አዎ ዛሬም ከቋንቋና ባህል የምተርፍ ኢትዮጵያዊ ነኝ! (በድሉ ዋቅጅራ) (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)

Bedluሰሞኑን አንድ የዩቲዩብ ቻናል ከአመት በፊት ከዋልታው ስሜነህ ባይፈርስ ጋር ያደረግኩትን ቃለ ምልልስ ቀንጭቦ፣ ‹‹አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ . . . የሚባል ቋንቋና ባህል እንጂ ሰው የለም›› በማለቴ የስድብ ዘመቻ እየመራብኝ ነው፡፡
.
ይህንን ሀሳብ የሚቃወም ሰው የመጀመሪያ መከራከሪያ መሆን የሚገባው፣ የዚህ ወይም የዚያ ብሄረሰብ ወይም ጎሳ አባል ነን፣ በሚሉ ሰዎች መካከል ከቋንቋቸውና ከባህላቸው ሌላ የሚለያቸውን ጉዳይ በማቅረብ መከራከር ነው፡፡ ለምሳሌ በአንድ አማራና ኦሮሞ መካከል ከቋንቋና ከባህላቸው ውጭ ምን ልዩነት አለ? ልዩነቱ ሁለቱ ከሆነ ደግሞ በተቀረው ሁሉ ይመሳሰላሉ ማለት ነው፡፡ በሁለቱ ስለተለያዩ የተለያዩ ሰዎች ናቸው ካልን ደግሞ፣ ሰው ከቋንቋና ባህል የሚተርፍ መገለጫ የለውም ማለታችን ይሆናል፡፡
.
በመሰረቱ ሰው ድርብርብ (ዘርፈ ብዙ) የማንነት መገለጫዎች አሉት፤ ግለሰባዊ – ቤተሰባዊ – ቀዬያዊ – ጎሳዊ/ብሄረሰባዊ – ብሄራዊ – ሰብአዊ፡፡ ከነዚህ መካከል አንዱ ላይ የጨነገፈ ወይም አንዱ ላይ የተጣበቀ የማንነት አበያየን ለጤነኛ ማህበረሰባዊ አወቃቀር ጋሬጣ ነው፡፡ ግለሰባዊ ማንነትን ጨፍልቆ፣ ብሄራዊ ማንነትን አሽቀንጥሮ፣ ጎሳና ብሄረሰብ ላይ ብቻ መጣበቅ የሰብአዊነት ውርጃ ነው፡፡ ላለፉት ሀያ ሰባት አመታት የተከሰተውም ይኸው ነው፡፡
.
ማንነትን በብሄረሰብን ወይም በጎሳ ብቻ መበየን ሰው በመሆናችን ከተጎናጸፍነው የሰብአዊነት ጸጋና ክብር ያወርዳል፡፡ ዛሬ የሌላው ብሄረሰብ ሞት እንደራሳችን የማያመን፣ አልፎም የሌላውን ብሄረሰብ ሞት እንደፖለቲካዊ የስልጣን መወጣጫ ስልት የምንከተለው፣ ማንነታችን ብሄራችንን ተሻግሮ ሰብአዊ እሴቶችን እንዳይመለከት በመሰንከሉ ነው፡፡
.
ለማኝኛውም እኔ ማንነቴ በግለሰብቴ፣ በአባትነቴ፣ በሰፈሬ፣ በብሄሬ፣ በሀገሬና በሰውነቴ በየደረጃው የሚገለጽ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡
.
.
ኢትዮጵያዊ ነኝ
.
በላሊበላ አስቀድሼ፣ ሸህ ሁሴን ባሌ የተገኘሁ፤
በአባ ገዳ ተመራርቄ፣ መካ ላይ እርዝቅ ያገኘሁ፡፡
ሀመር የቡርጆ አደራ
ፈጣሪ ከሰጠኝ በረከት፣ ዘመን አያነጥፈው ወረት፤
የሚገባኝን ለሰጠኝ፣ የሚገባውን የምገመድል፤
ለሞላልኝ የማላጎድል፡፡
በሲዳማ ጨንበለላ፣
በወላይት ጊይታ፣
ቢያሻኝ በቅዱስ ዮሀንስ፣
የዘመን ጥባት የምከትብ፣ አዲስ አመት የማወድስ፡፡
በጅምላ የማልቀመስ፤
በችርቻሮ የማልረክስ፡፡
ኢትጵያዊ ነኝ!!
ኢትጵያዊ ነኝ!!
ሳነቴ ላይ ውርጭና ጉም፣ ዳሽን ጫፍ ግግር በረዶ፤
ደሎ መና የአዋራ ጭስ፣ ዳሎል ላይ የእሳት እርጎ፡፡
ይርጋለም ያጋጥኳትን ላም፣ ወለጋ ላይ አስጠቅቼ፤
ትኩስ እንገርዋን የጠጣሁ፣ አክሱም ጫፍ ጥገት አስሬ፤
ሰሜን ያለብኩትን ወተት፣ በአርሲ ጮጮ የሞላሁ፤
