ሦስቱ ኢትዮጵያውያን-ትረካ – ሰሎሞን ጌጡ ከኑረንበርግ

ethiopawinetባለፈው ሳምንት ‘ሁለቱ ሰልፎች’ በሚል ርዕስ በቀረበው ፅሁፍ ውስጥ በተጨባጭ ያሉትን የሁለቱን ሰልፎች: ኢትዮጵያዊነት እና ዘውጌነት ቅርንጫፎች እና በመካከላቸው ያለውን ጉድኝት ለመቃኘት ሞክረን ነበር። በዚህ ፅሁፍ ደግሞ የሦስቱን ኢትዮጵያውያን ፍላጎት እና ብሶት እንደሚከተለው በትረካ መልክ እንቃኛለን:-

“አቤት የዛሬው ቅጠል…ልክ እንደ ኢትዮጵያ ፓለቲካ እርካታን ያጎናፅፋል” አለች ፍየል/ጉዲት ቀና ብላ በጊት/መቻልን በቆሪጥ እያየቻት። “ፐ… አሽሙር መሆኑ ነው። መቼ ነው ደግሞ የኛ ፓለቲካ ሲያስደስት ያየሽው፤ እንደው ደርሶ ሆድ ይቆርጣል እንጂ። ነገሩ እውነትንሽን ነው ፤ በየእለቱ ከመብገን እንዳንቺ መቀለጃ እና መጫወቻ ማድረጉ ሳይሻል አይቀርም ፤ ቢያንስ የግል ጤናሽን ትጠብቂያለሽ።” አለች መቻል ተክዛ። “ መቀለጃ?” አለች ጉዲት ከጣሪያ በላይ እየሳቀች። “ እራሱ ፓለቲካው ኮሜዲ አይደል እንዴ፤ በቀደምለት የተከሰተውን አልሰማሽም?” “ ምን ሆነ ደግሞ ያንቺ ጉድ አያልቅ መቼስ?” “ አንዱ አሉ በቁምጣ ‘ ኢትዮጵያ አትፈርስም…ኢትዮጵያ አትፈርስም!’ እያለ እየጮኸ በሩጫ መንደሩን ሲዞር ዋለ አሉ።” “ ሂጅ ወግጅ! እና ይሄ ምኑ ነው ኮሜዲ? ደግሞ ሰምቻለው እንደዛ ያረገው የእትዬ ሀገሬ ልጅ ‘አደራ’ አይደል እንዴ? እውነቱን እኮ ነው ፤ ምንም ያህል ባንዶች እና ዘረኞች ቢተባበሩ ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን አትፈርስም! ፈጣሪ ይጠብቃታል።” አለች መቻል ጠንከር ባለ ድምፀት።

“እኔ መች ትፈርሳለች አልኩኝ ፤ ግን ደግሞ አትፈርስምን ምን አመጣው? አልሰማሽም እንዴ የጦጢትን እና የአያ ጅቦን ጨዋታ? አያጅቦ ጦጢትን “ ነይ ውረጂ አልበላሽም.. እንጫወት” ሲላት ጦጢት ሆዬ “ እሺ ግን አልበላሽምን እዚህ ምን አመጣው?” እንዳለችው። አሁን ‘ አትፈርስምን’ እዚህ ምን አመጣው። ደግሞ ኮሽ ባለ ቁጥር አትፈርስም..አትፈርስም እያሉ ከመንጫጫት፤ አቅዶ እና ተባብሮ መታገል አይሻልም።”  “ እንዴ.. እና የትዬ ሀገሬ ልጅ ‘አደራ’ አልታገለም ነው ምትይኝ?” አለች መቻል በቁጣ። “አይ…አንቺ ደግሞ ነገር ቶሎ አይዘልቅሽም፤ እየቀለደኮ ነው ምልሽ” አለች ጉዲት እያላመጠች። “እየቀለደ ባይሆንማ ከወንድሞቹ ጋር በጋራ ይታገል ነበር። ና.. በጋራ ሰላማዊ ሰልፍ እንውጣ ሲሉት አይደል እንዴ እምቢ ብሎ መንደሩን ሲሮጥ የዋለው። ከወንድሞቹ ጋር ያለውን ህብረት እያፈረሰ ፤ ኢትዮጵያ አትፈርስም…አትፈርስም ማለት ለኔ ስላቅ ነው።” አለች ጉዲት እየተቆናጠረች።

