስፈላጊ መደለል እንደሆነ ግልጥ ነው። የትምህርት ደረጃውና መስኩም ሆነ የሕይወት ዳራው አይፈቅዱለትምና። መጽሐፉ በግሁድ የሚያሳየን ነገር ቢኖር፣ ለፖለቲካ ፍርፋሪ ሲባል፣ እውነት የተጨፈለቀበት፣ ታሪክ የተዛነፈበት፣ ሐቀኛነት የተቈላመመበት የጭፍን ወገንተኝነት ትርክት መሆኑን ብቻ ነው።

መጽሐፉ ፕሮፖጋንዳ በጠማቸው የቀዬው ተወላጆች በሆኑት ባለሥልጣናት ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት አትርፎለታል ብቻ ሳይሆን፣ እነሱም በምረቃው ተገኝተው በተለመደው የውዳሴ ጋጋታቸው የጓጓውን ዕውቅና ሊሰጡት በቅተዋል። ለመጽሐፉም ሆነ ለደራሲው ዋጋ የሰጠ ግን እምብዛም አልነበረም። ያኔ ነው እንግዴህ በርካታ አንባቢ ሊያገኝ ሲል፣ በፊት “በማወቄ ይቈጨኛል” ሲል በተናዘዘው አማርኛ መተርጐም እንዳለበት ሳያፍር የገለጠው። ይኸ ዐይነት አጣብቂኝ የገጠመው እሱ ብቻውን አይደለም። ሌሎችም ብዙዎች አጃቢዎች አሉት ማለት ይቻላል። ከነዚህ መካከል፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ጉጅሌ ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ እንደምሳሌ ሊወሰድ ይቻላል። ኦሮሞኛ ከማይናገር ባለጉዳይ ዕቃ እንዳትገዙ ሲል ለደቀመዛሙርቱ የቸረውን ምክር ረስቶ ወደኦሮሞኛ የተረጐመውን መጽሐፍ ገዢ ሲያጣ፣ እሱም በበኩሉ ለሰፊ ገበያ ሲል ወደአማርኛ መተርጐም ይኖርብኛል ማለቱ አልቀረም። ይኸ ሁሉ የሚያሳየን፣ ወደድንም ጠላንም አማርኛ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊነታችንም መግለጫ ነው ብል ስሕተት አይመስለኝም፤ ቀጥለንም የምናየው ጉዳይ ይሆናል።

የወያኔ የአማርኛ ጥላቻቸው ቋንቋውን በጅልነታቸው “አማራ” ከሚል ብሔረሰብ ጋራ በማያያዛቸው መሆኑ አይካድም። ዛሬ የወያኔ መሪዎች የቆዳቸውን ቀለም በመለወጥ፣ በረሃ የገባነው “የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነትና የራስን አስተዳደር በራስ የመወሰን መብት” የሚል ዓላማ አንግበን ነው ቢሉም፣ እውነቱ በአገራችን አቈጣጠር በ1968 ዓም ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ በማያፋልም መንገድ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል። ይኸ ሰነድ፣ ወያኔን ለትግል ያነሣሣው “ቄሣራዊነትን [ኢምፔርያሊዝም]፣ ባላባታዊ ሥርዐትንና [ፌውዳሊዝም] የአማራ ብሔረሰብ ጭቈናን” ለመዋጋት ነው ይላል። የትግሉም ዓላማና ተግባር ደግሞ፣ “ከነዚህ ሦስቱ ነፃ የሆነ የትግራይ ሬፓብሊክ ማቋቋም ይሆናል” ሲል ፍርጥ አድርጎ አስፍሯል። ስለዚህ የድርጅቱ መግለጫ፣ ጨቋኞች ብሎ በግንባርቀደም ጠላትነት ከፈረጃቸው ሥላሴዎች መካከል አንዱ የ”አማራ ብሔር’ ነው።
እዚህ ላይ ልብ ይባል። ወያኔ ደመኛ ጠላቴ ነው እያለ ያለው አማርኛ ተናጋሪውን መንግሥታዊ ሥርዐቱን፣ ወይንም ገዢውን መደብ ሳይሆን፣ በጅምላ በጭፍኑ“አማራ” ብሎ የሚጠራውን “ብሔር”፣ ማለትም የአማራውን ሕዝብ በነቂስ ነው። አንዱን ብሔር በዚህ መልክ መፈረጅ ራሱ፣ ወያኔዎችን በእኩል ከናዚዎች ጋር ያስመድባቸዋል። ወያኔ “አማራ” ብሎ ሕዝቡን እንደጨቋኝና ጠላት በመፈረጅ፣ በብሔረሰቡ ላይ ጦርነት ያወጀበት ገና በበረሃ ሳለ ነው ማለት ይቻላል። ሌላው ቀርቶ መግለጫው ከክተት ጦር አዋጅ ይለያል ብሎ ለማመን እንኳን ያዳግታል። ድርጅቱ በተግባርም ያሳየው ይኸንኑ ጠባይ ነውና። እንዲያውም በሥልጣን በቈየበት ኻያሰባት ዓመታት ወያኔ ‘ብሔረሰቡን’ የጥቃቱ ኢላማ በማድረግ በሰው ልጅ አንደበት የማይነገር በደልና ግፍ እንደፈጸመበት የሚያረጋግጡ፣ አስተማማኝነታቸው የማያጠራጥር፣ በጽሑፍ የተመዘገቡ፣ በሥዕል የተቀረጹ የውስጥም ሆነ የውጭ አገር ማስረጃዎችና የዐይን እማኞች አሉ።

የወያኔ መሪዎች በተበከለና በመሃይምን አስተሳሰባቸው አማርኛን ከአማራ ብሔር ጋር አስተሳስረው በማየት ቢጠሉትና ደጃዝማች ተክለብርሃንም “አማርኛ”ን በመማር ያጠፋሁት ጊዜ “ይቈጨኛል” ቢል ምንም የሚገርም አይመስለኝም። የሚገርመውስ “እኰራበታለሁ” የሚል ቃል ቢጠቀም ነበር። በግሌ አስተያየት የወያኔ አማርኛን መጥላት የአሳብ ድኽነታቸውን አመላካች ከመሆን በስተቀር ሌላ ፋይዳ የለውም። የቋንቋውን ታላቅነትና ታሪካዊ አገልግሎቱን ያጐለዋል እንጂ አይቀንሰውም። እስኪ በመማራቸው እንደዚህ የሚቈጩት “የአማርኛ” ቋንቋ ምን ያህል ጥንታዊና አኩሪ መሆኑን ጨረፍጨረፍ አድርጌ በጥቂቱ ብገልጥ አንባቢዬን አላሰላቸውም ብዬ አምናለሁ።ገለጻዬን ከቋንቋ ሰብእና እንድጀምር ይፈቀድልኝ።

