የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) በቅረቡ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተከትሎ በተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት ለሚዲያዎች የሠጠው ሙሉ መግለጫ!

Abnየአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) በቅረቡ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል እና ሌሎች አንዳንድ አካባቢዎች ፅንፈኛና የጥላቻ ኃይሎች በቅንጅትና ቀድሞ በታቀደበት መልኩ ሰፊ የሆነ የሚዲያ ቅስቀሳ በማድረግ በሕዝባችን ላይ ኃይማኖትና ዘር ተኮር ጥቃቶች መፈፀማቸው ይታወቃል፡፡ ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የተፈፀመው ጥቃት የዘር ማጥፋት ወንጀል(genocide) መሆኑን በመግለፅ ወንጀሉ በትክክለኛ ስሙ እንዲጠራ፣ ጥፋተኞቹ በሕግ እንዲጠየቁ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

አብን ችግሩ በመፈፀም ላይ እያለ መንግስት ዜጎቹን የመጠበቅ ግዴታውን በአግባቡ እየተወጣ እንዳልሆነ ቅሬታውን ለሚመለከተው አካል በወቅቱ ያሳወቀ ሲሆን ጥቃቱ እንዲቆም ከመጠየቅ ጎን ለጎን ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖችና ስጋቶቹን በመለየት በወንጀል ድርጊት የተሳተፉ አካላት ዙሪያ መረጃዎችን በመሰብሰብ ፍትኅ የማስፈንና ወገናችንን የመታደግ ተጨባጭ የሆነ ስራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ድርጅታችን ይሄን በተመለከተ በፍትኅ መስፈን ጉዳይ፣ በሕግ የበላይነት መረጋገጥ ዙሪያ የተያዘውን አቅጣጫ ስኬታማነት፣ ተጎጂዎችን በማቋቋም ዙሪያ ያሉትን ሂደቶች በትኩረት እየተከታተለ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ድርጅታችን አብን በሕዝባችን ደኅንነት በአጠቃላይ በሀገራችን ሕዝቦች አብሮነት እና በሀገራችን ሉዓላዊነት መከበር ዙሪያ ያለውን ሚና ከመቸውም ጊዜ በበለጠ መልኩ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሊያረጋግጥ ይወዳል፡፡
የተፈጠረውን ችግርና በሕዝባችን ላይ የደረሰውን አደጋ በተመለከተ አብን በድርጅታችን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውሳኔ መሰረት በአብን ዋና ፅ/ቤት ሰኔ 29 ቀን 2012 ዓ.ም ለሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫው በኢንተርኔት አለመኖር ምክንያት በማኅበራዊ የትስስር ገፆቻችን ተደራሽ ሳይሆን የቆየ ሲሆን ድርጅታችን የሰጠውን ሙሉ ጋዜጣዊ መግለጫ ከዚህ በታች ተያይዟል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ከተግባራዊ ምዘና ይልቅ ድንገቴ ዲስኩር የሚያስቀድሙ አካላት በዚህ ውስብስብ ሂደት መካከል ውል መያዝ የሚቻልበትን ቅኝት አጢነው ቢከታተሉ ለሕዝባችን የተሻለ መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡
★★★ ★★★ ★★★ ★★★
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰኔ 29 ቀን 2012 ዓ.ም ለሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃን የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፡፡
.
የውጭ ጠላቶች ሀገራችንን በቀጥታ ለመውረር ለበርካታ ጊዜያት ሙከራ ያደረጉ ሲሆን ይህ አልሳካ ሲላቸው የውስጥ ልዩነቶችን የሚያሰፉ እና የእርስበእርስ ግጭቶችን የሚያነግሱ የሐሰት ትርክቶችን ቀምረው መሥራት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ ለእነዚህ የውጭ ኃይሎች ሴራ የገበሩ አማራና ሀገር ጠል ኃይሎች መጠናከር ሀገራችንንና ሕዝባችንን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ ሀገርና ሕዝብ በጠላትነት ፈርጀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የተቀናጁበት የጋራ አጀንዳ ጥላቻ ነው፡፡ ውሸትን በመደጋገም እውነት ለማስመሰል ተግቶ የሚሰራው ይህ የጥላቻ ኃይል የመብትና ነፃነት ጥያቄዎችን ዘወትር የሚለፍፍ ሆኖ ተግባራዊ ሥምሪቱ ግን የመብትና የነፃነት ገፈፋ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የሀገራችን ሕዝቦች «አርቴፊሻል» በሆነ «እኛ» እና «ሌሎች» በሚል የሚከፋፍል ከመሆኑም በላይ በሕዝቦች መካከል ዘመናትን የተሻገሩ በጎ ቁርኝቶችን የሚክድ እና የሚያነውር፣ በጥቅሉ እታገልለታለሁ የሚለውን ሕዝብ ጭምር በደረጃ የሚመድብ፣ ለርካሽ የፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል የማያመነታ አፋኝና ነውረኛ ስብስብ ነው፡፡ ይህ የጥላቻ ኃይል እንደዋዛ ሲጎለብት ሀገር ወዳዱ ኃይል ይሄን የሚመጥን የፖለቲካ አስተሳሰብ እና አደረጃጀት መመሥረት ባለመቻሉ ምክንያት ሀገራችንን በምስቅልቅል ውስጥ የኋልዮሽ እንድትጓዝ አድርጓት ቆይቷል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  1.3 ሚሊየን ብር የነፈግናቸው ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ

