አምልኮ ይብቃን ፤ ከግለሰብ ይልቅ ለትውልድ የምናሻግራት ሀገር ትበልጣለችና!! –  ከመኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

abiy w

እንደመጊቢያ

በኢትዮጵያ የህዝብ ና የመንግሥት ታሪክ ውሥጥ ፣መንግሥት  ለህዝብ፣”በሚገባው ልክ፣”የሚገባውን ክብር የሚሠጥ እንዳልነበረ ይታወቃል።(በዛ ጊዜ ዘመን ፣የሥልጣኔ ደረጃ ፣  ርእዮት እና የኃያላን ሀገሮች ተሥፋፊነት  ተፅእኖን አዳብላችሁ ድምዳሜ ላይ መድረሥን እንዳትዘነጉ።)

ያለፉት ዘመናት ፣ከፈጣሪ የተቀቡ ንጉሣዊ ና የመሳፍንት አገዛዞች ፣ህዝቡን፣” እኔ አውቅልሃለሁ።” ሲሉት፣ ከደርግ ጀምሮ እሥከ ወያኔ ኢህአዴግ የነበሩት መንግሥታት ደግሞ፣ በህዝብ ሥም ፣በቡደን ሥም፣በቋንቋ ሥም ጥቂቶች ብቻ በህዝብ ጫንቃ ላይ ተቀምጠው ነበር።

እነዚህ ሁለት መንግሥታት ፣ የጎላ ልዩነት ቢኖራቸውም ግልፅ አንድነት አላቸው። ሁለቱም፣ ራሳቸውን መሳፍንት ያደረጉበት እና አምልኩኝ በማለት ያላከበሯቸውን ፣ ተቀናቃኞቻቸውን በመግደል፣በማሠር፣የህዝብ ጠላት እንደሆኑ በማጉላት ይመሳሰላሉ።ቅጥያ ሥም በመሥጠት ና በጠላትነት በመፈረጅ፣ እና በማሣደድ ሥልጣናቸውን ለማራዘም የጣሩበት መንገድም ያመሣሥላቸዋል።ያም በአብዮት ሥም፣ቀኝ መንገደኛ፣የኢፔራሊዝም ቡችላ፣አድሃሪ፣ቀልባሽ፣መሐል ሠፋሪ፣ፊውዳል፣የአብዮታችን ጠላት ወዘተ ሲል፣ይሄ ደግሞ ትምክህተኛ፣ነፍጠኛ፣ጠባብ፣የብሔር፣ብሔርሰቦች ጠላት ይል ነበር። ሁለቱም ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚገባውን ክብር ያልሰጡበት፣ የአገዛዝ ዘመን እንደቀልድ  እብሥ ብሏል።

 አንድ

እነሱን እዚህ ላይ ለጊዜው አንጠልጥለን  የንጉሦቹን የአገዛዝ ዘመን ለአፍታ እንቃኝ። የንጉሳውያኑ የአገዛዝ ዘመን ፣በቀጥታ ከነገደ ይሁዳ ጋር የተገናኘ፣ በክርስትና ኃይማኖት ላይ የተመሠረተ፣ሰለሞናዊ ወይም ይሁዳዊ ነበር።ንጉሦቹም ከዓምላክ ተቀብተናል ሥላሉና ብዙሃኑም፣” ይህንን ትርክት” እውነት ነው።ብሎ እንዲቀበል በኃይማኖቱ አማካኝነት ሥለተነገረው፣የሀገረና የህዝብ ገዢ ነኝ የሚለውን መሣፍንትና መኳንንት ፣መለኮታዊ ሥልጣን እንዳለው ያምን ነበር።ሞላው የኢትዮጵያ  ዜጋ ያምን ነበር ብለን መደምደም ግን አንችልም።ሀገሪቱን እነማን እንደሚያሥተዳድሮት ወይም ገዢዎቹ እነማን እንደሆኑ የማያውቀው ይበዛ እንደነበር ማዋቁም ከጅምላ ረገማ ያድነናል ።

በዛ ያለማወቅ እና የጭለማ ዘመን የሀገሪቱ ዜጋ ዘጠና ፐርሰቱ በገጠር የሚኖር በመሆኑ እና በቂ መሠረተ ልማት እና የዕውቀት መገብያ ትምህርት ቤት ሥለሌለው ፣ገዢዎቹን ያለማወቁ አይገርምም ።ከዚህ እውነት አንፃር፣ አብዛኛው ዜጋ፣  በየተራ ሢፈራረቁ የነበሩትን ንጉሦች “ፈጣሪ የሾመልኝ ገዢዎቼ ናቸው።” ብሎ ባያምንም፣ጥቂት የማይባለው፣ የከተማ ኗዎሪ ግን፣ንጉሦቹን ከማመን አልፎ የመልክ እንደነበር አይካድም።ይህ የማምለክ ሥነ-ልቦናም፣ንጉሦቹ፣በጦርነት፣በብሽታ እና በአመፅ ሲወድቁ፣  እንዲሸበር እና ለህይወቱ እንዲሰጋ እንዳደረገው በታሪክ ተጠቅሶል። የዚህን እውነት ለማሳየት፣የዓፄ ዮሐንስ ፣ የዓፄ ቴዎድሮስ ፤ የንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እና የፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያምን አገዛዝ መጥቀሥ በቂ ነው።

