የሰው አረሞች ተነቃቅለዋል አቀንጭራዎቹ ይቀራሉ – ዳኛቸው ቢያድግልኝ

232

ከረዥም የጥሞና ጊዜ በኋላ መለስ ማለት ተገደድኩ። እ ኤ አ ኦገስት ዘጠኝ 2013 ከሰባት አመት በፊት መሆኑ ነው  “በመግደል የሚኖሩ በማሸበር የሚከብሩ የሰው አረሞች” በሚል ርዕስ ትንሽ ነገር መጻፌን አስታውሳለሁ፡፡ ብዙዎች ወያኔዎችን እውነትም የሰው አረሞች ሲሉም ተደምጠዋል። በስማቸው የኮሩ ይመስል በአረምነታቸው ዘለቁበት።  በብዙ ጥረትና ልፋት፣ ብዙ መስዋዕትነትም ተክፍሎ አረሞቹ ተነቃቅለዋል። መጠነኛ እፎይታም የተገኘና መጪው ዘመን ምርታማ የሚሆን እየመሰለ ነው። በዚህ ብዙ ደስተኞች ቢኖሩም የአየር ንብረት መለዋወጥና አስተማማኝ ትንበያ ለመሰጠት ያለመቻሉ ለብዙዎች ነገን እንዲጠራጠሩ በጥንቃቄም እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል።

የተነቃቀሉት አረሞች ዳግም እንዳይበቅሉ ተደርገው ሳይሆን የቶሎ ቶሎ ነገር ሆኖ ከማሳው ላይ አውጥተን ስለጣልናቸው አፈሩንና ድንጋዩንም ቆንጥጠው እንደገና ለመብቀልና ቢቻል ፍሬዎቻቸውን መልሰው ከእርሻው ማሳ በትነው እነርሱ ሞታቸውን ለመጠበቅ ጠውልገው የተጋደሙ ነው የሚመስለው። ከሰብሉ በመሻማት ያከማቹት ንጥረነገር ፍሬ እስኪያፈሩ ሊያቆያቸው የሚችል በመሆኑ ያ እድል ከቶውኑ ሊሰጣቸው አይገባም። ሥሮቻቸው አፈር ከቆነጠጡ መልሰው የማንሰራራት እድል ስለሚሰጣቸው እንደ ጎበዝ ገበሬ ቢቻል እነርሱኑ ወደ ማዳበርያነት የሚቀይረውን ‘ኮምፖስት’ የማድረግ ሥራ በፍጥነት ቢሰራ ሰርቀው ያከማቹት ንጥረ ነገር ለሰብል ልምላሜ እገዛ እንዲውል ያደርጋል።  እንግዲህ ከውጭ ወራሪ የባሱት የወያኔ አውራዎች ተነቃቅለው ሲወጡ አብዮት የሰለቻት ኢትዮጵያ እስቲ ሌሎቻችሁም ተደመሩና ወደ እድገት ጎዳና ሰልጠን ባለ መንገድ እንጓዝ የሚል ከተለመደው መንገድ ወጣ ያለ አመራር ተከስተ። ፊደል የቀረጸችና ቋንቋን ያበለጸገች ሀገር ውስጥ እንዳልተፈጠርን እውቀት አጥሮን መነጋገር ጠፍቶን በ ‘ሸ’ ና በ ‘ቸ’ መገዳደል ባለፈው ይብቃ። የተሰደዳችሁት ለሀገራችን ሌላ አማራጭ አለን በማለታችሁ ከሆነ ኑና ተቃውሞውን ወደ ፉክክር እንለውጠው መባሉን የሞኝ መንገድ ያደረጉት ቂሎች እንደ ድል አድራጊ ይንጎማለሉ ጀመር።

ይባስ ብለው በኦሮሞ ስም የተደራጁት አጥፊዎች ቡራኬውን ከተነቃቀለው አረም ተቀብለው አገር ማመሱን የጀግንነት አደረጉት። ለወያኔ አድረው ከግብፅ ቡራኬ ተቀብለው ኢትዮጵያ ትውደም እያሉ የዘር ማጥፋት ወንጀልን በኢትዮጵያውያን ላይ መተግበራቸውን ስትመለከቱ ከአረምም እጅግ የከፉ አቀንጭራዎች እኒህ እርኩስ ተልዕኮ ይዘው የተነሱት ዘገምተኞችና ቅጥረኞች መሆናቸውን ትመሰክራላችሁ።

