“የውጭ ሃይሎች በሠሩት ሴራ ድርጅቶቼ ላይ ጥቃት ተፈፀመ ብዬ ከነበረኝ አቋም ወደ ኋላ አልመለስም” አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ

Haile“የውጭ ሃይሎች በሠሩት ሴራ ድርጅቶቼ ላይ ጥቃት ተፈፀመ ብዬ ከነበረኝ አቋም ወደ ኋላ አልመለስም፤ ኢትዮጵያ የመጀመሪያም የመጨረሻም አማራጬ ስለሆነች ከሀገሬ ውጭ ሄጄ ማልማትም ሀብት ማፍራትም አልመኝም፤ የምሠራው ለራሴ ቢሆንም ህልሜ ሀገሬን ማሳደግ፤ ለሌሎችም የሥራ ዕድል መፍጠር ነው” – አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ

 • በሰሞኑ ክስተት ከኔ በላይ አርባ ሃምሳ ዓመት ሠርተው ያፈሩት ንብረት የወደመባቸው ሰዎች እንኳን ቢሆኑ እንዲህ አይነት ጉዳት ደርሶብናል ብለው ወደ ኋላ ይላሉ ብዬ አልገምትም። ምክንያቱም በሀገራቸው ካልሠሩ የት ሊሠሩ ይችላሉ። ግን ደግሞ መንግሥት የተሰበሩ ቅስሞችን መጠገን ይገባዋል ብዬ አስባለሁ።
 • የሻሸመኔም ይሁን የዝዋይ ህዝብ የእኛን ድርጅት የሚመካበት ነው። በእርግጠኝነት የሆቴሉን ጥቅምና ለከተማው ያለውን አስተዋጽኦ የተረዱ ነዋሪዎች በዚህ ጥቃት ላይ ይሰማራሉ የሚል እምነት የለኝም።
 • እኔ ከሀገሬና ከህዝቤ ጋር ከመኖር ውጭ ያሉ ሌሎች አማራጮችን የምመለከት ሰው አይደለሁም። ሀብት ያፈራሁት በሩጫው ዘርፍ ሀገሬን ወክዬ ባስመዘገብኩት ጥሩ ውጤትና በተሰጠኝ ሽልማት ነው።
 • ሀገሬና ህዝቤ ለእኔ እዚህ መድረስ ባለውለታዎቼ ናቸው፤ ኢንቨስት ባደረግኩ ቁጥር ለሀገሬ ዕድገት አስተዋጽኦ እያበረከትኩ እንዳለሁ ይሰማኛል። ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠርኩ ይመስለኛል። በከተሞች ዕድገትና ዘመናዊነት ላይ አስተዋጽኦ አበረክታለሁ።
 • የውጭ ሃይሎች በሠሩት ሴራ ድርጅቶቼ ላይ ጥቃት ተፈፀመ ብዬ ከነበረኝ አቋም ወደ ኋላ አልመለስም። ኢትዮጵያ የመጀመሪያም የመጨረሻም አማራጬ ስለሆነች ከሀገሬ ውጭ ሄጄ ማልማትም ሀብት ማፍራትም አልመኝም። የምሠራው ለራሴ ቢሆንም ህልሜ ሀገሬን ማሳደግ፤ ለሌሎችም የሥራ ዕድል መፍጠር ነው።
 • ውድመት የደረሰባቸው ድርጅቶች በእኔ ስም ያሉ ቢሆንም የሥራ ዕድልን በመፍጠር፣ ለከተሞች ዕድገትና ውበት በመስጠት፣ ለመንግሥት ገቢ የሚያስገኙ በመሆናቸው ጉዳቱ የእኔ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ነው። ይህ አገራዊ እንጂ ግላዊ ጉዳት አይደለም።
 • እንዲህ አይነቱ ተግባር በወቅቱ ከሚያወድመው ኢኮኖሚ በተጨማሪ የሀገርን ገጽታ በማበላሸት በመጪው ኢኮኖሚላይም ተጽዕኖ የሚያደርስ ነው።
 • ኢንቨስትመንትም ሰላምና መረጋጋት ይፈልጋል። ማንም ሰው ቢሆን መዋዕለ ነዋዩን የሚያፈሰው የነገ ጥቅሙን አስቦ ነው። በነገ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ሲኖሩ ነው ሰው የዘራውን ማጨድ የሚቻለው። ዋስትና በሌለበት ሁኔታ ማንም ተነስቶ መዋዕለ ነዋዩን ያፈሳል ተብሎ አይታሰብም።
 • ትልቁ ችግር ነገ እንደዚህ አይነት ውድመት ላለመፈፀሙ ምን ዋስትና አለ የሚለው ነው። ስለዚህ ኢንቨስት ማድረግ በሚፈልጉ የውጭም ይሁን የሀገር ውስጥ ባለ ሀብቶች ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩ አያጠራጥርም።