የማንኛውም ቋንቋ መሠረታዊ ዓላማው የሰውን ልጅ ርስበርስ ማግባባት ነው። የሰው ልጅ በተፈጥሮው ማኅበራዊ ነው። ከዱር አራዊትና እንስሳት የሚለየው ማኅበራዊ እንዲሆን በሚያስገድደው በሥነልቦናው መሆኑ ግልጥ ነው። ማኅበራዊ ግንኙነቱ በሰፋ ቊጥር የሁለንቴናው በተለይም የሥነልቦናው ዕድገቱም ደረጃ በዚያው ልክ እየላቀ፣ እየገዘፋና እየጠለቀ ይሄዳል፤ አለበለዚያ ዕጣፈንታው ልክ ዘሩ ከበቀለበት ሰፈር ዐልፎ ሄዶ ለመንሰራራት እንዳልታደለ ዱባ ይሆናል፤ ማለትም ግለሰቡ በሰውነቱ ቢገዝፍም እንኳን፣ በሥነ ልቦናው ቀጭጮ ይቀራል። አስተሳሰቡና አመለካከቱ እንደማደግና አካባቢውን ለውጦ ራሱን እንደመለወጥ፣ የቀዬው ጠባብ ባህልና ቋንቋ ሰለባ ከመሆን አያመልጥም። በተቃራኒው፣ ማኅበራዊ አድማሱ በሰፋ ቊጥር የመላ ሰብእናው ዕድገትም በዚያው መጠን፣ ከዚያም በበለጠ፣ ሊፋፋ ይችላል። አሁን መላይቷ ዓለም አንድ ትልቅ መንደር እየሆነች ባለችበት በኻያአንደኛ ዘመን ደግሞ የቋንቋ ጥቅሙ ዘርፈብዙ ነው። ቋንቋ፣ የበለጠና የተሻለ ዕውቀት ለመገበየት፣ የገዛ ራስን ጥቅም ለማራመድ፣ ዕድል ለማስፋት፣ ግንኙነት ለማጠናከር እጅግ በጣም ይረዳል። ስለዚህ ማንኛውንም ቋንቋ ማወቅ ይረዳል እንጂ በምንም መልክ አይጐዳም ብል ስሕተት ያለበት አይመስለኝም። በታሪክ የሰው ጠላት ሊኖር ይችላል፤ አለምም። የቋንቋ ጠላት ግን የለም፤ ሊኖርም አይችልም። ለዚህ አባባሌ እንደማስረጃ አንዳንድ ምሳሌዎችን ልጥቀስ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  መታሰር ምንም ማለት አይደለም። አስሮ ሰብአዊ መብትን መጣስ ግን የትም ሀገር የለም! ከአጥናፍ ብርሃኔ

ከሮማውያን ቀደም ብለው የመጡ ግሪኮች፣ በጊዜያቸው የሚታወቀውን ዓለም ሲገዙ ብዙ ግፍ ፈጽመዋል። እነሱ ሲወድቁ የዘረጉት አፍመፍቻ ቋንቋቸው ግን አብሮ አልወደቀም። ይልቅስ “ሥልጡን” ቋንቋ በመባል፣ በጊዜው እንደዛሬው የእንግሊዝኛ ሚና በመጫወት የአብዛኛው ዓለም መግባቢያ ሁኖ ለማገልገል በቅቷል። ባንድ ቃል የሰው ልጅ ይበልጥ ማኅበራዊ እንዲሆንና፣ ስለራሱና ስለቀረው ዓለም ዕውቀቱን እንዲያዳብር ረድቶታል። ሌላው ቀርቶ የአምላክ ቃል ነው ተብሎ የሚታመነው አዲስ ኪዳን የተጻፈው፣ ብሉይ ኪዳንም ዕብራይስጥን ለማያውቁ ለመጀመርያ ጊዜ የተተረጐመው፣ በዚህ በጨቋኞች ቋንቋ ነው፤ ማለትም በጽርዕ። ከዚህ ግንዛቤ በመነሣት መደምደም የሚቻለው፣ ግሪኮች በተግባራቸው እንደጠላት ቢፈረጁም፣ ቋንቋቸው ግን የሰውን ልጅ በማቀራረብ፣ ዕውቀትን በማቋደስ፣ ግንኙነቱንና የማሰብ አድማሱን በማስፋት፣ የጋርዮሽ ሰንሰለቱንና ዝምድናውን በማጥበቅ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳበረከተ ነው። የጊዜው ሕዝብ አፍኖት ይዞት የነበረውን ጠባብ የጐጥና የጐሣ መንደር ቅርፊት ሰብሮ ወጥቶ በሰፊው ዓለም ዘለል መለል እንዲል አድርጎታል። በዚህ ልክ፣ የሰፊው ዓለም ሕዝብ መግባቢያ በመሆን ጽርዕን በቋንቋነት የተኩት እንደሮማውያኑ ላቲን፣ እንደፈረንጆቹ ፈረንሳይኛ፣ እንደዐረቦቹ ዐረብኛ፣ እንደብሪታኖቹ እንግሊዝኛ ለዚህ ማዕርግና ደረጃ የበቁት፣ ቋንቋዎቹ አፍመፍቻቸው የሆኑት ተናጋሪዎቻቸው ልክ እንደግሪኮቹ ባንድ ወቅት አምባገነንና ጨቋኝ ኀይል ስለነበሩ ብቻ ነው። ስለዚህ ቋንቋ የሚታወቀው በጠቃሚነቱ እንጂ፣ ጨቋኝም መጥፎም በመሆን አይደለም። ሮማውያን፣ ፈረንሳዮች፣ ዐረቦችና እንግሊዞች ቋንቋቸውን ሊያስፋፉ የቻሉት በፍቅር ሳይሆን፣ ሌላውን ወግተው አሸንፈው በማስገበር ነው። እነሱ እንደኀያል ገዢዎችና መንግሥታት ጊዜያቸው አብቅቶ ከሥልጣናቸው ማማ ቢወድቁም፣ ቋንቋቸው ግን ድሮ ከሥራቸው የነበረው የተለያየ ዘይቤ ተናጋሪ ጭቁኑ ሕዝብ ዕውቀት እንዲገበያይበት፣ አሳብ እንዲለዋወጥበት፣ ካገሩ ውጭ ሲሄድ ከሌላው ብሔረሰብ ጋር እንዲግባባ ረድቶታል።

በወያኔዎችና፣ ልክ እነሱን በመሰሉት በአንዳንድ የጐሣዎቻችን መሪዎች ነን ባዮች አእምሮ ውስጥ፣ አማርኛ ተቈራኝቶ የሚገኘው፣ እነሱ “አማራ” ብለው ከሚጠሩት ኅብረተሰብ ጋር ነው ብያለሁ። ይሁንና እንደዚህ የመሰለ አስተያየት ካንድ ፊደል ካልቈጠረ፣ የታሪክን ሂደትና ምንነት ከማያውቅ ግለሰብ ብቻ ነው ሊመነጭ የሚችለው ቢባል ስሕተት አይመስለኝም። ቢሆንም አይገርምም። የወያኔ ባለሥልጣኖች የተማርን የተራቀቅን ነን ባዮች ናቸው። አሁን ወደማይመለስበት አገር ከሄደው ከመሪያቸው አቶ መለስ ጀምሮ እኛ አናውቅም ወይንም የትምህርት መስካችን አይደለም የሚሉት የዕውቀት ዘርፍ አልነበረም። በሁሉም እንደተካኑ ነው የሚነግሩን። ርግጥ ነው በጭፍኑ የሚከተሏቸውን መንጋዎቻቸውን በቊጥር ካላስገባን በስተቀር፣ የድርጅቱ ዋኖቹ መሪዎች፣ ማለትም የርእዮተ ዓለም አሳብ አመንጪዎችና አራማጆች ከመላጐደል መጠነኛ ዘመናዊ ትምህርት የቀመሱ እንደሆኑ አይካድም። ከነዚህ ከተማሩት ትምህርታት መካከል፣ አሁን ላሉበት አስቀኚ ብሔራዊ ማዕርግ ካበቃቸው አንዱና ዋነኛው ልክ እንደደጃዝማች ተክለብርሃን አማርኛን ማወቃቸውና አቀላጥፈው መናገራቸው መሆኑ የማያጠራጥር ሐቅ ነው።

