የትግራይ ህዝብ የማይሳተፍበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ አይኖርም… ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ

aaa 696x379 1ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በትግርኛ ቋንቋ በነበራቸው ቆይታ፥ “በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የፌዴራል መንግስት ይሁን እኔ በበኩሌ የትግራይ ህዝብ የማይሳተፍበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይኖራል ብለን በፍፁም አናስብም” ብለዋል።

“የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ምስረታ ጀምሮ እስከሁን ድረስ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ቆይቷል አሁንም እየተጫወተ ነው” ሲሉም ገልፀዋል።

“ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ አሁን ባለንበት ወቅት ሶስት ችግሮች አሉ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ ከእነዚህም የመጀመሪያው ከለውጥ ጋር የተያያዘ ችግር ነው፣ ሁለተኛው የብልፅግና ፓርቲና ህወሐት ካላቸው ግንኙነት ጋር የተያያዘ ነው፣ ሶስተኛው ደግሞ ልዩነት ማስፋት የሚፈልጉ አካላት የሚፈጥሩት ችግር ነው ብለዋል።

ሀሳብን በነፃነት ከመግለፅና ከሚዲያ ጋር በተያያዘ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ ይሁን በሁሉም ክልሎች አሁን ያሉ ሚዲያዎች ቀደም ሲል በሀገር ደረጃ ኖሮ አያውቅም፤ ይህ ሁሉም ሰው የሚያውቀው ሀቅ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ “በሀገሪቱ ያሉ ሚዲያዎች በአጠቃላይ ችግር እንዳላቸው ይታወቃል። የመንግስት ይሁን፣ የግል ወይም የሀይማኖት ሚዲያዎች በተለያዩ ምክንያቶች ችግር አለባቸው። የትግራይ ሚዲያዎችም ከዚህ ድክመት ነፃ አይደሉም” ሲሉም ተናግረዋል።

ሰሞኑን በብሮድካስት ባለስልጣን የተወሰደው እርምጃ ከአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ በማባባስ ሚና ስለነራቸው ነው ብለዋል።

ባለስልጣኑ የወሰደው እርምጃ ሀገርን የማዳን ጊዜያዊ እርምጃ ብቻ ነው ብሎ መውሰድ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ እርምጃው የትግራይ ህዝብ አፍ እንዳይኖረው ተብሎ የተወሰደ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም ብለዋል።

የሕግ የበላይነትና ዴሞክራሲን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ የህወሓት መሪዎች በፌዴራል መንግስት የሕግ የበላይነትና ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ እንደሚፈልጉ ሁሉ በትግራይ ክልልም እንደዛ መፍቀድ አለባቸው ብለዋል።

“በፌዴራል ብቻ ዴሞክራሲ ብለህ በክልል ዴሞክራሲ ሊኖር አይገባም ማለት አትችልም” ያሉ ሲሆን፥ ዴሞክራሲ በፌዴራልም ይሁን በክልል ለሁሉም ህዝብ እና ፖለቲካ ፓርቲ አስፈላጊ እንደሆነ ሊያውቁ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ “በምርጫ አስፈላጊነትና ግዴታ ላይ ልዩነት ያለን አይመስለኝም፤ ለምርጫ ቀጠሮ በመያዝ እየተዘጋጀን እያለን ሁሉም ሰው እንደሚያውቀው የኮቪድ 19 ፈተና አጋጥሞናል። እንደሚታወቀው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫ እስኪደረግ በስልጣን ያሉ አካላት እንዲቀጥሉ ወስኗል። ይህ ውሳኔ ለብልፅግናም ለህወሓትም ይሰራል። ለህወሓት ለብቻው አትችልም የሚል ውሳኔ የለም” ብለዋል።

ምርጫ ከአንድ ዓመት በኋላ የሚደረግ ጉዳይ ሆኖ እያለ የትግራይ ክልል መንግስት በሚሊየኖች የሚቆጠር በጀት መድቦ ክልላዊ መርጫ አካሄዳለው ማለቱ ይገርማል ብለዋል።

