ያልተዘመረለት ጀግና – ሰለሞን ታደሰ (ሻምበል)

General Hussen Ahmed ያልተዘመረለት ጀግና    ሰለሞን ታደሰ (ሻምበል)በቅርቡ በማህበራዊ ገጽ ባገኘሁት መረጃ መሰረት የሰሜኑ ጦርነት በሸንፈት ከተገባደደ ከ29 ዓመት ቦኋላ በጄኔራል ሁሴን አህመድ ደጋፊዎች እና በሚተቿቸው መካከል የማየው እሰጥ አገባ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንድሰጥ ጋበዘኝ።

በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ወታደራዊ ኮሌጅ የ4ኛ አመት ተማሪ ሳለሁ የናደው እዝ በ1980 ዓ.ም በመደምሰሱ ምክንያት የቀረኝን አንድ ዓመት ሳልጨርስ በእናት አገር ጥሪ ወደ ኢትዮጵያ ከጓደኞቼ ጋር በመጠራታችን የኤርትራዉን ጦርነት 12ኛ ብርጌድ ከተመደበበት ከመስከረም 1/ 1945 ዓ.ም ጀመሮ እስከ 1983 ድረስ የነበረውን የሁለተኛ አብዮታዊ ሰራዊትን ታሪክ በጥልቀት ለማጥናት ሞክሬያለሁ።ምንም እንኳን ከጄኔራል ሁሴን ጋር አብሮ የመስራት እድል ባይገጥመኝም በኢትዮጵያ ሰራዊት ውስጥ ለ18 አመታት በማገልገል የሻምበል ማእረግ በመድረሴ፣ በኤርትራ በነበረው ጦርነት ዙሪያ የተጻፉ መጽሃፎችን በማንበብ እና ከሳቸው ጋር ካገለገሉ የሰራዊቱ አባላት ጋር ባደረኩት ውይይት ስለ ጦር ሜዳ ውሏቸው በቂ ግንዛቤ አግኝቻለሁ።

ኮሎኔል አምሳሉ ገብረዝጊ”የኤርትራ መዘዝ” በሚለው መጽሃፋቸው ገጽ 116-117 ላይ እንዳሰፈሩት ሜ/ጀኔራል ሁሴን አህመድ በትውልዳቸው የወሎ ሰው ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪ ሳሉ በአጼ ሃይለ ስላሴ ተመርጠው ቀ/ሃ/ስላሴ ጦር አካዳሚ( ሃረር) ተልከው ወታደራዊ እና የአካዳሚ ትምህርታቸውን ተከታትለው በም/መ/አለቅነት ተመርቀዋል። Alumni/First Course/Haile Selassie I Harar Military Academy በሚለው ድህረ ገጽ መረጃ መሰረት ስማቸው በ22ኛ መስመር ላይ ይገኛል።ይህ ቁጥር Gentleman Cadet(GC#) የሚባለው የመለያ ቁጥራቸው ነው።
ለተጨማሪ ወታደራዊ ትምህርት አሜሪካ ተልከው ስልጠና የተከታተሉ ሲሆን በ United Nations India-Pakistan Observation Mission በወታደራዊ ታዛቢነት ኢትዮጵያን ወክለው አገልግለዋል።ከዚህ ተልኳቸው ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በመማር በ Public Administration የመጀመርያ ዲግሪ ተቀብለዋል። በተለያዩ አስተዳደራዊ ሃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተው ደርግ ሲቋቋም ደግሞ የሌ/ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም አማካሪዎች መሃል አንዱ ሆነው አገልግለዋል። የሚሊሺያ ጦር ሲቋቋም ደግሞ በብርጌድ አዛዥነት፣ የ14ኛ ሚሊሽያ ክ/ጦር አዛዥ፣የዉቃው እዝ ም/አዛዥ እና ዋና አዛዥ እና የሁለተኛ አብዮታዊ ሰራዊት ዋና አዛዥ በመሆን አገልግለዋል።

ጄኔራል ሁሴን አህመድ ከፍተኛ የአስተዳደር ችሎታ ያላቸው፣ ለበታቾቻቸው ጥሩ ምሳሌ የሆኑ፣በስነ ስርዓት የታነጹና ጥሩ አስተማሪ፣በሙያቸው በቂ እውቀትና ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ በመሆናቸው ጥራት ያለው የዉግያ አመራር የሰጡ ናቸው በማለት ምስክርነታቸውን ያስቀምጣሉ።