ይሁንና እነሱም ሆኑ አጫፋሪዎቻቸው ኢትዮጵያን በአፄ ምኒልክ ዳግማዊ እጅ ተጠፍጥፋ የተፈጠረች አገር አድርገው እንደሚያቀርቡልን ሁሉ፣ አማርኛንም በንቀት “የምኒልክ ሰፋሪዎች” ቋንቋ በማለት ለማጣጣል ከመሞከር አልተቈጠቡም። ልብ ባይሉት ነው እንጂ፣ የምኒልክ ሰፋሪዎች ልክ የኢትዮጵያውያን ሥልጣኔ ፈርቀዳጆች አባቶች እንደነበሩት አክሱማዋያን ከአንድ አካባቢ ወይንም ብሔረሰብ የመነጩ አልነበሩም። የ”ምኒልክ ሰፋሪዎች” ተብዬዎቹ፣ አማርኛ ይናገሩ እንጂ፣ ከመጡበት ብሔረሰብና አካባቢ አኳያ ካየናቸው፣ ወደሰማንያ ከመቶ በላዩ የኦሮሞ፣ የጉራጌ፣ የትግራይ፣ እንዲሁም የቤኒሻንጉል ኅብረተሰብ አካል ነበሩ። በአንድ ቃል፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በጉልህ የሚያንጸባርቁ፣ የተለያዩ ብሔረሰቦች ስብጥር ሲሆኑ፣ ይናገሩ የነበሩት ቋንቋም የዚህ ስብቅል ገጽታና ባሕርይ ገላጭ ነበር። በጥቅሉ፣ አማርኛ በባሕርዩም ሆነ በአመጣጡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በግሁድ የሚታዩበት መስተዋት ነው ማለት ይቻላል።
አክሱማውያን የጥንት የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ፈርቀዳጆች እንደነበሩ፣ የምኒልክ ሰፋሪዎችም የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ሥልጣኔ መሥራቾች እንደሆኑ አይካድም።

አክሱማውያንን በተመለከተ፣ አለቅጥ እየተደጋገመ በመኖሩ እውነት ለብሶ የቀረ የሐሰት ትርክት አለ። ከአማርኛም ጋር ትስስር ስላለው፣መጥራት ይገበዋል ባይ ነኝና እንዳስተካክለው ይፈቀድልኝ። ብዙውን ጊዜ አክሱማውያንን እንደአንድ ወጥ ብሔረሰብ አድርጎ የማየት ጥልቅ ሥር የሰደደ ዝንባሌ አለ። የወያኔ መሪዎች ደግሞ አክሱማውያንን ከትግራይ ጋር ማዛመድ ብቻ ሳይሆን የትግሬ ብሔረሰብ ናቸው እስከማለትም እንደደረሱ ይታወቃል። በወያኔ ትርክት መሠረት የአክሱማውያን ሥልጣኔ በጠቅላይ ግዛቱ የሚኖሩት የትግሬዎች ከፍተኛ ቅጅት ነው። ሐቁ ግን ከዚህ በታች እንደምናየው፣ አክሱምና ሥልጣኔዋ ከትግራይ ጋር ያላቸው ቁርኝነት፣ ዛሬ ትግራይ ተብሎ በሚጠራው ግዛት ውስጥ መገኘታቸው ብቻ ነው።

አክሱማውያን ራሳቸውን የሚጠሩት “አግኣዚያን”ና “ኢትዮጵያውያን” በሚል መንታ ስም ሲሆን፣ መዛግብቱ የሚመሰክሩልን “ትግሬ” ከሁለቱም የተለየ ማንነት እንዳለው ነው። ወያኔዎች “አግኣዚያን” ትግሬዎች ናቸው ከሚል እምነት በመነሣት አግኣዚ የተባለ በብዙዎች ዘንድ የተጠላ እንደሆነ የሚነገርለትን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት አቋቁሞ እንደነበር ይታወቃል። መሪያቸው አቶ መለስ ራሱ የአክሱምን ሥልጣኔ እንደትግራይ አድርጎ ብቻ በመገመት “የአክሱም ሐውልት ለወላይታ” ምኑ ነው እስከማለትም ዘባርቋል ይባላል። ታሪክ የሚነግረን ሐቅ ግን የአክሱምን ሐውልቶችንና ሌላውንም ሕንጻ የገነቡት፣ ፊደል ቀርጸው ግእዝ ቋንቋቸውን ለጽሑፍና ለታሪክ ያበቁት፣ በዘመናቸው በጣት ከሚቀጠሩ ገናና መንግሥታት አንዱ የነበሩት አክሱማውያን፣ የብዙ ብሔረሰብ መስተጋብር እንደሆኑ ብቻ ነው። እነዚህ ቈይተው፣ በመላዋ ኢትዮጵያ ተስፋፍተው፣ ለዘመን አዝማናት በመወላለድ ዘራቸው በዝቶ፣ የመላዋ ኢትዮጵያ ሕዝብ አባቶች ሁነዋል። ስለዚህ ወያኔዎች እንደሚነግሩን፣ አክሱማውያን ባንድ ትግራይ በተባለች ጠባብ ምድር የተወሰነ ሕዝብ አልነበረም። ሐቁ ከኢትዮጵያ ዐልፈው፣ ባሕር ማዶ ተሻግረው፣ በሰሜን እስከፋርስና ግብጽ፣ በደቡብ እስከጥንቱ አዛኒያ ሥልጣኔአቸውን የዘረጉ፣ አግኣዚያን ወይንም ነፃ ሕዝብ በመባል የሚታወቁ ናቸው። አክሱማውያን በፍጹም ትግሬዎች አይደሉም ብቻ ሳይሆን፣ በዘመናቸው ትግራይ የሚባል መሬትም፣ ማንነትም እንደነበረ የሚመሰክሩ መዛግብት እስካሁን ድረስ አልተገኙም።

ከ“ትግራይ” ጋር ተመሳሳይ ቃል ለመጀመርያ ጊዜ በታሪክ ተጠቅሶ የሚገኘው በሁለተኛና በሦስተኛ ዘመነምሕረት አካባቢ በተሠራው የአዱሊስ ዙፋን በመባል በሚታወቀው፣ ቈይቶ ቆስሞስ ዘህንደኬ በስድስተኛ ዘመነምሕረት ቀድቶ ለትውልድ ባስተላለፈው ሐውልት ላይ ነው። በዚህ ሰነድ፣ “ከትግሬዎች ጐሣ አንዱ” የሚል ቃል ይገኝበታል። ይኸም የሚያመለክተው በአዱሊስ ወደብ አጠገብ የሚገኝ ሕዝብ ሲሆን፣ ምናልባትም ዛሬም እዚያ አካባቢ ያለውን የ“ትግሬ” ብሔረሰብን እንጂ የትግራይን አውራጃ አይደለም ተብሎ ይታመናል። ከሰነዱ በግልጥ የሚንረዳ ሐቅ ቢኖር “አግኣዚያን”ና “አክሱማውያን” የአንድ ዐይነት ሕዝብ መጠርያ ስሞች ሲሆኑ፣ “ትግሬ”ና “አግኣዚያን” ግን ሁለት የተለዩ ሕዝብ መሆናቸውን ነው። ”ትግሬ” የሚለውም ቃል የተለያየ ትርጒም ቢሰጠውም፣ በርግጠኝነት የሚታወቀው “ገባር” [ወይንም በቋንቋችን ተመጣጣኝ ትርጉም የሌለው የእንግሊዝኛው “serf”] በሚለው ፍቹ ነው።

