አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ዕርዳታ ለመከልከል እያሰበች ነው

Dam GERDበአባይ ግድብ ጉዳይ ከጅምሩ ለግብፅ ወገንተኛ መሆኗን ስታሳይ የነበረችው አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የዕርዳታ ዕቀባ ለማድረግ እያሰበች መሆኑን ፎሪይን ፖሊሲ (Foreign Policy) ዛሬ (ረቡዕ) ባወጣው ዘገባ ገለጸ። ይህ የፕሬዚዳንት ትራምፕ አቋም በአስተዳደራቸው ውስጥ ክፍፍል መፍጠሩ አብሮ ተዘግቧል።

አባይን በተመለከተ “ማድረግ የምችለውን መንገድ ሁሉ እጠቀማለሁ” በማለት ስትናገር የነበረችው ግብፅ የፕሬዚዳንት ትራምፕን እጅ በመጠምዘዝ በኢትዮጵያ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ በርትታ እየሠራች ነው።

ግብፅና አሜሪካ ለዘመናት የቆየ የጥቅም ተጋሪዎች ናቸው። እኤአ ከ1980ዓም ጀምሮ አሜሪካ ለግብፅ $40 ቢሊዮን ዶላር የሚሊታሪና $30 ቢሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ዕርዳታ ማድረጓን የስቴት ዲፓርትመንት መረጃ ያመለክታል።

በበርካታ ጥቅሞችና ቀጣናዊ ግንኙነቶች የተሳሰሩት ግብፅና አሜሪካ ለየትኛውም ፓርቲ የወገነ ፕሬዚዳንት ቢመረጥ ከግብፅ ጋር ያለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሲቀየር አልታየም። የረጅም ጊዜ የአሜሪካ ወዳጅ የነበሩት አምባገነኑ ሆስኒ ሙባረክ ከሥልጣን እንዳይወርዱ አሜሪካ የጣረችውን ያህል በሕጋዊ መንገድ የተመረጡትን መሐመድ ሙርሲን በሕገወጥ መንገድ እንዲወርዱ በማድረግ በኩል ጉልህ ሚና ተጫውታለች።

በስዊዝ ካናል ግብፅ ባላት የባህር የበላይነት ለአሜሪካ የሚሰጠው ጥቅም፤ ግብጽ የእስራኤል ወዳጅ በመሆኗ እና ኢራን የአካባቢውን የበላይነት ለመውሰድ የምታደርገው ጥረት እንደ እስራኤልና አሜሪካ ግብፅንም የሚያሳስባት በመሆኑ፤ በመካከለኛው ምስራቅና በሰሜን አፍሪቃ በየጊዜው የሚነሳው አሸባሪነት እና ጽንፈንነት መባባስ፤ ግብፅ ያላት ጂኦፖለቲካዊ አቀማመጥና ይህም ለአሜሪካ ያለው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ፤ ወዘተ አሜሪካንን እና ግብፅን በወፍራሙ አጋምዷቸዋል።

አባይን በተመለከተ የትራምፕ አስተዳደር ጉዳዩን እየተመለከተ ያለው በአፍሪካ መነጽር ወይም በኢትዮጵያ ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ያሳድራል ከሚለው አኳያ እንዳልሆነ ፎሪይን ፖሊሲ የኋይት ሃውስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራን ለማስመለስ የኢህአዴግ ልኡካን በጄኔቫ

በተለይ የአባይ ድርድር በሦስቱ አገራት (ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን) እና በአሜሪካው የገንዘብ ሚኒስቴር መ/ቤት አማካኝነት እንዲካሄድ ከተወሰነ ወዲህ በገንዘብ ሚ/ር እና በተለምዶ እንዲህ ዓይነት ድርድሮችን በመሸምገል የሚታወቀው ውጭ ጉዳይ (ስቴት ዲፓርትመንት) መካከል መቃቃር ተፈጥሯል።

“ሁኔታው እንዲህ አይደለም” በማለት የሚናገሩት የገንዘብ ሚ/ር ቃል አቀባይ “የገንዘብ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚህ ሒደት ውስጥ በትብብር እየሠሩ ነው፤ በሁለቱ መ/ቤቶች ያሉት ቡድኖችም እንዲሁ” በማለት ተናግረዋል።