በመጨረሻም የግንቦት13 /1983 ዓ.ም የፕሬዝዳንት መንግስቱን አገር መልቀቅ ተከትሎ ላለፉት ሃያ ዘጠኝ አመታት በስደት በመኖር ላይ ይገኛሉ።

ከዚህ በመቀጠል በተለያዩ ጊዜ አወዛጋቢ የሆኑት 4 አበይት ጉዳዮች እናያለን።

 

ኢላበረድ

ሻምበል ተስፋዬ ርስቴ በ2001 በታተመው “ምስክርነት” በሚለው መጽሃፉ በገጽ 312-313 ላይ 506ኛ ንኡስ ግብር ሃይል “ሀ” አዛዥ የሆኑትን ኮሎኔል ሁሴን አህመድ ለታሪክ ሽሚያ ሲሉ ጦሩ ላይ ጉዳት አድርሰዋል ብሎ ይከሳል። ኮሎኔል እስጢፋኖስ ገብረመስቀል( በወቅቱ የ506ኛ ግብር ሃይል ም/አዛዥ የነበሩ) “ለሀገር ፍቅር ሲባል የተከፈለ መስዋእትነት” በሚለው መጽሃፋቸው ገጽ 261-274 በሰፊው ተንትነው ጉዳቱ የደረሰው ሻምበል ተስፋዬ እንዳለው በችኮላና ከጥንቃቄ ጉድለት ወይም ለታሪክ ሽሚያ ሳይሆን ትእዛዝ የመጣው ከአብዮታዊ ዘመቻ መምሪያ ከኮሎኔል ገብረክርስቶስ ቡሊ እና የሶቭየት አማካሪያቸው ጄ ቮሮሆቭ መሆኑን ገልጸው የእርምት ማስተካከያ ጽፈዋል።

የ506ኛ ግብር ሃይል የማይደፈር የተባለዉን እና ሻእቢያ ይመጻደቅበትና ይኩራራበት የነበረውን የአስመራ ዙርያ ምሽግ ህዳር 12/1971 ዓ.ም የደረመሰ ጀግና ጦር ነው።
በዚህ ባልተለመደ ትእዛዝ መሰረት ኮሎኔል ሁሴን መልሶ መቋቋም ያላደረገ ጦራቸውን ይዘው ከአዲተክለዚ በምሽት ወደ ከረን ተንቀሳቀሱ። የወገን ጦር ኢላበረድ ደርሶ ከታንክና ከተሽከርካሪዎች ወርዶ ቀኑን ሙሉ በውግያ እና በጉዞ ስለደከመ ማረፍ ጀመረ።ሳያውቀው የሻእቢያ ደፈጣ ውስጥ ገብቶ ኖሮ ያልታሰበ ውግያ ገጠመው።

የዚህን የውግያ ዉሎ ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማርያም(በወቅቱ የ506ኛ- ለ ንኡስ ግብር ሃይል አዛዥ) በ”የጦር ሜዳ ውሎ” መጽሃፋቸ ገጽ 246 ላይ እንደሚከተለው አስቀምጠውታል።

“የሻእቢያ ጦር በመጀመርያ በሞርታርና በእጅ ቦምብ ቀጥሎም በቀላል መሳርያ ትጥቁን በፈታ፣መሳርያዉን ባጋደመ የወገን ጦር ላይ የተኩስ ዉርጂብኝ አወረዱበት።መሬት ቀዉጢ ሆነ። የወገን ጦር የሞት ሞቱን ከጠላት ጋር አንገት ለአንገት እየተናነቀ በእጅ ቦምብና በሳንጃ እየተዋጋ ከጠላቱ እንደተናነቁ ተቃቅፈው ወደቁ።

እዝና ቁጥጥር አልነበረም።የሬድዮ ግንኙነት ተቋረጠ። ታንኮችና ወታደራዊ ተሽከካሪዎች አብዛኛዎቹ በጸረ ታንክ መሳርያ ወደሙ። የኤላበረድ ምድር በደም ታጠበ።ሰማዩ በጥቁር ጢስ ተሸፈነ።የመድፍ እና የታንክ ጥይቶች በሙቀት ሃይል በራሳቸው ጊዜ ወደ ተለያዩ አቅጣጫ እየሄዱና እየፈነዱ የወገንና የጠላት ተኩስ መለየት አልተቻለም። የሰው ልጅ ሬሳ በእሳት ተለብልቦ ወገንና ጠላት መለየት አይቻልም።ሜዳው በሙሉ የሰው ልጅ ሬሳ ነው።ተዋጊ ጄቶች እየተመላለሱ ቦምብ ይጥላሉ፣መትረየስ ይተኩሳሉ፣ወገንና ጠላት ስለተቀላቀለ ማን በማን ላይ እንደሚተኩስ በዉል አላወቁም። የወገን ጦር በወገን ተዋጊ ጀቶች ከጠላት ጋር አብረው ይደበደባሉ።”