የአክሱም ሥልጣኔ የትግራይ ወይንም የትግሬዎች ሥልጣኔ ነው የሚል መዝገብ እስካሁን ድረስ አልተገኘም፤ ይገኛል ብዬም አላምንም። አክሱማውያን ግን ራሳቸውን “አግኣዚያን”ና “ኢትዮጵያውያን” በመባል ይጠሩ እንደነበር ተጨባጭ ማስረጃ አለ። ትግራይ የተባለ አገርም ሆነ ግዛት በአክሱማውያን ዘመን አልነበረም። ቃሉ እንደአንድ አካባቢ ማለትም እንደአንድ ምድር በታሪክ መዝገብ ላይ ብቅ ያለው የአክሱም ሥልጣኔ አካትቶ ከሞተ በኋላ ዘገይቶ በዐሥረኛ ዘመነምሕረት ላይ ነው። የአክሱም ከተማም የታሪክ አጋጣሚ ሁኖ ትግራይ በተባለ ምድር ውስጥ ይገኝ እንጂ፣ የግዛቱ አካል የሆነበት ወቅት ግን በታሪክ አልነበረም ማለት ይቻላል።አክሱም ራሷ ዘውዳዊ ሥርዐት ተገርስሶ፣ የደርግ መንግሥት ሥልጣን እስከጨበጠበት እስከቅርብ ጊዜ ድረስ፣ ከትግራይ ገዢ ሥልጣን ውጭ የሆነች፣ ራስ ገዝ ከተማ ነበረች። ትተዳደርም የነበረው በአክሱም የመጀመርያ አቅኚ አባቶች በመባል በሚታወቁት በሰባቱ ነገዶች በተመረጠ መሪና [ቀሪጌታ]፣ ከማእከላዊ መንግሥት የበላይ ሁኖ እንዲቈጣጠር ብቻ በየጊዜው ይሾም በነበረው ንቡረእድ በተባለ ባለሥልጣን ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ይታደሏል እንጅ….!” - አሰፋ ጫቦ

የአክሱም ሥልጣኔ የትግሬዎች ሥልጣኔ ነው ማለት ታሪክን አላግባቡ ማፋለስ ካልሆነ በስተቀር እውነቱን አያንፀባርቅም። ትግራይ የአክሱም ሥልጣኔ ልትቋደስ የበቃችው የኢትዮጵያ አካል በመሆኗ ነው እንጂ አክሱማውያን ትግሬዎች በመሆናቸው፣ አክሱምም የትግራይ አካል ስለነበረች አይደለም። የአክሱማውያን ሥልጣኔ የመላ ኢትዮጵያውያን፣ ከዚያ በዘለለ ደግሞ የአፍሪቃውያንና የሁሉም ጥቊር ሕዝብ ሥልጣኔ ነው።
አማርኛ ከዘመነ አክሱማውያን ጀምሮ ህልው ቋንቋ መሆኑ ቢገመትም፣ ለብሔራዊ ቋንቋነት የበቃው ግን የአክሱምን ሥልጣኔና መንግሥት ከሞተበት ተነሥቶ እንደገና እንዲያንሰራራ ለማድረግ በበቁት ዛጐዎች ነው። ይሁንና እነሱ አማርኛን የመንግሥት ቋንቋ እንዲሆን ቢወስኑም፣ የትውልድ አገሩ ግን “ቤተአምሐራ” እንደሆነ ይነገራል። በታሪክ ምድረ አምሐራ የምታወቀው የተለያዩ የኢትዮጵያውያን ብሔረሰቦች መናኸርያ በመሆን እንጂ የተወሰነ ጐሣ መኖርያነት አይደለም። በአፈታሪክ መሠረት ከትግራይና ከትግሬ ይልቅ ለአክሱማውያን የሚዛመደው የዘርሐረጉን ከአክሱም የሚመዝዘው የዚህ የቤተ አምሐራ ነዋሪ ሕዝብ ነው። የ“አምሐራ” ትርጒሙ ደግሞ፣ ልክ እንደአግኣዚያን “ነፃ ሕዝብ” “ጨዋ ሕዝብ” ማለት እንደሆነ ነው። አማርኛ በስም ከዚህ ምድር ጋር ቢቈራኝም፣ የአክሱማውያን ቅርስና ውርስ እንደመሆኑ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን የጋራ አፍመፍቻቸው ወይንም መግባቢያ ቋንቋቸው ሁኖ ቀርቷል። ይኸም ሊሆን የቻለው፣ በአፄ ምኒልክ ትእዛዝ ወይንም በፖሊቲካ ግፊትና ውሳኔ አይደለም። ከንጉሠ ነገሥቱ ዘመነአዝማናት አስቀድሞ፣ ቢያንስ ከስምንት መቶ ዓመታት በፊት ነው። አማርኛ ለዚህ ሰብእና የበቃው፣ ልክ አሁን “የሥልጡን ሕዝብ ቋንቋዎች እንደሚሏቸው እንደእንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ ኢጣሊያንኛ”፣ እሱም ከሌሎች የአካባቢው ቋንቋዎች ተወዳድሮ በማሸነፍና በሰፊውም ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትና ተወዳጅነት ስላተረፈ ብቻ ነው። የወሰነውም የአምሐራ ምድር ነዋሪ ሕዝብ ሳይሆን፣ ከብዙዎች ቋንቋዎች መካከል መርጦ “ልሳነ ንጉሥ” ማለትም “የንጉሥ ቋንቋ” ይሁን ያለው የዛጐ መንግሥት ነው። ይኸንን ነው እንግዴህ አፈታሪኩም የሚያጠናክረው።

“የዛጐ ሥርወ መንግሥት” መሪዎች አገዎች እንደሆኑ ይታወቃል። ስለዚህ የራሳቸውን አገውኛ ቋንቋ ትተው አማርኛን “የንጉሥ ቋንቋ” እንዲሆን የሚመርጡበት ምንም ዐይነት ምክንያት የለም። የመረጡትም፣ አገውኛ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ስላወቁና፣ ወንዝ በማያሻግር በ”መንደራቸው” ዘይቤ ሰፊዋን ኢትዮጵያ መግዛት እንደማይችሉ ስለተረዱት ብቻ መሆኑ አያጠራጥርም ። በዘመነመሳፍንት የተዳከመው የሰለሞናውያን መንግሥት መልሶ ሲጠናከር፣ አማርኛ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ መግባቢያ እንዲሆን የወሰኑት ደግሞ የትግራዩ ተወላጅ አፄ ዮሐንስ ራብዓይ እንጂ የሸዋው ንጉሠነገሥት ምኒልክ አልነበሩም። ስለዚህ አማርኛን እንደብሔራዊ ቋንቋ የማድረግ ውሳኔ የአማራ ብሔረሰብ ናቸው ተብለው ከሚታመኑት ሰለሞናውያንም ሆነ ከአፄ ምኒልክ ጋር ማዛመድ ታሪካዊ ቅሌት ብቻ ሳይሆን መሠረተቢስ ልበወለድም ነው።

ከጥንተፅንሰቱ ጀምሮ፣ አማርኛ ቢያንስ ቢያንስ በሦስት ዘርፎች የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት መሠረታዊ መግለጫና መለዮ ለመሆን በቅቷል ማለት ይቻላል።