“በአንድ በኩል የኮሮና ቫይረስ ለትግራይ ስጋት አይደለም ማለት ነው?፤ እዛ ያለው ሰው ኮሮና አይይዘውም አይገድለውም ማለት ነው?’ ወይ ደግሞ ዘመናዊ የሆነ ህክምና እና መድሃኒት ስላለን ችግር የለውም ማለት ነው። ለመረዳት አስቸጋሪ በመሆኑ እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ ለማንሳት ያስገድዳል ያሉ ሲሆን፥ ቫይረሱ ለኢትዮጵያ ይቅር ለአሜሪካም አስቸግሯል፤ ትግራይ ለብቻው ኮሮና ችግር አይፈጥርብኝም ብሎ ማመን እንዴት ቻለ የሚል ጥያቄ መነሳት ያለበት ይመስለኛል” ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ መንግስት ሚሊየኖች በመመደብ ምርጫ ከሚያደርግ ሁለት ሶስት የውሃ ጉድጓድ ለምን አይቆፍርም? የፌዴራል መንግስት ተበድሮ ነው በመቐለ ከተማ ውሃ እየሰራ ያለው። በአክሱምም የውሀ ችግር አለ። በበብዙ የትግራይ ዞኖች የውሀ ችግር በብዛት ይታያል። ወይ ደግሞ አንድ ሆስፒታል ለምን አይሰራም? አንድ ትምህርት ቤት ለምን አይገነባም? ሲሉም ይጠይቃሉ።

“ሁኔታው በዚህ መልኩ ሲታይ ዝም ብሎ ምርጫ ከማካሄድ በዝርዝር ገምግሞ የተሻለ መንገድ መምረጥ ለህወሓት ይሁን ለትግራይ ህዝብ ጥሩ ይመስለኛል” ሲሉም ገልፀዋል።

“ከዚህ ውጭ የፌዴራል መንግስት በክልል ጉዳይ እጁን አስገብቶ አያውቅም፤ ለቀጣይም አያደርገውም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ ይህ ማለት ግን የፌዴራል መንግስት ሀላፊነት አሳልፎ ይሰጣል ማለት አይደለም፤ ህገ መንግስቱ ባስቀመጠው የፌዴራል ስልጣን መሰረት የሚሰራው ይሆናል ብለዋል።

የፌዴራል መንግስት ለትግራይ ክልል ከሚገባው በጀት ይሁን ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች አንድ ሳንቲምም ቢሆን አላጎደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ ለወደፊትም እንደማያደርግ እና ይህን ለማድረግ ህጉ እንደማይፈቅድለትም አንስተዋል።

“የትግራይ ክልል መንግስት ግን የፌዴራል መንግስት ህጋዊ አይደለም፣ አናወቀውም፣ አናምንበትም፣ ከሱ ጋር ለመስራት አንችልም እያለ የበጀት ብቻ ጥያቄ በማንሳት እርምጃ ወሰደ ማለት የሚገባ አይመስለኝም” ሲሉም ተናግረዋል።

ከኤርትራ ጋር የተጀመረው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በተመለከተም “በአሁኑ ወቅት መልካም የዲፕሎማሲእና ፀጥታን የተመለከተ ግንኙነት አለን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ።

በኢኮኖሚ በኩልም የስልክ፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትና በሌሎች ዘርፎችም በጋራ መስራት መጀመሩን ጠቅሰው፤ ይህ ደግሞ ቀስ እያለ ወደ ተሻለ ደረጃ ሊደርስ የሚችል መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህ ግንኙነት ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ከሆነች ትግራይም አብራ ትጠቀማለች፤ የትግራይ ጥቅምም የኢትዮጵያ ጥቅም ነው፤ ነጣጥለህ ትግራይ ብቻዋን ትጠቀማለች ወይም ትጎዳለች የሚል ግምገማ እንደማይሰራም ገልፀዋል።

በቅርቡ በኤርትራ በነበራቸው ቆይታም ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር በተለይም በልማት እና በሁለቱ ሀገራት ግኑኝነት ላይ መምከራቸውን አስታውሰው፤ በሁለቱም ሀገራት በኩል በተሻለ ደረጃ የመስራት ፍላጎት ስላለ በቅርቡ እየተሻሻለ እና እያደገ ይሄዳል የሚል እምነት እንዳላቸውም አስታውቀዋል።