“አዬዬ.. ወይኔ አድርዬ ፤ ምስኪን..” አለች መቻል ደረቷን መታ መታ እያደረገች። “እሱማ ምን ያድርግ ፤ ጎደኞቹን በግፍ አስረውበት እኮ ነው። ደግሞ ማነው ይሄ ታላቅ ወንድሙን..አዎ ‘አቶ መዝሙርን’ ጎደኞቼ በግፍ ስለታሰሩ እናስፈታቸው፤ አግዘኝ እና ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በጋራ እንጩኸላቸው..ሲለው ፤ አቶ መዝሙር ሆዬ አይሆንም ችግር ያመጣል …ስላለው እኮ ነው ተናዶ ከሰልፋ የቀረው። አቶ መዝሙር ግን ክፋ ነው! ምናለበት የወንድሙ ጎደኛ ለሱስ ጎደኛው አይደል? እንዲፈቱ ማይጠይቅለት? እሱ እንደው ከፈቺዋቹ ጋር ግንኙነት አለው ይባላል። አለች መቻል በቁጭት።

“አይ መቻል…እስቲ አንዳንዴ ብርጭቆ ውስጥ ያለውን ግማሽ ጎደሎ ብቻ ሳይሆን፤ ግማሹ እንደሞላም ተመልከቺ። ለምጣዱ ሲባል ለግዜው አይጧን ማሳለፍ አስፈላጊ ነው፤ አልያ ጦም ማደር ይመጣል። ነገሩ አቶ መዝሙርም ችግር አለበት…መች እንደ ታላቅ ወንድም ለወንድሞቹ ከለላ እና መከታ ሆናቸው? ከዚህ ቀደም አሉ…ጥቂት የማይባሉ ወንበዴዋች ወንድሞቹን ‘አደራን’ እና ‘አብነትን’ የሻሞ ሲያንገላቷቸው እና ወደ ከርቸሌ ጭነዋቸው ሲሄዱ..አቶ መዝሙር እያየ እንዳላየ ሆኖ ነው አሉ ሹክክ ብሎ ጥሎአቸው የሄደው። አረ እንደውም ወንድሞቼ አይደሉም ብሎ ክዷል ነው ሚባለው።” አለች ጉዲት በአሽሙር። “ጥፊ ከዚህ ቀጣፊ…ሁሌ እንደቀላቀልሽ። ነገሩ ይበለኝ እኔ ነኝ ጥፋተኛ…ወላጆቼ ከሀጥዕ ጋር ህብረት አይኑርሽ ሲሉኝ…እምቢ ብዬ ፍየልን ጎደኛ አርጌ ፤ እናንት ፍየሎች ክፉዎች ናችሁ። ጉዳችሁን  ያልሰማሁ መሰለሽ? ሁለቱ የሰፈራችን ወጣቶች ሀገራቸውን ጥለው እና በርሀ አቋርጠው ሲሰደዱ..ቀዬው በጋራ ሲያለቅስ ፤ ፍየሎች እልል ስትሉና ስትስቁ እንደነበር ሰምቼአለው። አሁን ደርሶ ተቆርቋሪ ትመስያለሽ” አለች መቻል በንዴት። “እና ጫታችንን…ገረባችንን ሳይቀር እያመነዠጉ ፆማችንን ሲያሳድሩን የኖሩት ልጆች ተሰደዱ ብለን ልናለቅስ ኖሯል? ሌሎቹ ግን ሲሰደዱ እንደሌላው አዝነናል” አለች ጉዲት እንደ መቻል መቀመጫዋን በላቷ ለመሸፈን እየታገለች¡።