ጄኔራል ሁሴንን ጨምሮ ከዚህ ውግያ የተረፉ የሰራዊቱ አባላት በፈጣሪ ሃይል ሁለተኛ እድል ያገኙ እንጂ ሌላ ቃል አይገኝለትም። እንዲህ አይነቱን የጦር ሜዳ ውሎ አጠልሽቶ በማጣመም ማቅረብ ለህሊና የሚከብድ እና መስዋእት በከፈሉ ጀግኖች ላይ መቀለድ ይሆናል።

General hussien Ahmed ያልተዘመረለት ጀግና    ሰለሞን ታደሰ (ሻምበል)

አልጌና-የውቃው  እዝ  መደምሰስ

አልጌና እስከ 45 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርስ በጣም ከፍተኛ ሙቀት ያለው ለወታደራዊ እንቅስቃሴ የማይመች ግን ደግሞ ናቅፋን ለመቆጣጠር በጣም አስፈላጊ የሆነ በምስራቅ ወደ ቀይ ባህር ፣በምእራብ ደግሞ ወደ ሱዳን የሚያዋስን ቦታ ነው። ከቀጠናው ስፋት በመነሳት ከቀይ ኮከብ ዘመቻ ጀምሮ ውቃው እዝ 15 እግረኛ ክፍለ ጦር፣ 19ኛ ተራራ ክፍለ ጦር፣23ኛ እ/ክ/ጦር እና 29ኛ ሜካናይዝድ ብርጌድ ተመድበዉለት ጠላት ናደው እዝ ላይ ከጀርባ ጥቃት እንዳያደርግ ቀጠናውን ሲጠብቅ ቆይቷል። ጠላት በ1974ዓ.ም የቀይ ኮከብ ዘመቻ እንዲከሽፍ ያደረገው በዚህ ግንባር ባደረገው የቀድሞ ማጥቃት ነው።
የዚህን ግንባር አስፈላጊነት በመረዳት ይመስላል ሻእቢያ ውቃው እዝን ለመደምሰስ በ 1975 ዓ.ም እና በ1976 ዓ.ም አጋማሽ ላይ በተደጋጋሚ ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቷል።

ሻለቃ ንጋቱ ቦጋለ”ትውልድን ያንቀጠቀጠ ጦርነት” በሚለው መጽሃፋቸው እንደገለጹት 19ኛ ተራራ ክ/ጦር ወደ ናደው እዝ ለቆ እንዲዛወር ሲደረግ ከቃሮራ እስክ ተክሲ ያለዉን ቀጠና ውቃው እዝ በ23ኛ ክ/ጦር እና በ15ኛ ክ/ጦር ብቻ እንዲከላከል ተደረገ። በወቅቱ የእዙ ዋና አዛዥ ሆነው የተሾሙት ኮሎኔል ሁሴን አህመድ(ሜ/ጄኔራል) የዚህን የሃይል ማነስ ጉዳይ ለበላይ አካል በተደጋጋሚ ሪፖርት ቢያደርጉም ምላሽ አለማግኘታቸውን በወቅቱ የእዙ ልዩ መገናኛ ከነበረው አስፋው ዘአልጌና ከሚባል ወታደር መረዳት ችያለሁ። ሻእቢያም ይህ መረጃ የደረሰው በሚመስል መልኩ ያለ የሌለ ሃይሉን አሰባስቦ በሚያዝያ 1976 ዓ.ም የውቃውን እዝ ደመሰሰ።በዚህም ምክንያት ኮሎኔል ሁሴን አህመድ ወደ አዲስ አበባ ተወስደው በወታደር ፖሊስ እስር ቤት 6 ወር ታስረው ምንም ጥፋት ስላልተገኘባቸው ሪፖርቱ ለሊቀመንበር መንግስቱ ሃይለማርያም ቀርቦ ተፈቱ በማለት በወቅቱ የአጣሪ ኮሚቴው አባል የነበሩት ኮሊኔል እስጢፋኖስ ገብረመስቀል በመጽሃፋቸው ግጽ 330 ገልጸዉታል።ትንሽ ስህተት ቢገኝባቸው ኖሮ በ1974 ዓ.ም የ21ኛ ክ/ጦር አዛዥ የነበሩት የኮሎኔል ዉብሸት ማሞ እድል ይገጥማቸው ነበር።ያም በጦሩ ፊት መረሸን ነው።