አንደኛ፣ ከላይ እንዳልሁት፣ ጥንተመሠረቱ ዛሬ ወሎ ተብሎ ከሚጠራው ከቤተ አምሐራ አካባቢ ነው ተብሎ ቢታመንም፣ አማርኛ ከአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በመቀማመምና በመዛነቅ የተወለደና ያደገ እንደሆነ አይካድም። ስለዚህ፣ ልክ በምሥራቅ አፍሪቃ የባሕር ጠረፍና አካባቢው እንደሚገኘው የሱዋሂሊ፣ ወይንም በዛሬዋ ናይጀርያ እንዳለው ሐውሳ፣ ወይንም እንደክሬኦል ቋንቋዎች፣ አማርኛም የብዙዎች የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች አስተዋፅዖ ያለበት እንደሆነ መገንዘብ ይገባል። የሥነ ቋንቋ ምሁራን፣ ሴማዊ ብለው ይጠሩታል። ሐቁ ግን በባሕርዩ ሰማንያ ከመቶ ኩሻዊነት አለው። ስለዚህ አማርኛ፣ በርካታውን የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን ዘዬዎች የሚያንፀባርቅ፣ ለማንኛዉም ሳያዳላ ሰፊውን የሚወክል፣ ከአብዛኛውም ጋር የሚያስተሳስር ቋንቋ ነው። ከዚህም የተነሣ፣ አለቃ ታዬ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ” በሚለው በ1920 ዓም በታተመው መጽሐፉ እንዳስቀመጠው፣ አማርኛ “ፈጽሞ የሠለጠነ፣ ያማረ” እንደአንዳንዶቹ ጉሮሮ የማያንቅ፣ ምላስ የማይዶለዱም፣ ገለልተኛ፣ ግልጽና ጥርት ያለ ቋንቋ ነው። ባንድ ቃል ባጭሩ ይገለጥ ቢባል፣ የኢትዮጵያውያንን የፈጠራ ችሎታና የአሳብ ርቀት በሚገርም መልኩ የሚያሳይ አስደናቂ ቋንቋ ነው። የሌሎችን ብሔረሰቦች ድምፅ ለማቀፍና ለማስተናገድ ሲል፣ ከግእዝ የወረሳቸውን ፊደላት በማዳቀል አሻሽሎና ከየዘይቤው ጋር አጣጥሞ ተጨማሪ ሆኄያት ሊፈጥር ችሏል። ባጭር ቃል፣ ሌላውን ማቀፍና ማስተናገድ የኢትዮጵያዊነት አንኳር ባሕርይ እንደሆነ ሁሉ፣ የአማርኛም ዋናው መለዮው ከሌሎቹ ቋንቋዎች በተለየ መልኩ ይኸንን ተመሳሳይ ጠባይ ማንፀባረቁ ነው።

በሁለተኛ ደረጃ፣ የቤተሰብ ወይንም የአካባቢው ቋንቋ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ከጐሣው ጋር እንደሚያተሳስር ሁሉ፣ አማርኛም በአገር ደረጃ መላውን ሕዝብ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያውያን ጋር ያቈራኘዋል። ማእከላዊ መንግሥት ጠንካራ በነበረበት ወቅት ብቻ ሳይሆን፣ የባላባቶች ጡንቻ በጠናበት በዘመነ መሳፍንትም እንኳን አማርኛ ቋንቋቸው ያልሆኑ፣ የየአካባቢው መሪዎች ሳይቀሩ፣ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ይጻጻፉ የነበሩት በአማርኛ ነበር። ይኸም ማለት ከሥልጣናቸው ሥር ያለው ሕዝብ ይጠቀም በነበረው በአፍመፍቻ ቋንቋው አይደለም ማለት ነው። ወያኔዎች ልብ አላሉትም እንጂ፣ አፄ ዮሐንስ እንደነሱ የትግራይ ተወላጅ ናቸው። ግን አማርኛን የኢትዮጵያ መንግሥት ቋንቋ በማድረግ ብቻ አላቆሙም። የአገሪቷ ንጉሠነገሥት እንደመሆናቸው፣ መንግሥታዊ ሥራቸውን ያካሄዱት በቀዬአቸው ዘይቤ ማለትም በአፍመፍቻቸው ”ትግርኛ” ሳይሆን፣ በብሔራዊው የ“አማርኛ’ ቋንቋ እንደነበር ታሪክ ያስረዳናል። እንደኢትዮጵያ ንጉሥነገሥት ለትግርኛ ተናጋሪ ሕዝባቸው ሲናገሩ፣ ወደትግርኛ ተርጓሚ አቁመው በአማርኛ እንጂ በራሳቸውና በሕዝባቸው አፍመፍቻ ቋንቋ አልነበረም። አገር ሊወርር የመጣውን ባዕድ ጠላት እንዲቋቋምና እንዲመክት የክተት አዋጃቸውን ለመላዋ ኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተላለፉት በትግርኛ ሳይሆን በአማርኛ ነው። በዚህ አዋጅ ነው እንግዲህ ከማንኛውም የዘመናችን ምሁራን ገለጣና አመለካከት በበለጠ መልክና ስልት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ምን መሆናቸውን በተጨባጭና ግዙፍ ማስረጃ ተንተርሰው፣ እንዲህ ያሉት፤ “የኢትዮጵያ ልጅ ሆይ፣ ልብ አድርገህ ተመልከት። ኢትዮጵያ፣ አንደኛ፣ እናትህ ናት፤ ሁለተኛ፣ ዘውድህ ናት። ሦስተኛ፣ ሚስትህ ናት። አራተኛ፣ ልጅህ ናት። ዐምስተኛ፣ መቃብርህ ናት።” እንደዚህ በመሰለ ቀላል ግን ግሩም፣ ድንቅና አስቀኚ፣ ማንም ኢትዮጵያዊ በሚገባው የአማርኛ ቋንቋ ነው እንግዴህ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ምሥጢርና ትርጒም ምን እንደሆነ የነገሩልን።

እንዲሁም በምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በ፲፱ኛ ዘመነ ምሕረት በማቈጥቈጥ ላይ የነበሩ ራስገዝ የባላባት መንግሥታት፣ ኦሮሞኛ አፍመፍቻቸው ሁኖ እያለ ይጻጻፉ የነበሩት በአማርኛ እንጂ በኦሮሞኛ አልነበረም። ቈይቶም በኢጣሊያን ሁለተኛ ወረራ ወቅት፣ በእንግሊዝ ጐትጓችነት “የምዕራብ ኢትዮጵያ የጋላ ባለቃልኪዳን መንግሥታትን” ለማቋቋም የቃጡት፣ እነደጃዝማች ሀብተማርያምን የመሳሰሉት ገዢዎች፣ ከእንግሊዝና ከኢጣልያን መንግሥታት ባለሟሎች ጋር የተጻጻፉት በኦሮሞኛ ሳይሆን፣ በአማርኛ ነበር። ወደበስተኋላ ገፋ ካልን ደግሞ፣ የዘመነ-መሳፍንት የኦሮሞ ገዢዎችም ቢሆኑ የተጠቀሙት አማርኛ እንጂ፣ ኦሮሞኛ አልነበረም። ከነሱ በፊት በዐሥራሰባተኛ ዘመነምሕረት መጀመርያ ላይ የኦሮሞ ብሔረሰብ አባል እንደሆነ የሚነገርለት የወቅቱ ንጉሠነገሥት ከፍተኛ ባለሟልና ምሁር ደጃዝማች ጢኖ ከዐረብኛ እያነጻጸረው “የኛም አማርኛ ቋንቋችን” በማለት የቋንቋውን ታላቅነት በማወደስ አድናቆቱን ገልጧል። እነዚህ ኋለኞቹ የኦሮሞ መሪዎችና ልሂቃን የሱን ፈር ቢከተሉና ከአፍመፍቻቸው ዘይቤ ይልቅ ለአማርኛ ዕውቅና ቢሰጡ አይገርምም። ሌላው ቀርቶ፣ ግራኝም ሆነ የሠራዊቱ አባላት አማርኛ ይናገሩ እንደነበር፣ የወረራ ታሪክ ጸሓፊው ይመሰክርልናል።