የውጭ ወራሪ ኃይሎችን ዓላማ እንዳለ ተቀብሎ የጥላቻ ትርክቱ በሰነድ ጭምር አስፍሮ የተደራጃው የትሕነግ/ሕወኃት ስብስብ መንግስታዊ ሥልጣንን መቆናጠጥ በመቻሉ አማራና ሀገር ጠልነትን በሕገ-መንግሥት እና በተለያዩ የፖሊሲ ማዕቀፎች በማስረፅና መዋቅሮችን በመዘርጋት በርካታ የትርክት ደቀመዛሙርትና አንጋቢዎች አፍርቷል፡፡ ስለሆነም ይህ በጥላቻ ላይ የተመሰረተው ትርክትና መገለጫዎቹ እንዲሁም ጥላቻን ለማስረፅ በሚል የተቀረፁ ሕግጋት እና ፖሊሲዎች እንዲሁም ለማሳኪያነት የተመሰረቱ ተቋማት ተፈትሸው መከለስ ወይም መወገድ ያለባቸው ሲሆን ለዚህም በመጀመሪያ እውነት የሚፈለግበት፣ ጥፋተኞች የሚጠየቁበት እና ተጎጅዎች የሚካሱበት የተሟላ የሽግግር ፍትኅ ምዕራፍ እንዲከፈት፣ በቀጣይ የብሔራዊ ውይይትና ድርድር መድረኮችን ማመቻቸት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡

1. ወቅታዊ ሁኔታ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈፀመውን ግድያ በወቅቱ በሰጠው የሐዘን መግለጫ ማውገዙ ይታወሳል፡፡ በተጨማሪም ፓርቲያችን በሰጠው መግለጫ የወንጀል ድርጊቱ ተመርምሮ ተገቢው ፍትኅ እንዲሰጥ ጠይቆ ነገር ግን ገና የምርመራ ውጤት ሳይታወቅ በተለያዩ አካላት የተሰጡ ብያኔዎችን ተከትሎ በንፁሃን ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጥቃቶችን መንግስት እና ሕዝብ እንዲከላከላቸው አሳስቦ ነበር፡፡

ነገር ግን ያለምንም ማስረጃ ብያኔ የሰጡ አካላት ከድርጊታቸው ከመቆጠብ ይልቅ የመደበኛ ሥምሪታቸው አካል የሆነውን ብሔርን ከብሔር የማጋጨት ሥራቸውን በማስተጋባት በተለይም በአማራው ሕዝብ ላይ ይፋዊ የዘር ጭፍጨፋ (massacre/massacre-genocide)፤ የዘር ማፅዳት (ethnic cleansing) እና የዘር ማጥፋት (genocide) ጥሪዎችን በማኅበራዊ ድረገፆች እንዲሁም ለዚሁ ዓላማ መቀስቀሻ በከፈቷቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጭምር ሲያስተላልፉ እና ሲያስተጋቡ ቆይተዋል፡፡ ይህ ክስተት ሙሉ በሙሉ የተጠበቀ አልነበረም ማለት ባይቻልም የተገለጠበት ደረጃ ሲታይ በሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ወንጀል ወቅት ቅስቀሳ ሲያደርግ የነበረውን RTLM ሚዲያ የነበረውን ሚና ጋር ተቀራራቢ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ከዘር ጭፍጨፋው ማግስት ጥፋትን በማድበስበስ ወንጀለኞች ያለተጠያቂነት እንዲታለፉ እየተሰራ መሆኑንም ድርጅታችን ተገንዝቧል፡፡

ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም የሰሞኑን ይፋ የዘር ማጥፋት ጥሪ መነሻ በማድረግ እና ተዋንያኑን በመለየት አማራ ጠሉ ኃይል በታሪክ ክፍተት ሀገራዊ ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ወቅት ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በሕዝባችን ላይ ሲፈፀሙ የቆዩትን ዘር ተኮር ጥቃቶች በጥቅሉ የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈፀሟቸውን አካላት በምልሰት ማየት እንደሚቻል ለሕዝባችን ለመጠቆም ይወዳል፡፡
ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀሙት ዘር ተኮር ግድያዎች በድንገት የተከሰቱ አይደሉም፡፡ ጥቃቱ ረጅም ጊዜ ተወስዶ የተሰናዳና መሰናዶውም አብዛኛው ስልቱ በድብቅ የተከናወነ ቢሆንም ሊፈፀም የሚችል ሰለመሆኑ በደንብ ይታወቅ እንደነበረ ማስተባበል አይቻልም፡፡ ለበርካታ ጊዜያትም ተፈፅሟል፡፡ በመንግሥት በኩል የነበረው መለሳለስ ለጥቃቱ መፈፀም የራሱ ድርሻ እንዳለውም እና አጥፊዎቹ ተደጋጋሚ ጥፋት እንዲፈፅሙ እንዳደፋፈራቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡ የተፈፀሙት ወንጀሎች በትክክለኛ ስማቸው እንዳይጠሩ የበኩሉን አሉታዊ አስተዋፅዖም አድርጓል፡፡
አብን በተለይ የሀገራዊ ምርጫ መተላለፍን በተመለከተ የሕዝብን ዘላቂ ጥቅም፣ የሀገር ሉዓላዊነትና አንድነትን፣ ዘላቂ ሠላም መስፈንን እንዲሁም በተጨባጭ ያለውን የጤናና ተያያዥ ችግሮች መነሻ በማድረግ ለአገራችን የሚያስፈልገው መንግስት መር የሽግግር ጊዜ እንጅ የሽግግር መንግሥት አይደለም የሚል አቋም መያዙ ይታወሳል፡፡ አብን እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው መደበኛ የሕገ-መንግሥት ትርጉም መሠረት በማድረግ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ሀገራችንና ሕዝባችን ላይ ከውስጥና ከውጭ የተጋረጡ አደጋዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት መመከት የሚችል የተጠናከረ ማዕከላዊ መንግስት መኖር አለበት የሚል አቋም በመያዝ እንጅ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በጎንደር ክ/ሃገር ሳንጃ ወረዳ የልዩ ሃይል አዛዥ ሻለቃ ቀለሙ ክብረት መገደላቸው ተሰማ

ድርጅታችን በጊዜው የደረሰበት ውሳኔ የሕዝባችንን ቋሚ ጠላቶች ለሕዝባችን ያላቸውን የማይነጥፍ ጥላቻ በሚገባ ስለሚረዳ ከፅንፈኛ ኃይሎች ጋር በጥምረት የሚመሰረት ሀገራዊ መንግስት ሊኖር እንደማይችል ተረድቶ የያዘው ፖለቲካዊ አቋም እና የሰጠው መግለጫ ማዕከላዊ መንግስቱንና ሀገራችንን ለማፍረስ ቀጠሮ ይዘው ለነበሩት የጥፋት ኃይሎች ከጠበቁት ውጭ የሆነና ከፍተኛ ተስፋ የመቁረጥ ያስከተለባቸው ጭምር ነበር፡፡ በዚህ መነሻ በሕዝባችን ላይ ጥቃቶችን ለመፈፀም ፍላጎቶች እንዳሉ ጠቁሞ መንግስት ይኼን ለመከላከል ልዩ ዝግጅት እንዲያደርግ አብን ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ድርጅታችን ገልፆት የነበረው ተጨባጭ ስጋትና ጠይቆት የነበረው ልዩ የመከላከል ዝግጅት ተግባራዊ ምላሽ ባለማግኘቱ ምክንያት ሕዝባችን የዘር ማጥፋት ወንጀል ሰለባ ሊሆን ችሏል፡፡