 • እንደሰው ስታስብ በተደጋጋሚ እንዲህ አይነት ጥቃት ሲደርስብህ ተስፋ ልትቆርጥ ትችላለህ። በተለይ ደግሞ በራስህ ወገን እንዲህ ዓይነት ጥቃት ሲፈፀምብህ ጉዳዩ የበለጠ ያስከፋል። ግን ደግሞ ኢትዮጵያ ሀገሬ ነች።
 • ብዙዎች ንብረት ሳይሆን ህይወት ከፍለው እዚህ አድርሰዋታል፤ እኛም ዋጋ እየከፈልን እናስቀጥላታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም።
 • በእንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ሥራችንን እንቀጥላለን ስንል ሰዎች እንደ እብድ ሊቆጥሩን ይችላሉ። ድርጅቶቻችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ በመሆናቸው ጥቃት ከደረሰባቸው ውጭ ያሉት በሙሉ አሁንም በሥራ ላይ ናቸው።
 • ለእኔ ዋናው ችግር ትውልዱ ሀገርን ለመገንባት በሚያስችል የትምህርት ሥርዓት ውስጥ አለማለፉ ነው። ዕድገቷን የማይፈልጉና ጥቅማቸውን ማስከበር የሚፈልጉ የውጭ ሃይሎች ደግሞ ይህንን አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ነው።
 • ህዝብ መንቃት አለበት እላለሁ፤ ህዝብ እስኪ ነቃ ድረስ ግን መንግሥት የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል። ቤተሰብ ልጆቹን ቆንጥጦ እንደሚያሳድግ ሁሉ መንግሥትም የሚያስተዳድረውን አካል አስቀድሞ ቆንጠጥ ቢያደርግ እንዲህ አይነቱን ጥፋት ማስቀረት ይቻላል።
 • ችግሮችን የሚያባብሱ ሚዲያዎችን ትክክለኛውን መስመር ማስያዝ ከመንግሥት ይጠበቃል። በተለይ ሶሻል ሚዲያው ላይ የሚታየው ልቅነት እንዲህ አይነት ችግሮችን በማባባስ የሚኖረው ሚና ቀላል ባለመሆኑ መታረም ይኖርበታል።
 • መንግሥት ሕግን ማስከበር፤ ሕብረተሰቡም ከመንግሥት ጎን መቆም ይኖርበታል። አስተማማኝ ሰላምን በመፍጠር ዜጎች ያለስጋት የሚኖሩባትን ኢትዮጵያ ማረጋገጥ ይኖርበታል። ይህ ሲሆን ነው ባለሀብቱ መዋዕለ ነዋዩን በማፍሰስ በኢትዮጵያ ዕድገት ላይ የድርሻውን መወጣት የሚችለው።
 • ከዚህ በፊትም በደቡብ ክልል በተፈጠረ ግርግር እራሳቸው የመንግሥት ተማኞች በተመኑት መሠረት ወደ 28 ሚሊዮን ብር የሚገመት ጉዳት እንደደረሰብኝ አረጋግጠዋል። መንግሥት ለደረሰው ጉዳት ካሳ እንደሚከፍል ቢናገርም እስከ አሁን ተፈፃሚ አልሆነም።
 • ይህ እያለ ደግሞ አሁን በሆቴሎቹ ላይ በደረሰው ውድመት ወደ 290 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ደርሶብኛል። ሁለቱም ሆቴሎች ባለ ሦስት ኮከብ ደረጃ ያላቸውና የተሟላ ዕቃ ያላቸው ነበሩ።
 • ወጪው የሚያጠራጥር ከሆነ አንድ ባለ ሦስት ኮኮብ ሆቴል በምን ያህል ብር መጠናቀቅ ይችላል በሚለው ማወቅ ይቻላል። ከህንፃው በላይ ሆቴሎቹ በየክፍሎቹ የያዟቸው ቁሶች ከሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ናቸው።
