‘አማራነት’ን መፍራት (Amhara Phobia) – በገ/ክርስቶስ ዓባይ      

በገ/ክርስቶስ ዓባይ
ሐምሌ 23 ቀን 2012 ዓ/ም

Amhara

የአማራነትን ምሥጢር ለመረዳት እጅግ በጣም የመጠቀና የጠለቀ ዕውቀት ያስፈልጋል። ታላቁ መጽሐፍ እንደሚናገረው “የጥበብ መጀመሪያው እግዚአብሔርን መፍራት ነው!” እንግዲህ እግዚአብሔርን የማያውቅ ወይም ደግሞ የማይፈራ ሁሉ የአማራነትን ምስጢር ለመመርመርና ለመረዳት ከቶ አይችልም። ስለሆነም አማራ ያልሆኑ ሁሉ የበታችነት ስሜት ይንጣቸዋል፤ ያሰቃያቸዋል። ከዚህም የተነሣ አማራነትን ይፈራሉ፤ ይንቀጠቀጡማል። በመሠረቱ አማራነት እንዴት ተወለደ (ተፈጠረ)?

የአማርኛ ቋንቋ እስከ 950 ዓ/ም ድረስ በአክሱም ቤት መንግሥት የልዑላዊያን ቤተሰቦች ልዩ የመግባቢያ ቋንቋ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። አማርኛን የሚናገሩት በጣም የተማሩ፤ የተመራመሩ፤ ፈጣሪያቸው የሆነውን እግዚአብሔርን እጅግ የሚፈሩና የሚያመልኩ ነበሩ። ነገር ግን የአክሱም ሥርወ መንግሥት የመጨረሻው ንጉሥ የነበረው ‘አንበሳ ውድም’ በጣም የደከመ መንግሥት ከመሆኑ የተነሳ በዮዲት ጉዲት በደረሰበት ድንገተኛ ጥቃት ከሥልጣን ተወግዶ ወደ ደቡብ በመሸሽ (አማራ ሳይንት) አሁን መካነ ሰላም እየተባለ በሚጠራው የወሎ ግዛት አካባቢ መሥፈሩ ይታወቃል።

ከዚያም የአማራነት ሥነ ልቡና በአካባቢው ቀስ በቀስ እየተዛመተ መስፋፋት ጀመረ። አማራነት አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪነት ብቻ እንዳልሆነ ከዚህ ቀጥሎ ለማብራራት እሞክራለሁ። አማራነት ከላይ እንደተጠቆመው በቅድሚያ ‘እግዚአብሔርን መፍራት ነው!’ ቀጥሎም ሠራተኛና በራሱ ላብ የሚተዳደር እንጂ የማንንም ሰው የግል ሀብትና ንብረት በመዝረፍ ለመበልጸግ አይደፍርም። ሁሉን የሚያይ አምላክ አለና! እንዲህ ያለውን ቅሌትና የወረደ ተግባር በምንም መልኩ አይፈጽምም።

አማራነት ሙሉ እምነቱን በፈጣሪው ላይ የጣለ ስለሆነ ማንንም አይፈራም። ከመጠን ያለፈ በራስ መተማመን አለው። በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረውን ማንኛውንም ሰው ያከብራል። ሰውን ያከብራል ስንል፤ ራሱን የበታች አድርጎ እንዳልሆነ መታወቅ አለበት። ከሃይማኖቱ በወረሰው መሠረት ልክ እንደ ጻድቁ አብርሃም  እንግዳ ተቀባይ ነው። የእግዚአብሔር እንግዳ ወደ ቤቱ ከሄደ እግሩን አጥቦ፤ ምግብ አብልቶ፤ መኝታ ጎዝጉዞ በደንብ ያስተናግዳል። ይህ ከአማራነት መገለጫዎች እንደ አንዱ አድርገን ልንወስደው እንችላላን።

እንግዲህ ይህ የአማራነት ሥነ ልቡና በአካባቢው የሚኖሩትንና የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ የነበሩትን ሁሉ በፍቅር እያቸነፈ ማረካቸው። በዚህ ሁኔታ ቋንቋው፤ የሥራ ባህሉ፤ ሃይማኖቱና ሥነ ምግባሩ ሁሉንም አጥለቀለቀ። ከሁሉም በላይ ቋንቋው የግዕዝ ፊደላትንም የተላበሰ በመሆኑና በቀላሉ ለማንበብና ለመጻፍ በማስቻሉ ግዛቱን በኃይል ሳይሆን በፍላጎት እንዳስፋፋ ለመገመት አያስቸግርም።