አሜሪካ ለኢትዮጵያ ለመከልከል ያሰበችው ዕርዳታ ዓይነት ግልጽ አልሆነም። ነገርግን የሰብዓዊ ዕርዳታን እንደማይጠቀልል የአስተዳደሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይናገራሉ። በ2019 አሜሪካ ለኢትዮጵያ ከሰጠችው $824.3 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ $497.3 ሚሊዮን ዶላሩ ለሰብዓዊ ዕርዳታ የተለገሰ ነበር።

ስማቸው እንዳይጠቀስ በመናገር ለፎሪይን ፖሊሲ አስተያየታቸውን የሰጡ የተለያዩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንደሚሉት በስቴት ዲፓርትመንት እና በዩናይትድ ስቴትስ የዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ ውስጥ የሚገኙ ሹሞች አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ለመውሰድ ያሰበችውን የዕርዳታ ቅነሳ ይቃወማሉ ብለዋል። በተለይ ኢትዮጵያ በእንደዚህ ዓይነት አደገኛ የፖለቲካ ለውጥ ውስጥ ባለችበት ጊዜ ጉዳዩ በአዲስ አበባና በዋሽንግተን መካከል እየተንገረገበ ያለውን ግንኙነት ይጎዳዋል በማለት ይናገራሉ።

ከዚህ አንጻር አንድ ባለሥልጣን እንደተናገሩት ስቴት ዲፓርትመንት ከገንዘብ ሚኒስቴር የመጣውን ጥያቄ “እያቀዛቀዘው” ይገኛል ብለዋል።

ሌሎች ሁለት ባለሥልጣናት ደግሞ ገንዘብ ሚ/ር ስቴት ዲፓርትመንትን ከድርድሩ ቆርጦታል፤ በአዲስ አበባ፣ በግብጽና በካርቱም የሚገኙ ዲፕሎማቶችም እንዲሁ ከድርድሩ ተቆርጠው ወጥተዋል ይላሉ።

ከዚህ በተጻጻሪው ደግሞ ሌላ ባለሥልጣን ይህ እውነት አይደለም፤ የሦስቱም አገራት ተደራዳሪ ቡድኖችና በየአገራቱ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በትብብርና በቅርበት እየሠሩ ነው በማለት ያስተባብላሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  In Dexter's laboratory lives the smartest boy you've ever seen

የትራምፕ አስተዳደር በዚህ ዓይነት ውዝግብ ውስጥ ባለበት ወቅት ሌሎች የአገር ውስጥ ችግሮችና የመጪው የአሜሪካ ምርጫ ተዳምረው የዕርዳታ ዕቀባውን ሊያለዝቡት ይችላሉ የሚል አስተያየቶችም ይሰጣሉ። ሌሎች ደግሞ አሜሪካ ከግብፅ ጋር ያላትን ወዳጅነት በይፋ በማሳየት የተጠቀመችበት ትርፋ አልባ፣ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የተወራ ነው በሚል ያጣጥሉታል።

በዚህ ሁሉ ውዝግብ ውስጥ ኢትዮጵያ በዓላማዋ ጸንታ የመጀመሪያው ውሃ ሙሌት ማድረጓ የዓለምአቀፍ ሚዲያን ትኩረት የሳበ ዜና ሆኗል።

ባልተጨበጠ ዕቅድ በስሜት ብቻ በመገፋፋት በቀድሞው የበረሃ ወንበዴዎች መሪ መለስ ዜናዊና ግብረአበሮቹ ሲመዘበር የቆየውን ግድብ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አመራር ባጭር ጊዜ ውስጥ ለዚህ ፍሬ ማብቃቱ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አስደስቷል፤ የባለቤት ስሜትም አጎናጽፏቸዋል።

ጎልጉል


https://www.amharic.zehabesha.com/trump-mulls-withholding-aid-to-ethiopia-over-controversial-dam/

1 Comment

  1. Hoping now Trump administration will regret now from previous mistakes and they will be motivated to offer billion of dollars for completion of the project instead of withholding. They will never do as stated on fake news. Fairness starts here for such so called democrat country, USA.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.