 

በ1981 ዓ.ም  ኩዴታ  ስለነበራቸው  ሚና

ሌላው ጄኔራል ሁሴን የሚከሰሱበት ጉዳይ የ1981 ዓ.ም ኩዴታ በማፍረስ ተባባሪ ሆነዋል የሚል ነው።ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገው የጄኔራል ደምሴ ቡልቶ ልጅ የሆነው ደረጀ ደምሴ”አባቴ ያቺን ሰአት” ብሎ በጻፈው መጽሃፍ ስለ ጄኔራል ሁሴን የማክሸፍ ተሳትፎ ማስረጃ ማግኘት እንዳልቻለ ገልጿል።
ሻለቃ ጌታቸው የሮም “ፍረጂ ኢትዮጵያ” በሚለው መጽሃቸዉሜ/ ጄነራል ሁሴን እና ብ/ጄኔራል ገብረመድህን መድሃኔ ከመጠርጠራቸው በስተቀር በማክሸፉ ሴራ ላይ ለመካፈላቸው የሚያስረዳ ሰነድ ወይም ማስረጃ አልተገኘም ብለዋል።
ሻለቃ ጌታቸው የሮም መፈንቅለ መንግስቱን ከአሜሪካ ሆኖ ሱዳንና የኤርትራ በረሀ በመሄድ፣ኢትዮጵያ ደግሞ ባንድ በኩል ከነጄኔራል መርእድ ንጉሴ እና ጄኔራል ፋንታ በላይ ጋር ፣በሌላ በኩል ከነኮሎኔል ተስፋዬ ወልደስላሴ (የደህንነቱ ሃላፊ) እና የፕሬዝዳንት መንግስቱ ልዩ ጸሃፊ ከሆነው ከሻምበል መንግስቱ ገመቹ ጋር ያስተባበረው የ”ነጻ የኢትዮጵያ ወታደሮች ንቅናቄ” አባል ነበሩ።ይህን ተልእኮ በበላይነት ሲያስተባብሩ የነበሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ነበሩ።

 

በግንቦት 1983 ዓ.ም  አስመራን  በሄሊኮፕተር  ለቆ  ስለመውጣት

ወደ ዝርዝር ጉዳይ ከመሄዳችን በፊት የኤርትራን አጠቃላይ ሁኔታ ማየት ጠቃሚ ነው።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ የነበራት ታሪክ እንዳለ ሆኖ በጣሊያን ለ50 ዓመታት ቅኝ መገዛቷ፣ከዛም በእንግሊዝ ስር ለ10 ዓመት በሞግዚትነት ስር መውደቋ ጉዳይዋ በUnited Nations እንዲታይ አደረገው። ከ 8 ዓመት እልህ አስጨራሽ ክርክር ቦኋላ በ UN Resolution 390-A(V) መሰረት September 15,1952 G.C ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ተቀላቀለች።አጼ ሃይለ ስላሴ የነአክሊሉ ሃብተ ወልድን ምክር አልቀበል ብለው ፌዴሬሽኑን November 15,1962 G,C እንዲፈርስ አደረጉ።ይህን አጋጣሚ አስፍስፋ ትጠብቅ የነበረችው ግብጽ የኤርትራን ነጻነት የሚፈልጉትን በግልጽ መርዳት ጀመረች።

