በአንድ ሀገር ውሥጥ መንግሥት መኖሩ የሚታወቀዉ በዲሞክራሲ መኖር አይደለም: – ተሥፋዬ በቀለ ከምዕራብ አዉስትሬልያ

Lawandorder01በዜጎች በሠላም ወጥቶ የመግባት ዋሥትና (law and order) መጠበቅ ነው:: የትም አገር ዉስጥ መንግሥት ከሌለ ሕዝባዊ ማን አለብኝነት (አናርኪይ) ይንሠራፋል::

እኛ አገር ግን መንግሥት እያለ ሕዝባዊ ማንአለብኝነት እንደ ደራሽ ዉሃ ድንገት እየመጣ ዜጎችን ይጨፈጭፋል:: ገድሎ እስከመሥቀል –  እስከ ማቃጠልና በመኪና እስከመጎተት ይደርሣል:: ሰዉን በሕግ_ ዉሻን በሠንሠለት ገድቦ መያዝ ምድራዊ ግዴታ ነው:: ታድያ መንግሥት ባለበት ሀገር ሰዉ እንደ ንብረት እዴት ይወድማል  …?
ያኔ የጫካ ወንበዴዎች ተብለዉ በሚድያ ብቻ የምናዉቃቸው በመለስ ዜናዊ ተመርተዉ አዲስ አበባ የገቡት አማፂ ኃይሎች መንግሥት አልነበሩም:: ግን የ “law and order” ጀግኖች ነበሩ:: “law and order” ለማስጠበቅ መንግሥት መሆን አላስፈለጋቸዉም:: ኢ ሔን ለማድረግ ለነሱ ሰዉ መሆን ብቻ በቂ ነበር::
ታድያ ዛሬ ምነዉ የክልል መንግሥት –  የፌደራል መንግሦት ብለን_ መንግሦት በመንግሦት ሁነን ሣለ ሀገር ሲነድ ቁመዉ የሚያዩ ጉዶች ላይ ወደቅን ? እሺ መንግሥታዊ  ኃላፊነቱ ይቅር _ እንዴት ነዉ ሠባት ሠዓት የፈጀ ሠቆቃ ንፁሃን ዜጎች ላይ ሲፈፀም ሠብአዊ ተነሳሺነት የማይኖራቸዉ ?
ኢሔ ወንጀል ተራ የሕግ ጥሠት አይደለም:: ጅምላ የሰው ፍጅትና ግዙፍ የንብረት ውድመት ነው:: በኦሮምያ ክልል ዉስጥ ሦሥት ጊዜ የደረሰዉን ጅምላ ጭፍጨፋ ደምረን ካስከተለዉ ሠቆቃ ጋር አያይዘን
ካየነው ዓለም ዐቀፉን የዘግናኝ ጅምላ ጭፍጨፋ መለክያ መሥፈርት ያሟላ ጥቃት ነዉ::
የክልሉና የፌደራሉ መንግሥት ግን የሠቆቃዉን ኢሠብአዊ ግዝፈት አሳንሶ ለማሳየት የደረሠዉን እልቂትና ውድመት “ግጭት ” ሲሉት በተደጋጋሚ ተስተውለዋል:: ኢሔ በወንጀሉ ጭብጥ ላይ የተቃጣ የትርጉም አፈና ጉዳዮን በገለልተኛነት ለመዳኘት መንግሥታዊ ቅንነት አለመኖሩን አመላክቶን አልፏል:: በመሆኑም ለጥቃት አድራሹ ወገን የልብ ልብ ሠጠና ለሦሥተኛ ዙር ዕልቂት ወገኖቻችንን ዳረገ ::
የሦሥተኛዉ ዙር ጅምላ ጭፍጨፋ በግልፅ የሚያሣየዉ ከአሁን በፊት በተደረጉት ሁለት ጭፍጨፋዎች ላይ በሕግ የተወሠደዉ የተጠያቂነት እርምጃ የደረሰዉን ዕልቂትና ዉድመት ያልመጠነ መሆኑን ነዉ::

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአማራ ትግል፣ ኢትዮጵያዊነትና የቴዎድሮስ ካሳሁን ዘፈን

ሕጉ :-
1/ በደረሠዉ ጥፋት ክብደት ልክ አልከበደም !
2/   በደረሠዉ ጥፋት ቁመና ልክ በጠያቂነት አልቆመም !