ስለሆነም ድርጅታችንና አመራሮቹ በሁለት መሠረታዊ የፖለቲካ እና የሞራል አጣብቂኝ ውስጥ እንዳሉ ለመሸሸግ አንፈልግም፡፡ በአንድ በኩል ሀገራችንን ለማፍረስ አቅደው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከመቸውም ጊዜ በላይ ከውጭና ከውስጥ የተጠናከረና የተቀናጀ ሥምሪት ውስጥ በገቡበት በአሁኑ ወቅት ምኞታቸው እንዳይሳካ ለማረጋገጥ በሚደረገው ሀገራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ አንድ ወሳኝ አካል በመሆን ታሪካዊ አደራችንን መወጣታችን የሚያኮራን ሲሆን ይህ እስከመጨረሻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ለሀገራችን አንድነት ብሎም ሉዓላዊነት መከበር ቅንጣት የማናመነታና በግንባር ቀደምትነት እንደምንሰለፍ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡ በሌላ በኩል የአማራ ሕዝብ አንድ ወሳኝ የትግል ምዕራፍ የሆነው በማንነቱ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን በመመከቱ እንቅስቃሴ ሰፊ እና የተጠናከረ የእሳቤ፣ የአደረጃጀት እና የሥምሪት ጉዳይ በቅጡ መፈተሸና መከለስ እንዳለበት ለመገንዘብ ችለናል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ተጨማሪ ጉዳት በመቀነስ ረገድ የኦሮሞ አባቶችና እናቶች ተጠቂዎችን በቤታቸው በማስጠለል፣ ጋቢያቸውን መንገድ ላይ በማንጠፍና አጥፊዎችን በመማፀን ጭምር የተወጡት ሚና የበርካቶችን ሕይወት መታደግ የቻለ በመሆኑ ለዚህ የከበረ ወገናዊ ሥራቸው ከፍ ያለ ምስጋናና ክብርን መስጠት እንፈልጋለን፡፡

2. ዝርዝር አቋሞች
ከላይ በዝርዝር የቀረቡትን ነጥቦች መነሻ በማድረግ ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የሚከተሉትን አቋሞች እንደያዘ ለመግለፅ ይወዳል፡፡

ሀ/ በአርቲስት ሀጫሉ ላይ የተፈፀመው ግድያ ተራ የግለሰብ ግድያ እንዳልሆነ እንገነዘባለን፡፡ መንግስት በግድያው በቀጥታ የተሳተፉትን፣ ሥምሪት የሰጡትን እና በማናቸውም መልኩ ድጋፍ ያደረጉትን ኃይሎች በሙሉ በመለየት ለሕግ እንዲያቀርብ እንጠይቃለን፡፡

ለ/ መንግስት በአርቲስት ሀጫሉ ላይ የተፈፀመውን ግድያ ሰበብ በማድረግ መንግስትንና ሀገርን ለማፍረስ በግልፅ የተንቀሳቀሱትን አካላት እና በሕዝባችን ላይ የዘር ማጥፋት ጥሪ ሲያቀርቡ እና ሲያስተጋቡ የነበሩ ግለሰቦችን፣ ቡድኖችንና ሚዲያዎችን እንዲሁም በወንጀል ሥምሪቱ ከላይ እስከታች ድረስ የተሳተፉትን ሁሉ ለሕግ እንዲያቀርብ እንጠይቃለን፡፡

ሐ/ ቀደም ብሎ ለበርካታ ጊዜያት እና በተለይም ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል እና ሌሎች አንዳንድ አካባቢዎች በሕዝባችን ላይ የተፈፀመው ወንጀል የዘር ማጥፋት ወንጀል (genocide) መሆኑን በመቀበል በትክክለኛ ስሙ የመጥራት ኃላፊነት እንዲጣል፤ በማናቸውም ስሜት ወይም ለፖለቲካ ፍጆታ ግብዓት ሲባል ጥፋተኞቹ በእርቅ፣ በምህረት ወይንም በይቅርታ እንዳይታለፉ እያሳሰብን ጉዳዩ በሕግ የበላይነት አግባብ ካልተስተናገደ የሀገራችን ኅልውና አደጋ እንደሚገጥመው ስጋታችንን ከወዲሁ ለማጋራት እንወዳለን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወያኔ እና የቅድመ-ምርጫ ግምገማው- ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት

መ/ ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በወቅታዊ የሀገራችን ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግስት ጋር ሚያዚያ 27 ቀን 2012 ዓ.ም ባደረገው ውይይት እንዲሁም ሚያዚያ 29 ቀን 2012 ዓ.ም ባወጣው የአቋም መግለጫ ፅንፈኛ ኃይሎች በሕዝባችን ላይ ልዩ ጥቃት ሊፈፅሙ እንደሚችሉ ገልፆ መንግስት ልዩ የመከላከል ዝግጅት እንዲያደርግ በሚል ያቀረበው ማሳሰቢያ በተገቢው ክብደት ያልተወሰደ መሆኑን በመገንዘብ በዚህ ረገድ ጉዳቱን ለማስቆምም ይሁን ለመቀነስ በተደረገው እንቅስቃሴ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አካላት ላይ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ በመንግስት በኩል ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ እናሳስባለን፡፡

ሠ/ በሀገራችን ውስጥ ሀገር አልባ የሆኑ ወገኖች በደረሰባቸው ዘር-ተኮር ጥቃት ምክንያት ለዘመናት ጥረው ግረው ያፈሯቸው ንብረቶች የተዘረፉና የወደሙባቸውና እነሱም ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ በመሆኑ መንግሥት ሕዝቡን በማስተባበር የድጋፍና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን በአስቸኳይ እንዲያከናውን ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ረ/ መንግስት በዚህ ሰፊና የተቀናጀ የዘር ማጥፋት እና ሀገርን የማፍረስ ወንጀል የተሳተፉ አካላት ለወንጀል ሥምሪታቸው ማስፈፀሚያ የሚያውሉትን የገንዘብ ምንጮች በመለየት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ፣ በቀጠይም የጥፋት ምንጮችን ከማድረቅ ባሻገር የሚታገዱ ገንዘቦችና የሚያዙ ንብረቶች ተጎጅዎችን ለማቋቋም እና ሕጋዊ ካሳ ለማስከፈል እንዲያውል እንጠይቃለን፡፡

ሰ/ ከአሁን በኋላ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በምንም መልኩ መፈፀም እንዳይችሉ የማድረግና የመከላከል ኃላፊነቱን ከወዲሁ ለመወጣት መንግሥት ተግቶ እንዲሰራ እያሳሰብን ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ በማናቸውም አካባቢ በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ የመኖርና ንብረት የማፍራት መብቶቻቸው የሚከበሩበት የፖሊሲ ማዕቀፎች ተቀርፀው ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲደረጉ እንጠይቃለን፡፡ በዚህ ረገድ ዜጎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ጥቃት እንዳይደርስባቸው ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ መብቶቻቸው የሚከበሩበት፣ ተገቢው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ውክልና እንዲያገኙ የሚደረግበት ቅቡልና ሥርነቀል ለውጥ መካሄድ እንዳለበት ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

ሸ/ ከዚህ ሁሉ የወንጀል መረብ ጀርባ ያለውን ትሕነግ/ሕወኃት፦
 የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትሕነግ/ሕወኃት የዘር ማጥፋት የፈፀመና ሀገር ለማፍረስ እየሰራ ያለ የወንጀል ድርጅት መሆኑን በመግለፅ ከሰላማዊ ፓርቲዎች ዝርዝር እንዲሰርዝ በድጋሜ እንጠይቃለን፡፡
 የፌደራል መንግሥት በትሕነግ/ሕወኃት ላይ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ሕግ እንዲያስከብር እየጠየቅን ድርጅቱ ለወንጀል ማስፈፀሚያነት ያደራጃቸውን በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ ድርጅቶች፣ የፋይናንስ ምንጮች እና አካውንቶች ላይ እገዳ እንዲጥል እንጠይቃለን፡፡
 የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የትሕነግ/ሕውኃት ኃይል የወንጀል እስትንፋሱን ያስቀጠለባቸውን የንግድም ይሁን ማናቸውንም የግንኙነት መስመሮችን ሙሉ በሙሉ እንዲያቋርጥ፤ ሌሎች ክልሎችም በወንጀል ቡድኑ ላይ ተመሳሳይ እርምጃዎችን እንዲወስዱ እንዲያስተባብር በአፅንኦት እየጠየቅን በዚህ ረገድ የሚወሰዱ እርምጃዎች በትሕነግ/ሕወኃት ላይ ብቻ ያነጣጠሩ እንጅ በትግራይ ሕዝብ ላይ ጉዳት የማያደርሱ ሆነው እንዲፈፀሙ ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ለማስገንዘብ ይወዳል፡፡

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጰያ
ሰኔ 29 ቀን 2012 ዓ.ም

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.