ዓፄ ዮሐንስ በእምነታቸው የገዘፉ፣ የክርስቶስ እና የክርስትና አፍቃሪ እንደነበሩ ይታወቃል።ክርስትና እንዲሥፋፋ ፣እምነት የሌላቸውን ወደ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በሰላም እንዲመጡ እንዲያምኑ ከማድረጋቸውም ባሻገር፣መስሊሞቹን በሰይፍ ክርሥቲያን ማድረጋቸውንም ታሪክ ይነግረናል።…

ዓፄ ዮሐንስ በአክራሪ ኃይማኖተኝነት ብቻ ሳይሆን፣በጀግንነታቸውና ለሀገራቸው ዳር ድንበር፣በመተማ  ፣አንገታቸውን የሰጡ ፣ የራሥ ቅላቸው ካርቱም ውሥጥ በድርቡሽ ሠራዊት የተጨፈረበት፣ ኢትዮጵያ ለዘላለም የምትዘክራቸው፣የኢትዮጵያ ዜጎችም እጅግ የሚያከብሯቸው፣ጀግና ሰማዕት መሆናቸው እርገጥ ነው።

አፄ ዮሐንስ  ድል እያደረጉ ሳለ ነበር ድንገት በጥይት ተመተው የቆሰሉት።የመቁሰላቸው ወሬ ሲሰማ እያጠቃ ያለው ሰራዊት ማፈግፈግ በመጀመሩ ፣ድርቡሾች ያልታሰበ ድል አግኝተዋል።ይህ አንዱ መሪን የማምለክ በሽታ የጎንዮሽ ጉዳት ነው።

ዓፄ ቴዎድሮስ፣እንደ ዓፄ ዮሐንስ ፣ባህላቸውን እና ኃይማኖታቸውን ለሌላ ህዝብ በግድ  አሥገድዶ ለመጋት ሲጥሩ አልተሥተዋሉም።፣ማለት ይቻላል ።አጭር የሥልጣን ዘመናቸውን ከመሣፍንታት ጋራ ሲዋጉ እና ኢትዮጵያን  ለማዘመንና የተበታተነውን ሥልጣን በአንድ ንጉሥ ፣አጠቃሎ ለማሥተዳደር ሲጥሩ በሴራ ፖለቲካ የተጠለፉ መሪ መሆናቸው ግን አይካድም ።

ይህ ብቻ አይደለም በኢትዮጵያ ነገሥታት ታሪክ፣ዘራቸውን ከይሁዳ ጀምሮ የሚቆጥሩ እንዳልነበሩና፣ በአሥተሳሰባቸውም  ከነበረው የወቅቱ ዜጋ የቀደሙ እንደነበሩ ታሪክ ይመሠክራል ።በነበራቸውም ተራማጅ አሥተሳሰብ ሳቢያ፣ከህዝቡ ነባር ባህል ፣ወግ፣እና ልማድ ጋራ ተላትመዋል።

ይልቁንም ከእምነት አንፃር፣ ከሠራተኛ ብዛት ይልቅ ተቀምጦ ሰማይን በመመልከት የሚውለው በመብዛቱ ፣በኦርቶዶክስ ቤተ ክርሥቲያን አሠራር ላይ ጣልቃ በመግባት ከሰባት ባነሰ ካህን ሁሉም ቤተክርሥቲያን እንዲተዳደር በማድረግ የቀረው፣አርሶ እንዲበላ በማሥገደድ ፣ከቤተክርስቲያኗ ጋራ ታላቅ ቅራኒ ውሥጥ መግባታቸው ለውድቀታቸው ዋንኛ ሰበብ ሆኗል።በወቅቱ አራተኛው መንግሥት ወይም እንደመገናኛ ብዙሃን የሚያገለግለው በየአጥቢያው ያለው ቤተ ክህነት ነበርና ሰፊ ሥም የማጠልሸት ፕሮፖጋንዳ ተነዛባቸው።

በዚህ በውሸት በገነነ ፕሮፖጋንዳንዳ ሰበብም በህዝቡ የነበራቸው ቅቡልነት እንዲሸረሸር ፣በቤተ ክርስቲያኗ ካህናት አማካኝነት  ሥማቸውን ጥላሸት የመቀባት ታላቅ ሴራ፣እንዲሠምር  ፤ በህዝብ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት  እንዲመክን እና ተከታይ እንዳይኖራቸው ተደርጓል።በመጨረሻም ያለአንዳች ሃይ ባይ የእንጊሊዙ ጀነራል ናፒየር ጦር መቅደላ ድረሥ ዘልቆ ፣ በዘመናዊ መድፍና የጦር መሣሪያ ጥቂት ጦራቸውን ድል በማድረግ፣የአገዛዝ ዘመናቸው እንዲያከትም ቢያደርግም፣የእሳት ሰደድ የሆነው እጃቸውን ግን ለመያዝ ከቶም አልቻለም።

