በአማራ ክልል ሰርገው የገቡ 85 የጥፋት ሃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ

110320086 1705210939630247 5155253098853841386 nበአማራ ክልል ውስጥ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ተልእኮ ተቀብለው ወደ ክልሉ ሰርገው የገቡ 85 የጥፋት ሃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ፡፡
ርእሰ መስተዳድሩ በማእከላዊና በሰሜን ጎንደር ዞኖች የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን ትናንት በመረቁበት ወቅት እንደተናገሩት የጥፋት ሃይሎቹ የክልሉን ሰላም በማደፍረስ ክልሉን የግጭት ቀጠና ለማድረግ ተልእኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው፡፡
እነዚህ ጸረ-ሰላም ሃይሎች በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ሰርገው የገቡት ጸበልተኛ፣ መነኩሴና የአዕምሮ ህሙማን በመምሰል እንደሆነ የጠቆሙት ርእሰ መስተዳድሩ እኩይ አላማቸውን ሳያሳኩ በህብረተሰቡ ትብብርና ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
የጥፋት ተልእኮ በመቀበል ወደ ክልሉ ገብተው የነበሩት እነዚህ ጸጉረ ልውጥ ግለሰቦች ታዋቂ ሰዎችንና ከፍተኛ አመራሮችን የመግደል፤ በሃይማኖት ተቋማትና በታሪካዊ ቅርሶች ላይ ጉዳት ለማድረስ እቅድ ይዘው የገቡ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ለውጡ የገፋቸው የህወሓት ቡድን ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ዳግም ወደ ስልጣናቸው ለመመለስ ሌት ተቀን እየሰሩ ናቸው ያሉት አቶ ተመስገን እኩይ ሴራቸውን በማክሸፍ ህዝቡ የጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
የስልጣን ተስፈኛው ቡድን አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል አማራና ኦሮሞን እርስ በእርስ በማጋጨት ሀገር አፈራርሶ ወደ ስልጣን ለመምጣት የሸረበው ሴራ ከሽፎበታል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የፌደራሉ መንግስት በሌሎች አካባቢዎች የወሰደውን ህግ የማስከበር እርምጃ አሁንም በቀሩት አካባቢዎች መውሰድ ይገባዋል ሲሉም ርእሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡
“ትጥቃችንን ሳንፈታ ወደ ማንም ጣታችንን ሳንቀስር ውስጣችን አጥርተንና አንድነታችንን ጠብቀን የሚመጡ ስጋቶች ካሉም በጋራ እየመከትን ልማታችንን ማስቀጠል ለነገ የማይባል ተግባራችን መሆን አለበት” ብለዋል፡፡
የአማራና የትግራይ ህዝብ ለዘመናት ተዋልዶና ተጋብቶ በታሪክ ሂደትም ተጋምዶ የኖረ ህዝብ መሆኑን የጠቆሙት ርእሰ መስተዳድሩ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ግጭት ለማስነሳት የሚጥሩ ሃይሎችን እረፉ ሊላቸው ይገባል ብለዋል፡፡
መጪው ጊዜ የአማራ ህዝብ ከሌሎች የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች ጋር አብሮና ተባብሮ የሚኖርበት ዘመን መሆኑን ጠቅሰው ብልጽግና ፓርቲም ይህን ተልእኮ ከዳር ለማድረስ ታሪካዊ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡
የአማራ ህዝብ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን የማንነትና የድንበር ጉዳዮችም በስርዓት መመለስ አለባቸው በሚል የድሮው ብአዴን የአሁኑ ብልፅግና አቋም ይዞ ችግሩ እንዲፈታ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
እነዚህን ጥያቄዎች አድበስብሶ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ የተፈፀመውን ጥፋት በማስተካከል ብልፅግና ፓርቲ በህግ አግባብ እንዲፈታ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
ፋኖነት በአማራ ህዝብ ልብ ውስጥ የታተመ የክብር ስም ነው ያሉት አቶ ተመስገን ይህን የጀግንነት መለያ ስም ህዝቡ በክብር እንዲጠብቀውም አሳስበዋል።
እንደኢዜአ ዘገባ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በማእከላዊና በሰሜን ጎንደር ዞኖች ስር ባሉ ሁለት ወረዳዎች ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን መርቀዋል ።
(ኢፕድ)

2 Comments

  1. Write your comment…በአመራ ክልል የሚሠራው የጸጥታ ማሸኸበር ሰራ በተለይም ሰርጎ ጠቦችን በሠያዝ በኩል የምትዐ
    ደነቁ ናችሁ ።

  2. ይህ በድን የሆነ የአቢይ ተላላኪ ሰውዬ ተደብቆ ቆይቶ ከየት መጣ ዛሬ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.