የውጭ አገር ጸሓፊዎችም የሚነግሩን አማርኛ ምን ያህል በኢትዮጵያ እንደተስፋፋ ነው። በአውሮጳ የኢትዮጵያ ጥናት መሥራች በመባል የሚታወቀው ጀርመናዊው ኢዮብ ሉዶልፍ በዐሥራሰባተኛ ዘመነምሕረት መኻል ላይ ሲጽፍ፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የየራሳቸው ዘይቤዎች [የአካባቢ ቋንቋዎች] ቢኖሩም፤ ማናቸውም ከወንዝ እንደማያሻግሩ፣ “ልሳነ ንጉሥ” ተብሎ የሚጠራው አማርኛ ግን፣ በግእዝ ቋንቋም ሆነ በሁላቸውም የኢትዮጵያ ዘይቤዎች ላይ የበላይነት እንዳገኘ ይነግረናል። አማርኛን የሚናገር መንገደኛ መላዋን ኢትዮጵያ ከጫፍ እስከጫፍ አላንዳች ችግር መጓዝ እንደሚችልም ይገልጥልናል። ይኸ ሁሉ የሚያመለክተን አማርኛ የመላ ኢትዮጵያውያን ቋንቋ ከሆነ አዝማናት ማስቈጠሩንና፣ በአገሪቷም የሚኖረው ሕዝብም ዋና መተሳሰርያውና መግባቢያው ሁኖ እንደቈየ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የወታደሮቻችን ነገር - ከዲ/ን ዳንኤል ክብረት

ሦስተኛ፣ ኢትዮጵያዊነትን ለመላው ዓለም ጐልቶ እንዲፈነጥቅ፣ የኢትዮጵያም ታሪክ ጠባይ ከሌላው ዓለም የተለየ እንዲሆን፣ ከረዱት ምክንያቶች አንዱ አማርኛ በመኖሩ እንደሆነ አይጠረጠርም። የታሪክ ሰዎች፣ የቀሩት አፍሪቃውያን በቀላሉ የአውሮጳውያን የቅኝ ግዛት ምርኮኞች እንዲሆኑ ካበቋቸው ምክንያቶች አንዱ፣በርካታውን ሕዝብ የሚያግባባ አንድ-ወጥ ቋንቋ ስላልነበረ እንደሆነ ይነግሩናል። ከዚያም ባሻገር፣ ባለሥልጣናቱ ትእዛዝና መምርያ ለሕዝብም ሆነ ለበታቾቻቸው በጽሑፍ የሚያስተላልፉበት የጋራ ቋንቋ ባለመኖሩ ነው ብለውም ያትታሉ። በዚህ ረገድ ስለኢትዮጵያውያን የሚነገረው እጅግ በጣም የታደሉ ሕዝብ እንደሆኑ ነው። ከመላዋ ጥቊር አፍሪቃ በተለየ መልኩ፣ በርካታው ሕዝብ የሚግባበት ቋንቋ አላቸው። ከዚያም በዘለለ የንግግር ብቻ ሳይሆን በፊደል የተቀረጸ ብቸኛው የአፍሪቃ ቋንቋ እንደመሆኑ ኢትዮጵያውያንን ከመላው ጥቁር ሕዝብና አፍሪቃ ልዩ ያደርጋቸዋል። ምክንያቱም በ፲፮ኛ ዘመነምሕረት በርካታውን ዓለም ከሥልጣኑ ሥር ባንበረከከው በኦቶማን [ቱርኮች] ወራሪ ጦርም ሆነ፣ ሦስት መቶ ዓመት ቈይቶ በ፲፱ኛ ዘመነምሕረት መላ አፍሪቃንና አብዛኛውን ነጭ ያልሆነውን ዓለም ተቈጣጥሮ በነበረው በአውሮጳውያኑ ቅኝገዢ ሠራዊት ድል ሊጐናፀፉ የቻሉት፣ አማርኛ እንደብሔራዊ ቋንቋ በማገልገሉ ነው ይባላል። አለአማርኛ ለመላው ዓለም አስቀኚና አስደናቂ ታሪክ ያፈራው የኢትዮጵያውያን ጀግንነትና ትግል፣ በቋንቋ ካለመግባባት የተነሣ ሳይገነባ እንደቀረው እንደባቢሎን ግምብ ከንቱ ሊሆን በቻለ። ኢትዮጵያም ኩሩ የነፃነት ታሪኳን ለመጠበቅ ባልቻለች፤ ኢትዮጵያውያንም ዛሬ የሚታየውን የሥነልቦና ጥንካሬንና አልበገርነትን ከትውልድ ወደትውልድ ለማስተላለፍ ባልታደሉም ነበር ተብሎ ይነገራል።
ከላይ የተባሉት ነገሮች የሚነግሩን ነገር ቢኖር፣ አማርኛና ኢትዮጵያዊነት ርስበርስ የሚወራረሱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች እንደሆኑ ነው ማለት ይቻላል። ወደዐሥራስድስተኛ ዘመነምሕረት መጨረሻ ላይ የኦቶማኖችን ጦር የደመሰሰው አፄ ሠርፀድንግል በአክሱም በክብር ሲነግሥ፣ የቀረቡት የመሣርያ ዐይነቶችና ጨዋታዎች “የቱርክና የአማራ” ነበሩ ሲል የታሪክ ጸሓፊው ይነግረናል። የተዋጋው ጦር ልክ በዐሥራዘጠነኛ ዘመነምሕረት ላይ ኢጣሊያንን እንደተዋጋው እንደዐድዋው ሠራዊት፣ ከመላዋ ኢትዮጵያ አካባቢ የተወጣጣ እንደመሆኑ፣ “አማርኛ” ከነዋሪው ሕዝብ ቋንቋነት ዐልፎ የ“ኢትዮጵያዊነትም” መግለጫ እንደሆነ ያመለከታል ብል የተሳሳተ ግንዛቤ አይመስለኝም። በዘመናችንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሲስፋፋ፣ የሕዝቧ ክብር በዓለም ከፍ ሲል፣ አማርኛም አብሮ በዚያው ልክ ሲያድግና ሲከብር፣ ሲደነቅ ታይቷል። ለምሳሌ፣ በሺዘጠኝ መቶዎቹ መካከል በብዙዎች አገሮች በተለይም በምዕራብ ዓለም ዩኒቬርሲቲዎች ራሱን የቻለ የአማርኛ ጥናት ክፍል እንደነበረ ብዙዎቻችን በዐይናችን ያየነው ጉዳይ ነው። “ያትውልድ” ከተባለው የሠረፀው የወያኔዎች ቡድን ሥልጣኑን ከተቈናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ ግን የኋላ ደራሾቹ እንደነሱዋህልና ሀውሳ የመሳሰሉት አማርኛን እየተኩ ለመሄድ በቅተዋል። የአማርኛ ጥናት ማእከሎችም ተማሪ አጥተው እየተዘጉ መሄዳቸው፣ የኢትዮጵያ ታላቅነት፣ አገሪቷም በዓለም-ዐቀፍ ደረጃ ያላት ተደማጭነት፣ የሕዝቧም ሆነ የኢትዮጵያዊነት ክብር ምን ያህል እንደወረደና እንደዘቀጠ፣ እንዴትስ እንደተዘቀዘቀ አመልካች ነው ቢባል ከእውነት የራቀ አስተያየት አይመስለኝም።
ደጃዝማች ተክለብርሃንና ወያኔ፣ እንዲሁም እነሱን የመሳሰሉት የዘመናችን አገርበቀል የሆኑት አብዛኞቹ አክራሪና የግራና የቀኝ ዘመም ድርጅቶች እንደሠለጠኑ ቋንቋዎች አድርገው የሚያዩት ድንበር ረግጠው ወሰን ተሻግረው የሌላውን ሕዝብ መብት ደፍጥጠው፣ ባህሉን ጨፍልቀው የበላይነታቸውን ተቃዋሚ ደምስሰው፣ በሌላው በመጫን የተስፋፉትን ነው። አብዛኛው እንደእንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ የመሳሰሉ የምዕራባውያን ቋንቋዎችም ሆኑ፣ እንደዐረብኛ ያሉት የጐረቤቶቻችን የመካከለኛ ምሥራቅ ቋንቋዎች “የሠለጠኑ” እንዲሆኑ የበቁት በዚህ መልክ እንደሆነ አመልክቻለሁ። አማርኛ ግን በዕድሜ ከነዚህ ሁሉ ባለፀጋ ሁኖ እያለ፣ እንደነሱ ሊስፋፋ ያልቻለበት በሕዝብ የመግባባት ፍላጎት እንጂ በጉልበት ላይ የተመሠረተ ቋንቋ ባለመሆኑ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ትርጒም የለውም። ገዢው ክፍል ራሱ ከተለያየ አካባቢና ቋንቋ ተናጋሪ የመጣ አካል እንደመሆኑ እንደሌላው አገር ባለሥልጣናት ከሥሩ በነበሩት ሕዝብ ላይ ቋንቋውን በግድ የመጫን ዝንባሌ አላሳየም። አፄ ዮሐንስ የአፍመፍቻቸው ቋንቋ ትግርኛ ሁኖ ሳለ፣ አንድ ወጥ ሃይማኖት ሕዝቡ እንዲከተል በግሁድ ሲያስገድዱ፣ አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆን ከመወሰን ዐልፈው የግዴታ ሁሉም ቋንቋውን መናገር አለበት የሚል አዋጅ ግን አላወጡም።