ሌላው የአማራነት ጠባይ እሱ ሌላውን እንደማይነካ ሁሉ፤ በአትንኩኝ ባይነቱም ይታወቃል። አማራነት ከምንም በላይ ነፃነትን የሚወድ፤ በአገሩና በሚስቱ ለሚመጣበት ዋዛን የማያውቅ ሲሆን፤ ጠብ ጠማኝ ግን አይደለም። አንድን ግለሰብ ወይንም ቡድን ደካማ መሆኑን አይቶ በዕብሪት ተነሳስቶ በደል ወይም ግፍ ለመፈጸም አይደፍርም። ፈጣሪውን ስለሚፈራ ሥነ ልቡናው አይፈቅድለትም። እንዲያውም ፍቅርና ወዳጅነት መገለጫዎቹ ናቸው። እንዲህ ያለውን ጨዋነት ማንኛውም ለሐቅ የቆመ የሰው ልጅ የሚስማማበትና የሚደግፈው ሲሆን ለሌቦች፤ ለዘራፊዎች፤ ለአጭበርባሪዎችና ለእምነት የለሾች ግን ቅስም የሚሰብር ክስተት ነው።

በአሁኑ ሰዓት አማራነት በመላው ዓለም ተስፋፍቶ ይገኛል። በተለይ በመላው የጥቁር ሕዝብ ሠርጾ ገብቷል። እርግጥ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ከፋፈሉን እንጂ፤ መላው ጥቁር ሕዝብም ኢትዮጵያዊ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ እነዚህ አውሮፓውያን በሚከተሉት የከፋፍለህ፤ አዳክመህ ግዛው ፖሊሲ መላዋን አፍሪካ (የቀድሞዋን ኢትዮጵያ)  በዘር፤ በቋንቋ፤ በሃይማኖትና በጎጥ እየከለሉ ትናንሽ መንግሥታትን ፈጥረዋል።

ይህ ብቻም አይደለም፤ በማከታተል የራሳቸውን የወደፊት አጀንዳና ዕቅድ የሚያረጋግጥላቸው የፈጠራ መጻሕፍትም በማሳተም፤ የአዲሱን ትውልድ ልብ ሲያሻክሩና ሲያሸፍቱ ኖረዋል። ወደፊትም ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ በዚያው ላይ ተጨማሪና ተደራራቢ ሴራ መሸረባቸውን አያቆሙም። የመጀመሪያውን መጽሐፍ እንደ ማጣቀሻ እየተጠቀሙ የሐሰት ትርክታቸውን ያስፋፋሉ። እንዲህ ያለውን እርካሽ መጽሐፍ በማነብነብና ተጓዳኝ ማመሳከሪያ መጽሐፍ ሳያዩ ወይንም ከሊቃውንት ሳያገናዝቡ እንደወረደ ተቀብለው፤ እራሳቸው ከስረው ሌላውን ወገንም የሚያከስሩ የዘመኑ ድንጉላን ሞልተዋል።

አማራነትን፤ ነጭ የተባለ ሁሉ ይፈራዋል። ለምሳሌ ኢትዮጵያችን የአድዋ ጦርነትን ድል የተቀዳጀችው በአማራነት ሥነ ልቡና እንደሆነ ማጤን ያስፈልጋል። በዚህም ምክንያት አውሮፓውያንን ለሽንፈት የዳረጋቸውን ‘የአማራነትን ሥነ ልቡና’ ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋት ከመቶ ዓመታት በላይ ጥረዋል። ግን አማራነት ከፈሪሃ እግዚአብሔር ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ምንም ሊያደርጉት አልቻሉም። ይሁን እንጂ በጥቅም የተገዙ ወይንም እራሳቸውን የአማራ ሥነ ልቡና የሌላቸው አድርገው በሚገምቱና የበታችነት ስሜት በሚንጣቸው ሰዎች አማካይነት፤ በቀላሉ የማይታይ ጥፋት ሲሠሩ ቆይተዋል፤ አሁንም እየሠሩ ናቸው።

የኦሮሞ ልሂቃን ነን ብለው ራሳቸውን የሾሙት ሕዝቄል ገቢሣ፤ በቀለ ገርባ፤ ፀጋዬ አራርሣ፤ ጀዋር ሞሐመድ ወዘተ. የአማራነት ሥነ ልቡና ስለሌላቸው ብቻ፤ አማርኛ ተናጋሪ የሆነውን ሁሉ እንደ ጠላት አድርገው ለማሳየት እየጣሩ ናቸው። እንዲህ ያለውን ለምለም መሬት የፈጠረላቸው ሟቹ መለስ ዜናዊ እንደነበር የሚያጠያይቅ አይሆንም። መለስ እራሱ አማራነትን እየፈለገ ሳያገኘው እንጦሮጦስ ወርዷል። ምክንያቱም፤ ውሸት፤ ዘረፋ፤ ግድያና፤ ጥላቻ የሰይጣን ተግባራት እንጂ አንዱም ፈሪሃ እግዚአብሔር የለበትም። ‘ሞኝ ያስያዙትን አይለቅም!’ እንዲሉ መለስ ከአውሮፓውያን መጽሐፍ የኮረጀውን በተግባር ለማዋል እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ሲታትር እንደነበር የሚካድ አይደለም።

የኦሮሞ ድንጉላን ደግሞ እሱ በልካቸው ያሰፋላቸውን፤ ባራስ ያለመተማመን እና የበታችነት ስሜት ካባ፤ ደርበው ምንም የማያውቀውን የኦሮሞ ወጣት ቄሮ፤ሸኔ፤ አባ ቶርቤ እያሉ በመንጋ ተነሳስቶ የራሱን ሀብት እና ንብረት እንዲያወድም እያደረጉት ነበር።