ለጠቅ አርጋም “ቆይ ጎዲት ተረጋጊ..እሺ ይቅርታ፤ ደግሞ የሦስተኛውን ኢትዮጵያዊ የትዬ ሀገሬን ልጅ ‘ የአቶ አብነትን’ ነገር መች አወጋውሽ?” አለች ጉዲት መቻልን እየተሻሸች ለማረጋጋት እየሞከረች። መቻልም በመረጋጋት “ደግሞ እሱ ምን አረገ ልትይኝ ነው? ‘አቶ አብነት’ እንደው ሰው አክባሪ እና ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነው።” “ነገሩማ ሦስቱም በኢትዮጵያዊነታቸው የማይጠረጠሩ ናቻው ፤ አይግባቡም አይተባበሩም እንጂ። አቶ አብነት ማ” አለች ፍየል በመንጠራራት “ወንበዴዋች በተደጋጋሚ ጥቃት ሲያደርሱብኝ…ማን ደረሰልኝ? በስሜ ከመነገድ ውጪ፤ እራሴን በራሴ ብቻ እመክታለው ብሎ ከወንድሞቹ ጋር መተባበሩን እርግፍ አርጎ ትቶታል አሉ። በተለይ ከአቶ መዝሙር ጋርማ ሆድና ጀርባ ሆነዋል። አንዴ አብረው ጥቃት ስለደረሰባቸው ከአቶ አደራ ጋር ብቻ ነው አልፎ አልፎም ቢሆን ሚጠያየቁት። በተጨማሪም ሌላው ዋናው የጠባቸው መንስኤ የወላጆቻቸው ወረት ነው የሚባለው። ሀብቱን የኔ ነው…የብቻዬ ነው በማለት በተናጥል ለመጠቀም ስለሚፈልጉ ነው አሉ የተጣሉት።”

“እንዴ ሀብት ከሆነ ታድያ ለምን ነው መምሬ ጥላኤን ጠርተው የእኩል የማያካፍሏቸው?” አለች መቻል በመገረም ስሜት “ አይ በጊት…ሀብቱ እኮ ቁስ ወይም ገንዘብ አይደለም፤ ህዝብ ነው። እንዴት አርገው ነው የእኩል የሚካፈሉት? እንዲያው በአውቅልሀለው ዝም ብለው ህዝቡን እያደናገሩ ከፋፈሉት እንጂ።” አለች ጉዲት ቁጢጥ እያለች። ታዲያ ሀብቱ ህዝብ ከሆነ…ስለምን ነው ህዝቡ እራሱ አንዳቸውን የማይመርጣቸው ወይም የማያስማማቸው?” አለች መቻል። “እንዴ መቻል..ለካ አንዳንዴም ነገር ይዘልቅሻል..?” አለች ጉዲት በማስካካት። ለጠቅ አርጋም “ እውነት ነው ህዝቡ ሊያስማማቸው ወይም አደብ ሊያሲዛቸው ይገባል! ነገሩ እነሱስ መናቆሩን ከየት አመጡት? ምንጩ ህዝብ አይደለም ብለሽ ነው? ነው እነሱ ናቸው ህዝቡ ላይ የጫኑበት?” አለች ጉዲት ግራ በመጋባት ስሜት።

“እስቲ ተጠየቂ በጊት” “ልጠየቅ” አለች መቻል ቀና ብላ። “ በእውነት ግን እነዚህ ሦስቱ የእትዬ ሀገሬ ልጆች አባታቸው አንድ ነው?” “ኡ…አንቺ ሃጢያተኛ ዞር በይልኝ ከፊቴ፤ እኔ እንደአንቺ  መቀመጫዬን/ነውሬን ገልቤ አልሄድም ጥፊልኝ ከዚህ…አንቺ ሀጢያት ልታስገቢኝ ነው ፍላጎትሽ አለች” መቻል በምሬት። “እንዴ ታዲያ ምን ችግር አለው መቀመጫሽን በላትሽ እንደሸፈንሽ ሁሉ ፤ ሀጢያትሽንም እንደ ፃድቃን በንስሀ ትሸፍኒዋለሽ” አለች ጉዲት በምፀት።

“አረ እንደውም በቀደም እረኛው የተረተውን አልሰማሽም?” “ ደሞ እረኛ ምን አለ?” አለች በጊት ቁጣዋን እረስታ በመጎጎት ስሜት።