2 Comments

 1. እኔ የጠ/ሚሩ ሃሳብ አልፎ አልፎ አይገባኝም። በፓለቲካ የሚነገሩና የማይነገሩ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ የስልጣኑን እርከን እንደተረከቡ ወደ ግድቡ ጎራ በማለት ጎብኝተው ከተመለሱ በህዋላ ” እንኳን ባጭር ጊዜ በአስር ዓመትም አያልቅ ግድቡ” በማለታቸው ይመስለኛል ቆፍጣናው ኢንጂኒየር ስመኘው ራሱን ያጠፋው (ያው እንደተነገረን)። አሁን ደግሞ ዶ/ር ደብረጽዪን ጋር ተባብራችሁ ስሩ ማለት ምን ለማለት ፈልገው ነው? እሳቸው አይደለም እንዴ በቅር “ከኤርትራ ጋር ሆነ ትግራይን እንቀጥቅጥ” ይላሉ ተነስ ታጠቅ፤ ስንቅ አሰናዳ የሚሉት። ስለ ፈንቅል ሲናገሩ “የሚፈነቀል ነገር የለም። የሚፈነቀለው የሚቀበርበት ድንጋይ ብቻ ነው” ነበር ያሉት። በእርግጥ ወያኔ አሁንም ጥርሱ አልቆ ገንፎ እየበላ ጃጅቶ ስልጣን ላይ ይኑር ማለት ነው? እኮ የዶ/ር አብይ ሃሳብ የሾኬ ጠለፋ ነው የእውን? አይ ፓለቲካ። ሁሌ መወሽከት!
  የክልል ፓለቲካና የጽንፈኞች ግርግር የሚያምሳት ሃገር እየመሩ ሰው በየቀኑ ከቀየው እየተጎተተ አንገቱ እየተቀላ ምርመራ ላይ ነን፤ አጥፊዎችን እያደንን ነው ወዘተ የሚባለው ለምን ይሆን? የገደለን መግደል፤ ቤት ያቃጠለንና የዘረፈን በህጉ መሰረት ዘብጥያ ማውረድ ተገቢ እያለ በልመና ሰላም ይመጣ ይመስል ሁሌ ለስላሳ መሆን ለእንስሳትም አልተመቸም። ተበሉ እንጂ በሌላው አራዊት!
  አሁን በተዘዋዋሪ የቅኝ ግዛት አፍሪቃን ጠፍራ የያዘቸው ቻይና በሃገሯ ውስጥ ከ 56 በላይ የሰው ዘርያዎች በሃበሻው አባባል ነገድ/ዘር/ጎሳዎች አሉ። ሌላውን ሰው ያጨናነቃትን ህንድን ስንመለከት ወደ 2000 የሚጠጉ የተለያዪ ቋንቋና ባህል ያላቸው በምድሪቱ ላይ ይኖራሉ። የኦሮሞ ጭፍን ፓለቲከኞች በሃገር ውስጥና በውጭ ግን ኦሮሚያ ለኦሮሞ ብቻ ሲሉን አያፍሩም። የዓለም ህዝብ በዘርና በቋንቋው ቢመነዘርና ክልል ቢበጅለት ጊዜውን ለመገዳደል ብቻ ነው የሚያውለው። ሰው ያለውን ነገር ሲከልል ወይም ሲያጥር አትምጡብኝ ማለቱ ነው። የሃገራችን የእብድ ፓለቲካ ወንዝ በማያሻግር ቋንቋና ጊዜ ባለፈበት ባህል ተተብትቦ ወንድምና እህቱ ሲገል ደስ ብሎት አሼ ገዳሜ ይላል። አሁን ሃገሪቱ የሚያስፈልጋት ቆራጥና ጠንካራ መሪ ነው። የማንም ዘርና ሃይማኖት ተከታይ ይሁን ሰው ከገደለ መገደል አለበት። በፈጠራና