ጉጅሌዎቹ አሁን ከማሳው ውጭ ያሉ አረሞች ናቸው አደገኛነታቸው እጅግም ነው። የከፋውና እጅግ አደገኛው አረም ግን አቀንጭራው ነው። አቀንጭራን ለማታውቁ እንደስሙ የሰብል ዘር የሚያቀነጭር ጥገኛ (ፓራሳይት) የሆነ እጽዋት ነው። እነደ በቆሎ፣ ማሽላ ዘንጋዳና ተመሳሳይ ዝርያ ያላቸውን ሰብሎች አቀጭጮ ምርት አልባ ያደርጋል።  ሰርቶ መብላት ፈጽሞ ተፈጥሮው አይፈቅድለትምና ስሩን ወደ ሰብል ስር በመስደድ ይጣበቅና ሰብሉ በስሮቹ አማካይነት የሚሰበስበውን ውሃና አልሚ ንጥረ ነገሮች ሁሉ ልክ እንደ ቱቦ ገጥሞ ይመጠምጠዋል። አፈር ውስጥ ሆኖ ስለሚመገብ አብዛኛው ጥፋት አቀንጭራው ከመሬት በላይ ብቅ ከማለቱ በፊት ይፈጸማል። እህሉ የቀነጨረ ይሆናል ይህ ቀድሞ የማይታይ አረምን የጠንቋይ ወይም ሰላቢው አረም (witch weed) ይሉታል። ከመሬት ብቅ የሚለው ዘሩን ለማብዛት የሚያማልሉ አበባዎቹ እንዲያፈሩለት ነው። ልክ ቆንጨራና ዱላ ይዘው ሰው ለማረድና ዘቅዝቆ ለመግደል እንደተሰማሩት እም ቦቃቅላዎች ማለት ነው። ይህ ጥገኛ  አረም አንዱ ብቻ እስከ ሃምሳ ሺህ ዘር ሲያፈራ ዘሩ ደግሞ መሬት ውስጥ ሳይበሰብስና ሳይሞት እስከ አስራ አምስት አመት ይኖራል። ምግቡ መኖሩን ሲያረጋግጥ ብቻ ነው ስሮቹን አግደም የሚሰደውና  የጥፋት ሥራውን የሚጀምረው። የኢትዮጵያ አክራሪ ጎጠኞችም እንደዚያው ናቸው። ሰው የደከመበትና የለፋበትን የኔ ነው እንደሚሉትና ለዘረፋ እንደሚወጡት ማለት ነው። ከዘመናት በአንዱ የኦሮሞ ነፃ አውጪ መሪ የሆኑ ጉምቱ አዛውንት “የኦሮሞ ልጅ የረገጠው መሬት ሁሉ የርሱ ነው” ብለው ሲናገሩ “ስዊድንም ቢሆን?” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ይመስለኛል ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው አገር ይመስለኛል።

አቀንጭራ ጥፋቱ የሚያይለው የመሬቱ ልምላሜ አነስተኛ ሲሆን ነው። እነዚህም የሚከፉት አገር ችግር በገጠማት የሽግግር ወቅት ነው። 27 አመት ኮሽታ ሳያሰሙ የነበሩ ድንገት የለውጡ መሪዎች እኛ ነን። መጤዎች ሁሉ ካገር ይውጡ ይሉና ሕዝቡን አባልተው ፈትለክ ይላሉ፣ ይህንን ስንት ጊዜ አይተናል። ኢትዮጵያ ውስጥ የዘረኛነት መርዝ መረጨት ከጀመረ ቆይቷል። አብዛኞች የሚመስላቸው በአንድ ዘር ላይ የተነጣጠረ ጥቃት ነው። ነገሩ እንደሱ አይደለም። ኢላማቸው ኢትዮጵያዊነት ነው። የራሳቸውም ዘር ቢሆን ኢትዮጵያን ካስበለጠ ያጠፉታል። አቀንጭራዎቹ የሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት ላይ ቸክለው አገር ለማተራመስ እንደሚያደርጉት ማለት ነው። እንደ አሰልጣኞቻቸው ገድለው ለቅሶ የሚመጡ። ወገናቸውን አስገድለው ድጋፍ የሚያሰባስቡ  ከንቱዎች ናቸው። አገር ጠንከር ባለች ጊዜ አንገታቸውን ደፍተው ከሰራ አማርጠው ከስልጣን ተካፍለው ይቀመጡና ሃገር ችግር ውስጥ ስትገባ ተጨቆንን ተዋረድን ብለው አይተውት የማያውቁትን ሕዝብ ለአመፅ ይጠራሉ። ይህ ብዙ ጊዜ የተደጋገመ የአቀንጭራ ተግባራቸው ነው።