“እረኛውማ…. “ አህያ መጣች ተጭና ክምር

ኢትዮጵያዊነት ይከፈል ጀመር” አለ።”

“አረ ወግጅልኝ አንቺ መልቲ…ይህ የእረኛ ሳይሆን የአንቺ እና የመሰሎችሽ ተረት ነው። ኢትዮጵያ አትፈርስም! ኢትዮጵያዊነትም አይከፈልም!” አለች መቻል በጩኸት። “አይ በጊት.. አንቺም እንደ አቶ አደራ መሆንሽ ነው? እረኛውማ ትክክል ካልሆነ ፤ ዛዲያ ለምን ነው የትዬ ሀገሬ ልጆች የተከፋፈሉት? ለምንስ ነው በጋራ ማይቆሙት? ለምንስ ነው በህብረትና በቅንጅት ማይታገሉት? ድር ቢያብር አንበሳ ያስር የሚለውን እና ከእናታቸው አፍ የማይለየውን አባባል ዘንግተውት ነው? ባንዳ እና እና ዘረኞችን መመከት እና ኢትዮጵያን እንዳትፈርስ ማድረግ የሚችሉት በህብረት እና በአንድነት ብቻ ሲቆሙ መሆኑን እረስተውት ነው ወይስ መታወር ነው?”

“ ይግረምሽ እንደውም… እትዬ ሀገሬ አራተኛውን ኢትዮጵያዊ ልጅ አርግዘዋል ነው ሚባለው።” አለች ጉዲት በሹክሹክታ። “የሦስቱ መነታረክ አልበቃ ብሏቸው ነው አራተኛ ሚያረግዙት? አንቺ ዋሾ!” ብላ መቻል በመንደርደር ጉዲትን በቀንዷ ልትነርታት ስትል ፤ ጉዲት በደመነፍስ ወደጎን በመስፈንጠር አመለጠች። እየሸሸችም “እውነቴን እኮ ነው ከኢትዮጵያውያን ጋር ጋር ሰላማዊ ሰልፍ አንወጣም፤ ክርስቲያኖች ለብቻችን ድምፃችንን እናሰማለን የሚል አራተኛ ኢትዮጵያዊ እየመጣ ነው። የልጁ መምጣት አስፈላጊ ቢሆንም ቅሉ ፤ ከቀሪዋቹ የትዬ ሀገሬ ልጆች ጋር በህብረት እና በቅንጅት ለመታገል ፍቃደኛ ካልሆነ ባይመጣ ይሻላዋል። አንድ እንጨት ብቻውን ይነዳል? አንድ እጅስ ብቻውን ያጨበጭባል? ለምንድን ነው ኢትዮጵያዊነትን ሚከፍሉት? ለምንስ ነው በጋራ በመታገል የሰላም፣ የአንድነት እና የዲሞክራሲ ጉዞውን የማያሳጥሩት?” አለች ጉዲት በመውተርተር።

“ፍሬ ነገርሽ ህብረት እና አንድነት ከሆነስ ደግ ነው! እኔ ደግሞ ሀሜት ስታበዢብኝ የተለመደ ቅጥፈትሽ መስሎኝ።” አለች መቻል በመረጋጋት። “እንደ ዘመኑ ጠማማ አንድ እንጨት ይነዳል፤ አንድ እጅም በምልክት ቋንቋ ያጨበጭባል ብዬ አላደርቅሽም። እውነት ነው ኢትዮጵያዊነትን ልንከፍለው አይገባም! የትዬ ሀገሬ ልጆችም ህብረት እና ቅንጅት ያስፈልጋቸዋል።” አለች መቻል ወደ ቀልቧ በመመለስ። ዛዲያ የትዬ ሀገሬን ልጆች ማን ያስታርቃቸው? የትኛውስ ምሁር ያቀናጃቸው ያስተባብራቸው? እራሳቸው ነገሩ ዘልቋቸው ይቀናጁ እና ይሰናሰሉ ይሆን? ተስፋ እናድርግ!

 

“ሀገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ ፤ ነገራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ የእምቧይ ካብ”!

ይቆየን..

ሰሎሞን ጌጡ ከኑረምበርግ

25.07.2020

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.