የኢትዮጵያን ጠላት በሚያነደው የእሳት ሰደድ እጃቸው የሽጉጣቸውን ቃታ ሥበው ፣ለመላው ኢትዮጵያ ጀግንነታቸውን አብሥረው፣ሀገርና ህዝብን አኩርተው በመሞት የወራሪውን የኢንግሊዝን ጦር እና ታላቋን ብሪታንያን ያሳፈሩ ትውልድ የሚኳራባቸው ጀግና መሪ ናቸው።ይህንንም ያረጋገጠ ግጥም በዘመኑ ተገጥሟል፦

ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ በጃቸው

ገደልን እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው

(ጀግናው ቴዎድሮስ ሞቶም አሸነፋቸው)

ምን ይሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው ???

በወቅቱ የነበረው ብዙሃን(ተራው ህዝብ) እሳቸውን ከማድነቅና ከማምለክ ውጪ ሥለመጪው የሀገር መሪ ሲያሥብና ሲጨነቅ አልተሥተዋለም።

ንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከእምዬ ምንሊክ( ለንጉሥ ሚኒልክ ደግነት  ብዙሃኑ ህዝብ የወጣላቸው ሥም ነው።)  ተፈጥሯዊ ሞት በኋላ እውነተኛውን ወራሽ ልጅ ኢያሱን፣በሴራ ፓለቲካ በተባባሪዎቻቸው አማካኝነት ሥማቸውን በማጠልሸት ፣ተቀባይነት በማሳጣት ለንጉሠ ነገሥትነት የበቁ፣ በሴራ የሚመራ አገዛዝን የመሠረቱ ፣በሳል መካሪዎችን በዙሪያቸው ያሰባሰቡ መሪ ነበሩ።ይህንን እውነት የፊትአውራሪ ኃይለጎርጊሥ(ሐብቴ አባ መላ) አባባል ይመሠክርልናል።

“ቁጭ ብለን የሰቀልነውን፣ቆመን ማውረድ አቃተን።” ማለታቸውን ታሪክ ያሥታውሳል።

ንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣እንደተፈሩ፣እንደተከበሩ ና እንደተመለኩ እሥከሞት እዘልቃለሁ፣በማለት ኢትዮጵያን ለአርባ ዓመታት ገዝተዋል።በ80 0መታቸው እንኳን ሥልጣን በቃኝ በማለት ለዘመናዊ አሥተዳደር እጅ ለመሥጠትና ሥልጣን ለማካፈል አልፈለጉም።”ዛሬም ህዝብ ያመልከኛል ሥልጣኔን አላከፍልም።የኢንግሊዝ ዓይነት አሥተዳደር በሀገሬ እንዲመሠረት አልፈቅድም።እኔ ከሞትኩ ሠርዶ እንዲበቅል አልፈልግም ።”በሚል ግትር አቋም፣ይህቺን ሀገር በዘዴ ወደሥልጣኔ ለመውሰድ የሚደረገውን የምሁራንን ትግል ማኮላሸታቸው ይታወቃል።

በመጨረሻ እሳቸውም ፣አሽከሮቼ ናቸው በሚሏቸው ወታደሮች በትራስ ታፍነው፣የሞትን ፅዋ፣እንደማንኛውም ሰው ቀመሱ።ሰው መሆናቸውም የበለጠ ተረጋገጠ ።ዓምላኪዎቻቸውም  “ለካሥ ንጉሡም እንደኛ ሰው ነበሩ?”ሲሉ በመገረም ጠየቁ።ከዛስ?

ሁለት

ጊዜዊ ወታደራዊ መንግሥት ወይም “ደርግ” ሥልጣንን ባለው ጠመንጃ ጉልበት በመያዝ፣ሀገርን አረጋግቼ፣ፓርቲዎች እንዲቋቋሙ በማድረግ ሥልጣኔን  ለሲቪል መንግሥት እለቃለሁ ብሎ ሲያበቃ፣ቀስ፣በቀስ ሥልጣን እየጣመው፣በመምጣቱ “ከዝሆን በላይ ማን አለና!?” በማለት ህዝብ መረጠኝ ብሎ፣አንድ ዓይነት አሥተሳሰብ ባለው፣የኢትዮጵያ ሠራተኛ ፓርቲ  “ኢሠፓ ” ሥም ሸንጎ አቋቋመ።እናም “ፈጣን ነው ባቡሩ ፣ቀርፋፎች እንዳትገፈተሩ!”  በማለት እያሥፈራራ ጉዞውን ቀጠለ።

