ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በፊንላንድ – ሄልሲንኪ፣ ፊንላንድ 

Finlandበሃገራችን ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተፈጸመውን የዜጎች መጨፍጨፍ፡ የሃገርና ግለሰቦችን ንብረቶች ማውደም ተግባሮች ዓላማው ሃገርን ለማፍረስ የታለመ መሆኑን በማመን፡  ከቀኑ ሰባት ሰዓት ተኩል ጀምሮ ሐምሌ 30 ቀን 2012 በፊንላንድ የምንኖር ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሄልሲንኪ ሠላማዊ ሠልፍ እናደርጋለን።

በዚህም ዕለት ሠልፈኞቹ ለፊንላንድ መንግሥት ፓርላማ አፈ ጉባዔ፡ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴውና ለሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተዘጋጁ ደብዳቤዎችን እናቀርባለን።

ደብዳቤያችንም የሚጠይቀው፡ ‘የዘር ማጥፋት’ ዓላማቸውንና ድርጊቶችን ከመዘርዘር ባሻገር፣ ችግሩን ፊንላንድ መንግሥት በግልጽ ከማስረዳት ባሻገር፡ ለነፍሰ ገዳዮችና ዘራፊዎች የአፍራሽ ፕሮፓጋንዳቸው ምንጭና ማስፈንጠርያ እንዳትደረግ፡ መንግሥት የእነዚህን አፍራሽ ወንበዴዎች ድርጊቶች በግዛቱ ውስጥ እንዲከላከል ጥሪ ማቅረብን ይጨምራል።

እስካሁን በምናውቀው  የታዋቂው ኢትዮጵያዊ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሣን ግድያ ሠበብ አሥባብ በማድረግ፣ የዜግነት ኃላፊነት የማይሰማቸው አፍራሽ ኃይሎች፡ ጽንፈኛና ቅጥረኞች የተለያዩ አደገኛ ወንጀሎች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ በሠጠው መግለጫ ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ አረጋግጧል። እነዚህም:-

ሀ) በዝርያቸውና እምነታቸው ምክንያት ዒላማ ያደረጓቸውን ወገኖቻችንን አሠቃቂ በሆነ መንገድ መጨፍጨፋቸው፤

ለ) መጠነ ሠፊ የግልና የመንግሥት ማምረቻዎችና ኤኮኖሚያዊ ንብረቶች ማውደማቸው፤

ሐ) ይህ ድርጊትም ለመጀመሪያ ጊዜ ሣይሆን፣ እነዚህ ወገኖች በዚህ መልክ በእናት ሃገራችን ላይ ያዘነቧቸው የሽብር ተግባሮች ሃገርን የማዳከምና ብሎም የማፍረስ ዓላማ አካል መሆኑን በማመን፤

በዚህ የተሰማንን ቁጣ በፊንላንድ መንግሥትና ሕዝብ በኩልም እንዲታወቅና፣ የሃገሩ መንግሥትም የችግሩን ምንጭና የጽንፈኞቹን አፍራሽ ዓላማ ተገንዝበው ከኢትዮጵያ ጋር እንዲቆሙ ሐምሌ 23 ቀን 2012 ዓ.ም.  በሄልሲንኪ ተሰባስበን በምናደርገው ሠላማዊ ሠልፍ ጥሪ እናደርጋለን።

ደብዳቤያችንም የኢትዮጵያ መንግሥት ለዜጎቹ ድኅንነት ያለበትን ኃላፊነትና ግዴታዎች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በብቃት አልተወጣም የሚለውን እምነታችንን ይገልጻል።

በተጨማሪም የዜጎችን ደኅንነትና መብቶቻቸው መከበርን በተመለከተ፣ እንዲሁም በሕጉ መስክ ዜጎች ሙሉ በሙሉ በሕግ ለመብቶቻቸው መጠበቅ፣ ለችግሩና ዕውነቱ ፍንትው ብሎ መውጣት መንግሥት የሚጠበቅበትን በገለልተኝነት እንዲወጣ እንጠይቃለን።

ከመፈክሮቻችንም መካክል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

  • ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
  • ኢትዮጵያውያን አንለያይም አንድ ሕዝብ ነን
  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ብሔርና ድንበር የላትም
  • ታሪክን ማዛባትና ታሪካዊ ቅርሶችን ማጥፋት ወንጀልና ኃሏቀረነት ነው
  • የአገር ሃብትና ንብረትን ማውደም ፀረ ሕዝብና ፀረ ዕድገት ነው
  • በሃይማኖትና በብሔር ጥቃት የሚያደርሱ ግለሰቦች በሚገባ ተጠያቂ ይደረጉ
  • በአክራሪዎችና ጽንፈኞች ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንዲወሰድ አጥብቀን እንጠይቃለን
  • የኢትዮጵያ ሕዝብ ይደመጥ
  • የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብዓዊ መብቶች ይከበሩ

 

በፊንላንድ ነዋሪ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያ

ሄልሲንኪ፣ ፊንላንድ

አስተባባሪው ግብረ ኃይል

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.