ኢሔ ማለት :-
የክልሉ መንግሥት ፍትሕን ለማረጋገጥ ሣይሆን ሕገተሣትፎን ለማስተናገድ ያህል ብቻ ሠርቷል ማለት ነዉ:: ኢሔ ማለት ደሞ ዕልቂትና ዉድመት በደረሠባቸዉ የኦሮሚያ አከባቢዎች የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎች የሕግ ይሁንታ እነጂ የሕግ ከለላ የላቸዉም ማለት ነዉ::
* አደጋዉ ያለዉ እዚህ ጋ ነዉ::
ሕጉ ድሮም ነበር – ኦሮሞ የሆኑትም ያልሆኑትም ዜጎች ድሮም የነበሩና አብረዉ የኖሩ ናቸዉ:: ስለዚ ችግሩ  ከሕጉም አይደለም – ከሕዝቡም  አይደለም:: ችግሩ አስተዳደሩን የሚዘዉሩት ሰዎች የሥብዕና አሠላለፍ ከአስተዳደርና ከፍትህ ሳይንስ አፈንግጦ ወደ ዛገ ዘረኝነት የሸፈተ መሆኑ ነዉ:: አስተዳደሩን የሚዘዉሩት ሰዎች የሕጉን አፈፃፀም ይዘዉራሉ:: በእነዚህ ሰዎች ሕጉ ሳይሆን የሕጉ አተገባበር  “አይዞህ አለሁልህ በለዉ  – ግን  አትቁምለት ” በሚል ሸፍጠኛ የሕግ አካሔድ የተቀረፀ ነዉ ::  በቃልም ሆነ በፊደል “አለሁልህ” ሲል ሕጉ የሕግ ይሁንታ ይሠጥሃል:: የሕግ አተገባበሩ ግን ሕጉ በአካል ላንተም ሆነ ስላንተ እንዳይቆም የተሠጠህን የሕግ ይሁንታ ተግባራዊነት ይነሣዋል:: ኢሔኔ “ሕግ የተፃፈለት ነገር ግን ሕግ ያልቆመለት – ለአደጋ የተጋለጠ ከለላ አልባ ዜጋ ትሆናለህ” ማለት ነዉ:: በተለያዩ የኦሮምያ አካባቢዎች ዉስጥ ለዕልቂት የተዳረጉት ወገኖቻችን ያለቁት እዚህ መቀራቅር ውስጥ ገብተዉ ነዉ::
ኢሔን ሕጉን ተከልሎ የሚሠራ ‘defacto policy” ቀርፀው ወደ ሥራ የገቡት አስተዳደሩን የሚዘውሩት ሰዎች ናቸዉ:: ሕጉንም – ፖሊሱንም – ልዩ ኃይሉንም – ሕዝቡንም የሚገዙ እነሱ ናቸዉ:: “if they are incharge, they are accountable” ሕጉ ግልፅ ነዉ ::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዐምሐራ / ነፃ ህዝብ | ቬሮኒካ መላኩ

አሁንም የክልሉ መንግሥት :-
1/ ለተገደሉት የሕይወት ካሣ
2/ ለወደመዉ ንብረት መተኪያ
3/ ለተፈናቀሉት የፈለጉበት ቦታ
ሂደዉ አዲስ ሕይወት የሚጀምሩበት መቋቋሚያ ከሞራል ካሣ ጋር እዲከፍላቸዉ
በሕግ መያዝ አለበት::
የፌደራሉ መንግሥት ኢሄን ፍትሃዊ ግብ ለማሣካት ከክልሉ ዓመታዊ በጀት ላይ ቀንሶ የእነዝህን ስዎች ካሣ በመክፈል የሕግ ተጠያቂነትን በቃል ሳይሆን በተግባር ማረጋገጥ ይጠበቅበታል ::
ኢሄ እስካልተደረገ ድረስ አሁንም ኦሮምያ ውስጥ ላሉ ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎቻችን የሕግ ከለላ የለም:: በሕይወት ላሉት በሕይወት የመኖር ዋስትናቸዉ የሚረገጠዉ በግፍ ለተገደሉት ፍትሕ ሥናገኝ ብቻ ነዉ ::
ኢሄ ጥያቄ የሕግ ጥያቄ የሚሆነዉ ጉዱዩ በሀገር ዉስጥ በሀገራችን መንግሥት ከታየ ብቻ ነዉ :: ፌደራሉ መንግሥት ኢሄን ጥያቄ እንደተለመደዉ አለባብሶት ካለፈ _ ኢሄ ጥያቄ ወደ ዓለም ዐቀፉ መድረክ ይሄዳል :: ያኔ ግን የሕግ ጥያቄ አይሆንም – ከዛ በላይ ነዉ:: ያኔ እኛም የምንጠይቀዉ ኢሄን ብቻ አይሆንም :: የወንጀሉ ጭብጥ እዛጋ ሲደርስ የሚመዘዉ መዘዝ
ብዙ ነዉ :: ኢትዮጵያ ኢሄን ማሣካት የሚችሉ በዓለም ዙርያ የተበተኑ ብዙ ብርቅዬ ልጆች አሏት::ሗላ ያገራችን መንግሥት
እንዳያዝንብን:: ዓለምዓቀፉ ሕግ መንግሥታዊ ሉዓላዊነትን የሚያከብርላቸዉ “law and order” በማስጠበቅ መንግሥታዊ ሕልዉናቸዉን {legitimacy} ማስከበር ለቻሉ መንግሥታት ብቻ ነዉ:: መንግሥታዊ ሉዓላዊነት ሥልጣን አይደለም – ዕዉቅና ነው:: ዕዉቅና ደሞ ፀንቶ የሚቆመዉ በተሠጣቸው ዕውቅና ልክ ፀንተዉ ለቆሙት ብቻ ነዉ::
ስለዚ… ፌደራሉ መንግሥት በተሸከመዉ ኃላፊነት ልክ የጉዳዩ ክብደት ገብቶት መፍጠን አለበት:: እየነደደ ያለዉ ሣሩ አይደለም _ ሰዉ ነዉ !
ኢሄ… መንግሥት እንዳለው ግጭት ሳይሆን አናርኪውን በሚሾፍሩት የክልሉ መሣፍንት ለፌደራሉ መንግሥት የቀረበ የመንግሥትነት ፈተና ነዉ:: እዚህ ጋ እየተፈነና እየተፈተሸ ያለው መንግሥት የሥልጣን መምበር ላይ መቀመጡ አይደለም – በሀገር ልክ መቆሙ ነው… !
ለመንግሥታችን ልቦና ይሥጥልን እያልኩ ለዛሬ በዚሁ አበቃሁ… !

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስ ለኢህአዴጋዉያን “ወገኖቼ” - ይገረም ዓለሙ

“ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር…!”
ተሥፋዬ በቀለ
ከምዕራብ አዉስትሬልያ::

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.