የከተማና የገጠሩ ህዝብ ባገኘው የከተማ ቤትና የመሬት ባለቤትነት ቱሩፋት “ደርግ ሺ ዓመት ይንገሥ “አለ።ህዝቡ እንዲህ ቢልም በደርግ ውሥጥ የአንድ ሰው አምልኮ እንጂ ፣ዴሞክራሲ፣እና ለነገ ትውልድ ማሰብ ባለመኖሩ ፣ለውጪ እና ለውሥጥ ጠላቶቻችን የተመቸ አመራር በደርግ ውሥጥ ተሰግሥጎ ነበር።ህዝብ  ከወቅታዊ ችግሩ መፍትሄ አንፃር በሥሜታዊነት  በየዘመኑ የተነሱ አምባገነን መንግሥታትን ሲደግፍ ኖሯል።

ደረግ የወታደራዊ መንግሥት ነበረ።ለመንግሥትነት ያበቁትም የጠልፎ መጣል ወይም የሴራ ፓለቲካ አራማጆች የእርሥ በእርሥ ሹክቻ ነው።የወቅቱም የዓለም ፖለቲካል ኢኮኖሚ ደርግን ጠቅሞታል።

የወቅቱ ፖለቲካል ኢኮኖሚ መዘውር ያለው በሶቬት ህብረት እና በአሜሪካ መዳፍ ውሥጥ ነበር።እናም ደርግ በምሁራኖቹ ምክር(ለምሳሌ፣ በእነ ሰናይ ልኬና በእነ ኃይሌ ፊዳ )አማካኝነት ወደ ሶሻሊሥቱ ዓለም ጎራ ተቀላቀለና ማርክሲስት ነኝ አለ።እናም ኢማሌድህ የተባለ ማርክሲስት ድርጅትን መሥርቶ ወደ ኢሠፓአኮ(የኢትዮጵያ ሠራተኛ ፖርቲ አደራጅ ኮሚሺን ) ነት፣ ወዲያው ተቀየረ። ከዛም ኢሠፖ (የኢትዮጵያ ሠርቶ አደር ፖርቲ) የሚባል ፖርቲ መሠረትኩ በማለት ” ከጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም አብዮታዊ አመራር ጋር ወደፊት ! ” በማለት በዝሆንነት ሥልጣን ያዘ።

ደርግ በዝሆንነት፣የበላይ ራሱን ሲያደርግ፣ የብዙሃኑ ጭፍን የግለሰብ አምልኮ እንዳገዘው ይታወቃል። ኮ/ል መንግሥቱን ጥቂት የማይባሉ ዜጎች በመላው ኢትዮጵያ ያመልኳቸው ነበር። “ምነው እንደሳቸው ዓይነት አንድ አሥር ሰው ሀገሬ በኖራት ?” ብሎም የመኝ ነበር።እነዚህ ዜጎች በስሜት ተገፋፍተው እንዲህ ዓይነት ድምዳሜ ላይ መድረሳቸው ባያሶቅሳቸውም፣በተጨባጭ ግን ደርግ ፀረ-ዴሞክራሲ እና ፀረ-ፍትህ እንዲሁም ፀረ-ሰብአዊ መብት ነበር።የደርግ መሪ የነበሩት ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃ/ማርያም ፍፁም አምባገነን እና የአንድ አብዮተኛን ደም በሺ ፀረ-አብዮተኛ ደም ለመመንዘር ቆርጠው የተነሱ ከህግ በላይ የሆኑ ፈላጭ፣ቆራጭ መሪ  ነበሩ። (ያለሐፍረት ቂጡን በሳንጃ እየወጋን…ከመኪና እየዘለለ..ወዘተ እያሉ በሥተመጨረሻ በክቡሩ ሰው ላይ ማሾፋቸውንም አንዘነጋም።)

ደርግ በመንግሥቱ ያለአዋቂ ሳሚነት፣በሃምሳለቃ ለገሠ አሥፋው፣ፎጋሪነት ፣የፖለቲካና የወታደራዊ ኃይሉን የሚዘውረው አመራር ሽባነት ተኳታኩቶ ሀገሪቱንም የባህር በር አሳጥቷል።

ሀገሪቱ የባህር በር እንዳታጣ መንግሥቱ ኃይለማሪያም እሥከ መሥዋትነት ሊዋጋ አልያም የአሰብ ራስ ገዝ በኢትዮጵያ እንዲካተት ከአሜሪካኖቹ ጋራ መደራደር ይችል ነበር።ወይም አሥቀድሞ በ1981 ዓ/ም መፍረክረኩን  አምኖ ፣ለኢትዮጵያ አንድነት ሲል፣  ሥልጣኑን ለጠንካራ እና ለመሰዋትነት ለተዘጋጀ፣በኃቅ ሀገርን ለመምራት ለሚችል፣የሀገር ወዳድ ሥብሥብ፣ ሥልጣኑን ማጋራት ማጋራት ነበረበት።ሥልጣኑን ለማጋራት ባለመፈለጉ፣ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ተሥማምቶ ሀገሪቱን አሥገንጥሎ ወደ ዙምባቢዌ ከብልሏል ።ይህ የመሪው የመንግሥቱ ኃይለማሪያም ፍርጠጣ በኢትዮጵያ የጀግንነት ታሪክ ትልቁ የታሪክ ጠባሣ ሆኖ ተመዝግቧል።በአሣፋሪነቱ።