የአማርኛ ታላቅነቱ የሚታየው በስፋቱና በተናጋሪው ብዛት ከ’ሥልጡኖቹ’ ቋንቋቸው መካከል ባይሆንም፣ በቀረው በማንኛውም መስክና መስፈርት ግን ይበልጣቸዋል ማለት ይቻላል። ሐቁን ለመናገር፣ በዘመናዊ ፈጠራዎች ቃላት ጉድለት ካልሆነ በስተቀር፣ በምንም ዐይነት ደረጃ ሊወዳደሩት አይችሉም ማለት ይቻላል። የኪነጠቢብ ሥራ በሚመስል የሆኄያቱ ውበትና ድምቀት፣ በአነባቡ ቀላልነት፣ እንዲሁም በይዘቱ ጥልቀት፣በመልእክቱ ምጥቀት፣ በገለጣው ረቂቅነት፣ አማርኛ ወደርየለሽ፣ ምርጥና ዘመናዊነትን ያሟላ ቋንቋ መሆኑ አይካድም። ሆኄያቱ ከሌሎቹ አገሮች ሲተያዩ በቊጥር በዛ ያሉ ይምሰሉ እንጂ፣ ሐቁ ግን ከአብዛኛዎቹ ቋንቋዎች ፊደላት ሲነጻጸሩ እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው። እንደላቲን በትልቅና በትንሽ፣ በእጅ፣ በመኪናና በአጭር ጽሕፈት ሲጻፉ የተለያዩ ፊደሎች የሉትም። አንዴ ጠንቅቋቸው ላወቃቸው በቅልጥፈትና በጥራት፣ በቀላልነትና በግልጽነት፣ እንዲሁም በመልካቸው ቅርጸት፣ በሚይዙት የቦታ መጠን ማንኛውንም የሌላውን ዓለም ቋንቋ ፊደላት በእጅጉ ያስንቃሉ።
ይሁንና፣ ከሌሎች አገሮች ብሔራዊ ቋንቋዎች ጋር ሲተያይ፣ በሁሉም ረገድ አመቺና የረቀቀ ቋንቋ ቢሆንም፣ ከዕድሜው ርዝመት አንጻር ሲሰላ ግን እንደነሱ ሊያድግ አልበቃም። ያ ያልሆነበትም ምክንያት ግልጥ መሰለኝ። ከላይ እንደተገለጠው፣ አብዛኞቹ የዓለም መንግሥታት ከተከተሉት መርህ በተለየ መልኩ፣ የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግሥት ቋንቋዉ የአፍመፍቻው ባልሆነው ኅብረተሰብ ላይ በግድ መጫን የለበትም እያለ ያራምድ የነበረው መንግሥታዊ መርህ ነው። ይኸ አቋም አማርኛ እንደሌሎቹ የዓለም ብሔራዊ ቋንቋዎች በቶሎ የማደግ ዕድሉን እንደቀጨው አይጠረጠርም። ይሁንና የራሱ ፊደል ያለው የዕድሜ ብቻ ሳይሆን የንግግር ከበርቴ የሥነጽሑፍ ቋንቋ መሆኑ በበኩሉ ተቀባይነቱ በአገሩ ብቻ ሳይሆን በመላዋ አፍሪቃ ለመስፋፋት ችሎታም ዕድሉም እንዳለው አይካድም። ያልሆነበት ምክንያት ከቋንቋው ደካማነት ሳይሆን፣ ከአገሩ መሪዎች ነዘኅላልነትና ብሔራዊ ራእይ ጉድለት፣ ከምሁራኑና ልሂቃኑ መደብ የአሳብ ድኽነትና የአመለካከት ጠባብነት ብቻ ነው።
ከሺዘጠኝመቶስድሳዎቹ ጀምሮ እየተደጋገመ በመተረክ እንደእውነት የተወሰደ ሐሰት አለ። እውነቱን ለመናገር ሐሰት ሳይሆን ልበወለድ [myth] ነው ልበለው። ይኸውም አማርኛ ብቻ ካልሆነ በስተቀር፣ ቋንቋችንን እንዳንናገር በመንግሥት ተከልክለን ነበር የሚል የቋንቋና የባህል ጭቈና ትርክት ነው። የራሴን ጨምሮ አፍመቻቸው አማርኛ ባልሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች ኑሬአለሁ። የአካባቢው ያልሆነ ሰው እስካልገጠመው ድረስ፣ በየሄድሁበት የአካባቢው ሕዝብ ርስበርሱ ይናገር የነበረው በየራሱ ዘይቤ እንጂ በአማርኛ ሲናገር አልገጠመኝም። አማርኛ እንደሌላው ትምህርት በትምህርት ቤቱ ለመማርያ ከተመደበለት ሰዓት አልፎም አያውቅም። በመንግሥት ጋር በሚደረገው ግንኙነትም ቢሆን፣ ቋንቋውን ለማያውቀው በቋሚ አስተርጓሚ እንደሚከናወን ራሴ በገዛ ዐይኔ ያየሁትና የገጠመኝ ጉዳይ ነው። ልክ እንደብሔር ጭቈና ትርክት፣ የአማርኛም የግድ ጫና መረን የለቀቀ የጽንፈኞችና የተከታዮቻቸው የሐሰት ፍብረካ እንጂ ምንም ዐይነት እውነተኝነት የለውም ማለት ይቻላል።
አማርኛ እንደሌሎቹ ቋንቋዎች በጉልበት ባይጫንም፣ ዘመናዊ ቃላትን ወደጐን ብለን ከሌላው ብናመዛዝነው ከየትኛውም አገር ቋንቋ፣ ‘ሥልጡኑ’ እንኳን ሳይቀር እሱን ያህል የተጣበበና የተራቀቀ የሥነጽሑፍ ዘርፍ አላዳበረም። የትኛ አገር ቋንቋ ነው በንግግር ጥልቀቱ፣ በአሳብ ርቅቀቱ፣ በፈሊጥ ምጥቀቱ በምሥጢራዊ ይዘቱ የአማርኛን ቅኔ የሚስተካከል። የትኛ አገር ነው እንደሰምና ወርቅ አስቀኚ፣ በምሳሌያዊ አነጋገሩ የበለጸገ ቋንቋ ያለው። አላንዳች ጥርጥር ኢትዮጵያዊው አማርኛ ብቻ ነው ማለት ይቻላል። እንግዴህ ደጃዝማች ተክለብርሃን ወልደአረጋይ ማለት የሚገባው “አማርኛ በመማሬ ያጠፋሁት ጊዜ ይቈጨኛል” ሳይሆን ምን ጊዜም ቢሆን ያኰራኛል፤ አለበለዚያም “ሁሉንም አጠናቅቄ ባለመማሬ ይቈጨኛል” መሆን ነበረበት። የሚያሳዝነው እሱና ድርጅቱ እንዲህ ዐይነቱን የመጠቀና የተራቀቀ ከፍተኛ አስተሳሰብ ለማስተናገድ አልታደሉም።