 • በአጠቃላይ በተለያዩ ድርጅቶቼ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች ብዛት ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጋ ነው። አሁን በሁለቱ ሆቴሎች ይሠሩ የነበሩ ወደ አራት መቶ ሠራተኞች ከሥራ ውጭ የሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እነዚህን ሠራተኞች ወደሌሎች ቦታዎች ወስደን ተደርበው እንዲሠሩ ለማድረግ አስበን ነበር፤ ግን በኮቪድ 19 ምክንያት ሌሎቹም ቢሆኑ በሚፈለገው ደረጃ እየሠሩ አይደሉም።
 • ኢትዮጵያን የገጠማት ውስጣዊ ችግር ነው ብዬ አላምንም። ውጫዊ ችግሮች ተባብሰው በመምጣታቸው ነው ውስጣዊ ችግሮች የተወለዱት። በተለይ ከታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ላይ እያንዣበበ ያለው አደጋ ዛሬ በዚህ ደረጃ የተገለፀ ቢሆንም ለበርካታ ዓመታት የኖረ መሆኑን የሚያስረዱ ታሪኮች አሉ።
 • አሁን ግብጾች በህዳሴው ግድብ ላይ ያለንን ተጠቃሚነት በጦርነት መቀልበስ እንደማይችሉ ሲረዱ እርስ በእርሳችን በማጋጨት ሀገሪቱን ማተራመስ መፈለጋቸውን የሚያሳዩ ሁኔታዎች እየተከሰቱ ነው።
 • በእኔ ዕይታ በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት ሀዘናቸውን ለመግለጽ የወጡ ሰዎች የግብጽን አጀዳ ለማስፈፀም ተልዕኮ ባላቸው አካላት ተጠልፈው እንዲህ አይነቱ ውድመት ሊደርስ ቻለ ነው የምለው።
 • ለብዙ ዓመታ የተገነቡ ከተሞች በግማሽ ቀን ዶግ አመድ ለመሆን የበቁት በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የፖለቲካ ልዩነት ሳይሆን በውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት ነው። አሁን መጠንቀቅ ያለብን በቀጣይ ምን ታስቦ ይሆን በሚለው ላይ ነው።
 • የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ዓላማቸው ህዝቡን ነፃ ማውጣት ከሆነ መጀመሪያ ህዝቡን ከድህትና ከኢኮኖሚ ችግሩ ነፃ አውጡት ብዬ መምከር እፈልጋለሁ።
 • ወጣትነት ሁሉ ነገር ነው። ይህን ወርቃማ ጊዜ ለመልካም ነገር እንዲያውሉት እመክራለሁ። አቅማቸውን ተጠቅመው ጥሪት እንዲቋጥሩ፤ በስሜት ከመነዳት ይልቅ ቆም ብለው ነገሮችን እንዲያስተውሉ እምክራቸዋለው።
 • ሀጫሉ እዚህ ቦታ ላይ ለመድረስ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሏል። ታስሯል ተገርፏል፤ ያም ሆኖ ወደ የትም ሳይሸሽ ትግሉን አጠናክሯል። መጨረሻም ለሞት ተዳርጓል። ስለዚህ ሀጫሉ ሰማዕት ሆኗል ነው የምለው።

ምንጭ አዲስ ዘመን ሐምሌ 16 ቀን 2012 ዓ.ም

1 Comment

 1. አትሌት ሀይሌ መልካም ተናግረሃል ። አንተ አንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ስጋት ሳያድርብህ በነፃነት በሃገርህ ሰርተህ እንድትኖር ለመፍትሄው አስተዋፅዖ አድርግ። ህዝብን በግፍ የጨፈጨፉ ንብረት ያቃጠሉ ያወደሙ ተይዘው ፍርድ እንዲያገኙ ይደረግ። ቄሮ ብቻውን አይሰራም ። ከላይ እሰከታች በመንግስት መዋቅር ውስጥ ባሉ ሰወች የሚደገፍ የኦነግ የአራጆች መንጋ ነው ። ህዝብ ፍርድ ይጠብቃል

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.