የኢትዮጵያ ጦርም ይህ ኩብለላ ጭንቅላቱን በመዶሻ የተመታ ያህል እንዳሳመመው ታሪክ የዘገበው እውነት ነው።ሰውየው ወንበራቸው ላይ እንደ ቋንጣ ተጣብቀው ይሞታሉ ተብሎ ነበር የታሰበው።”ዳግማዊ ቴውድሮስ ናቸው መንጌ !”ለማለት የቋመጠም ነበር።…

ከደርግ ውድቀት  በኋላ ፣ የትግራዩ ነፃ አውጪ ነኝ ባዩ “ወያኔ ኢህአዴግ” የኢትዮጵያ መንግሥት ሆነ ።የኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑንን ሳያረጋግጥ፣ የሽግግር መንግሥት ሆኖ እያለ፣ አይኑን ሳያሽ ኤርትራ ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ እንድትገነጠል ሥምምነቱን ለተመድ በአንደኝነት ገለፀ።

ይህንን እውነት መለሥ ብለን ስናጤነው እጅግ የሚያሳዝነን ነው።ህወሓት የኢትዮጵያ መንግሥት ሆኖ እንዲሁም ያለማንም ጣልቃ ገብነት ትግራይን እያሥተዳደረ    እንኳን  የነፃ አውጪነቱን ሥም ያለመቀየሩ “የመጀመሪያዎቹን ባንዶች ዓላማ” አሥፈፃሚነቱን ይመሠክርልናል።የመጀመሪያው ባንዳ ፣ኤርትራን አሥገንጣይ  በግብፅ መንግሥት ሠልጥኖ ኤርትራን ለመገንጠል ከኢዲሪስ አዎቴ ጋራ ግምባር ፈጥሮ የተዋጋን “ወልደአብ ወልደማሪያም ነው። ” ህወሓት ከዚህ የግብር አባቱ ዓላማ የዘለለ ሌላ ዓላማ የለውም።በደሙ ውሥጥም ኢትዮጵያዊነት የለም።ቢኖር እኮ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነ የነፃ አውጪነት ሥሙን ይቀይር ነበር።ግን አልቀየረም።27 ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ እያሥተዳደረን የነበረው የግብፅ ባንዳ ነው።በሜቴክ አማካኝነትም ግድቡ በጎርፍ እንዲፈራርሥ የማይረባ ግንባታ ሲያሥደርግ የነበረ የህሊና ቢሥ የሆዳሞች ጥርቅም ነበር።

መንግሥት ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በህሊና ቢሥነት እና በሆዳምነት ይታወቃል።የኢትዮጵያን ጦር የደርግ ጦር ነው ብሎ አፈናቅሏል።አያሌ የሀገርን ንብረት በሥርቆት ለግል ጥቅሙ አግዟል ።ሠርቋል።አያሌ ምሁራንን ከዩኒቨርስቲው አባሯል።በቋንቋ ሥም ብዙዎቹን የሲቪል ሠርቪሥ ባለሙያዎች ሥራ አልባ አድርጓል።ያለ ፍርድ ፣በጅምላ ፍረጃ ሌባ ነው ወዘተ ነው ብሎ በአደባባይ ገድሏል።(ኋላ ላይ እሥከምትያዝ ሌብነት ሥራ ነውና በሥራህ ቀጥል በማለት ሌብነትን አበረታቷል።ሀገራዊ የሆነ ሥሜት እና በዜግነት መኩራት እንዳይኖር አድርጓል።ሀገራዊ ሥሜት ያላቸውን በግምገማ ትምክህተኛ፣ነፍጠኛ፣ጠባባብ፣አሸባሪ በማለት አሸማቋል።

ይህ ማሸማቀቅ ጥቂት የማይባሉት ኢህአዴጎች የሚያመልኩት መለሥ ከሞተ በኋላም ተጠናክሮ በመቀጠሉ ፣የፍትህ ፣የእኩልነት፣የሰብዓዊ መብት ጥያቄው እየጋለ መጥቶ አመፅ ተከተለ ።አመፁ ሲስፋፋም ብዙዎቹ የህወሓት ሰዎች ከበርቴ ሥለነበሩ በሱሥ ባህር ውሥጥ እየዋኙ ነበር።ቁልፍ ፣ቁልፍ የመንግሥት ሥልጣን በያዙት፣በወታደራዊ፣በፖሊሥና በሲቪል መሪዎቻቸው ተመክተው ነበር የሱስ ዋናውን ያጦጦፉት። ይሁን እንጂ ፣የተመኩባቸው ሊያድኗቸው ከቶም አልቻሉም።

የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር በቋንቋው መማር።በቋንቋው አሥተዳደራዊ መፍትሄ ማግኘት እንዳይደለምበአመፁ ፍፃሜ፣ ተረጋገጠ።የሰው ልጅ በምልክትም ሊግባባና ሊረዳዳ ይችላል ።የምልክት ቋንቋ የመግባብያ ቋንቋ ነው።የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው መብት ና ነፃነቱ እንዲከበርለት ነበር።

ህዝቡ ማለትም ኢትዮጵያዊነቱን አምኖ በዜግነቱ ኮርቶ የሚኖረው ህዝብ፣ ተፈጥሯዊ እና ህገ መንግሥታዊ መብቱ እንዲከበር ይፈልግ ነበር።

የንግግር ና የህሊና ነፃነቶችን ወይም መብቶችን ፤የመደራጀት፣በሰላማዊ መንገዶች የመቃወም፣በየትኛውም የሀገሩ ክፍሎች ተዘዋውሮ የመሥራት ፣የመኖር እና ንብረት የማፍራት ፤የፈለገውን እምነት የመከተል ፣በህይወት የመኖር ፣ፍትህ በእኩልነት የማግኘት መብት።ከበሽታ የመጠበቅ መብት።ወዘተ በእኩል ደረጃ በየትኛውም ክልል አልነበረም።

(የማይካደው ነገር በቋንቋ ሥም ጥቂት ጉልበተኞች፣ደፋሮች ና ህሊና ቢሶች ፣ከመንግሥት ሌቦች ጋር ተመሣጥረው በመሬት ችርቻሮ ሚሊዮነር እና ቢሊዮነር እንዲሆኑ አድርገዋል።መሪው አቶ መለሥ በግልፅ እንደተናገሩት “በቀላሉ የማይመነጠር የሙሥና ደን ፈጥረው ነበር።”ይህ እውነት ነው ከመንበራቸው ያወረዳቸው።ይህ እውነት ነው ጀግናው የትግራይ ህዝብ ልጅ ጫማ ሥር ወድቀው ከመጣብን የህዝብ ቁጣ አሥጥለን እያሉ  እንዲማፀኑ ያደረጋቸው።

የትግራይ ህዝብ አካል የሆነው ሚሊሻ፣ልዩ ኃይልና ፖሊሥ ፣በህዝቡ ላይ በሚደርስ ጭቆና የተነሳ ፣ብሶት በወለደው   አመፅ በሚከሰት የተቃውሞ እንቅሥቃሴ፣  ከህዝቡ ጋር እንደሚቆም ማወቁ ለንሥሐ ያበቃቸዋል ብዬ አምናለሁ።በቅርቡ በዚምባቡዌ እና በሱዳን የተከሰተውን አመፅና የወታደሩን ወገንተኝነት ማሥታወሥ የወያኔ ደልቃቃ ባለሥልጣኖችን ከእንቅልፋቸው አንቅቶ ለንሥሐ ካላበቃቸው መጨረሻቸው ጥርሥ ማፋጨት ይሆናል።

ሦሥት

ዛሬ የሀገሪቱን የሥልጣን መንበር የያዘው የለውጥ መንግሥት ከመጋቢት 24/2010 ዓ/ም ጀምሮ ፣የተጓዘበት መንገድ በነውጥ የተሞላ ነበር።በኢትዮጵያዊነት ለውጥ ሊያሥከትል የሚችለውን የየከተሞችን ወጣት ኃይል ቢያሠባሥብም ፣ኋላቀሩ፣የ19ኛው ክ/ዘ የቋንቋ፣ የጎሣ እና የነገድ አሥተሳሰብ ፣በይቅርታ በገቡት ላይ ሠፍሮ፣ ሃምሳ ዓመት ወደኋላ ሀገሪቱን በመጎተት ፣ የቆዳ ማዋደድ እና የዘረኞች  ፍልሥፍና  ነፍሥ ዘርቶ ሀገር ሠላሞን እንድታጣ እያደረገ ነው።

እነዚህ ሰዎችን ” የቋንቋ እና የጎሣ (እናንተ የዘር እና የብሔር እኩልነት የምትሉት) እኩልነት ፣በደርግ የሶሻሊሥት ሥርዓት እውን ሆኗል ።ጭቁን የሚባሉ ወደጨቆኝነት፣ተጨቋኝ የተባሉት ወደጨቋኝነት ተቀይረው፣ሰውን ያለፍርድ በእጅ ብልጫ ገና ከጅምሩ ገድለዋል።መሬት እና ትርፍ ቤትን ለህዝብ እና ለጪሰኛው አከፋፍለዋል።…በአጠቃላይ ሁሉንም እኩል አድርገዋል።ሴቶችን ጭምር ከማጀት ወደ አደባባይ አውጥተዋል።ይባሥ ብለው  ኃይማኖትን ተራ በማድረግ ፣ ጥቂት የማይባለውን ወጣት ከግብረ ገብ ውጪ አድርገው ፈጣሪውን በማሥካድ፣ ሥድ አድርገውታል።….” ከዚህ ጥያቄ ውጪ ምን ነበራችሁ? ብለን ልንጠይቃቸው ይገባል።እውነቱን ዛሬም ባይቀበሉትም።