በአሻጥር ሰው እንዲነሳሳና ሌላውን እንዲገልና ንብረት እንዲወድም ያደረጉ ደግሞ እልፍ ዘመን ዘብጥያ ይውረድ። እኔን ያየህ ተቀጣ ይሁን! አሁን ሽምግልና ገለ መሌ ይቅርታ ይደረግላቸው የሚሉ ስራ ፈት ሽማግሌዎችም አርፈው ይቀመጡ። ይህ እርቅና ሽምግልና አይሻም ህግን ተከትሎ ፍርድ እንጂ። ለነገሩ ወያኔ ጋ የሄድት ሽማግሌዎች “ዘገያቹሁ” አደል የተባሉት። ሰው ለሰላም ዘግይቶ አያውቅም። ግን ወያኔ የጦር ታምቡር ከመታን በህዋላ መጣችሁ አሁን ያማረን መዋጋት ነው መልዕክቱ። ማን ማንን ይወጋል? እስከ መቼ ድረስ ነው እናንተ ደጀን ቆማችሁ ህዝባችን የምታጫርሱት? የትግራይ ህዝብ ግጭት አይፈልግም። በወያኔ የፈጠራ ጥሩንባ ግን በግድ ወደ እሳት ሊማግድት አሰፍስፈዋል። ይህ ሴራቸው ራሳቸውን ይበላል። ቃሌን አስምሩበት ሌላውን እንዲገሉ ያስታጠቋቸው ወታደሮች ናቸው ተመልሰው የሚወጓቸው። የመገዳደል ፓለቲካ ጊዜው አልፎበታል። ይልቅስ እሳት ቆስቋሽና አቀባይ ከመሆን ራስን አስተካክሎ ለህዝባችን አንድነትና ሰላም መቆም ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለቀረው የሃገሪቱ ኗሪ ማለፊያ ነው።
  ጠ/ሚ አብይም ቃላቸው አጠር፤ ነገራቸው ኮስተር፤ እርምጃቸውን ፈጠን በማድረግ በየቀኑ የምፈጸሙ ዘግናኝ ድርጊቶችን ምንጭ በማወቅ መፍትሄ እስካልሰጡ ድረስ መንግስታቸው አደጋ ላይ ነው። ሃገሪቱ ከ80 በላይ የሚበልጡ ብሄር ብሄረሰቦች የሚኖርባት ምድር እንጂ ቁጥሬ በዛ በሚል ጠማማ የፓለቲካ እይታ የኦሮም የአማራና የትግሬ መኖሪያ ብቻ አድርጎ መሳልም ህጋዊነት የለውም። ህዝባችን ሰላም እንዲያገኝና በፈለገው የሃገሪቱ ክፍል እንደ ልቡ ሰርቶ ለመኖር እንዲችል የክልል ፓለቲካ መናድ አለበት። ወያኔ ከደ/አፍሪቃ የአፓርታይድ አሰራር የቀዳው ይህ ወልጋዳ የፓለቲካ ሾተል ከህዝባችን እምነትና እይታ ላይ እስካልተወገደ ድረስ ዝንተ ዓለም ስንጋደልና የእህል ክምር አቃጥለን ለዓለም ህዝብ ተራብኩኝ ማለታችን አይቀሬ ነው። ኦሮሞ መሆን የሚያሸበርቀው ሌላው የህበረተሰብ ክፍልም ባህሉን ወጉን ሲጋራው ነው። እንደ ጠማማው በቀለ ገርባ “ኦሮምኛ ካልተናገሩ እቃ አትሽጡላቸው” እንዳለው ጠንጋር ሃሳብ ከሆነ ጥላቻን እንጂ ፍቅርን የኦሮሞ ህዝብ አያገኝም። ልብ ያለው እይታው ከክልሉ ይራቅ። አለዚያ እልቂት እንጂ ሰላም አይኖርም። በቃኝ!