ይህ ከላይ የተጠቀሰው እውነታ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊሰጠው ሲገባ በንጉሱም ሆነ በደርግ የተወሰደው ግን ወታደራዊ እርምጃ ነው።የዚያድባሬን የወረራ ጦርነት ተከትሎ ኢትዮጵያ በውስጥም በዉጭም በተወጠረች ጊዜ ሻእቢያና ጀበሃ ከአስመራ፣ምጽዋ፣ ባሬንቱና አዲቀይህ በስተቀር መላ ኤርትራን ተቆጣጥረው ለድል ተቃርበው ነበር።የኮሎኔል መንግስቱ ሃይለ ማርያም መንግስት በምስራቅ የተገኘውን ድል በሰሜን ለማስፋፋት ሻእቢያና ጀብሃን በ1971ዓ.ም በሁሉም አቅጣጫ በመግፋት እስከ አፋቤት ማሳደድ ተችሎ ነበር።ከዚህ በኋላ ጦርነቱ እስከ መጨረሻው ሽንፈት ድረስ ምንም ለውጥ ሳያመጣ ለ12 ዓመታት ቀጠለ።በተለይ በ 1974ዓ.ም ብዙ የተነገረለት እና ከፍተኛ ወጪ የወጣበት”የቀይ ኮከብ ዘመቻ” ያለ ውጤት በሽንፈት አለቀ። ወንበዴን ላንዴና ለመጨረሻ ለማጥፋት የታቀደው በኢትዮጲያ ብር 1 ቢሊዮን የወጣበት ሲሆን ሶቭየቶች 2 ቢሊዮን ዶላር(2 Billion USD) የሚያወጣ መሳርያ አቅርበው ነበር።ቀጥሎ ደግሞ በ 1980 ዓ.ም ዋናው ተከላካይ እና አፋቤትን ለ9 ዓመት ሲከላከል የነበረው ናደው እዝ ተደመሰሰ። በ የካቲት 1982 ዓ.ም ደግሞ የምጸዋ ወደብ በሻእቢያ ቁጥጥር ስር ዋለ።ከዚህ በኋላ ለ አንድ ዓመት ከ 3 ወር የ150,000 ወታደር ቀለብ፣ነዳጅ እና ጥይት የሚጓጓዘው በሶቭየት አንቶኖቭ አውሮፕላኖች ነበር።እንደ ኢትዮጵያ ላለ ደሃ አገር ይህን ማድረግ በጣም ይከብዳል።
እነዚህ ሁሉ የጦርነቱ መጨረሻ ምእራፍ ማሳያ ነበሩ።ሶቭየት ህብረት ከ1983 ዓ,ም በኋላ በብድር መሳርያና ነዳጅ ማቅረብ እንደምታቆም ጎርባቾቭ በሃምሌ 1980 ዓ,ም ለፕሬዝዳንት መንግስቱ ነግረዋቸው ነበር።ኮሎኔል መንግስቱንም አገር አስጥሎ ያስኬደው ይሄ ነው።ለኔ ይህ ጦርነት በቀይ ኮከብ ሽንፈት ጊዜ አብቅቷል።

እንደ አንድ ወታደር አዲስ አበባ በቤተ መንግስት ዘመቻ ደውለው መመሪያ መጠየቃቸውን አብሬው ከተማርኩት የመገናኛ መኮንን መረጃ አግኝቻለሁ።ከፕሬዝዳንት መንግስቱ አገር ጥሎ መሄድ በኋላ ጦሩ ደቀመሃሪን ለቆ አስመራ ነው የገባው። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ጄኔራል ሁሴን ምን ተአምር እንዲሰሩ እንደሚጠበቅ ለኔ ግራ ይገባኛል።እኔም እሳቸው ቦታ ብሆን የማደርገውን ነው ያደረጉት።

ምንም እንኳን በመጽሀፍ የተጻፈ ማስረጃ ባላገኝም በኤርትራ ጦርነት አስመራ የሚገኘው የሁለተኛው አየር ምድብ እና የኢትዮጵያ ባህር ሃይል የተጫወቱት ሚና ወደር የለውም።

በተረፈ ለእናት ኢትዮጵያ ብለው ከቤተሰቦቻቸው ለበርካታ ዓመታት ሳይገናኙ መስዋእት የከፈሉትን ጀግኖቻችንን እየዘከርን ይህ በሽንፈት ያለቀ የጦርነት ፋይል ላንዴና ለመጨረሻ ብንዘጋው ጥሩ ይመስለኛል።

 

ሰለሞን ታደሰ (ሻምበል)
Boston,Massachusetts

 