ይህንን እውነት ግን ዛሬም ጭቆና እና ተጨቋኝ በሌለበት ፣ነፃ አውጪዎቹ ፣ጎምቱ ፖለቲከኞች አይቀበሉትም። “ዛሬም ጭቆና አለ።ዛሬም በባርነት የሚኖር ነፃ ያልወጣ ግለሰብ ፣ቡድን ወይም ህዝብ አለ ።” ብለው፣በሠላም እንታገላለን ብለው፣በይቅርታ የገቡ፣የበሥተጀርባ የገንዘብ ድጋፋቸው የነ ግብፅ የሆነ ሀገርን የመገንጠል ህልም ያላቸው ቡድኖች ያምናሉ።ግብፅ ለምንድነው አክራሪውን የሙርሲን መንግሥት በአልሲሲ ጦር ያሥገለበጠችው?ከቶሥ ለምንድነው እርሱን እና አክራሪዎችን ሁሉ ወደ ዘብጥያ የላከችው?በሀገሯ ሠላም፣ፀጥታ፣የህግ የበላይነት እንዲከበር አይደለምን?በበኩሌ ህዝብ የሚፈልገው፣ነፃነት፣እኩልነት፣ወንድማማችነት፣ፍትህ፣ሚዛናዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲሁም የህግ የበላይነት ሳይሸራረፍ እንዲከበር ነው።

የህግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ መንግሥት ካለ፣ማንም፣ማንንም ያለ ፈቃዱ እና ያለህግ ከመሬቱ ላይ አያፈናቅለውም።ማንም  ጉልበተኛ በሀገር ኗሪነት ሥም እየተነሳ ፣ይህንን መዓድን ያለእኔ ፈቃድ አታወጣም በማለት ቡር ፣ቡር እያለ፣ መንገድ አይዘጋም።ንብረት አያቃጥልም።…

በየትኛውም ቋንቋ የተደራጁ በነፃ አውጪ ሥም የተደራጁ ቡድኖች ወይም ድርጅቶች ለተራው ህዝብ የሚያሥገኙት ፋይዳ የለም።እርግጥ ነው፤ በሥሙ በመነገድ ለራሳቸውና ለዘመዶቻቸው ሀብት ያፈራሉ፣ልጆቻቸውንም በአውሮፖና አሜሪካ አሥተምረው ተንቀባረው እንዲኖሩ ያደርጋሉ።በውጪ ሀገር ገንዘብ በዶላር ያከማቻሉ።በሀገር ውሥጥ ደግሞ ኪራይ የሚሰበሥቡበት ፎቅ ይገነቡና፣በየወሩ እሱን እየሰበሰቡ ” ዓለም በጎኔ አለፈች።” ይላሉ።

ለውጡን በሪፎርም ደረጃ ዝቅ እንዲል እየገፋፋ አቅመ ቢሥ እንዲሆን ያደረገው ይህንን ሁሉ ፣በህግ ተጠያቂ የሚያደርግ እውነት እና የህግ ጥሰት፣” ይቅር ለፈጣሪ።” በማለቱ ነው። ከወያኔ ኢህአዴግ የተኮረጁ የቋንቋ ፣የጎሣ፣የመንደር፣እና የወንዝ መተማመኖች እንዲቀጥሉ በመፍቀዱ ነው።ለውጡ አሠሡንም ገሠሡንም በአንድ ላይ ይዞ ለመጎዝ መምረጡ እና በጊዜ ሂደት በውሥጡ ያለውን ቆሻሻ አጠራለሁ ማለቱ በራሱ ፣ለውጡን በሪፎርም ደረጃ ዝቅ አድርጎታል።

ይህ ወደ ሪፎርም ደረጃ ዝቅ ያለው ለውጥ፣ከኃጫሉ ሁንዴሣ ሞት በኋላ ፣ወደለውጥ የመሸጋገር ብልጭታ ቢያሳይም፣ብልጭታው ወደ በርሃን ከፍ እንዲል ፣”የአራተኛውን መንግሥት “ኃቀኛ ድጋፍ ይፈልጋል።ጋዜጠኞች ልብ በሉ፣አድር ባይ ብዕር ይህን የለውጥ ጅማሮ ይገለዋል።