ኢትዮጵያዊ ሆኖ ኢትዮጵያን ማፍረስና ማጥፋት የሚፈልግ ዘረኛ ሊባል አይገባም ቅጥረኛ ብቻ እንጂ!! በዚህ ተሰባስበው አገራቸውን ለማፍረስ በደቦ የሚዘምቱቱ ደግሞ ዘገምተኞች ናቸው ማለትም ማስተዋል የጎደላቸው አቀንጭራዎች!! ከሰሞኑ የምናየው እውነት የዚህ ማስረጃ ነው። በትረ መንግስቱን ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ይዘውታልና ለክስ አይመችም ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን ከማንም በላይ ከፍ አድርጎ ስሟን የሚጠራ በመላው አገሪቱ ያሉ ሁሉ መሪዬ ነህ ያሉትን ሰው ለመግደል ማሴርና ለማንኳሰስ የኖቤል ሽልማቱ ለትራምፕ ይገባል በሚሉ ጅላጅሎች መፈክር የኦሮሞ ስም ሲረክስ ማየት ያሳዝናል። ለመሆኑ ትወክሉናላችሁ ያላቸው ማን ነው? ለመሆኑ ኦሮሞ በታሪኩ ተሰምቶና ታይቶ የማይታወቅ ግፍ 27 አመት ሙሉ ሲፈጸምበት እነዚህ የሰሞኑ ሽማቂዎች የት ነበሩ? ለባርነትና ለመላላክ የፈቀዱ ግለሰቦች አስሮ ሲገርፋቸው የነበረ ዘረኛ እግር ስር ወድቀው የሚማጸኑና እንደ አጫሉ አይነቱን ጎበዝ የሚገድሉ ደካሞች ኦሮሞን ፈጽሞ አይወክሉም። ኢትዮጵያን አዋርደው ለግብጽ አድረው ከግብጽ ተልዕኮ ተቀብለው ኢትዮጵያን ለማፈረስ የሚታገሉ ሁሉ ህግ የጣሱ ግለሰቦች ሳይሆኑ አገር ለማጥፋት የቆረጡ ጠላቶች ናቸው። ያሰማሯቸው ጠላቶቻችን በነርሱ ጅልነት እንዴት እንደሚስቁ ሳስብ ቁጭት ይንጠኛል። ኦሮሞ በደምና በአጥንቱ ያቆማትን አገር ኦሮሞ ነን የሚሉ ከወያኔ ጋር እጅና ጓንት ሆነው አገር ሲያፈርሱ የሚመለከቱት ጀግ ና የኦሮሞ ልጆች ምን እንደሚሰማቸው መገመት ቀላል ነው።

እነኝህ ታይተውና ተሰምተው የማይታወቁ ሸኔ ቶርቤ ከርቤ የሚባሉት የዚህ የአቀንጭራ ምሳሌዎች ናቸው። የኦሮሞ ወጣቶች ለታሪክ የሚተርፍ ትግል ታግለው ወያኔን በማሽቀንጠሩ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው። ከአማራው ጋር በመናበብ በርካታ ሥራዎችን ሰርተዋል እሰከ ባህርዳርም ዘልቀው እምቦጭን ከውሃ እያወጡ እዘንጭ ሲያደርጉት ኮርተንባቸዋል። የራሱ ክብርና ስም የማይገደው ጥገኛው ድርጅት በኦሮሞ ስም መሪዎቹ ከወያኔዎችና ከጌቶቹ ከግብፆች የቤት ሥራውን ተቀብሎ የገዛ ወገኑን በእሳት ሊማግድና ያልለፋበትንና ያልሰራበትን ለመዝረፍ የአቀንጭራ ተግባሩን በሰፊው ተያይዞት መመልከት ያማል። ባንክ ዘረፉ፣ ድሃ አፈናቀሉ፣ ሰው ዘቅዝቀው ሰቀሉ፣ አራስ የተኛችበት አረዱ አሁን ለይቶላቸው “ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ” ለማለት ደፈሩ። የኦሮሞ ነፃ አውጪ በርግጥም የቅጥረኞች ጥርቅም እንደሆነና የኢትዮጵያ ጠላቶች እንዳሻቸው የሚጋልቡት ፈረስ መሆኑን ከሰሞኑ ከወያኔ ጋር ተቆራኝቶ አደባባይ ሰልፍ ሲወጣ ተመልክተናል። የረገፈው የኦሮሞ ሕዝብ ደምና አጥንት አልጎረበጣቸውም፣ ያ ሁሉ የኦሮሞ ወጣት እልቂትና መከራ ከወያኔ ትዕዛዝ አላናጠፋቸውም። ከግብፅ ዳረጎት አላላቀቃቸውም። ከዐለም በፊት የሰለጠንን ዲሞክራሲን ያስተማርን ሰላምን የሰበክን የአባ ገዳ ልጆች ነን የሚሉት ከእንስሳ ያነስ ሰብዕና ታየበቸው፣ ድንቁርናና አረመኔነታቸው ለዓለም ማሳየታቸው ያሳፍራል። እኒህ በምንም መመዘኛ የኦሮሞን ሕዝብ አይወክሉም ሊወገዙና መንግሥት ያለምንም ማመንታት የፈጠነና የቀለጠፈ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል። ትንሽ መዘናጋት የሺህ ሰዎችን ሕይወት ሊቀጥፍ ብሎም አገርን ሊያፈርስ ይችላልና።

ኢትዮጵያ በነፃነት ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!!!

1 Comment

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.