 2. ጠቅላይ ምኒስተር አብይ አህመድ በትግርኛ የሰጠው ቃለ ምልልስ በመቶ አስር ከመቶ 110% ጥሩ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ባሁኑ ስዓት ካለችበት ሁናቴ ተነስቶ ግን በ100% ሊስተገበር ይችላል ባይባልም፣ ግን ለማንኛውም ኢትዮጵያ ካለችበት ሁናቴ ትገላገል ዘንዳ እንደ ጥሩ መንደርደርያ ሃሳብ ሊወሰድ ይገባል:: ጦርነት የሚባል ነገር ህልቀትን እንጂ ጥቅምን የማያስከትል ለመሆኑም አስምሮበታል፣ ይህ አባባል ካሁን በፊት የነበረውን “ሕረዶ-ቕተሎ” ባህርያትን አስወግዶ ኢትዮጵያውያን እርስበራሳቸውም ሆኑ ከጎረቤት ሃገሮቻቸው ጋር በሰላም ይኖሩ ዘንዳ ያደፋፍራል:: እስከዚህን ጊዜ ድረስ በጣም ጥሩ::
  ችግሩ ግን አንድ ቅራኔን ተወጥቶ ሌላ ቅራኔ ሲመጣና ሎሎች ሃይሎችም እጃቸውን ሲከቱ፣ የተወጠነው ጥሩ ነገር ወደ ሌላም ሊለወጥ ስለሚችል ነው:: በአብይ ዘመነ መንግስትም እንዲህ አይነት ነገር ታይቷል:: ገና አብይ መጥቶ ከኢሳያስ ጋራ ሰላምታ ከመለዋወጡ፣ ኢሳያስ ሳዋን ሲከፈት አብረው ቆመው ካስመረቁት ከነስብሓት ጋራ ኢትዮጵያን በመዝረፍ ጉዳይ ላይ ስለተጣሉና ኢሱም ቂምታው እስካሁን ጊዜም ስላልወጣለትና በእነሱ ላይ መበቀልንም እንደ ተቀዳሚ ተግባር አድርጎ ስለወሰደ፣ ህግና ስነስርአት በሌለው መልኩ የታጠቀ ሃይልን እነ ስብሓት ወደ ተደበቁበት መቐለ ዘንዳ ማሾለኽ ሆኖ ተገኘ፣ ይሄ ደግሞ በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃከል ለኖቤል ሽልማትም ሁሉ የሚያበቃ “ሰላም” በሚካሄድበት ስዓዓት ላይ ነው የተከሰተው:: እንደዚህ አይነት ተግባራትን ስናስታውስ፣ ለማንኛውም ግን ጠንቀቅ ማለትን ችላ ላለማለት እንገደዳለን::
  ስለሆነም ባጠቃላይ በተለይ ተጋሩ ጠንቀቅ ብለውም አብይ ለሰነዘረው የሰላም እጅ፣ እንደ መልስ የሰላም እጅ መሰንዘር ይገባል፣ እጅ ተሰናዝሮ ደግሞ ወደ ጭብጥ ነጥቦች መድረስ ያስፈልጋል:: በድብብቅም ሳይሆን በግልጽና በህዝብ ፊት መካሄድ ይገባዋል::
  ክልል ትግራይ ፈደራልን መታዘዝ አለበት፣ ትጥቁን ግን እንደነ ኢሳያስ አይነቶቹ ቂምበቀልተኛ እስካሉ ጊዜ ድረስ ዝም ብሎ መፍታት አይችልም፣ የነኢሳያስ ባህል ከ1965 ዓ.ም. ገደማ ጀምሮ እስከ አሁንም በ“ሕረዶ-ቕተሎ” ተበክልዋልና ሰላምን አስመልክቶ እነዚህን ለማመን አይቻልም፣ ለነገሩ እነ ኢሳያስ 2000 ዓ.ም. ገደማ በነ “በርሀ ሻዕቢያ” አብቅቶላቸው ነበር፣ ግን MLLT ዘረፋዋን ትቀጥል ዘንዳ በጥባጮች ስለሚያስፈልጓት፣ እነ በርሀ ተገደሉና እነ ሻዕቢያ በሂይወት ተረፉ፣ ዘራፊው ፖለቲካም እንዳለው አለ::
  ጭብጥ ለመሆን፣ ትግራይም እንደማንኛውም ክልል ለፈደራል ትገዛለች፣ ትጥቅዋን ግን አትፈታም፣ የትጥቅዋ ተግባር የጠቅላላ ኢትዮጵያን ድንበርን ማስጠበቅ ይሆናል የትግራይንም ጠላት ከተከሰተም ለመከላከል፣ ከአጥቂነት መቆጠብ አለበት የሚታዘዘው በትግራይ ፖለቲካና የኢትዮጵያ ድንበር ከተደፈረም ፈደራል በትግራይ ፖለቲካ በኩል አድርጎ ድንበር ወደ ተጠቃበት ያሰልፈዋይ፣ ይሄ ሁናቴ አካባብያችን ዘንዳ በጥባጮች እስካሉ ጊዜ ድረስ ይሰነብታል፣ በመጨረሻው ግን በጥባጮችና ዘረፋም አልቆላቸው ፅዮን ህዝቦችዋንና ግዛቶችዋን ስታሰባስብ ኢትዮጵያም በመጪው ትውልድ እንዳገና ትዋቀራለች::
  የዚያን ሰው ይበለን
  Unity in diversity!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.