ማጠቃለያ

ጋዜጠኞች የሙያ ሥነምግባሩ በሚፈቅድላቸው መሠረት፣ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክ ለዚህ ትውልድ በማሥረጃ እና በመረጃ አሥደግፈውም ማሣወቅ ይኖርባቸዋል።ለዚች ሀገር ሉአላዊ ክብር ከጠላቶቿ ጋር በጀግንነት ተጋድለው የወደቁትንም በማውሳት፣ይህ ተውልድ ይህቺን ሀገር ያገኘው በታላቅ መሥዋትነት እንጂ እንዲሁ በዋዛ እንዳይደለ ሊያሥገነዝቡትና የሀገር ፍቅሩን በማጎልበት በኢትዮጵያዊነቱ እንዲኮራ ሊያደርጉት ይገባል።

ከዚህ አንፃር አንዳንድ በሳተላይት የሚተላለፉ ሚዲያዎች ዘወትር እያቀረቡት የላውን ነፃ ሃሳብን አደንቃለሁ።በሶሻል ሚዲያውም እንደ ” ዘ ሐበሻ” ያሉት ሚዲያዎች ሃሳብን በነፃነት እና በእኩልነት ማሸራሸራቸው ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ምሥረታ የጎላ አሥተዋፆ አለው።

” ከአድር ባይ ሚዲያ ባዶ ምሥል ይበልጥ ይናገራል።” እና።ምንም የሚናገሩት እውነት  ከሌላቸው ሚዲያውን በክላሢካል ሙዚቃ ብቻ ቢተውልን የበለጠ ለማሰብ ይረዳናል።

ዛሬ ኢትዮጵያ ካለፉት ዘመናት መንግሥታት ትንሳኤና ውድቀት፣ የምትማርበት የሞት እና የሽረት ጊዜ ላይ፣ትገኛለች።ይህንንም የለውጡ መንግሥት ከጅምሩ የተገነዘበ ይመሥለኛል።እናም ካለፉት መንግሥታት ውድቀት የበለጠ የመማር ዕድል እንዳለም የተገነዘበ ይመሥለኛል።ይህንን ያልኩትም ከፖርቲው ሥያሜ ተነሥቼ ነው።ከዘር የፀዳ “ብልፅግና ” የተሰኘ ፖርቲ መመሥረት በራሱ አንድ የለውጥ እምርታ ነው እና የምር ብልፅግናን እንዲያመጣ ፣ሃቀኛ ሂስ በመሥጠት ልንደገፈው ይገባል።ዝም ብለን በደምሳሳው በየቴሌቪዢኑ ዛሬም የደርግ እና የወያኔን የወገነ ፕሮፖጋንዳ የምንነዛ እና ሁል ጊዜም ጠ/ሚ እንዳሉት ማለት የምናበዛ እና ያዘጋጀናቸውን ካድሬዎች የምናሥለፈልፍ ከሆነ በቀቀኖች እንጂ ጋዜጠኞች ልንባል አይገባንም።

አንድን ክንውን በዛ ጊዜና ሰዓት በሚዲያ ካቀረብነው ፣ያ ክንውን ካለፈ በኋላ ሁሌ መደጋገሙ አሥፈላጊ አይደለም። ግለሰቡ ከልት ልሁን ሳይል በራሱ ከልት ለመፍጠር መጣጣር አግባብ አይመሥለኝም።

“የብልፅግና ፖርቲም” ቢሆን በውሥጡ ከመሪው ከዶክተር  አብይ አህመድ እኩል ወይም የበለጠ ማሰብ የሚችሉ ምሁራኖቹን ማካተት ሲችል ነው፣ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና የሚያሻግር  ፖርቲ የሚባለው።ትላንት መለሥ ሲሞት የሚተካውን እንዳልፈጠረ ሁሉ፣ነገም አብይ ሲሞት የሚተከው የለም። እያልን ማላዘን የለብንም።ይህ በራሱ አምልኮ ነውና ከአምልኮ እንድንወጣ ፖርቲው ገና ብዙ ሥራ ና ከሌሎች ተቃዋሚ ፖርቲዎች እሥከመዋሃድ የሚያደርሥ ሆደ ሰፊነት ይጠበቅበታል እላለሁ።

እውነቱን ለመናገር ለእኔ ከብልፅግና ፖርቲ ይልቅ ኢትዮጵያ ትበልጥብኛለች።እናም አምልኮ መፍጠርም ሆነ አንድ ግለሰብን ለማምለክ መጣጣር ይብቃ።ለሀገር ሁለተናዊ ጥቅም ፣ ለህዝቦቿ እኩል ተጠቃሚነት፣ለጋራ እድገቱ፣ለብልፅግናው፣ላልተሸራረፈ ፍትህ፣ለሠላም፣ለህግ የበላይነት በመላ ሀገሪቱ መሥፈን ሁላችንም በቅን ልቦና እንሥራ ።ይህቺ ሀገር ህግ የበታች ሆኖ ከተተረማመሠች ማናችንም ተጠቃሚ እንደማንሆን ዛሬ በሠላሙ ወቅት እንገዘብ ።አምልኮ ይብቃ!!

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.