============================================

ዶር. ኀይሌ ላሬቦ

10 Comments

 1. God Bless this graceful intellectual, professor Haile Larebo.

  Forget the dis-tractors, your virtue and wisdom will shine for ever and ever.

  Thank you professor for telling the truth.

 2. ፈጣሪ ሣይደግሥ አይጣላም። “ወላድ በድባብ ትሂድ!” የሚባለው ለዚህ ነው። ሀገራችን ይህን እጅግ ድንቅ ሰው የመሠሉ በጣት የሚቆጠሩ ምሁራን ባይኖሯት ኖሮ የሀገራችን ታሪክ ተዳፍኖ የማንም አክራሪ ጎሠኛና ሆዳም ብንዳ መፈንጫ እንደሆነች ትቀር ነበር።
  የፕሮ. ኃይሌ ላሬቦን ጽሑፍም ሆነ ንግግር አለማንበብና አለማድመጥ ፈጽሞ አይቻልም። እግዚአብሔር ረጅም ዕድሜ ከጤናና ከተሟላ ሠላም ጋር ይሥጥልን፤ የኢትዮጵያን የማይቀር ትንሣኤም ያሣይልን፤ያሣየን።
  በዩቲዩብም እንዲነበብ ቢደረግ ተደራሽነቱን ያሰፋዋልና መልካም ነው። ዕውቀት ጠል የሆነው አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ይህን መሠል እውነተኛ ትንትኔ ቢያነብና ቢሰማ በጊዜ ሂደት የተወለጋገዱ ነገሮች እየተቃኑ ሊሄዱ ይችላሉ።

 3. ዘረያቆብ ነህ ዘረ ሐጎስ ኢትዮጵያዊነት ላይ ያነጻጸረ መልካም ጽሁፍ ሲጻፍ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ደምህ ይፈላል እራስህን መቆጣጠር ባለመቻልህም ስድብህ ይከተላል። አቅምህ የስድብ አቅም ካልሆነ በስተቀር እንደ ሐይሌ ላሬቦ የተሟላ ጽሁፍ ልከህ እንመልከተው። ይህ የጠገበ ምሁር ወደፊትም ወደ ሁዋላም ተጉዞ ምልከታውን ሰጠን ሌላው ቢቀር አንተም ብልግናህን የገለጽክበት በዚህ ቋንቋ ነው።
  እዚህ እየተክለፈለፍክ እየመጣህ አትቃጠል አትምጣ ኢትዮጵያዊነት አንተ እንደፈለግኸው ሳይሆን ሐይሌ እንደሚለው እያበበ ነው የመጣው የሚመጣው።
  እንዲህ አይነቱ ደካማ አሰራር ያንተ ሰዎች የሚጠቀሙበት ነው ተሞከረ አልሰራም ነቃ በል እንጅ።
  እንዴ መች ነው ነገርን አገናዘብህ ቁም ነገር የምትጽፍበት ለነገሩ ቤተሰብ የለህም እንጅ ቢኖሩህ ካንተ ምን ሊማሩ ነው? ቢኖ ነገር እየጠጣህ ኢትዮጵያን ክፍል አትምጣ የምታነበው ሁሉ የኢትዮጵያን ታላቅነትና ተስፋ በመሆኑ ደም ብዛትህ ጨምሮ በተቀመጥክበት ይገለብጥሀል እመነኝ።

  ነጻ ወጥተሀል ነጻነትህን አጣጥም ወደሁላ አትመልከት እሱ አልፎበታልና መንፈስህ ሰላም እንዲያገኝ ወይ ወደ ጥልያን ወይ ወደ አረብ ሂደህ ኑር በማንኛውም የሚቀርቡህ እነሱ ናቸውና መቼም ለኢትዮጵያዊነት ክብር የታደልክ አይደልህምና። ሀይሌ ላሬባ ለዚህ ብልግናህ መልስ ይሰጠኛል ብለህ አትጠብቅ።

 4. ቶም ከተማሩ አይቀር እንዳንተ ነው ለትግሬዎች ኑርላቸው አንተም የገብረኪዳን ደስታን ጽሁፍ ተጋተው ይሄ ላንተ አይመጥንም ይበዛብሀል።እኛ እናንተ ዘንድ አንመጣ እዚህ ምን ቀራችሁ? ልታብዱ ነው መሰል።

 5. Thank you, Professor Haile Larebo! God bless you! Your text sends a big historical message to our enemies and to those who are confused with the propaganda of our enemies they shall know what is really happening with clarity. It is a rich and based on knowledge content.Great!

 6. ፕሮፌሰር ላሬቦ፣ ታላቅ ሰው ነዎት። የ ታሪክ ምሁር ማለት እንደ እርስዎ አይነቱን እንጂ እንዲሁ ለ ፖለቲካ ፍጆታ ታሪክን እያጣመመ የሚጽፍ አይደለም። እባክዎ የዘመኑ ፖለቲከኞችን ትርክት ልክ በእንደዚህ አይነት ጽሁፍዎ ማጋለጡን ይበርቱበት። ለ ኢትዮጵያውያን ብዙ ትምህርት ይሰጣልና።
  ረጅም ዕድሜ ከ ሙሉ ጤንነት ጋር እመኝልዎታለሁ።

 7. ግሪክ፣ ላቲን፣ እንግሊዘኛ፣ አረብኛ እና ግእዝ ቛንቛዎችን ደግሞ ደጋግሞ መማርና master ማድረግ የሚያስፈልገው፣ Platon-Aristoteles, Seneca-Giordano Bruno, Shakespear, Mohammed እና እንዲሁም ያሬድን የመሳሰሉትን ከትውልድ እስከ ትውልድ ቢተላለፍ የማይወድቅ እውቀቶችን ተመራምረው ስላስተላለፉና እነዚህ እውቀቶች ላይ ተመርኩዞ ጠቅላላ እውቀትን ኣዳብሮ ለመገንዘብና በዚያው ላይም ከጨመሩ በኋላ “Freiheit ist radikale selbstbestimmung in der Gestaltung von sich selbst und der Natur” (Fichte) ለማስተገበር ይጠቅማል::

  ያንተው መንደር ያበቀላቸውን Universal Genieዎችን ፣ ማለትም the Platons, Senecas, Shakespears, Mohammeds እና እንዲሁም ያሬድ-ያሬዳውያን ብትጠቅስልን?

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.