በተጨማሪም አንዳንድ የማንነት ቀውስ (identity crisis) የተጠናወታቸው የሰይጣን ፈረሶችም አልታጡም። ራሱን ተስፋዬ ገ/አብ እያለ ሲጠራ የነበረው በመጀመሪያ ኤርትራዊ ነኝ ይል ነበር። አሁን ደግሞ ‘ገዳ ገ/አብ በሚል ስም ኦሮሞ ሆኛለሁና እወቁልኝ!’  በማለት ዲስኩሩን ይነፋል። ከአሜሪካ መልስ በሚል ርዕስ የጻፈውን ሕልሙን አየሁለት። ‘የምፅዋ ወደብ ሙቀቱ ስለናፈቀኝ እዚያ ሄድኩ በማለት አናፋ!’ ማንን ለማስጎምጀት ይሆን? ‘ኦሮሞ ነፃ ስትወጣ ከገላን እስከ ቢሸፍቱ እርሻ አርሳለሁ፤ ከብት አረባለሁ’ በማለትም ቃዥቷል። ማንን ለማናደድ ይሆን? ‘አማራነትን የመፍራት አባዜ፤’ (Amhara Phobia) እንዲህ ያለውን የቅዠት ሕልም ያሳያል።

አማራነት እንዲሁ የሚገኝ አይደለም ጥልቅ ዕውቀትና ሥነ ምግባር ነው። በሰው ደም አይነግድም፤ወጣቶች በግብታዊነት ተነድተው ለህልፈት እንዲበቁ አያደርግም፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የሰይጣን ተግባር ነውና።

አሥመራ የነበረው የአሜሪካ ቃኘው ስቴሽን፤ ደካማ ኢርትራዊያን ወንድሞቻችንን ‘ጀሆቫ ዊትነስ’ በሚል ዲቃላ ሃይማኖት ተብትቦ፤ ከአማራነት አስተሳሰብ ሊያስወጣቸው ሞክሯል። ከእነዚህ ውስጥ እንግዲህ ገዳ ገ/አብም ሳይኖርበት አይቀርም። ለምን? የማንነት ቀውስ አጋጥሞታልና! ነገር ግን አንድ ያልተረዳው ነገር አለ። ይኸውም እንኳን የኦሮሞ ነፃነትን ሊያይ ይቅርና ነገ ኤርትራ ወደ እናት አገሯ ስትዋሀድ ገዳ ገ/አብ የት ነው መድረሻው?

መቼም ቢሆን ያኔ፤ እናት ኢትዮጵያችንን ለማፍረስ ሲገዘግዛት የኖረውን ሰው እንኳን ደህና መጣህ ብላ የምትቀበለው አይመስለኝም።

ከማክሰኞ ሰኔ 23ቀን 2012 ዓ/ም ወዲህ ግን አማራነት በኢትዮጵያ ምድር እያበበ ይገኛል። ከዚህ በኋላ በውጭ መንግሥት ጣልቃ ገብነትም ይሁን በአገር ውስጥ ቅጥረኛ ከሐዲያን፤ ወይንም በብልጣ ብልጥ  ፖለቲከኞች የሚታለል ኢትዮጵያዊ እንደሌለ በልበ ሙሉነት መመስከር ይቻላል። ምንም እንኳ በውጭ አገር የሚኖሩና የበታችነት ስሜት የተቆራኛቸው የመለስ ደቀመዝሙሮች፤ የሰው ደም ለማፍሰስ የሚሰብኩ ባይታጡም፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን የኦሮሞ ወጣቶችን የሚያታልል አንድም ኃይል ሊፈጠር አይችልም።

ከዚህ በኋላ ኦሮሞ፤ በቄሮ ስም፤ የኦሮሞን ወጣት ተግባርና ኃላፊነት ለማበላሸት ተንኰል ሲሸርቡበት የቆዩትን ከማጋለጥ በስተቀር እነርሱን በመከተል ንጹሐንን አይገድልም፤ ማንኛውንም መሠረተ ልማት አያወድምም። እንዲያውም የፖለቲካ ተስፈኞች ሰርገው በመግባት በስሙ እንዳይነግዱ ነቅቶ ይጠብቃል። የሕወሃት ካድሬ የሆነው አሉላ ሰሎሞን ከነማን ጋር እየተገናኘ እንደሆነና በኦሮሞ ክልል በሚኖሩ የሌላ ማኅበረሰብ ላይ ሊያደርግ ያቀደውን ሤራ ሁሉ፤ የኦሮሞ ወጣቶች በንቃት እየተከታተሉት ነው። የአማራነት ሥነ ልቡና በኢትዮጵያ ምድር እንደ ሰደድ እሳት እየተዛመተ ይገኛል። የኢትዮጵያ ጠላቶች ተስፋ ቁረጡ!

አዲዎስ!

 

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.