2 Comments

  1. እኔ የደርግንና የሻቢያን ፍልሚያ የማወዳድረው በቬትናምና በአሜሪካ መካከል ከሆነው ፍልሚያ ጋር ነው። የሮም አወዳደቅ ይሉሃል እንደ ሁለቱ ነው። በታንቡርና በጉራ ጀምሮ እንደ ሸክላ በመፍረክረክ የታሪክ አተላ የሆነው ደርግ የተረታው በሻቢያና በወያኔ የጦርነት ስልት አይደለም። ራሱ ባመነጨው የያዘው ጥለፈው የፓለቲካ አሻጥር እንጂ! የካድሬ ጋጋታ የማይለየው የግንባር ጦርነት ለሃገራቸው በውጭና በውስጥ ተምረው አመራር ሊሰጡ የሚችሉ ወገኖችን ያገለለ ለደርግ ሥርዓት አጎብዳጆችን ያለ ችሎታቸው የሾመ፤ ጠላትን አሳዶ ከመምታት ይልቅ ደርግ እንዳይከፋው እየተባለ ውድ የሰው ህይወት የተገበረለት የጦር አውድማ ነው። እነ ጄ/ታሪኩን ገድሎ፤ ሌሎችን አስሮና ያለምንም በቂ ጥናትና ዝግጅት ከቦታ ቦታ እያዛወረ ያለሙያቸው በመመደብ በአይነ ቁራኛ እንዲጠበቁ ያደረጋቸው የሃገሪቱ ቆርጥ ቀን ልጆች እልፍ ናቸው።
    ሜ/ጀኔራል ሁሴን አህመድና ሌሎችም ለሃገራቸው የለፉ፤ ሃገራቸውን የሚወድ ሁሉ በስደትና በሃገር ውስጥም ይህ ነው ለማይባል ሰቆቃ ተዳርገዋል። ቀሪዎቹም ወያኔና ሻቢያ የከተማ አለቆች በሆኑ ማግስት እየተለቀሙ ታስረዋል፤ ተገለዋል፡ ሞቶ ተገኘ እየተባለም ተቀብረዋል። ጄ/ገናናው ሽፈራው አንድ የሻቢያና የወያኔ ስኳድ ፈልፍሎ ካለበት በመሄድ አምጥቶ የረሸነው እንደ ምሳሌ ይጠቀሳል።
    ችግሩ የትናንቱ አይደለም። የትላንቱ ከትላንት ጋር አልፏል። በዚህ ዙሪያ ላይ እክሌ ልክ ነበር እነዚያ ሃገር ሽጠዋል ምናምን መባሉ ፍሬ ቢስ ነው። ከወያኔና ከሻቢያ ጥይትና እስራት የተረፈው ቀሪ የቀድሞ ሰራዊት አሁን በሃገሪቱ ላይ እየደረሰ ያለውን እልቂት ለማቆም ዘር፤ ሃይማኖት፤ ቋንቋና ክልልን ተገን ሳያረጉ ለህዝባችን ሰላምና ደህንነት መስራቱ ይበጃል። የድሮውማ ከተወሳ ግምሹ ፈገግ ሲያደርግ ቀሪው ደግሞ የቁም ህልም ሆኖ በዓይናችን ላይ ሲታይ ተራፊው ትራጄዲ ነው። እስቲ አንድ ነገር ልበል። ሰውየው በሰራዊቱ ውስጥ ለቤተሰብ ተቆራጭ ደሞዝ ከፋይ ነው። ግን የሞተና የተማረከውን ደርግ ለይቶ የማውቅ ስልቱ ደካማና ካወቀም በህዋላ በተዋረድ ለሚመለከተው ማስተላለፉ ዳተኛ በመሆኑ ደሞዝ ከፋዪ ይህን ተጠቅሞ ብዙዎችን ሳይከፍል ወደ ኪሱ ያስገባል። ሁሌ ዳንስ ነው ሁሌ ጮቤ ረገጣ። ታዲያ ጉዳዪ ሲነቃበት ወደ ጎረቤት ሃገር ለመኮብለል ጠረፍ ጥግ ካለች ከተማ አንድ ሆቴል ውስጥ ተወሽቋል። ይህን የደርጉ የስለላ ድርጅት ደርሶበት ሁለት ወታደሮች ስፍራው ይደርሱና ሙሉ ወታደራዊ ሰላምታ ሰጥተው እንደሚፈለግ ይነግሩታል። እሱም የታጠቀውን ሽጉጥ አውጥቶ አንደኛውን ሲመታው ሌላው የያዘውን ክላሽ ያርከፈክፍበታል። ነገሩም በዚያ ያከትማል። በደርግ ጊዜ ያለቀሰው የሞተበት ብቻ አይደለም። በግፈኞች ሴራ የሚበላው ያጣም ጭምር እንጂ! በቃኝ!

  2. Write your comment…”ለመሆኑ አንተ ማነህ?”ተፅፎ የተሠጠህን ዛሬም ደገምከው?

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.