ጋምቤላ ወተቱን ንጬ፣ የሀረሪ ቆንጆ የቀባሁ፡፡
ወሰን የለሽ እግረ ፌንጣ፣
ሞተ ሲሉኝ ብን – ትር የምል፣ ሄደ ሲሉኝ የምመጣ፤
የቅዠት ምች፣ ህልም ፈቺ፣ ዳነው ሲሉኝ የማገረሽ፤
ወሰን አልባ እግረ ሞረሽ፡፡
ጎጥ አይበቃኝ – የሀገር ስፍር፤
ጎሳ አይገልጠኝ – የሰው ስእል፡፡
ኢትጵያዊ ነኝ!!
ኢትጵያዊ ነኝ!!
ማሳዬ ላይ ገበሬ፣ ምድር አራሽ፣
ድንበሬ ላይ ወቶአደር፣ ጠላት ደምሳሽ፤
ከበሬዬ ቀንበር ከሞፈር፣
ከወገቤ ላይ ዝናር፣
ከጀርባዬ ላይ ዲሞትፈር፣
የማላጣ፤
ለወደደኝ እንዳወዳደዱ፣ ከማሳዬ ፍሬ የማልሰስት፤
ለጠላኝ እንደ ድርፈቱ፣ ከጀርባዬ ባሩድ የምግት፤
እልኸኛ!
እንደምስጥ በቁም የምጥል፤
ተበድዬ የማልተኛ፡፡
ለደፈሩኝ አድዋን ያህል ተራራ፣ ሀውልት ያቆምኩ በሀገሬ፤
ነጻነቴን – ሰንደቄን ያተምኩ፣ ሮም ላይ ተሻግሬ፤
ያውም እንደፈጠረኝ፣ በባዶ እግሬ፤
ኢትጵያዊ ነኝ!!
እንደ እየሱስ እንጂ በፍቅር፣
ለመርዘኛ የተንኮል ስፍር፣
የማልመች፣ አታጥልሉኝ ባይ፣
ክታብ የአብሮነት ሲሳይ.፣
በጅምላ የማልቀመስ፤
በችርቻሮ የማልረክስ፡፡
ኢትጵያዊ ነኝ!!
ጃውሌ የደንጊያ እጣን፣ ከርቤ ከጊንር ቋጥሬ፤
አቦዳይ ጫት ተዘይሬ፤
ጂማ ካባጁፋር መንደር፣ ከአዎል – በረካ ጀባ፤
ሶዶ ዋዳ ተዘፍኖልኝ – ጎዴ ላይ ቃጢራ አድሬ፤
አፋር ላይ በግመል እንገር፣ ምርቃናዬን የሰበርኩ፤
የሀገሬን ባንዲራ፣ ለአፋር ግመል ማተብ ያሰርኩ፡፡
ወሰን የለሽ፣ እግረ ፌንጣ፣
ሞተ ሲሉኝ ብን – ትር የምል፣ ሄደ ሲሉኝ የምመጣ፤
የቅዠት ምች፣ ህልም ፈቺ፣ ዳነው ሲሉኝ የማገረሽ፤
ወሰን አልባ እግረ ሞረሽ፡፡
ጎጥ አይበቃኝ – የሀገር ስፍር፤
ጎሳ አይገልጠኝ – የሰው ስእል፡፡
ኢትጵያዊ ነኝ!!
ተጨማሪ ያንብቡ:  አገራዊ ቀውስና  የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን መሪዎች ሚና በታሪክ                                                                                                                                                                                                  

1 Comment

  1. እግዚአብሔር ዕድሜና ጤና ይስጥህ ወንድሜ ዶ/ር በድሉ፣ እውነት ብለሃል። ከሰው የወረዱ የዘመናችን ሀገርና ሕዝብ አጥፊ ፣ ክልል ጥራዝ ነጠቅ ጉዶች ለሚነዙት ወሬ አንዳች ሳትበገር፣ከጎንህ ያሉትን የእናት ሀገራችንን የኢትዮጵያን ትንሳኤ በተስፋ የሚጠባበቁ ሚሊዮኖች የሀገርህን ልጆች እያስብህ አሁንም አብዝተህ ፃፍ፣ተመራመር፣ በዕውቀትና በእውነት መንገድ ላይ ተመላልስህ አመላልስን። ዘመን ተሻጋሪ አስተሳስብህና፣ ፍላፃ ብዕርህ ምናልባትም አንተ ከምትገምተው በብዙ እጥፍ በላቀ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ገብቶ የሀገር ፍቅርን፣አንድነትንና፣ለእውነት መቆምን የሚያጠናክር መልካም ተግባር ነውና በርታ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.